“መዝሙሩማ” መዝሙር ነው – የኅብረ-ዜማ ውጤት፣
ሕዝብን ያስተሳሰረ – የአንድነት ሰንሰለት፤
ከምስራቅ እስከ ምዕራብ – ከደቡብ እስከ ሰሜን…
ተዳርሶ በድንገት፣
በቅብብሎሽ ያስተጋባ – የነጻነት አዝማች ልደት!
ደራሲውም ሕዝብ ነው – መሳሪያውም ባህላዊ፣
ዘረኞችን እሚያሸማቅቅ፣ ግፈኞችን እሚያርበደብድ…
ኃያል ድምፅ ምትሃታዊ!
“መዝሙሩማ” መዝሙር ነው – የብሩህ ዘመን ብስራት፣
በደም ቀለም የተጻፈ! – እሚዘመር በሕዝብ አንደበት!
(ስማ! አቶ “ጌታቸው”!) . . .
ከእንግዲህማ አትልፋ – ዘመንህን በከንቱ አትጨርስ፣
ክፋት ፕሮፓጋንዳህን – እሳት ባገር ከመለኮስ፣
ይልቁንስ ጠጋ በል -“ሕዝበ-መዝሙሩን” በደንብ አጥና፣
ያንተም መፃዒ ዕድል – በሕዝብ ድል እንዲቃና!
እንጂማ!…
መዝሙሩማ ኀብረ-መዝሙር ነው! ሀገር-አድን ታሪክ ሰሪ፣
ጆሮን ሰጥቶ ማዳምጥ ነው፣ ለብሁኅን ድምጽ ጥሪ!!
ጌታቸው አበራ፣ ነሐሴ 2008 ዓ/ም/ኦገስት 2016
(የወያኔው የኮሙዩኒኬሽን ሚ/ር አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በቅርቡ በስሩ የሚያዛቸውን ጋዜጠኞች ሰብስቦ፣ ወያኔ እንደ ግል ንብረቱ በሚቆጣጠረው የሀገር ሚዲያ ያሰራጨውን ጋዜጣዊ መግለጫ ካየሁ (ከሰማሁ?) በኋላ፣ ከልካይ በሌለበት እንደልቡ እየተወራጨ የሚያግተለትላቸውን ቃላት አገጣጥሞ ሃሳቡን ለመረዳት ባብዛኛው ቢያስቸግረኝም፤ በመላ ሃገሪቱ የተቀጣጠለውንና ለነጻነትና ለፍትህ የሚደረገውን የሕዝብ ትግል እንደልማዱ በእብሪትና በንቀት ተሞልቶ “መዝሙር..መዝሙር..” እያለ ሊያላግጥበት ሲሞክር በማጤን፣ ይህች አጭር ግጥም ምላሽ ትሆነው ዘንድ ተጫረች)
Leave a Reply