
ከጅብ ከበሮ የተሰራ አታሞ ዘወትር እንብላው፤ እንብላው ይላል የሚል ተረት ሰምቻለሁ ልበል? አዎ፤ ሳልሰማ አልቀርም። ሀሳቡም ግን ጅብ ቆዳ ሆኖ እንኳን (ቆዳ ሆኖ ብቻ አይደለም አታሞ ተለጉሞበትም) ያው የተፈጥሮ እንብላ ባይ ባህሪውን አይተውም ማለት ይመስለኛል። ያው ቢሞትም ቆዳው የጅብ ነዋ።
ይህን ምሳሌ ያስታወሰኝ የሰሞኑ የአምስት የዖሮሞ ድርጅቶች ያወጡት ጠብ ያለሽ በዳቦ አይነት መግለጫ ነው። በእርግጥ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች አይነተኛ ተግባር ምናልባትም ቋሚ ስራ መግለጫ ማውጣት ስለሆነ ድርጅቶቹ ያው እንደለመደው ሰብሰብ ብለው እስቲ መግለጫ እናውጣ ቢሉ ያባት ይባል ነበር። የነዚህኞቹ ግን የዘር አዋጅ እንጂ መግለጫ የሚባል ስላልሆነ በእውነቱ በጥብቅ የሚያነጋግርም የሚያስተዛዝብም ምናልባትም ደግሞ ህግ ካለም በህግ የሚያስጠይቅ ግዴለም አቅልለን እንመልከተው ካልን ደግሞ ታላቅ የፖለቲካ ነውር ነው።
በዳይ ተበዳይ፣ ገዳይ አጋዳይ፣ አጥፊ ጨፍጫፊ ሳንል ሁሉን ይቅር ለግዜር ብለን በፍቅር አዲስ መንገድ እንጀምር፤ አርባጉጉ በደኖ፣ ጉዳፈርዳ ጨለንቆ ሳንል ያለፈውን ጠባሳ ለታሪክ አበሳ ወደ ኋላ ጥለን ባዲስ መንፈስ የጋራ ሀገራችንን እንገንባ በምንባባልበት በዚህ መልካም ጊዜ ይህን የመሰለ የጠብ ድግስ ማሰናዳት ምን ይሉታል። የዖሮሞ ህዝብ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር ሆኖ የጠብና ጥላቻ ታሪክን በመለወጥ ጣና ኬኛ ኢትዮጵያ ኬኛ እያለ የሰላምና የፍቅር ዜማ ሲያዜም የነዚህ ዖሮሞ ድርጅቶች ሰይፍ አንሱ እንጫረስ ጥሪ የጤና ነው። ትላላችሁ? ገና ሩጠው ያልጠገቡ ለጋ የዖሮሞ፤ ያማራና ሌሎችም ዜጎች የረገፉትስ ለዚህ ነበር? የነዚህ ቀንበጥ ወጣቶች ደም ሳይደርቅስ አዲስ እልቂት መሻት ከእድሜ ጠገብ የዖሮሞ ፖለቲከኞች የምንጠብቀው ነው?
እርግጥ መግለጫውን (ምን መግለጫ የጦርነት አዋጅ ልበለው እንጂ) ለማውጣት በአዲስ አበባ ከተሰበሰቡት የዖሮሞ ድርጅቶች ከጥቂት ግለሰቦች በቀር ብዙዎቹ ለእልቂትና ግጭት አዲስ አይደሉም። በዖሮሞ ህዝብ ስም ብዙ የሰሩ ናቸው። እናም ጭር ሲል አልወድም ቢሉ ላይገርም ይችላል። ግን የዖሮሞ ህዝብ ከወንድሞቹ ጋር ደም ቢፋሰስ ምን ይጠቀማሉ? የዚህ ደግ ህዝብ የመከራ ዘመንስ ቢያበቃ ምን ይጎዳሉ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል።
ፍቅር፣ መቻቻልና ሰላም ከምንጊዜውም በላይ እጅግ አስፈላጊ በሆነበት በዚህ ወቅት ወደኋላ ሄዶ የቂም ድሪቶ መጎተት አያስፈልግም እንጂ ይህንን መርዘኛ መግለጫ ካወጣው ስብስብ መሃከል እኮ አያሌ ኢትዮጵያውያንን በዘር ለይቶ የጨፈጨፉና ያስጨፈጨፉ ግፈኞች አይኖሩም ብላችሁ ነው? እነዚህ ሰዎች ደም ካላዩ ህልውና የላቸውም። የዖሮሞ ህዝብ ከሌላው ወገኑ ጋር ሰላም የሆነ ቀን አይናቸው ደም ይለብሳል። የህልውናቸ ፍፃሜ የደረሰ ያህል እረፍት ያጣሉ። ለነርሱ የህዝብ ግችት የህልውና ዋስትናቸው ነው። እንዲያ ባይሆን ኖሮ እዚህም እዚያም በሰበብ ባስባቡ የንፁሃን ደም በሚፈስበት በዚህ ወቅት፣ ህዝብ በፍቅርና ሰላም እንዲቀራረብ በሚለፋበት በዚህ ወቅት፣ እርስ በእርስ በመጠፋፋት ሀገር እንዳይጠፋ ጀግኖች የዖሮሞ ልጆች እየወደቁ እየተነሱ ባሉበት በዚህ ፈታኝ ጊዜ፣ የጦርነት አዋጅ የሚመስል መግለጫ ተብዬ የነገር ፍለጋ ሀተታ መፃፍ ያስፈልግ ነበር? በባህሪያቸው በኢትዮጵያውያን የእርስ በርስ ግችት ሲያተርፉ የኖሩና የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም የሚያከስራቸው ቡድኖች ባይሆኑ ኖሮ በሰላም ጊዜ ብቻ በጥሞና ክርክርና ውይይት መቀመጥ ያለባቸውን ስሜት የሚያስቆጡ ኮርኳሪ አጀንዳዎችን መጎተት ያስፈልግ ነበር። እነዚህ ቡድኖች በእርግጥ ለዖሮሞ ህዝብ ሰላምና ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በፍቅር እንዲኖር የሚመኙ ቢሆኑ ኖሮ በዚህ ደግ ህዝብ ላይ ሌላው ወገን ጥርጣሪ የሚችር ተንኳሽ እና መርዘኛ ፕሮፓጋንዳ መዝራት ይገባ ነበር?
እነዚህ ሰዎች የደም ሰዎች ባይሆኑ ኖሮ ያላበሳቸው ለተቸፈቸፉ ህጻናት፣ ክብራቸው በገዛ ቀያቸውና ብታቸው ለተደፈሩ ለታረዱ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው አንዲት የሀዘን መግለጫ የምትሆን የሰባዊነት ማሳያ ቅንጣት ቃል ሊተነፍሱ እንዴት ህሊናቸው ያምፅባቸው ነበር? እናም ከጅብ ቆዳ የተሰራው ከበሮ እንብላው እንብላው እንደሚል ሁሉ በደም ታሪክ የተሰሩ ቡድኖችም ዛሬም ደም ደም ቢሉ ያሳዝን ይሆናል እንጂ አይገርምም።
እነዚህ ቡድኖችና ከነሚድያቸው ለጦርነት አዋጅ አዲስ አበባ የገቡ መሰል ድርጅቶች ከለከፋቸው የህዝብ ደም ሱስ ሌላ ይህን ህዝብ የሚያቃቅር ክፉ መግለጫ በዚህ ወቅት እንዲያወጡ የገፋቸው ተጨማሪ ምክንያት ሳይኖራቸው አይቀርም።
ይህም የዖሮሞን ህዝብ ጨምሮ የኢትዮጵያውያንን ሁሉ ልብ የማረከው የነዶክተር አቢይና ለማ መገርሳ የፍቅርና የሰላም ጥሪ ያሳደረባቸው ስልጣን የማጣት ጉጉት ነው። የነዚህ ጀግና የዖሮሞ የለውጥ ሀይሎች ከልሎች ወንድሞቻቸው ጋር ሆነው ያሳዩት ተጋድሎ ያስገኘላቸው የህዝብ ድጋፍ ለነዚህ የድል አጥቢያ አርበኛ የዖሮሞ ድርጅቶች የስልጣን እርካብ ሊያደርጉት ያቀዱትን የዖሮሞ ህዝብ ድጋፍ የሚያሳጣቸው ስለመሰላቸው በፍርሃት ተንጠዋል። በመሆኑም በፍቅር ያልማረኩትን የዖሮሞ ህዝብ የጠብ ጎራ ፈጥረው ከጎናቸው እንዲሰለፍ ለማድረግ የጥላቻ መርዝ ከመቀመም የተሻለ መንገድ ይፈልጉ ዘንድ ተፈጥሯቸው አልፈቀደላቸውም። እናም ከዖሮሞ ህዝብ የተገኙ የለውጥ መሪዎቹን ያለጥርጣሬ ሆ ብሎ የደገፈውን ኢትዮጵያዊ እነሆ ዖሮሞን ሊያጠፋ ተነሳ ሲሉ አሟረቱ። እግዚአብሄር ይቅር ይበላቸው።
ቸር ያሰማን ጃል
zobar2006@gmail.com
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply