የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሃት) በመቀሌ ከተማ ባደረገው ስብሰባ ላይ በጥንቃቄ ተመርጠው የተጠሩ ታማኝ ካድሬዎችና አባላት የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰሙ፡፡ የትግራይ ፌስቡክ ተጠቃሚዎች አብዮታዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው መሆኑ በአባይ ወልዱ የሚመራው የህወሓት አንጃ አሳወቀ። አንጃው ይህንን አብዮታዊ እርምጃ እንደሚወስድ ያሳወቀው “12ተኛ ጉባኤ እንዴት አለፈ …?” በሚል አጀንዳ በየመንግሥት መስርያ ቤቶች፣ ከመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች፣ የክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ካድሬዎችና ነዋሪዎች ውይይት በተካሄደበት ጊዜ ነው።
በመቀሌ ማዘጋጃ ቤት ማክሰኞ 3/13/2007 ዓም በአቶ ተስፋአለም ተወልደብርሃን (የመቀሌ ከንቲባ)፣ አቶ አሰፋ ተገኝ ምክትል ከንቲባ የተመራ ስብሰባ የተካሄደ ሲሆን “የህወሓት ጉባኤ ምን ይመስላል?” የሚል አጀንዳ ተሰጥቶት ነበር። የትግራዩ አንጃ በጉባኤው ወቅት በፌስቡክና በተባራሪ ወሬ የአቶ አባይ ወልዱ ስም ክፉኛ ጠፍቷል በሚል እሳቤ የስም እዳሴ እያካሄዱ ነው።
1) ህወሓት ተከፋፍሏል የሚል ወሬ ውሸት ነው።
2) ዳዊት ገብረእግዚአብሔር በትግራይ የሰጠው ቃለ መጠይቆች ውሸት ናቸው።
3) በፌስቡክ የሚሰራጩ መልዕክቶች ውሸት ናቸው፤ እንዳታምኑ።
4) የጉባኤው ተሳታፊዎች ሚስጢር እንዲጠብቁ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም በቀጥታ ስርጭት ሊባል በሚችል ደረጃ የስብሰባው መረጃ በፌስቡክ ተዘግቧል።
5) በአሁኑ ሰዓት ሁለት ዓይነት ጠላቶች አሉን። ፊት ለፊት ወጥተው የሚታገሉን እንደ ዓረና የመሰሉ እና በውስጣችን ሆነው የሚታገሉን ኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች (ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በፌስቡክ ደረጃ ህወሓት መስለው ጀርባችን የሚወጉን ሃይሎች) ናቸው።
6) አባይ ወልዱ ሙስናን የሚጠየፍ፣ ታግሎ የሚያታግለን ጀግናና ብቁ መሪ ነው።
7) በፌስቡክ ተጠቃሚዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንወስዳለን።
8) ጉባኤው ፍፁም ዲሞክራሲያዊና በድል የተጠናቀቀ ነበር ወዘተ
የሚል ሃሳብ ወደ ተሳታፊዎች አቅርበዋል።
ተሰብሳቢዎቹ ታማኝ ካድሬዎችና አባላት በጥንቃቄ የተመረጡ ቢሆኑም ያቀረቡት ሃሳብና ተቃውሞ ግን ስብሰባው ላዘጋጀው አካል አስደንጋጭ ነበር።
ከተሳታፊው የቀረቡት ጥያቄዎች፤
ሀ) አባይ ወልዱ በጉባኤተኛ በ20ኛ (የፌስቡክ ማህበረሰብ ከክፍል 20ኛ፤ ከዩኒት 1ኛ ብሎ የቀለደበት ነው) ደረጃ ተመርጦ እያለ በሊቀመንበርነት እንዴት ሊመረጥ ቻለ? እዚህ ላይ የጉባኤው ዲሞክራሲያዊነት የቱ ላይ ነው?
ለ) እነ አርከበ በድምፅ እንዲሳተፉ የተደረገበት፣ ለማዕከላዊ ኮሚቴ እንዳይወዳደሩ የተከለከሉበት አሰራር በየትኛው ደንብ ይገኛል?
ሐ) ዘመኑ ያመጣው የፌስቡክ ቴክኖሎጂ ህዝቡ እንዳይጠቀም እርምጃ እንወስዳለን ማለታችሁ ጊዜው የ21ኛ ክፍለ ዘመን መሆኑ ስላልገባችሁ ነው? የሃይል እርምጃው ቴክኖሎጂውን ምን ያህል ይቆጣጠረዋል ብላችሁ ታስባላችሁ?
መ) አቶ ዳዊትና ተቃዋሚ ድርጅቶች የሚነሱት ጉዳይ በመሬት ያለና በየዕለቱ የሚያጋጥመን ሃቅ ሆኖ ሳለ አትመኑት፤ ውሸት ነው፤ ማለታችሁ ችግሮቹን ለመፍታት አቅም እንዳጠራችሁ አያመላክትም ወይ? የሚሉትና ሌሎች ፈታኝ ጥያቄዎችና ሃሳቦች የቀረቡ ሲሆኑ የመቀሌ ከንቲባና ምክትሉ የሚመልሱት አጥተው አንገታቸው አቀርቅረው በሃፍረት ከስብሰባው ወጥተዋል።
የተለያዩ የቢሮ ሃላፊዎች የመሩት የመንግስት ሰራተኞች ስብሰባዎች እየተካሄዱ ያሉ ሲሆኑ ዘመቻው አቶ አባይ ወልዱ የደረሰባቸው የይውረድልንና የስም ማጥፋት ዘመቻና የጠፋው ስም እንደገና የማደስ ስራ ተጠምደው ይገኛሉ።
የዚህ ዘመቻ ትኩረት ተደርጎ ያለው ፌስቡክና የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ናቸው። ሰብሳቢዎች በተለያዩ መድረኮች ፌስቡክ ወጣቱ ትውልድ በአሉታዊ ጎን እያበላሸው፣ የተቃውሞ መንፈስ እየበረዘውና እየበከለው በመሆኑ መንግስት እርምጃ ይወስዳል በማለት አዋጅ እያስነገሩ ይገኛሉ።
በክፍለ ከተሞች ከተካሄዱ ስብሰባዎች የሓወልቲ፣ ዓይደር፣ ሓድነትና ቀዳማይ ወያነ ተሰብሳቢዎች ከፍተኛ ውጥረት የተፈጠረ ሲሆን ባለመግባባት ሊበተን ችለዋል።
ፌስቡክ አስመልክተው ከቀረቡት የአብዮታዊ እርምጃ ይወሰዳል ዛቻ ለትግራዩ አንጃ ደጋፊዎች የቀረበ ግምገማ “በቁጥር እኛ እንበዛለን፣ ለኢንቴርኔት አክሰስ እኛ እንቀርባለን፣ እነዚህን በጣት የሚቆጠሩ የፌስቡክ ተቃዋሚዎች መቃወምና ማሸነፍ ለምን አቃተን…?” የሚል ቁጭት አቅርበዋል።
እቺ ነገር መንግስቱ ሃይለማርያም “ትጥቅ አቀረብን፣ ስንቅ አቀረብን፣ አሁን የቀረን ልብ ማደል ነው። እንደ ወያነ ጠንክራችሁ አትዋጉም ወይ…!” ብሎ ያደረገው የተስፋ መቁረጥና የስርዓቱ ማብቅያ አመላካች ንግግር በእጅጉ ይመሳሰላል።
የህወሓት አንጃዎች ክፍፍል ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን በነዶ/ር ሰለሞን ዑንቋይ ለቀናት የፈጀ ሽምግልና ከመበተን እንደዳኑ ፀሓይ የሞቀ ሃቅ ለመካድ ቢሞክሩም ከህዝቡ የተሸፈነ ግን አልነበረም።
አሁን በመላ የትግራይ ወረዳዎች የአባይ ወልዱን ስም ለመገንባት ከፍተኛ ጥረት በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የአዲስ አበባው አንጃ ፊታውራሪ የሆኑት ደብረፅዮን በ12ኛ ጉባኤ ላይ በፌስቡክ የሚነሱ ሃሳቦች እንደ ትልቅ የሃሳብ ምንጭ ተቆጥረው በጉባኤው ቀርበው እንደተወያዩበትና ለጉባኤው እንደ ግብአት እንደተጠቀሙበት ለቪኦኤ መግለፃቸው ይታወሳል።
የአባይ ወልዱን ስም ለማጥፋት አገልግሎት ላይ ውለዋል የተባለው ፌስቡክና ተቃዋሚ ተጠቃሚዎች አብዮታዊ እርምጃ ይወሰድባቸዋል። የእርምጃው ዓይነት ምን ሊሆን እንደሚችል እስካሁን በውል አልታወቀም። ሆኖም የኢንቴርኔት ማእከላት ሊዘጉ ይችላሉ። ማነው ትግራይ ሰሜን ኮርያ ያላት? ያው ውድድራችን ከሰሜን ኮርያ መሆኑ ነው።
ትግራይ ለምትገኙ ፌስቡክ ተጠቃሚዎች ኢትዮጵያውያን አብዮታዊ እርምጃ እንዳይወሰድባችሁ የመንፈስ ዝግጅት ብታደርጉ እንመክራለን።
ነፃነታችን በእጃችን ነው…!
IT IS SO… …!
ምንጭ፡ Amdom Gebreslasie ፌስቡክ
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply