* በ“ጋዜጠኛነት” ስም የሚፈጸመው የሚዲያ ሸፍጥ
በትግራይ ክልል “ከ200 በላይ ኢንዱስትሪዎች ሥራ ጀምረዋል” በሚል ፓርላማ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው ሪፖርት “ከእውነት የራቀ ነው” ሲሉ የከሰሱት የትግራይ ክልል ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ 212 ኢንዱስትሪዎች ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ሥራ እንዲጀመሩ ክስ ባቀረቡበት ዜና ጎን ለጎን አስታወቁ።
ዜናው የክስ ሳይሆን አሃዱና ቲክቫህ በቅብብሎሽ አንዱ ሌላውን ዋቢ አድርገው ባሰራጩት ዜና መግቢያና ርዕስ ቀዳሚ ያደረጉት “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፓርላማ ያቀረቡት ሪፖርት ከዕውነት የራቀ ነው” በሚል ነው። ዜናው በመሪ ርዕሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የቀረበውን ክስ አላብራራም፣ እርሳቸው ካሉት ጋርም አላነጻጸረም።
የትግራይ ኢንዱስትሪ ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ መሐሪ ገብረሚካኤል “በአሁኑ ወቅት በክልሉ ሥራ የጀመሩት ለትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃ የሚያቀርቡ ሁለት መቶ አነስተኛ ፣ አምስት መካከለኛ እንዲሁም አሥራ ሁለት ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ናቸው” ሲል ዜናው በትምህርተ ጥቅስ የተጠቀሰውን አንቀጽ ማስፈሩን ያዩ ለዝግጅት ክፍላችን “ሚዲያዎቹ ዜና አያነቡም፣ ወይም አይረዱም፣ አለያም ሙያዊ ግድፈት አለባቸው” ሲሉ ተችተዋል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እሽቅድድም በሚመስል መልኩ ለላይክና ተከታይ ለማሰባሰብ የሚሰሩ ዜናዎች በስሙ የሚማልበትን “ጋዜጠኝነት” እያደር ቁልቁል እያወረደው እንደሆነ ያመለከቱ፣ ሚዲያዎቹ ለማስተላለፍ የፈለጉትም አሳብ በዕርጋታ ሊሰሩ እንደሚገባ መክረዋል። የተጠቀሱትን የክልሉ የኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ እውነት በመናገራቸው ሊመሰገኑ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ በፓርላማ ሪፖርታቸውና ማብራሪያቸው ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ በትግራይ ከሁለት መቶ በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች ሥራ እንዲጀመሩ መደረጉን መግለጻቸው ይታወሳል። ለትግራይ በቀጥታ ከፌደራል መንግሥት ከ37 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰጠቱን በጠቆሙበት ማብራሪያቸው ከሁለት መቶ በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጋቸውን ከማመልከታቸው ውጭ ዝርዝር ጉዳይ አላነሱም።
በዚሁ የትግራይን ጨምሮ መላው የአገሪቱ ህዝብ እየሰማ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ወደ ሥራ የገቡት ከሁለት መቶ በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች አነስተኛ፣ መካከለኛ፣ ታላላቅ ኢንዱስትሪዎች፣ ጥሬ ዕቃ አቅራቢዎች ወዘተ” ብለው በዝርዝር ሲያስረዱ አልተሰሙም፤ በዚያ ልክ እንዲያስረዱም አይጠበቅም።
መረጃውን የሰጡት ኃላፊ ሳይሆን ሚዲያዎቹ ባልተባለ ጉዳይ ነቀፌታን ማቅረባቸውና ከንቀፌታው በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአደባባይ የተናገሩትን ንግግር ባልሰማ ማለፋቸው መነሻው ምን እንደሆነ እንዳልገባቸው ዜና የሚከታተሉ በጽሁፍ “ይገርማል” ሲሉ ልከውልናል። ዜናውን ዐውዱ እንዲስተካከል አድርጎ መሥራቱም ያስፈለገው በዚሁ ጥቆማ መሠረት ነው።
ለነጮች ግብዓት ይሆን ዘንድ ከወር በፊት የሪፖርተር እንግሊዝኛ ጋዜጣ “የአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም በአርክቴክት ችግር ሳቢያ ለአፍሪቃ መሪዎች ጉባኤ እንደማይደርስ ወዳጆቼ ነገሩኝ” ሲል ያስተላለፈውን ዜናም ያስታወሱ አሉ።
ሲጎርስና መሬት ሲሰጠው የታከለ ዑማ ቃል አቀባይ የነበረው ሪፖርተር አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ መቋቋሙ ይፋ በሆነበት ቀን፣ ከፓርላማ ፌስቡክ ባገኘው ዜና “የምክክር ኮሚሽኑ ሥራዬን አቆማለሁ ሲል አስጠነቀቀ” በማለት የዘገበውን ለአብነት የሚጠቅሱ “በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ማስታወቂያ የሽያጭ ኪሳቸውን የሚያድለቡ ሚዲያዎች፣ ከመንግሥት እጅ ሽልማት እየወሰዱ ቅምጥ ላደረጋቸው ኃይል ዓላማ ግብዓት መሆናቸው አንድ ሊባል ይገባል” ሲሉ ለሚሰሙ ጥቆማ አቅርበዋል።
የትግራይ ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሰጡት መረጃ ዕውነትነት ያለው በመሆኑ ለሌሎች የክልሉ ቢሮዎችና ኃላፊዎች ትምህርት የሚሰጥ እንደሆነ ዜናውን ያተመለከቱ ተናግረዋል። አያይዘውም ዜናውን በቅብብሎሽ የዘገቡት ሚዲያዎች እርስ በርስ የሚጣላ ዜና ከመሥራት ራሳቸውን ቢያርቁና ከአደባባይ ስህተት ራሳቸውን እንዲጠብቁ መክረዋል።
ሚዲያዎቹ በዘገባቸው ማገባደጃ “ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጥር 28 ቀን 2016 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ተገኝተው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ከ200 በላይ ኢንዱስትሪዎች ሥራ ጀምረው ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው ብለው ነበር” የሚል ሃረግ ከትተው ከላይ በርዕስ የተነሱበት የውግዘት ዜና በራሳቸው አምክነውታል። ዜናውን ጠልቀው ሳያነቡ በማኅበራዊ ገጾች የሚራቡ በሚበዙበት አገር መረጃው ምን ያህል ጉዳት እንደሚያስከትል ከወዲሁ መገንዘብ እንደሚገባ ተመልክቷል።
“ይሁን እንጂ” ይላል ዘገባው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ካስታወሰ በኋላ፣ “ይሁን እንጂ የትግራይ ክልል ኢንዱስትሪ ቢሮ፤ በክልሉ ከጦርነቱ በኋላ ሥራ የጀመሩ ኢንዱስትሪዎችን በተመለከተ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበላቸው ሪፖርት በተጨባጭ መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር የተራራቀ ነው ሲል ሪፖርቱን ውድቅ አድርጓል” ሲል ዳግም ከራሱ ጋር ይጣላል። ሪፖርቱ ከራሱ ጋር አንቀጽ በአንቀጽ ከመላተም አልፎ “መሬት ላይ ካለው ዕውነት ጋር የተራራቀ ነው” ሲል የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሳሳተ ሪፖርት ስለማቅረቡ በንፅፅር አላሳየም።
አቶ መላኩ አለበል የሚመሩት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቀረበ የተባለው የተሳሳተ ሪፖርት በዜናው ጭራሽ አልተካተተም። ወይም ኃላፊው እንዲዘረዝሩና የስህተተ መረጃ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለመቅረቡ በዋቢነት የተቀመጠ አንዳችም አመልካች ሃረግ አልተካተተም። ይህ በሆነበት “ሃሰተኛ” ተብሎ የተፈረደበት ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ለመጠየቅና መረጃውን ምሉዕ ለማድረግ ስለመሞከሩም የተባለ ነገር የለም።
“የቢሮው ም/ኃላፊ አቶ መሐሪ ገብረሚካኤል በአሁኑ ወቅት በክልሉ ሥራ የጀመሩት ለትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃ የሚያቀርቡ 200 አነስተኛ፣ 5 መካከለኛ እንዲሁም 12 ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ናቸው” ብለዋል በማለት በአሀዱና በቲክቫህ የተዘገበው ዜና ተቃውሞ ለማቅረብ የተዘገበ ቢሆንም ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ በትግራይ ሥራ የጀመሩ ኢንዱስትሪዎች ከሁለት መቶ በላይ መሆናቸውን ጠቅሰው ዝርዝር ሳያቀርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለተናገሩት ማረጋጋጫ የሰጠ ዜና ሆኗል። ዜናው 217 የተለያዩ ደረጃ ያሏቸው ኢንዱስትሪዎች ሥራ መጀመራቸውን ኃላፊው አምነው ምስክርነት እንደሰጡ ማረጋገጫ ሆኖ የሚመዘገብ ሆኗል።
ዜናው ከላይ ከዘገበው ጋር ዳግም ሲላተም “ነገር ግን” ብሎ የጀምራል። “ነገር ግን ሁለት መቶ አሥራ ሰባት ኢንዱስትሪዎች ሁለገብ ድጋፍ ተደርጎላቸው ሥራ ጀምረዋል ተብሎ የተገለጸው ከእውነታው ጋር የተራራቀ ነው ሲሉ ተናግረዋል” ሲል ኃላፊውን እንደፈለገው ያላጋቸዋል።
“ከፍተኛ የብድር እና የወለድ መጠንን ጨምሮ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር አሁንም ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ሥራ እንዳይጀምሩ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ በቀጠለበት አግባብ ሁለገብ ድጋፍ ተደርጓል ለማለት አያስደፍርም ሲሉ ተችተዋል” የሚለው ዘገባ የድጋፍና የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር በመላው አገሪቱ የሚታይ እንደሆነ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት የሚያስታውቀው ችግር መሆኑን አንስቶ ተቺውን ስለመጠየቁ የተባለ ነገር የለም።
ከትግራይ ጦርነት ጋር ተያይዞ በተጣለ ማዕቀብ፣ የኢኮኖሚ ሸርና ሽፍትነት፣ የብድር መቆምና የዓለም ወቅታዊ ቁመና እንደ ምክንያት ተጠቅሶ በፓርላማ መቀረቡን ኃላፊው አስታውሶ ዜናውን ለማመጣጠን ስንዝር ያልተራመደው አሃዱ ሚዲያ፣ “ከ37 ቢሊዮን ብሩ ስንት ደረሳችሁ? ስንቱን ተጠቀማችሁበት” ብሎ ቢያንስ ለማዳመቂያ እንኳን ስለመጠየቁ በዜናው አልተመለከተም።
“በክልሉ በነበረው ግጭት የተነሳ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ከነበረበት ከፍተኛ ጉዳት በዘላቂነት እንዲያገግም መሬት የወረዱና ተጨባጭ ድጋፎች እንዲደረጉም ነው የትግራይ ክልል ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐሪ ጥሪ ያቀረቡት” በሚል የተቋጨው ዜና ቲክቫህ “ይህ መረጃ ባለቤትነቱ የአሀዱ ነው” ሲል ምስጋና በመስጠት ነው።
ዜናውን ከአስተያየት ጋር በካሜራ አንስተው የላኩልን “ኃላፊው ሃቀኛ ናቸው። ሌሎችም እሳቸውን መምሰል አለባቸው። ለዚህ ተግባራቸው በአደባባይ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል፤ ሌሎቹም ቢሮዎች እንዲሁ ምስክርነታቸውን ቢሰጡ መልካም ነው፤ መተማመንን ይፈጥራል፤ ዜና ሳታነቡ ርዕስ አይታችሁ የምታጋሩም ተማሩበት” ብለዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply