ወንድም ራያ ጀማ የ5 ወንድ እና የ3 ሴት ልጆች ጎልማሳ አባት ነው። ወደ ሳውዲ የመጣው ድህነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የፖለቲካው ሙቀት አለያም የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ገፍቶት አይደለም። ሳውዲ የመጣው፣ በእስልምና እምነቱ በሚያዘው መሰረት በህይወት ዘመኑ የሚጠበቅበትን ለማድረግ ከብቶቹን ሽጦ የሃጅ ጸሎት ለማድረግ ነበር . . . ዳሩ ግና የጅማው ገበሬ ራያ ጀማል እንደ ቀሩት ጓደኞቹ ጸሎቱን አድርጎ ለመመለስ አልቀናውም! ከሀጃጅ ጓደኞቹ ተለይቶ ከቤተሰብ እንደራቀ ፣ ላለፉት ሁለት አመት ከመንፈቅ ገደማ ሳውዲ በእንግልት ጊዜውን ሊገፋ ግድ ብሎታል። ምክንያቱም የሃጅ ጸሎቱን ከውኖ መካ ውስጥ መኪና አደጋ ደረሰበትና ነው!
የራያ ጀማል ጉዳት. . .
ራያ ጀማል በደረሰበት የመኪና ግጭት የተለያየ የአካሉ ክፍል በጠና ስለተጎዳ በከፍተኛ ህክምና መካ ውስጥ ለሁለት አመት ተኩል ገደማ በሳውዲ የመንግስት ሆስፒታል ሲረዳ ቆይቷል። የመጓጓዣ የማረፊያና የኢንሹራንስ እስከ 55 ሽህ ብር የሚደርስ ገንዘብ ከፍሏቸው ለጸሎት ያማጡት የሃጅ ኮሚቴዎችም ሆኑ የጅዳ ቆንስል ራያ ጀማልን ሊረዱት ቀርቶ ሊያዩት አልቻሉም! ይህ የሆነው ስለ ራያ ጀማል መረጃ ስላልነበራቸው አይመስለኝም፣ ይህን ስል መረጃው እንደነበራቸው እኔም መረጃ አለኝና ነው!
ለሃጅ ጸሎት መጥቶ ስለደረሰበት የመኪና አደጋ በያዝነው ሳምንት የ50 ኢዩቤልዩ በአሉን ባከበረው የጀርመን ራዲዮ ዜናውን አቅርበነው ነበርና የቆንስሉም የሃጅ ኮሚቴ ኃላፊዎች ያውቃሉ! ከዚህ ሁሉ በኋላም ልክ የዛሬ አንድ አመት ገደማ የጅዳ ቆንስል ተወካይ ራያ ጀማል በነበረበት የሽሻ ሆስፒታል ለሌላ ጉዳይ ሄደው አግኝተውትም እንደነበር ተገፊው ወንድም አጫውቶኛል። ተወካዩ ራያ ጀማልን ስላጋጠመው የመኪና አደጋ በዝርዝር ጠይቀውት መመለሳቸውን ከተጎጅው ጋር በያዝነው ሳምንት ባንድ ምሽት ከወደቀበት የጅዳ ቆንስል አካባቢ በሚገኘው የአንድ አረብ ሃብታም አጥር ኩርትም ብሎ ባገኘሁት አጋጣሚ አጫውቶኛል። ይህ ሁሉ ሆኖ የዜጎች ጉዳይ የሚለመከታቸው የቆንስል ኃላፊዎች ራያ ጀማልም ሆነ ጉዳዩ የት ደረሰ ? ብለው አልጠየቁም!
ራያ ጀማልን ሳገኘው . . .
የወንድም ራያ ጀማልን ወደ ጅዳ መምጣትና አቤቱታ የማቅረቡ መረጃ ደረሰኝ። ፈልጌ አጣሁት። አንድ ምሽት ወደ ኮሚኒቲ ካፍቴሪያ ሳዘግም ከግቢው ውጭ ባለ አጥር ታዛ ተኝቶ አየሁት። ራያ ጀማል ነው ግን አላልኩም። ተጠግቸ ለማነጋገር ብሞክርም መተኛቱን ተረዳሁና ትቸው ሄድኩ። በካፍቴሪያ አካባቢ ስለወደቀው ወንድም ጠየቅኩ፣ ራያ ጀማል ለመሆኑ በቂ ምልክቱ በምርኩዝ “ክራንች ” እየታገዘ እንደሚመላለስ ሲነገረኝ አገግሞ ከመካ ሽሻ ሆስፒታል የወጣው ራያ ጀማል መሆኑን ተረዳሁ።
ራያ ጀማልን በቀጣዩ ቀን አግኝቸው አወጋን። ከሁለት አመት በላይ በሳውዲ የመንግስት ሃኪም ቤት በህክምና ሲረዳ የቆየው ኢትዮጵያዊ በቀኝ ጎኑ ደገፍ በሚልባት ምርኩዝ “ክራንች” እየታገዘ፣ እያነከስ ጉዳዩን ለማስፈጸም ላይ ታች ይላል። ፍትህ ሊያገኝና ወደ ሀገሩ ሊሸኝ፣ የሞት መርዶውን ሰምተው ያለቀሱ ቤተሰቡን ተሰናክሎም ቢሆን ይቀላቀል ዘንድ ተስፋ ሰንቆ ከመጣበት ቤቱ የሚደግፈውም ሆነ፣ ለጎኑ ማሳረፊያ መጠለያ የሚሰጠው አጥቷል። የገዛ ሃገሩ ሰዎች ክብር አልሰጠነውምና በዚህ ሙቀት ከቆንስሉ ርቆ ባለው የአረብ ግንብ ጠጋ ብሎ ውሎ ያድራል . . .
ራያ ጀማልን ከፍ ሲል ኢትዮጵያዊነቱ ፣ ዝቅ ሲል ቋንቋውን የሚናገሩት የቀየው ልጆች ሞልተው ተርፈዋል፣ ሁላችንም ግን ጉዳቱን እንኳ ጠጋ ብለን መጠየቅ ገዶናል። አቅም የለሾቹ በጥድፊያው ብንወጠር ጧትና ማታ የሚያዩት የቆንስል ዲፕሎማቶችና የልማት ማህበር አባላት ብሶቱን ሰምተው ለምን ጨከኑበት? ማለቴ አልቀረም . . . መልስ የለኝምና አዘንኩ!
የወንድም ራያ ጀማልን ጉዳይ በቅርብ ርቀት ላለፉት ሁለት ሳምንታት ላላነሰ ጊዜ ስከታተል ቆየሁ። ጉዳዩ በቆንስል ኃላፊዎች በኩል ለጉዳይ ፈጻሚው ተላልፎ ጉዳዩ ሲንከባለል ቢሰነብትም ወደ መጨረሻ ራያ ጀማል ወደ ሀገሩ ለመላክ መወሰኑና ቲኬት ኮሚኒቲው እንዲያቀርብ ትብብር በቆንስል ሸሪፍ የመጠየቁ መረጃ ከአንድ የኮሚኒቲ የምክር ቤት አባል መረጃው ደረሰኝ። (በዚህ ዙሪያ ከጥቂት ቀናን በፊት ባቀረብኩት ተመሳሳይ መረጃ ቅሬታ ያቀረቡልኝ አንድ ጠቋሚ ሃሳብ በመቀበል ሳጣራ ግን ቆንስል ሸሪፍ ኬሩ ራያ ጀማል የቲኬት ጥያቄውን ለኮሚኒቲ እንዲያቀርብ በስሙ ደብዳቤ ጽፈው ማዘጋጀታቸውንና ለኮሚኒቲው ምክትል በስልክ “ተባበሩት” ማለታቸውን ማረጋገጥ ችያለሁ)
ከቆንስሉ ግቢ ለቀን ወደ ኮሚኒቲ ጉዳዩን ለማጣራት ራያና እኔ ተያይዘን ስንወጣ ከቆንስሉ ባለጉዳዮች መግቢያ በር ነጻ ግልጋሎት የሚሰጡትን የድርጅትና የኦሮሞ ልማት ማህበር አባል ጋር ተገናኘን። ሳያቸው በስጨት አልኩና ስማቸውን ጠርቸ “የዚህ ወንድም ጉዳይ ወደ ሃገሩ ለመላክ ሲወሰን አንድም እንደ ዜጋ አለያም እንደ ተወላጅ ለምን መብቱን ማስከበር ለምን ተሳናችሁ?” ስል ጠየቅኳቸው። ግራ ተጋብተው . . . “ይህ ወንድም እንደ ተገልጋይ ሲወጣ ሲገባ ከማየት ውጭ ታሪኩን አላውቅም!” ብለው ሲመልሱልኝ ራያን እንዲጠይቁት አድርጌ በኦሮምኛ አውርተው ጨረሱ፣ ወደኔ መለስ ብለው “እውነት እልሃለሁ፣ ምንም አይነት መረጃ የለኝም!” በማለት በአግርሞት መልሰውልኝ በእንግልቱ ዙሪያ ስናወጋ ሌላው የጅዳ ኮሚኒቲና የኦሮሚያ ድርብ ስልጣን ያላቸው እድሜ ጠገብ ወዳጀን አገኘኋቸው . . .
ለኃላፊው ኮሚኒቲውም ቲኬት እንዲያቀርብ መጠየቁን በማውሳት “ራያው ጀማል ጉዳዩን ሳይጨርስ ለምን ቲኬት ለመስጠት ተስማማችሁ? ” ብየ ጠየቅኳቸው። ኃላፊውም ስለ ቲኬቱ ጥያቄው መቅረቡን ከማመን ባለፈ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ አለመሰጠቱን ጠቁመው ጉዳዩን ከቆንስል ሸሪፍ ኬሩ ጋር እየተነጋገሩበት እንደሆነ ጠቁመውኛል። ከእኒህ ወዳጀ ጋር ውይይታችን እንደቀጠልን ወደ ካፍቴርያው አመራን። በድጋሜ ከራያ ጀማል ማግኘት አለባቸው የምለውን መረጃ ጠይቀው እንዲረዱ አደረግኩ። መጠለያን በሚመለከትም ሃላፊነቱን ቆንስሉ ከወሰደ መጠጊያ እንደማይጠፋ በመጠቆም ፈቃድ ያመጡልኝ ዘንድም አሳሰብኳቸው። ከሰነበተበት ሜዳ ወደ የግል መጠለያ ለመውሰድ ፍቃዱን እንደሚጠይቁልኝ አጫወቱኝ። ኃላፊው የሰጡኝን ምላሽ ሁሉንም ለማመን ሞከሬ እንዲከታተሉት ጭምር ተመካክረን ተለያየን!
ይህ ከሆነ ከአንድ ቀን በኋላ የኦሮሞ ተወላጆች ማህበር አመታዊ በአላቸውን ሊያከብሩ ስለ አከባበሩ ዝግጅት መክረው ሲወጡ የኦሮሞው ተወላጅ ኢትዮጵያዊ ራያ ጀማል ጉዳይ በተሰብሳቢዎች ተነስቶ ራያ ጀማልን ማነጋገራቸውን ሰማሁ። ሁሉም በሆነው አዝነው በተለይም የድርጅት አባላቱ በቁጭት ለመፍትሄው ከቆንስሉ ጋር እንደሚመክሩ ጠቁመው፣ ማረፊያ እስኪ ያዘጋጁለት በቆንስሉ ግቢ እንዲያድር አድረገው ተለያዩ።
መሽቶ ነጋ፣ የተባለው ደረሰ፣ ቃል የገቡት የውሃ ሽታ ሆነው ቀሩ! ባዩት ያዘኑት ሰብዕና አስገድዷቸው ለወንድም ራያ ጀማል ጎኑን የሚያሳርፍባት ፍራሽና መላብስ እንባቸውን እያዘሩ አቀብለውት ብቻ አልሄዱም። እስከ ዛሬ ደረስ አደየመጡ ይጠይቁታል! ራያ ጀማል ከዚያች ቀን በኋላ በኦሮሚያ ማህበር አባላት የዚያች ምሽት ተማጽኖ ከኮሚኒቲው ግቢ ማደር ቢችልም በቀጣዩ ቀናት ከቆንስሉና ከኮሚኒ ቲው ግቢ እንዳያድር ተከለከለ! ወንድም ራያ ጀማል ያገገመው ስብራቱ በእንግልቱ እየተቀሰቀሰ እየወጋው እየተሰቃየ ነው ። ከሃገሩ ባንዴራ የቅርብ ርቀት ባሉት የአረብ ሃብታሞች አጥር ታዛ ኑሮን በመከራ በመግፋት ላይ ነው!
“ጉዳዩ ተሸፋፍኖ ሊሄድ ነው!” ብለን የሰጋነው የራያ ጀማል ጉዳይ ብዙዎቻችን ያስቆጨ ቢሆንም ዛሬ ነገሮች ተቀያይረዋል ብየ ነበር ከቀናት በፊት። ይህንንም ያልኩት የቆንስሉ ጉዳይ ፈጻሚ አቶ መሃዲና ወንድም ራያ ጀማል ወደ መካ በማቅናት ከመካ ትራፊክ ፖሊስ ጋር የመነጋገራቸውን ሰናይ መረጃ ሰምቸ ነበርና ነው … እቀጥልበታለሁ ብየ ጉዳዩን በእንጥልጥል የተውኩት ጉዳይ ፈጻሚውና ወንድም ራያ ጀማል ከመካው ጉዞ ያገኙትን ውጤት ይዠ ለማምጣት ይቻለኛልና ነበር። አነሆ ጉዳዩ የተያዘበትን የመካ ትራፊክ ፖሊስን ያነጋገሩት ጉዳይ ፈጻሚ የራያን መዝገብ አስቀርበው የገጨውን መኪና ባለቤት በስልክ ማነጋገራቸውን ተገፊው ወንድም አጫውቶኛል። ከዚህ ቀደም ራያ በሆስፒታል እያለ 10 ሽህ የሳውዲ ሪያል ሊሰጡት ፈቃደኛ ሆነው የነበሩት ሳውዲ ዛሬ 3 ሽህ ሪያል ካሳ ሊከፍሉ ፍቃደኛ መሆናቸውን መግለጻቸው ይህም ካልተቀበሉ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ እንደሚችሉ መነገራቸውን ራያ ጀማል ገልጾልኛል። ወንድም ራያ ከአመት በፊት የሆነውን እያስታወሰ ይህው ሳውዲ የገጨው መኪና ባለቤት ወደ ሆስፒታል መጥተው “10 ሽህ ሪያል ካሳ ልክፈልህ እና ሹፊሬ ከእስር ይፈታ!” ብለው የሆስፒታሉ ዶክተሮች መቃወማቸውን ይናገራል። ምክንያታቸው ደግሞ “ጉዳቱ ከፍተኛ በመሆኑ በክፍያው ማነስ የተነሳ ኢንባሲ ቢጠይቀን አደጋ እንወድቃለን” በማለት ዶክተሮች ፈቃደኛ ባለመሆናቸውን ጉዳዩ መጨናገፉን ራያ ጀማል ከኦሮምኛና አረብኛውን ከአማርኛ ጋር እየቀላቀለ በቁጭት አጫውቶኛል።
ትናንት ምሽት ወንድም ራያ ጀማልን ደጋግሞ ስልክ ደውሎ እንድጎበኘው ጠይቆኝ ላነጋግረው ሄድኩ … ጉዳዩን ሰምቶ ብዙዎች ተስፋ ሰጥተነው የነበረው ተስፋ ተሟጦበት አገኘሁት ። ዛሬስ ምን አዲስ ነገር አለ ምን ሆንል አልኩት! “አይይ አቶ ነቢዩ ትናንትና ዛሬ ሙቀቱም ነው መሰል ወገቤን መላ የተጎዳ አካሌን ይጠዘጥዘኛል፣ ያመኛል፣ ማረፊያ የለኝም፣ ሜዳ ላይ ለ18 ቀናት ስሰቃይ ማረፊያ ያልሰጡኝ የሚረዱኝ አይመስለኝም ፣ ጉዳየን አሁን አንደዚህ በሜዳ ላይ ሆኘ በፍርድ ቤት ለመከታተል አልችልም!
እዚህ ላይ ራያ ጀማል አደጋ ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ አይተውት የማያውቁት የሃጅ ኮሚቴ ሃላፊዎችም ሆኑ የጅዳ ቆንስል የት ነበሩ? አልልም። የጅዳን ኮሚኒቲ ቲኬት ከመጠየቁ በፊት መደረግ የነበረበት ጉዳይ ለምን ክትትል አልተደረገም ? አልልም! የራያ ጀማል ጉዳይ አይነት እና ከዚያም የከፉ የመብት ጥሰቶች ተፈጽመው ቆንስል መስሪያ ቤቱ እያሸማገለ የጨረሳቸው ጉዳዮች በርካታ ናቸው። ያም ሆኖ ጉዳትን ከግምት ያሰረገባ ሽምግልና ነበር ብሎ ለማናገር እንቸገራለን። ይህ ካልሆነ ደግሞ ቢቀር ይሻላል። የመብት ጥሰትን በተልካሻ ካሳ ከማሸማገል ወደ ተገቢ ህጋዊ ፍርድ ቤት ማድረስ ይቀላልና ቢታሰብበት መልካም ነው። ይህ ከማድግ ባለፈ እያሸማገሉ ጉዳዩን ሸፋፍኖ ተበዳይን ወደ ሀገር መሸኘት ሊቆም ይገባል! ትናንት በቆንስል መስሪያ ቤቱ ዙሪያ የምናውቀው፣ ጩኸን ማስቆም ያልቻልነው ጉዳይ በሽፍንፍንና በግዴለሽነት ዛሬ ሁነኛ ኃላፊ መጥተው ነገሮች እየተስተካከሉ ባለበት ሁኔታ በደል በቆዩት ዲፕሎማቶችና በሰራተኞች በእንዝላልነትና በሽፍንፍን ሲያልፍ ማየት ግን ነፍሴ አትፈቅድም!
በራያ ጀማል ጉዳይ እሱ እንዳለው ወራት የሚጨርሰውን ጉዳዩን እዚህ ሆኖ ለመከታተል ይከብዳል። ማረፊያ የለውምና ለከፋ ችግር ላይ ነው። ራያ ጀማል ያለው ተጨባጭ አማራጭ አንድም መሄድና ወክልና መላክ ፣ መጠላያ አግኝቶ ጉዳዩን መከታተል ፣ ይህ ካልሆነም የሚሰጡትን ተቀብሎ ወደ ቀየው መቀላቀል ብቻ ነው። በእኒህ ውስብስብ አማራጮች ላይ ብቻውን ይወስን ለማለት የሚከብደው የሚሰጠው ሀሳብ ከችግር ጭንቀቱ አንጻር ይሆናልና ተበዳዩ ይጎዳል። የቆንስል ሃላፊዎችና የሚመለከታቸው በዚህ ረገድ አማራጮችን ከህግ አንጻር ተመልክተውና አዋቂ አመካክረው አስፈላጊውን ድጋፍ ቢያደርጉለት ቤተሰቡን በትኖ ለከፋ አደጋ በተዳረገው ወንድም ነፍስ መታደግ መቻል በምድርም በሰማይ ጽድቁ ለራስ ነው! ስለ ራያ ጀማል የማጠቃለው መብቱ እናስከብርለት፣ የቻልን እንደ አቅማችን እንርዳው በማለት ነው ፣ የምለው ከዚህ ያለፈ አይደለም!
ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
መጋቢት 10 ቀን 2007 ዓም
Leave a Reply