- ዳንኤል ሺበሺ ከወህኒ ያስተላለፈው መልእክት
ከቤተሰቡ በተገኘው መረጃ መሰረት ዳንኤል የተወለደው በደቡብ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ያደገው እንደአብዛኛው ኢትዮጵያዊ በለምለሟ ቁጫ ወረዳ አረንጓዴ መስክ ሮጦና ተራራና አቀበት ወጥቶ ነው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ንቁ ነበርና ቤተሰቡ ወደ ትምህርት ቤት ሰደደው፡፡ ተማረ፡፡ እስከ ዩኒቨርስቲ በመዝለቅም ቀጠለ፡፡ ከዚያም ሳይማር ወዳስተማረው ህብረተሰብ በመመለስ ማገልገሉን ተያያዘው፡፡ ግና ትምህርት የአለማችንን ተጨባጭ ሁኔታ እንዲለይ አስችሎት ነበርና በሚሰራው ስራ ብቻ ሊረካ አልቻለም፡፡ ህዝቡ ላይ የማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና የማህበራዊ ፍትህ እጦት እንደሚያሰቃየው ተመለከተ፡፡
ወጣቱ ዳኒ በተደጋጋሚ እንደሚናገረው ‹‹ህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለውን በደልና ግፍ ከንፈር በመምጠጥ ብቻ ማቆም እንደማይቻል አውቅ ነበር፡፡ እንደ አንድ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ምን ማድረግ እንዳለብኝ እጨነቅ ነበር፡፡ ወቅቱ ደግሞ ደርግ ወድቆ፣ ኢህአዴግ ስልጣን ይዞ የሚንደፋደፍበት ስለነበር ሁኔታዎች ወዴት ሊያመሩ እንደሚችሉ ለመገመት ሁሉ አይቻልም ነበር›› ይላል፡፡
ነገር ግን ‹‹ነፃ አውጭዎቹ›› ስልጣንና ሀብትን በሚለማመዱበት በዚያ ጊዜ መራራ ትግል ያካሄዱት በደርግ አገዛዝ መከራ የሚበላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃ ለማውጣት እንደሆነ በመስበካቸውና ከመንገድ ስለተቀበሉት ዴሞክራሲ በማውራታቸው ‹‹እስኪ እንያቸው!›› የሚል ስሜት መፈጠሩ አልቀረም፡፡ ይሄ ስሜትም ወጣቱ ዳንኤል ሺበሺ ላይ በማደሩ የኢህአዴግን ሁኔታ በአንክሮ ይከታተል እንደነበር ተናግሯል፡፡ በመቀጠልም ከታጋዮቹ ሌላ ጥሪ መጣለት ‹‹እናንተ ወጣቶች እኮ ዴሞክራሲያዊ ስርኣት ለመገንባት የምናደርገውን ትግል ብትደግፉን ይችን ሀገር መቀየር እንችላለን!›› የሚል ነበር፡፡
ዳንኤል ከዚህ በፊት በተለያዩ መድረኮች ይናገር እንደነበረው ‹‹ብታግዙን ጥሩ ነው›› የሚለውን ሀሳብ በወቅቱ ብዙ ወጣቶች በቀናነት በመውሰድ ‹‹ለሀገራችን መስራት ከቻልን ብናግዛቸው ጥሩ ነው›› በሚል ኢህአዴግን ተቀላቀሉ፡፡ ዳንኤል ሺበሺም በደኢህዴን በኩል የኢህአዴግ አባል ሆነ፡፡ አቶ ሃይለማሪያምን ጨምሮ ከአሁን አሳሪዎቹ ጋርም አብሮ ሰራ፡፡ የተባለው ዴሞክራሲ የማስፈን ነገር ከልብ አይደለምና ልዩነቶች እየተፈጠሩ መጡ፡፡ ዳንኤልና ሌሎች አንዳንድ ወጣቶች የምንላችሁን ብቻ ተቀበሉ፤ የምንላችሁን ብቻ ስሩ . . . የሚለው የህወሃት/ኢህአዴግ ትዕዛዝ መጀመሪያ ከተባሉት ጋር የሚጋጭ ነበርና የመርህ ጥያቄ ማንሳት ጀመሩ፡፡ የውስጥ ትግልም አደረጉ፡፡ ከኢህአዴግ ጋር ለመስራት ያደረገው ሙከራም ብዙ ርቀት ሳይሄድ በአጭሩ ተቀጨ፡፡ የስርዓቱን ውስጣዊ አፋኝ አሰራር ያየው ዳንኤልም በአደባባይ እንደማይጠቅም በመናገር በሰላማዊ መንገድ ለማስወገድ የሚደረገውን ትግል ተቀላቀለ፡፡
ዳንኤል ሺበሺ የኢዴፓ አባል የነበረ ሲሆን ቅንጅት ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ካደረጉና እስካሁን ድረስ የሚያሰቃይ ድብደባ ከደረሰባቸው ወጣቶች አንዱ ነው፡፡ የአንድነት ፓርቲ መስራችና የደቡብ ቀጠና ኃላፊ በመሆን ከተመሰረተ ጀምሮ የሰራ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ የድርጅት ጉዳይ ምክትል ኃላፊ በመሆን በትጋት የሚታገል የዴሞክራሲ አርበኛ ነው፡፡ ዳኒ ባለትዳርም ነው፡፡ የሚያምንበትን ፊት ለፊት የሚናገር፤ ደፋር ነገርግን ፈገግታ የማይለየው ዳኒ በትግል አጋሮቹ ዘንድ (ዳኒ ደቡብ) በመባል በቁልምጫ ይጠራል፡፡ ዳኒ ደቡብ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የሚፈፀሙ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶችን በማጋለጥ ይታወቃል፡፡ በቅርቡ ደግሞ የመብት ጥያቄ ባነሳው የቁጫ ህዝብ ላይ የተወሰደውን የጅምላ እስር በማውገዝ ያጋለጠና ይህንንም በተለያዩ ሚዲያዎች ይፋ ያደረገ እንዲሁም ለሚታገሉ ሁሉ መልካም አርአያ ሊሆን የሚችል ወጣት ነው፡፡
በዚህ አስከፊ ስርዓት ጥርስ የተነከሰበት ዳኒ ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም አገር አማን ብሎ ወደ ስራ ሲሄድ በፖሊሶች ተከቦ በካቴና ከታሰረ በኋላ ቤቱ ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2፡00 ሰዓት ተፈትሾ ወደ ማሰቃያው ማዕከላዊ ተወስዷል፡፡ ከሃያ ወር ግፍና እንግልት በኋላ ዳንኤል ሺበሺ ከወህኒ ይለቀቃል። አገዛዙ በርሱ ላይ ላቀረበው የፈጠራ የሽብርተኝነት ክስ ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ።
ብዙም አልቆየም የአገዛዙ ኮማንድ ፖስት እንደገና ወደ ወህኒ አወረደው። ዳኒ በአሁኑ ወቅት ባላጠፋው ጥፋት ፣ ባልሰራው ወንጀል፣ እንደገና አገሩን እና ሕዝቡን በዉደዱ፣ ኢትዮጵያን በመዉደዱ ከሌሎች በመቶ ሺሆች ከሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ጋር በወህኒ እየማቀቀ ነው።
አገዛዙ ዳንኤል ወደ ወህኒ መዉሰድ ብቻ ሳይሆን፣ በወህኒ አንድ እስረኛ ማግኘት የሚገባውን መሰረታዊ መብት ተነፍጎ፣ ከፍተኛ የዉሃ እጥረት ያለበት፣ ቱሃን የበዛበት እሥር ቤት ነው እየተሰቃየ ያለው።
እነ ዳንኤል ሺበሺን በማሰር ግን ህጋዊና ሰላማዊ ትግሉን ማስቆም አይቻልም፡፡ ዛሬ ትግሉ ብዙ አንዷለሞችን፤ ብዙ አናኒያ ሶሪዎችን፤ ብዙ ኤሊያሶች ፣ ብዙ እዮኤሎችን፣ ብዙ ዶ/ር መረራ ጉዲናዎችም፣ ብዙ ዳንኤሎችን፣ ብዙ አስቴሮችን፣ ብዙ ንግስት ይርጋዎችን፣ ብዙ ኮሎኔል ደመቀ ዘዉዴዎችን ያፈራና ትግሉን በቁርጠኝነት የሚቀጥል ነው፡፡ እንደሚባለው ሊነጋ ሲል መጨለሙ አይቀርም፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
የሚሊዮኖች ድምጽ
Leave a Reply