“…. የመከላከያ ሰራዊት አባላት የተገነባው በደሃ ልጆች ነው። እባካችሁን እንደናንተው የድሃ ልጆች ወገኖቻቹህን አትግደሉ። ተንደላቃችሁ የምትኖሩም ለዚህ ህዝብ ራሩለት። ለራሳችሁ ጥቅም ስትሉ ይህን ህዝብ አታስፈጁት…” ሲሉ አቶ በቀለ ገርባ ለኢህአዴግ የመከላከያ ሰራዊትና ለህወሃት ታማኝ አገልጋይ ሹመኞች ጥሪ አስተላለፉ። አሁን በተያዘው መንገድ ከተቀጠለ ለማንም አይበጅም ሲሉ በግልም ሆነ በጋራ ህዝብን የሚያከብር ታሪካዊ ውሳኔ እንዲወስኑ ተማጸኑ። አቶ ኦባንግ ሜቶና አርቲስት ታማኝ በየነ “የሞቱት ዜጎች ሞት የሁላችንም ሞት ነው” ሲሉ ሁሉም ያገባኛል በሚል ስሜት ድጋፍ እንዲሰጥ ጥሪ አቀረቡ።
አቶ በቀለ በዲሰምበር ፩፫ ቀን ፳፩፮ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፣ መከላከያ ሰራዊት ማለት ህዝቡን ከአምባገነኖች የሚታደግ እንጂ የራሱን ህዝብ የሚገድል ባዕድ ሃይል አይደለም ብለዋል፡፡ “ለምን እንደ ባዕድ መታየት ትፈልጋላችሁ” በማለት የጠየቁት አቶ በቀለ “እባካችሁ ራሩ” ሲሉ ለምነዋል።
“የድሃ ልጅ በድሃ ላይ እንዲዘምት መደረጉ ያሳዝናል” ሲሉ ሃዘን በተሞላበት ስሜት የተናገሩት የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር “በአሰቃቂ ሁኔታ ልጆቻቸውን እየመገቡ ጦማቸውን የሚውሉ ወላጆች በሚኖሩበት አገር እናንተ ተንደላቃችሁ የምትኖሩ ራሩ” በማለት ሁሉም ጊዜና ወቅቱን በመመርመር ወደ ልባቸው እንዲመለሱ አሳስበዋል። አያይዘውም “እባካችሁ እግዚአብሔርን ፍሩ” ሲሉ ከራሳችን አገርና ከሌሎች አገራት ትምህርት እንዲወስዱ ተማልደዋል።
ለህዝብ ርህራሄ የሌላቸው አንድ ቀን በሃላፊነት እንደሚጠየቁ ያሳሰቡት አቶ በቀለ አጠንክረው ተናግረዋል። ከ፶ በላይ ዜጎች መገደላቸውን፣ መረጃው ሲሰበሰብ የሟቾች ቁጥር እንደሚጨምር በመግለጽ የችግሩን ስፋት አሳይተዋል።
በተመሳሳይ ርዕስ ኢሳት ያወያያቸው አቶ ኦባንግ ሜቶና አርቲስት ታማኝ በየነ የአንድ ኢትዮጰያዊ ሞት የሁላችንም ሞት ሆኖ ሊሰማን እስካልቻለ ድረስ ኢትዮጵያዊነት መገለጫው ምን ሊሆን ነው ሲሉ ጠይቀዋል። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ “ህወሃት ገና ከጅምሩ መግደል ሲጀምር ሌሎች በኅብረት ቢቃወሙ ኖሮ ዛሬ ደረጃ ላይ አይደረስም ነበር” ሲሉ የህብረትን አስፈላጊነት አስምረውበታል።
አርቲስት ታማኝ በየነ በበኩሉ ዋቢ መረጃዎችን በማጣቀስ የህወሃትን ገበና ካስታወሰ በኋላ “አንዱ ሲሞት ሌላው ዝም የሚል ከሆነ ሞት በእያንዳንዳችን ደጅ ትመጣለች፤ ባርነቱም ይቀጥላል” ሲል በሰውነት ደረጃ ብቻ እንኳን ሃዘኔታችንን ልንገልጽ እንደሚገባ አመልክቷል። “መቃወም እንዴት ያስገድላል” ሲል ጠይቆ “ጥቂቶች ይሉናል፣ እነሱ ናቸው ወይስ የሚቃወሟቸው ናቸው ጥቂቶች” በማለት ይመልሳል። እንደገናም “የሚመሩን ፲፻ አይሞሉም” ይልና በመገረም በ፻ ሺህ የሚቆጠርን ህዝብ “ጥቂቶች” ሲሉ መስማት በህዝብ ላይ የመዛበት አይነት እንደሆነ ያሳያል። ህብረት አስፈላጊ ነው ሲል ጥሪውን አቅርቧል።
“ነጻ መውጣት መብት ነው” የሚል የቆየ እምነት ያላቸው የሰላማዊ ትግል አራማጁ አቶ ኦባንግ “ከሳጥናችን ካልወጣን ዋጋ የለንም” ሲሉ አሁን ሁሉም ያለው “ምን አገባኝ” በሚል ሳጥን ውስጥ እንደሆነ አስረድተዋል። አንዱ ላይ ጉዳት ሲደርስ፣ አንዱ ሲገደል፣ አንዱ ሲነካ ዝም ማለት የህወሃትን እድሜ እንዳረዘመው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ አመልክተዋል።
“ቅኝ ወራሪዎች መጀመሪያ የሚወሩትን አገር ይከፋፍላሉ” ያሉት አቶ ኦባንግ “አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አገዛዝ፣ የቅኝ ገዢዎቹ ቀለም ተመሳሳይ ከመሆኑ በቀር ከደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ አገዛዝ ተለይቶ አይታይም” ሲሉ አገሪቱን እየገዛ ያለውን የትግራይ ህዝብ ተገንጣይ ቡድን ተመሳሳይ ስልት እየተጠቀመ መሆኑን ተናግረዋል።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Leave a Reply