በቴክሳስ ጠቅላይ ግዛት በቪክቶሪያ ከተማ መሰጊዳቸው ለተቃጠለባቸው ሙስሊሞች በከተማዋ የሚገኘው የአይሁድ ምኩራብ በሩን ከፈተላቸው፡፡
እንደ ሲኤንኤን ዘገባ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ በቪክቶሪ ቴክሳስ የሚገኘው እስላማዊ ማዕከል (መስጊድ) ቃጠሎ ደርሶበት ነበር፡፡ ይህንን የተመለከቱ በከተማው የሚገኘው የአይሁድ ማኅበረሰብ አባላት የአምልኮ ቦታቸውን ለሙስሊም ወገኖቻቸው መሰብሰቢ እንዲጠቀሙበት የምኩራባቸውን ቁልፍ ሰጥተዋቸዋል፡፡
“አሁን ያገኘነውን ዓይነት ዕርዳታና ድጋፍ አናገኝም ብዬ በፍጹም አልተጠራጠርኩም” ያሉት የእስላማዊ ማዕከሉ ፕሬዚዳት ዶ/ር ሻሒድ ሐሽሚ ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው የቀዶ ጥገና ባለሙያና የአይሁድ ቤተመቅደስ አባል የሆኑት ዶ/ር ጌሪ ብራንፍማን ወደ ዶ/ር ሻሒድ ቤት በመሄድ ቁልፉን አስረክበዋቸዋል፡፡
መስጊዱን እንደገና ለመሥራት ከዘጠና አገራት ለአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ዕርዳታ በማግኘታቸው የተደነቁት የመስጊዱ ኃላፊ ከቪክቶሪያ ከተማ ነዋሪዎች ያገኙት ድጋፍ የሚጠብቁት የነበረና ከማኅበረሰቡ ጋር ካላቸው ግንኙነት አንጻር የሚኮሩበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከእንደዚህ ዓይነት መከራ ውስጥ ይህንን የመሰለ ትብብርና መረዳዳት መታየቱ በርካታዎችን አስገርሟል፡፡
“ሰዎች እንደዚህ ሲተባበሩ ማየት የሆነ ተስፋ ይሰጣል” በማለት የሙስሊም ጉባዔው አባል የሆነው ዑመር ራሺድ ለሲኤንኤን ተናግሯል፡፡
እኤአ በ2015ዓም በኮፐንሃገን ዴንማርክ የአይሁድ ምኩራብ ጥቃት ከደረሰበት በኋላ በኦስሎ ኖርዌይ በሚገኝ ሌላ የአይሁድ ምኩራብ ላይ ጥቃት እንዳይደርስ ለምዕመናኑ ከለላ በመስጠት ከአንድ ሺህ በላይ ሙስሊሞች “የሰላም ቀለበት” በማድረግ አጥር መስራታቸው የሚታወስ ነው፡፡
(ዜናው የተቀናበረው እና ፎቶዎቹ የተወሰዱት ከሲኤንኤን እና ሜትሮ ዘገባ ነው)
ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply