• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

እነ “ሻኪራ” በአሞራ ገደል

August 19, 2013 07:20 pm by Editor Leave a Comment

የዛሬ ሳምንት ሀዋሳ ነበርኩኝ፡፡ የወትሮዋ ሳቂታዋ ሀዋሳ አልነበረችም፡፡ አኩርፋለች፡፡ ሌላ ችግር ገጥሟት ግን አይደለም፡፡ ክረምቱ ነው ያስኮረፋት፡፡

ዝናቡ፣ ቅዝቃዜውና ደመና የሸፈነው ሰማይ ተጫጭነዋት ነበር፡፡ እንደኔ እንደኔ ሀዋሳ ደርሶ አሞራ ገደልን ሳይጐበኙ መመለስ ካለመሄድ እኩል ነው፡፡ እዚህ ስፍራ ዓሳ እንደጉድ ይበላል፡፡ ያውም ቁጥር – ልክ እንደ ስጋ፡፡ የአሳ ቁርጥ ተመጋቢዎች በእንጨት ግድግዳ በተከበበው ዳስ መሳይ ቤት ውስጥ ግፊያውና መረጋገጡን ተያይዘውታል፡፡ በሀዋሳ ሀይቅ ዳር ባለው በዚህ ስፍራ ሰው ከአንድ ቦታ አሳውን ይገዛና እዛው ዳስ ቤት ውስጥ የአሳውን እሾክ እያስወጣ ቁርጡን በሳህን እየያዘ ማባያውን ለማግኘት ሁለት ጐን ለጐን የተቀመጡ ማባያ አቅራቢዎች ጋር መገናኘት ይጠበቅበታል፡፡ አንዱ “ዳጣ” የተባለው እና ከሚጥሚጣ እንዲሁም ከሌሎች ቅመሞች የተሰራ የሚያቃጥል ማባያ ሲሆን (እኔ በጣም ከማቃጠሉ የተነሳ “እንላቀስ” ብየዋለሁ) ሁለተኛው ትንንሽ ክብ የበቆሎ ቂጣዎች ናቸው፡፡ ሁለት ወጣቶች የአሳ ቁርጥ ከግፊያው ውስጥ ይዘው ወጥተው አንዱ ሌላውን፣ “ሂድና ሲዲ ይዘህ ና፣ ታዲያ ስክራች እንዳይኖረው” ሲል አስጠነቀቀው፡፡ ሲዲ ምንድነው ስል ጠየቅሁት አንዱን ወጣት፡፡ “ሲመጣ ታይዋለሽ” አለና ዳጣ ሊያስጨምር መስከረም ወደ ተባለች ዳጣ ሻጭ አመራ፡፡ እኔም “ስክራች እንዳይኖረው” የተባለውን ሲዲ በጉጉት መጠበቅ ጀመርኩ፡፡ ለካስ ሲዲ የሚሉት የበቆሎውን ቂጣ ነው፡፡ “ስክራች” የተባለው ደግሞ ያረረ እና የተሰነጣጠቀ እንዳይሆን ለማለት የተጠቀሙበት አገላለፅ ነው፡፡

ከወጣቶቹ የእንብላ ግብዣ ቀረበልኝ፡፡ የአሳ ቁርጥ በልቼ ስለማላውቅ ብፈራም “ሲዲ”ውን በዳጣ ግን አልማርኩትም፡፡ ወጣቶቹ ቁርጡን እየበሉ ሳሉ አንዱ “ሲዲውን በርን (burn) አድርገው” ሲል ሰማሁ፡፡ ደሞ ምን ማለት ይሆን አልኩኝ – ለራሴ፡፡ ለካ ቂጣው ስለላቀ ጨምር እና ግዛ ለማለት ነው፡፡ በሳቅ ታጅቤ አብሬያቸው ቆየሁ፡፡ በአሞራ ገደል ከአሳ ቁርጥ ባልተናነሰ የአቮካዶ ቁርጥም እንደ ጉድ ይበላል፡፡ ታዲያ የአቮካዶም ማባያ ዳጣ ነው፡፡ የሲዲ ሻጮቹ ሴቶች ቁጥር በርካታ ነው፡፡ ተደርድረው “ከእኔ ግዛ፣ ከእኔ ግዛ” ይላሉ፡፡ ከሁሉም ዳጣ በመሸጥ ፋታ አጥታ የምትተጋው ግን መስከረም ናት፡፡

መስከረም ላለፉት አራት አመታት በዚህ ስፍራ ዳጣ በመሸጥ ስራ ላይ መቆየቷን አጫውታኛለች፡፡ በዚህ ስፍራ ጠዋት ጠዋት ዳጣ በጅምላም በችርቻሮም ትሸጣለች፡፡ በአካባቢው ከልጅ እስከ አዋቂ ሁሉም የአሳ ቁርጥ በሊታ ነው፡፡ እርግጥ የተጠበሰ አሳም በስፍራው ይገኛል፡፡ ግን ቁርጥ ተመጋቢው በቁጥር ይልቃል፡፡ የተጠበሰ አሳ ከአሞራ ገደል ይልቅ በፍቅር ሀይቅ በኩል ኦሲስ አሳ መሸጫ ውስጥ ይገኛል፡፡ በዚህ ቦታ የአሳ ሾርባው ተጠጥቶ አይጠገብም፡፡

እነሆ ሌላ ትዕይንት፡፡ የአሳ ቁርጥ ሲሰራ የሚጣለውና ትርፍራፊውን የአሳ ስጋ በፌስታል በመያዝ እና በአካባቢው አባ ኮዳ ተብሎ ለሚጠራው ግዙፍ የወፍ አይነት እየወረወሩ በመስጠት ሌላ ስራ የሚሰሩም ታዳጊዎች አስደምመውኛል፡፡ እንግዳ ሆነው ከሄዱ ይህ ወፍ በረጃጅም ማንቁርቱ ስጋውን ለመያዝና ከተቀናቃኙ ሌላው ጓደኛው ለመቅደም የሚያደርገው ዝላይ አይን ያፈዛል፡፡ ብልጣብልጦቹም ታዳጊዎች “ሂዱና ፎቶ ተነሱ” ብለው ወፉ አካባቢ እንዲቆሙ ይነግሩዎታል፡፡ እርስዎም በዚህ ትዕይንት መሀል አንድ ታሪካዊ ፎቶ ልነሳ ብለው ወፉ ስጋ ለመቅለብ የሚያደርገውን ዝላይ እየተመለከቱ ፎቶ ሲነሱ ይቆዩና እግዜር ይስጥልኝ ብለው ሊሄዱ ሲሉ “እንዴ ጋሼ (እትዬ) አስር ብር ይክፈሉ፤ ይህንንም ስራ የምንሰራው እኮ በማህበር ነው” ብለው እርፍ ይላሉ፡፡ እየሳቁም እየተገረሙም ከፍለው ይሄዳሉ፡፡ ሌሎች በርካታ ትዕይንቶችም በዚህ ስፍራ ይገኛሉ፡፡

እነ ሻኪራ በአሞራ ገደል አሁን ደግሞ ወደነሻኪራ ልውሰዳችሁ፡፡ በዚህ ስፍራ ካስደነቁኝ ነገሮች ሁሉ የእነ ሻኪራ ጉዳይ ነው፡፡ በ2010 የአለም ዋንጫ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደ ጊዜ ሻኪራ በስፍራው ተገኝታ “ዋካ ዋካ ዚስ ኢዝ ታይም ፎር አፍሪካ” የሚል ዘፈን ማቀንቀኗ ይታወሳል፡፡እነሻኪራ ይህን ዘፈን ከነዳንሱ በዚህ ስፍራ አሳምረው ያቀልጡታል፡፡

የቡድን መጠሪያቸው “እነ ሻኪራ” ይሰኛል፡፡ ሂሩት አሸናፊ፣ ሀይማኖት ቶሳ እና መሰረት ኦሳ፡፡ ሂሩትና ሀይማኖት የ7 ዓመት ህፃናት ሲሆኑ የአንደኛ ክፍል ተማሪዎች መሆናቸውን ነግረውኛል፡፡መሰረት ደግሞ ዕድሜዋ ስምንት አመት ሲሆን የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ እነዚህ ህፃናት ጐስቋላ ኑሮ እንደሚኖሩ በማየት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ አለባበሳቸው፣ ፀጉራቸው አጠቃላይ ሁኔታቸው ኑሯቸው ምቾት የራቀው መሆኑን ይመሰክራል፡፡ ከሁለቱ አንዷ ጫማ አልተጫማችም፡፡ ሂሩት ከላይ የለበሰችው አዳፋ ሹራብ ከጠዋቱ ብርድ ሊከልላት አልቻለም፡፡ ሀይማኖት ደግሞ ፀጉሯ ክፉኛ ቆሽሿል፡፡ ጉብኝቴን ጨርሼ ወዳረፍኩበት ለመመለስ ባጃጅ ኮንትራት ስይዝ አጠገቤ ያለ አንድ ወጣት “እነ ሻኪራ ፈረንጆቹ መጡላችሁ” ብሎ ሲነግራቸው ብን ብለው ወደ ፈረንጆቹ ሮጡ፡፡ ፈረንጆቹ የህፃናቱ ፍላጐት የገባቸው አይመስሉም፤ አልፈዋቸው ሄዱ፡፡ እኔ ጠርቼ አናገርኳቸው፡፡ ባለ ባጃጁም እስካናግራቸው እንደሚጠብቀኝ ነግሮኝ፣ የሻኪራን ዘፈን እየዘፈኑ ብር እንደሚቀበሉ ጠቆመኝ፡፡ እነዚህ ህፃናት አማርኛ በደንብ አይችሉም፡፡ ነገር ግን እየተኮላተፉም ቢሆን መግባባት ችለናል፡፡ “የሻኪራን ዘፈን ከነዳንሱ እንበልልሽ” አሉኝ፡፡
“ቀጥሉ” አልኳቸው፡፡

“በወላይትኛ ዳንስ ይሻልሻል ወይስ በራሷ በሻኪራ?” አማረጡኝ፡፡

“በወላይትኛም በሻኪራም እፈልጋለሁ” አልኳቸው፡፡

“ዋካ ዋካ” ተጀመረ፡፡ ዘፈኑ ወዲያው “ዱርሳ ዱርሳ” ወደተሰኘ ሌላ የአካባቢው ዘፈን ተቀየረ፡፡ አከታትለው የትዕግስት ወይሶን “ገደ ገዳ” ቀጠሉ፡፡ ልጆቹ ነገረ ስራቸው አይን ያፈዛል፤ አንጀትም ይበላሉ፡፡ የሚገርመው እኔ ደንሱልኝ ብያቸው እየደነሱ አይናቸውና ልባቸው ሌላ ጋ ነው፡፡ ሌላ የሚያስደንሳቸው ሰው ፍለጋ በሀሳብ ይባዝናሉ፡፡ መቼ ስራውን እንደጀመሩ ስጠይቃቸው በአንድ ቃል “ዱሮ ነው የጀመርነው” ሲሉ መለሱ፡፡

“አሁን ስንት ታስከፍሉኛላችሁ?”

“የፈለግሽውን ስጭን፤ እኛ ይህን ያህል እያልን አንጠይቅም፡፡”

“እዚህ ስትሠሩ፣ ትምህርታችሁስ?” አልኳቸው፡፡

“አሁን ትምህርት ቤት ዝግ ነው፤ ሲከፈት ግን ከትምህርት ቤት በኋላ እየመጣን እንሰራለን” አሉኝ፡፡

እነዚህን ህፃናት በቀን ስንት ብር እንደሚያገኙና ብሩን ምን እንደሚያደርጉት ጠይቄያቸው ነበር፡፡ በቀን እያንዳንዳቸው ከ10 እስከ 40 ብር እንደሚያገኙና ለእናታቸው እንደሚሰጡ ነገሩኝ፡፡ በዚህ የልጅነት እድሜ ወላጆቻቸውን ይደግፋሉ ማለት ነው፡፡ ከእኔ ጋር እያወራን ዕድሜዋ ገፋ ያለ አንዲት ፈረንጅ ስትመጣ አዩና እሷ ጋ ሄደው ለመደነስ ልባቸው ቆመ፡፡ 10 ብር ሰጥቼ ልሸኛቸው ስል የወደፊት ምኞታቸውን ጠየቅኋቸው፡፡ እንደ ሻኪራ ታዋቂ ዘፋኝና ዳንሰኛ መሆን እንደሚፈልጉ ነገሩኝ፡፡ በት/ቤታቸው እንዲህ አይነት እንቅስቃሴ ያደርጉ እንደሆነም ጠይቄያቸው ነበር፡፡ “ት/ቤት እኛ መደነስ እንፈልጋለን ስንል አይፈቀድልንም፤ እዚህ እየመጣን ነው የምንደንሰው” አሉኝና አመስግነውኝ ወደ ፈረንጇ በቀጫጭን እግሮቻቸው ተፈተለኩ፡፡ ፈረንጇም እግዜር ይስጣት ቆማ በተመስጦ ዳንሳቸውን እየተመለከተች፣ ፎቶግራፍ ስታነሳቸው ነበር፡፡ እቺ ፈረንጅ ከእኔ የተሻለ ጉርሻ እንደምትሸጉጥላቸው በልቤ ተስፋ አደረግሁኝ፡፡ ከሁሌም ያሳሰበኝ ግን የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው ነው፡፡ እንደምኞታቸው ይሳካላቸው ይሆን? ብዙ ፈተና ይጠብቃቸዋል፡፡ አንድዬ ይርዳቸው፡፡ (ምንጭ፤ አዲስ አድማስ)

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Social Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • “አስደንጋጭ”! 1 ሚሊዮን ከሚጠጋ ተፈታኝ ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገባው 30 ሺህ (3.3%) ብቻ ነው  January 27, 2023 09:11 am
  • የማይዘነጋዉ የኢትዮጵያዊያኖች የጀግንነት ተጋድሎ ታሪክ፡- ኮሎኔል ባጫ ሁንዴ (ታጠቅ) January 27, 2023 06:12 am
  • ጎርጎራ – የመጻዒው ዘመን ሙሽራ! የዉበት ፈርጥ! January 17, 2023 04:18 pm
  • ሁለተኛው መስቀል አደባባይ January 17, 2023 04:13 pm
  • በአቡዳቢ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን January 17, 2023 04:08 pm
  • በንፋስ ስልክ ላፍቶ ስምንት የመሬት ሌቦች ተያዙ January 16, 2023 11:36 am
  • ሺሻ ሲያስጨሱ በተገኙ ሆቴሎችና የምሽት ጭፈራ ቤቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ January 16, 2023 08:50 am
  • በሐሰተኛ መታወቂያ የደኅንነት አባል ነን ብለው ሲያጭበረብሩ የነበሩ ተያዙ January 13, 2023 02:03 pm
  • ተሽከርካሪ ወንበር ለትግራይ – “ናይ ኣካል ጉዱኣት ተሽከርካሪ ዘለዎ ወንበር” January 12, 2023 07:17 pm
  • የአማራው ኩራት፣ የኢትዮጵያ ዘብ፣ የትህነግን ቅስም ሰባሪ! January 12, 2023 04:00 pm
  • በኢትዮጵያ ላይ የተጣሉ ማዕቀብ እና ሌሎች አስገዳጅ ሕጎች ሙሉ ለሙሉ ተሰረዙ January 12, 2023 01:52 pm
  • የቻይና ዕዳ ስረዛ “Payday Loan Diplomacy” ወይስ ኢትዮጵያን ያዳነ ተግባር? January 12, 2023 11:00 am
  • የአዲስ አበባ አስተዳደር ከቋንቋ ጋር በተያያዘ ውሳኔ አስተላለፈ January 12, 2023 10:46 am
  • “አምባሳደሩ” የቀድሞ ጌቶቻቸውን እንዲያቋቁሙ ተሾሙ January 11, 2023 03:47 pm
  • መከላከያ ሸኔን የሚዋጉ ሚሊሻዎችን አሠልጥኖ አስመረቀ January 10, 2023 05:37 pm
  • በሰባት ተጠርጣሪዎች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ January 10, 2023 03:36 pm
  • የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አቅጣጫ January 6, 2023 03:26 pm
  • “ከዕብሪቱ አስተንፍሰነዋል” – ኢሳያስ January 2, 2023 07:29 pm
  • [ኢትዮጵያን] “አስታክኮ ኤርትራን መውጋት ለሚፈልግ ኃይል አንተባበርም” January 2, 2023 07:11 pm
  • የ፰ ወር ሕጻንና ጨቅላ ወንዶች የሚደፈሩባት ትግራይ December 14, 2022 02:49 pm
  • “ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው” የደጎች አውራ የመቄዶኒያው ቢንያም በለጠ December 14, 2022 09:59 am
  • “የሀብት ምዝገባ መረጃው ለሕዝብ ክፍት ይደረግ “ December 13, 2022 10:30 am
  • የኢትዮጵያ ዓለምአቀፋዊ የሌብነት ደረጃ December 13, 2022 09:42 am
  • ለብረት አቅላጮች ለመሸጥ በኤሌክትሪክ የብረት ማማዎች ስርቆት የ100 ሚሊዮን ብር ኪሳራ December 13, 2022 09:26 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2023 · Goolgule