• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ይድረስ የፈጣሪን ስም ለጠሩ ዶ/ር አብይ አህመድ

April 26, 2018 02:11 pm by Editor 1 Comment

በ 44 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ መሪ በመሆን ለመጀመሪያ ጊዜ “ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ”  እያሉ ንግግርዎን ሲያሳርጉ አይቶ ሕዝበ ኢትዮጵያ በደስታ ተሞልቷል። እኔ ግን እያሉ ያሉት ይህ የማሳረጊያ ቃል በሕዝብ ፊት ብቻ ሳይሆን በአምላክ ፊት ምንና ምንን በሃላፊነት ሊያስጠይቅዎ እንደሚችል የነገሩ ክብደት እጅግ አሳስቦኛል።

የፈጣሪ ስም ከተነሳ ዘንዳ፥ ይህ ፈጣሪ የሚሰጠን በረከት ምንነት ይታወቅ ዘንድ ያስፈልጋል። “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” ሲባል ዝንተ አለም አሳልፈን ዛሬን ደረስን። እስከ ዛሬ “ትዘረጋለች” ከማለት አልፈን “ዘረጋች” ወደማለት ሳንሸጋገር ሦስት ሽህ ዓመታት ጠበቅን። በዚህ ፅሁፌ ይህ 3000 ዓመታት ያስቆጠረው ትንቢት ተፈፀመ የሚያስብለው ሁኔታ ምን እንደሆነና፤ የፈጣሪን በረከት የጠየቁት እርስዎ ስለዚህ በረከት ሊኖርዎት የሚገባውን ግንዛቤ ለመጠቆም እሞክራለሁ። የዚህ ጉዳይ ተጠያቂነት ሁላችንንም የሚመለከት ስለሆነ የኛን ድርሻም ለማመላከት እሞክራለሁ።

ይህ ጉዳይ ከሃይማኖት የሚወግን አይደለም። ሃይማኖት የግል ነው፤ ሀገር የጋራ ነው። ሁሉም ሰው ልቡ የፈቀደውን እምነት በነፃነት እንዲለማመድ አምላክ ለሰው ልጆች የሰጠው ነፃ ምርጫን ነው። ስለዚህ መንግስት ሁሉንም ሃይማኖቶች ያለ አድልዎ በእኩልነት የሚያስተናግድ መሆን አለበት። ኢትዮጵያ ልጆቿ በተለያዩ ቤተ እምነት ጥላ ስር ናቸው። ነገር ግን ባብዛኛው ሁሉም ፈሪሃ ፈጣሪ እንዳላቸው መገንዘብ ይቻላል። ሰላምታ በተሰጣጡ ቁጥር እንኳን ይህንን ፈጣሪ በሰላምታቸው ውስጥ ሳያስገቡ አያልፉም።

የጥንት ነገስታት የአምላክን ስም እንደሚጠሩ ሁላችንም የምናውቀው እውነት ነው። የአምላክን ስም ሲጠሩ ግን የኢትዮጵያን መለኮታዊ ጥሪ ያማከለ አልነበረም። እነዚህ ነገስታት የኢትዮጵያን መለኮታዊ ጥሪ አግተው፤ በምትኩ መለኮታዊ ጥሪን በራሳቸው ዘውድ ላይ እንዲያጠነጥን አደረጉ። ስለዚህም የሰለሞን ስረወ መንግስት በመባል የሚታወቀውና የንግሥና ስልጣናቸውን ከእስራኤሉ ንጉሥ ስለሞንና ኢትዮጵያዊቷ ንግስት ሳባ የዘር ቆጠራ ጋር ያቆራኙ በርካታ ነገስታት በምድራችን እንደ ነገሡ ታሪክ ይነግረናል። ከዚህም በላይ የዛጉዬ ስረወ መንግስት የሚባለው የንግስና ስልጣናቸውን ለማረጋገጥ በእስራኤሉ ሙሴና ኢትዮጵያዊቷ ሲፓራ ዘር ቆጠራ ይደገፉ እንደነበር ይታወቃል።

የኢትዮጵያ መለኮታዊ ጥሪ ግን በአንድ ሰው መሪና በእርሱም ንግስና የሚተረጎም አይደለም። ኢትዮጵያ (ሕዝቧ ሁሉ እንደ አንድ ሆነው) እጆቿን እንደምትዘረጋ ታየላት። የኢትዮጵያ ጉዳይ ከእስራኤል ታሪክም የተለየ ነው። የእስራኤል ታሪክ በግለሰብ ላይ ያጠነጠነ ነበር። ጥንት አንድ ግለሰብ የሆነው አብርሃም እጆቹን ወደ ፈጣሪው ስለዘረጋ፤ ዛሬ አይሁድ ሙስሊምና የክርስትና እምነት ተከታዮች ሁሉም አብርሃምን አባታችን ነው ብለው እንደ አዕማድ ያዩታል። የኢትዮጵያ ታሪክ ግን በሕዝብ ላይ ያጠነጠነ ነው። ስለዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ አንድ ሰው ሆኖ፤ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪ በዘረጋች ጊዜ፤ ዓለም ሁሉ በምሳሌነት የሚያያት ምድር እንደምትሆን ነገን የሚደርስ ሰው የሚያየው ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያ አብሮነት (መደመር) እንደ ዘር ሆኖ የአፍሪካን አብሮነት (መባዛት) ይፈጥር ዘንድ ማን ያውቃል?

የኢትዮጵያን ነገሥታት ታሪክ የተደመደመው በጃንሆይ ንግሥና ነበር። ከዚያ በሁዋላ እስከ ዛሬ ድረስ ያሉት መንግስታት ራሳቸውን ንጉሥ ብለው አይጥሩ እንጂ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለስልጣን ሆኖ አገልጋዩ እንዲሆን መንግስትን ለመምረጥ ስላልታደለ፤ እነዚህ መንግስታት ንጉሦች እንደሆኑ መቁጠር እንችላለን። በዐመፅ ወይም በውርስ ነግሠዋልና።

የኢትዮጵያ መለኮታዊ ጥሪ መቼ ይፈፀማል? ይህ መለኮታዊ ጥሪ እንዲፈፀም አንድ መንግስት አዋላጅ መንግስት ለመሆን መወሰን አለበት። ይህም አዋላጅ መንግስት ስልጣንን ለሕዝብ አስረክቦና ሕዝብን ንጉሥ አድርጎ፤ ንጉሥ የሆነው ሕዝብ በተራው አገልጋይ የሚሆነውን መንግስት በሐቅ ምርጫ እንዲመርጥ ዕድል ሲያገኝ ነው። ያኔ ይህ ንጉሥ ለመሆን የሚታደለው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በምርጫው ፈጣሪን የምድራችን ንጉሥ እንደሆነ ዕውቅና ለመስጠት ፋታ ያገኛል። ያኔ ኢትዮጵያ እጆቿን ዘረጋች ተብሎ የእፎይታ ዘመን ጅማሬ ይሆንልናል።

ሃይማኖትና መንግስት ለየቅል ሆነው እና ክህደት ተስተናግዶ ሲያበቃ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ፈጣሪ ኢትዮጵያን እንዲባርክ በባለስልጣናት ጉባኤ የተጠየቀበት ጊዜ ቢኖር ዛሬ ነው። ዶ/ር አብይ አህመድ “ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ” በማለት ለሚቀጥሉት መሪዎቻችን ፈር ቀዳጅና ፋና ወጊ ሆነዋል። ይህ አባባል የራስዎን ግንዛቤ እንደ ግለሰብ የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን፤ በሕዝብ ልብ ውስጥ ያለውን የጋራ ግንዛቤ ማስተጋባትዎ እንደሆነ ጭምር መቆጠር አለበት። ከእንግዲህ የመንግስትም ሆነ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች ይህንን የፈጣሪ በረከት ለመጠየቅ ህሊናቸው ብቻ ፍቃድ ይስጣቸው። ይሁንና ከእነርሱ በላይ ባለስልጣን የሆነ የኢትዮጵያ አምላክ እንዳለ ተዐምረኛዋ ኢትዮጵያ ይታወቅላት።

ታዲያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዶ/ር አብይ ይህንን የፈጣሪ ስም ሲጠሩ፤ እንደ ቀድሞ የእግዚአብሔርን ስም ይጠሩ እንደነበሩ ንጉሦች የመንግስትን ንግሥና ለማስቀጠል ሳይሆን፤ ሕዝቡ ንጉሥ የሚሆንበት አዲሲቷ ኢትዮጵያ እንድትወለድ፤ አዋላጅ ባለስልጣን መሆንን ብቸኛ ተልዕኮዎ እንደሆነ መቁጠር ይገባዎታል። ለዚህም በሕዝብ ዘንድ እንደ ስጦታ እየተቆጠሩ እንደሆነ የኢትዮጵያ ልጅ የሆኑት ዶ/ር አብይ አህመድ እርስዎም የሚያውቁት ይመስለኛል።

የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ተፎካካሪ ብለው እንደጠሩ ተሰምቶ ደስ አለን። ግን እነዚህን ፓርቲዎች ተፎካካሪ ስለተባሉ እውነትም ተፎካካሪ ሊሆኑ አይችሉም። የዲሞክራሲ ምህዳሩ ከሌለ አማራጭ ሃይል ለመሆን በአሳብ ዙሪያ ለመሰብሰብ አይችሉም። ያላቸው ምርጫ ዲሞክራሲ እስኪወለድ ድረስ መቃወም ነው። ስለዚህ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሆኑ፤ በመጀመሪያ ዲሞክራሲን የሚያዋልዱ አዋላጅ ለመሆን ቆርጠው መነሳት ይኖርብዎታል። አዲሲቷ ኢትዮጵያ የምትወለደው ልጆቿ ሁሉ ሲሳተፉ ስለሆነ፥ በመጀመሪያ ዲሞክራሲ መወለድ አለበት። ያኔ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተባባሪ አዋላጅ ሆነው ይገለጣሉ። በመጨረሻም አዲሲቷ ኢትዮጵያ በሕዝቧ ንጉሥነት ትወለዳለች። በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ ወደ ፈጣሪ እጆቿን ለመዘርጋት የምርጫ ነፃነት ይኖራታል። እስከ አሁን ግን ለዘመናት የንጉሣውያን መንግስታት እስረኛ እንደሆነች አለች።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ንጉሥ የመሆን ዕድል ካገኘ፤ ፈጣሪን የምድራችን ንጉስ እንደሆነ ዕውቅናን በደስታ እንደሚሰጥ የሚያውቅ የኢትዮጵያ አምላክ፥ እስካሁን ኢትዮጵያን ከጥፋት እየጠበቀ ዛሬ ደረስን። ዘረኝነት ከፋፍሎን እንዳያጠፋን ስጋት ውስጥ ገብተን ነበር። ዛሬ ፍቅር አሸንፎ በአንድ ልብ እንደ አንድ ቤተሰብ ለመሆን እየተሰራንና እየተያያዝን ያለንበት ወቅት ነው። የሁሉም ነገር ማሰሪያ ፍቅር እንዲሆን እያደረግን፤ ምድራችን በዲሞክራሲ፥ በፍትህ፥ በመልካም አስተዳደርና በልማት እንድትመነጠቅ ሁላችንም ለበጎ ስራ ተግተን አዲስ ታሪክ ይሰራ።

ዶ/ር አብይ አህመድ ይህንን ታላቅ ተልዕኮ እንዲወጡ፤ ሁላችንም ወደ ፈጣሪ እሳቸውን በፀሎትና በምልጃ የምናቀርብበት ጊዜ ነው። ኢትዮጵያ በምጥ ላይ ነችና ሁላችንም አብረን በምጥ ሆነን ወደ ፈጣሪ እንቃትት ዘንድ ይገባል።

ትልቁ የፈጣሪ በረከት ለዚህ ሁሉ ተልዕኮ መሠረት የሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብ ቤተሰብነት ወደ ብርሃን ማምጣት ነው። ይህንንም በተመለከተ አንድ ነገር ልበልና ልቋጭ፦ አሜሪካኖች ስለ አሜሪካ “One Nation Under God” (በአምላክ ስር ያለ አንድ ሕዝብ) ይላሉ። ኢትዮጵያ ደግሞ “One Family Under God” (በፈጣሪ ስር ያለ አንድ ቤተሰብ) ይሁንልን!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰበ
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርካታልም
ዶ/ር ዘላለም እሸቴ፥ ኢሜል ethioStudy@gmail.com

(ፎቶ፤ጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ በአዋሳ)


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።

Print Friendly, PDF & Email

60

SHARES
Share on Facebook
Tweet
Follow us
Share
Share
Share
Share
Share

Filed Under: Uncategorized Tagged With: Left Column

Reader Interactions

Comments

  1. Eyerus says

    May 14, 2018 01:43 pm at 1:43 pm

    ዶ/ር ዘላለም እሸቴ፡

    እውነት ብለዋል!የሚያዋጣን በስም ብቻ የምንጠራውን እግዚአብሔርን እንደ ቃሉ በመኖር ማዳኑ በምድራችን ከዚያም በአፍሪካና በመላው ዓለም ላይ የተገባላት የትንቢት ቃል ሲፈጸም ማየት ነውና እኔም ዶ/ር አቢይ ንግግራቸውን ወደ ተግባር እንዲመነዝሩት እያሳሰብኩ ለተግባራዊነቱም የሚጠበቅብንን ሃላፊነት ለመወጣት ሁላችንም በጾም በጸሎት የታገዘ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ በያለንበት በመሆን ይህ በጎ ሃሳብና ትብብር ለምናውቃቸው ወገኖቻችን ሁሉ እንዲጋባባቸው ብናደርግ መልካም ይመስለኛል!!!

    ስለዚህ እርስዎ ዛሬ ስላቀረቡት አስተማሪና መካሪ ጽሑፍ ይበል በማለት እያመሰገንኩ እዚህ ላይ ለብእርተኞቻችን/ለጸሓፊዎቻችን በሙሉ የሚከተለውን ብዬ ሃሳቤን ልጨርስ፡
    ብዕሮቻችሁ እንዲህ እንደ ዶ/ር ዘላለም እሸቴ መልካም፣ እውነት፣ ፍቅርና ለሁላችንም የሚጠቅም በጎ መልእክት ያለው ቀለም እንዲተፋ የዚህን ጽሑፍ አስተማሪ ሞዴልነት ተጠቅማችሁ እኛን አንባቢ ደንበኞቻችሁን ትጉህ አንባቢዎች እንድታደርጉን በፍጹም ትህትና እጠይቃለሁ???

    የሚያዋጣን፡
    እውነት!እውነት!እውነት!!!
    ፍቅር!ፍቅር!!ፍቅር!!!

    እውነቱ ይነገር ነኝ
    ካለሁበት

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • የአየለ ጫሚሶ ቅንጅት ፈረሰ January 18, 2021 02:31 pm
  • ህወሓት ተሠረዘ!!! January 18, 2021 01:32 pm
  • ዓሲምባ፣ ሣልሳዊ ወያኔና ባይቶና ከመፍረሳቸው በፊት ማብራሪያ እንዲሰጡ ተነገራቸው January 18, 2021 01:00 pm
  • ቤተሰቦች አስከሬን መውሰድ እንደሚችሉ ተነገረ January 14, 2021 06:48 pm
  • ስብሃት፤ “ከሞትን ቆይተናል፤ … አሁን የቀብር ሥነ-ስርዓታችን” እየተፈጸመ ነው January 14, 2021 01:37 pm
  • “ተመልሰን እንነሳለን” ያሉት ህወሓቶች ተመልሰው ወደማይነሱበት ተሸኙ January 13, 2021 01:12 pm
  • አፋር ነፃ አውጪ (ኡጉጉሙን) ለመጠቀም የታቀደው የህወሃት ሤራ ከሽፏል January 13, 2021 01:10 pm
  • ህወሃትን ወደ ጅቡቲ ለማሻገር ሲሰሩ የነበሩ የአፋር ታጣቂዎች በሰላም ወደ ክልሉ ገቡ January 13, 2021 06:47 am
  • በታህሳስ ወር ብቻ ከ344 ሚሊየን ብር በላይ የኮንትሮባንድ ዕቃ ተያዘ January 13, 2021 06:10 am
  • የብልፅግና ፓርቲ ቀጣይ ፈተና ምን ሊሆን ይችላል? January 13, 2021 04:10 am
  • ለትምህርት እንዲሆነን January 11, 2021 01:20 pm
  • “ከተቀበሩበት የጃርት ጉድጓድ ነው ያወጣናቸው” መቶ አለቃ ስዩም ቱርቦ January 11, 2021 12:11 pm
  • የተደመሰሱና በቁጥጥር ሥር የዋሉ የወንበዴው አባላት ይፋ ሆነ January 7, 2021 01:16 pm
  • ዐቢይና መኮንኖቹ በመቀሌ፤ “ድሉ የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው” December 13, 2020 02:36 pm
  • ወንበዴው ህወሓት ከ1.4 ትሪሊዮን ብር በላይ ዘርፎ በውጭ አገራት ባንኮች አስቀምጧል December 8, 2020 01:05 am
  • ማይካድራ – የትህነግ የዘር ማጥፋት ጥግ ቋሚ ምስክር December 8, 2020 12:57 am
  • የወልቃይት ጠገዴ እናቶች ሰቆቃ ሲታወስ December 8, 2020 12:50 am
  • የደብረጽዮን ዋሻ December 7, 2020 11:30 pm
  • ባለ ከዘራው ኮሎኔል December 7, 2020 05:15 pm
  • ሰላማዊ ሕይወት በማይጨው December 7, 2020 04:12 pm
  • ተጠርጣሪ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊሶች የመያዣ ትዕዛዝ ወጣባቸው December 7, 2020 11:46 am
  • ከ3 ሺህ በላይ ተተኳሽ ጥይቶች በወልዲያ ጉምሩክ ሊያሳልፉ የሞከሩ 4 ግለሰቦች ተያዙ! December 7, 2020 11:18 am
  • ወንበዴዎቹ ይጠቀሙባቸው የነበሩ ተሽከርካሪዎችና የግል ሰነዶቻቸው ተያዙ December 7, 2020 10:50 am
  • ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በሶማሌ ክልል ተመሠረተ December 7, 2020 10:31 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2021 · Goolgule