• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

በብሔር ፖለቲካ ሥር “የተቀበረው ፈንጂ”!

December 10, 2013 09:46 am by Editor 5 Comments

የብሔር ጥያቄ በኢትዮጵያ ምላሽ እንዳገኘ የሚያስተጋባው ኢህአዴግ “የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” በዓልን ማክበር ከጀመረ ስምንት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በአንፃሩ “ተመልሷል” የተባለው ጥያቄ እንደተቀበረ ፈንጂ በየጊዜው በየቦታው እየፈነዳ በህይወት፣ በንብረትና በኢትዮጵያዊነት ላይ አደጋ ማድረሱን ዳዊት ሰለሞን ሁነቶችን በመጥቀስ ይሞግታል፡፡

ከአስርት አመታት በፊት

የኢትዮጵያ ተማሪዎች በለውጥ አብዮት ናፍቆት እየተናጡ ነው፡፡ እዚህም እዚያም በተፈጠሩ ቡድኖች የማርክሲስት-ሌኒንስት ፍልስፍናን የሚሰብኩ የርዕዮተ ዓለም ጽሁፎች ይነበባሉ፡፡ ተማሪው ይከራከራል፣ የሌኒኒዝም ፍልስፍና ቀለም ቀለም መሽተት ለጀመረው የ1960ዎቹ ትውልድ ልብ የቀረበ ሆኗል፡፡ ፍልስፍናውን በአገራቸው የፖለቲካ ግለት ለመተርጐም የቋመጡት ወጣቶች በሁለት ጠርዝ ተሰልፈው በኢትዮጵያ ያለው “የመደብ ወይስ የብሔር ጭቆና ነው” በሚል በጠረጴዛ ዙሪያ ይፋለማሉ፡፡

የብሔር ጭቆና በአገሪቱ መስፈኑን ለማሳመን ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከሩ ከነበሩ ተማሪዎች መካከል የብዙዎችን ቀልብ ለመስረቅ የበቃው ዋለልኝ መኮንን በተማሪዎች መጽሔት “On the Question of Nationalities in Ethiopia” የሚል ጽሑፉን ማስነበብ ጀመረ፡፡ ዋለልኝ በጽሑፉ ኢትዮጵያ አንድ አገር ሳትሆን ብዛት ያላቸው ብሔሮች በአማራ የበላይነት ተጨፍልቀው የሚኖሩበት መሆኗን ሞገተ፡፡ የዋለልኝን መከራከሪያ የተቀበሉ ተማሪዎች የብሔር ጥያቄን ዋነኛ መፈክራቸው አድርገው አረፉት፡፡ በአገሪቱ የሰፈነው ጭቆና የመደብ መሆኑን በመግለጽ “አንዱን ብሔር ጨቋኝና ሌላውን ተጨቋኝ” በማድረግ የተነሱትን እነ ዋለልኝን የተቃወሙ ተማሪዎች የብሔር ጭቆናን በሚያስተጋቡ ተማሪዎች “የነፍጠኛ ልጆች” የሚል ተቀጥላ ተበጀላቸው፡፡

ዋለልኝ ከማርክሲስት – ሌኒኒስት ፍልስፍና በቀጥታ የገለበጠባቸውን ቃላቶች በመጠቀም ኢትዮጵያን “የብሔሮች እስር ቤት” በማለት ሰየማት፡፡ በዋለልኝ እንደተዋወቀ የተነገረለትን የተጨቆነ ብሔርን ነፃ የማውጣት ፍልስፍና የትግራይ ተማሪዎች መሬት ላይ ለማዋል በማቀድ የነጻ አውጪነት ቡራኬን ተቀብለው ደደቢት በረሃ ገቡ፡፡ ወጣቶቹ ትግላቸውን በማስመልከት በእጅ ጽሑፍ ባሰፈሩት የመጀመሪያ ማኒፌስቷቸው ትግራዋይ በአማራ ጨቋኝ ብሔር ሲጨቆን መቆየቱን በመግለጽ ጨቋኙን (አማራን) ብሄር በጠብ መንጃ ትግል በመፋለም ትግራይን ነፃ ለማውጣት መነሣታቸውን አወጁ፡፡ በለስ የቀናቸው የትግራይ ነፃ አውጪዎች መላዋን ኢትዮጵያን በመዳፋቸው ስር ካስገቡ በኋላ በ1987 በጸደቀው ህገ መንግሥት የጆሴፍ ስታሊንን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አተረጓጐም ሳይጨምሩና ሳይቀንሱ እንዲሰፍር በማድረግ የስታሊን ደቀ መዛሙርት መሆናቸውን በተግባር አሳዩ፡፡

የአገሪቱ የመንግሥት አወቃቀርም ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም እንዲሆን ተፈረደበት፡፡ ከብዙ አስርት አመታት በኋላ በዋለልኝ መኮንን “የብሄሮች እስር ቤት” ተብላ ከተጠራችው ኢትዮጰያ የተጨቆኑ ብሄሮችን ነፃ ለማውጣት ብሶት አርግዞት እንደወለደው የነገረን ገዥው ፓርቲ ራሱን በነጻ አውጪዎች ሰረገላ ካስቀመጠ 22 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የነገው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓልም በገዥው ፓርቲ እምነት ጥያቄው ምላሽ ለማግኘቱ አይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ ለፓለቲካ ፍጆታ እየዋለ ከሚገኘው ህዳር 29 በስተጀርባ መሬት የረገጡ እውነታዎችን ለመፈተሽ የተነሱ ሰዎች ከ73 የሚልቁ ብሄር ተኮር የፖለቲካ ድርጅቶችን ያገኛሉ፡፡ የእነዚህ ፓርቲዎች ዋነኛ የትግል ማዕቀፍ “ጥያቄው” አለመመለሱን የሚያሳይ ነው፡፡ በአገሪቱ ከመቼውም ግዜ በላይ መንግስትን በትጥቅ ትግል ለማንበርከክ ዱር ቤቴ ያሉ “ብሔር ተኮር” ድርጅቶች ስለመኖራቸውም እየተደመጠ ነው፡፡

በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ጭምር ዘውጌ ተኮር ግጭቶች በስፋትና በብዛት እየተደመጡ ነው፡፡ “በኢትዮጵያዊነት” ጥላ ተሰባስበው የትውልድ መንደራቸውን በመልቀቅ በሌሎች ክልሎች ሀብትና ንብረት ያፈሩ ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራቸው እንደ ባይተዋር ተቆጥረው “እየተገደሉ ነው፡፡ በአሩሲ፣ በአርባጉጉ፣ በበደኖ፣ በአፋር፣ በትግራይ፣ በወለጋ፣ በአሰበ ተፈሪ፣ በጋምቤላ፣ ኦጋዴን፣ ጉራፈርዳና በቦረና “ከክልላችን ውጡ” የተባሉ የሌላ ክልል ተወላጆች ተፈናቅለዋል፣ ንብረታቸውን ተዘርፈዋል፣ ከእነ ህይወታቸው ጉድጓድ ውስጥ ተወርውረው ሴቶቻቸው ተደፍረዋል፡፡

በዘመነ ደርግና ከዚያ ቀደም በነበሩ አስተዳደሮች ግጭቶች የሚነሱባቸውና የሰው ህይወት ለከፋ ጉዳት የሚጋለጥባቸው አጋጣሚዎች የነበሩ መሆናቸውን መካድ ባይቻልም እነዚህ ግጭቶች ግን ይነሱ የነበሩት በግጦሽ መሬት ፍለጋ እንደነበር መዘንጋት አይገባም፡፡ በአገሪቱ የጐሳ ፖለቲካ አየሩን ከተቆጣጠረበት ከ22 ዓመታት ወዲህ ግን የግጭቶች ይዘትና መንስኤ ወደ አንድ ጫፍ በማዘንበል ላይ ይገኛል፡፡ “ክልላችንን ለቅቃችሁ ውጡ” የሚለው ድምፅ በሁሉ ልብ ማስተጋባት ሲጀምር “በህዝብ መካከል አለመተማመንን በመዝራት በመጨረሻ የሚያሳጭደው ውጤት አገርን ለመበታተን ይዳርጋል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል የሚከበረውም “እኛና እነርሱ” በሚል መንፈስ መሆኑም የተቀበረው ፈንጂ ሰዓቱን እየሞላ እንዲሄድ ከማድረግ ውጪ የሚፈይደው ነገር ስለመኖሩ ብዙዎች ይጠራጠራሉ፡፡

ሁሉም የራሱን መንደር እየፈለገ ወደቀረበው እንዲሄድ የሚያደርግ መድረክ መፈጠሩን የሚተቹት ዶክተር ዘውዱ ውብእንግዳ “የፌደራሊዝም ታሪካዊ አመጣጥ” በሚለው መጽሐፋቸው ትዝብታቸውን እንዲህ ያሰፍራሉ፡፡ “በደርግ ዘመን ቀበሌዎች ስብሰባ ህዝቡን ሲጠሩ በ … ቀበሌ የምትገኙ … አዳራሽ ስብሰባ ስላለ እንዳትቀሩ ይሉ ነበር፡፡ አሁን ግን … ብሔር ተወላጅ የሆናችሁ … አዳራሽ እንድትገኙ ማለት ተጀምሯል፡፡ በፊት በአንድ ቀበሌ መኖር የአብሮነት መለኪያ ተርጐ ይወሰድ ነበር፡፡ አሁን ግን በአንድ ቀበሌ መኖር ብቻ በቂ ሳይሆን የብሔር ማንነት እንደመታወቂያ እየተወሰደ ነው” ይላሉ፡፡ ልዩነቶቻችን ጐልተው እንዲታዩ የሚደረጉባቸው መድረኮች በመንግሥት አታሞ እየተጐሰመላቸው አጀንዳ ሲሆኑ ከማየት የበለጠ ህመም የሚፈጥር ነገር የለም፡፡

በዓሉ የሚከበርባቸው ሥነ ሥርዓቶች ለኢህአዴግ ቱባ ባለስልጣናት አትሮንስ በመሆን ከማገልገል በዘለለ የብሔር ፖለቲካው፣ ፌዴራሊዝሙና የክልል መንግሥታት ነጻነት ለውይይት የሚቀርብባቸው መድረኮች አለመዘጋጀታቸውና እስካሁን ብሔርን/ዘውጌን ተገን በማድረግ በተፈጠሩ ቀውሶች ዙሪያ ውይይት የሚደረጉባቸው መንገዶች አለመፈጠሩ በእኔ እምነት በዓሉን “ከፈንጠዝያ” የዘለለ አያደርገውም፡፡ የአማራው ባህል ለትግሬው፣ የጉራጌው ለኦሮሞው፣ የከምባታው ልጅ ለስልጤው እየተሰጠች ያደግንባት አገር፣ አፋሩ ለሃድያው ዘብ የሚቆምባት ምድር ያፈራችን ሰዎች ለአክሱም ሀውልት ጋምቤላው የሚጨነቅባት የቅኖች ምድር ኢትዮጵያ በብሔር ፖለቲካ በናወዙ ጥቂት ቡድኖች ትልቁን ምስል ጠብቃ እንድትኖር እነዚህ መድረኮች “የእኛና የእነርሱ” የሚሉ ስሜቶች ስር ሳይሰዱ የሚቀርቡባቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡ ያን ጊዜም “የተቀበረው ፈንጂ” ይመክናል፡፡

የብሔር ፖለቲካ መዘዝ

በአገሪቱ ከ84 የሚልቁ ብሔረሰቦች እንዳሉ ከመነገሩ ባሻገር የትኛው የማኀበረሰብ ክፍል ብሔር፣ የትኛው ብሔረሰብ ወይም ሕዝቦች የሚሰኙት የትኞቹ እንደሆኑ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ በአንዳንድ አደባባዮች የጆሴፍ ስታሊንንና የዋለልኝ መኮንን ንግግሮች እንደወረደ በመደስኮር “አንደበተ ርትዕ” ተብለው የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ እንኳን እነዚህን የማኀበረሰብ ክፍሎች ሳይተነትኑ አልፈዋል፡፡ ከስምንት ዓመት ወዲህ መንግሥት የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በተለየዩ ሥነ ሥርቶች እንዲከበር እያደረገ ነው፡፡

በዚህ ቀን ከተለያዩ የማኀበረሰብ ክፍሎች የመጡ ሰዎች በመሰባሰብ እለቱን ይዘክራሉ፡፡ በዚህ ቀን እንኳን የትኛው ብሔር፣ የትኛው ብሔረሰብ፣ የትኞቹ ደግሞ ህዝቦች መሆናቸው አይታወቅም፡፡ ነገር ግን ፍቺ ባልተገኘበት ሁኔታ በዓሉ ይከበራል፡፡ ሌላው አስገራሚ ነገር በህገ መንግሥቱ “ሕዝቦች” ተብለው የተጠቀሱ ክፍሎች ምንም አይነት መገለጫ የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡ ለምሣሌ ህገ መንግሥቱ ስለመሬት የሚለውን እንውሰድ፡፡ መሬት የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በዚህ መነሻነትም ክልሎች በቋንቋ መነሻነት የየራሣቸውን ወሰን እንዲካለሉ ተደርገዋል፡፡ ህዝቦችስ? ነገሩን ትንሽ ለጠጥ በማድረግ እንውሰደው፡፡

በጉራፈርዳ ሰፍረው የነበሩ አማሮች “እንደ ህገወጥ ሰፋሪ ታይተው በክልሉ መንግሥት ውሣኔ ለአመታት ይዘውት የቆዩትን መሬት ጥለው እንዲሰደዱ ተደርገዋል፡፡ መሬቱን እንዲለቅቁ የተደረጉት “የክልሉ ተወላጅ” ባለመሆናቸው ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች የክልሉ ተወላጅ ባይሆኑም ሕዝብ በመሆናቸው እንደ ህገ መንግሥቱ የመሬት ባለይዞታነት መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባ ነበር፡፡ የፌዴራሊዝሙ ተሳክሮት ዶክተር ዘውዱ በመጽሐፋቸው ለፌዴራል መንግሥት ምስረታ መንስኤ የሚሆን መሠረታዊ ነጥብ “ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ መንግስታት ወይም የየራሣቸውን መንግሥታዊ አስተዳደር ያካበቱ ሕዝቦች በፈቃደኝነት ላይ ተመስርተው የሚያቋቁሙት ሦስተኛ መንግሥት ነው፡፡ ስለሆነም ፌዴራላዊ መንግሥት ከትንሹ ቁጥር ሳንነሳ የሦስት መንግሥት ጥምር ነው” ይላሉ፡፡ በዘውዱ ገለፃ ፌዴራሊዝምን በማስተዋወቅ የመጀመሪያዋ ተጠቃሽ አገር ለመሆን የበቃችው ለ100 ዓመታት ያህል በእንግሊዝ ቅኝ ተገዝታ የነበረችው አሜሪካ ናት፡፡

ቅኝ ገዢዋ እንግሊዝ ሀገሪቱን በ13 የቅኝ ግዛት አስተዳደሮች በመከፋፈል ስታስተዳድር ቆይታለች፡፡ አሜሪካኖች ራሣቸውን ነፃ ካወጡ በኋላ ተከፋፍለው የነበሩት ክልሎች በፌዴራሊዝም አማካኝነት መልሰው አንድነታቸውን አግኝተዋል፡፡ ሌሎች በቅኝ ግዛት ስር የነበሩና የተለያዩ አስተዳደሮችም የአሜሪካውን ፌዴራሊዝም በአርአያነት በመከተል የተበታተኑት አንድ መሆን ችለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር ግን የጐሳ በመሆኑ በአለም ከሚታወቀው የፌዴራሊዝም አመሰራረት ጽንሰ ሀሣብ ያፈነገጠ ነው፡፡

በህገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት የክልል መንግሥት ለማቋቋም መመዘኛ ሆኖ የቀረበው ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች በሚል መነሻነት ነው፡፡ አስቀድሜ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በአገሪቱ ውስጥ ከ84 የሚልቁ ብሔረሰቦች ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ክልል እንዲመሰረቱ እውቅና የተሰጣቸው ዘጠኙ ብቻ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹስ? ለምን ክልል የመመስረት መብትን ተነፈጉ?

በህገ መንግሥቱ በዘጠነኛ ክልልነት የተቀመጠው “የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል” ተብሎ እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት ክልሎች የተመሠረቱት ቋንቋን ማዕከል ባደረገ መልኩ ቢሆንም ይህ ወደ ደቡብ ሲያመራ “ጂኦግራፊያዊ” እንደሆነ የተፈለገበት መንገድ ለማንም ግልጽ አይደለም፡፡ በደቡብ ክልል ከ46 የሚልቁ ብሔረሰቦች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ብሔረሰቦች በሌሎች ክልሎች የሚገኙ ብሔረሰቦች የራሣቸውን ክልልና መንግሥት የሚመሰርቱበትን መብት ሲጐናጸፉ በደቡብ ያሉት ግን ይህንን መብት ተነፍገዋል፡፡

የፌዴራሊዝሙ አወቃቀር በቋንቋ በአንድ ቦታ ሲሰራ በሌላ ቦታ በጂኦግራፊ መሆኑም የአወቃቀሩን ተሳክሮት ወለል አድርጐ ያሳያል፡፡ በጎሳ ላይ የተንጠለጠለ የመንግሥት አወቃቀር በሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ኮሶቮና ሩሲያን በመሳሰሉ አገራት የፈጠረውን ሰብአዊ ቀውስ የተመለከቱ ሰዎች የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት የአወቃቀር ተሳክሮት በአገሪቱ ላይ በጊዜ የማይተነብይ ምስቅልል ሊፈጥር እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡ (ዳዊት ሰለሞን)

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Politics Tagged With: Full Width Top, Middle Column

Reader Interactions

Comments

  1. Hussein Gada says

    December 10, 2013 04:58 pm at 4:58 pm

    ዳዊት ሰለሞን ዛሬስ ቃዠ በጣም እጅግ በጣም ኃላ ቀር ጊዜ ያለፈበት ትራክ አስነበብከን ባለፉት ሰረዐት የነበሩትን ዕዉነታን በእጅጉ የካደ በኢትዮጵያ የነበረዉን ብሔራዊ ጭቆና አንደልነበረ አድርገህ ማቅረብህ ያለፈዉ ስረዐት ናፋቂ መሆንህን ቁልጭ አድርጎ ያሳዬ ፁሁፍ ነዉ

    Reply
    • Hussein Gada says

      December 10, 2013 06:01 pm at 6:01 pm

      በእዉነት እኛ በበለፈዉ ስረዐት የያትኛዉ ብሔራሰብ በየትኛዉ ብሔር ላይ ጭቆና አደረሰ የሚል አመላከከት የለንም የማይካደዉ እዉነት ግን የአማራዉ ገዥ መደብ የራሱን የበለይነት ለማረጋገጥ በዚህ አገር ያልጨፈጨፈዉ,የልዘረፈዉ,ብሔራዊ መብቱን ባህሉን ቁዋንቁዋውን ታሪኩን ያላጠፈበት የለም. በዚች ሀገር ይደርሱ የነበሩ ብሔራዊ ጭቆና በህዝቦች ትግል ተንኰታኩታል. የነበራዉንጭቆና ለታሪክ ትተን አሁን መሰራታዊ ለዉጥ ዉስጥ በገባንበትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት ፈጥራን በመረጥነዉ ጎደና እያተጉዋዝን ባለንበት ወቅት ጉደዩን እያራገበችዉ ያለችሁት እናንተ ናችሁ

      Reply
  2. Efrem says

    December 10, 2013 07:27 pm at 7:27 pm

    ፈረንጆቹ “የተቀማጭ ፖለቲካ ” (አርም ቼር ፖለቲክስ) የሚሉት ይህንን ነዉ ። ይህንን በመሰለ ጥልቅ ትንተና በሚሻ ጉዳይ ላይ ለመጻፍ ስትነሳ ሌላዉ ቢቀር አንዳንድ ጥናቶችን ማገላበጥ ይገባህ ነበር ። ጫፍ ተይዞ ጉዳዮችን ወደ ሚፈልጉበት አቅጣጫ ማሮጥ ቀላል ነዉ ። ዋለልኝ በኢትዮጵያ ስለነበረዉ የብሔር ጭቆና ሲጽፍ እንደነወያኔ የመደብ ጭቆናን ብመካድ ወይም ወደሁለተኛ ደረጃ አዉርዶ አልነበረም ። ተወዳጁን ድረ ገጽህን በዚህ መልኩ አታሳንሰዉ ። ሌላ ማስተካከያ መጣጥፍ ብታወጣ ይመረጣል።

    Reply
  3. kedir says

    December 10, 2013 11:59 pm at 11:59 pm

    First z concept of Ethiopianism should be redefined.

    Reply
  4. yigermal says

    December 13, 2013 05:33 am at 5:33 am

    As usual the woyane dogs start barking when they smell the truth. The writer clearly put the reality. Whether you accept it or not, woyane (the puppet of fascism) planted the explosives which will explode gradually just like in Rwanda, Kosovo etc. Woyane thought that it will run away safely. As the proverb says,”yeman bet tefto, ye man yinoral.” The only solution for woyane is to bring national reconciliation in the country, to invite all oppositions to the negotiation table, and to do nation wide election. Other than this, there will be no solution except chaos.

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • የ-አብሮነት ማኅበር የመረጠው ሕቡዕ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይፋ ሆነ November 5, 2025 12:06 pm
  • “የኢሳያስ አፈወርቂ ውድቀት አይቀሬ ነው … “ፅምዶ” ራዕይ ዓልባ” ነው – ሼትል ትሮንቮል October 26, 2025 10:15 pm
  • አሜሪካ ስላልተቀበለችው ነው “የሽሽግር መንግሥት” ስብሰባው በአምስተርዳም ተካሄደው October 25, 2025 11:09 pm
  • በዓባይ ግድብ ምረቃ፡ የሕዝብ ደስታ፣ የቴድሮስ ካሳሁን ዝምታ September 14, 2025 04:27 am
  • ኢትዮጵያ የውኃ ኑክሊየር ማብላያዋን ልታስመርቅ ነው  August 29, 2025 11:46 pm
  • መከላከያ በፋኖ አመራሮች ላይ እርምጃ ወሰደ፤ ዘመነ በ“አንድ ማንኪያ ቅንነት” አንድ እንሁን አለ August 23, 2025 12:35 am
  • ፋኖን በፋይናንስና በሎጂስቲክስ የሚደግፉ የጎጃም ባለሃብቶች ከስደት ሊመለሱ ነው August 14, 2025 12:42 am
  • የበቀለ ገርባ የአሜሪካ ጥገኝነት ማመልከቻ ውድቅ ተደረገ August 13, 2025 12:16 pm
  • ሞዐ ተዋሕዶ “ነጻ አውጪ ግምባር” – ሞነግ August 13, 2025 12:58 am
  • የሃይማኖትና የመንግሥት ጥምረት በረከት ወይስ መርገም?  August 5, 2025 09:18 pm
  • የባከነ የስደት ሕይወት ከደባርቅ እስከ ኖርዌይ July 29, 2025 05:44 pm
  • “በዚህ ዓመት መጨረሻ ትግራይን እንቆጣጠራለን”፤ ቲፒኤፍ July 22, 2025 01:28 am
  • Rusted screws, metal spikes and plastic rubbish: the horrific sexual violence used against Tigray’s women July 4, 2025 01:48 am
  • በሞርሞን ቤ/ክ ዕርዳታ የኪዳነምህረት ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ማምለኪያ ሥፍራ አገኘች July 2, 2025 01:28 pm
  • የበረከት ስምዖን “አየር ላይ ትዕይንት” አየር ላይ ተበተነ July 2, 2025 01:24 am
  • “ዐቢይ ይውረድ፣ እኛ እንውጣ፣ በተራችን እንግዛ” ስልቴዎች (ስብሃት፣ ልደቱ፤ ቴዎድሮስ) June 11, 2025 01:56 am
  • ኤሊያስ መሠረት የሚሠራው ለማነው? ለብጽልግና? ወይስ …? June 3, 2025 01:27 am
  • በግንቦት 20 – የሁለት መሪዎች ወግ May 28, 2025 02:01 am
  • በፈቃዳቸው የተመለመሉ ወጣቶች ሁርሶ ሥልጠና ጀመሩ May 22, 2025 09:11 am
  • ድብቁ ሤራ ሲጋለጥ – “ሦስትን ወደ አራት” May 21, 2025 01:01 am
  • ከትግራይ ሾልኮ የወጣው ምሥጢራዊው ሰነድ ምንድነው? May 20, 2025 09:18 am
  • በደቡብ ጎንደር በጸዳሉ ደሴ የተመሩት 72 ታጣቂዎች እጃቸውን ሰጡ May 19, 2025 02:24 pm
  • የተመሠረተው የፋኖ አደረጃጀት ዋነኛ ዓላማው ድርድር መሆኑ ተነገረ May 14, 2025 11:07 pm
  • ከፍተኛ የፋኖ አመራሮች መገደላቸው ተነገረ May 6, 2025 10:40 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2025 · Goolgule