- ማነው የዋሸው? ጃዋር? የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ወይስ የኦዴፓ ምክትል ሊቀመንበር?
- መንግሥት በሕዝብ ገንዘብ ጥበቃ የሚያደርግለትን ጃዋርን በሌሊት የሚከብበት ምን ምክንያት አለ? ማለቴ ተከቦ የተቀመጠው በመንግሥት ጠባቂዎች አይደለም ወይ?
- ለምን ጃዋርስ ተፈጠረ የተባለውን ነገር ሆን ተብሎ በመንግሥት የተቀነባበረና “እኔን ለማጥቃት የተፈጸመ ድርጊት ነው” አለ? ማለቴ ይህ ዓይነት ጥርጣሬ ካለው እንዴት በመንግሥት ታጣቂዎች እየተጠበቀ ዕንቅልፍ ወስዶት ያድራል? እንዴት እንዲህስ ሊያስብ ይችላል? ወይስ ጠባቂዎቹን የራሱ አድርጓቸዋል?
- ከመቼ ወዲህ ነው የመንግሥት ታጣቂዎች በመንግሥት ተመድበው ሳለ ራሱ መንግሥት፤ ለዚያውም እንደ ጃዋር አገላለጽ ዋናው ኮማንደር ለቃችው ውጡ ሲላቸው እንቢ ሊሉ የቻሉት? ከመንግሥት ይልቅ ታዛዥነታቸው ለጃዋር ያደላ ነው ማለት ነው? በዚህ ዓይነት መንግሥት በሌሎች ሥፍራዎች ያሉትንስ ወታደሮች ማዘዝ ተስኖታል? ከመቼ ወዲህ ነው መንግሥት የመደበው ፖሊስና ወታደር ትዕዛዝ የሚቀበልበትን ሰዓት የሚመርጠው? ምነው ስንቱን በእኩለ ሌሊት ቤቱን ሰብረው እያዳፉ ይወስዱ የለምንዴ?
- ይሄ ትእዛዝ ሰጠ የተባለው ዋና ኮማንደር ማን እንደሆነስ አይታወቅም ወይ? ከታወቀስ መንግሥት እንዴት አላውቅም አለ?
- የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የግል ጥበቃዎችን ስናነሳ ቆይተናል ብለው ቀድሞም የተወሰነ ነገር መሆኑን ገልጸዋል፤ በጃዋር ላይ ግን ይህ ትዕዛዝ አልተሰጠም ካሉ ታዲያ ማን አዘዘ? ለምንስ ከተወሰነ በጃዋር ላይ ቀድሞ ሳይፈጸም ቀረ? ወይስ ትዕዛዝ ተላልፎለት ጭለማን ተገን ለማድረግ አድፍጦ ይጠብቅ የነበረ የመንግሥት አካል ነበር?
- አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የመንግሥት የደህንነት ባለሥልጣን ድርጊቱ በሌሊት መፈጸሙ ልክ ባይሆንም ትእዛዙ ግን ቀድሞ መሰጠቱን ከተናገሩ ክፍተቱን የሚጠቀም ድብቅ ኃይል በመንግሥት ውስጥ መኖሩን አያሳይም ወይ?
- የአቶ ሽመልስ ይቅርታስ መነሻው በመንግሥት የተወሰደው እርምጃ ስህተት ነው ከሚል ነው? ወይስ በሌሊት መፈጸሙ? ጥበቃው ይቀጥልልሃልን ምን አመጣው? እንዲያ ከሆነ ለምን የመንግሥት አካላት እርስ በርሱ የሚጋጭ መግለጫ መስጠት አስፈለጋቸው?
- ጃዋርስ የተፈጠረውን ነገር ለመንግሥት ባለሥልጣናት በተለይም ከኦዴፓ ሰዎች ጋር ካለው ቅርበት አንጻር ችግሩን በውስጥ መስመር ከእነሱ ጋር መነጋገር እና መፍታት እየቻለ ለምን በማህበራዊ ድረ ገጽ ለደጋፊዎቹ የድረሱልኝ ጥሩ አቀረበ? አቅሙን ሊያሳይ? ወይስ በፍርሃት ከመደናበር?
- ጃዋር ቤት አካባቢ ደረሰ የተባለው ከበባ ምሽቱን ከሆነ የተፈጸመው ለምን ፖሊስና የመንግሥት አካላት ሌሊቱን ሁኔታውን በማረጋጋት ሕዝቡ ወደ አደባባይ ሳይወጣ በፊት አፋጣኝ ምላሽ አይሰጡም ነበር? የአቶ ሽመልስ ካመሻሸ መግለጫ መስጠት ምን ይሉታል? ከተበጠበጠ በኋላ ማንን ሊያረጋጉ ነው?
- በሕዝቡ መካከል የእርስ በርስ ግጭት እንዲነሳ፣ በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት ማነው ተጠያቂው?
- መንግሥት በምን ምክንያት ነው ኪሱ በዶላር ላበጠ ሰው ከድሃ ሕዝብ በተገኘ የግብር ገንዘብ ደሞዝ እየከፈለ ለጃዋር ለዚህን ያህል ጊዜ ጥበቃ የሚመድበው?
- ጃዋር በቅርቡ ለህወሃት ያቀረበው የአጋርነት ጥያቄ፣ በLTV ቀርቦ ዐቢይ ላይ ያንጸባረቀው አቋም እና ድንፋታ፣ የጃዋር የድረሱልኝ ጩኸት እንዳሰማ ህወሃት በመግለጫ አለሁልህ ማለቷ ብዙዎች እንደሚሉት የተጠነሰሰ ነገር ይኖር ይሆን? ክስተቱ ከዐቢይ የውጭ ጉዞ ጋርስ ይገናኙ ይሆን? ተደጋግሞ እንደተስተዋለው በአገሪቱ የተከሰቱ ዋና ዋና ሰበር ዜናዎች ዐቢይ እግሩ ወጣ ማለቱን ተከትለው የሚመጡ ስለነበሩ ነው። እንግዲህ የእኔ አዕምሮ ውስጥ እነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኙ እየተንገዋለሉ አብረውኝ ያድራሉ። ለተጎዱት ሰዎች ከማዘን ባለፈ ምን ለማለት ይቻላል።
ከላይ የተዘረዘሩት ጥያቄዎች ምላሻቸው ምንም ይሁን ምን መንግሥት ግን በአገሪቱ ውስጥ የሕግ የበላይነት ለማስፈን የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ ይገባል። ሕዝቡም ለመብቱ ብቻ ሳይሆን ለሕግ አክባሪነትም አብሮ ሊቆም ይገባል።
ያሬድ ሃይለማርያም (የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)
Leave a Reply