ትህነግ ብዙ ወጪ ያደረገበት የሎቢ ሥራ ኪሣራ እየገጠመው ነው
አሜሪካ ኢትዮጵያን ወደ አጎዋ ለመመለስ ፍንጭ አሳየች
የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሜሪካ የንግድ ልዑክ የተነሱበትን ቅሬታዎች በተመለከተ ተጨማሪ “አዎንታዊና ገንቢ” ዕርምጃዎችን የሚወስድ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ከተጠቃሚነት የተሰረዘችበትን የአሜሪካ መንግሥት ከቀረጥ ነፃ የንግድ ዕድል (አጎአ) በተመለከተ የንግግር ሒደት ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ጥር 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ከጋዜጠኞች ጋር በስልክ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ ኢትዮጵያ ከአውሮፓውያኑ ጥር ወር 2022 ጀምሮ ከአጎአ ተጠቃሚነት የታገደችው የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን ከሰብዓዊ መብትና ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የተቀመጡ መስፈርቶችን ባለማሟላቷ መሆኑን መናገራቸውን ኋይት ሀውስ በድረ ገጹ አስታውቋል፡፡
ይሁንና የኢትዮጵያ መንግሥት የተነሱበትን ቅሬታዎች አስመልክቶ ተጨማሪ ዕርምጃዎችን የሚወስድ ከሆነ አሜሪካ በየጊዜው ከሚደረገው የአገሮች ሁኔታ ምዘና ውጪ የንግግር ሒደት ውስጥ እንደምትገባ ባለሥልጣኑ ለጋዜጠኞቹ አብራርተዋል፡፡
“ነገር ግን በዚያ መንገድ ለመሄድ በመጀመሪያ ደረጃ ለአጎአ መቋረጥ ምክንያት በሆኑት ጉዳዮች ላይ ጉልህ የሆነ ማሻሻያ ማየት አለብን” ብለዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ታኅሳስ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር ንግግር ማድረጋቸው የተገለጸው የቀድሞውን የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማንን የኢትዮጵያ ጉዞ አስመልክቶ በመግለጫው ላይ የተነሳ ሲሆን፣ ከፍተኛ ባለሥልጣኑ ፌልትማን (አምባሳደር) ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ያደረጉት “በኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ” መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የቀድሞውን የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማንን በመተካት የተሾሙት አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ መቼ ወደ ቀጣናው ለመጓዝ እንዳሰቡ ለባለሥልጣኑ ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን፣ የልዩ መልዕክተኛው የጉብኝት ቀንን በተመለከተ የተወሰነ ቀን አለመኖሩን ገልጸው “ነገር ግን ረዥም [ጊዜ] እንደማይሆን እንጠብቃለን፤” ብለዋል፡፡
ጥር 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በስልክ ንግግር ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ሁለቱ መሪዎች ንግግር ያደረጉት በፕሬዚዳንት ባይደን ጥያቄ መሠረት መሆኑን እኚሁ ስማቸው ያልተጠቀሰው ከፍተኛ ባለሥልጣን በመግለጫው ላይ ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች ባደረጉት የስልክ ንግግር የኢትዮጵያ መንግሥት በእስር ላይ የነበሩ ፖለቲከኞችን የክስ ሒደት ማቋረጡን አስመልክተው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ምሥጋና ማቅረባቸው ተገልጿል፡፡ የስልክ ንግግሩን አስመልክቶ ጥር 2 ቀን 2014 ዓ.ም. በፌስቡክ ገጻቸው መልዕክት ያሰፈሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) “በጋራ በመከባበር ላይ የተመሠረተ ገንቢ ተሳትፎ ማድረግ ትብብራችንን ለማጠናከር ትልቅ ጥቅም እንዳለው ሁለታችንም ተስማምተናል” ማለታቸው አይዘነጋም፡፡ (አማኑኤል ይልቃል – ሪፖርተር)
ትህነግ “Tigray Center for Information & Communication” በሚል ስም አሜሪካ አገር በፈጠረው ድርጅት አማካኝነት በፖለቲካው ዘርፍ ድል ለመቀዳጀት በርካታ የውስወሳ (ሎቢ) ሥራዎች ሲያከናውን ቆይቷል። በተለይ “Von Batten Montague York PC” ለሚባለው ወትዋች ድርጅት በርካታ ገንዘብ በመክፈል ከዓላማው አንጻር ውጤቶችን አምጥቷል። በተለይ ኢትዮጵያን ከአጎዋ በማስወጣት ረገድ ወትዋቹ ድርጅት በተከፈለው ልክ ሥራውን ፈጽሟል። ሆኖም አሁን አሜሪካ ኢትዮጵያን ወደ አጎዋ ለመመለስ እንደምትነጋገር መግለጽዋ በርካታ ገንዘብ የፈሰሰበት የትህነግ ውትወታ ቁሻሻ መውረጃ ውስጥ ተጥሎ ተጠርጎ እንደጠፋ መዋዕለ ንዋይ አድርጎታል። ይፈጥራል የተባለው የፖለቲካ ተጽዕኖም ትህነግን መልሶ የሚያፈርስ እየሆነ መጥቷል።
በቀጣይ ዘላቂ ወዳጅ የሌላት አሜሪካ የፈለገችውን ሊያሳካላት ያልቻለውን ትህነግ በማስወገድ ሒደት እንደተጠመደች ፍንጮች እየታዩ መሆናቸውን የደረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply