የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጥንታዊው የሼክ አህመድ ሳለህ አልዛህሪ (ሎምባርዲያ ሬስቶራንት የሚገኝበት) ሕንፃ ቅርስ መሆኑን በባለሙያዎች አረጋግጦ ክብካቤና ጥበቃ እንዲደረግለት ሲያሳስብ ቢቆይም፣ ሰሞኑን ባወጣው ሰርኩላር ሕንፃው ቅርስ አይደለም በማለት የቀድሞውን ውሳኔ ሽሯል፡፡
ቢሮው ታህሳስ 25 ቀን 2006 ዓ.ም. ለአዲስ አበባና ዙርያዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ልማት ፕላን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ጽፎ በነበረው ደብዳቤ፣ ሕንፃው ቅርስ መሆኑን ገልጾ በማስተር ፕላኑ በቅርስነት እንዲያዝ አስታውቆ ነበር፡፡
ቢሮው በጻፈው ደብዳቤ ከፌዴራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ከቅርስ ምዝገባ፣ ቁጥጥርና ደረጃ ማውጣት ዳይሬክቶሬትና ከቅርስ ጥገናና እንክብካቤ ዳይሬክቶሬት፣ እንዲሁም ከራሱ ቢሮ በተውጣጡ ባለሙያዎች በዝርዝር ተጠንቶ የቅርስ መሥፈርት እንደሚያሟላ መረጋገጡን አስታውቆ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ታህሳስ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ የሕንፃውን ቅርስነት ያረጋገጠ መሆኑን ቢሮው ገልጾ፣ የማስተር ፕላን ጽሕፈት ቤቱ ሕንፃውን በቅርስነት እንዲያዝ ጠይቆ ነበር፡፡
በዚህ መሠረት የማስተር ፕላን ጽሕፈት ቤቱ እያዘጋጀ ባለው ማስተር ፕላን ላይ ሕንፃው ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ አድርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ ፕላን ኢንስቲትዩት በባህል ቢሮው ውሳኔ ላይ ተመሥርቶ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በሙሉ ሕንፃው ቅርስ መሆኑን አውቀው አስፈላጊው ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርጉለት ማሳሰቢያ ሰጥቶ ነበር፡፡
ነገር ግን ከወራት ቆይታ በኋላ የከተማው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ቀደም ሲል የደረሰበትን ውሳኔ በመሻር፣ ይህ ጥንታዊ ሕንፃ ቅርስ አለመሆኑን ጠቅሶ አዲስ ሰርኩላር ሰሞኑን አስተላልፏል፡፡
ቢሮው ለማስተር ፕላን ጽሕፈት ቤት፣ በግልባጭ ደግሞ ለከተማው መረጃ ፕላን ኢንስቲትዩት በላከው ደብዳቤ ሕንፃው ቅርስ በመሆኑ በማስተር ፕላኑ በቅርስነት እንዲመዘገብ መጠየቁን አስታውሷል፡፡ ነገር ግን ቢሮው፣ “በከተማችን እየተካሄደ ያለው ልማት መደናቀፍ የሌለበት በመሆኑና ሕንፃውም የቅርስነት መስፈርት የማያሟላ ስለሆነ በቅርስነት እንዳይመዘገብ የተወሰነ መሆኑን አውቃችሁ፣ እየተዘጋጀ ባለው ማስተር ፕላን ላይ በቅርስነት እንዳይመዘገብ፤” በማለት ጉዳዩን በጥልቀት መርምሮ የደረሰበት ነጥብ መሆኑን ገልጿል፡፡
በዚህ መነሻ የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ይህን ሕንፃ ጨምሮ በአካባቢው የሚገኙ ልዩ ልዩ ግንባታዎችን በማንሳት፣ በ10.6 ሔክታር መሬት ላይ የመልሶ ማልማት ፕሮጀክት ለማካሄድ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ፣ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ውሳኔ መነሻ በማድረግ ቦታውን ለማልማት መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
“ይህንኑ ደብዳቤ መነሻ በማድረግ ለክፍለ ከተሞችና ለሚመለከታቸው አካላት እንዲያውቁት በማድረግ የመልሶ ማልማት ሥራው ቀጥሏል፤” በማለት ኤጀንሲው በመግለጫው አስታውቋል፡፡
የክፍለ ከተማው መሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት ለሕንፃው ነዋሪዎች የሰጠው የመጨረሻ ቀነ ገደብ በመጠናቀቁ በሕንፃው ላይ የሚገኙ አብዛኛዎቹን ቤቶች አሽጓል፡፡ ነገር ግን በሕንፃው ላይ የሚገኙ ተከራዮችና የሼክ አህመድ ወራሾች ሕንፃው መፍረስ እንደሌለበት ብሎም እንዳይታሸግ ለማድረግ ወደ ፍርድ ቤት ሄደዋል፡፡ ሜክሲኮ አካባቢ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል አጠገብ የሚገኘው የሼክ አህመድ ሕንፃ በ1926 ዓ.ም. ነው የተገነባው፡፡ (ምንጭ: ሪፖርተር)
Leave a Reply