• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

አድዋ ለኔ

March 4, 2014 05:58 am by Editor Leave a Comment

እኔ የምኖረው በአሜሪካ ነው። በአሜሪካ ሆኜ የአድዋን በዓል አከበርኩ። የኢትዮጵያዊያን ድረገፆችን እየተመላለስኩ ቃኘኋቸው። ሬዲዮኖችን አዳመጥኳቸው። የስልከ ልውውጦችንና የእንግዶችን ሃሳቦች ተከታተልኩ። ስደሰት፣ ሳዝን፣ በጣም ስደሰትና በጣም ሳዝን ዋልኩ። ሲመሽና የምኝታ ሰዓቴ ቀርቦ ባልጋዬ ላይ ስጋደም፤ እንቅልፍ ቶሎ አልወስድህ አለኝ። መገለባበጡ ለውጥ አላመጣ ሲል በሃሳብ መዋተቱን ተያያዝኩት። አድዋ ለኔ ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ ከዕለቱ ወደላይና ወደታች መዋዠቅ ጋር ተዛምዶ አፋጠጠኝ። እውነት አድዋ ለኔ ምንድን ነው?

አድዋ ከመቶ ዓመት በፊት የተከሰተ ጉዳይ ነው። በዚያ ጊዜ የተካፈሉትና የነበሩት አሁን የሉም። አድዋ በአንድ የሀገራችን አካባቢ የተፈፀመ ጉዳይ ነው። ታዲያ ለኔ ከአንድ መቶ ዓመት በኋላ ላለሁት ምኔ ነው? በዚህ ጉዳይ ላይ ስመላለስበት እኩለ ሌሊት ሆነ። ለካስ እንዲያው በቀላሉ በጃችን የያዝነውን ነገር ጠፍረቅ አድርገን ስንይዘው፤ ያሙለጨልጫል። በልጅነቴ ገና  አንድ ወር ሲቀረው ላከብር እንደፋደፍ የነበርኩት ወጣት፤ አሁን ለምን አንደማከብረው ራሴን ስጠይቀው፤ መልሱ ጊዜ ወሰደብኝ። ስደተኛ ስለሆንኩ ነው? ወይንስ ይኼም በናንተ ቤት አለ?

ዓያችሁ፤ አዲስ አበባ ተወልዶ አሜሪካዊ ነኝ የሚል የፈረንጅ ልጅ አለ። ዋሺንግተን ዲ. ሲ. ተወልዶ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል የሀገሬ ልጅ አለ። ከወላጆቻቸው የወረሱት ስለሆነ ነው። ይኼ በልብ ውስጥ ገብቶ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚያስብለው ኢትዮጵያዊነት የበቀለውና የለመለመው የትና እንዴት ነው? ኢትዮጵያዊነት ከመወለጃ ቦታ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ከሆነ፤ ታዲያ የት መጣ? ማነው ባለቤቱ?

ይኼ ኢትዮጵያዊነት የበቀለው፤ ፋሺስት ጦሩን ከቶ ሀገራችንን ሊወር ሲመጣ፤ ባንዳዎች በጣሊያን፤ ሹምባሽ ቁልባሽ የሚል ተለጣፊ ሹመት ተቀብለው፣ ለፋሽስቱ ሰግደው፣ አብረውት ተሰልፈው፣ አንዳንዶቹ መስቀላቸውን በአክሱም ቤተክርስትያን ይዘው ፋሽስቱን ጣሊያን ገዥያችን ብለው ውዳሴ ሲገቡ፤ አንዳንዶቹ ከጣሊያን ፋሽስት መሣሪያና ገንዘብ ተቀብለው ከፋሽስቱ ጋር በማበር በትግራይ ምድር የሚዋጉትን በመርዝ ጢስና በመንገዳቸው የጠርሙስ ስብርባሪ በመበተን በዱርና በገደሉ በመከታተል ሲወጓቸው፤ በባዶ እግራቸው፣ በስስ ስንቅ (ያለበቂ ስንቅ) ዘምተው፤ ወደ ቤታቸው ባልተመለሱት አርበኞቻችን ሕይወት ነው። በኤርትራ የነበሩ ወገኖቻችን፤ ጣሊያን ያስታጠቃቸውን መሣሪያ አንግበው፤ ያንተ አስካሪስ አልሆንም በማለትና ወደ መሐል ኢትዮጵያ በመምጣት፤ ከወገኖቻቸው ጋር ሲዋጉ በወደቁት ኢትዮጵያዊያን ደም ነው። ኢትዮጵያዊነት የለመለመው በአድዋና በመሰል አኩሪ አባቶቻችን ባደረጉዋቸው ተጋድሎዎች ነው። አድዋ የተፈጠረችውና ያበበችው፤ በኢትዮጵያዊነት በኢትዮጵያዊያን ደም ነው።

ይህ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያዊነት ያደገው፤ ከድርቡሽ ጋር በተደጋጋሚ በጎንደርና በመተማ በተዋደቁት አባቶቻችን ቆራጥነት ነው። በግብፅና በቱርክ፣ በጣሊያንና በእንግሊዝ ድጋፍ በሱዳን በተደጋጋሚ በኤርትራ ምድር፤ እምቢ ለሀገሬ ብለው በተሰው አባቶቻችን ደም ነው። በቅርብና በሩቁ ታሪካችን፤ በሀገራዊ አንድነት፤ ጠላትን በመመከት፣ የመሬታችንን ጭብጥ አፈር አላስነካም ባሉ አያቶቻችን ነው። ደህነቱን እና ጥጋቡን፣ ደስታውን እና ሐዘኑን፣ ልጅ መውለዱን እና መዳሩን፣ ጎጆ መስራቱን እና አውድማ መጣሉን አብረው በሠሩበት ሀቅ ነው። አብረው የግጦሽ ከብቶቻቸውን ባዋሉባቸው ሽንተረሮች ነው። ወንዞችንና ተራሮችን ተባብረውና ተጋርተው ኣቆዩልን እውነታ ነው።

በሶማሊያ ወረራ፤ እብሪተኛው ሰይድ ባሬ ጦሩን ከቶ፤ ያጎረሰውን እጅ ነካሽ የሆነው ወገንተኛው አምባገነን ሕገወጥ ራሱን “የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር” ብሎ የሚጠራው ቡድን ከሶማሌ ጋር ወግኖ ሲዋጋን፤ እምቢ ለሀገሬ ብለው በቆራጥነት በወደቁት ኢትዮጵያዊያን ደም ነው። የሰው በላው የመንግሥቱ ኃይለማርያም ደርግ፤ መንግሥቱ ኃይለማርያምን በሥልጣን ለማቆየት ከአንድ ትውልድ በላይ በጨረሳቸው ኢትዮጵያዊያን ሕይወት ነው። ኢትዮጵያዊነት የቆየው፤ መንግሥቱ ኃይለማርያም ሀገራችንን እንድትበታተን ሀገር አውዳሚ የአስተዳደር መመሪያውን በተግባር ሲያውለው፤ ከመንግሥቱ ይልቅ ኢትዮጵያ ትበልጥብኛለች ብለው ሕይወታቸውን በሠጡ ኢትዮጵያዊያን ደም ነው። ባድሜ ላይ በቀሩት ወጣት ኢትዮጵያዊያን ደም ነው። ዛሬም ይኼ ፀረ-ኢትዮጵያ ገዢ ቡድን በየእስር ቤቱ በአጎራቸው ቆራጥ ኢትዮጵያዊያን ጀግንነት ነው። ዛሬም ሀገራቸውን ባገኙት መንገድ ለቀው በምድረ በረሃና በስደት እየረገፉ ባሉት ኢትዮጵያዊያን ሕይወት ነው። ኢትዮጵያዊ ያደረገን ይኼ ነው። ዛሬ ሀገራችንን ለመበታተን ይኼ ወገንተኛ አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት የሚተገብረውን ፀረ-ኢትዮጵያ አካሂያድ እምቢ ብለው በቆሙ ጀግኖች ሕይወት ነው። አድዋ ይኼ ነው፤ የማንነቴ ምሰሶ። ማቸነፋቸው ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት ባንድ ላይ ሀገራዊ ተግባር ማድረጋቸው ነው። ያ ነው አድዋ!

አድዋን የማከብረው ደም ስለተዘራበት ሳይሆን፤ ኢትዮጵያዊነትን ስላጎለበተልኝ ነው። ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ስለተነሱበትና ደማቸውን ስላፈሰሱበት ነው። ሴት ወንድ፣ ወጣት ሽማግሌ፣ ነጋዴ አርሶ አደር፣ ቄስ ወታደር ባንድ ላይ ሀገሬ ስላለበት ነው። ለወራሪ የሀገሬን አፈር አላስቀምስም ብለው፤ ቤታቸውን ጥለው፣ በወጡበት ሳይመለሱ ስለቀሩበት ነው። እህል ባገልግል፣ ስንቅ ባህያ፣ እግርን ያለጫማ፤ በጎራዴና በጦር ስለዘመቱበት ነው። አድዋን እነሱ በሕይወታቸው የኔ ኢትዮጵያ ስላደረጉልኝ፣ ቢቸፉም ኖሮ ስላቸነፉም፤ አድዋ የኔ ናት። ስላቸነፉም፤ አድዋ ኢትዮጵያዊነቴን በልቤ ሞልቼ ደረቴን እንድነፋ አድርጎኛል። አድዋ የኔ ናት። አድዋ የኔ ናት። አድዋ የኔ ናት።

በኢትዮጵያዊነት አቸናፊነቱ እኮ፤ አድዋ ኢትዮጵያዊነት አልበቃው ብሎ፤ ለዓለም ጥቁሮች ሰንደቅ ሆኗል! ጥቁርን እንደሰው አልቀበልም ያለውን የነጭ እብሪት፤ ሆን፣ እንደሰው ብቻ ሳይሆን፣ እንደእኩል ብቻ ሳይሆን፣ እንዳቸነፈው እንዲቀበል እንደኮሶ እየመረረው እንዲጋት አድርጎታል። ታዲያ አድዋ በኔ መከበር ይነሰው! አድዋ ኢትዮጵያዊነት ይነሰው! ኢትዮጵያዊነታችን ለመቅደላ፣ ለመተማ፣ ለዶጋሊ ይነሳቸው? አሁን የኛ ተራ ነው። አሁን ለኛ ኢትዮጵያዊነታችን የሚለመልመው፤ ለም መሬታችን ለባዕድ አይሠጥም ብለን ስንታገል ነው። አሁን ለኛ ኢትዮጵያዊነታችን የሚለመልመው፤ የሀገሬን ደንበር አላስነካም ብለን ስንቆም ነው። ኢትዮጵያዊነታችን የሚፈካው፤ ዘረኝነትን፣ መከፋፈልን፣ አድልዎንና ሙስናን ወጊዱ ብለን ስንመነጥራቸው ነው።

ኢትዮጵያዊነታችን ሕያው የሚሆነው አንዳችን ለአንዳችን ስንቆም ነው። ኢትዮጵያዊነታችን የሚኖረው ኢትዮጵያ ስትኖር ነው። አድዋ ይከበራል። ኢትዮጵያ እስካለች አድዋ አለ፤ አድዋ ኢትዮጵያ ናትና! ለዚህ ነው የማከብራት። በሕይወት እስካለሁ ድረስ አድዋን አከብራታለሁ።

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Opinions Tagged With: Left Column

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • ጎርጎራ – የመጻዒው ዘመን ሙሽራ! የዉበት ፈርጥ! January 17, 2023 04:18 pm
  • ሁለተኛው መስቀል አደባባይ January 17, 2023 04:13 pm
  • በአቡዳቢ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን January 17, 2023 04:08 pm
  • በንፋስ ስልክ ላፍቶ ስምንት የመሬት ሌቦች ተያዙ January 16, 2023 11:36 am
  • ሺሻ ሲያስጨሱ በተገኙ ሆቴሎችና የምሽት ጭፈራ ቤቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ January 16, 2023 08:50 am
  • በሐሰተኛ መታወቂያ የደኅንነት አባል ነን ብለው ሲያጭበረብሩ የነበሩ ተያዙ January 13, 2023 02:03 pm
  • ተሽከርካሪ ወንበር ለትግራይ – “ናይ ኣካል ጉዱኣት ተሽከርካሪ ዘለዎ ወንበር” January 12, 2023 07:17 pm
  • የአማራው ኩራት፣ የኢትዮጵያ ዘብ፣ የትህነግን ቅስም ሰባሪ! January 12, 2023 04:00 pm
  • በኢትዮጵያ ላይ የተጣሉ ማዕቀብ እና ሌሎች አስገዳጅ ሕጎች ሙሉ ለሙሉ ተሰረዙ January 12, 2023 01:52 pm
  • የቻይና ዕዳ ስረዛ “Payday Loan Diplomacy” ወይስ ኢትዮጵያን ያዳነ ተግባር? January 12, 2023 11:00 am
  • የአዲስ አበባ አስተዳደር ከቋንቋ ጋር በተያያዘ ውሳኔ አስተላለፈ January 12, 2023 10:46 am
  • “አምባሳደሩ” የቀድሞ ጌቶቻቸውን እንዲያቋቁሙ ተሾሙ January 11, 2023 03:47 pm
  • መከላከያ ሸኔን የሚዋጉ ሚሊሻዎችን አሠልጥኖ አስመረቀ January 10, 2023 05:37 pm
  • በሰባት ተጠርጣሪዎች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ January 10, 2023 03:36 pm
  • የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አቅጣጫ January 6, 2023 03:26 pm
  • “ከዕብሪቱ አስተንፍሰነዋል” – ኢሳያስ January 2, 2023 07:29 pm
  • [ኢትዮጵያን] “አስታክኮ ኤርትራን መውጋት ለሚፈልግ ኃይል አንተባበርም” January 2, 2023 07:11 pm
  • የ፰ ወር ሕጻንና ጨቅላ ወንዶች የሚደፈሩባት ትግራይ December 14, 2022 02:49 pm
  • “ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው” የደጎች አውራ የመቄዶኒያው ቢንያም በለጠ December 14, 2022 09:59 am
  • “የሀብት ምዝገባ መረጃው ለሕዝብ ክፍት ይደረግ “ December 13, 2022 10:30 am
  • የኢትዮጵያ ዓለምአቀፋዊ የሌብነት ደረጃ December 13, 2022 09:42 am
  • ለብረት አቅላጮች ለመሸጥ በኤሌክትሪክ የብረት ማማዎች ስርቆት የ100 ሚሊዮን ብር ኪሳራ December 13, 2022 09:26 am
  • በትግራይ የሰላም ስምምነቱን መሠረት ያደረገ የሽግግር ፍትሕ እንደሚፈጸም ተገለጸ December 13, 2022 09:20 am
  • ከ30 ሚሊየን ብር በላይ በሚሆን ሌብነት የተከሰሱት የደኅንነት መ/ቤት ሠራተኞች ክስ ተመሰረተ December 13, 2022 09:06 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2023 · Goolgule