
ለ’ክቡር’ ጠቅላይ ሚኒስትር፣
ለኢሕአዴግ ሊቀ-መንበር፣
ጠቅላይ ‘አዛዥ’ ለ”አግዓዚ” ጦር…፤
ይድረስ ለአቶ ኃይለማርያም!
በስምዎ ባዘሏት ወላዲተ-አምላክ..
በወልድ በእየሱስ ክርስቶስ ስም ልያዝዎ፣
ኢትዮጵያን በጥይት አያቃጥሏት…
እግዚአብሔር አባት ይቅር ይበልዎ!
በደርግም ሆነ በወያኔ ዘመን ባገር ያሴሩ፣
እስከዛሬ ሕዝብን ሲያስጨፈጭፉ የኖሩ፣
“እግዚአብሔርን አናውቅም” ብለው የካዱ ነበሩ፤
እርስዎ ግን፣
ከቤተሰብዎ ጋር ማዕድ ሲጋሩ፣
የየዕለቱን ጸሎትዎን ሲያበስሩ፣
የአምላክን ስም ነጋ-መሸ እየጠሩ፣
ይመስለኝ ነበር በእምነት የከበሩ፤
… ግና ከልብ እውነት ካልዘመሩ፣
ትዕዛዛዊ ቃላቱን ካልተገበሩ፣
እምኑ ላይ ነው ታዲያ አምልኮዎ?
የአምላክን መሻት መፈጸምዎ?
ከአረመኔዎች ጋር ተሰልፈው፣
እግዜርን ከካዱ ጋር አብረው፣
እባክዎን ሕዝቡን አያስጨርሱት፣
ይተውማ ይመልሱት፣ አዋጅዎን ይቀልብሱት፣
ለዕልቂት “ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ” ያሉትን..
ተጸጽቻለሁ ብለው ይሻሩት!
ካልቻሉም ይመንኑ፣
ባገር ላይ ቅስፈት ከሚተውኑ!
የእነሱንማ ይተውት…
የነያሬድ…፣ የነገብረመስቀል … ዘሮች ሆነው፣
ከጽላቱ ማደሪያ ምድር ተፈጥረው፣
መስቀሉን ያሳደዱ፣ ታቦቱን ያዋረዱ፣
ፈጣሪያቸውን በይፋ የካዱ..፣
በደም ልክፍት ያበዱ..፣
ናቸውና ባገርና በሕዝብ ህይወት የሚቀልዱ..፣
ይድረስ ለርስዎ—ለኃይለማርያም የምልዎ፣
“እምነት ማተብ አለኝ” ስለሚሉ፣
በእየሱስ ክርስቶስ ስለሚምሉ፣
እውን ከሆነ ማተብዎ—እንዲከበር ነው ህያው ቃሉ!
… የወለምታውን ጉዞ -ገና ከጠዋቱ ሲጀምሩ፣
የእግዚአብሔርን ዘለዓለማዊነት – ለ”ከንቱው የሰው ልጅ” ሲቸሩ፣
ትንሿ ልጅዎ ነበረች – “ምነዋ አባዬ..” ብላ ያረመችዎ፣
በዜጎችዎ ላይ ጦርነት ሲያውጁ – ዛሬስ ማን “ሃይ” ይበልዎ?!
የዓለምን ገዢ ጌታ – ክቡር እግዚአብሔርን ከፈሩ፣
ቃለ-እየሱስ ክርስቶስን – በእውነት ከልብዎ ካከበሩ፣
እባክዎ ጦርዎን መስበቅ ያቁሙ- ጎራዴዎንም ወዳ’ፎቱ ይመልሱ፣
ባረመኔ አግዓዚዎች- የንጹኃን ዜጎችን ደም አያስፈስሱ!
ጌታቸው አበራ
ነሐሴ 2008 ዓ/ም
(ኦገስት 2016)
Leave a Reply