ለሕዝቦች አርነት — ላገርህ አንድነት፣
አርቀህ ማለምህ — አሕዛብን ማንቃትህ፣
“..ጠጣሩ እንዲላላ..” ምክር መለገስህ፣
“በረከት” አድርገህ “ርግማን” ማውረድህ..፣
አቤት! “ለነሱማ” እጅግ ማስፈራትህ!
እነ-ኮሎኒያሊስት — ደግሞ እነ-እምፔሪያሊስት…፣
ያገርህ ደመኞች፟- ህሊና የለሾች፣
የሞራል፣ የባህል፣ የታሪክ አልቦዎች፣
አጠገብህ መቆም ከቶ ሲሳናቸው፣
እሚያረጉት ሲያጡ — ወኔ ሲከዳቸው፣
ሃቅን ስለሚሸሹ፟- መበለጥን ስለማይሹ፣
ምኑ ነው እሚደንቅህ? “ዕብድ” ነውስ ቢሉህ!
ለኛ እንጂ ጥበብህ — ባለቅኔነትህ፣
የታሪክ፣ የባህል፣..መምህርነትህ፣
የፍትህ፣ ያንድነት.. ዓርማ ቤዛነትህ..፣
“ለነሱማ” አስፈሪ — ልክ-ልኩን ነጋር፣
ቆጥቋጭ የግር-እሳት — ቀሳፊ የጎን ውጋት፣
ሾተላይ ጸሐፊ — ታሪክ አሳላፊ…፤
ጌታቸው አበራ
ኅዳር 2007 ዓ/ም
(ኖቬምበር 2014)
ይህቺ ግጥም የተጫረችው የዛሬ 15 ዓመት ገደማ ነው። በወቅቱ በጀርመን አገር እየታተመች ትወጣ በነበረች “ራዕይ” በምትሰኝ መጽሔት ላይ፣ ጉምቱው ደራሲና ገጣሚ ጋሼ ኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው)በተከታታይ እጅግ አስደናቂ የሆነ ቃለ-ምልልስ አድርጎ በነበረበት ወቅት፣ ስላለበት አገር ኑሮ ሲጠየቅ የመንግስት አካላት ሳይቀሩ በኑሮው ላይ ጣልቃ እንደሚገቡና እንዲያውም “ዕብድ ነህ ይሉኛል” ብሎ ስለነበር፣ አንጀቴን በልቶት፣ “ለነሱማ ዕብድ ነህ” በሚል ርዕስ የጻፍኳት ነበረች። የግጥሟን ቅጂ በወቅቱ ለጋሼ ኃይሉ መላኬን አስታውሳለሁ።
ሌላ የማስታውሰውን አንድ ልጨምር፤ በምን ምክንያት እንደሆነ በውል ባላውቅም፣ ጋሼ ኃይሉ (ገሞራው)በስደት የሚኖርበት የስዊድን መንግሥት ባንድ ወቅት እንደ ቁም-እስረኛ አርጎት በነበረበት ወቅት፣ በሆላንድ የኢትዮጵያውያን ማኅበር የወቅቱ ሊቀ- መንበር የነበረው ግርማ አያሌው፣ የእውቁ ደራሲያችን ከቦታ ወደ ቦታ የመዘዋወር መብት እንዲከበር የሚጠይቅ ደብዳቤ በማኅበሩ ስም ለስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመጻፍ፣ ደራሲያችን ወገን እንዳለው ከማስመስከሩም በላይ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለማኅበሩ የሰጠውን የደብዳቤ ምላሽ እንዳሳየኝ አስታውሳለሁ።
ጋሼ ኃይሉ፣ በችግርና በመከራ ሲከራተት ቢኖርምና በጣም የሚሳሳላትንና የሚወዳትን እናት አገሩን ዳግም ሳያይ ቢቀርም፣ ለምንም ሳይበገር ታላላቅ የጥበብ ስራዎቹን ለታሪክና ለትውልድ በህያውነት ከትቦና አስረክቦ አልፏል። የመኖርን ትርጉም በአርዓያነት ለማውረስ በብርቱ ጥሯል።
ጋሼ ኃይሉ!መልካም ዘልዓለማዊ ዕረፍት !!
Leave a Reply