ጥምል እየዞረ በሰማዩ ማገር
በመሬቱ ዙሪያ ዕውነት የሚናገር
ጠባሳው ያልጠፋ የታሪክ አሻራ
መሬቱ መሰለኝ ጠላት የሚያፈራ።
አገር በቀል ይሁን የሰው አገር ባዕዳ
ዐይን እየማረከ የሚጋብዝ እንግዳ
ከጥንት ጀምሮ እንደ እሚታወቀው
ጠላት የሚያፈራ ለምለሙ መሬት ነው።
ለምለሙ መሬት ነው ጦርነት አብቅሎ
ቤት አልቦ ያስቀረኝ ከቀዬ አፈናቅሎ።
ለም መሆኑ ቀዬ አፈረ – መሬቱ
ጠላቶቸን ጋብዞ ዛሬም እንደ ጥንቱ
ኮሪያው ይሁን ህንዱ ወይ የዐረቢያው ጉምቱ
እንዲያፈናቅለኝ ገፍትሮ በሀብቱ
ምክኒያት የሆነኝ ጫካውና ዱሩ
ጠላቴ ተግሬ ነው መባቀያ አፈሩ።
አያበቅሉ አብቅሎ አያፈሩ አፍርቶ
የሚያፈናቅለኝ ተጎጆየ አውጥቶ
ተግሬ ነው ጠላቴ ተቆምኩበት ምድር
ለምለሙ መሬቴ ገዳይ በሰናድር።
ማጣት ዕርዛቴን ሞቴን እንዲፈጥር
ተፈጥሮው አድርጎት የቆምኩበት ምድር
ለምላሜ ለብሶ ሜዳ እስከ ተራራ
ዐይን እየማረከ ጠላት እያፈራ
ለሙ መሬቴ ነው ኧረ እናንተ ሆዬ
የሚያፈናቅለኝ ካደግሁበት ቀዬ።
ከፍ ያለው በስልጣን በደሉ የከፋ
ዝቅ ያለው የመሬት በጉልበት ዘረፋ
ጠላቴ ተግሬ ነው በልፅጎ የፋፋ።
ጠላቴ ተግሬ ነው ተቆምኩበት መሬት
ተተክሎ ያደገ ገድሎ የኔን ህይዎት።
ወፍ ዘራሽ አቃቅማ እንደ አሽዋ አፍሶ
ባገረ መሬቱ እሾህ አልከስክሶ
መቆሚያ መሄጃ መራመጃ ነስቶ
ጠላቴ ተግሬ ነው የወጋኝ ተነስቶ።
ወደ ኋላ ዞሬ ስቃኘው ታሪኬን ከዘመናት ጋራ
በግብጽና በቱርክ በጣሊያን ወረራ
ከጥንት ጀምሮ ለክብሬ መደፈር
ጠላቴ ተግሬ ነው ሁሌም ያ ለም አፈር።
ሰኔ 2003
አብርሃም በየነ
መሬቶቻቸውን ተነጥቀው ተቀያቸው ተነቅለው ስደተኝነትን ለተዳረጉት ለጎደሮች፣ ለጋምቤላዎች፣ ለቤንሻንጉሎች፣ ለአፋሮች፣ ለኮንሶዎችና ለኦረሞ ገበሬዎች መታሰቢያ ትሁን።
abraham3106@comcast.net
Leave a Reply