ትንሿ የ’ሕል ዘር፤
ዐይን እንኳ ብትገባ የማትቆረቁር፤
ድንገት ጠብ ብትል የማትገኝ ከምድር፤
ቁልቁል አሾልቃ በንቀት እያየች፤
በድሃው ወገኔ ከት ብላ ሳቀች!
…….. እጅጉን አሾፈች::
አሹቅህን አውልቅ – ሽንብራህን ቆርጥም፤
ባቄላህን ጠርጥር – በቆሎህን ከርትም፤
እኔን ካሁን ወዲያ እንኳን ልትበላኝ፤
ድንገት በመንገድ ላይ ባይንህም አታየኝ፤
እያለች አፌዘች፤
በወገኔ ሳቀች !………. በወገኔ አሾፈች !!
አረም እንዳይውጣት – ወፎች እንዳይለቅሟት፤
ካቡን ዙሪያ ክቦ – ከብቶች እንዳይበሏት፤
አጭዶና ከምሮ – በሬዎች ለጉሞ፤
ሲወቃ እንዳልዋለ – ቀኑን ሙሉ ቆሞ_ _ _፤
በመንሽ አበጥሮ – በቁና ለክቶ፤
በሰፌድ አንፍሶ – በስልቻ ከቶ፤
ነቀዝ እንዳይበላት – ብርድ እንዳያጠቃት፤
ወቅቶ በጎተራ – እንዳላስቀመጣት_ _ _፤
አንተ አትቀምሰኝም! ብላ ኮበለለች፤
ጢያራ ተሳፍራ አማሪካን ገባች::
እየተቁለጨለጭክ – ባይንህ ብትቀላውጥ፤
መልሰህ መላልሰህ – ምራቅህን ብትውጥ፤
እንዳማረህ ይቅር – ከቶ አንተ አትበላኝም፤
ባንተ አፍ ገብቼ – ባንተ ሆድ አላድርም፤
ብላ ጤፍ አፌዘች በወገኔ ሳቀች፤
………. በወገኔ አሾፈች::
ከድሃው ወግነው የቀሩት በሃገር ፤
ባቄላ በቆሎ ጓያውና አተር፤
ሆኖ አለመታደል – ጓያ እግር ሲሰብር፤
አተር ሆድ ሲወጠር _ _ _፤
እንዲሉ!
ምክንያት ሳይፈጥር – አይጣላም እግዜር፤
ተመስገን ባቄላ ያስተነፍስ ጀመር::
የልመና ስንዴ – እያለ ልምጥ ምጥ፤
እሹሩሩ ቢባል – አይወጣ ከምጣድ፤
ጉልቻ ዘብ ቢቆም! – እሳት ቢንቦለቦል!
ምጣድ እሹሩሩ – ማሰሻ ቢያባብል!
ብጥስጥስ እያለ – ኩርፊያውን ማን ሊችል?!
ከመሰቅሰቂያ ጋር አንስቶ አምባጓሮ፤
ከምጣድ ሳይወጣ ቀረ ሆኖ እንኩሮ ::
የጎደለበትን፤ ቀን የጣለውን ሰው፤
ጤፍ እንኳን ባቅሟ አየኋት ስትንቀው፤
ከፍ ዝቅ አድርጋ ስትገላምጠው፤
ስታበሻቅጠው::
ጤፍ እንኳን ባቅሟ!
በኑሮ ውድነት የተነሳ፤ ጤፍ መብላት እንደሰማይ ለራቃቸው ወገኖቼ ማሽታወሻ ትሁንልኝ::
ሃምሌ 17/ 2007 ዓ.ም (July 24/2015)
Leave a Reply