ባገሩ የሚኮራ ፤ ሀገሩን አፍቃሪ
ለወገን ሟች ስፍሱፍ ፤ አብሮነት ዘማሪ
የነፍስ ስደተኛ ፤ እውነት አስመስካሪ
የሀገሩ ነገር ፤ የወገኑ እጣ
ሁሌ የሚያስጨንቀው ፤ ሲበዛ ግፍ ጣጣ
ስለተገለለ ፤ አማራጭ ስላጣ
እኛን ካልሆንክ ተብሎ ፤ ሕሊናው ተሸጣ
ደሞ ስለተገፋ ፤ ታይቶ እንደ ባላንጣ
አላፈናፍን ተብሎ ፤ ጅቡ እየተቆጣ
አላቃምስ ተብሎ ፤ በራብ እየተቀጣ
ወገን ሲለይበት ፤ ሆኖ ዘር መረጣ
ቢብሰው ተነሣ ፤ ለስደት ጎረፈ
ከሞት ጋር ተፋጦ ፤ ሞትን እያለፈ
ግፍ እየተጋተ ፤ እየተቀሰፈ
ገና ባልጸናለት ፤ በጨቅላ ትከሻ
ስንት ስቃይ ዐየ ፤ የጣር መጨረሻ
ወገኑን እያጣ ፤ የዓሣ ሲሳይ ሆኖ
በአራዊት ተበልቶ ፤ በድንገት ታድኖ
ስለተደፈረ ፤ እራሱን ኮንኖ
በራብ በውኃ ጥም ፤ እየቀረ ደብኖ
በኢሰብአዊ ግፍ ፤ በአውሬ አረመኔ
ለኩላሊት ልቡ ፤ ታርዶ በጭካኔ
ከዚህ የተረፈው ፤ ሲደርስ ያ ወገኔ
ከገባበት ሀገር ፤ ተአምር እያስጻፈ
ጎኑን ሳያሳርፍ ፤ ሳይዝ የተረፈ
አንቀው ሊመልሱት ፤ እየተጠረፈ
ባዶ እጁን ሊጥሉት ፤ እየተገፈፈ
ሊይዙት ሲያሳዱት ፤ ሲሮጥ እየከነፈ
ሀገር እንደጠላ ፤ እንደተጸየፈ
መመለስን ጠልቶ ፤ ዋ! ተንገፈገፈ
ወደ ሲዖል ባሕር ፤ እንደሚጣል ቆጥሮ
ለማምለጥ ሲሯሯጥ ፤ በነፍሴ አውጭኝ በሮ
ከገሃነም ጭፍራ ፤ ጽድቅ ከጨነገፈ
ትናንትን ከረሳ ፤ ነገን ካከሸፈ
ሊያመልጥ ሲበረግግ ፤ ዋ! ተንዘፈዘፈ
መንገድ ላይ ወደቀ ፤ ተደነቃቀፈ
በእሳት ጥይት አረር ፤ እየተገረፈ
የሞት ስደተኛው ፤ እየሮጠ ዐረፈ
ስንትን ሞት ተሻግሮ ፤ ሊያልፍለት አለፈ
ባዶ እጀን አልሄድም ፤ ቃሌ ካልሠመረ
አላሳፍራትም ፤ ብሎ እንደፎከረ
በናፍቆት ተቆልቶ ፤ ፍቅሯን እያዜመ
ተደፍቶ ቀረላት ፤ አስከሬን ተመመ
የሚታደግ አጥቶ ፤ ታፋሪ ተፈሪ
የኛ ብሎ የሚለው ፤ መንግሥት ተቆርቋሪ ፡፡
ሀገር እርምሽን አውጭ ፤ ይብቃሽ ይቅር ምጡ
እናት አባት ወገን ፤ ሐዘን ተቀመጡ
ሳተና ልጆችሽ ፤ የአንችን ቀን ሊያመጡ
መልሰው ላያዩሽ ፤ ቀሩ እንደወጡ ፡፡
ኅዳር 3 / 2006 ዓ.ም.
Leave a Reply