
አሁን የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ በመቀልበስ እንደዘበት ከእጁ አፈትልኮ የወጣውን ስልጣን መልሶ ለመጨበጥ መቀሌ የመሸገው ምንደኛው ኃይል የማይፈነቅለው ድንጋይ የማይሸርበው ሤራ የለም። ይህ ጥቅመኛ እና ሴረኛ ቡድን ገና ከፍጥረቱ ጀምሮ በኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ላይ ቂም እና ጥላቻን ጸንሶ ወደ ስልጣን በመምጣቱ የአገሪቱን መሰረታዊ ጥቅሞች ለባዕዳንና ለታሪካዊ ጠላቶቻችን ጭምር አሳልፎ ሲሰጥ ቆይቷል። ነጻ ያልወጡት የትህነግ ነጻ አውጪ ነን ባዮች የጥንታዊት ግሪክ ፈላስፎች እነ ሶቅራጥስ፣ ኤዞፕ፣ አሪስቶትል፣ ዲዮዶሩስ እና ሌሎችም በታሪካዊ የፍልስፍና ድርሳኖቻቸው ደጋግመው እያወደሱ የጠቀሷትን ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት በማዋረድ እና በማንኳሰስ የአማራ ነፍጠኞች ተረት እንጂ ኢትዮጵያ ከመቶ ዓመት የዘለለ ታሪክ የላትም የሚል ጥላቻን ያዘለ ትርክት ፈጥረው ጀግኖች ለዘመናት ደማቸውን የገበሩበትን የነጻነት ተምሳሌት ሰንደቅ ዓላማ ጭምር መናኛ ጨርቅ ሲሉ በመዛበት ብሔራዊ ክብርን እና ኩራትን እንዲሁም አገራዊ አንድነትን ከዜጎች ሕሊና ለመፋቅ ብዙ ደባ መፈጸማቸው ትላንት በገሃድ ያየነው ሃቅ ነው።
በግብራቸው ዲያቢሎስን የሚያስንቁት የግንባሩ አመራሮች እና ደቀመዝሙሮቻቸው ሥልጣን በሕዝባዊ ትግል እና በለውጥ አራማጁ ኃይል ጥረት በተነጠቁ ማግሥት “እኛ እየዘረፍን እየከፋፈልን እየገደልን እና ሕዝብን ከሃገር እያሰደድን ያልገዛናት ኢትዮጵያ ዛሬውኑ ትፍረስ ሱዳን ባለውለታችን ናት አልበሽር ይኑርልን!” የማለታቸው ምስጢሩም ከዚሁ እኩይነታቸው ጭፍን ጥላቻቸው እና ራስን ከልክ በላይ የማፍቀር ስነልቦናዊ ቀውስ /Narcissistic personality disorder – NPD/ የሚመነጭ ነው።
በዚህ አጭር መጣጥፍ ስለ ትህነግ መጠነ ሰፊ የአገር ክህደት ሴራ ዘርዝረን የምንዘልቀው አይደለምና በቀጥታ ወደ መልዕክታችን ማለፉን መረጥን። በዶ/ር ዓብይ የሚመራው የለውጥ አመራር ሂደት ዓመት ሊሞላው ተቃርቧል። በውጭም በአገር ውስጥም ዓለማቀፉን ማህበረሰብ ጨምሮ ስልጣን በተረከበው መንግሥት በመልካም ጎዳና እየተዘወረ ባለው የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ደስታውን እየገለጸ ነው። ደም ምሱ የሆነው ትህነግ ወያኔ ግን ዛሬም የንጹሃንን ደም በሴራ ፖለቲካ በመላ አገሪቱ እያፈሰሰ በለመደው እኩይ ቁማሩ ገፍቶበታል።
አበው ትዕግስትም ልክ አለው ይላሉ። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች/የፍልሰተኞች መርጃ ተቋም ጥናት መሰረት በእርስ በእርስ ግጭት በዓለም የመጀመሪያ ደረጃ የምትገኝ ሰላማዊ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው በግፍ የሚፈናቀሉባት አገር መሆኗ ዜጎችን ሁሉ እንድንቆጭ የሚያደርገን ነው። እ.ኤ.አ በ 2018 ዓ.ም ይፋ የሆነው ይኸው ጥናት በ 6 ወራት ጊዜያት ውስጥ በአገር ውስጥ ግጭት በመላው ዓለም ዙሪያ ከተፈናቀለው 5 ሚሊዮን ያሕል ሕዝብ በኢትዮጵያ ብቻ ወደ 1.5 የሚጠጋ ሰው ከቤት ንብረቱ መፈናቀሉንም መጠቆሙ የችግሩን ስፋት እና ጥልቀት ቁልጭ አድርጎ አመላካች ነው። አብዛኛው ሰው ሰራሽ የሕዝብ መፈናቀል የተከሰተው ጠግበው እና ሰርቀው በማይጠረቁ እኩያን የትህነግ ወያኔ መንደርተኞች በቀነባበረው የከፋፍለህ ግዛ ሴራ መሆኑን ስናስብ ደግሞ ሃዘናችንን እጥፍ ድርብ ይሆናል።
ሕዝባችን ላለፉት 28 ዓመታት ከኢጣሊያ ማፍያዎች ሲሲሊያን ካሞራ እና ኮሳ ኖስትራ እጅግ በከፋው ነፍሰበላው የአፍሪካ ማፍያ ቡድን እራሱን “የትግራይ ነጻ አውጪ ነኝ” በሚለው ሕወሃት/ትህነግ ከባድ ስቃይ እና ውርደት ደርሶበታል። ተገድሎዋል፣ ተደፍሮዋል፣ ሃብት እና ንብረቱን ተቀምቷል ከአገር እንዲሰደድም ተደርጓል። ትህነግ እንደ ድርጅት ኢህአዲግም እንደ ግንባር በግልም በቡድንም በየጊዜያቱ በሕዝባችን ላይ መጠነሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን አምነው ነግረውናል። ይሁን እንጂ ወያኔ ይህን ለ28 ዓመታት እንደ በሬ ጠምዶ ሲያርሰው የኖረውን ሕዝብ ያለ ይሉኝታ ትውልድ ከፍሎ በማይጨርሰው ዕዳ እስክትዘፈቅ ሲበዘብዛት የኖረውን አገር ከባርነት ቀንበር ነጻ በመልቀቅ የተጀመረው የዲሞክራሲ ሥርዓት እንዲያብብ ፈጽሞ ፈቃደኛ አይደለም። ለዚህም ነው “የቲም ዶ/ር ዓብይ መንግሥት አቅመቢስ ነው አገር መምራት አልቻለም ሕዝብ እርስ በእርስ እየተጫረሰ የሚፈናቀለው እየበዛ ነው ወያኔ ይማረን” የሚል ስሜት በማህበረሰቡ ውስጥ እንዲፈጠር ለማድረግ በአራቱም አቅጣጫ እሳት እየለኮሰ የበርካታ ንጹሃንን ሕይወት በየቀኑ ጭዳ ማድረጉ።
ዶ/ር ዓብይ ሆይ እንዲህ እንልሃለን፤ ትህነግ ከእንግዲህ በቃ ይበቃል ሊባል ይገባዋል። ባላፈው መጣጥፌ እንደገለጽኩት ወያኔ ከ60 ሺህ በላይ የትግራይ ወጣቶችን ለትግል አሰልፎ ወታደራዊ የደርግ ሥርዓትን የተዋጋው ለውጥ ለማምጣት ሳይሆን ታሪካዊ ክህደትን በአገሪቱ ላይ ለመፈጸም ነው። እርግጥ ነው በኤርትራውያኑ መለስ ዜናዊ ስብሃት እና ሌሎችም ነባር ታጋዮች አጋፋሪነት በቅኝ ግዛት ወራሪነት ኢትዮጵያን ፈርጆ ኤርትራን በመገንጠል የትንሿን አገር ትንሳኤ በሸፍጥ ለማብሰር “ነጻነት ወይስ ባርነት” በሚል ሕዝበ ውሳኔ የተካሄደን ትራጄዲ ተውኔት ከጀግንነት ቆጥሮ መዘከር አላዋቂነት ብቻ ሳይሆን ዕውነታንም በቅጡ አለመገንዘብ ጭምር ነው።
ከዚህ ሌላ ዛሬ በየዕለቱ በመቶ ሚልዮን የሚቆጠር ዶላር ለወደብ ኪራይ አገልግሎት የምንገፈግፍበትን አሰብ አሳልፎ በመስጠት የተፈጸመው የለየለት ክህደት በትጥቅ ትግሉ ወቅትም ኢትዮጵያን በመውጋት አገር እንዲያፈርስ ውለታ ለዋለለት የሱዳን መንግሥት በአባይ ጸሃዬ አማካኝነት ከኢትዮጵያ ድንበር ከ 23 ሺህ ሄክታር በላይ ለም መሬት ከመተማ ደለሎ ቆርሶ ያስረከበበት አሳፋሪ ድርጊት በየትኛውም መመዘኛ ጀግንነት ተደርጎ በታሪክ ሊወሳ ይገባዋል የሚል እምነት የለንም።
ሆደ ሰፊው የለውጡ መንግሥት የዲሞክራሲ ምህዳሩን በማስፋት በአገር ልማት እና እድገት ላይ እንዳይተጋ ጉያው ውስጥ ተሸሽጎ አዲስ አበባ ላይ ሰላም መቀሌ ላይ የጥፋት ነጋሪት የሚጎስመው ይህ ነውጠኛ ኃይል በሂደት የዶ/ር ዓብይን መንግስት ተአማኒነት ገዝግዞ መቃብር አፋፍ ከማድረሱ በፊት አመራሩ ከያዘው አዚም ነቃ ብሎ በሴረኛው ትህነግ ላይ ፈጣን የማያዳግም እርምጃ ሊወስድ ይገባዋል። ይህን የምንለው አለምክንያት አይደለም። ትህነግ ከአራት ዓመት በፊት አዴፓ ውስጥ አስርጎ ባስገባቸው ታማኞቹ አማካኝነት በምዕራብ ጎንደር ኣራት ወረዳዎችን ከክልሉ መንግሥት ዕውቅና ውጭ ከልሎ የቅማንት ነጻ አውጭ የሚል በማቋቋም ከባድ የጦር መሳሪያ እና ስልጠና ጭምር በመስጠት ለብዙ ሺህ ዘመናት ተዋልደው በኖሩት የአማራ እና የቅማንት ህዝቦች መካከል የማይታረቅ ደም አፋሳሽ ቁርሾ በመፍጠር ተጨማሪ መሬት በግርግር ለመቀራመት ብሎም መላውን የአማራ ክልል በተለይም ከትግራይ ጋር የሚጎራበተውን ታሪካዊውን የጎንደር ምድር ለማጥፋት ታሪካዊ ጠላቶች እንኳ የማይፈጽሙትን ሴራ አመቻችቷል።
ይህ ብቻ የሚመስለን ካለን ተሳስተናል። ትህነግ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ በነበሩት እና አዲስ አበባ ዋናው ፖስታ ቤት ወደሚገኘው ቢሮዋቸው ሲገቡ በጥይት እንዲመቱ አድርጓቸው በነበረው ሟቹ የሶማሌ ተወላጅ ዶ/ር አብዱል መጅድ ሁሴን አማካኝነትም በድሬዳዋ አስተዳደር የፈጸመው እኩይ ሴራ ዛሬ ሰዓቱን ጠብቆ እንደ ተጠመደ ቦምብ መፈንዳት መጀመሩ ወያኔ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለረጅም ዘመናት የነበረው ህልም ሌላው ማሳያ ሆኖ የሚጠቀስ ነው።
በሕገመንግሥቱ ድሬዳዋ እንደ አዲስ አበባ ሁሉ የበርካታ ብሄረሰቦች መኖሪያ በመሆኗ ሯሷን ችላ እንድትተዳደር ቢወሰነም ይኸው “40:40:20” በመባል የሚታወቀው ማለትም 40% ለሶማሌ ፓርቲዎች 40% ለኦሮሞ ፓርቲዎች እና ቀሪው 20% የፓርላማ መቀመጫ ለሌሎች ብሄሮች ፓርቲዎች የሚፈቅደው /ለከተማዋ አስተዳደር ያወጣው 40-40-20 የተባለ የሥልጣን ኮታ ድልድል/ ወይም አድሏዊ የአፓርታይ የፓርላማ አወቃቀር ሥርዓት ላለፉት በርካታ ዓመታት በድሬዳዋ አስተዳደር ገቢራዊ ሲደረግ ቆይቷል። ይህ ብቻ ሳይሆን በተለይም ትህነግ ከዶ/ር አብዱልመጅድ ጋር በሸረቡት ሴራ አብዛኛዎቹ የሶማሌ ብሄርን ወይም ፓርቲን ውክልና ጨብጠው ስልጣን ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተወላጆች ሳይሆኑ የጎረቤት አገር ሶማሊያ ሞቃዲሾ እና ፑንትላንድ ጎሳ አባላት የመሆናቸው ጉዳይ እንደ ታላቅ ክህደት ሲቆጠር ቆይቷል።
ሰሞኑን እንዳየነውም በጥምቀት በዓል ክቡር ታቦታት ካህናት እና ምዕመናን በድንጋይ እንዲወገሩ በማድረግ የፍቅር ከተማዋን ድሬዳዋ ትህነግ የሃይማኖት እና የብሄር ግጭት ማቀጣጠያ ለማድረግ በማህበራዊ ሚድያዎቹ ጭምር ሲሯሯጥ ማየቱ እጅግ አሳዛኝ ነው ። ለዚህ አገር በታኝ የወያኔ እኩይ ሴራ በየአቅጣጫው የሚነደውን የተንኮል እሳት ማጥፋት የሰርክ ተግባሩ ያደረገው የዶ/ር ዓብይ መንግስት አሁንም ትዕግስትን በልቡ ሰንቆ ትህነግን በጉያው አቅፎ መጓዙን ምርጫው አድርጎታል። ወያኔ በማዕከላዊ ምስራቅ የአገሪቱ ክፍል የምትገኘውን ድሬዳዋ ሐረርን እና ሶማሊያን በመዳፉ ስር አስገብቶ የቆየው በቀድሞ የትህነግ ወታደራዊ ታጋዮች ፊታውራሪነት የሚመራውን የዶላር የጦር መሳሪያ የጫት የቀንድ ከብቶች እና ልዩ ልዩ ሸቀጦችን ያለቀረጥ ከሃገር የሚያስወጣበት እና የሚያስገባበት የህገወጥ ንግድ ኔትወርክ እና የኮንትሮባንድ መናኸሪያ ዋና ቀጣናው ስለሆነ ነው።
ትህነግ ህዝብ ተወያይቶ ያልመከረበትን ሕገ መንግሥት አጽድቆ ከአጎራባች ክልሎች የመሬት ወረራ ከመጀመሩ አስቀድሞ በ 1976 ዓ.ም ዳግም ባዘጋጀው ማኒፌስቶው መሰረት ወደፊት ራሷን ችላ ተገንጥላ በምትመሰረተው “የታላቋ ትግራይ” ወይም “አባይ ትግራይ” ካርታ መሰረት ከአማራው ከአፋር ከቤኒሻንጉል አካባቢዎች ተቀምተው የሚካለሉ መሬቶች በዝርዝር ሰፍረዋል። እስካሁን እንደ ሁመራ ወልቃይት ጸገዴ አላማጣ ራያ ያሉ የአማራ ታሪካዊ ርስቶችን ቀምቶ ከ65% በላይ የትግራይንን ክልል ያሰፋው ወያኔ የአፋርን ክልል በማዳከም ዕምቅ የተፈጥሮ ሃብቱን ለመበዝበዝ እና በሂደትም የሚፈልጋቸውን በጨው ሃብት በፖታሽ እና ማዕድን የበለጸጉ መሬቶቹን ለመቀማት ክልልሉ የብጥብጥ ቀጣና ሆኖ እንዲቆይ ከአፋር ወረዳዎች እንደ ገዳማይቱ አዳኢቱ እና ኤንዱፎ ያሉ ወረዳዎችን በግፍ ቀምቶ ለሶማሊያ ኢሳ ጎሳ አባላት በመስጠት ዛሬም ደም እንዲፋሰሱ እና ከረጅም ዘመን ጀምሮ ጎረቤት ሶማሊያዎች እስከ አዋሽ አርባ ድረስ የኢትዮጵያ መሬትን የመውረር ሕልማቸው በሂደት ዕውን ይሆን ዘንድ በኢትዮጵያ ታላቅ የታሪክ ክህደት ፈጽሟል።
ዛሬ የአፋር ወገኖቻችን ደም ወያኔ ባቀነባበረው ሴራ በከንቱ እየፈሰሰ ይገኛል። “በሌላ መገዛት ነውር እና ውርደት ነው” የሚል መሰሪ አስተምህሮን የአገሪቱ ዋልታ እና ምሰሶ ለሆነው የትግራይ ሕዝብ በመስበክ አገሪቱን እንደግል ንብረቱ ለምዕተ ዓመታት እግር ከወርች አስሮ እየበዘበዘ ለመግዛት የሚያልመው ጥቅመኛው እና ምንደኛው ትህነግ የለየለት የኢትዮጵያ ጠላት ነው የምንለው ከምንም ተነስተን አይደለም። የአገሪቱ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግም ሆነ እራሱ ወያኔ ያጸደቀው ሕገ መንግሥት ተብዬው ምንም እንኳ ለይስሙላይ “ከወንጀሎች ሁሉ የከፋው ወንጀል በአገር ሉዓላዊነት ላይ የሚፈጸም ክህደት ነው” ቢልም ከ23 ሺህ ሄክታር በላይ የኢትዮጵያን ለም መሬት ቆርሶ በእብሪት እና በማን አለብኝነት ለሱዳን አሳልፎ የሰጠው ትህነግ ዛሬም ከነሙሉ ስልጣኑ እና ክብሩ የስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጦ ለውጥ አራማጁን የዶ/ር ዓብይን መንግስት መቀሌ ላይ እየወረፈ እና አቅመቢስ ነው እያለ እያጣጣለ እንደ ሹም ዶሮ ማነው የሚነካኝ በሚል ስሜት ተኮፍሶ እናየዋለን።
ስለ ትህነግ ሃጢአት እና ደባ በአንድ ጀምበር ዘርዝሮ መግለጽ እጅግ ከባድ ነው። የትግራዩ ነጻ አውጭ ነኝ የሚለው ይህ እኩይ ቡድን በጋምቤላም በአኝዋኮች ላይ በመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ ዓለም ያወቀውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ብቻ ሳይሆን ነባሩን ተወላጅ በማባረር እና በማንገላታት መሬቱንም በግፍ ለመቀራመት ሲል ትልቅ ደባ ፈጽሟል። ለዘመናት በመሰረታዊ የልማት አገልግሎት እጦት እና በድህነት የሚንገላታው ደሃውን የጋምቤላው ወገናችን እንደ ካራቱሪ ላሉ የህንድ ቱጃሮች ሳውዲስታርን ለመሳሰሉ የአረብ ዲታዎች እንዲሁም በትግራይ ተወላጆች በኢንቨስትመንት ስም ለም መሬቱን ያለካሳ እየተቀማ ለሰቆቃ ተዳርጓል። ይህም ሳያንስ በእርስ በእርስ ግጭት የተፈናቀሉ ከ500 ሺህ በላይ የደቡብ ሱዳን ተወላጆችን እንደ ኩሌ ቀበሌ ባሉ የስደተኛ ጣቢያዎች እንዲጠለሉ በማድረግ በሰብአዊ አገልግሎት ስም ሲነግድባቸው ቆይቷል። የሚገርመው ግን በቅርቡ እሱ የወጠነውን ሴራ ገቢራዊ የሚያደርግ እና በየትም ዓለም ላይ በስደተኞች አቀባበል ተፈጽሞ የማያውቅ ልዩ መመሪያ በማውጣት ከግማሽ ሚልዮን በላይ ለሚሆኑት ለእነዚሁ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች የኢትዮጵያ መንግስት ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ በአገሪቱ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸቱን ሰምተናል። ከ2.5 ሚልዮን በላይ ዜጎቻችን በዘራቸው ምክንያት ከየክልሉ እየተፈናቀሉ በጫካ የሰቆቃ ሕይወት በሚገፉበት ሁኔታ የጋምቤላን ክልል በእጅ አዙር ለደቡብ ሱዳን ሰፋሪዎች የመስጠቱ ሁኔታ እጅግ አደገኛ እና በአገር ሉአላዊነት ላይ የተቃጣ የወያኔ የሴራ ፖለቲካ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል።
የመብራት ሃይል ኤሌክትሪክ መስመር ቀጣይ የነበረውን እና ከእውቀት ነጻ መሆኑ የሚመሰከርለትን የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ኢሌ እነ መለስ ዜናዊ በራሳቸው አምሳል ቀርጸው ለእኩይ ዓላማቸው ማስፈጸሚያ ሲጠቀሙበት ኖረዋል። በሚልዮን የሚቆጠር የክልሉን በጀት ለቀን ጅቦቹ የህወሃት የጦር መኮንኖች በማከፋፈልም ለዓመታት ከፍተኛ ምዝበራ መፈጸሙን ነው ምስክሮች የሚገልጹት። የትህነግ ማፍያዎች የኦጋዴን ነጻ አውጭ ድርጅትን እና አልሽባብን ይዋጋል በሚል ሽፋን ከ35 ሺህ የሚልቁ የአብዲ ኢሌን ልዩ ነፍሰገዳይ ፖሊሶች አሰልጥኖ በማደራጀት እና ሄጎ የተባሉ ነውጠኛ ወጣቶችንም መልምሎ ሁከት በመፍጠር በለውጡ ማግሥት ህዝብን በደቦ እንዲፈጁ ቤተ እምነቶችን እንዲያቃጥሉ ማድረጉ በመሪር ሃዘን የምናስታውሰው አስከፊው የትላንት ጠባሳችን ነው። ወያኔ ዛሬም ድረስ አካባቢውን የጦር ቀጣና ለማድረግ እንቅስቃሴ ማድረጉን አላቆመም።
ወያኔ ዋናው የአባይ ወንዝ ምንጭ የሆነው የግሸን አባይ አካባቢ ህዝብ ተጠቃሚ እንዳይሆን አማራውን ለመጉዳት ብቻ ሳይሆን በውሃው ተፋሰስ ትግራይን በመስኖ ለማልት እንዲሁም ከሱዳን እና ከግብጽ ጋር ለሚኖረውም ዘላቂ ትብብር እና ወዳጅነት እንደ ጂኦ ፖለቲካ ስትራቴጂ ለመጠቀም የወንዙን የፍሰት አቅጣጫ ለማስቀየር በቢልዮን የሚቆጠር ዶላር ተጨማሪ ፈሰስ አድርጎ በ15 ኪሎሜትር ርቀት የአባይን ግድብ ሱዳን ድንበር ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመገንባቱም ምስጢር ግንባታው ከታቀደለት አገራዊ ፋይዳ ይልቅ ታላቅ ሴራ እና ደባ እንዳለበት ሳይታለም የተፈታ ነው።
ከላይ በማሳያነት የጠቀስናቸውን ታላላቅ ሴራዎች በአገርም በሕዝብም ላይ ሲጎነጉን የኖረ ቡድን ነው እንግዲህ ከነፈጸመው አያሌ ዓይን ያወጣ ዘረፋ እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ይቅርታ የቸረውን ሕዝብ እና ለውጥ አራማጅ መንግስት ያለ ይሉኝታ ዞር ብሎ ከጀርባ ሆኖ የሚወጋው። ለመሆኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወያይቶ እና ተከራክሮ በአብላጫ ድምጽ በቅርቡ ያጸደቀውን የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮምሽን የትግራይ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ህገመንግስቱን ስለሚፃረርና ህገመንግስቱን ስለሚጥስ በክልሉ ውስጥ እንዳይፈፀምና ወደ ተግባር እንዳይገባ የሚል ውሳኔ በሙሉ ድምፅ አጽድቄያለሁ ማለቱ አሁን በስልጣን ላይ ላለው ሕዝብ ለሚደግፈው መንግስት ያለውን ንቀት እና ጥላቻ አያመለክትም ትላላችሁ?
ተጣማሪ የመንግስቱ አካል ነኝ ብሎ የሕዝብ እንደራሴ ለሚወስነው ውሳኔ አልገዛም ማለት ንቀት ብቻ ሳይሆን በራሱ ለእነ ዶ/ር ዓብይ አንዳች የሚያስተላልፈው መልዕክት አለና ይቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም እንደሚባለው ተረት ስልጣን ከማጣ ኢትዮጵያ ትፍረስ ብሎ ከመጣ ምንደኛ ለውጥ መጠበቅ ለራስም ለአገርም አደጋን መጋበዝ በመሆኑ በጊዜ መላ እና ዘዴ መፈለጉ ብልህነት ነው። ሕግ “ከዘገየ ፍትህ እንደቀረ ይቆጠራል”ይባላል።
በሚልዮኖች የሚቆጠር ወገኖቻችንን ደም እንዲፈስ የሰብአዊ መብት ጥሰት በመፈጸም ዋናውን የተንኮል ሴራ ሲያቀነባብሩ የኖሩ እንደ ጌታቸው አሰፋ አባይ ጸሃዬ እና ሌሎችም ወንጀለኞችን በጉያው ደብቆ በጋራ የፈጸመው እኩይ ተግባር እንዳይጋለጥ አትንኩብኝ፣ አትድረሱብኝ እያለ ዛሬም ስልጣን ላይ ተፈናጦ የሚታየው ትህነግ የወንጀለኖች ተባባሪ ሆኖ በመንግሥት አመራር ውስጥ መቀጠሉ ለለውጥ አራማጁ የዶ/ር አብይ ቀጣይ የፖለቲካ ጉዞ ትልቅ ጠባሳን ጥሎ ስለሚያልፍ ለህግ እስኪገዛ የበጀት እና የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን ከመጣል ጀምሮ ወንጀለኞችን በግዳጅ ለፍርድ እስከማቅረብ እንቅስቃሴ የማድረጉ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት ይገባል። በተረፈ ለትግራይ ሕዝብ አማራጭ ሃሳብ ይዘው የቀረቡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አስተዳደሩን ተክተው የሚሰሩበትን ሁኔታ ከማመቻቸት ጀምሮ የወንጀለኞች ምሽግ የሆነውን ትህነግ በመላ አገሪቱ እንዳይንቀሳቀስ ማዕቀብ እስከማድረግ በመጓዝ ዓለም በጉጉት የሚያየውን የለውጥ ጅማሮ ማጠናከር ከዶ/ር ዓብይ አመራር ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
መይሳው ሳልሳዊ
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply