
“ፓርላማ” ተብሎ ሲጠራ በነበረው የኢህአዴግ ሸንጎ በቅንነትና በታማኝነት ሲያገለግሉ የነበሩት ተሾመ ቶጋ አሁን ደግሞ የቀድሞ ጌቶቻቸውን መልሶ የማቋቋም ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
በነበራቸው ቆራጥ የካድሬ ስብዕና ከአፈ ጉባዔነት ወደ አምባሳደርነት የተሸጋገሩት ተሾመ ቶጋ ላለፉት አራት ዓመታት በቻይና አምባሳደር ነበሩ። ከቻይና በፊትም እንደ ሌሎቹ የኢህአዴግ ካድሬዎች ባሳዩት ታማኝነት አምባሳደር ተብለው በተለያዩ አገራት ሲንከራተቱ ነበር።
በፓርላማው ቆይታቸው ከትህነግ ሰዎች እጅግ በበለጠ ለሥርዓቱ ታማኝ በመሆን የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ አባሎችን በማሰቃየት ደርሰው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ አባላት ሲናገሩ በማዋከብ ከዚያም አልፎ ከሚሰጣቸው ጊዜ ላይ በመቁረጥ እንዳይናገሩ፣ ሃሳባቸውን ሳይጨርሱ የመናገሪያውን ድምጽ በማጥፋት፣ እየተናገሩ እያለ ጣልቃ በመግባት ንግግራቸውን እንዲያስተካክሉ በመነታረክ፣ ንግግራቸው ከአጀንዳው ጋር የተያያዘ አይደለም በማለት አፍ በመካፈት፣ በበርካታ የመብት ገፈፋ ተግባር ላይ ተሠማርተው እንደነበር የብዙዎች ትዝታ ነው።
ከዚህም የተነሳ የከተማ ፌዘኞች ቴሌ ይሸጠው የነበረውን የ፲ ብር ካርድ ተሾመ ቶጋ እያለ ይጠራው ነበር፤ የሞቀ ወሬ ላይ ምንም ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ደቂቃው ሞላ በሚል ይቆርጠው ስለነበር። በተለይ ጅንጀና ላይ ያለ ወጣት እንዴት እንደሚሰማው በመገመት የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ አባላት በተሾመ የደረሰባቸውን መረዳት ይቻላል።
ቀድሞ “አምባሳደር” ሲባሉ የነበሩት ተሾመ “አቶ” ተብለው፤ እጅግ አሰልቺና አድካሚ ብዙ ጭቅጭቅ የበዛበትን የመልሶ ማቋቋም ሥራ ይሠራሉ። ይህንን በድል ሲጨርሱ አቶ ተብለው ጡረታ ይወጡና እሳቸውም በጡረተኛነት ይቋቋማሉ።
በዚህ አጋጣሚ ቀድሞ አምባሳደር የነበሩ ካድሬዎች ከሹመት ሥልጣናቸው ሲለቅቁ “አቶ” ወይም “ወይዘሮ” ወይም “ወይዘሪት” ተብለው ሊጠሩ ይገባል እላለሁ። በትምህርት ያገኙትና የራሳቸው ውጤት የሆነ ማዕረግ አይደለም። ለምሳሌ አቶ ተሾመ ቀድሞ ዛፍ ቆራጭ ወይም አሣ አጥማጅ ቢሆኑ አሁን ሲጠሩ የቀድሞው ዛፍ ቆራጭ ወይም አሣ አጥማጅ፣ የቀድሞ የተከበሩ አፈ ጉባዔ፣ አምባሳደር ተብለው አይጠሩም። ስለዚህ ለተሾመ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ይህ አሠራር ተግባራዊ እንዲደረግ ሃሳብ እሰጣለሁ።
ስምን መልአክ ያወጣዋልና ለተሾመ መልካም ሹመት፤ መልካም አቶነት እመኛለሁ።
የተከበርኩ ነኝ ከፓርላማ ሠፈር
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣበ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply