- “የእኔ ሀብት ሰውነቴ ብቻ ነው የተመዘገበው ሀብት የእኔ አይደለም” ክንፈ ዳኘው
- የያሬድ ዘሪሁን አሰቃቂ ድርጊት በፍርድ ቤት ተነገረ
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ያሬድ ዘሪሁን፣ በተጠረጠሩበት ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በዜጎች ላይ ፈጽመውታል የተባለ አሰቃቂ ድርጊት በፍርድ ቤት ተነገረ።
አቶ ያሬድ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ማክበርና ማስከበር ሲገባቸውና ሕዝብ እንዲያገለግሉ የተሰጣቸውን ሥልጣን ወደ ጎን በመተው፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ከነበሩት አለቃቸው አቶ ጌታቸው አሰፋ የሚቀበሉትን ትዕዛዝ ለበታቾቻቸው ኃላፊዎችና ሠራተኞች በማስተላለፍ፣ ዘግናኝና ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውንና እንዲፈጸም ማድረጋቸውን የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ መርማሪ ቡድን፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ቅድመ ምርመራ ያስረዳል።
ተጠርጣሪው በርካቶች የግንቦት ሰባትና የኦነግ አባል እንደሆኑና በሽብርተኝነት እንዲጠረጠሩ እንዲታፈኑ ማድረጋቸውን፣ መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። የታፈኑ ዜጎች የታሰሩበትን ቦታ እንዳያውቁ ዓይናቸውን በጨርቅ በማሰር ወደ ሥውር የማሰሪያ ቦታ በመውሰድ፣ ከአምስት ወራት በላይ ታፍነው እንዲቆዩ ማድረጋቸውንም አክሏል። በርካታ ዜጎች ታፍነው በተሰወሩበት ቦታ ከባድ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው፣ በካቴና በታሰሩ እጆቻቸውና እግሮቻቸው መካከል እንጨት በማስገባት ተሰቅለው እንዲደበደቡ፣ በኤሌክትሪክ በማንዘር (ሾክ በማድረግ)፣ በመግረፍ፣ ብልታቸው በፒንሳ እንዲጎተትና እንዲተለተል በማድረግ፣ ራቁታቸውን በቆሻሻ ቦታ በማቆየት፣ በጉንዳን እንዲበሉና ራቁታቸውን ጫካ ውስጥ እንዲጣሉ በማድረግ ከባድና ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውንም መርማሪ ቡድኑ ገልጿል።
አቶ ያሬድ የተጠርጣሪ ቤተሰቦችን በማገትና መያዣ በማድረግ ልጆቻቸውና ወገኖቻቸው ወደ ኤርትራ እንዲሄዱ ካደረጉ በኋላ፣ ድንበር ላይ በፀጥታ ሰዎች እንዲያዙ በማድረግ በሽብርተኝነት ከተፈረጀ ድርጅት ጋር ሊቀላቀሉ ሲሄዱ እንደተያዙ በማስመሰል ሐሰተኛ ክስ እንዲመሠረትባቸው ያደርጉ እንደነበርም በምርመራ መታወቁ ተገልጿል። በዚህ ድርጊታቸውም ሌሎች ዜጎች እንዲሸበሩና ተረጋግተው እንዳይኖሩ በማድረጋቸው፣ ከባድና ጭካኔ የተመላበት ኢሰብዓዊ ድርጊት በመፈጸም ወንጀል መጠርጠራቸውን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
ተጠርጣሪው ለረዥም ጊዜያት የሕግ አስፈጻሚ ሆነው ሲሠሩ ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጭ እንዲወጡ በከፍተኛ ገንዘብ በመደራደርና ያልተገባ ጥቅም በማግኘት፣ ያልተገባ ሀብት ማከማቸታቸውንና ሕዝብን ለማገልገል የተሰጣቸውን ሥልጣን ያላግባብ በመጠቀም የሙስና ወንጀልም መጠርጠራቸውን መርማሪ ቡድኑ አስታውቋል። አቶ ያሬድ በሕግ እንደሚፈለጉ እያወቁ በአግባቡ ቀርበው ለሌላው አርዓያ መሆን ሲገባቸው፣ ከጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በመሰወራቸው በፀጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ክትትል ረቡዕ ኅዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ከምሽቱ አምስት ሰዓት በኦሮሚያ ክልል ዱከም አካባቢ በአንድ ሆቴል ውስጥ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውም ተገልጿል። ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር አለማዋላቸውን ያወቁ ተጎጂዎች ወይም የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባቸው ዜጎች ፍርኃቱ ስላልለቀቃቸው የምስክርነት ቃላቸውን መቀበል አለመቻሉን፣ የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት መርማሪ ቡድኑ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። ፍርድ ቤቱ አቶ ያሬድ ፈጽመውታል የተባለው የወንጀል ድርጊት ግልጽ መሆን አለመሆኑን ጠይቋቸው ግልጽ መሆኑን ተናግረዋል። ለቀረበባቸው አቤቱታ ምላሽ የሚሰጡት በራሳቸው ወይም በሕግ ባለሙያ ታግዘው ስለመሆኑ ተጠይቀው፣ በችሎት የተገኙ ቤተሰቦቻቸውን ጠይቀው በሕግ ባለሙያ ለመታገዝ መልስ እንደሚሰጡም ተናግረዋል። ፍርድ ቤቱም የእሳቸውን ክርክር በመስማት ለማክሰኞ ኅዳር 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።
አቶ ያሬድን ደብቀው እንዲሰወሩ (እንዲጠፉ) አድርገዋል ተብለው ተጠርጥረው የተያዙት የንስሐ አባታቸው አባ ሀብተ ማርያም ኃይለ ሚካኤልና የአቶ ያሬድ ሾፌር ነው የተባለው አቶ አሸናፊ ታደሰ፣ ኅዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበዋል። የንስሐ አባት መሆናቸውን ያረጋገጡት መነኩሴው፣ የንስሐ አባት ያደረጓቸው የአቶ ያሬድ ባለቤት መሆናቸውንና አቶ ያሬድን የሚያውቋቸው በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም. መሆኑንም ለፍርድ ቤት ተናግረዋል። በተጨማሪም ሁለቱንም ወደ ግሸን ይዘዋቸው መሄዳቸውን፣ አቶ ያሬድ ግን “መንግሥት ፈልጎኛል” በማለት ከኮምቦልቻ ከመመለሳቸው ውጪ ምንም የማያውቁ መሆኑን ለፍርድ አስረድተዋል። የተናገሩት እውነት ስለመሆኑም በራሳቸው መስቀልና በመጽሐፍ ቅዱስ መማል እንደሚችሉም ተናግረዋል። አቶ ያሬድ ወንድሞችና እህቶች እያሏቸው ለእሳቸው ሚስጥር ሊነግሯቸው እንደማይችሉ ተናግረው፣ ስለእሳቸው የተባለው ሁሉ ሐሰት መሆኑንና እሳቸው ቤተ ክርስቲያንና ገዳማትን ከማሠራት ውጪ ሌላ ነገር እንደማያውቁም አክለዋል። እሳቸው የሚጠብቋቸው ሦስት ሕፃናት እንዳሉ በመጠቆም፣ ፍርድ ቤቱ ዋስትና ፈቅዶላቸው እንዲወጡና ባዘዛቸው ጊዜ እንደሚቀርቡ በመግለጽ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። አብሯቸው የታሰረውና የአቶ ያሬድ ሾፌር ነው የተባለው አቶ አሸናፊም የእሳቸው ረዳት እንጂ ሾፌር አለመሆኑን አስረድተዋል። አቶ አሸናፊም እሳቸው ያሉትን በማረጋገጥ ዋስትና እንዲከበርለት ጠይቋል።
መርማሪ ቡድኑ ግን ዋስትናውን ተቃውሟል። ምክንያቱ ደግሞ ዋናው ተጠርጣሪ አቶ ያሬድ አለመያዛቸውን፣ የደበቁዋቸው ሰነዶችና ያጠፉትም ሰነድ ስላለ መረጃ ሊደብቁና ለተጠርጣሪውም መረጃ በመንገር ሊያሸሹ ስለሚችሉ መሆኑን አስረድቷል።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ፖሊስ አቶ ያሬድን ባለመያዙ ተጠርጣሪ መያዣ መሆን እንደሌለባቸው ለመርማሪ ቡድኑ በመንገር፣ ሰነዶችን በሚመለከት ግን ፍርድ ቤቱ ተገቢ ሆኖ ማግኘቱን በመግለጽ ከተጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ አሥር ቀናት ፈቅዷል። አቶ ያሬድ ኅዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ሌሊት 5፡00 ሰዓት አካባቢ በቁጥጥር ሥር በመዋላቸው፣ መርማሪ ቡድኑ መነኩሴውንና ሾፌር ነው የተባለውን ግለሰብ ሊለቃቸው እንደሚችል እየተነገረ ነው።
ሌላው ባለፈው ሳምንት ኅዳር 4 ቀን 2011 ዓ.ም. በሑመራ በኩል ወደ ሱዳን ሊወጡ ሲሉ በትግራይ ክልል ልዩ ኃይል በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም፣ በቀረበባቸው የወንጀል ድርጊት ላይ ክርክር አላደረጉም። ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ኅዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ተገልጾላቸዋል። ጄኔራሉ ከሰኔ 2 ቀን 2002 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. መጨረሻ ወር ድረስ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲሠሩ እንደነበር የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ቅድመ ምርመራ ያሳያል። መርማሪ ቡድኑ እንዳስረዳው በተለይ ከ2004 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ በኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ የውጭና የአገር ውስጥ ግዥ በእሳቸው ትዕዛዝ መፈጸሙን ጠቁሞ፣ ግዥዎቹ የተፈጸሙት ግን የኮርፖሬሽኑን የግዥ መመርያ ወደ ጎን በመተው ያለምንም ጨረታ መሆኑን አክሏል። ግዥዎች ሕግን መሠረት አድርገው መፈጸም ሲገባቸው፣ ሕዝብን ሊጠቅሙ የሚችሉ ትልልቅ ግንባታዎች፣ ማለትም የህዳሴ ግድብ፣ የህዳሴ ግድብ ደን ምንጣሮ፣ የስኳር ፋብሪካ ግንባታዎች፣ የተለያዩ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታዎችና ሌሎች የኢንዱስትሪ ሥራዎችን ማሠራት የሚችል በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከተለያዩ የፕሮጀክቶቹ ባለቤቶች ጋር ውል መፈራረማቸውን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል። ነገር ግን ተጠርጣሪው በገቡት ውል መሠረት ወይም በተቀበሉት ክፍያ ልክ በአግባቡና በገቡት ውል መሠረት አለመፈጸማቸውንም አብራርቷል። የመንግሥትና የሕዝብ ኃላፊነትን ወደ ጎን በመተው፣ ሕግን በመተላለፍ፣ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ኮንትራቶችንና ግዥዎችን ያለምንም ጨረታ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለቅርብ ጓደኞቻቸውና ሌሎች የውጭ ድርጅቶችን ለመጥቅምና ለመጠቀም በማሰብ፣ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም በርካታ የሕዝብ ገንዘብ እንዲዘረፍና እንዲባክን ማድረጋቸውንም መርማሪ ቡድኑ ተናግሯል። በከባድ የሙስና ወንጀል እንደሚጠረጠሩ እያወቁም ከአገር ሊወጡ በሑመራ በኩል ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም አክሏል። በመሆኑም ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል።
መርማሪ ቡድኑ ጄኔራሉ ስለተጠረጠሩበት ጉዳይ ለፍርድ ቤቱ ካስረዳ በኋላ ዋና ዳይሬክተሩ ክርክሩን እንዴት እንደሚቀጥሉ፣ ማለትም በራሳቸው ወይም በሕግ ባለሙያ ተደግፈው ስለመሆናቸው በፍርድ ቤቱ ተጠይቀው፣ ሙያው ስለሌላቸው በሕግ ባለሙያ ተደግፈው መከራከር እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። በመቀጠልም ሀብት ንብረት እንደሌላቸው፣ ያላቸው የወር ደመወዝ 4,000 ብር ብቻ መሆኑን በመግለጽ መንግሥት የሕግ ባለሙያ እንዲያቆምላቸው ጠይቀዋል። መርማሪ ቡድኑ ሀብት እንዳላቸው ጠቁሞ ቢቃወምም፣ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል። በመሆኑም ምንም ዓይነት ሀብትና ንብረት እንደሌላቸው በመግለጽ መጽሐፍ ቅዱስ በመያዝ መሃላ ፈጽመዋል። ፍርድ ቤቱም የጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከላካይ ጠበቆች ጽሕፈት ቤት ተከላካይ ጠበቃ እንዲመድብላቸው ትዕዛዝ በመስጠት ለሐሙስ ኅዳር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዳር ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።
ኅዳር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ሁለት ተከላካይ ጠበቆች የተመደቡላቸው ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ለክርክር ተዘጋጅተው የቀረቡ ቢሆንም፣ መርማሪ ቡድኑ ግን ሀብት እንዳላቸው፣ የፀረ ሙስና የሀብት ምዝገባ ሰነድ ይዞ በመቅረብ ተቃውሞ አቅርቧል። በሰነዱ ላይ የተመዘገበው 5,333 ብር፣ 80,000 ብር ግምት ያለው ተሽከርካሪና ቢሾፍቱ የሚገኝ መኖሪያ ቤት መሆኑንም አስረድቷል። ገንዘብ ወጪ ያደረጉበትን የባንክ ሰነድም አያይዞ አቅርቧል። ፍርድ ቤቱ ሰነዱን ከተመለከተ በኋላ ጄኔራሉ እንዲያረጋግጡ ሰጥቷቸው ከተመለከቱት በኋላ፣ “እኔ ያስመዘገብኩት 5,000 ብር ብቻ ነው፣ ቤት የለኝም። ከተገኘብኝ ይወረስ። በባንክም ያለኝ ገንዘብ 2,500 ብር ብቻ ነው። የእኔ ሀብት ሰውነቴ ብቻ ነው (በእጃቸው አካላቸውን እየነኩ) የተመዘገበው ሀብት የእኔ አይደለም፤” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
ፍርድ ቤቱ ለደቂቃዎች ከተወያየ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ፣ ምንም እንኳን በፀረ ሙስና ኮሚሽን የተመዘገበው ሀብት የእሳቸው መሆኑን ባያረጋግጡም፣ በ15 ቀናት ውስጥ ከባንክ 100 ሺሕ ብር ወጪ ማድረጋቸውን ሰነድ ስለሚያሳይ፣ በእነዚህ ቀናት ውስጥ ፍርድ ቤቱ ገንዘቡ ያልቃል የሚል ግምት ስለሌለው፣ በራሳቸው የሕግ ባለሙያ ቀጥረው እንዲከራከሩ ብሏል። ኅዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ተከላካይ ጠበቃ እንዲመደብላቸው የሰጠውን ትዕዛዝም አንስቷል። በመቀጠልም ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ተጠይቀው፣ “ዘመዶቼ ካቆሙልኝ ልመካከር፤” በማለታቸው፣ በችሎት ከተገኙ ዘመዶቻቸው ጋር ለደቂቃዎች እንዲነጋገሩ ተፈቅዶላቸዋል። ከተነጋገሩም በኋላ እስከ ማክሰኞ ኅዳር 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ማግኘት እንደሚችሉ አስረድተው ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል።
በእሳቸው የምርመራ መዝገብ የተካተቱት ወድማቸው አቶ ኢሳያስ ዳኘውም የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ኦፕሬሽን ኃላፊ ሆነው ሲሠሩ፣ ከወንድማቸው ጋር በመመሳጠር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለኮርፖሬሽኑ እንዲሰጥ በማድረግ ከፍተኛ የሕዝብ ገንዘብ ብክነት እንዲደርስ ማድረጋቸውንና ተገቢ ያልሆነ ሀብት ማፍራታቸውን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል። ለተጨማሪ ምርመራም 14 ቀናት እንዲፈቀድለትም አመልክቷል።
ተጠርጣሪው ፈጸሙ የተባለው ወንጀል ከተነገራቸው በኋላ እንዴት ክርክር እንደሚያደርጉ ተጠይቀው፣ ምንም ሀብትም ሆነ ንብረት እንደሌላቸው በመግለጽ፣ መንግሥት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ጠይቀዋል። መርማሪ ቡድኑ የእሳቸውንም ተቃውሞ ነበር። ፍርድ ቤቱ ስላላቸው ቋሚ ንብረት ጠይቋቸውም፣ “ምንም ነገር የለኝም፤” ብለዋል። የመንግሥት ሠራተኛና የቤተሰብ ኃላፊ መሆናቸውን ሲያስረዱ፣ ደመወዛቸውን ፍርድ ቤቱ ጠይቋቸው፣ “አላውቀውም” ካሉ በኋላ፣ ትንሽ አስበው “8,000 ብር ይሆናል” ብለዋል። ፍርድ ቤቱ የግለሰቡ ሀብት መኖር አለመኖር ወደፊት ታይቶና ተጣርቶ የሚወሰን መሆኑን በማስታወቅ፣ የመርማሪ ቡድኑን ተቃውሞ ውድቅ በማድረግ ቃለ መሃላ እንዲፈጽሙ አድርጓል። ተከላካይ ጠበቃ ለኅዳር 10 ቀን 2011 ዓ.ም. እንዲቀርብላቸውም ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ከሜቴክ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ከቀረቡት መሃል ተማሪ መሆኗን ለችሎቱ የገለጸችው ወ/ሪት ትዕግሥት ታደሰ፣ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የተለያዩ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ሠራተኛ ወ/ሮ ፍፁም የሺጥላና በድለላ ሥራ ላይ መሆኑ የተገለጸው አቶ ቸርነት ዳና ናቸው።
ወ/ሪት ትዕግሥት በሕግ መፈለጉን እያወቀ ተሰውሯል ከተባለው በሜቴክ የኅብረት ማኑፋክቸሪንግ ግንባታ ኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጅ ጋር፣ የጥቅም ተባባሪ መሆኗን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል። ተፈላጊ ተጠርጣሪ የመንግሥት ሠራተኛ መሆኑን እያወቀች ከደመወዙ በላይ በሆነ ገንዘብ መኖሪያ ቤት፣ ተሽከርካሪና ሌሎች ጥቅማ ጥቅም በስሟ ማግኘቷንም መርማሪ ቡድኑ ገልጿል። ገንዘቡ የሕዝብ መሆኑንና ለሕዝብ ፕሮጀክት የሚውል እንደነበርም አክሏል።
ወ/ሮ ፍፁም የሺጥላ ደግሞ፣ “ፍፁም ኢንተርቴይመንት” በሚባል ድርጅት ከሜቴክ ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር ለሕዝብ ፕሮጀክት ከተመደበ ገንዘብ ላይ 954,770 ብር ድጋፍ ተደርጎላት ጥቅም ማግኘቷንና በሕዝብ ገንዘብ ላይ ጉዳት ማድረሷን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል። ሁለቱ ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበት ወንጀል ከተነገራቸው በኋላ፣ ክርክሩን እንዴት እንደሚቀጥሉ ተጠይቀው ምንም ዓይነት ሀብትም ሆነ ንብረት እንደሌላቸው ለፍርድ ቤቱ በመግለጽ መንግሥት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ጠይቀዋል። ሁለቱም ቃለ መሃላ እንዲፈጽሙ ተደርገው የተከላካይ ጠበቃ ጽሕፈት ቤት ጠበቃ እንዲሰየምላቸው በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ተመድቦላቸዋል።
የተመደቡላቸው ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ተጠርጣሪዎቹ የተጠረጠሩበት ወንጀል ዋስትና እንደማይከላከል፣ ተጨባጭ የሆነና የወንጀል ፍሬ የሌለው ጥርጣሬ በመሆኑ፣ የዋስ መብታቸው ተጠብቆላቸው በውጪ ሆነው እንዲከራከሩ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። ወ/ሪት ትዕግሥት ተማሪ መሆኗን ለፍርድ ቤቱ ገልጻ፣ የፈተና ወቅት በመሆኑ መፈተን እንድትችል ለፍርድ ቤቱ አመልክታለች። መርማሪ ቡድኑ ግን ገና የሚያጣራው ምርመራ እንዳለውና ተባባሪያቸውንም መያዝ እንደሚቀረው በማስረዳት፣ ዋስትናውን ተቃውሞ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት ጠይቋል። ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፣ መርማሪ ቡድኑ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ አሥር ቀናት በመፍቀድ ለኅዳር 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል። ወ/ሪት ትዕግሥት የመፈተኛ ፕሮግራሟን በማመልከቻ ስታሳውቅ እንደሚፈቀድላት ተነግሯታል።
ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ሌሎች ሁለት ግለሰቦችም ታስረው ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ተጠርጣሪዎቹ ሳጅን ኪዳኔ አሰፋና አቶ ሳሙኤል ጊዴሳ ናቸው። ሳጅን ኪዳኔ ኦነግና የግንቦት ሰባት አባላት ናቸው ተብለው በሕገወጥ መንገድ ታፍነውና ዓይናቸውን ታስረው ሥውር እስር ቤት ገብተው የነበሩ በርካታ ዜጎችን በመግረፍ፣ በመደብደብና የተለያዩ ሥቃዮችን በማድረስ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤት አስረድቷል።
አቶ ሳሙኤል የተባለው ተጠርጣሪ ደግሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አባል የነበረ መሆኑን መርማሪ ቡድኑ ጠቁሞ፣ እሱም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከውጭ በር ላይ አፍኖና ዓይናቸውን አስሮ በመውሰድ ከአምስት ወራት በላይ በማቆየት ከፍተኛ የሆነ ድብደባና ሥቃይ በማድረስ፣ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን አስረድቷል። ግለሰቡ ሰበታ አካባቢ የሚገኙ ባለሀብቶችንና ነዋሪዎችን “ደኅንነት ነኝ” በማለት፣ በማስፈራራትና በሐሰት ማስረጃ እንዲታሰሩ በማድረግ ተገቢ ያልሆነ ሀብት መሰብሰቡንም መርማሪ ቡድኑ ተናግሯል።
ተጠርጣሪዎቹ ፈጽመዋል የተባለው የወንጀል ድርጊት ከተገለጸላቸው በኋላ ሀብት ንብረት እንደሌላቸው በመሃላ በማረጋገጣቸው፣ ተከላካይ ጠበቃ ተመድቦላቸዋል። የቆሙላቸው ጠበቆች ግለሰቦቹ ላይ የቀረበው ክስ ዋስትና እንደማይከለክል ገልጸው፣ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ቢጠይቁም መርማሪ ቡድኑ ተቃውሟል። ፍርድ ቤቱ ክርክሩን ከሰማ በኋላ ዋስትናውን ውደቅ በማድረግ ፖሊስ የጠየቀውን 14 ቀናት በመፍቀድ ለኅዳር 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ሌላው በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው በሜቴክ ሥር የሚገኘው የፓወር ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጅ ኮሎኔል አሰፋ ዮሐንስ ናቸው። ኮሎኔሉ የሜቴክ ሠራተኛ እንደነበሩ መርማሪ ቡድኑ ጠቁሞ፣ ወደ ፓወር ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ሲቀየሩ የጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካን ለማስገንባት ከአንድ የቻይና ኩባንያ ጋር የ55,640,000 ዶላር ውል በመፈጸም፣ ኩባንያው ሥራውን ሳይሠራ ከአገር ሲወጣ ዝም ማለታቸውን አስረድቷል። በሌላ በኩል ከሌላ ኩባንያ ጋር ደግሞ የ6,400,000 ዶላር ውል ፈጽመው ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ከተከፈለው በኋላ፣ ሥራ ሳይሠራ ከአገር ሲወጣ ዝም ማለታቸውንና አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ችግር እንዳለባት እያወቁ ገንዘብ እንዲሸሽ ማድረጋቸውን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል።
ተጠርጣሪው የሕግ ዕውቀት እንደሌላቸው ተናግረው ደመወዛቸው 8,000 ብር እንደሆነና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን፣ በስማቸውም ሌላ ምንም ቋሚ ንብረት እንደሌላቸው ተናግረው፣ መንግሥት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው በመሃላ አረጋግጠው ጠይቀዋል። ፍርድ ቤቱም ተከላካይ ጠበቃ እንዲቆምላቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል።
መርማሪ ቡድኑ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባልደረባ የነበሩትን አቶ ተስፋዬ ኡርጌና ሌሎች ሁለት ተጠርጣሪዎች ኮሎኔል ጉደታ ኦላናና ኮሎኔል ሰጠኝ ካሳዬ የተባሉ ግለሰቦችን መርማሪ ቡድኑ አስሮ ያቀረባቸው ቢሆንም፣ ለችሎቱ የቀረበው አቤቱታ የወጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግን የተከተለ ባለመሆኑ፣ ተስተካክሎ ለሰኞ ኅዳር 10 ቀን 2011 ዓ.ም. እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል። አቶ ተስፋዬ ኡርጌ በሰኔ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. የቦምብ ጥቃት ተጠርጥረው ከታሰሩ አምስት ወራት ሆኗቸዋል።
ሰሞኑን ከኅዳር 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥጥር ሥር የዋሉና በመፈለግ ላይ የሚገኙ 96 ተጠርጣሪዎችና ቤተሰቦቻቸው የባንክ ሒሳብ፣ ንብረትና ድርጅቶቻቸው እንዳይሸጡ፣ እንዳይለወጡና ለሦስተኛ ወገን እንዳይዘዋወሩ በፍርድ ቤት ዕግድ ተጣለባቸው።
ዕግድ ከተጣለለባቸው ተጠርጣሪዎች መካከል የሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘና ቤተሰቦቻቸው፣ የብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁርንዲና ቤተሰቦቻቸው፣ የብርጋዴር ጄኔራል ጥጋቡ ፈትለ፣ የአቶ ጌታቸው አሰፋና ልጃቸው፣ የሀሺም ቶፊቅ (ዶ/ር)፣ የአቶ ያሬድ ዘሪሁንና የ14 ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ በአጠቃላይ የ192 ሰዎች የባንክ ሒሳብ፣ ተንቀሳቃሽና ቋሚ ንብረት፣ እንዲሁም 13 ድርጅቶች እንዳይሸጡ፣ እንዳይለወጡና ለሦስተኛ ወገን እንዳይተላለፉ ዕግድ ተጥሎባቸዋል። (ይህ ዜና ሪፖርተር ላይ ሲወጣ የተሰጠው ርዕስ “በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩት የአገር ውስጥ ደኅንነት ዋና ኃላፊ አሰቃቂ ድርጊት በፍርድ ቤት ተነገረ” የሚል ነበር)
Wassie Haile says
በእኔ እምነት ፈጣሪ የኢትዮጵያ ሕዝብ መከራ ለአንዳና ለመጨረሻ ጊዜ ያበቃ ዘንድ እና በቃሉ መሰረት ኢትዮጵያን ከእንግዲህ እስከ ዘላለሙ ሊባርካት በመወሰኑ በክቡር ጠ/ሚ ዶ/ር አብይና በክቡር ዶ/ር ለማ መገርሳ ተመስሎ መጥቷል።