ሰሞነኛ መነጋገሪያ የሆነው “ለፖለቲካ እስረኞች ይቅርታ ልሰጥ ነው?” የሚለው ድንገተኛየወያኔ ዛባር (ቅዠት) መሰል ወግ ከመንገዳችን እንዳያወጣን መነጋገሩ አስፈላጊ ሆኖ ስለተሰማኝ የዚህ ጽሁፍ ማጠንጠኛ ላደርገው ፈቀድኩ። “የእስረኛ መልቀቅ” ጩኸት ከአፋኞቹ አፍ አምልጦ እንዲወጣ ያስገደደው ዋነኛ ሀቅ የህዝብ እምቢተኛነትና አልገዛም ባይነት አመጽ ለመሆኑ አንዳች ብዥታ እንደሌለን እየታወቀ ወያኔ “ምህረትና-ይቅርታ” በሚሉ ቃላቶች ዙሪያ፤ በማፈራረቅ ሲዋዥቅ አውቆም ሆነ ሳያውቅ በፈጠረልን “አጀንዳ” የተነጠቀውን ኳስ አስመልሶ ዋናውን የነጻነት ጥያቄበብርሃን ፍጥነት ወደ እስረኛ የማስፈታት ባህሪ እንዳይወርደው ልብ ማለት የተገባ ነው።
ለመሆኑ አሁንም አሁንም አጥፍቻለሁ፤ በስብሻለሁ፤ ተግማምቸ -አግምቻችኋለሁ እያለ ሲወሻከት የነበረው የወሮበላ ቡድን “ይቅርታ አስጠይቄ እለቃቸዋለሁ?!” ሲለንና ደግሞ ደጋግሞ ባደባባይ የተናገረውን ሲክድ፤ ዛሬም በአስራአንድ ከሃምሳዘጠነኛው ደቂቃ ላይ ቆሞ እንኳ እያፌጠብን እንደሆነ ዘንግተን የመቅዣበሩ ምክንያት የሆነው ህዝባዊ ቁጣ ቢቀዛቀዝ የድንገቴው “ምህረት” ወግ “እንቁልልጭ” ከመሆን እንደማይዘል የሚጠራጠር ይኖራል?
የዚህ ጽሁፌ መዳረሻ እንግዲህ ይህን “ባዶ አማላይ ዜና” የተንተራሰበትን መሰረታዊ የጽንሰሃሳብ ሽንቁር አስታክኬ የወያኔን የስነልቡናና ሰብእና ስንኩልነት ከታሪካዊ ዳናው ጋር በማጣመርለማመላከት ነው።
ለእኔ ለዚህ ጽሁፍ አቅራቢ “ከምህረት” ተብየው “የእንቁልልጭ” ወግ ይልቅ ከዚያ በፊት በተላለፈው ዛቻ ጀርባ የሚታየው ወያኔ ነው ይበልጥ ትኩረቴን የሚስበው። ከውሳኔው ጀርባ ጥፍሩን እንደንስር አሞራ አንጨፋርሮ የቆመው ወያኔ “መርህ-አልባ የህዝብ ግንኙነት” የሚለውን ክስ ሲመዝ ወዲያውኑ ትውስ ያለኝ ከዛሬ 37 ዓመት በፊት ተፈጥሮ የነበረ ታሪካዊ ሁኔታ ነበር።ከበዙ በጥቂቱ ከዚህ ጽሁፍ ጋር ተያያዥነት ያለው የታሪክ ክፍልእነሆ።
ጊዜው 1972 ዓ.ም ቦታው ሱዳን አገር ገዳሪፍ በምትባለው ትንሽ የሱዳን ከተማ ውስጥ የተፈጸመ ነበር። ባሳዛኝ ሁኔታ የመፈራረስ አደጋ የተጋረጠበት ኢሕአፓ-ኢሕአሠበብዙ መስዋእትነትና ትግል ከደርግ ጋር ተፋልሞ ነጻ ያወጣቸውን የጎንደር አውራጃዎችና ወረዳዎች ለቆ ወደ ሱዳን ሲሰደድ በትግራይና ኤርትራ ተራሮችና በርሀዎች ላይ ተንሰራፍቶ ይንቀሳቀስ ለነበረው የወያኔ ጦር ሌላ ያልጠበቀው አደጋ ከፊቱ ተደቀነበት። የኢሕአፓ-ኢሕአሠ ሞት ሰርግና ምላሹ ቢሆንም፤ከትግራይና ኤርትራ ውጭ ያለውን ሰፊ የኢትዮጵያ ግዛት የሚገዛ ግዙፍ ሰራዊት ያደራጀ “ጠላት” እያለ እንቅልፍ ተኝቶ ማደር የማይታሰብ ጉዳይ ሆነበት። ስለዚህ በሰላም ተረጋገቶ ትግራይን ለትግራውያን የተመቸች “ገነት” አድርጎ ለማስቀጠል “ኢትዮጵያ” የምትባለው አገር ከዓለም ካርታ መጥፋት ይኖርባታል። ይህ ብቻ ነበር ትግራይን ገንጥሎ ለመኖር ብቸኛና ዘላቂ ዋስትና የሚሰጠው።
ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ደግሞ ደርግን ተዋግቶ በመጣል ብቻ የሚጠናቀቅ ተግባር አልነበረም፤ ደርግንም ለመጣል ቢሆን አሁን ካለበት አደረጃጀትና ቅርጽ የተለዬ ስልታዊ የቅርጽ ለውጥ ያሰፈልገው ነበር።አዲሱ ቅርጽ በዘላቂነት ኢትዮጵያ እንድትጠፋ እጇን በጇ የምትበላበት “መርህ” ላይ ተመስርቶ መቀየስ ነበረበት፤ ስልቱም “ኢትዮጵያዊ” የሚል ካባ ያጠለቀ፤ ዋናው ግቡና ተልእኮው በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ስም እየማለ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ማጥፋት የሆነ “የትሮይ ፈረስ” ማዘጋጀት። ለዚህ ደግሞ የኢ.ሕ.አ.ፓን ፍርስራሽ መጠቀም ወቅቱን የጠበቀ መልካም ታሪካዊ አጋጣሚ ነበር።
ፍርስራሹን በመጠቀም በቀላሉ ወደ መሃል ኢትዮጵያ ሰርጎ መግባት፤ ይህንን ለማስፈጸም የሚሰባሰበው ከፍርስራሽ የተገኘ ቡድን ደግሞ በመርህ ደረጃ “ ኢትዮጵያ እየተባለች የምትጠራው አገር የአማራ ወራሪ ንጉስ በነበረው ምንሊክ ተጠፍጥፋ የተሰራች የብሄሮች እስር ቤት ስለሆነች፤ የትግሉም መነሻና መዳረሻ በምኒሊክ የተሰራችውን በአማራ ትምክህተኛ ማንነት ላይ ተመስርታ የተገነባቸውን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አጥፍቶ በመቃብሯ ላይ የራሳቸው ሙሉ ነጻነት ያላቸው ብሄር-ብሄርሰቦችና ህዝቦች የሚፈጥሯት አዲስ አገር መፍጠር” ነው የሚለውን እውነት መሰል ኩሸት መቀበል የመጀምሪያ ግዴታውይሆናል። የዚህ ስልታዊ የትሮይ ፈረስ ቀለም “ የብሄር ትግል” ማስፈጸሚያ ሆኖ ሲቀርብ ዋናው “ኢትዮጵያን የመበታተን መርህ” በወያኔ ልብ ውስጥ ተደብቆ የፈረሱ ቀለም የማደራጃ ስልቱን ተቀብሎ ዘመቻው ቀጠለ።
ይህንን ተልኮ የማስፈጸም ሃላፊነት የተሰጠው የዚያን ጊዜው ተጋድሎ ህዝቢ ሐርነት ትግራይ (ተ.ሐ.ሕ.ት) የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ወደ ቀሪው የኢትዮጵያ ግዛቶች መረማመጃ ድልድይ ለመስራት የሚያገለግልውን የኢ.ሕ.አ.ፓ ፍርስራሽ በማሰባሰብ ስራ ተጠምዶ መጣደፉን ቀጠለ። የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የቅርምቱን ትዕይንት ቀዳሚ ገቢር ለመተወን ለትሮይ ፈረስነት ከታጩት አሁን በህይወት ካሉና በህይወት መኖራቸውን ከማላውቃቸው ጥቂት የኢ.ሕ.አ.ፓ አባላት ጋር በመሆን የመሳተፍ እድል ስለገጠመኝ “መርህ” የሚባለውን ጸረ-ኢትዮጵያ ስሌት የማዳመጥ ታሪካዊ እድል ገጥሞኛል። ለማንኛውም ገዳሪፍ ከተማ ውስጥ ይገኝ በነበረው የዚያን ጊዜው (ተ.ሐ.ሕ.ት) ጽ/ቤት ውስጥ በተካሂያዱ ተከታታይ ስብሰባዎች በተፈጠረው መሰረታዊ የታሪክና ፖለቲካ ትርክት አለመግባባት የተነሳ የተጀመረው ውይይት ተቋረጠ።
ከጥቂት ዓመታት በሁዋላ “ኢህድን” በሚል ስም ከወያኔ ጋር ተባብሮ መንቀሳቀስ የጀመረ ከኢህ.አፓ ፍርስራሾች አንድ ወገን መፈጠሩን በሰማሁ ጊዜ “ከወያኔ ጋር አብሮ ለመሰለፍ ያስቻለው የመርህ ጥያቄ “ጉዳይ በአይምሮየ አቃጭሎ ነበር። ያ ጥያቄ ወያኔ በ1972 ዓ.ም ለኔና ለጓደኞቼ ቀርቦልን የነበረው ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬ አልነበረኝም። ከዚያ በኋላ በ1983 ዓ.ም ወራሪው ወያኔ ኢህ.አ.ዴ.ግ በተባለው የትሮይ ፈረሱ ተሳፍሮ አዲስ አበባ ሲገባ ከ10 ዓመት በፊት ሱዳን አገር ላይ ሲጠነሰስ ያየሁትና የሰማሁት “ለኔ” ኢትዮጵያን የመበተን “የመጨረሻው ሴራ መጀመሪያ” እንደሆነ ለመረዳት ማንንም ማማከር አላስፈለግኝም። ውስጤ በሆነው ሁሉ ቢቆስልም ወደፊት ከጊዜ ጋር በማቀርባቸው ዝርዝር ታሪካዊና ፖለቲካዊ መሰናክሎች ምክንያት በቅርብ ከማውቃቸው ወዳጆቼ ጋር ካደረግሁት ውይይት ያለፈ ማድረግ ሳይቻለኝ ቀረ።
በመቆየት ይሆናል ብየ ያልጠበቅሁት “የትሮይ ፈረሱ ቀለም” ያማለላቸው ኢትዮጵያውያን ሲበዙና ወያኔም ተደላድሎ የሃገሪቱን ንብረት ያለርህራሄ በመዝረፍ ተግባር ላይ ሲሰማራ ቢያንስ-ቢያንስ የማፈራረስ መርሁን የሚያስረሳ ጨዋታ ውስጥ የገባ እየመሰለኝ ሄዶ ነበር። ፈጽሞ ግምቴ መሳሳቱን ግን የሰሞኑ ህኔታ አረጋገጠለኝ። ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ ያኔ በ1972 ዓመተ ምህረት የሰማሁትናለኔና አብረውኝ ለነበሩት ጓደኞቼ ቀርቦልን የነበረውና በእንጭጩ የተጨናገፈው ስብሰባ ዋና ምክንያት የነበረው አሰቃቂው “የመርህ” ጥያቄ እስከዘንድሮ መኖሩን ያረጋገጠ ክስተት ሲፈጠር እንደገና ብልጭ ያለብኝ “የማይሞተው የወያኔ ኢትዮጵያን የመበተን እቅድ” ነበርና እየደነቀኝም እየጎፈነነኝም ቢሆን ጨዋታን ከስሩ እንዲሉ የማውቀውንና የገባኝን ያህል ለመተንፈስ የተገደድኩትም በዚህ የተነሳ ነው።
ለኔ ወያኔ ኢትዮጵያዊ ድርጅት አይደለም- ሆኖም አያውቅም፤ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ.ም ከትሮይ ፈረስነት ያለፈ ህልውና የለውምም ለማለት የሚያደፋፍረኝ በተግባር የተረጋገጠ በተዛባ ታሪካዊ፤ ርዕዮተዓለማዊና ፖለቲካዊ ፍልስፍና ላይ የተመሰረትመርህ እንዳለው ከመገንዘብ ነው። አዲስ የተቀላቀሉት የኦህዴድና ብአዴን መሪዎች ፤ የሚመሩት ድርጅት “ ከትሮይ ፈረስነት የዘለለ” ተልኮ እንደሌለው ቀደምት አለቆቻቸው እነበረከትና አባዱላ፤ኩማ ደመቅሳ “በጥልቀት” ሳያስጥኗቸው በመቅረቱ ያለተልኮው “መርሁን ጥሰው” መስራት በመጀመራቸው የወያኔን ቆሽት እስኪሸተን ድረስ ጠብሰውታል። በወያኔ ዘለቄታዊ እቅድ “አይንና ናጫ” ሆነው መቀጠል ይገባቸው የነበርባቸውን የአማራንና ኦሮሞ ህዝቦችን አንድነት በመስበክ “የለየለት በመርህ ላይ የተፈጸመ ክህደት ፈጽመውብኛል“ በማለት የተላለፈውን ውሳኔ ያዘጋጀውም ይኼው ላለፉት አርባ አመታት ጥፋቷን ሲደግስላት የኖረውና ከመግለጫው ጀርባ ያየሁት እውነተኛው ወያኔ ነው። ለኔ “ምህረት” የሚለውን ቧልት የሚያውራው ሳይሆን “መርህ-አልባ” ብሎ የጮኽው ነው ወያኔው።
ስለዚህም ነው የምህረቱ መግለጫ ከጊዜ መግዣነት የዘለለ ፋይዳ እንደማይኖረው ግልፅ ሊሆን የሚገባው። ለዚህም ነው ይህንን ተከትሎ ስለሚፈጠረው ውጤት ብዙ ሳንጨነቅ በጀመርነው ነጻ የመውጣት ትግል ላይ ብቻ ማተኮር ወሳኝ የሚሆነው።
ከላይ ላስረጅነት ባቅረብኩት ቅንጭብ ታሪክ አንጻር ብዙ ምርምር የማያሻው የሰሞኑ የወያኔ ጎራ የቁም መቀዣበርና ያስተሳሰብ ድርቅ በጉልህ የሚታየው ከምህረቱ ቧልት አስቀድሞ ባወጣው ባለስምንት ነጥብ እብሪት አዘል የተንሸዋረረ አቋም መግለጫ ነበር። የመግለጫው መንሸዋረር ከሁሉም በላይ ገዳይና ሟች ባንድ ገበታ ተቀምጠው ገዳይ ሟችን በጠራራ ጸሃይ የሚታረድበትን ቢላ ሲያስለውና ሟችም መሞቱን በጸጋ ተቅብሎ በራሱ ሞት አብሮ መዶለቱን እንድንቀበል በድፍረትና ያለይሉኝታ ማንባረቁ ነበር ።
ሌላውና ከሁሉም በላይ የሚገርመው ደግሞ አውቆም ይሁን ተሳስቶ ወይም በተለመደው ማን አለብኝነት ተደፋፍሮ ወያኔ “የብሄረሰቦች፤እስር ቤት” የሚላትን ኢትዮጵያ ከዓለም ካርታ ለማጥፋት የደገሰው፤ አስቦና አልሞ የተነሳበት “የብተና መርህ” አደጋ እንደተጋረጠበት፤ አፍ አውጥቶ አይኑን በጨው አጥቦ በእብሪት ያምባረቀበት ፋሽስታዊ ዛቻ ከዚሁ ታሪካዊ ባህሪው የመነጨ መሆኑ አንድ ነግር ሆኖ የተጀመረው ህዝባዊ ትግልና ኢትዮጵያዊ አንድነት የተደገሰልንን ጥፋት ጥሶ መጎምራቱን ማሳያ ምልክትነው ።
የህዝቡ ትግል ጉልበት ሌላ ያረጋገጠው አስቂኝና አስገራሚ ሀቅ አለ።
የፋሽስታዊው መግለጫው ዋና ሃይለ ቃል “በመርህ ላይ ያልተመሰረተ የህዝብ ግንኙነት ተፈጥሯል!!”በሚለው ውሳኔ መነሻነት ሞት የተደገሰላቸው የብአዴንና የኦህዴድ መሪዎች በተባባሪነት ሰጥተውታል ስለተባለው መግለጫ ውነትነት መላ መተን ሳናበቃ፤ ለ27ዓመታት ሌት ተቀን እንደሌለ ሲነገረን የነበረው “ፖለቲከኛ” የሚለው መንፈስ ድንገት ነፍስ መዝራቱን ፤ የለም ሲሉን ከነበሩት ነውርየለሽ ወሮበሎች አፍ ስንስማ ሕዝባዊ ትግሉ የፈጠረውን መደነባበርና ሽብር ይገልጥልናል። ዞሮ ዞሮ “ጅብ እስኪይዝ ያነክስ” እንዲሉ ወያኔ ያሰበውን እስኪያስፈጽም “በየሴኮንዱ ያማልሉልኛል የሚላቸውን የህዝብ አጀንዳዎች እያነሳ መሰንቀር፤ እንደቀጠለ ነው፤ ባድመ፤ አባይ፤ ባንዲራ፤ ፖለቲካ እስረኛ… ይቀጥላል፡ ኢትዮጵያ እስክትፈራርስ።
የነገሬ መነሻ እንግዲህ ከራሱ ከወያኔ ባህሪና በተለይም ከድንገቴው መግለጫ በፊት ባሳለፈው “የወዮላችሁ” ውሳኔ ሃይለ-ቃል ላይ ያነጣጠረ የሆነው እውነተኛው ወያኔ እርቃኑን የታየበት መስተዋት ስለነበር ነው።
ተጠናክሮ የቀጠለውን ህዝባዊ እምቢተኝነትና የነጻነት ትግል አጣጥሎ በዛቻና ማስፈራሪያ የተሞላ መግለጫ በሰጠ ማግስት እንደድንገቴ ብልጭ ያደረገው ጥቂቶችን “ዕልል” ያሰኘው የተወላገደ አጨናባሪ መግለጫ ከጊዜ መግዣነትና የማይዝል ቧልት ሊሆን ይችላል ብሎ መጠርጠርን ተገቢ የሚያደርገውም ባንድ ጀምበር የታየበት የስርዝ-ድልዝ ጋጋታ ሌላው ውነት ነው።
ይሁን ብለን በትግስት ልናየው ብንፈልግ እንኳ የድንግቴው “ምህረት” በተግባር እስኪረጋገጥ ለአንዳፍታም ቢሆን ሳይዘናጉ መታገል ለውይይት የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፤ ምክንያቱም ትግሉ እስረኛ የማስፈታት ሳይሆን ጀግኖቻችን የታሰሩበትን ዓላማ የማስፈጸም ነውና። ስለዚህ ዓላማው ከእስርም ከግድያም የላቀ ስለሆነ ወያኔ ለአንድ አፍታም ቢሆን በዚህ ደረጃ አሳንሶ ሊሰጠን ባሰበው አጀንዳ ተወጥረን “በማን ይፈታል አይፈታም” እንቶፈንቶ የምናጠፋው ጊዜ እንደሞኝ መንገድ መሪ በወያኔ ማጭበርበሪያ ስልት ደግሞ-ደጋግሞ መውደቅን ያስከትላል። ከዚህ ስተት የምናመልጠውና የታሰሩትም ሆነ በመንፈስ የታሰርነው ሁላችን ነጻ የምንወጣው ወራሪዎቻችን ላንዴና ለመጨረሻ አገራችንን ለባለቤቶቹ ኢትዮጵያውያን ሲያስረክቡን ብቻ ነው በሚለው የዘላቂ ድል አቅጣጫ ያተኮርን እንደሆነ ነው።
አይናውጣው የወሮበሎች ቡድን የሰጠው መግለጫ ያበሳጫቸው አንዳንድ ወገኖቼ “ህዝብን ከህዝብ ማቀራረብ በምን መለኪያ ነው የመርህ መጣስ የሚባለው? “ ሲሉ በብሽቀት ሲተቹ፤ ሌሎች ደግሞ በወያኔ የጦር መሪዎችና በሶማሌ ነፍሰበላ ገዥዎች ትብብር የተከናወነውን ህዝብን ከህዝብ በጭካኔ የማገዳደል ሴራ “መርህ -አልባስ ከተባለ እሱ ነው” በማለት ሲሞግቱ ተደምጠዋል። እኔ ደግሞ ሁለቱም አስተያየቶች ልክ አይደሉም በማለት እብሪተኛው ወያኔ ያለውን መቶ በመቶ ደግፌ ቅን ወዳጆቼን በትህትና ነቅፌ ለመሞገት የተደፋፈርኩት ከላይ በጠቃቀስኳቸው ዋነኛ ምክንያት ነው።
ከመነሻዬም እንዳመለከትኩት እብሪተኛው ወያኔ እንደሚለው የለማ መገርሳና የገዱ አንዳርጋቸው ቡድኖች የህዝቡን ቁጣ አሽትተው በጊዜ ከህዝቡ ጉያ መለተማቸው ቡድኖቹ ከተፈጠሩበትና ከተሰለፉበት ድርጅት ዓላማ አንጻር፤ በተለይም ጌታቸው ከወጠነው ስር የሰደደ የመበታተን እቅድ አኳያ “ታላቅ የመርህ ክሕደት” ፈፅመዋል፤ መባሉ ለወያኔ እውነት ነው። ፈጣሪያቸውና ጌታቸው የወሮበላው ቡድን በገደምዳሜ ያፈነዳውም ይህንኑ ሀቅ ነው። ከላይ እንደገለጽኩት በ1983ዓ.ም ድፍን ኢትዮጵያን ወርሮ በምንይልክ ቤት መንግስት የመሸገው ወራሪ ሃይል ዋና ተልኮው “ኢትዮጵያ “ በሚል ስም የሚጠራውን ህዝብ የመበታተን መርህ ለማስፈጸም የሚያስችለውን አደረጃጀት ሰርቶ እንደገባ ግልጽ አድርጊያለሁ።
ባልጠበቀው ሁኔታ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት በኦሮሞና አማራ መሀከል የታየው የአንድነትና አብሮነት ቁጣ ግን ይህንን በመርህ ላይ የተምሰረተ መሰሪ አደረጃጀት ከስር መሰረቱ አነቃነቀው፡፤ ኢትዮጵያውያን ከኢጣልያ ቅኝ ገዥዎች ወዲህ ዳግም የበግ ለምድ በለበሱ ወራሪዎች የተነጠቀውን ነጻነታቸውን የማስመለስ መራራ ትግል ሲጀምሩ ፤ ላለፉት 40 ዓመታት በወያነ ጠንሳሾች ሲቀነቀን የነበረውና “ኢህአዴግ” እየተባለ የሚጠራውን ስብስብ መፍጠር ያስቻለው መርህ እንደበረዶ ሲቅልጥ እንደክረምት ሙጃ ሲጠወልግና ሲሽመደመድ ማየት ባለቤቱን የበግ ለምድ ለባሽ ወራሪ ቢያንቅጠቅጠውና ቢያዛብረው አያስገርምም።
አስረግጦ ለመናገር ያስገደደው፤ “ ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል” እንዲሉ በሀዝብ ዓመጽ ጥንቢራው የዞረው ወራሪ ቡድን፤ የአማራና ኦሮሞ ህዝብ አይበገሬነት እንደማኖቤላ ቀስቅሶ ያባነናቸው የአፍራሽ ሃይሉ ስብስብ መሪዎች የነበሩት የለማና የገዱ ቡድኖች “ ጌቶቻችን ህዝቦቻችን ናቸው” ብለው ፈጣሪያቸው ወያኔ ከፈለመላቸው ጎዳና ወጥተው በተቃራኒው መቆማችውን ሲመለከት “መርህ-አልባ” ነው ብሎ ቢወነጅላቸው ሃሰት የለውም።የሱ ሃቅ ለሌላው ኢትዮጵያዊ ሞት ቢሆንም ላለፉት አርባ ዓመታት የታገለበትና የተዋደቀበት “መርህ” ሲጨናገፍ መዛበር ቢጀምር አያስደንቅም። ታላቅ ክብር ለኦሮሞና ኣማራ ህዝቦች ሰማእታት ይሁንና በደማቸውና በከፈሉት መስዋእትነት ገዳዮቻቸው “በመርህ ስም” የሰነቁላቸውን የጥፋት ድግስ ባደባባይ አስገለጠጡት።
በሌላ በኩል የወያኔ ነፍጠኞች ከሶማሌ ቀምቶ አደር ጃዊሳዎች ጋር በሽርክና የሚያካሂዱት ሕዝብን-በሕዝብ፤ ወንድምን በወንድም ወዘተ ላይ የማነሳሳት፤ የመግደልና የማገዳደል ተግባር ከዚሁ ወያኔ ከተመሰረተበት “መርህ” የመነጨ የበግ ለምድ ለባሽ ወራሪነት መሰረታዊ አላማ ውጤት በመሆኑ የተደረገውን ሁሉ ከቡድኑ መሰረታዊ ማንነት አንጻር ከታዬ አንዳችም የመርህ መፋለስ ስተት እንደሌለበት መረዳት አያዳግትም ። ይልቁንስ ጠፍጥፌ ሰርቻቸዋለሁ ብሎ የተመካባቸው ባማራና ኦሮሞ ስም ያደራጀው ድርጅት አውራ መሪዎች ያልፈጸሙለትን ከሶማሌ ወገኖቻችን መሀከል በበቀለ የሙጃ ፈረስ በመርህነት የቆመበትን የደም ምሱን ሊቃመስ አስችሎታል።
ይልቅ ይህ የሰሞኑ ሁኔታ ለማንኛችንም ፤ አውቀን አይናችንን ለጨፈነው፤ የለብሱትን የበግ ለምድ አይተን “በየዋህነት” ወራሪነታቸውን ስንጠራጠር ለባጀነው፤ ወይም ለደገሱልን የመተላለቅ ዓላማ ማሰፈጸሚያነት የተጠቀሙበት ጎሳን መሰረት ያደረገው ያደረጃጀት የጥፋት ዱላ ሰለባ ሆነን ለተገኘነው ፤ ወይም በሌላ በራሳችን በሆነ ሰበብ ለ27ዓመታት ያነክስንበት “የወያኔ ይሻሻል ይሆናል ቅዠት” ላንዴና ለመጨረሻ ያበቃለት መሆኑን ልብ ላለ ማነቃቂያ ደወል ነው።
ይህን ደወል አዳምጠን ውነትነቱን ከተቀበልን ኳሷ ከወያኔ እጅ መውጣቷን ለመገንዘብ “የበለስን ጫፍ አይቶ የበጋን መቃረብ ከመተንበይ” ያነሰ ማስተዋልን ብቻ ነው የሚጠይቀው፡፤ ይህ ከፊታችን የሚታየው የወያኔ የቀን ቅዠትና መዛበር ዋና ምንጩ የህዝቦች አይበግሬነትን ተከትሎ የመጣ የምጥ ጣር መገለጫ እንጂ “በመርህ” ደረጃ የተሰለፈበትንና ደም የገበረበትን ማንነቱን እንደማይቀይር አፍ አውጥቶ በድፍረትና በቁጭት ባስጠነቀቀበት መግለጫ መሳይ ዛቻ አረጋግጦልናል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያውያን ከንግዲህ ወዲያ ዳግም ወደትፋታቸው የሚመለሱበት ዘመን ማብቃቱን ወራሪዎቻችን “በጥልቀት “ ከተረዱት የማይታሰበውን “በጥልቀት የመታደስ መዝሙራቸውን” አቁመው በዚች የመጨረሻዋ ደቂቃ እንኳ “እስከዛሬ የደገስንላችሁ የእልቂት ድግስ ተነቅቷልና የወንድ በር ስጡን” በማለት ልባችንን የሚያራራ እንጉርጉሮ ቢጀምሩ ይበጃቸዋል።
ወራሪው የወያኔ ቡድን “መርህ ጥሰዋል” ባላቸው “ፍጥረቶቹ” ላይ የተለመደ የቅጣት በትሩን ለማሳረፍ ጥርሱን ነከሶ ባንቀጫቀጨ ማግስት በግፍና ባረመኔያዊ ጭካኔ በእስር ስም አግቶ ሲያንገላታቸው የነበሩትን ግፉዓን እስረኞች” በይቅርታ ልፈታ ነው” የሚለውን ቧልት መሰል አናዳጅ ወጉን አቁሞ ዝቅ ብሎ ምህረት ቢጠይቅ ፤ ቢያንስ ቢያንስ ሊጠራርገው የቀረበው ህዝባዊ ማዕበል ባለቀ ሰአትም ቢሆን እንኳ ለሰባዊ ፍትህ እንዲበቃ የሚያስችለውን እንጥፍጣፊ እድል እንዳይነፍገው ባመቻቸ ነበር።
ከንግዲህ መናደድ ካላብኝ የምናደደው በራሴና የኔ በምላቸው ወገኖቼ ብቻ ነው፤ ዘወትር ወያኔ እንድፍርፋሪ በሚወረውርልን አጀንዳ የጨበጥነውን ያሸናፊነት ኳስ እያስነጠቅን መቀጠል ከጅልነትም ያልፈ ነሆለልነት ነው። የዱቼ የሃሳብ የልጅ-ልጆች በብርሃን ፍጥነት “የለም “ ሲሉን የኖሩትን “አለ” ብለው ሲነግሩን ቢያንስ ቢያንስ መቀላመዳቸውን እንዳወቅንባቸው የሚገባን ባይመስላቸው እንኳ መቼም ጊዜ የሚነግሩንን ሁሉ እንዳልተቅበልናቸው የሚረጋገጠው ቁጣችን በጀመረው የሃሳብ አሸናፊነትና የበላይነት ጉልበት የቀጠለ እንደሆነ ነው።
የእነለማ ና ገዱ ቡድንም “በሬ ካራጁ ይውላል “ የሚለውን የቆየ አባባል አስታውሶ ማንነቱን በይፋ ያጋለጠው የወራሪ ስብስብ “ለራት ሲያስቡን ለምሳ አደረስናቸው “ ብሎ ሳይቀራመታቸው መለስ-ቀለስ ማለታቸውን ትተው ጉልበትና ልብ ከሰጣቸው ህዝብ ጎን ለትመው መቀጠል ለዘለቄታው እነሱነታቸው የሚሻል ብቸኛ መንገድ መሆኑን ከዘነጉ ከድሮውም ቢሆን ከቀልባቸው አልታረቁም ነበር ማለት ነው።
ወዲያም አለ ወዲህ፤ በህዝባዊው ማእበል ተጠራርገው ወደዳር የወጡትም ሆኑ ማእበሉን ተከትለው የነጎዱ በያጋጣሚው እየተደናቅፉ ቢቀሩ እንኳን የተጀመረው የነጻነት ይገባኛል ትግል በጠራራ ፀሃይ መቀዣበር የጀመረውን የወያኔ ቅኝ ግዛታዊ የጭካኔ ስራት ግባተ መሬት ሳያረጋግጥ አይመለስም። ከፊታችን ያለው ውነት የወራሪዎቻችን ዠንበር አዘቅዝቃ ልትጠልቅ እየተንደረደረች መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በልጆቿ የተባበረ ክንድና መስዋዕትነት እስከዓለም ፍጻሜ ይዘልቃሉ። የነገ ሰው ይበለን።
ጌዲዮን በለጠ (gedionbe56@yahoo.com)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
በለው! says
“ሰበር ዜና፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ እንደሚፈቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አስታወቁ፡
_____________________________!
“በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት በፍርድ ቤት የተፈረደባቸው ወይም ደግሞ ወንጀል በመፈፀም ድርጊት ተጠርጥረው በአቃቢ ህግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የሚገኙ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች የተሻለ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በምህረት ህግና ህገመንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ እንዲፈቱ ይደረጋል::” ጠቅላይ ሚኒስተር ሃይለማርያም ደሳለኝ
—————————————–!
ሲተረጎም ……>>>
” አሁን እስረኞች እና ቤተሰቦቻቸው የገዢውን ፓርቲ መልካም ገጽታ ለማጠልሸት ለሰበዓዊ መብት ተከራካሪ አካላት የሚያጋልጡትና የውጭ ዕርዳታ ገቢውን የሚያስቆሙበትን ፓርቲው አውቋል፡፡ ዋነኛው እየተማረሩና እየተሰቃዩ ያሉት በህወሓት/ኢህአዴግ ፖሊስና መርማሪዎች በሚደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት (ጥፍር መንቀል፡በነገድ መዘለፍ፡የዘር ፍሬ ማኮላሸት፡ ሴት ልጅ እርቃነ ሥጋ ማቆም፡ ጭለማ ቀዝቃዛ ምድር ቤት ማጎር፡ በቤተሰብ የሃይማኖት አባትና የሕግ ባለሙያን አለማገናኘት፡አስፈላጊውን ሕክምና መነፈግን) ሳይሆን፡ ድሮ ደርግ ሲያደርገው በኖረው ግርፋት፡ በሰሙት ዘግናኝ ታሪክ እየተረበሹ /እየተጨነቁ ስለሆነ፡ የእኛን ዲሞክራሲያዊ ብሔርተኛ የእሥረኞች አያያዝ፡ ከፍተኛ ቁጥር ዕሥረኛ በሚይዝ፡ ደርጃውን በጠበቀ ዘመናዊ እሥር ቤት፡ በከፍተኛ ወጪ እንደተገነባ እንደሆነ እናበስራችኋለን።” ዓለም በቃኝ እሥር ቤት ተዘግቶ፡ ኢትዮጵያ በቃችን የሁሉም የቁም እሥር ቤት ሲከፈት እንዲህ ጮቤ ያስረግጣል?
ሕዝቡ ዙሪያውን በለቅሶ ደስታውን እየገለፀ ነው፡ ሙዚየም ሊጎበኝ ትኬት ለመቁረጥ ይጋፋል!? ጉድ ነሽ የአንኮበር ቅጠል።
**************************************************!
>› ቅድሚያ የአንዲት ሀገረ ኢትዮጵያ ሙሉ ዜግነት ሊኖር፡ የመናገር የመጠየቅና ፈጣንና ግልጽ ምላሽ የማግኘት፡ የመሰብሰብ፡ የመንቀሳቀስ፡የመሥራት ነጻነት፡ የፖለቲካል ኢኮኖሚ እኩል ተጠቃሚነት፡ ተፈጥሯዊ የሰው ልጆች መብት እንጂ የፓርቲ ስብስቦች ችሮታ አደለም መሆንም አልነበረበትም። ግን በመፈቃቀርና በመፈቃቀድ ሆኗል። ዲያስፐሩ በተቃዋሚ እሥረኛ ይፈታ ቁማር ጮኸ ህወሓት/ኢህአዴግ ተቀብሎ ቀወጠው መርህ አልባ ቡልጠቃ!ተንታኝና በታኝ….ሌላው
“መርህ አልባ” ግንኙነት አራት ሰዎች በ፭ ባንዲራ ቆመዋል…መግለጫው የፓርቲ እንጂ የፌደራል መንግስት(የፍትህ ሚ/ር) አደለም። ሕዝብ ፍትህ የለም!ሲል ፍርድ ቤትና ዳኛ በፓርቲው የሚዘውሩ ናችው ማለቱ አግባብ ነው። …ውሳኔውም የተነበበው በፓርላማ አደለም፡ የፌደራሉም መንግስት ሰንደቅ የለም። እንኝህ ሰዎች ፬ የእህት ፓርቲ ከአንድ የግንባር ባንዲራ ጋር በ፭ ባንዲራ በ፱ ክልል ባንዲራ በ፩ ፌደራል ባንዲራ በድምሩ በ፲፭ ባንዲራ ሀገር ያሸብራሉ።
ከዚያ አጋር ፓርቲ፡ ተቃዋሚ ተፎካካሪ ፓርቲ ፸፭ እንግዲህ ፺ ባንዲራ አላቸው መርህ አልባ ግንኙነት ማለት ይህ አደለም?።
ከዚያ የቸርች፡ የሴቶች፡ የወጣቶች፡ አዛውንቶች፡ የሲቪል ማኅበራት፡ ዲያስፐርስ፡ አነስተኛና ጥቃቅን ተጠርናፊዎች ማኅበር፡ኢንዱስትሪያል ፓርክ፡ የበጎ አድራጎት፡ ኢንቨስተሮች፡ የጋዜጠኞችና ልማታዊ አክቲቪስቶችና አርቲስቶች ባንዲራ ሲጨመር …ቋንቋ፡ባንዲራና ካርታ ያላቸው ሁሉ የእራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን እስከመገንጠል ሕገ መንግስታዊ ልዩ ጥቅማጥቅም እውን ሆነ ማለት አደለምን!?
ታዲያ ይህ ማኒፌስቶ(ሕገመንግስቱ)ይከበር፡ የነገድና ቋንቋ ተኮር ፌደራሊዝሙ ከሚነካ በአንገታችን ሜንጫ አይባል ምን ይባል?
በእውነት ይህ ወሮ በላ ቡድን በባንዲራ፡ ባርኔጣ፡አንገት ልብስ፡ካኒቴራ በማተም ማን ይስተካከለዋል? እያንዳንዱና ሁሉም ተጠቃሚ ቃሚና አቃቃሚ ስለሆነ ይህ ሥርዓት እንዲቀየር ይፈለጋልን? በእርግጥ ህወሓት ስንት የተማረ ኅይል ቢኖረው የብሔር የበላይነት አለ ሊያስብል ቻለ? መሠረታዊ ነገሩ አድርባይ! አውርቶአደር! ልዩጥቅማጥቅመኛ! አስመሳይ! አጋስስ! በመብዛቱ የተፈጠረ ዓይን ያወጣ ዘረፋ በመሆኑ በታሰረች ሀገርና ሕዝብ እስረኛ ቢፈታ የቁም እስረኛነቱ ይቀጥላል።
**የፖለቲካ ምሕዳር ለማስፋት ሁሉም የፖለቲካ እሥረኞች በምሕረት እና በይቅርታ ይፈታሉ” ተባለ አሉ ፕሬዘዳንቱም(ካሉ) ፍትሕ ሚ/ሩም(ካሉ)።
አንድ ወቅት ይቺ ቃል ድንገት ፓርላማ ተከስታ ተጠቅላዩ ሚ/ር ለገሠ መለሰ ሲያንቆለጳጵሷት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ‘ምህዳር’ የፖለቲካ ሜዳ መሆኑን አላውቅም ነበር ዛሬ ገና ነው ቃሉን የሰማሁት” አሉ.. አዳሜ ሳቀ…. የተሳቀቁም አሉ።
__ እነኝህ የፖለቲካ እስረኞች እንዴት ምሕዳሩን አጠበቡት? እነሱንስ በመፍታት የፖለቲካ ምሕዳር የሚሰፋው እንዴት ነው? የፖለቲካ ምሕዳር ካርታ ሥራ ድርጅት ሚ/ር እስር ቤት ውስጥ ተቋቁሟል ማለት ነው? ታመስን እኮ ወይ የፖለቲካ ቁሌት? ዘይገርም!