ሌባዬ. . .
ድምጹ ሳይሰማ ኮቴውን አጠፍቶ
በጠራራ ፀሐይ የደጄን በር ከፍቶ
መዝለቅ የጀመረው ክርችም በሬን ከፍቶ
ምን ሊዘርፈኝ ይሆን በምኔ ጎምጅቶ?
በማለት ኖላዊት ሽመልስ ስትጠይቅ የሚከተሉት መልሶች ተሰጥተዋታል፡፡
(ምልልሱን ያገኘነው ከፌስቡከ ሲሆን እርስዎም የሃሳብ በመስጫውን በመጠቀም ምላሽዎን እንዲሰጡ እንጋብዝዎታለን፡፡)
*************************************************************************************
ጠንቀቅ
አለሽ ንብረት አለሽ
አንቺዬ ሃብት አለሽ
ገንዘብ የማይገዛው
ለራስሽ ያልታየሽ
እጅግ የበለጠ
ከወርቅ፤ አልማዝ፤ ከእንቁ
አድፍጦ ሊዘርፍሽ
ያመጣው ከሩቁ
እመኚኝ ሃብት አለሽ
ዘብ የሚያስፈልገው
ብቻ ችላ ብለሽ እንዳታሰርቂው፡፡
(ብሌን ከበደ)
***************************************************************************************
በጠራራው ፀሀይ ሊዘርፍሽ የመጣ
ምን ዓይነት ደፋር ነው ምን ዓይነት ፈጣጣ!
በይ ጠንቀቅ ብለሽ ልብሶችሽን ሳይሆን ልብሽን ጠብቂ
ወርቁም ጌጡም ያለው እዚያው ነው እወቂ
እኔ ነግሬአለሁ ኋላ ተጠንቀቂ!
(ሁዳድ ንጉሤ)
**************************************************************************************
የተረፈችውን ስንቴ ተቆንጥራ
እንዳታልቅ ስሰስት ስተባ ስፈራ
ልቡን አደንድኖ ለልቤ ሳይራራ
ሊዘርፍ ይሄ ደፋር መጣ በጠራራ
(ቡቲካ ሽመልስ)
**************************************************************************************
ምን አይነት ደፋር ነው
shame እንኳን የሌለው
ሌባን ሌባ መስረቁ
ነበረ የሱስ ድፍረት
ይሄን ጠንቅቆ አለማወቁ
ቅኔ ምትደረድሪ
እንደሆንሽ ዘራፊ
ይህን አላውቀ የሌባ ጀማሪ
ሊዘርፍሽ የመጣው
እልም ያልሽ ዘራፊ
መሆንሽን አረ ማን ይንገረው?
(ኤልሳ ተገኔ)
**************************************************************************************
ቶማስ ለማ ለቡቲካ ሲመልስ፡-
ባጉል ቀን ተለክፎ
አካላቱ ዝሎ ፣ ሰዉነቱ ሰንፎ
የጣለዉን ዕቃ
ሊፈልግ ቢመጣ
አወይ “ያንች ነገር” ሌባ አስባለው በቃ
************************
አበባሽን ይዘሽ ፣ በቀን ስትዞሪ
ቢመጣ በቀፎሽ ፣ ንብ ሆኖ ማር ሰሪ
እንጀራ ጋጋሪ
ሌባ ማለት ትተሽ ፣ ጓዳዉን መርምሪ
በጎድኑ ግቢ ፣ በክፍተቱ ቅሪ
በቀን የሚገኝ ነው ፣ ፍቅር እዉነትን አብሪ
(ዘገብረየሱስ መስከረም 2004)
(ምልልሱን ያገኘነው ከፌስቡከ ሲሆን እርስዎም የሃሳብ በመስጫውን በመጠቀም ምላሽዎን እንዲሰጡ እንጋብዝዎታለን፤ ታዲያ በግጥም መሆኑን አይዘንጉ፡፡)
እሺ እንዲህ እንበል እሱማ ተሳስቶል
ንብረት ያለሽ መስሎት ሊዘርፍሽ ከጅሎል
እጅግ የሚገርመዉ ያንቺ መደንገጥ ነዉ
ንብረት እንደሌለሽ ልብሽ እያወቀዉ
Anchim minim yelesh-Lesum kentu lifat
Berishin kerchimesh-Lik ende balehabt
Layagegn layzerfish- Kenu alefebet!!!
አንቺም ምንም የለሽ – ለሱም ከንቱ ልፋት
በርሽን ከርችመሽ – ልክ እንደባለሃብት
ላያገኝ ላይዘርፍሽ – ቀኑ አለፈበት፡፡
የቆለፍኩትን በር ይበርግደዉ ይግባ
ለማግኘት ከቻለ አንዳች የሚረባ
እስኪ ቆዩኝማ ምን ይሁን ብይ ነው በሬን የከረቸምኩ
አልማዝ እንደሸሸግኩ ወርቁን እንደደበቅኩ?
የቤቱ ባዶነት ልቤ እያወቀዉ ለካስ በከንቱ ነዉ በቴን የከረቸምኩ
ሥረቃት! ስረቃት!
በጎን የምትወጂው
እስከሆነ ድረስ
ቢጎተት ?!
ቢመለስ ?!
ያሻውን ቢቆምጥ?!
ከሌባሽ ሌብነት
ተማርከሽለታል
ተሰርቀሽለታል
በጠፍ በጨረቃ
“ይዘኸኝ ሂድ” አይነት
አቆላምጠሸ ጠርተሸ
ሌባሽ ከሆነልሽ
አንቺን የሚከፋሽ
ባይሰርቅሽ እንደሆን ልቤ ጠርጥሮታል
ሂድ!? በሚለው ቃልሽ ናልኝ ብሰሺዋል
ሌባዋ ሂድላት
ስረቃት! ስረቃት!
(አበበ አዲስ)