ያልተጠበቀ ባይሆንም እንዲህ ተጣድፎ የሚጠፋበትን ፈንጂ ለመርገጥ ማሰቢያ ያጣል ብየ አልገመትኩም ነበር፤ ግን ሆነ፤ ወያኔ የቀረችውን የመጨረሻ ጥይት ለመተኮስ ሌባ ጣቱን ምላጩ ላይ አስረግጧል። ቀድሞም ከቦታ ጠባቂነት የዘለለ ድርሻ ያልነበራቸውን ጠቅላይ ሚንስትር ገፋ አድርጎ በትረስልጣኑን የነጠቀው ወራሪው የወያኔ ጦር መሪዎች ቡድን እንደ ዘመነ መሳፍንቱ ሚካኤል ስሁል የፈቀደውን ሊያነግስ የጠላውን ሊያወርድ ከምንይልክ ቤተ መንግስት ገብቷል።
ቀድሞውንም በራሱ በፈጣሪው የተናቀውና የተናደው የይስሙላ “ህገ መንግስት “ ተብየ ባዶ ሰነድ ሙሉ በሙሉ በጠመንጃ ነካሾቹ የሰራዊት መሪዎች በፈረሰበት አገር የወያኔ ሰራዊት የሚከላከለው ሰነድ ሳይኖረው ቤት መንግስቱን መውረሩ የመሪዎቹን የዘረፋ ንብረት ከመከላከል የዘለለ ህዝባዊ ተለዕኮ የለውም።
በፈረሰና ህልውና በሌለው ሚንስትሮች ምክር ቤት ስም “ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” በሚል አምባገነናዊና ፋሽስታዊ አዋጅ አገሪቷ ሙሉ በሙሉ በወያነ ሰራዊት መዳፍ ስር ስትወድቅ ከምስለ ሰውነት የዘለለ ነፍስ የሌለው ፓርላማ ተብዬ ጉድ ፤ አንዳች ማለት አለመቻሉ የይስሙላውም ህገ መንግስት ግባተ መሬት መፈጸሙን በይፋ በማብሰር የጥፋቷ የመጨረሻ ቀለህ መቀባበሏንም አረጋግጦልናል።
ስለዚህ የሚጠብቁትም፤ የሚከላከሉለትም ህግና መንግስት በሌለበት ከተሸከሙት ጠብመንጃ ውጭ ህጋዊም ሆነ ህዝባዊ መሰረት የሌላቸው ወራሪ ወያኔዎች በመጭው ጊዜ ባንቀልባቸው አዝለው የሚያሾሩት “ጠቅላይ ሚንስትር” የሚባል አፈ-ወያነ ሊሰጡን ወይም ሙልጭ ብለው በለመደው ፈጣጣ አይናቸው እንደለመዱት በጠመንጃቸው ሊነዱን እያመቻቹን ነው።
ጨርሶ ያልገባቸው ወይም ፈቅደው ሊቀበሉት ያልቻሉት ፍርሀትን በሞት ጥሶ የወጣ ሁልቆ መሳፍርት ኢትዮጵያዊ ከፊታቸው እየጠበቃቸው መሆኑን ነው። ስለዚህ ጉልበተኞቹ የኢትዮጵያን ህዝብ በሌለና በፈራረሰ ህግና መንግስት ስም የሚያስፈራሩበት የህግም ሆነ የሞራል ብቃት ሊኖራቸው አይችልም፤ ራሳቸው ህገ-ወጥ ናቸውና።
ይልቁንስ የዘመናችን “ስሁሎች” ሊረዱት የሚገባቸው እውነት ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ እጣ ሳይሆን የወያነ እጣ የሚወሰነው በጉልበታቸው ወንበር ላይ በሚሰቅሉት “ጠቅላይ ሚንስትር” አንደበትና ድርጊት መሆኑን ነው። እንደ እስከዛሬው በፈራረሰና በማይሰራ ህገ-መንግስት ስም እያሳበቡ ኮርኩመውና ሸብበው ሲረግጡትና ሲመዘብሩት የነበረው ህዝብ ግርዶሹን ጥሶ ፍርህቱን አራግፎ የነጻነት ጎዳና ላይ መግባቱን እየጎፈነናቸውም ቢሆን መቀበል ነው። ያሻቸውን እየሾሙና እየሻሩ በህዝብ ቁስል እንጨት እየሰነቀሩ በሞቱ እያላገጡ መቀጠል ፈጽሞ እንዳበቃለት መረዳት ከተሳናቸው ሊስቧት በተዘጋጁት የመጨረሻ ጥይት ቀለህ የጣፈንታቸውን መራራ ጽዋ ለመጎንጨት ተዘጋጅተዋል ማለት ነው።
ማንም ይሁን ማን በባለነፍጦቹ ወያኔዎች የሚሾመው “ጠቅላይ ሚንስትር” ህጋዊ መሰረት የሌለው መሆኑን ተገንዝቦ በበዓለ ሲመቱ በሚያደርገው ንግግር “የኢትዮጵያ ህዝብ የጠየቀውን የስርዓት ለውጥ ጥያቄ የሚያስተናግድ ብሄራዊ እርቅና ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ጥሪ በድፍረት በማድረግ ራሱን ከምስለ-ሰውነት የዘለለ ባይምሮው የሚመራ ሰው መሆኑን እንደሚያሳየን ተስፋ እናድርግ። ካንደበቱ የሚውጡት ቃላቶችም መጭውን የኢትዮጵያ ህዝቦች የትግል አቅጣጫና የወያነን የመጨረሻ ጥይት መዳረሻ እንደሚያመላክቱ ልብ ሊለው ይገባል!!
ጌዲዮን በቀለ (Gedionbe56@yahoo.com)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply