
የቀድሞው የኢትዮጵያ የሽግግር ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር ኋላ ላይ ደግሞ የኢፊድሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ ከአውስትራሊያዊው የኤስ.ቢ.ኤስ የአማርኛ ራዲዮ ባልደረባ ጋዜጠኛ ካሳሁን ሰቦቃ ጋር ያደረጉትን በሶስት የተከፈለ ሰፊ ቃለመጠይቅ በአንክሮ ተከታተልኩት:: አቶ ታምራት ብዙ ነገሩን፤ ብዙ ደበቁንም:: ከምንም በላይ አቶ ታምራት በረጋ አንደበት ከቁጣ እና ከብስጭት የጸዳ ቃለምልልሳቸውን በዚህ አጋጣሚ ሳላደንቅ አላልፍም::
እርግጥ ነው ቃለመጠይቁ ሰፊ ቢሆንም በደምሳሳው አቶ ታምራት በመለስ ዜናዊ ተታለልኩ የሚል ቃና ያለው መልዕክት እንዳስተላለፉ ነው የተረዳሁት:: ከምንም ነገር በላይ አሁን ከሚከተሉት ሃይማኖት ጋር አያይዘው ቢሆንም ኮሚኒዝም አንደርዮት አለም በፍጹም የስሕተት እና የጥፋት መንገድ አንደነበር በአደባባይ መናገራቸው ለኔ ታላቅ ቁም ነገር ሁኖ አግኝቼዋለሁ:: የዚያችን ሃገር አንድ ሙሉ ትውልድ ያጫረሰ አና አሁንም ድረስ ለተጣባን ግራ መጋባት እና ውዥንብር መነሻ የሆነውን ቁልፍ የታሪክ ስሕተት ነቅሰው በይፋ ማውገዛቸው የሚያስመሰግን ምግባር ነው:: አዎን ሌሎች የዘመኑ የፖለቲካ መሪዎችም አገራችን ከተረጋጋ ሁኔታ ተነስታ በጎደለው መሙላት ሲገባ በተፈጠረው አጉራ ዘለል የፖለቲካ እብደት ላለፉት አርባ አመታት ለደረሰው እልቂት ፣ መበታተን ፣ ውድመት አና አስከፊ ድህነት ምክንያትን ለመመርመር ቃሊቲ ፩፪ አመት መውረድ የሚያስፈልግ አይመስለኝም:: ትውልድ እንዲማር በዛ ፖለቲካ ውስጥ የነበራችሁ እባካችሁ ውጡና ተናገሩ፣ ጻፉም!
ወደ ውይይቱ ጭብጥ ስመለስ አቶ ታምራት የተጓዙበትን ጠመዝማዛ ህይወት ለመመርመር የቃሊቲውን የእስር ዘመን በደምብ እንደተጠቀሙበት ለመረዳት ይቻላል:: ሁሉንም ባይሆን አንድ አንድ በሳቸው ላይ ይነሱ የነበሩ ክስ እና ስሞታዎችን በገደምዳሜም ቢሆን ለማመን ወኔ አሳይተዋል:: አቶ ታምራት የሆነውን እና የነበረውን ሁሉ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጊዜውን ጠብቀው ለማሳወቅ ፍላጎት አንዳላቸው(በመጽሃፍ መልክ ቢሆን የበለጠ ተመራጭ ይሆናል!!) በመናገራቸው ከዚህ በፊት የተባሉ ጉዳዮችን ማንሳቱን አልወደድኩትም:: ይልቁንም የአቶ መለስ እና የአጋሮቻቸው የውስጥ ለውስጥ ፖለቲካ ሴራ ተጠቂ አንደሆኑና በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ሊባል የሚችል የስም ማጉደፍ ዘመቻ እና እንግልት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል:: ተዘረፈ ስለተባለው ገንዘብ፤ ከሼክ አላሙዲን ተቀበሉት ስለተባለው (ይመስለኛል ፩፮ ሚሊዮን ዶላር) ፤ በስዊዝ ባንክ በልጃቸው ብሌን ጌታቸው ስም ተቀምጦ ተገኘ የተባለውን እጅግ ብዙ ሚሊዮን ዶላር በሙሉ የግል ባህሪ ችግር እንደነበረባቸው ለማመን ወኔ ያሳዩት አቶ ታምራት ያልነበረ አና ያልሆነ የሃሰት ውንጀላ እንደነበር ተናግረዋል;; በቂ መረጃ በሌለበት ሁኔታ ለማመንም ሆነ ላለማመን መወሰን መቸኮሉን አልፈቀድኩም:: ስለዚህም ወደፊት በጉዳዩ ላይ አቶ ታምራትም ሆኑ ሌሎች ጸሃፍት የሚሉን ነገር ይኖራልና እስከዚያው እንጠብቅ:: በነገራችን ላይ ሙሉ ቪዲዮን እዚህ መመልከት ይቻላል በፍጹም አቶ ታምራት የስነ ምግባር ጉድለት እንደነበረባቸው ከማመን በዘለለ ገንዘብ እንደዘረፉ አና ከአገር እንዳሸሹ ያመኑት አንዳች ነገር የለም::
አቶ ታምራት ያሉንን እውነት ነው ብለን እንውሰድና ስለምን አቶ መለስ አቶ ታምራትን አዋርደው እና ስማቸውን በጭቃ ለውሰው ለአመታት በእስር አማቀቋቸው?? የምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ታምራት ላይኔ ከስልጣን መውረድ ዜና የታወጀ ለት ማታ ይመስለኛል በሁለት ሰዓት ዜና ላይ በራሳቸው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ አንደበት ታላቅ ስሕተት እንደሰሩ ፤ በአቶ መለስ “ብረት ያላሸነፈው ጀግና ስኳር ጠልፎ ጣለው” የገሎ ማዳን ንግግር ታጅቦ ሲቀርብ ላዳመጠ ሰው አቶ ታምራት በርግጥም ከዛ በኃላ በተለያየ ጊዜ በፍርድ ቤት እና በአቶ አማረ አረጋዊ በሚታተመው የሪፖርተር ጋዜጣ እና መጽሔት የቀረቡባቸውን ተከታታይ ክሶች አምኖ ለመቀበል በጣም ቀላል ነበር::
እኔም እንደ አንድ ዜጋ አቶ ታምራት በይፋ በቲቪ መስኮት ብቅ ብለው ባመኑት ጉዳይ ላይ ከዛ በኋላ የወጡ ተከታታይ ዘገባዎችን ለመጠራጠር ምክንያት አልነበረኝም:: በምስጢር ብቻ ሊነሱ የሚችሉ ፎቶግራፎችን የያዙ ዘገባዎች በሪፖርተር ጋዜጣ አና መጽሔት ላይ በተከታታይ ይወጡ እንደነበር አስታውሳለሁ:: እንደ አቶ ታምራት ገለጻ እና አንደ እኔ አረዳድ ከሆነ በፓርላማ ቀርበው ያመኑት ጉድለት ከግል ባህሪ (ከሴት ጋር የተያያዘ መሆኑን በዚሁ ቃለ ምልልስ በጨረፍታ ያመኑ ይመስለኛል) የተያያዘ እንጂ በፍጹም ተዘረፈ ከተባለ ገነዝብ ጋር ያልተያያዘ አንደሆነ ነው:: ‘ብልሁ’ አቶ መለስ ግን በግርድፉ ‘ስኳር’ የምትል አሻሚ ቃል በመጠቀም አቶ ታምራት በይፋ ኋላ ላይ ዘረፉ የተባሉትን ገንዘብ እንደዘረፉ በራሳቸው አንደበት እንዳመኑ አድረገው አቀረቧቸው:: አቶ ታምራት ራሳቸውን ከወነጀሉ ወዲያ ይህን አላረግኩም ይህን አልሰራሁም ቢሉ ሰሚ ጠፋ፤ በጣም ሊሰሩበት የሚገባ መልካም እድሜም በቃሊቲ ባከነ።
የአሰብ ወደብን በሚመለከት አቶ መለስ “አሰብ ለኢትዮጵያ ሊሰጥ አይገባም!” ብሎ መከራከሩን እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ እስር ቤት ሆኜ ነው የሰማሁት ያሉት በጣም ካስገረሙኝ ጉዳዮች አንዱ ነው:: በደርግ መውደቂያ መዳረሻ ወቅት የተባሉት ድርድሮች ሲካሄዱ አቶ ታምራት በግንባሩ ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን እንደነበራቸው (ዋና ጸሃፊ ይመስለኛል) ነገር ግን የመንግስት ለውጥን በሚመለከት ይደረጉ የነበሩ ውይይቶች ላይ አለመገኘት ብቻም አይደለም ውይይቶ/ድርድሮቹ ካለቁ በኋላ የተደረሱ ስምምነቶችን የማወቅ መብት እንኳን አልነበራቸውም ብሎ ለማመን በጣም አስቸጋሪ ነው:: ህወሃት በጣም ምስጢረኛ ድርጅት እና ብሔራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ጭምር የህወሃት ፖሊት ቢሮ አባላት ብቻቸውን እየተሰበሰቡ ይወስኑ እንደነበር ኋላ ላይ ህወሃት ሲሰነጥቅ ይወጡ ከነበሩ መረጃዎች ለመገንዘብ ችለናል:: ታዲያ አማራን ፣ ኦሮሞን ፣ ሲዳማን አና ሌሎችንም ወክለናል የሚሉ የስርዓቱ ጎምቱ ባለስልጣናት ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮችን መወሰኑ ይቅርና የማወቅ እንኳን መብት አልነበራቸውም/የላቸውምም ማለት ነው??
በወቅቱ አቶ ታምራት ኤርትራውያን በኢትዮጵያ ውስጥ ይሰሩ ከነበረው የንግድ ውንብድና ጋር በተያያዘ ከአቶ መለስ ጋር አለመግባባት እንደነበራቸው ይነገር ነበር። ጉዳዩ እውነትነት ሊኖረው ቢችልም አቶ ታምራት ሙሉ ሱፋቸውን ግጥም አርገው በፓርላማ ቀርበው በራሳቸው አንደበት ከፍተኛ ጥፋት እንደፈጸሙ እና በስልጣም መቀመጥ እንደማይገባቸው ካመኑ ወዲያ ለብዙዎች ለእስራቸው ሌላ ምክንያት መጠየቅ አስፈላጊ አልነበረም:: ዛሬ ላይ ተቁሞ ላለፉት ሁለት ኣስረተ ኣመታት የተከሰቱ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኹነቶችን ከአቶ መለስ የተኩላ ስብዕና ጋር አያይዞ ለተመለከተ ሰው ጉዳዩ በእርግጥም አቶ ታምራት እንደሚሉት ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው:: ዘልቀው ባይገቡበትም በወቅቱ የሻዕቢያ ባለስልጣናትም ሆኑ በወያኔ ውስጥ የነበሩ አቶ መለስን ጨምሮ አፍቃሪ ሻዕቢያ ባለስልጣናት ዘንድ ኤርትራ እና ኤርትራዊያንን በሚመለከት ይሰጡ የነበረው አስተያየት በበጎ አይታይ እንደ ነበር ገልጸዋል:: ይህ ነገር በርግጥም ጥቂት አመታት ቆይቶ የፈነዳውን ጦርነት እና ከጦርነቱ መፈዳት ጋርም ኤርትራዊያን በኢትዮጵያ ይሰሩ የነበረውን የንግድ ፣ ብሔራዊ ጥቅምን እና የአገር ህልውናን የሚፈትን የውንብድና ስራ መጋለጥ ላስተዋለ ሰው በርግጥም የአቶ ታምራት ታላቁ ወንጀል ፖለቲካዊ እንደነበር መገመት ያስችላል::
የአቶ ታምራትን ከስልጣን መወገድ እና ቃሊቲ መውረድ ተከትሎ የተሾሙት አቶ ተፈራ ዋልዋ እንደነበሩ ይታወሳል:: ነገር ግን የፖለቲካ ስብዕና በመገንባት እና በመድረክ መታየትን በሚመለከት ጎልተው የወጡት ኢትዮጵያዊነታቸው ብዙ ጊዜ በጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚገባው አና በዘር ሃረግም ኤርትራዊ የሆኑት አቶ በረከት ስምዖን ነበሩ:: አቶ በረከት ከአቶ ታምራት መከስከስ በፊት በቲቪም ሆነ በሌላ መድረክ የማይታዩ ሰው መሆናቸውን ላስተዋለ በርግጥም በደንብ የታሰበበት የሸፍጥ ፖለትካ ስራ እንደተሰራ መገመት ያስችላል:: በፖለቲካ ሳይንስ የስም ታዋቂነት የሚባል አንድ እሳቤ አለ:: ፈረንጆቹ (name recognition) የሚሉት ማለት ነው::
አቶ ታምራት የፓርቲያቸው የብአዴን ዋና ጸሀፊ እና በግንባሩ ውስጥም ከፍተኛ አመራር በመሆናቸው ፤ ከላይ እንደጠቀስኩትም ነባር ታጋይ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞም ስማቸው በደንብ የሚታወቅ መሆኑና በዚያም ላይ በቁጥር ከፍተኛ የሆነውን የአማራ ብሔር ስለሚወክሉም(ህጋዊ ውክልና አላልኩኝም!!) ጭምር ለአቶ መለስ ግልጽ አማራጭ በመሆን የስልጣን አደጋ ሊደቅኑ እንደሚችሉ እና በዚሁም ሰበብ አቶ መለስ የኋላ ኋላ በአቶ ስየ ፣ በአቶ ተፈራ ዋልዋ እና በተለይም በአርከበ እቁባይ ላይ እንዳደረጉት የአቶ ታምራትን ደካማ ጎን ተጠቅመው እንዳስወግዷቸው ለመገመት በቂ ምክንያት ያለ ይመስለኛል::
ለአቶ መለስ መጠባበቂያነት በስሌት የተቀመጡት የኋላ ኋላ የፖለቲካው ከባቢ አየር አስገድዶዋቸው የአሁኑን ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ኃይለማሪያምን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርነት ከማስቀመጣቸው በፊት ለቦታው ሲኳሉ እና ሲወለወሉ የነበሩ አቶ በረከት ስምዖን እንደነበሩ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርብ የሚከታተሉ ታዛቢዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው:: የአቶ መለስን የፖለትካ ሸፍጥ እና በህወሃት ውስጥ እ.ኤ.አ. በ2008 የነበረውን የውስጥ የፖለትካ ትርምስ ለመረዳት ይህን የዊኪሊክስ ኬብል ይመልከቱ::
የኢትዮጵያ ህዝብ ከጀርባው በራሱ ልጆች ተባባሪነት ተደጋግሞ ተወግቷል:: አቶ ታምራት በመግቢያዬ እንዳልኩት ብዙ ያለነገሩን/የደበቁን ነገር አለ:: ዳግም በአዲስ ክርስትና ተወልጃለው ያሉን አቶ ታምራት አንደዜጋ ብዙ እዳ አለባቸው:: ይህንን ህዝብ ማገልገል እና መካስን ጨምሮ ብዙ የተደበቁ እውነቶችን የመንገር እና የማስረዳት ሃላፊነት አለባቸው ብዬ አምናለሁኝ::
አቶ ታምራት ቃል እንደገቡት ለኢትዮጵያውያን በእሳቸው በኩል የነበረውን እውነት የሚነግሩበትን ወቅት በናፍቆት እጠብቃለሁ አገር እና ትውልድ ይድን ዘንድም በጣም ግልጽ የሆነ፣አስተማሪ እና ዘካሪ የሚሆን መጽሃፍ(tell all) ይጽፋሉ ብዬም እጠብቃለሁኝ::
khirpa@hotmail.com
References
n.d. Tamrat Layne on SBS Radio (Interview in Amharic).
1996. Tamrat Layne stepping down from power official video. October.
Wikileaks. n.d. ANECDOTES ON RULING PARTY RIFTS. Accessed 2013.
Give me a break. This is not the time to listen to Tamrat Layne’s story. This is a time when we need to unite as one people and talk about our country future and move forward .There is no moral or history we expect to learn from losers like …..