በአሜሪካ የደቡብ ካሮላይና ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማ የሸንጎ ሕንጻ ላይ ከ50 በላይ ሲውለበለብ የነበረው ሠንደቅ አርብ ወረደ፡፡ “ውሸት ለዘላለም መቆየት አይችልም፤ የዘረኝነት ምልክት እና ዘረኝነት መፍረስ ይገባቸዋል” በማለት የሠንደቁን መውረድ የደገፉ ተናገሩ፡፡
በእንግሊዝኛው አጠራር “የኮንፌዴሬት” ሠንደቅ የሚባለው በአሜሪካ የእርስበርስ ጦርነት ወቅት ከኅብረቱ ለመለየት የፈለጉ ግዛቶች የራሳቸውን ፕሬዚዳንት መርጠው ከኅብረቱ ደጋፊዎችና አብርሃም ሊንከን ጋር ጦር በገጠሙበት የተጠቀሙበት ሠንደቅ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት አብርሃም በአሜሪካ ውስጥ የተንሰራፋውን በዘር ላይ የተመሠረተውን ባርነት ለመደምሰስ ህግጋትን እያወጡ በነበሩበት ወቅት በባሪያ ፈንጋይነት የሚታወቁት የደቡብ ጠቅላይ ግዛቶች የባርነትን መወገድ በመቃወም ከኅብረቱ ለመገንጠል በመፈለጋቸው በአሜሪካ የእርስበርስ ጦርነት ተቀሰቀሰ፡፡
ጥቁሮችን እጅግ አሠቃቂና ፍጹም ኢሰብዓዊ በሆነ መልኩ ሲያሰቃዩ፤ በግፍ ሲገድሉ፤ ከነህይወታቸው በእሣት ሲያቃጥሉ፤ ሴቶቻቸውን ቀን በጥጥ ለቀማና በመሳሰለው ሥራ በሃሩር በግፍ ሲያሰሩ ቆይተው ማታ ደግመው ይደፍሩ የነበሩ፤ የተወሰነላቸውን ጥጥ በቀኑ መልቀም ያልቻሉ ሌሊቱን ጀርባቸው እስኪተለተል ሲገርፉ የነበሩ፤ በነጋታው ልብሳቸው በደም ርሶ ከቆዳቸው እንደተጣበቀ በጥጥ ለቀማ እንደገና እንዲሰማሩ ግፍ ሲፈጽሙ የነበሩ፤ በነጮች ሰፈር መንገድ ላይ ሲሄዱ በመገኘታቸው ብቻ ከነህይወታቸው በእንጨት አስረው በእሣት እያቃጠሉ የደስታ መጠጥ ሲጠጡ እና የፍም ጥብስ እየበሉ በሰው ስቃይ ሲዝናኑ የነበሩ፤ … ጥቁሮች ነጻ መውጣት የለባቸውም በማለት ለጦርነት ሲሄዱ የተጠቀሙት ሠንደቅ ነበር ይህ “የኮንፌዴሬት” ሠንደቅ የተባለው፡፡
በደቡብ ካሮላይና ግዛት በቅርቡ በቤተክርስቲያን በጸሎትና መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ የነበሩ ጥቁሮችን የገደለው ነጭ ወጣት ይህንን የግፍ ሠንደቅ ይዞ የበላይነቱን ማሳያ አድርጎ የተነሳበት ፎቶ ከተለቀቀ ወዲህ ይህ ሠንደቅ ከመንግሥት ሕንጻ ላይ እንዲነሳ የቀረበው ሃሳብ ከፍተኛ ክርክር አስነስቶ ነበር፡፡ የጠቅላይ ግዛቱ ገዥ በውሳኔው ላይ ፊርማቸውን በማስቀመጥ ካጸደቁት በኋላ የግፍና የደም እንዲሁም የሰቆቃ መለያ የሆነው ሠንደቅ አርብ በይፋ ወርዷል፡፡
በሥነሥርዓቱ ላይ የነበሩ የግፉ ሰለባዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ “ይህ ሠንደቅ የክፍፍል፣ የዘር፣ የወገንተኝነት፣ አንዱ ከሌላው የበለጠ ወርቅ ዘር ስለሆነ ገዢ መሆኑን የሚያሳይበት፣ የርኩሰት መለያ ነው፤ መውረዱ ተገቢ ነው” ብለዋል የጥቁር ሰብዓዊ መብት ተከራካሪ፡፡
“አሜሪካ የተገነባችው በዘር ላይ ነው፤ የዘረኝነት ሥርዓት እና ምልክቱ ሁሉ ደግሞ መፍረስ አለበት” በማለት የጥቁር ወጣቶች ኅብረት ሃላፊ ተናግሯል፡፡ “ውሸት ለዘላለም መኖር አይችልም፤ ይህ ሠንደቅ የውሸት መለያ ነው” በማለት ለጥቁሮች መብት የሚከራከረው ድርጅት ኃላፊ ተናግረዋል፡፡
“ግፍ፣ ሰቆቃ፣ ሃዘን፣ ስቃይ፣ መታሰር፣ መገደል፣ አምባገነንነት፣ ዘረኝነት፣ ከፋፋይነት፣ እና እነዚህን የሚወክሉ መለያዎችና ምልክቶች ሁሉ የፈለገ ቢያደርጓቸው ቀናቸውን ጠብቀው ከተሰቀሉበት ከነሰቃዮቹ መውረዳቸው አይቀርም” በማለት የሠንደቁን መውረድ አስመልክቶ አንድ አዛውንት ጥቁር የተናገሩት አሁንም በተመሳሳይ ሠንደቅ ዓላማ ምልክትነት እየተጨቆኑ ለሚገኙ ሁሉ ተስፋን የሚፈነጥቅ ሆኗል፡፡
ይህንን ሠንደቅ ዓላማ ከሌሎች የአሜሪካ ደቡባዊ ጠቅላይ ግዛቶች የማውረድ እንቅስቃሴ በሰፊው ተጀምሯል፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Leave a Reply