በአዲስ አበባና በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀናጀ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም አቅደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡
የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ በአዲስ አበባና በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች ሁከት፣ ሽብርና ትርምስ በመፍጠር ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማሳካት በሚንቀሳቀሱ የውጭ እና የውስጥ ፀረ-ሰላም ኃይሎች የሚደገፉ የሸብርተኞቹ የህወሓትና የሸኔ ቡድን አባላት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ ሴራ ወጥነው ወደ እንቅስቃሴ ለመግባት በዝግጅት ላይ እንዳሉ በጋራ ግብረ ኃይሉ በተደረገባቸው ጥብቅና የተቀናጀ ክትትል በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ይህን እኩይ የጥፋት ሴራ ለመፈጸም ከውጭ በተለያዩ አካላት በሚደረግላቸው የገንዘብና የሎጅስቲክስ ድጋፎች ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የሸብርተኞቹ የህወሓትና የሸኔ ቡድን አባላት ከከባድ እስከ ቀላል የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎችን ከመሰል ጥይቶች፣ ቦምቦችና ተቀጣጣይ ቁሶች ጋር ለጥቃት ሊጠቀሙባቸው ያዘጋጇቸው ቢሆንም፤ የታቀደውን የጥፋት ተልዕኮ ማክሸፍ መቻሉን መግለጫው አትቷል።
መግለጫው አክሎም ለሽብርተኞቹ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያና በሌሎችም አካባቢዎች ጭምር የተለያዩ ሀገራት የገንዘብ ኖቶች በህገወጥ መንገድ ሊተላለፉ እንደነበር ጠቁሞ፥ በተደረገ ጥብቅ ክትትልና ፍተሻም ለጥፋት ተልዕኮ መፈፀሚያቸው ሊጠቀሙበት የነበረ ከ305 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር እና ከ2 ሚሊየን በላይ የኢትዮጵያ ብር መያዙን አስታውቋል፡፡
መግለጫው እንዳብራራው ይህንን የጥፋት ተግባር ለመፈፀም ቀደም ሲል ትግራይ ድረስ ታጣቂዎቹን መልምሎ በመላክ ከሽብርተኛው የህወሓት ቡድን ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ በንፁሃን ዜጎች ላይ ብሄር ተኮር ጥቃቶችን ሲፈፅም የቆየው የአሸባሪው የሸኔ ቡድን የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ የገንዘብና የሎጅስቲክስ ድጋፎችን ሲያገኝ እንደቆየና በቡድኑ ላይ የመንግስት ፀጥታ አካላት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየወሰዱት ባለው ተከታታይ እርምጃ እየተዳከመና ከባድ ኪሳራ እያጋጠመው መምጣቱን ተከትሎ መሰረተ ልማቶችን እንዲያወድሙ እንዲሁም በታዋቂ ሰዎች፣ በከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና በዜጎች ላይ በተደራጀና በተጠና መንገድ ግድያ እንዲፈፀሙ አባ ቶርቤ በሚል የሰየማቸውን የከተማ ክንፍ አሸባሪዎች ወደ ተለያዩ ከተማዎች አሰማርቶ ነበር ብሏል፡፡
ለእነዚህ የሽብር ቡድኖች የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን፣ ቦምቦችን፣ ለፍንዳታ የሚውሉ ተቀጣጣይ ቁሶችን እንዲሁም ሰነዶችን በስውር ለመስጠት ሲያጓጉዙ የነበሩ በርካታ የቡድኑ ተጠርጣሪ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጋራ ግብረ ኃይሉ በመግለጫው አመላክቷል፡፡
ከተጠርጣሪዎች መካከልም አብዲሣ ጣፋ ቆጮልቴ እና ኤብሣ ተረፋ ቶኮሣ የተባሉት ግለሰቦች ከአማራ ክልል ሁመራ አካባቢ በኮድ ሁለት የታርጋ ቁጥር A70977-አ.አ ሚኒባስ መኪና የውስጥ አካል የተለያዩ የጦር መሳሪዎችንና ጥይቶችን ሰግስገውና ደብቀው መዳረሻቸውን ምዕራብ ኦሮሚያ አድርገው በደሴ በኩል አዲስ አበባ ሊገቡ ሲሉ ለገጣፎ ላይ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጿል።
በተመሳሳይ አርጆ አለማየሁ ዋቆ የተባለች የሸኔ ቡድን አባል ሶላር የተገጠመላቸው ዓለም አቀፍ የሳተላይት ስልኮችን በሞያሌ በኩል በማስገባት ወደ ተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በድብቅ ለማሰራጨት ስትሞከር ቡራዩ ከታ ላይ በቁጥጥር ስር መዋሏን የጠቆመው የጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫ፥ ራቢራ ዊርቱ ሞሲሳ፣ ደረጄ ዱጋሳ ሆርዶፋ እና ወንደሰን መግራ ታደሰ የተባሉ ሌሎች የሽብር ቡድኑ አባላትም ተጨማሪ የሳተላይት ስልኮችን ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ ለማስገባት ሲሞክሩ በነበረው ሚስጥራዊ ክትትል በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሷል፡፡
ሸብርተኛው የሸኔ ቡድን በተደራጀና በተጠና መንገድ ግድያ እንዲፈፅሙ አዲስ አበባና በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች ያሰማራቸው የአባ ቶርቤ ቡድን አባላት ተመሳስለው ጥቃት የሚፈፅሙባቸው የመከላከያ ሰራዊት የቀድሞ ደንብ ልብሶችንና እና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ጭምር በድብቅ ሲጓጓዙ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መግለጫው አትቷል።
አበራ ሙለታ፣ ለሊሳ አዳሙ፣ አበራ ጌታ፣ ሙሌ ስዩሜ እና አብርሃም አቡ የተባሉ የቡድኑ አባሎችና የድርጊቱ ተዋናዮች እንዲሁም አሽከርካሪውና ረዳቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መግለጫውም ጠቁሟል፡፡
የሽብር ቡድኑ በጅማ ከተማ ጥቃት ለመፈጸም ስምሪት የሰጣቸው ኢያሱ ለማ፣ ካሊድ ሰይድ፣ አብደላ አባ በላይ፣ ሰይፉ በላይ እና ነጋሳ ኬኔሳ የተባሉ ተጠርጣሪዎችም ከታጠቋቸው የእጅ ቦምቦችና እና ሽጉጦች እንዲሁም ከሌሎች የጥፋት ተልዕኮ መፈጸሚያ ቁሶች ጋር መያዛቸውንም ነው ያመላከተው፡፡
በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖሩና ለአሸባሪው የሸኔ ቡድን የገንዘብና የሎጅስቲክስ ድጋፎች የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ያመላከተው የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይሉ፥ እነርሱም ጀምበሩና አበበ አሜሪካ፤ ገመቹ፣ አብደላ እና ተርፋ አውስትራሊያ ዱጋሳ ኖርዌይ እንዲሁም ቶለሺ ታምሩ ወይም ገቢሴ፣ ገመቹ አቦዬ፣ ለማ ረጋሳ ወይም ቢቂላ እና ጃራ ቱለማ ኬንያ እንደሚኖሩም አውስቷል፡፡
እነዚህን የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ እየደገፉ ያሉትን በድምሩ 15 ተጠርጣሪዎችን ማንነት በማጣራትም ለህግ ለማቅረብ ከወዳጅ ሀገራት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጾ፥ በሀገር ውስጥ እስካሁን የቡድኑን የሽብር እንቅስቃሴ ለመግታት በተወሰደው እርምጃ የቡድኑን የከተማ ህዋስ አባላትን ጨምሮ 71 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብሏል፡፡
መግለጫው አያይዞም ለሽብር ቡድኑ የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ የ80 ተጠርጣሪ ግለሰቦች የገንዘብ ስርዓት እንዲቋረጥ የተደረገ መሆኑን እያሳወቀ፥ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቡድኑ ዋና ዋና የገንዘብ አስተላላፊ ተብለው የተጠረጠሩ 6 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል፡፡
ሌሎችንም በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን አመላክቷል፡፡
ከአሸባሪው የሸኔ ቡድንና ከሌሎች ፀረ-ሰላም ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ ይዞ ሲንቀሳቀስ የነበረው የሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አባላት ላይ የፈፀመውን የሀገር ክህደት ወንጀል ተከትሎ፥ መንግስት በወሰደው የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ የቡድኑ ቁልፍ አመራሮች እርምጃ ሲወሰድባቸውና ገሚሶች ደግሞ እጃቸውን በሰላማዊ መንገድ ሲሰጡ ጥቂት የታጠቁ የቡድኑ ሃይሎች በተንጠባጠበ መልኩ በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀሱም ነው የገለጸው፡፡
ቡድኑ የተወሰደበትን ተከታታይ እርምጃ መቋቋም ባለመቻሉ “ክብሪት” የሚል መጠሪያ የሰጠውን ገዳይ ቡድን በክልሉ ዋና ዋና ከተሞችና በአዲስ አበባም ጭምር ለማሰማራት መሞከሩንም አትቷል፡፡
በአሜሪካ የሚኖሩ ጀኔራል ፍስሃ ማንጁስ ካህሳይና ወዲ ምጉላት የተባሉ ግለሰቦች በሆላንድ የሚኖሩ ተክላይ እና አታክልቲ፣ እንግሊዝ የሚኖረው ታከለ፣ ስዊድንና ደቡብ ሱዳን የሚኖሩት ተስፋይ ንጉስና ሰይፈ አምባዬ የተባሉ ተጠርጣሪዎች ሽብርተኛውን የሕወሓት ቡድን በገንዘብ የሚደግፉ መሆናቸው በማስረጃ የተረጋገጠ መሆኑን በመግለጽ የጋራ ግብረ ኃይሉ ግለሰቦቹን በህግ ተጠያቂ የማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ነው ያስታወቀው፡፡
በሀገር ውስጥ ሆነው ለቡድኑ የገንዘብና የሎጅስቲክስ ድጋፎችን ሲያደርጉ የነበሩ 32 የቡድኑ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም እና በቡድኑ ለሽብር ድርጊቱ ሊውሉ የነበሩ የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች፣ የሬዲዮ መገናኛዎች እና ሌሎች ተቀጣጣይ ቁሶችም መያዛቸውን ጠቁሟል፡፡
እነዚህ ሽብርተኛ ቡድኖች ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማሳካት ሀገሪቱን ወደ ሽብርና ትርምስ ውስጥ በማስገባት የህዝቡን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ሴራ ወጥነው ለመንቀሳቀስ እየሞከሩ ቢሆንም የደህንነትና የፀጥታ አካላት ከህዝቡ ጋር በቅንጅት በመስራት ሴራቸውን አስቀድሞ ማክሸፍ መቻሉን የጋራ ግብረ ሃይሉ ገልጿል።
የሸኔና የህወሓት ሽብርተኛ ቡድን አባላት በመንግስት ጸጥታ ሀይሎች እየተወሰደባቸው ባለው ተከታታይ እርምጃ፥ በርካታ የቡድኑ አባላት መደምሰሳቸውንና መያዛቸውን እንዲሁም ለሽብር ተልዕኮ የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች፣ የእጅ ቦምቦች፣ ለፍንዳታ የሚውሉ ተቀጣጣይ ቁሶችና ሰነዶች መያዛቻውን አስታውቋል።
ይህን ተከትሎም የሽብር ቡድኖቹ ከፍተኛ ኪሳራና የስነልቦና ጫና ውስጥ መግባታቸውን መግለጫው አንስቷል፡፡
የጋራ ግብረ ኃይሉ የውስጥና የውጭ ጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቀናጅተው ሀገሪቱን ወደ ለየለት ትርምስ ለመክተትና ለማፍረስ እየሰሩ ቢሆንም፥ በርካታ ሴራዎችን አስቀድሞ በማወቅ ማክሸፍ መቻሉንና የትኛውም ሴራ ከመንግስት እንዲሁም ከደህንነትና ጸጥታ አካላት እይታ የተሰወረ አለመሆኑንም አስታውሷል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ በያዝነው ወር መጨረሻ ላይ ሀገራዊ ምርጫ ለማከናወን እንዲሁም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማካሄድ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገች ባለችበት በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ የውጭ ሀይሎች በቀጥታ ከሚደርስባት ጫና ባሻገር፤ ከተመቻቸው በጥቂት ተላላኪዎቻቸው የሸኔና የህወሓት ሽብርተኛ ቡድኖች ጥቃት በመሰንዘር ካልተመቻቸው በህቡዕ የተለያዩ አጀንዳዎችን በመፍጠር ሀገሪቱ ወደ ትርምስ እንድትገባ የተለያዩ እኩይ ሴራዎች እየተጠነሰሱ መሆናቸውን ህዝባችን ሊገነዘብ ይገባል ብሏል የጋራ ግብረ ኃይሉ በመግለጫው፡፡
በመሆኑም ህዝባችን ሰላሙንና ደህንነቱን ለመጠበቅ እንዲሁም የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ለማረጋገጥ ሴራዎቹን በማክሸፍ ለአፍታም አይን በማያስከድን ስራ ላይ የተሰማሩ የመረጃና ደህንነት እንዲሁም የጸጥታ ተቋማትና አካላትን የተቀናጀ እንቅስቃሴ በመደገፍ እያደረገ ላለው ትብብር የጋራ ግብረ ኃይሉ ላቅ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡
ተመሳሳይ ሀገር የማፍረስ እኩይ ሴራዎችን በማክሸፍ በኩል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን በቀጣይ ለህዝቡ የማሳወቅ ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን መግለጫው አረጋግጧል፡፡ (ኤፍ.ቢ.ሲ.)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
በዘመናት መሃል መለየት ያቃተን ማን ነው ሽብርተኛ
ማ ነው አሸባሪ በወገን በሃገር ክፋት የሚሰራ
እኛ የምናውቀው በኖርነበት ዘመን አይናችን የሚያየው
ያለፈን አጥላልቶ አዲሱም እንደዚያው የከፋ ሲሆን ነው።
በመሰረቱ ለውጥ ማለት በሃበሻ ምድር የጠገበን አውርዶ የተራበን በቦታው መተካት ማለት ነው። ያለፈ ታሪካችን ለዚህ እማኝ ስለሚሆን ምስክር አላቆምም። የቀይ መስቀል አምቡላንስ መኪናን ላፈና የሚጠቀም መንግሥት እቡይ እንጂ ጭላንጭል ብርሃን የለውም። ሴራና መጠላለፉ በወረፋ በሆነባት በዚህች ምድር ላይ የሚታመን ሰው ከጠፋ ዘመን ቆጥረናል። ሰው ቤ/ክርስቲያን ስላዘወተረ፤ መስጊድ ስለምሄድ የዛን ሰው ከፍታም ሆነ ዝቅታ አያሳይም። ዛሬ መሰቀል በአንድ እጃቸው ሽጉጥ በሌላው የወሸቁ እልፍ ናቸው። መንፈሳዊ ትምህርት ለማስተማር መድረክ ላይ የወጣን ሰባኪ በጠበንጃ ታጅቦ ሲገባ ማየት ጉድ ያሰኛል። እስቲ ይታያችሁ ለምዕመናኑ ምንም አትፍሩ ፈጣሪ ይጠብቃቹሃል ብሎ ሲናገር። ፊዝ አይሆንም እንዴ? በቅርቡ የሆነ ሰው አረፈና አስከሬኑ ሆስፒታል ለምርመራ ሄዷል ሲሉት አንድ አልቃሽ “እናንተ ደግሞ በቁማችሁ የሞታችሁ እንኳን የህክምና ባለሙያው ቀርቶ የሃማኖት መሪዎች የሚዋሹባት ሃገር ናት” አምጡና ቀብረን እንገላገል ሲል የተሰበሰበው ሰው ሁሉ በኮረና ምክንያት አፉ ተለጉሞ ስለነበር ይሁን ሌላ ትንፍሽ ያለ አልነበረም። እንደተባለውም ሰውዬው ገዳዪና ለምን እንደተገደ ሳይታወቅ አፈር ለብሶ አረፈ።
ቅጥ አምባሩን ያጣው የሃገራችን ፓለቲካ እንደ ድር አራዊት በየወገንህ በመባባል ሲፋለሙ ማየት በሃገርና ከሃገር ውጭ የተለመደ ሆኗል። በቅርቡ ዶ/ር ደብረጽዪንና ጌታቸው ረታ ለቀቁት የተባለውን ምስል አይቶ አንድ ሰው እንዲህ አለ “ይህ የትግል ጽናትን ያሳያል” ክራራይሶ ያሳኛል። ግን በዘር ፓለቲካ ለሰከረው ሃበሻ እውነት ቆማ እየመሰከረችለት እንኳን መስማት አይሻም። እልፍ የትግራይ ልጆች እነዚህ ሁለት ሙታኖች በለኮሱት እሳት የረገፉት ማን ያልቅስላቸው? መቼ ነው የትግራይ ህዝብ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ መኖሩ የሚያበቃው? ለወያኔ ሙታኖች ይህ ጉዳያቸው አይደለም። በ 27 ዓመት የስልጣን እድሜያቸው ለትግራይ ህዝብ የፈየድለት ነገር የለም። ይህ ዝም ብለን ከሚያልፍ ውሃ የተቀዳ ወሬ አይደለም የምናወራው። በአይናችን ያየነውን እጃችን የዳሰሰውን ነው። ታዲያ ድንገት በሆነ የፓለቲካ የሾኬ ጠለፋ አሁን በስልጣን ላይ ያለው የዶ/ር አብይ ስብስብ እየቆየ ወያኔን እየመሰለ መሄድ አብሯቸው እንደኖረና ወያኔአዊ ባህሪውም እንዳለቀቀው ያሳያል። በሽብር የተጠረጠሩ ሰዎች፤ በሽብር የተፈረጅ ድርጅቶች ወዘተ በማለት ሰውን በየምክንያቱ ዘብጥያ ማውረድና ያለ ፍርድ ማጎር ከደርግና ወያኔ ተግባር አይለይም። ይህን ስል አሸባሪዎችና ተንኮልን የሚሰሩ የሉም ማለት አይደልም። በአንድ ሽልጦ የሰው አንገት የሚቆርጥ ጨካኝ ትውልድ ያለባት ምድር ናት። ይሁን እንጂ ያለምንም መረጃ ሰውን በሰብብ ማጎርና ብሎም መግደል መጭውን የሃገሪቱን ተስፋ የበለጠ ያጨልመዋል እንጂ ፍንጣቂ ጮራ አያሳየንም።
የሃበሻው ምድር ችግር የትየ ለሌ ነው። ከዚህ ውስጥ 85% እኛው ራሳችን በራሳችን ላይ የምንለኩሰው ተንኮልና የፓለቲካ አሻጥር ክፋትና ያዘው ጥለፈው ማቆሚያ የለሽ መሸራገድ ነው። አንድ ከሩቅ ዘመን በፊት ጓደኛዬ የነበረ ሰው ጋ ተገናኝተን ስምና አድራሻ ስንለዋወጥ ስሙ ትንሽ ግራ አጋባኝ። እንዴ ምነው ስምህ ፊደላት (የላቲን) ደጋገመ ስለው ያው የኦሮሞ ፓለቲካ ነዋ አለና ሳቀ። እኔም ታዲያ ድሮ አማራ አጥምቆን ክርስቲያን አርጎን የራሳቸውን ስም ሰተውን እያልክ ትለፍ ነበር አሁን የኦሮሞው ፓለቲካ ስምህን ሲቀይረው ምን አልክ? ወይ ጉድ ምርጫ እንዳለኝ ሰው ምን ትጠይቀኛለህ በማለት እኔም የተሰጠኝን ስም ፊደሉን አስተካክዬ ከስልኩ ጋር ተለያየን። ይህ ፍጽም እብደት ነው። ሰው ራሱ ወዶ እንጂ ስሙንም ሆነ የአባቱን ስም የሚቀይረው ፓለቲከኞች በጅምላ እንዲህ መጻፍ አለበት ስላሉ መሆን አልነበረበትም። አይ ፓለቲካ እንዲህም ብሎ ለህዝብ መቆም የለ። የዘቀጠ ፓለቲካ! ትላንት አማርኛ አንሰማም አንናገርም ይሉን የነበሩ ጠባብ ብሄርተኞች ዛሬ በራችን አንኳኩተው በአማርኛ ሲያጫውቱን ስመለከት የፓለቲካችን ከንቱነት ያሳየኛል። ሰው መግደል ዝቅጠት ነው። ጀግንነት አይደለም። አሁን በየስርቻው ተሸጉጠው ያሉት ወያኔዎችና ወደ ሱዳን የተሻገሩት እንዲሁም ከሰላም አስከባሪው ሃይል ተለይተው አንመለስም ያሉት ሞታችን ሱዳን ያርገው ያሉት ውጭ ሃገር የመውጣት እድል እናገኛለን በማለት እንደሆነ እዚያው ያሉ ይናገራሉ። አፍንጫህን ላስ። ነጩ አለም ስልችቶናል። ደግሞስ የሰው አንገት ስትቀነጥስ፤ ሴት ወንድ ህጻን ሳትለይ ስትጨፈጭፍ ኖረህ እንዴት በነጻው ዓለምስ የሰከነ ህይወት ይኖርሃል? የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር ይላሉ። ድሮ ቀረ ወደ ምዕራቡ ሃገር ተጉዞ ራስን አሻሽሎ ሌላውን መርዳት። አሁን ያለው ነፋስ እጅግ አስፈሪና ወደፊትም የለየለት ፍጅት የሚያስከትል ነው። ስለሆነም ልብ ያለው ወደ ሃገሩ ተመልሶ የሰላም ኑሮን መኖሩ አማራጭ አይገኝለትም። ከዚያ በተረፈ የወያኔ ካድሬዎችና የግብጽ/ሱዳን የስለላ መረብ እየመለመሉ ወደ ሃገር በመላክ የእሳት ራት እንደሚያደርጓቸው የታመነ ጉዳይ ነው። በዘሩና በቋንቋው ለሰከረው ወገን አይገባውም እንጂ ነጩም ሆነ አረቡ የጥቁር ደም እንደ ውሻ ደም ነው የሚቆጥሩት። መቼ ይሆን የምንነቃው?
በመዝጊያው ያለምንም በቂ መረጃ ሰውን ማሰር፤ አሸባሪ ብሎ መፈረጅ፤ አፍኖ መደብደብ፤ ማስፈራራት ዶ/ር አብይ ከሚለፉት የመደመር ህሳቤ ጋር የምይገናኝ ድርጊት ነው። የህዝብ ጠንቅ ናቸው የተባሉ ሃይሎች ፍ/ቤት ሊቀርብ የሚችል መረጃ ከተሰበሰበ በህዋላ ቢታገቱ ይመረጣል። ሰውን እስር ቤት ከቶ መረጃ ላሰባስብ ማለት ሱሪን ያለ ቀበቶ ታጥቆ እንደመሮጥ ይቆጠራል። መንገላጀጅ። መገዳደላችን ይብቃ። የዘርና የቋንቋ ፓለቲካ ለማንም አይጠቅምም። የክልል ፓለቲካ አፓርታይድ ፓለቲካ ነው። በቃኝ!
zimetegnaw golgool says
U frozen in time golagool? Your lates news is dated May 1oth!!!! Your ‘latest’ is more than a month old in real time? Your sources are dried up or you tired of mix news with your biased opinion? Or could it be a change of heart?