
የፌደራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ የ2014 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲትን በተመለከተ ተቋማቸው ያካሄደውን የኦዲት ሪፖርት፣ ማክሰኞ ሰኔ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል፡፡
ለፓርላማው የቀረበው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ የ2014 ዓ.ም. በጀት አፈጻጸምን በተመለከተ በተደረገው የኦዲት ሥራ ስድስት ተቋማት አስተያየት ለመስጠት ያልተቻለባቸው ሲሆኑ፣ 19 ተቋማት ደግሞ የጎላ ችግር ያላባቸው ሆነው በመገኘታቸው ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ሒሳባቸው የጎላ ችግር ያለበት በመሆኑ ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት ከተሰጠባቸው ተቋማት መካከል
- የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣
- የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ፣
- የኢንፎርሜሽንና መረብ ደኅንነት አገልግሎት
- የፌዴራል ፖሊስ
- ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ፣
- ጂንካ ዩኒቨርሲቲ፣
- ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ፣
- ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ፣
- ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ፣
- አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣
- ቦሌሆራ ዩኒቨርሲቲና
- የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ይገኙበታል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር አስተያየት ለመስጠት አልቻልኩባቸውም ካላቸው ተቋማት መካከል
- የሪፐብሊኩ የጥበቃ ኃይል፣
- አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣
- ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣
- የቀድሞው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣
- የአደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽንና
- የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አሉበት፡፡
ከአንድ ዓመት እስከ ስድስት ዓመት ዕድሜ ያለውና ለመንግሥት ገቢ መደረግ የነበረበት 13.4 ቢሊዮን ብር ውዝፍ የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ዕዳ መኖሩ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
የተሟላ ወጪ ሳይቀርብ በወጪ መዝግበው የተገኙ መሥሪያ ቤቶች
- የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ 124 ሚሊዮን ብር፣
- የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር 65 ሚሊዮን ብር፣
- የአደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን 64 ሚሊዮን ብር፣
- የሰመራ ጉምሩክ ቅርንጫፍ 7.9 ሚሊዮን ብር፣
- የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን 5.6 ሚሊዮን ብር፣
- ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ 4.8 ሚሊዮን ብር፣ በድምሩ 307.5 ሚሊዮን ብር የተሟላ ወጪ ሳይቀርብ በወጪ መዝግበው የተገኙ መሥሪያ ቤቶች ናቸው ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል ከደንብና ከመመርያ ውጪ ያላግባብ ክፍያ ከፈጸሙ ተቋማት መካከል
- የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ 30 ሚሊዮን ብር፣
- የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ 22 ሚሊዮን ብር፣
- የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 11.8 ሚሊዮን ብር፣
- የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን 7.6 ሚሊዮን ብር፣
- የቤተ መንግሥት አስተዳደር 6.5 ሚሊዮን ብር፣
- አርሲ ዩኒቨርሲቲ 6.1 ሚሊዮን ብር፣ በድምሩ 134.2 ሚሊዮን ብር ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የግዥን ሕግ የጣሰ ክፍያ 592.4 ሚሊዮን ብር
የመንግሥት የግዥ አዋጅ ደንብና መመርያ ያልተከተሉ ግዥዎችን የፈጸሙ 82 ተቋማት በሪፖርቱ የተጠቀሱ ሲሆን፣ ከእነዚህ መሥሪያ ቤቶች የተገኘው የግዥን ሕግ የጣሰ ክፍያ 592.4 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ተቋማቱ
- ጉምሩክ ኮሚሽን፣
- ጂንካ ዩኒቨርሲቲ፣
- ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ፣
- የኢንፎርሜሽን መረብና ደኅንነት አገልግሎት፣
- የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካደሚና
- ቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ ናቸው፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት በተከፋይ ሒሳብ ተመዝግበው የተገኙ ነገር ግን ዝርዝር ማስረጃ ባለማቅረቡ የሒሳቡን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ እንዳልቻለ ያቀረቡ ሲሆን፣ ከእነዚህ ተቋማት መካከል
- የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አንድ ቢሊዮን ብር፣
- የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 583 ሚሊዮን ብር፣
- የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር 131.8 ሚሊዮን ብርና
- ጉምሩክ ኮሚሽን 96.5 ሚሊዮን ብር ይገኙበታል፡፡ በድምሩ 1 ቢሊዮን 903.5 ሚሊዮን ብር ነው።
ከተደለደለላቸው በጀት በላይ የተጠቀሙ መሥሪያ ቤቶችም በሪፖርቱ የተጠቀሱ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል
- ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ 358.9 ሚሊዮን ብር፣
- ዲላ ዩኒቨርሲቲ 125 ሚሊዮን ብር፣
- ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ 139.9 ሚሊዮን ብር፣
- ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ 166.7 ሚሊዮን ብር፣
- አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 113 ሚሊዮን ብር ናቸው፡፡ በድምሩ 903.5 ሚሊዮን ብር ነው።
የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በ2014 ዓ.ም የተፈቀደላቸውን በጀት መጠቀም ሲገባቸው ባለመጠቀማቸው የተገኘው አጠቃላይ ገንዘብ 35 ቢሊዮን ብር መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
በጀት ሥራ ላይ ካላዋሉ መሥሪያ ቤቶች
- የመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር 8.9 ቢሊዮን ብር፣
- የገንዘብ ሚኒስቴር 6.3 ቢሊዮን ብር፣
- የጤና ሚኒስቴር ሦስት ቢሊዮን ብር፣
- ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን 1.2 ቢሊዮን ብር፣
- የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አንድ ቢሊዮን ብር፣
- የትምህርት ሚኒስቴር 915 ሚሊዮን ብር፣
- የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር 599 ሚሊዮን ብር ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ዋና ኦዲተሯ በጀት ተከፈቀደ በኋላ አለመጠቀም የታቀዱ ሥራዎች ሳይከናወኑ ሊቀሩ ስለሚችሉና ተቋማትም ዓላማቸውን እንዳያሳኩ ስለሚያደርጋቸው፣ የበጀት ዝግጅትና የአጠቃቀም ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡
የተሽከርካሪ አጠቃቀምና አያያዝን በተመለከተ በሚያብራራው የኦዲት ሪፖርት በመንግሥት ተቋማት ውስጥ
- 188 ተሽከርካዎች ሊብሬ ያልቀረበበባቸው
- 694 ተሽከርካሪዎችና 56 ሞተር ብስክሌቶች ያለ አገልግሎት ወይም በብልሽት የቆሙ
- የባለቤትነት መታወቂያ ደብተራቸው በሌሎች መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶች ስም የሆኑ 275 ተሽከርካሪዎች፣
- የነዳጅ መቆጣጠሪያ (ጌጅ) የሌላቸው 44 ተሽከርካሪዎች፣
- የመድን ዋስትና የሌላቸው ወይም ያልተገባላቸው አሥር መኪኖች ይገኙበታል ተብሎ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
የኦዲት ሪፖርቱ ከተሰጠ በኋላ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ አባል አቶ ሙሉቀን አሰፋ፣ ‹‹በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ አስተባባሪነት በሚመሩ የሜጋ ፕሮጀክቶች ጉዳይ የገንዘብ አሰባሰብና አወጣጥን በተመለከተ የመንግሥት የፋይናንስን አዋጅ ደንብና መመርያ ተከትሎ እየተሠራ ስለመሆኑ ኦዲት አድርጋችሁ ከሆነ የኦዲት ሪፖርቱ ቢገለጽልን፣ ካላደረጋችሁ ደግሞ ኦዲት ላለማድረግ ምክንያታችሁ ምንድነው?›› በማለት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተሯ ወ/ሮ መሠረት ለተነሳው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ኦዲት ኣላደረግንም፣ ያላደረግንበት ምክንያት ምንድነው? የፌደራል ዋና ኦዲተር ተግባርና ኃላፊነት የመጀመሪያው በተከበረው ምክር ቤት የፀደቀውን በጀት የክዋኔ ኦዲት ማድረግ፤›› ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪ ደግሞ የመንግሥት ተቋማትም ይሁኑ የልማት ድርጅቶች በአዋጅ በተሰጣቸው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት የክዋኔ ኦዲት እንደሚደረግና ሪፖርት እንደሚቀርብ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ ቅድሚያ በተሰጠን ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት እንሄዳለን፡፡ አሁንም ግን እነዚህን ፕሮጀክቶች በተመለከተ የተመዘበረና የጠፋ ነገር ካለ በኦዲት የሚታለፍ ተቋም ስለሌለ፣ የፕሮጀክቶቹ ስምና የጎደለው ገንዘብ በግልጽ ከቀረበልን ለማየት ዝግጁ ነን፤›› ብለዋል፡፡ (ሪፖርተር)
በተዘጋው የበጀት ዓመት የባከነው ገንዘብ ይህም ማለት የተሟላ ወጪ ሳይቀርብ በወጪ የተመገበው፤ ከደንብና ከመመርያ ውጪ ያላግባብ ክፍያ የተፈጸመው፤ የግዥን ሕግ የጣሰው ክፍያ፤ የሒሳቡን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ያልተቻለበት እና ከተደለደለላቸው በጀት በላይ የተጠቀሙ መሥሪያ ቤቶች በአጠቃላይ የባከነው ብር 3 ቢሊዮን 841 ሚሊዮን ብር ነው።
ከሁሉ የሚያስደንቀው ሒሳባቸው የጎላ ችግር ያለባቸው ተብለው ከተጠቀሱት መሥሪያ ቤቶች በቀዳሚነት የተጠቀሰው የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መሆኑ ነው። መሥሪያ ቤቱ የድርጅቱ መፈክር አድርጎ የሚጠቀመው “ከሙስና የጸዳች ኢትዮጵያ” የሚል መሆኑ ይታወቃል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply