የፌደራል ዋና አቃቢ ህግ ሜቴክ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ በገዛቸው ሁለት መርከቦች አማካኝነት በህግወጥ የንግድ እንቅስቃሴ መሰማራቱን ገልፆ እንደነበር ይታወሳል። ሆኖም ግን በሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ሜ/ጄ ክንፈ ዳኘው ላይ የቀረበው ክስ ድርጅቱ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ አባይ እና ህዳሴ የተባሉትን ሁለት መርከቦች በመግዛት ከፍተኛ የገንዘብ ብክነት የሀገርና ህዝብን ሃብት ያለ አግባብ አባክኗል የሚል ነው። ሆኖም ግን ለድረገፃች አዘጋጅ በደረሰው መረጃ መሠረት ሜቴክ የገዛቸው ሁለት መርከቦች እ.አ.አ. እስከ 02 – 07/-01-2016 በምስራቅ አፍሪካዊቷ የኮሞሮስ (Comoros) ደሴት ሰንደቅ ዓላማ አያውለበልቡ በህገወጥ ንግድ ተሰማርተው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ በቀረበው የቴሌቪዥን ዶክመንተሪ ሜቴክ እ.አ.አ. በ2014 ዓ.ም አባይ እና ህዳሴ የተባሉን መርከቦች ከኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ያለ አግባብ መግዛቱና ለጥገና ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ማውጣቱ ተገልጿል። በመጨረሻም እ.አ.አ. በ2016 ዓ.ም ሁለቱን መርከቦች በዝቅተኛ ዋጋ ለሌላ ድርጅት መሸጡን ተገልጿል። በዚህ መልኩ ሜቴክ ከፍተኛ ገንዘብ ያለ አግባብ ከማውጣቱ በተጨማሪ ሁለቱን መርከቦች የኮሞሮስ ሰንደቅ ዓላማን እንዲያውለበልቡ በማድረግ በህገወጥ የባህር ትራንስፖርትና ንግድ ተሰማርቶ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
1) “አባይ” እና “ህዳሴ” እንደ “Padma” እና “Tika”
በመጀመሪያ እ.አ.አ. በ2016 ዓ.ም ከመላው ከአገልግሎት ውጪ በመሆናቸው ምክንያት ተቆራርጠው ለሌላ ነገር መስሪያ እንዲውሉ የተደረጉ መርከቦችን ዝርዝር (2016-List-of-all-ships-scrapped-all-over-the-world) አገኘን። በዚህ መረጃ መሰረት ተጠቀሰው አመት 862 መርከቦች አካላቸው ተቆራርጦ ለሌላ መርከብ ወይም ዕቃ መስሪያ ውሏል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በተራ-ቁጥር 172 እና 173 ላይ ሁለት የኢትዮጵያ መርከቦች ተዘርዝረዋል። በዝርዝሩ መሰረት አባይ እና ህዳሴ የተባሉት መርከቦች “Padma” እና “Tika” የሚል ስም ተሰጥቷቸው በኮሞሮስ ሀገር ሰንደቅ ዓላማ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር መረጃው ይጠቁማል።
በመጨረሻም እ.አ.አ. በ07-01-2016 ዓ.ም “Padma” የተባለችው መርከብ እንድትቆራረጥ በህንድ ሀገር ለሚገኝ “Alang” የተባለ ኩባንያ ተሸጣለች። “Tika” የተባለችው መርከብ ደግሞ በ02-02-2016 ዓ.ም በፓኪስታን ሀገር ለሚገኝ “Gadani” የተባለ ኩባኒያ መሸጧ ተጠቅሷል። ይሁን እንጂ በኮሞሮስ ሰንደቅ ዓላማ የሚንቀሳቀሱት እነዚህ ሁለት መርከቦች እስከተሸጡበት ዕለት ድረስ ባለቤታቸው፣ ለሥራ የሚያንቀሳቅሳቸው እና ተጠቃሚ ተብሎ የተጠቀሰው አካል ሜቴክ ሳይሆን “የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ” (Ethiopian Shipping and Logistics Service Enterprise) ነው።
በዚህ መሰረት ሜቴክ የሁለቱን መርከቦች ስምና ሰንደቅ ዓላማ ቀይሮ “የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ” ግን የመርከቦቹ ህጋዊ ባለቤት፣ ተጠቃሚና ተጠያቂ አድርጎ በሀገርና ድርጅቱ ስም በህገወጥ ንግድ ተሰማርቶ እንደነበር መገንዘብ ይቻላል። ስለሁለቱ መርከቦች የቀረበውን መረጃ ከታች ካለው ምስል መመልከት ይቻላል። በ2016 ዓ.ም በመላው ዓለም እንዲቆራረጡ የተሸጡት 862 መርከቦች ሙሉ ዝርዝር መረጃን ይህን ሊንክ (Excel) በመጫን ማውረድ ይቻላል።
“Padma” እና “Tika” የሚል ስም ተሰጥቷቸው በኮሞሮስ ሀገር ሰንደቅ ዓላማ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት አባይ እና ህዳሴ
2) ከኮሞሮስ ደሴት ወደ ካሪቢያን ደሴት
ከቅርብ አመታት በፊት ዊኪሊክስ (WikiLeaks) የተባለው ድረገፅ ባወጣው መረጃ መሰረት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ባለሃብቶች ገንዘባቸውን ወደ ካሪቢያን ደሴቶች በማሸሽ ከፍተኛ የሆነ የታክስ ማጭበርበር እንደሚፈፅሙ ማጋለጡ ይታወሳል። በእርግጥ በወቅቱ የፈትልኮ የወጣውን መረጃ በተወሰነ ደረጃ ለማየት ሞክሬ ነበር። ከዚያ በፊት ድረገጹ አስፈትልኮ ባወጣው የሚስጥር ሰነድ በአዲስ አበባ የቀድሞ የአሜሪካው አምባሳደር የነበሩት ዶናልድ ያማማቶ ስለ ቀድሞ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የግል ስብዕና እና ባህሪ፣ ከቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኃላፊ ከነበረው አቶ ጌታቸው አሰፋ ጋር ስላደረጉት ውይይት እና ሌሎች መረጃዎችን ማንበቤን አስታውሳለሁ።
በወቅቱ አፈትልኮ ከወጣው የሚስጥር መረጃ ውስጥ “Ethiopia” የሚለውን ቃል በመፈለግ ከሀገራችን ጋር በተያያዘ ያለውን መረጃ ማንበብ ችዬ ነበር። ከካሪቢያን ደሴቶች ጋር ተያያዞ የሚስጥር መረጃ በድረገፅ ሲለቀቅ በተመሳሳይ መንገድ ከኢትዮጵያ ጋር ተያያዥነት ያለውን መረጃ ለመፈለግ ሞክሬ ነበር። ነገር ግን የምፈልገውን ዓይነት መረጃ ስላላገኘሁ ነገሩን ችላ ብዬው ነበር። ባለፉት አመታት በሀገራችን ሲፈፀሙ የነበሩ የዘረፋና ሌብነት ተግባራትን አስመልክቶ በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አባምሳደር ሱሊማን ደደፎ ስለ ሜቴክ የተናገሩት ነገር ትኩረቴን ሳበው።
አምባሳደር ሱሌማን ሜቴክ ሁለት ያረጁ መርከቦችን ከኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ በመግዛት በህገወጥ ንግድ፣ ምንአልባት በጦር መሳሪያ ንግድ፣ ተሰማርቶ እንደነበር ጠቁመዋል። ሁለቱ መርከቦች በእርጅና ምክንያት የአገልግሎት ዘመናቸው ያበቃ በመሆኑ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ በዓለም አቀፍ የባህር ንግድ መስመር መንቀሳቀስ አይችሉም። በመሆኑም እንደ አምባሳደር ሱሌማን አገላለፅ ሜቴክ በካሪቢን ደሴቶች ከሚገኙ ሀገራት ሰንደቅ ዓላማ ለመግዛት ሲንቀሳቀስ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ መሠረት ሜቴክ “ትሬንዳድ እና ቴቤጎ” ከተባለችው ሀገር ሰንደቅ ዓላማ በመግዛት በህገወጥ ንግድ ተግባር ሳይሰማራ እንዳልቀረ ጥርጣሬያቸውን መግለፃቸው ይታወሳል። ነገር ግን ሜቴክ ሰንደቅ ዓላማ ለመግዛት ከምስራቅ አፍሪካ ተነስቶ ካሪቢያን ደሴቶች ድረስ ለምን ሄደ? ይህን ጥያቄ ለመመለስ በቅድሚያ የካሪቢያን ደሴቶች ለምን የህገወጥ ንግድ እና የገንዘብ ዝውውር መዳረሻ እንደሆኑ ማወቅ ያስፈልጋል።
3) በፖስታ ሳጥን የሚገዛ ዜግነት እና የባንክ አካውንት
ትናንሽ የሆኑት የካሪቢያን ደሴቶች ኢኮኖሚ በቱሪዝምና በፋይናንስ ዘርፍ ላይ የተመሰረተ ነው። በመሆኑም አብዛኞቹ የካሪቢያን ደሴቶች ቱሪስቶችን ወደ ሀገራቸው ለመሳብ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። በዚህ መሰረት ጎብኚዎች በሀገራቱ ለረጅም ግዜ እንዲቆዩ፣ በተደጋጋሚ ወደ ሀገሪቱ ተመላልሰው እንዲመጡ የዜግነት መታወቂያና የመኖሪያ ፍቃድ ማግኘት እጅግ በጣም ቀላል ነው። ለምሳሌ በአንድ የካሪቢያን ደሴት ዜግነት ለማግኘት በሀገሪቱ የፖስታ አገልግሎት ድርጅት ውስጥ አንድ የመልዕክት ሳጥን መግዛት ብቻ በቂ ነው። በደሴቱ ላይ እግሩ ያረፈ ሁሉ ወደ በፖስታ አገልግሎት ድርጅት በመሄድ የመልዕክት ሳጥን መግዛት ይችላል። ይህን የፖስታ ሳጥን ቁጥር በመጠቀም በሀገሪቱ በሚገኙ ባንኮች የራሱን የባንክ ሂሳብ ይከፍታል። ከዚያ በኋላ ወደመጣበት ሀገር ተመልሶ መሄድ ይችላል።
ስለዚህ አንድ ግዜ ወደ ካሪቢን ደሴቶች በሄደ የፖስታ ሳጥን የገዛ ግለሰብ የአገልግሎት ክፍያ በአግባቡ እስከከፈለ ድረስ የሀገሪቱ ዜጋ ሆኖ ይቀጥላል። ከዚህ በተጨማሪ በየትኛውም የዓለም ክፍል ሆኖ በካሪቢያን ባንኮች ውስጥ ያለውን ሂሳብ ማንቀሳቀስ ይችላል። ቀደም ሲል በተገለፀው መሰረት፣ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የመጡ ባለሃብቶች፣ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች፣ በዘረፋና ሌብነት ተግባር የተሰማሩ የመንግስት ባለስልጣናትና ሌሎች በህገወጥ ተግባር የተሰማሩ ሰዎች ወደ ካሪያቢያን ደሴቶች የሚሄዱት በቀላሉ ዜግነት ለማግኘት እና የባንክ ሂሳብ ለመክፈት ነው። ከዚያ በኋላ በህገውጥ ንግድ እና ዘረፋ የጋበሱትን ገንዘብ ወደ እነዚህ ሀገራት ባንኮች ያሸሻሉ፣ እንዲሁም በትክክለኛው መንገድ ሰርተው ያገኙትን ገንዘብ ከሀገራቸው የታክስ መስሪያ ቤት በመደበቅ ታክስ ያጭበረብራሉ። የሜቴክ ደግሞ ከሁሉም የተለየ ነው።
4) የጠፋችው የኢትዮጵያ መርከብ ተገኘች!
ለኢትዮጵያ የመርከብ ድርጅት ቀረቤታ ያላቸው ሰዎች በሰጡኝ መረጃ መሰረት የደርግ መንግስት፤ ነፃነት፣ አንድነት፣ አብዮት እና መንግስቱ ኃይለማሪያም የተባሉ አራት መርከቦችን መግዛቱን ይገልፃሉ። የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ “አብዮት” የተባለውን መርከብ “ህዳሴ” የሚል ስያሜ ሰጥቶታል። መንግስቱ ኃይለማሪያም የተባለውን መርከብ ደግሞ “የአባይ ወንዝ” ወይም በአጭሩ “አባይ” የሚል ስያሜ እንደሰጠው ይጠቀሳል። በመጨረሻም “ህዳሴ” እና “አባይ” የተባሉትን መርከቦች ሜቴክ ደግሞ “Padma” እና “Tika” የሚል ስያሜ በመስጠት በኮሞሮስ ባንዲራ ህገወጥ ንግድ ሲያከናውንባቸው እንደነበር ከላይ ተገልጿል።
የደርግ መንግስት የገዛው “ነፃነት” የተባለው መርከብ ያለበት ሁኔታ ለግዜው አልታወቀም። “አንድነት” የሚባለው መርከብ ግን “አንዲ” (ANDI) የሚል ስያሜ ተሰጥቶት “St. Kitts Nevis” በምትባል በጣም ትንሽ የካሪቢያን ደሴት ሰንደቅ ዓላማ ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። ዓለም አቀፉን የባህር ትራንስፖርት ለመቆጣጠር የሚያገለግለው የMarinetraffic.com በተሰኘው ድረገፅ መሰረት “አንድነት” የተባለችው መርከብ ከአገልግሎት ውጪ ወይም የጠፋች መሆኑን ይገልፃል።
መርከቧ በባህር ትራንስፖርት ትራፊክ እይታ ውስጥ ገብታ የነበረው እ.አ.አ. በ2015 ዓ.ም እንደሆነ ተጠቅሷል። ሆኖም ግን መርከቧ እስካሁን ድረስ እንድትቆራረጥ አልተሸጠችም። በድረገፁ ላይ የመርከቧን እንቅስቃሴ ለመከታተል ባደረኩት ጥረት አሁንም ድረስ በህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ እንደሆነች ለመረዳት ችያለሁ። ከታች ያለው ምስል የአንድነት መርከብን እንቅስቃሴ በካርታ ያሳያል።
በዚህ መሰረት ከሜቴክ በተጨማሪ አንድነት የተባለች ሌላ የኢትዮጵያ መርከብ በመሬት ካርታ ላይ እንኳን በግልፅ በማትታይ “St. Kitts Nevis” የምትባል ትንሽዬ ሀገር ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ በህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ እንደ ተሰማራ መገንዘብ ይቻላል።
Ethiopian Think Thank Group ስዩም ተሾመ
Leave a Reply