አምስተርዳምጉባዔላይለጥናትየቀረበጽሁፍ!
1.0 መግቢያ
የታሪክ ግዴታ ሆኖ የሰው ልጅ እንደማህበረሰብ ከተደራጀና፣ ስልጣንና ሀብት በጥቂት ሰዎች ቁጥጥር ስር መውደቅ ከጀመረ ወዲህ የአንድ ህዝብ ዕድልና የወደፊት ጉዞው፣ ታሪክ የመስራትና ያለመስራት ችሎታው በመጀመሪያ ደረጃ ሊወሰን የሚችለው ስልጣንን በቁጥጥራቸው ውስጥ ባስቀመጡ ጥቂት ሰዎች አማካይነት ነው። በታሪክ ውስጥ አንድ ህዝብ ከአንድ አገዛዝ ቁጥጥር ውጭ በሆነ መንገድ የራሱን ህይወት በነፃ ያደራጀበትና ታሪክ የሰራበት በተለይም ቀደም ብለው በነበሩ ስርዓቶች ውስጥ አልነበረም።
እንደሚታወቀው የአንድ አገዛዝ ምንነት የሚታወቀው ታሪክ ለመስራት ባለው ችሎታና አገርን ጥበባዊ በሆነ መልክ በማስተዳደር ረገድ ነው። አንድ አገዛዝ ታሪክን እንዲሰራ ከፈለገ ደግሞ ንቃተ-ህሊናው በጣም ወሳኝ ነው። በታሪክ ውስጥ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ስልጣን ላይ ባጋጣሚም ሆነ በጉልበት ቁጥጥ ያሉ ኃይሎች ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን ለመረዳት ብዙ ዐመታት ይፈጅባችዋል። ከዚህ በላይ ይልቅ ከውስጥና ከውጭ የሚመጣ ግፊት ለአንድ አገዛዝ አስተሳሰቡን መለወጥና ታሪክ ለመስራት መቻል ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወቱ የተረጋገጠ ነው። ይህንንም አጋጣሚ የሚጠቀምና ታሪካዊ ስራ ለመስራት የሚችል ኃይል ደግሞ ከንቃተ-ህሊና ባሻገር ውስጣዊ ፍላጎት(Will) እንዲኖረው ያስፈልጋል። ስልጣን ላይ የተቀመጠው እንዲያው ስልጣን ላይ ለመቀመጥ ብቻ እንዳልሆነ የሚገነዘብና የተገነዘበ ኃይል መሆን አለበት። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብና በተከታታይ የሚመጡትንም ትውልዶች ዕድል በሱ እጅ እንደወደቀ የሚያውቅ መሆን አለበት። ባጭሩ የታሪክ ኃላፊነት ያለበትና የተገነዘበ መሆን አለበት።
እንደሚታወቀው አገራችን የብዙ ሺህ ዐመታት ታሪክ እንዳላት ይነገራል። እጅግ ግሩም ግሩም የሆኑ ለጽሁፍና ለቋንቋ የሚያገለግሉም ፊደላት አላት።ግሩም ግሩም ባህሎችም አሏት። ይሁንና ግን ከዚህ የረዥም ጊዜ ታሪኳና ባህሏ ጋር የሚመጣጠን ስራና ህዝቡን የሚያስተሳስር ታሪካዊ ስራ ብዙም አለተሰራም። በራሳቸን ውስጣዊ ድክመት፣ በንቃተ-ህሊና ማነስ፣ በምርት-ኃይሎች አለማደግና በንግድ እንቅስቃሴ አለማበብ ምክንያትና፣ ከውጭው ዓለም ደግሞ ተገልለን በመኖራችን አዲስ ምሁራዊ ኃይል በማዳበር ታሪክን መስራትና ለስልጣኔ የሚያገለግል ባህላዊ ለውጥ ማምጣት አልቻልንም። በዚህም ምክንያት የተነሳ እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ ኑሮ የሚያመረቃ አልነበረም። በከፍተኛ የፊዩዳል ኑርሞችና እጅግ ተዝረክርኮ በገባ የካፒታሊዝም የፍጆታ አጠቃቀም በመተብተቡ የኑሮው ሁኔታ በጣም ወደ ኋላ የቀረ ነበር ማለት ይቻላል። በመሆኑም የየካቲቱ አብዮት ማንም ሳያዘጋጀውና ሳያስበው ሰተት ብሎ መጣ። ባለፉት 40 ዐመታት ደግሞ ህዝባችን የዚህ አብዮት አሉታዊ ውጤት ሰለባ በመሆን በተለያዩ የገዢ መደቦች ስቃዩን እያየ እንዲኖር ተፈርዶበታል። በተለይም 22 ዓመት ያህል ስልጣንን በተቆናጠጠ፣ አጀንዳው ብሄራዊ ባልሆነ፣ አገርን የሚሸነሽንና ለውጭ ከበርቴዎች በርካሽ ሳንቲም የሚቸበችብ፣ ልጆቻችንን ለአረብ ቱጃሮች እንደ ዕቃ በሚሸጥ፣ ዛሬን ብቻ የሚኖር በሚመስለውና የታሪክን ሚና በማይረዳና ባልተረዳ እጅግ አደገኛ ኃይል እየተሰቃየች ነው። የዛሬው የወያኔ አገዛዝ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለብዙ መቶ ዐመታት እንኳ ዝቀን ዝቀን ልንጨርሰው የማንችለውን የቤት ስራ ሰጥቶናል፤ እየሰጠንም ነው። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥና በማንኛውም የአገዛዘ ዘመን ባልተለመደ መልክ በጣም አስቀያሚ ስራዎችን እየሰራ ነው። ይህንን ካልኩ በኋላ ሶስት የታሪክ የስትራቴጂክ ስህተቶች ወይም ዕድልን ያለመጠቀም ችግርነት ያመጣውን መዘዝ በሚለው ላይ በሰፊው ልሄድበት እወዳላሁ።
2.0 የመጀመሪያው ስትራቴጄክ ስህተት- እንደሚታወቀው የዛሬው የአገራችን ችግር ትላንት ወይም ዛሬ የተፈጠረ አይደለም። ባለማወቅ ቀደም ብሎ በተለይም በአፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን የተፈጠረ ነው። በዚህ ላይ ብቻ የማተኩረው ከአፄ ኃይለስላሴ በፊት የነበሩትን የድሮዎችን የአገዛዝ ዘመን በአለማወቅም ሆነ ከውጭው ዓለም ጋር በነበራቸው የተራራቀ ወይም አልቦ ግኑኝነት ለመሰራት ያልቻሉትን ስራዎች ከቁጥር ውስጥ ባለማስገባት ነው።እዚህ ላይ ግንዛቤ ውስጥ እንዲገባልኝ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያን ዘመናዊ ለማድረግ አፄ ቴዎድሮስና አፄ ምኒልክ ከፍተኛ ትግልና አስተዋፆ አድርገዋል። ይሁንና ግን የቆሙበት ስርዓትና ህብረተሰብአዊ ድጋፍ ማጣት፣ በተለይም ደግሞ የሁለቱን መሪዎች አስተሳሰብ ተገንዝቦ ከእነሱ ጋር የሚጓዝ ምሁራዊ ወይም የኤሊት ኃይል ባለመኖሩ በዕቅዳቸው ብዙም ሊገፉበት አልቻሉም። ከዚህ ስነሳ ከአፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን በፊት መጠቀም ይገባን የነበሩ ዕድሎችን እዚህ ላይ መዘርዘሩ አሁን ለምናደርገው ትግል ይህን ያህልም ሊጠቅመን አይችልም። ታሪካችን ውስብስብና አስቸጋሪም ስለነበር ለአሁኑ ትውልድ በቀላል ቋንቋና የአሰራር ስልት ለማስረዳት ትንሽ ያስቸግራል። ስለዚህም በተለይም አፄ ኃይለስላሴና አገዛዛቸው ጣሊያን ከተባረረ በኋላ ለመጠቀም ያልቻሉትን አመቺ ዕድልና ስትራቴጂያዊ ስህተተቶች መዘርዘሩ እጅግ አስፈላጊ ነው ብዬ እገምታለሁ።
እንደሚታውቀው ጣሊያን ለሁለተኛ ጊዜ ኢትዮጵያን ሲወር በብዙ መቶ ሺህ ህዝብና ቆራጥ አገር ወዳዶችና የተማረ ኃይል ቢገድልም፣ ከዚያ ባሻገር ከተማዎች ገንብቷል። የአገዛዝ ዘመኔን ለማርዘምና ለማጠናከር እችላለሁ በሚል አስተሳሰብ ኢንዱስትሪዎችን፣ሆስፒታሎችንና የአስተዳደር መዋቅሮችን ዘርግቷል። ጣሊያን በአምስት ዐመት የወረራ ዘመኑ ከጥፋት ባሻገር ፊዩዳሊዝምን እንዳለ አንኮታክቶታል። የስርዓቱን መሰረት አናግቶታል። አፄ ኃይለስላሴ በድል አድራጊነት ስልጣን እንደገና ሲጨብጡ ይህንን ጣሊያን የወሰደውን ርምጃ ተጠቅመው በስረዓቱ ላይ ቢያንስ ለካፒታሊዝም ዕድገት ሊጠቅም የሚችል ፖሊሲ ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ ፊዩዳሊዝምን እንደገና ከሞተበት እንዲያንሰራራ አደረጉ። በዚህም ምክንያት በድሮው የኢኮኖሚና የህብረተሰብ(Economic and Social Status) ደረጃ ብቻ ተደስቶ ሊኖር የሚፈልግ የመሬት ባለቤትና የአስተዳደር ኃላፊ በማድረግ የአገራችንን ዕድገት ሊቀናቀን የሚችል ኃይል ብቅ እንዲል አደረጉ። በታሪክ ውስጥ እንደታየው እንደዚህ ዐይነት ስርዓቶች አንድ ጊዜ ስር ከሰደዱ ሀብትን የሚቆጣጠሩና ስልጣን የጨበጡ ጥቅሜ ይነካል በማለት ህብረተሰብአዊ ለውጥ እንደማይፈልጉና፣ የሚመጣም በተቻላቸው መንገድ ሁሉ መሰናክል እንደሚፈጥሩ ነው። በመሆኑም በተለያዩ የክፍለ-ሀገር ከተማዎች ኢንስቲቱሽናዊ ሪፎርም አድርጎ ኃላፊነትን ሊወስድ ወይም ሊቀበል የሚችል አዲስ ታታሪ ኃይል ከማፍራት ይልቅ የክፍለ-ሀገር፣ የአውራጃና የወረዳ አስተዳደሮችን ላልተማሩ ሰዎች ኃላፊነት በመስጠት፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበረሰብአዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ ንቃተ-ህሊና እንዳይዳብር አደረጉ። ለውጥም እንዳይኖር በሩን ዘጉ። በዚህም ምክንያት አብዮቱ እስከፈነዳ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ ወደ ኋላ በቀሩ የፊዩዳል ኢንስቲቱሽኖች ታስሮ ነበር። እንደሰው ልጅ ማድረግ የሚገባውን ሁሉ እንዳያደርግ ታግዶ ነበር። የእደ- ጥበብ ስራን፣ ኢንዱስትሪንና ንግድን እንዳያዳብር መንገዱ ሁሉ ተዘግተውበት ነበር። የአንድ ሰውም ልጅ ሆነ የአንድ አገር ህዝብ ዕድል ከዚያ አልፎ ሊሄድ እንዳማይችልና በእንደዚህ ዐይነት አኗኗር መኖር ተፈጥሮአዊ መሆኑን አድርጎ ተቀብሎት ነበር። ይህ ዐይነቱ አመለካከት የቱን ያህል ለለውጥ አስቸጋሪ መሆኑን መገንዘቡ ከባድ አይደለም።
2.1 ወደ ኢኮኖሚው ጉዳይም ስንመጣ፣ አፄ ኃይለስላሴ ስልጣናቸው ላይ እንደገና ከተመለሱ ጀምሮ የተከተሉት የኢኮኖሚ ፖሊስ በመሰረቱ ወደ ውስጥ የምርት ኃይሎችን ሊያሳድግ፣ አዳዲስና ውስጠ-ኃይላቸው ከፍተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ኃይሎች ብቅ እንዲሉ የሚያስችል ፓሊሲ አልነበረም። በመጀመሪያ በራሳቸውና በአገዛዙ አርቆ ያለማሰብ የተነሳ ለአዲስ ከበርቴያዊ ኃይል ብቅ ማለት ሊያገለግል የሚችለውን ኢንዱስትሪ እንግሊዝ እየነቃቀለች እንድትወስድ አደረጉ፤ ወይንም ደግሞ ካለምንም መከላከል ዝም ብለው አዩ። እዚህ ላይ አንድ የማይካድ ነገር አለ። ይኸውም እንግሊዝ ብልጣብልጥና የኢትዮጵያን በኢንዱስትሪ ማደግ የማትፈልግ ስለነበረች ውስጥ ያለውን ኢንስቲቱሽናዊ ድክመትና የንቃተ-ህሊና ማነስ መኖሩን ተገንዝባ ሁኔታውን በመጠቀም የኢንዱስትሪ ሀብቶችንና የመገናኛ መስመሮችን እየነቃቀለች ለመውሰድ ቻለች። ከዚህ ባሻገር በህዝቡ ያለማወቅ የተነሳ የጠላት ንብረት ነው እየተባለ ብዙ ሀብት ሊወድም ችሏል። የቀሩትን ንብረቶች መንከባከብ አልተቻለም። ጣሊያን በአምስት ዐመታት ውስጥ የገነባቸውን ከተማዎች ማስፋፋትና ውበት እየሰጡ የህዝቡን አስተሳሰብ ለመስብሰብ እንዲቻል አፄ ኃይለስላሴ በነበራቸው ውስጣዊ የማሰብ ኃይል ድካም የተነሳ ምንም ያደረጉት ነገር የለም። በየክፍለ-ሀገር ከተማዎችም ዘመናዊ አስተዳደር ስላልነበሩ ጣሊያን የሰራቸው እንደ ጅማ የመሰሉ ከተማዎች እንዳይሰፉና እንክብካቤ እንዳይሰጣቸው ተደረጉ። በአንፃሩ የጨአት መቃሚያ ቢቶች፣ ሻይ ቤቶች፣ የሴተኛ አዳሪዎች መደብርና ሱቅ በደረቴ ተስፋፉ። ይህ አንደኛው ጉዳይ ነው።
በከ1950ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በአገራችን ምድር የተተከለው የምትክ ኢንዱስትሪ (Import-substitution Industrialization) ተከላ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በአዲስ መልክ ሊያሳድግ የሚችል ኢንዱስትሪ አወቃቀር አልነበረም። ውስጠ-ኃይሉ በጣም ደካማ የሆነ የኢንዱስትሪ ተከላ ስለነበር፣ በተለይም አዲስ የፍጆታ አጠቃቀምን እንድንለምድና የአቀባባይ ከበርቴ ብቅ እንዲል ከማድረጉ ባሻገር ለአዲስ ዕድገት፣ ለሰፊ የውስጥ ገበያና ለስራ-ክፍፍል መዳበር የሚያመች አልነበረም። የዚህ ዐይነቱ ኢኮኖሚያዊ አወቃቀር ተፈጥሮአዊ ውስጣዊ ድክመት (Structural Weakness) ስለነበረው የአገራችንን አጠቃላይ የኢኮኖሚ አወቃቀር ሊለውጠው (Transform) አልቻለም። የገበያ ኢኮኖሚው በሰፊው እንዲዘረጋና አዳዲስና ውስጠ-ኃይላቸው ከፍ ያሉ የህብረተሰብ ኃይሎች ብቅ እንዲሉ የሚያግዝ አልነበረም። የውስጥ ገበያ በጠንካራ የኢንዱስትሪና ሰፋ ባለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ከመገንባት ይልቅ እዚህና እዚያ፣ እዚያው በዚያው የሚንቀሳቀሱና ደካማ በሆኑ ትናንሽ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ በበመርኮዙ ህዝባዊ መተሳሰር እንዳይኖር አገደ። ይህ በራሱ ደግሞ ከተማዎችና መንደሮች ዘመናዊ በሆነ መልክ እንዳይገነቡ፣ ፈጣንና ዘመናዊ የመገናኛና የመመላለሻ መንገዶች እንዳይዘረጉ አደረገ። ደካማ የሆነው የኢንዱስትሪ መስክና የተሰበጣጠረ የንግድ እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም የተንሰራፋው የፊዩዳል ወይም ከእጅ ወደ አፍ የአስተራረስ ዘዴ የህብረተሰብአችንን ሂደት ሊወስን ችሏል ማለት ይቻላል። በዚህ መልክ ደግሞ አዲስና ብሩህ የሆነ የምሁር እንቅስቃሴ ብቅ ሊልና ሊዳብር አይችልም። አዲስ የከበርቴ መደብም ብቅ ማለት አይችልም። ስለሆነም የአረጀውንና ወደኋላ ጎታች የሆነውን ስርዓት ሰፋ ባለ ሳይንሳዊ የምሁር መሳሪያ ሊዋጋና ለሰፊው ህዝብ ተስፋ ሊሰጥ የሚችል ኃይል ብቅ ሊል አልቻለም። አገዛዙንና የቆመበትን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ስርዓት ጥበባዊ በሆነ መልክ ሊያጋልጥ የሚችል ኃይል አልነበረም።
ወደ ዝርዝር ጉዳዮች ስንመጣ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ የዓለም ገበያና የዓለም ፖለቲካ በአዲስ መልክ የሚዋቀሩበት ዘመን ነበር። ኢኮኖሚያቸው የፈራረሰው የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ኢኮኖሚያቸውን እንደገና መልሰው ለመገንባት የሚጣደፉበት ጊዜ ነበር። የኮሪያ ጦርነት ተደምሮና የጃፓንና፣ በኋላ ደግሞ የደቡብ ኮሪያ ከጦርነቱ በኋላ ደፍ ደፍ ማለት በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ለመሰሉ አገሮች በጣም ጥሩ አጋጣሚ ነበር። እንደሚታወቀው አፄ ኃይለስላሴ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይም ተቀባይነትና ግርማ ሞገስ የነበራቸው መሪ ነበሩ። በአገራችንም ውስጥ እንደ እግዚአብሄር የሚፈሩና የሚከበሩ ነበሩ። በሌላ አነጋገር በታሪካችን ውስጥ ከፍተኛ የርዕዮተ-ዓለምና የፖለቲካ ሊጂቲሜሲ ነበራቸው። ይህንን በህዝብ ዘንድና በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበራቸውን ተቀባይነትና ዝና ወደ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ማህበራዊ ግንባታ ሊመነዝሩት አልቻሉም። ኢትዮጵያን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በማድረግ ራሷን የቻለች አገር እንድትሆን የወሰዱት የፖሊሲ እርምጃ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም።
ይህ በእንደዚህ እንዳለ አፄ ኃይለስላሴ ከ1953 ዓ.ም የመንግስት ግልበጣ ሙከራ የቀሰሙት ምንም ትምህርት አልነበረም። ስርዓቱንና አስተሳሰባቸውን ሊለውጡ የተዘጋጁ አልነበሩም። ሌላ አደጋ እንደሚመጣ የታያቸው ምክር ሲያቀርቡላቸውና በአዲስ ፕላን ሲቀርቧቸው፣ ይጠና፣ ግፉበት፣ ምከሩበትና እርምጃ እንወሰድ ከማለት ይልቅ ስልጣናቸውን የተቀናቀኗቸው ይመስል ሃሳብ ያቀረቡላቸውን ምኒስተሮች ከነበሩበት ስልጣን እንዲለቁ በማድረግ፣ ወይም ደግሞ ይህን ያህልም ተግባሩ ጎልቶ በማይታይ ምኒስተር ቦታ ላይ በማስቀመጥ ሀሞታቸው አንዲፈስ ያደርጉ ነበር ። አፄ ኃይለስላሴ በዚህ ዐይነት የተሳሳተ የፖለቲካ አስተሳሰብ ለብዙ መቶ ዐመታት ስልጣናቸው ላይ ብቸኛው ንጉስ ሆነው ለዘለዓለም እየተወደሱ የሚኖሩ መስሏቸው ነበር። በዚህም የተነሳ እንኳ ለሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ቀርቶ ለቤተሰቦቻቸው የሚያስቡ አልነበሩም። „እኔም ሰው ነኝ ልሞት እችላለሁ“ ብለው ቀደም ብለው ተተኪያቸውን ሊያዘጋጁ አልቻሉም። በተከተሉትም እጅግ አደገኛ ፖለቲካ በአካባቢያቸው ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው የአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የፖለቲካ ክፍተት ጥለው ለመሄድ በቅተዋል። ስልጣን ሊረከብና አገራችንን ካለምንም ውዝግብ ሊያስተዳድር የሚችል ህብረተሰብአዊ ኃይል ሳያዘጋጁ ጥለው አልፈዋል።
2.2 ፖለቲካዊ ስህተት– ይህ ብቻ አይደለም፤ አንድ ህብረተሰብ እንዴት እንደሚገነባ፣ እንደሚተሳሰርና፣ አንድ ህዝብ በአንድ ኃይልና በአንድነት እንዴት መነሳት እንደሚችል ከግንዛቤ ውስጥ ያላስገቡ መሪ አገራችንን ከብዙ አቅጣጫ አጋልጠው ሄደዋል። በዕውቀት ላይ ያልተመሰረተው ፖለቲካቸውና ሳይንሰ-አልባ የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸው ለተለያዩ ብሄራዊ አንድነታችንን ለሚቀናቀኑ ኃይሎች ቀዳዳ በርና መደራጃ መንገድ ሳያውቁት አዘጋጅተው ሰጥተውል። ከውጭ እየገቡ ብሄራዊ ነፃነታችንን የሚቀናቀኑ ኃይሎች እነዚህን ብሄራዊ አንድነታችንን የሚቀናቀኑ የውስጥ ኃይሎች፣ የውስጥ ለውስጥ እንዲያደራጁና በአገሪቱ ላይ አደጋ እንዲያደርሱ ሁኔታውን አመቻችተዋል። በኢኮኖሚው ድክመትና ብሄራዊ ባህርይ እጦት ምክንያት የተነሳ፣ በጊዜው የሰፈነውን የጭቆና አስተዳደር ተገን በማድረግ እዚህና እዚያ በብሄረሰብ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ፣ ብሄረሰባችንን ነፃ እናወጣለን የሚሉ እንደ አሸን እንዲፈልቁ አደረጉ። የኤርትራን ሁኔታና ጥያቄ በስነስርዓትና ፖለቲካዊ በሆነ መልክ መፍታት ሲገባቸው፣ አሻጥርንና የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲን የተካኑት መሪ ሁኔታውንና ሰቆቃውን ረገብ ከማድረግ እንዲባባስ አደረጉት። ከውጭና ከውስጥ የሚሸረበውን በአገራችን ላይ የሚያንዣብበውን አደገኛ ሁኔታ ባለመመልከታቸው አገራችንም ሆነ የእሳቸው አገዛዝ አደጋ ላይ ወደቁ።
ከዚህም በላይ አፄ ኃይለስላሴ፣ አሪስቶክራሲውና ቢሮክራሲው፣ እንዲሁም የተወሰነው የተማረው ወይም ኤሊት የሚባለው ኃይል የዓለምን ፖለቲካ በየዋህነት መነፅር ነበር የተመለከቱት። በአገሮች መሀከል ፉክክርነት እንጂ ወዳጅነት ሊኖር እንደማይችል የተገነዘቡ አልነበሩም። በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ብቅ ያለው አዲስ ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሚሊታሪ አሰላለፍና ኃይል በኢኮኖሚያቸው ወደ ኋላ በቀሩና ህብረተሰብአዊ መተሳሰር በሌላባቸው አገሮች አመቺ እንዳልነበር ግንዛቤ ውስጥ የተገባ አልነበረም። በዚህም ምክንያት ከአሜሪካንና ከተቀረው የምዕራቡ ኢምፔሪያሊስት አገር ጋር መወዳጀትና የተፈጥሮ ጓደኛ ማድረግ የቱን ያህል የራሱ መዘዝና መርዝ ይዞ እንደሚመጣ ጥናትና ጥንቃቄ አይደረገም ነበር። በዚህም ምክንያት ለአሜሪካንና ለተቀሩት የምዕራብ ኤምባሲዎች የተሰጠው ጋሻ መሬት የሚያክል የአምባሰደሮች መስሪያ ቤት አገራችንን ወደ ቅኝ-ግዛት አስተዳደር ደረጃ ለውጧታል ማለት ይቻላል። በየትኛውም አገር የማይታይ አጉል ለጋሽነትና የዋህነት ከውስጥ የአገራችንን ብሄራዊ ነፃነት ለሚቀናቀኑ ኃይሎች ማደራጃም እንደሚጠቅምም የተገነዘበ አልነበረም።
ይህንና ዘመናዊው የመንግስት ቢሮክራሲ፣ የሚሊታሪና የፀጥታው አወቃቀር በአሜሪካንና በተቀሩት የምዕራብ መንግስታት ተፅዕኖና ቁጥጥር ስር መውደቁ አንድ መንግስት ለአገርና ለህዝብ መስራት የሚገባውን ሚና እንዳይሰራ ሊታገድ በቅቷል። ከአውሮፓ የህብረተሰብ ታሪክም ሆነ ከጃፓንና ከደቡብ ከኮሪያ የምንማረው ነገር አንድ መንግስት በስነስርዓትና ለውጭ ኃይሎች መግቢያ ቀዳዳ እንዳይኖረው ሆኖ ከተደራጀ ለኢኮኖሚና ለህብረተሰብ ዕድገት አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር ነው። በታቃራኒው የመንግስቱን መኪና ለኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ክፍት የሚያደርግ ደግሞ መደላደልና ታሪካዊ ስራ መስራትን ሳይሆን ከአጭር ጊዜም ሆነ ከረዢም ጊዜ አንፃር ህብረተሰብአዊ ትርምስ ጥሎ እንደሚሄድ ነው የሚታወቀው። ስለዚህም አፄ ኃይለስላሴና ቢሮክራሲው ብሄረተኝነትና ንቃተ-ህሊና የጎደለው ፖለቲካ መከተላቸው ለሻቢያ፣ ለወያኔና ለሌሎች ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች መኮትኮቻና መደራጀት አመቺ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። እነዚህ ፀረ-ዲሞክራሲ፣ ፀረ-ስልጣኔ፣ ፀረ-ህዝብና ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ከተቀረው የምዕራቡ የካፒታሊስት ዓለም ድጋፍ ባያገኙ ኖሮ ብቻቸውን ሊደራጁና ኢትዮጵያን ሊቀናቀኑና አደጋ ውስጥ ሊጥሏት ባልቻሉ ነበር።
ስለሆነም ከላይ የዘረዘርኳቸውን መሰረተ-ሃሳቦች በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የተሰሩ ትልቆቹ የስትራቴጂክ ስህተቶችና የታሪክ ወንጀሎች ብዬ ጠራቸዋለሁ። ምክንያቱም አንድ መሪና አገዛዝ ለራሱና በራሱ ብቻ ተከልሎ ስለማይኖር የአንድን ህብረተሰብ አወቃቀር በየጊዜው መመርመር ስለአለበት ነው። የጎደለው እንዲሻሻል፣ የተሰበረው በየጊዜው እንዲጠገን ወይም ደግሞ በአዲስ እንዲለወጥ ማድረግ የአንድ አገዛዝና የፖለቲካ መሪ ታሪካዊና ሞራላዊ ግዴታ ነው። ፖለቲካን በቅጡ የማይረዳ፣ የሚነግሩትን የማይሰማ፣ የነገሮችን ሂደት ለመከታተል ብቃት የሌለው መሪ የመጨረሻ መጨረሻ በአገር ላይ ጉዳት አድርሶ ነው የሚሄደው። እንደዚህ ዐይነቱ የተበላሸ የፖለቲካ አካሄድ ወይም ግንዛቤ የጎደለው ፖለቲካ በተለያዩ አገሮች በተለያየ መልኩ በመካሄዱ ብዙ አገሮችን ውድቀት ውስጥ ከቶአቸዋል። እንዲንኮታኮቱና ተመልሰውም እንዳይንሰራሩ አድርጓቸውል። ከውድቀትና ከመከስከስ ተመልሰው ሊያንሰራሩና በሁለት እግራቸው ቆመው ሊሄዱ የሚችሉ አገሮች ከፍተኛ የሆነ የአደረጃጀት ባህልና ልምድ ያላቸው አገሮች ብቻ ናቸው። ለዚህ ምሳሌ ልትሆን የምትችለው ድሮ ምዕራብ ጀርመን እየተባለች ትጠራ የነበረችው አገር ነች። በሁለተኛው ዓለም ጦርነት የደረሰባትን ውርጅብኝና የቦምብ ናዳ ያፈራረሰውን ከተማዎቿንና ኢኮኖሚዋን በአስራ አምስት ዐመታት መልሳ በመገንባት ዛሬ የምናየው ደረጃ ለመድረስ ችላለች። በተቃራኒው ግን እንደኛ ያሉ አገሮችና ህብረተሰቦች እንደዚህ ዐይነት ውርጅብኝ ቢወርድባቸው ኖር በሁለትና በሶስት መቶ ዐመታት እንኳ ተመልሰው ማንሰራራት አይችሉም።
3.0 በአብዮቱ ወቅት የተፈጸመ የፖለቲካ ስትራቴጄያዊ ስህተት- ሁለተኛው ትልቁ ስትራቴጂያዊ ስህተት የምለው የ1966 ዓ.ም የየካቲቱን አብዮት የመንከባከብና በጥንቃቄ የመምራት ላይ የተደረገው ስህተት ነው። እንደሚታወቀው የየካቲቱ አብዮት ቀድሞ የተዘጋጀና ታስቦ የመጣ አይደለም። ጊዜውና ሁኔታው የፈጠረው ነው። የህዝባችን ሰቆቃ፣ መበደልና በኑሮ መሰቃየት የተነሳ የተፈጠረ ነው። እዚህና እዚያ በሚካሄዱ ወይም ደግሞ በከፍተኛ ድርጅታዊና ምሁራዊ ድጋፍ ተመርኮዞ ወይም ተደግፎ አይደለም የየካቲቱ አብዮት ሊፈነዳ የቻለው። የየካቲቱ አብዮት የአገዛዙን ደካማና ብቃት ማነስ ያጋለጠ ነው። አገዛዙ የቱን ያህል በደካማ መሰረት ላይ የቆመ መሆኑንና ዝም ብል በመመጻደቅ ብቻ የሚገዛ እንደነበር ያጋለጠ ነው። እንደዚህ ዐይነት በግብታዊ መልክ የሚንቀሳቀስን ህዝባዊ ኃይል ሊቋቋም ያልቻለ መንግስትና ምንም ዐይነት ስትራቴጂያዊ ዓላማ ባልነበረው አገዛዝ ነበር አገራችን አርባ ዐመት ያህል የተረገጠችው።
ስለሆነም የየካቲቱ አብዮት ሲፈነዳ ግራ ያልተጋባ አልነበረም። የፖለቲካውን ክፍተት ሊያሟላና ነገሮች ከቁጥጥር ውስጥ ከመውጣታቸው በፊት መስመር ሊያሲዝ የሚችል የተደራጀ ህብረተሰብአዊ ኃይል አልነበረም። ስለሆነም የየካቲቱ አብዮት የታሪክ ግዴታ ቢሆንም፣ በሌላ ወገን ደግሞ በነበረው ህብረተሰብአዊ ድክመት የተነሳ ለአደጋ የተጋለጠ ነበር። ይሁንና ግን፣ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዐመታት፣ በተለይም በመጀመሪያው ዐመት የኢትዮጵያ ህዝብ ብዙ ነገሮችን በጉግት ይጠባበቅ ነበር። በመሆኑም በህዝብና በምሁሩ ግፊት የተወሰዱት የመሬት ሪፎርም፣ የፊናንስ፣ የኢንሹራንስና ትላልቅ የንግድ ተቋሞች በመንግስት ቁጥጥር ስር መዋልና አንዳንድ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችም መወረስ ለለውጡ አስፈላጊ ነበሩ። እንደሚታወቀው እነዚህ ተቋሞች 90 በመቶ በሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ምንም ዐይነት የጎላ አዎንታዊ ሚና አለነበራቸውም። ለሰፊው ህዝብ የስራ መስክ የሚከፍቱና ገቢ የሚያስገኙለት የኢኮኖሚ ተቋሞች አልነበሩም። ስለዚህም በነሱ መወረስ የተነሳ ቅሬታ የገባው ወይም እርምጃውን ትክክል አይደለም ብሎ ዘመቻ ያካሂድ የነበረ በጊዜው የሰፈነውንና የነበረውን የኢትዮጵያን ህዝብ የኑሮ ሁኔታ የተገነዘበ አልነበረም ከማለት በስተቀር ብዙም ማብራሪያ መስጠት የሚያስፈልግ አይመስለኝም። በሌላ ወገን እርምጃዎች ሲወሰዱ በቂ ጥናት ተወስዷል ወይ አልተወሰደም በሚለው ላይ መነጋገር ይቻላል። ይህም ቢሆን ከጊዜውና ከነበረው የኃይል አሰላለፍ አኳያ ብዙም ማብራራት አይቻልም። አንዳንድ ስህተቶች ቢሰሩም በእንደዚህ ዐይነቱ ውዝግብና ሳይታሰብ በመጣ ሁኔታ ውስጥ ስህተቶች መሰራታቸው አይቀርም። በተለይም ደግሞ ወደ ኋላ ዞር ብለን የኢትዮጵያን ህዝብ የኑሮ ሁኔታ በምንመረምርበት ጊዜ ስለእርምጃዎች በበቂ ጥናት መወሰድና አለመወሰድ በቂ ግንዛቤ ልናገኝ እንችላለን። ቁም ነገሩና የሚያከራክረን ጉዳይ ይህ አይደለም።
የሚያከራክረን ጉዳይ እነዚህ እርምጃዎችና አንዳንድ ዲሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ተግባራዊ መሆን ሲጀምሩ እነዚህን እየተንከባከበ ተግባራዊ ሊያደርግ የሚችል ኃይል ነበር ወይ? በዚህ መሰረታዊ ጉዳይ ላይ ነው መወያየት ያለብን። በእኔ ዕምነትና ጥናት በጊዜው የተወሰዱትን ዲሞክራሲያዊ ሪፎርሞች ቀስ በቀስ ተግባራዊ ሊያደርግ የሚችል በቂ ኃይል ነበር። በጊዜው የነበረው ችግር ችሎታና በቂ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች እጥረት የመኖሩ ጉዳይ ሳይሆን፣ አብዛኛው ተራማጅ ነኝ የሚለውን ኃይል በአንድ ፕሮግራም ክልል ስር ለማሰለፍ ያለመቻልና በአንዳንድ ድርጅቶች ዘንድ ፍላጎት ያለመኖር ነበር። እያንዳንዱ ድርጅት ኢትዮጵያን የተገነዘበው የብዙ ሚሊዮን ህዝብ አገርና የተለያየ አስተሳሰብ ያላቸው በደንብ ያልተደራጁ ድርጅቶች አገር አድርጎ አልነበረም የቆጠረው። በተለይም የአብዛኛው ታጋይ ነኝ ባይ ድርጅት ዓላማ ስልጣን ላይ እንዴት ብዬ ቁጥጥ እላለሁ ከማለት በሻገር ማሰብ የሚችል አልነበረም። ስለሆነም እንዴት አድርጌ በአንድ ጊዜ ይህንንም ያንንም አግበስብሼ ስልጣን ላይ እወጣለሁ ነበር ህልሙና ሩጫው። ህልሙና ትግሉ ሰፊውን ህዝብ በስነስርዓት ማንቃትና የነገሮችን ሂደት ተገንዝቦ እጅ ለእጅ ተያይዞ አገር መገንባት አልነበረም። ስለሆነም በከፍተኛ ደረጃ በስልጣን በመታወሩ የተነሳ አንዳንድ ድርጅቶች የነሱን አካሄድና ዓላማ የሚቃወም በሙሉ እንደጠላት የሚፈረጅበትና ክትትል የሚደረግበት ነበር። ይህ ጉዳይ በጠቅላላው ተራማጅ ነኝ በሚለው ውስጥ ትልቅ መፈራራትን አስከተለ። መጠራጠርን አመጣ። በሌላ ወገን ደግሞ ይህ ዐይነቱ የልጆች ጨዎታ የኢትዮጵያን አንድነትና ብሄራዊ ነፃነት፣ እንዲሁም ማደግ ለሚቀናቀኑ ኃይሎች አመቺ ሁኔታ ፈጠረላቸው። ከዚህ በሻገር በስንት ጥረት እዚህና እዚያ የተቋቋሙትና የተደራጁት ህዝባዊ ድርጅቶች፣ ማለትም የሰራተኛው የሙያ ማህበር፣ የቀበሌ ማህበራት፣ የገበሬው ማህበር፣ የሴቶችና የወጣቶች ድርጅቶች ለአንድ ዓላማ እንዲሰለፉ ከማድረግ ይልቅ እያንዳንዱ ተራማጅ ነኝ የሚል ድርጅት የራሱ ተቀጢያ ለማድረግ መሯሯጥ ያዘ። በመሰረቱ እነዚህ ድርጅቶች ለሲቭል ማህበረሰብ፣ ብሎም ቀስ በቀስ ቢሮክራሲውን ሊተኩ የሚችሉ ነበሩ። ይሁንና ግና ርቆ ማሰብ የተሳነው በተራማጅ ስም ይምል የነበረው የህብረተሰብ ክፍል ድርጅቶችን ለመጥመድ ባለው ፍላጎትና ሽቅድምድሞሽ የተነሳ ድርጅቶችንንም ሆነ ሰፊውን ህዝብ ትልቅ ውዥንብር ውስጥ ከተታቸው። የመጨረሻ መጨረሻ እነዚህ ድርጅቶች በደርግ ቁጥጥር ስር እየወደቁ ሲመጡ ዲሞክራሲያዊና ህዝባዊ ባህርያቸውን በማጣት በነፃ ሊንቀሳቀሱ የማይችሉ ሆኑ። የአብዮቱ ድሎች በዚህ መልክ በራሱ ተራማጅ ነኝ በሚለው ስትራቴጂያዊ የፖለቲካ ስህትተ የተነሳ ተቀለበሱ፤ ወይም ደግሞ ተግባራቸው ሙሉ በሙሉ እንዲቀየር በማድረግ አንዳንዶቹ ወደ መጨቆኛ መሳሪያነት ተለወጡ።
በአብዮቱ ወቅት የነበረው ትልቁ ችግር በአብዮቱ ውስጥ ይሳተፍ የነበረውና በድርጅት ደረጃ የተደራጀው ይምል ይግዝ የነበረው በማርክሲዝም ስለነበር ነው። ስለሆነም ቢያንስ ልዩነቶችን ለማሳየት በተለያዩ የፖሊሲ ነክ ነገሮች ላይ በሰፊው የክርክር መድረክ ከመክፈት ይልቅ በማንም አገር ታሪክ ውስጥ በማይታወቅ መልኩ ጠበንጃ ቀስሮ መግደልና መገዳደል ሆነ። በዚህ መልክ ይህ ትልቅ ቲዎሪና ከስሙ በስተቀር ለብዙ ሰዎችም ግልጽ ያልሆነና ለመጠናትና ለመተንተን ዕድል ያላገኘ በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ፣ በተለይም አብዮቱን አጥብቆ በሚጠላው ግንዛቤ ውስጥ የተወሰደውና አጉል ዘመቻም ማካሄድ የተጀመረው ማርክሲዝምንና ሶሻሊዝምን ከአመጽ ጋር በማማያዝ ነበር። በእርግጥም አንድ ህዝብ ከሰላምና ከእረፍት፣ እንዲሁም እጅ ለእጅ ተያይዞ አገርን በጋራ ከመገንባት ይልቅ እንደዚህ ዐይነቱ ትርምስ ሲፈጠርና ወንድም ወንድሙን ሲገድል ሲያይ የግዴታ ሶሻሊዝምንና ማርክሲዝምን ከአመጽና ከፀረ-ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ጋር ማያያዙ የማይቀር ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ በተለይም የካፒታሊዝምን ዕድገት ከአመጽ ጋር ሳይሆን እንዲያው በጭፍኑ ከሰላም ጋር የሚያያይዙና ካለህብረተሰብአዊ ውዝግብ በፈቃድና በመምረጥ የተዘጋጀና የተገኘ ስርዓት አድርገው ለሚቆጥሩ በማርክሲዝም ላይ በቀላሉ ዘመቻ ለመክፈት ጥሩ አጋጣሚ እንደሚሆንላቸው የተገነዘበ አልነበረም። እዚህ ላይ ለማለት የምፈልገው፣ ከብዙ አቅጣጫ ሳይጠናና በአንዳንድ ድርጅቶች ውስጥ ሰፊ ክርክር ሳይደረግበት ወደ ጠብመንጃ ትግል ማምራት የቱን ያህል በማናውቀው ነገር ላይ ጥላቻን ለማሳደር እንዳስቻለን ነው። ይህም በመሆኑ አብዮቱ ከከሸፈ በኋላ በማርክሲዝም ስም ሲምልና ሲገዘት የነበረው ከዚያ በኋላ ስሙን እንኳ ለመጥራት እንድትልቅ ወንጀል አድርጎ ነው የቆጠረው። ሀፍረት ውስጥ መግባት ነው የጀመረው። „በዚህ ረገድና በዚህ ምክንያት ነው ስህተት ሊፈጠር የቻለው“ ብሎ ስህተቱን ሊያስረዳና አዲስ የትግል ፋና ሊቀድ አልቻልም። ይህንን እዚህ ላይ የማትተው የማርክሲዝም ናፍቆት ስላለኝ፣ ወይም ደግሞ አሁንም ቢሆን የህብረተሰባችንን ችግር ሊፈታ የሚችለው ብቸኛውና አማራጭ የሌለው ቲዎሪ ማርክሲዝም ነው ብዬ ስለማምን ሳይሆን፣ የተወሰኑ ኃይሎች በደንብ ሳያገናዝቡ የወሰዱት የአመጽ ርምጃ በማናውቀው ቲዎሪና አዲስ የህብረተሰብ ስርዓት ለመግንባት ያስችላል በተባለው ላይ እንደገና ተመልሰን የጭፍን ጥላቻ ማሳደራችንን ለማሳየት ብቻ ነው። ያም ሆነ ይህ በማርክሲዝምና በሶሻሊዝም ስም የተደረገው ግፍና መገዳደል አማራጭ እንዳይኖረን አድርጎናል። ምክንያቱም እስከዛሬም ድረስ የምናውቀው ሁለት ነገሮች ብቻ ስለሆኑ ነው። ሶሻሊዝም ወይም የገበያ ኢኮኖሚ። ይህ ዐይነቱ የግራው ፖለቲካዊ የስትራቴጂ ስህተት እስከዛሬ ድረስ ልንወጣ የማንችለው ትልቅ ውዥንብር ውስጥና የጨለማ ሁኔታ ውስጥ ሊከተን ችሏል። ለአገራችን ዕድገት የሚያመች ሌላ አማራጭ ሳይንስና ቲዎሪ እንዳንፈልግ አግዶናል።
ከዚህ ስንነሳ ሌላው ትላቁ የፖለቲካ ስህትተት፣ በዚህ ወይም በዚያ መስመር የተሰለፈው ተራማጅ ነኝ የሚለው ኃይል በጊዜው አገራችን የቱን ያህል በጠላት የተከበበችና ለጠላት ኢላማ ያመቸች መሆኑን የተገነዘበ አልነበረም። የኢትዮጵያን መዳከም በመገንዘብ በ1967 ዓ.ም ሻቢያ ጦርነቱን ያፋፋመበት ጊዜ ነበር። ሶማሊያ ደግሞ በተለይም የምስራቁን ክፍል ለመውረርና የታላቅ ሶማሊያ ህልሟን ተግብራዊ አደርጋለሁ ብላ የምትዘጋጅበት ወቅት ነበር። ሱዳን፣ ግብፅና የተቀሩት አረብ አገሮች በሙሉ የሚጠባበቁት የኢትዮጵያን መዳከምና መበታተን ነበር። በዚህ ላይ ደግሞ ሳያስበው ከቁጥጥሩ ስር የወጣችበት የመሰለውና ብሄረተኝነትን አጥብቆ የሚጠላው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረ-አበሮቹ ሁሉ የሚያስከትሉትን አደጋ ተራማጅ ነኝ የሚለው ኃይል በደንብ የተገነዘበ አልነበረም። ይህንን ሁሉ ግንዛቤ ውስጥ ሳያስገባ ነው ስልጣን ወይም ሞት ብሎ በመነሳት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ አጠቃላይ ጦርነት ያወጀው። ጦርነቱ እንደሚባለው የኢትዮጵያን ህዝብ ነፃ ለማውጣት የሚካሄድ ትግል አልነበረም። በግራም መጣ በቀኝ በኩል ጦርነቱ በመጀመሪያ ደረጃ ደርግን ለመጣል የሚደረግ ትግል ሳይሆን በተጨባጭ የሚመስለው ኢትዮጵያን ለመበታተን ነበር። ከዚህ ውጭ ማሰብ ስህተት ነው።
በዚህ ዐይነቱ ስትራቴጂያዊ ስህተት ኢትዮጵያችንን አደጋ ላይ መጣሏ ብቻ ሳይሆን በሁለትና በሶስት ትውልድ ሊተካ የማይችል ምሁራዊና የለውጥ ፈላጊ ኃይል እንዲወድም ተደረገ። ይህ ብቻ ሳይሆን ሳያውቀው የዚህና የዚያ ድርጅት አባል የሆነ ሁሉ በዚህኛው ወይም በዚያኛው ክንፍ ህይወቱ እንዲቀነጠስ ሆኗል። ልጆቻቸው የዚኽኛው ወይም የዚያኛው ድርጅት ካድሬዎች የነበሩ በመጠርጠርም እነሱም የጥይት ሰለባ ሊሆኑ በቁ። አንዳንድ ቤተሰቦች አስር የሚቆጠሩ እንዳሉ የጥይት ራት ሆነዋል። የሚወዷትን ኑሮና ህይወት ሳያውቁት ልጆቻቸው የዚህኛው ወይም የዚያኛው ደርጅት ካድሬ በመሆናቸው ህይወታቸው እንዲቀነጠስ ሆኗል። በህይወት የተረፉት ደግሞ በውድ ልጆቻቸው መሞት የተነሳ በሀዘን እንዲሰቃዩ ሆነዋል። ከዚህም በሻገር አንደኛው ተራማጅ ነኝ የሚል ድርጅት ሌላውን ያሳድድ ነበር። አንዱ ሌላውን ይገድል ነበር። ይገዳደሉ ነበር። በዚህም ይደሰቱ ነበር። በዚህ ዐይነቱ የመገዳደል ስልት እንደሚባለው ኢትዮጵያችን ብርቅ ልጆቿን ነው ያጣችው። ይህ የተራማጆች ርስ በርስ መተላለቅ ደግሞ ስልጣንና ፓለቲካን ምን እንደሆን መገንዘብ ለማይችለውና የአገር አስተዳደር ብቃት በሌለው እጅ ስር እንዲወድቅና አብዮቱ ከሸፈ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያን ዕድል ወሳኝ ሆነ። ደርግ የሚባለው ከሚሊታሪው የተውጣጣው ኃይል ሳያውቀው በአብዮቱ ውስጥ ሰተት ብሎ በመግባቱ ጥቂት ጉዞ ከተንገዳገደ በኋላ ራሱ ደግሞ በተቀሩት ተራማጆች ነን በሚሉት ላይ ጥይቱን ሰነዘረባቸው። ካለምንም ምህረት ቀነጠሳቸው። ስልጣን ለእኔ ብቻ ነው የሚገባው በማለት ብቻውን በመንገዳገድና ያልተማረ ካድሬ በመሰብሰብ አገር ማመስ ጀመረ። ሁሉም ነገር ወደጦር ሜዳ ብሎ አወጀ። ፉከራና ቀረርቶ ሆነ። ከእንግዲህ ወዲያ ማንም ሊቀናቀነኝ የሚችል ኃይል የለም በማለት መዝናናት ጀመረ። አገር ታመሰች።
በዚህ ሁሉ አርቆ ያለማሰብ የትግል ስልት ማነው ተጠቃሚው? የኢትዮጵያ ጠላቶች ካልሆኑ በስተቀር፣ ተራማጁም ሆነ ራሱ በተራማጆች ስም የሚመጻደቀው ደርግና ካድሬዎች ተጠቃሚ ሊሆኑ አልቻሉም። የነፃ አውጭ ድርጅቶች ነን የሚሉትም ኢትዮጵያን በመበታተንና በማዳከም መጠቀም ችለናል የሚሉ ከሆነ በጣም ስህተተኞች ናቸው። እንደምናየው ነፃ ወጣሁ ያለችው ኤርትሪያ ዛሬ ህዝቧ፣ በተለይም ወጣቱ እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚኖርባት አገር ነች። ህዝቡና በተለይም ወጣቱ ህይወቱ ከጦርነትና ከመበርገግ ጋር ብቻ የተያያዘ እንዲሆን የተረገመ ሆኗል። ነፃነት የሚለው ትልቅ ግዙፍ ፅንሰ-ሃሳብ አንድ ህዝብና ታዳጊ ትውልድ የመፍጠር ችሎታውን እየተጠቀመ አዲስ ህይወት የሚገነባበት ሳይሆን ወደ ጨለማነትና ወደ ዘለዓለማዊ ጦርነት የተቀየረበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ራሷም ሶማሊያ እንኳ ተጠቃሚ አልሆነችም። የራሷ የመሪዎቿ አርቆ አለማሰብና የድንቁርና ፖለቲካ፣ እንዲሁም የኢምፔሪያሊስቶች አሻጥር ሰለባ ነው የሆነችው። ምናልባት ሱዳንና ግብፅም ተጠቃሚዎች ሆነናል ብለው ገምተው ይሆናል። እነሱም ቢሆን ስህተተኞች ናቸው። እንደምናየው ሱዳን ለሁለት ተከፍላለች። የሁለቱም ሱዳኖች ተቻችሎ መኖር በፀና መሰረት ላይ የቆመ አይደለም። በምዕራቡ ዓለም በአንድ በኩልና በቻይና በሌላ ወገን በሚደረገው ፍጥጫና የጥሬ-ሀብት ቅርምት እሽቅድምድሞሽ እንደገና ጦርነት የሚነሳበት ሁኔታ ሊመጣ ይችላል። በሁለቱም ሱዳን አገዛዞች ውስጥ ጠንካራና የሰለጠነ የሲቭል ህብረተሰብ አካል ባለመኖሩና፣ በሰለጠነ ባህል የሚገለጽ እንቅሳቃሴ ስለማይታይ ሁለቱም ወደ መፈረካከስ ሊያመሩ ይችላሉ። የግብጽም ሁኔታ ዛሬ እንደምናየው ነው። በሚሊታሪዊና በአክራሪው የእስላም እንቅስቃሴ መሀከል መፋጠጡና መገዳደሉ ይቀጥላል። ያም ሆነ ይህ ተባለ እነዚህ በአንድ ወቅት ሲመጻደቁ የነበሩ የአካባቢ አገሮች በውስጥ በነበራቸው የአስተዳደር ድክመትና አርቆ ያለማሰብ ምክንያት ራሳቸው ተመለሰው ራሳቸውን እያፈራረሱ ነው። የዚህ ሁሉ ችግር የፖለቲካን ግንዛቤ ካለመረዳት የተነሳ ነው። በሰፊ ምሁራዊ መሰረት ላይና በሰፊ ኢኮኖሚ ላይ ያልተገነባ ህብረተሰብ የኋላ ኋላ መፈራረሱ የማይቀር ነው። ይህም የሚያረጋግጠው የፖለቲካ አሻጥርና የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ የፖለቲካ ስልት ከሆኑ ለአገር ዕድገት እንደማይበጁ ነው። የዚህ ሁሉ ችግር ደግሞ ሰፋ ያለና ጥልቀት ያለው እንዲሁም በሰፊ ምሁራዊ መሰረት ላይ ያልተገነባ ዕውቀት ያለመኖር ችግር ነው። የዚህ ሁሉ ችግር አንድ አገርና ህብረተሰብ እንዴት መመስረትና ከውስጥም ሆነ ከውጭ በሰላም ሳይረበሽ ሊጓዝ ይችላል የሚለው ስትራቴጂያዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ ጭንቅላት ውስጥ ካለመቋጠር ወይም ግንዛቤ ውስጥ ካለማስገባት የሚከሰት ነው።
በአገራችን ድክመት የተጠቀሙት አሜሪካና የምዕራቡ ዓለም ብቻ ናቸው። እንደሚታወቀው እነዚህ ኃይሎች የዓለምን ዕድል እኛው ብቻ ነን ወሳኝ ብለው ያስቀመጡና በዚህም ሎጂክ የሚንቀሳቀሱም ናቸው። ስለሆነም ከነሱ ቁጥጥር ውጭ እያንዳንዱ አገር የራሱን ዕድል በራሱ ጥረት መወሰን የለበትም። የፈለገውን ህብረተሰብ በሚፈልገው መልክ ማደራጀት የለበትም። በመሆኑም በራሱ ጥረት ተነሳስቶ ታሪክ ሰራለሁ የሚል ህዝብ ሁሉ በእንጭጩ መቀጨት አለበት። ጠንካራ ኢኮኖሚና ህብረ-ብሄር መገንባት የለበትም። የኢንዱስትሪ አብዮት ማካሄድ የለበትም። እንደ ማህበረሰብ፣ ህብረተሰብና ታሪክን እየሰራ አዳዲስ ባህልን እያደራጀ መኖር የለበትም። ይህ ዐይነቱ አካሄድም ቢሆን የአጭር ጊዜ አመለካከትና ዕቅድ እንጂ ከረጅም ጊዜ አንፃር ሲታይ ብዙም የሚያስኬድ አይደለም። ለትርፍና ለኃያልነት ብቻ ተብሎ የሚካሄድ ደካማ አገሮችን ማፈራረስ ወይም በራስ ቁጥጥር ስር ማድረግ የመጨረሻ መጨረሻ በራስ ላይ ጥይት እንደመቀሰር ይቆጠራል። የዓለምን ሰላም ያናጋል። ኃይል እንዲያልቅ ያደርጋል። ጦርነት እዚህና እዚያ ሲፋፋም የዓለም ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የዓለም ኢኮኖሚም ይናጋል። አምራቾች ምርቶቻቸውን የማይሸጡበት ሁኔታ ይፈጠራል። እንደሚታወቀው ካፒታሊዝም የጥሬ ሀብት ብቻ ሳይሆን ሰፊ ገበያም ያስፈልገዋል። በተትረፈረፈ መልክ የሚመረተውን ምርቱን ሌላ አገር ለመሸጥ በሌላው አገርም የመግዛት ኃይል መኖርና ማደግ አለበት። ይህንን ለማድረግ ደግሞ የግዴታ እያንዳንዱ አገር የራሱን ኢኮኖሚና የውስጥ ገበያውን ለማሳደግ ዕድል ማግኘት አለበት። ከተማዎች መገንባት አለበት። ህዝቡን ሊያገናኙ የሚችሉ ልዩ ልዩ የመመላለሻና የመገናኛ መስመሮች መዘርጋት አለባቸው። የህዝቡ ምርታማናት ማደግ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚደገፍና ለውስጥ ገበያ የሚውል መሆን አለበት። በተለያዩ የኢኮኖሚ መስኮች መሀከል መተሳሰርና የንግድ ልውውጥ መኖር አለበት። በዚህ መልክ የአንድ አገር ኢኮኖሚ ወደ ውስጥ ሲያድግና ሲስፋፋ፣ አዳዲስ የፍጆታ አጠቃቀምን የሚለምደው የህብረተሰብ ክፍል የወጭ ምርቶችን እየገዛ ለመጠቀም ፍላጎቱ ያድጋል። ይህ ሁኔታ ለዓለም ገበያ ማበብና በአገሮች መሀከል የንግድ ልውውጥ እንዲኖር ያመቻል። በአንፃሩ ግን አንድ አገር ወደ ጦርነት እንዲያመራ የሚደረግ ከሆነ ሰፋ ያለ ገበያ የመፍጠርና የምርት ኃይሎችን የማሳደግ ችሎታ ሊኖረው አይችልም። ስለሆነም በካፒታሊስት አገሮች የሶስተኛውን ዓለም አገሮች ለማዳከም የሚደረገው አጉል ተንኮልና የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካ አጭር እግር እንዳለው ሰው ነው። ብዙም መጓዝ የማይችል ከአጭር ስሌት አንፃር የተነደፈና የታሰበ የዓለምን ደህንነት የሚያናውጽ አቅድ የሌለው ፖለቲካ ነው። በተጨማሪም ዛሬ ኢምፔሪያሊስት ነኝ እያለ የሚመጻደቅ ኃይል ነገ ሊወድቅ ይችላል። ይህ ጉዳይ በታሪክ ውስጥ በተደጋጋሚ ታይቷል። ፐርሺያ፣ ግሪክና የሮማውያን ኢምፓየሮች በጥጋብና በመመጻደቅ ነው የተንኮታኮቱት። ከዚህ ዕድል የሚያመልጥ አንድም ኃያል መንግስት በፍጹም ሊኖር አይችልም። እያበጠ ሲሄድ በጥጋቡ ይፈነዳል።
ያም ሆነ ይህ የየካቲቱ አብዮት ድሎች በተግባር መመንዘር ያልቻሉትና ህዝባችንና የተቀረው ዲሞክራሲያዊ ኃይል በሰላምና በአድነት ተነስተው ለጋራ ዓላማ መታገል ያልቻሉት በራሳችን አርቆ አለማሰብ የተነሳ ነው። የዛሬውን ብቻ በማየታችን ነው። ነገ በአገራችን ላይ ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ከሁሉም አንፃር ባለመመልከታችን አገራችንን ማጋለጥ ችለናል። ሲነገረንና ስንመከር ባለመስማታችን የታሪክ ወንጀለኞች ልንሆን በቅተናል። በበቂው ያለተማረውንና የዋሁን ህዝባችንን ለጠላት አጋልጠነዋል። ከባርነት ነፃ ወጣሁ ብሎ ደስ ማለት ከጀመረው በኋላ እንደገና ወደ ባርነት እንዲመለስ አድርገነዋል። ከፊዩዳሊዝም በባሰ ሁኔታ ውስጥ እንዲውድቅና የውስጥና የውጭ ኃይሎች ሰለባ እንዲሆን ሳናውቀው አስተዋፅዖ ለማድረግ በቅተናል። በዚህ ዐይነቱ የትርምስ ሁኔታና በደርግ የአገዛዝና አርቆ ያለማሰብ ድክመት የተነሳና፣ በተለይም ከውጭ እየተደገፈ በመጣ ኃይል የኢትዮጵያ ህዝብ አዲስ የጨለማ ምዕራፍ ስር ሊወድቅ ችሏል። ይኸኛው ዘመን ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን ጊዜ የሚያካትት ነው። የወያኔ አገዛዝ ዘመን እለዋለሁ።
4.0 ወደ ሌላው የሶስተኛው ስትራቴጅ ስህተት ሀተታ ውስጥ ከመግባቴ በፊት ወያኔ ስልጣን እንደያዘ ሰሞን የተሰሩ ስህተቶችን ለመጥቀስ እወዳለሁ። እንደሚታወቀው ወያኔ ወይም የትግሬ ነፃ አውጭ ድርጅት ነኝ የሚለው በራሱ ኃይልና ጥንካሬ እየታገለ የመጣ ሳይሆን ከውስጥና ከውጭ የተደራጀለትን ሁኔታና ተገን በመጠቀም ነው ስልጣን ላይ ሊወጣ የቻለው። ከውስጥ በደርግ አገዛዝ የስለላ መዋቅር የሰለጠኑና ለአሜሪካን የሚሰልሉ የወታደሩን ድርጅት እንደበጣጠሱና ወያኔ በአሜሪካን ድጋፍ ስልጣን እንዲይዝ ሁኔታውን እንዳመቻቹ ይታወቃል። እዚህ ላይ ነው በኋላ ተቃዋሚ ነኝ ብሎ የተነሳውና ለኢትዮጵያ አንድነት እታገላለሁ ብሎ እዚህና እዚያ ሲሯሯጥ የነበረው የሰራው ስትራቴጂያዊ ስህተት። ምክንያቱም የወያኔን ስልጣን መያዝ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የተቀረው የካፒታሊስት አገር ስትራቴጂ አድርጎ መቀበልና መረዳት አልቻለም። ሌላው ቢያስረዳውም የሚቀበል አይደለም። ምክንያቱም አሜሪካንና ሌሎችን የካፒታሊስት አገሮችን እንደቅዱስ ነው የሚያያቸው። በፍጹም ወንጀልና አሻጥር የማይሰሩና፣ በዚህ ዓለምም ላይ ተልኮአቸው ለዓለም ህዝብ ሁሉ ሰላምንና ብልጽግናን ለማምጣት የሚታገሉና በእግዚአብሄርም የተላኩ አድርጎ ነው ስለሚቆጥራቸው።
እንደሚታወቀው በአብዮቱ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ ብሄራዊ ስሜትን እየተጎናጸፈና በአንድነት አዲሲቱን ኢትዮጵያ ለመገንባት የሚመኝበትና የሚታገልበት ወቅት ነበር። በኮሙኒዝም ስምና በአብዮት ስም አገሮችን የሚያምታታው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ይህንን እያደገ የመጣውን ብሄራዊ ስሜት ስር ከመስደዱ በፊት በእንጭጩ መቅጨት ነበረበት። ስለሆነም አብዮቱን የሚጠሉትንም ሆነ ለብሄረ-ሰብአችን መብት እንታገላለን የሚሉትን ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች በሙሉ ማስታጠቅ ነበረበት። በሃሳብና በገንዘብ መርዳት ነበረበት። ጊዜው ደግሞ ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚያመች ነበር። በተለይም ትንሽ የተደራጀና አስተማማኝ፣ እንዲሁም የሱን ስትራቴጂያዊ ዓላማ ሊያሟላ የሚችለው በሀገር አቀፍ ደረጃ የተደራጀ ሳይሆን፣ በሃይማኖት ወይም በብሄረ-ሰብ ስም ብቻ የተደራጀ በቀላሉ ሊታዘዝለትና ከውስጥ ህብረተሰብአዊ ውዝግብ በመፍጠር ህዝቡ እንዲበታተን የሚያደርግ መሆን አለበት። ይህ ጉዳይ ቀደም ብሎ በእነ ሄኔሪ ኪሲንገር የተጠነሰሰና የታቀደ ዓላማ ነበር። በተለይም የረዥም ጊዜ ታሪክና የህዝብ ብዛት ያላቸውን እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉትን አገሮች፣ አይ በብሄረ-ሰብ ስም ርስ በርስ እንዲናቆሩ ማድረግ፣ ካሊያም የሃማኖት ውዝግብ እንዲፈጠርና አለመረጋጋት እንዲኖር ማድረግ ነው። በዚህ መልክ እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ አገሮች በትርምስ ሲወጠሩ ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለባህላዊ ለውጥ ፋታ አያገኙም። በተለይም መለሰ ዜናዊ በእንግሊዞች የሰለጠነና በኋላ ደግሞ ከእነ ፓውል ሂንዝ ከሲ አይ ኤው ሰው ጋር የጠበቀ ግኑኝነት ነበረው። ከእነሙዘቬኒና ከእነ ካጋሜ ጋር ተደምሮ መለስ ዜናዊ አዲሱ ወጣትና ተስፋ የሚጣልበት ዲሞክራሲያዊ ኃይል ተብሎ አሜሪካን የሚኮራበት ሰው ነበር። ከዚህ ስንነሳ ወያኔን በተለያዩ ምክንያቶች አጥብቆ የሚጠላው ኃይል ይህንን የአሜሪካኖችን በውስጥ ኃይል ተጠቅሞ ሀገርን የመበታተን ወይም ደግሞ በዘለዓለማዊ ትርምስ ውስጥ እንዲኖር የማድረግ ፖለቲካ በማጥናትና በመገንዘብ እንዴት አድርገን ብንደራጅ ነው ከዚህ ዐይነቱ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ለመውጣት እንችላለን ብሎ ልዩ ዐይነት የትግል ፈለግ ለመከተል የተዘጋጀ አልነበረም። ነገሩም በፍጹም የገባው አይመስልም። ብቻ በአንድ በኩል ወያኔን በጭፍን እየጠላ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ራሱ የነፃ ገበያና የሊበራል ዲሞክራሲ አራማጅ ነኝ ማለት ጀመረ። ይህ ዐይነቱ ጥራት የጎደለው የፓለቲካ የትግል ዘዴ እስከዛሬ ድረስ ተቆራኝቶን እንዳለ ነው።
ያም ሆነ ይህ ወያኔ ስልጣን ሲጨብጥ የራሱ የሆነ ኢትዮጵያን የሚያስተዳድርበት አጀንዳ አልነበረውም። ከመጀመሪያውኑ ቆያለሁም ብሎ ያሰበ አልነበረም። ይሁንና ግን በአሜሪካኖችና በኢንግሊዝ የተዘጋጀለትን የክልልና የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀስ በቀስ ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምር ሁኔታዎች ለሱ እያመቹ እንደሚመጡ ግልጽ ነበር። በተለይም የክልልን ፖሊሲ በማወጅና ተግባራዊ በማድረግ ስልጣኑን ለማራዝም፣ አንደኛውን ከሌላው ብሄረ-ሰብ ጋራ እያጣላሁ እኖራለሁ ብሎ በመገመት፣ በአንድ በኩል በማወቅ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ባለማወቅ የእሳት ረመጥ ውስጥ እንዲወድቅ ተደረገ። ከህዝቡ ጋር መጣላቱ ብቻ ሳይሆን ዛሬ እንደምናየው ሁሉ ነገር ከቁጥጥሩ ስር እየወጣበት መጣ። የህዝቡ ርስ በርሱ መናቆር፣ አለመተማመንና አለመግባባት፣ በተለይም የሃይማኖት ጠያቄ ከፖለቲካ ጥያቄ ጋር መዛመዱና መባዛቱ፣ በዚህም መልክ በጠቅላላው ህዝብ ዘንድ መተረማመስ መፈጠር ለአገዛዙ መዳለደል የሚያመች ነበር የመሰለው። ይሁንና ግን ራሱ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚፈጥራቸው ህብረተሰብአዊ ቅራኔዎች ለአጭር ጊዜ ካልሆነ በስተቀር ከረዢም ጊዜ አንፃር ሊጠቅሙት እንደማይችሉ ሊገነዘብ የሚፈልግ አልነበረም፤ አይደለምም። መለሰ ዜናዊና ሌሎች ወያኔዎች ፖለቲካን የተረዱት እንደ ቁማር ጨዎታና እንደዱርዬዎች ሽወዳ እንጂ አገርን ማስተዳደሪያ ጥበባዊ መሳሪያ አድርገው አይደለም። በዚህም የተነሳ የኢኮኖሚና የማህበረሰብአዊ እንዲሁም ሌሎች ችግሮች እየተደራረቡ ሲሄዱ ይህንን መመለስ የማይችል መንግስት ውጥረት ውስጥ ይገባል፤ ገብቷልም። በራሱ ውስጥም ራሱን የቻለ ቅራኔ በመፍጠር ወደ አለመተማመን ያመራል፤ አምርቷልም። በመጨረሻም ከውስጥና ከውጭ በሚደርስበት ግፊት የመገርሰሱ ጉዳይ የጊዜ እንጂ የማይቀር የታሪክ ግዴታ ነው።
ይህ ዐይነቱ የፖለቲካ አካሄድ ከምን የመነጨ ነው? ሴኔካ የሚባለው ታላቁ የሮማውያን ፈላስፋና ፖለቲከኛ ማንኛውም በፖለቲካና በስነ-ምግባር ላይ የሚሰራ ስህተት በሙሉ የፊዚክስን፣ በተለይም ደግሞ የተፈጥሮን ህግ ባለማወቅ ምክንያት የሚከሰት ነው ይላል። በታሪካችን ውስጥ እስካሁን ድረስ የተሰሩት ስህተቶች በሙሉ የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ ካለማወቅ የተነሳ ነው። በተለይም አንዳንድ በጥራዝ ነጥቅነት የማርክሲዝምን ካባ ያጠለቁ ምሁራን ነን ባዮች የሚሰሩት ወንጀል አንድን ህብረተሰብ በተጨቋኝና በጨቋኝ መሀከል ክፍፍል በማድረግና፣ ጨቋኝ የሚባለው ሲወገድ፣ ኃይሉ ሲዳከምና ሲጠፋ ጭቁን የሚባለው የህብረተሰብ ክፍል ዕውነተኛ ነፃነትን የሚቀዳጅ ይመስላቸዋል። ማንኛውም ህብረተስብአዊ ለውጥና የነፃነት ትግል በእንደዚህ ዐይነቱ ሼማ የሚስራ አይደለም። እያንዳንዱ ህብረተሰብ ለማደግም ሆነ በዚያው ቀጭጮ ለመኖረና ጭቆናን እግዚአብሄር ያመጣው ጉድ ነው ብሎ ለመቀበል ህብረተሰቡ ያለፈበት የተለያየ የዕድገት ደረጃዎች፣ በውስጥ በግለሰቦች ደረጃ ራስን ለማሸነፍ የሚደረግ ትግል፣ የምርት ኃይሎችንና ስልጣንን የሚቆጣጠሩ ኃይሎች ያላቸው ታራካዊና ምሁራዊ ንቃተ-ህሊና፣ አንድ አገር ከውጭ ዓለም ጋር ያላት ግኑኝነት፣ ወዘተ…፣ እነዚህ ሁሉ በአንድ ህዝብና በአመራሩ ላይ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታሉ። የንቃተ-ህሊናውን የዕድገት ደረጃ ይወስናሉ። አንድ አገዛዝና ህብረተሰብ ፈልገው ጨቋኝና ተጨቋኝ ሊሆኑና ህብረተሰብአቸውም በዚያው የቀጨጨ ዕድገት ተረግመው እንዲኖሩ ከመጀመሪያውኑ የሚያቅዱትና የሚፈልጉት ነገር አይደለም። የገዢ ኃይሎችም ከመጀመሪያውኑ የእኩልነትና የስልጣኔ ጠንቅ ሊሆኑ አይችሉም። እነሱም የህብረተሰቡ ውጤቶች ስለሆኑ ማሰብ የሚችሉት ህብረተሰቡ በአዘጋጀላቸው የማሰብ ሁኔታ ብቻ ነው። በዓለም የስልጣኔ ታሪክ ውስጥ ለስልጣኔና ለሳይንስ አጥብቀው የታጋሉትን ታሪክ ስንመለከት በአቦሰጡኝ የተፈጠሩ ወይም ያንን ዕውቀት የተቀዳጁ ሳይሆን አመቺ ሁኔታ ስለአጋጠማቸው ነው። በተጨማሪም የነሱ ታታሪነትና ለአዲስ ነገር ጉጉ መሆን፣ እንዲሁም ተፈጥሮ የሰጣቸውን ነገሮችን በቀላሉ የመረዳት ኃይል እነዚህ ሁሉ ተደምረው የስልጣኔ አፍላቂዎችና የዕድገት ፈለግ ቀዳጆች ሆኑ። ወደ አገራችን ስንመጣ አገራችን በብዙ ነገሮች የታደለች አለነበረችም። በተለይም የፊዩዳሉ ስርዓት ለረዢም ጊዜ ተንሰራፍቶ መቅረቱና፣ ከውጭም እሱን የሚጋፋ ሌላ ዕውቀት በጊዜው መግባት ስላልቻለ የገዢዎችና የህዝቡ የማሰብ ኃይል ውስን ሆኖ ቀረ። ዕድገት የሚባለው ነገር ታፈነ። የህዝቡ ኑሮ አሰልቺ ሆነ።
ይህ አንደኛው ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ የማንኛውምም አገር ዕድገት እንደባዮሎጂካል ክንውን ነው። ከአንድ ቦታ በመነሳት ይስፋፋል፤ያድጋል። አንደኛው ከሌላው የተሻልኩ ነኝ የሚለው የብሄረ-ሰብ የገዢ መደብም ሆነ የህብረተሰብ ኃይል በዚያው ክልል ውስጥ የግዛት መድረኩን ያስፋፋል። በዚህ መልክ በአገራችንም ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አገሮች የተለያዩ ህብረተሰቦች ጠመዝማዛ ጉዞ በማለፍ አነሰም በዛም አገር የሚባል ነገር መስርተዋል። በታሪክ ውስጥ አመጽ አንድን ህብረተሰብ ለማዋቀርም ሆነ ወይም እንደ አገር ለመገንባት ወሳኝ ሚናን ተጫውቷል። እንደዚህ ዐይነቱ ድርጊት በኛ አገር ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በምዕራብ አውሮፓ ውስጥም ተካሂዷል። ከኛ ይልቅ በምዕራብ አውሮፓ ህብረ-ብሄርን ለመመስረት የተደረገው ትግልና ጦርነት እጂግ አሰቃቂ እንደሆነ የታወቀ ነው። የመቶ ዐመታት ጦርነት፣ የሰላሳ ዐመታት ጦርነት፣ የሰባት ዐመት ጦርነት፣ በየአገሮች ውስጥ ደግሞ ለዕድገትና ስልጣኔ ሽንጣቸውን ገትረው በሚታገሉት ምሁራን ላይ ይደርስ የነበረው ግፍና ግድያ፣ ሴቶችን እንደልዩ ፍጡር መመልከትና ማቃጠል፣ እንደዚሁም በየአገሮች ውስጥ የተካሄዱት የርስ በርስ ጦርነቶችን ስንመለከት ስልጣንን ከማጠናከርና አገርን ከማስፋፋት ጋር የተያያዙ ናቸው። ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ በጊዜው የነበረው ተራማጅ ነኝ የሚለው ኃይል ኢትዮጵያን የብሄረ-ሰብ እስር ቤት አድርጎ ሲቆጥርና በዚህም መሰረት ላይ ትግል አራምዳልሁ ብሎ ሲነሳ ከሌሎች አገሮች ታሪክ ያልተማረው ብዙ ነገሮች አሉ። ይህንን የተመለከተውና ሁኔታውን ያነበበው የህብረተሰብን አስቸጋሪ ጉዞ በደንብ ካለማጥናቱ የተነሳ ነው። በትንሽ ዕውቀት ብቻ ለመረዳት በመፈለጉና በመቻኮሉ ነው።
በመሆኑም ወያኔ የኢትዮጵያን የህብረተሰብ አወቃቀር በሳይንሱ መነጽር በደንብ ለማየት ባለመቻሉ የተነሳና፣ ጊዜ የመጣለት ስለመሰለው ለከፋፍለህ ግዛ የሚያመቸውን፣ የክልል ፖሊሲ ግን ደግሞ ዕውነተኛ ነፃነትን የማያጎናጽፍና ከአጭር ጊዜም ሆነ ከረዢም ጊዜ አንፃር ህብረተሰብአዊ ትርምስን የሚያስከትል አጉል ፖሊሲ መከተል ጀመረ። ተግባራዊ አደረገ። በዚህም የተነሳ የየብሄረ-ሰቡ አመለካከት ጠባብ እንዲሆን አደረገ። ከመፈቃቀርና በጋራ ተነሳስቶ ዲሞክራሲያዊ አገር ከመገንባት ይልቅ ኢትዮጵያ የሚለውን ጽንሰ-ሃሳብ ከጠላትነትና ከጨለማነት ጋር በማያያዝ፣ በተለይም ተጨቁነናል የሚሉ የብሄረ-ሰቦች ተወካዮች ወይም ኤሊቶች ነን የሚሉ በኢትዮጵያ፣ በአማራና በቋንቋው ላይ ትልቅ ዘመቻ አካሄዱ። በተለይም እንደዚህ እያሉ ይሰድቡሃል፣ ይንቁሃል እየተባለ የውስጥ ለውስጥ የተስፋፋው አጉል ዘመቻ፣ ከተለያዩ ብሄረ-ሰቦች ለተውጣጣው የብሄረ-ሰብ ኤሊት ነኝ ባይ በዝቅተኛ ስሜትነት በመወጠር በአማርኛ ቋንቋ ላይ፣ በአማራና በጉራጌ ብሄረ-ሰብ ላይ፣ እንዲሁም ደግሞ በኢትዮጵያችን ላይ ዘመቻ ማካሄድ ጀመረ። ይህ ብሄራዊ ስሜት የሌለውና አገርና ህብረተሰብ ምን ማለት እንደሆነ ያልገባው፣ ከዚህም ሆነ ከዚያኛው ብሄረሰብ የተውጣጣው አዲሱ ኤሊትና፣ የተወሰነውም የአማራ ኤሊት ከወያኔ ጋር በማበር በኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ ማካሄድ ጀመሩ። በዝቅተኛ ስሜት በመወጠርና ለፈረንጅ በመስገድ አገርን አፍራሽ ፖሊስ ተግባራዊ በማድረግ እንደ ኮሞዲቲ ገበያ የመሳሰሉትን የኢትዮጵያን ገበሬ ወደ ባርነት የሚለውጠውን ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ። ይህ አልበቃ ብሎአቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠር ንጽህ ህዝብ ገደሉ። ቤተክርስቲያን አቃጠሉ። የተወሰነው ቀዬውን እየለቀቀ እንዲሄድ አደረጉ። በዚህም የተነሳ ህብረተሰባዊ ትርምስ ተፈጠረ። ይህ ዐይነቱ የውዝግብ ፖሊሲ ወያኔ ያወጣው ብቻ ሳይሆን በእንግሊዝ፣ በአሜሪካንና በተቀረው የምዕራቡ ዓለም የተደገፈና፣ በተለይም በእንግሊዝና በአሜሪካን አገሮችን የማዳከም ስትራቴጂ የወጣ ነው። ከዚህ ውጭ ማሰብ ትልቅ የፖለቲካ ስህተት ነው። ያም ሆነ ይህ ወያኔ በድንቁርናው የተነሳ የኢትዮጵያ ህዝብ አካል አይደለሁም ብሎ በመመጻደቅና የፈረንጅን ቡራኬ ያገኘ መስሎት በአገራችን ላይ ትልቅና በቀላሉ ሊፋቅ የማይችል የስትራቴጂ ስህተት ሰራ። ኢትዮጵያን እንደ ህብረ-ብሄርና እንደ አገር እንዳትገነባና እያንዳንዱም ዜጋ ዕውነተኛ ነፃነቱን እንዳይቀዳጅ ትልቅ መሰናክል ፈጠረ።
የክልል ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ወያኔ ልዩ ዐይነት የኢኮኖሚም ፖሊሲ ሲከተል ብቻ ነው። ይህም ፖሊሲ በራሱ የፈለቀ ሳይሆን በውጭ ኃይሎች የተቀነባበረና ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ሀብት እንዳይፈጠር የሚያደርግ የተቅዋም ፖሊሲ(Structural Adjustment Program) ተብሎ የሚጠራ ህብረተሰብን የሚበታትን አደገኛ ፍልስፍና ነው። እንደሚታወቀው ወያኔ ስልጣን ላይ ከመውጣቱ በፊት ያራምድ የነበረው የአልባኒያው ዐይነት የሶሻሊስትን ፕሮግራም ነበረ ተግባራዊ አደርጋለሁ የሚለው። በአሜሪካኖችና በእንግሊዞች ድጋፍ ስልጣን ሊጭብጥ ሲል ከቀረቡለት ቅድመ-ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ የኒዎ-ሊበራልን የኢኮኖሚ አጀንዳ ተግባራዊ ማድረግ ነው። ጠቅላላውን ኢኮኖሚ በነፃ ገበያ ስልት ማዋቀር ነው።
በ1984 ዓ.ም ይህንን የነፃ ኢኮኖሚ አጀንዳ ቀስ በቀስ ተግባራዊ ሲያደርግ በተለይም ስትራቴጂክ የሆኑ ቁልፍ ቁልፍ የኢኮኖሚ መስኮችን ኤፈርት በሚባለው ቁጥጥር ስር ማዋል ቻለ። የመንግስት ሀብቶች ወደ ግል ሲዛወሩ በአብዛኛው ተጠቃሚዎች በአመራር ላይ ያሉ የወያኔ ሰዎችና ኤፈርትን የሚቆጣጣሩ ከፓርቲው ጋር የተቆላለፉ ግለሰቦች ናቸው። በዚህም መልክ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥቂት ሰዎች ሀብታም መሆን ሲጀምሩ፣ የአገሪቱ ገበያ ደግሞ ከውጭ ለሚመጣ ዕቃ ማራገፊያ ሆነ። በዚያው መጠንም ከምርት ጋር ያልተያያዙና ሀብት የማይፈጥሩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች እየተስፋፉ ሄዱ። በእርሻው መስክ ደግሞ የአበባ ተከላና ወደ ውጭ የሚላኩ የእርሻ ውጤቶች በመመረት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ፈሩን እየለቀቀ መጣ። በሌላ ወገን ደግሞ ከረዢም ጊዜ አንጻር ታላቋን ትግሬ እገነባለሁ የሚለው የወያኔ አገዛዝ ከሌሎች ክፍለ-ሀገሮች መሬት በመንጠቅ ግዛቱን በማስፋፈት ኢኮኖሚያዊ መሰረቱን ለማስፋፋት ተያያዘ። በዚህ መልክ እየሰፋ የመጣውን የትግሬ ግዛት በኢንዱስትሪ ለማጥለቅለቅ ሲጣደፍ፣ ሌሎች ክልሎች ደግሞ እንዲቀጭጩ ሁኔታውን ማበላሸት ጀመረ። በወያኔ ዕቅድ መሰረት ሌሎች ክፍለ-ሀገሮች ወይም ክልሎች ጥሬ አምራችና አቅራቢ ብቻ ሆነው መቅረት አለባቸው። በዚህ ዐይነት የድንቁርናና የህብረተሰብን ህግ በሚጥስ ፖሊሲው በትግሬም ሆነ በተቀረው የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የገበያ ወይም የካፒታሊዝም ስርዓት እንዳያድግ አደረገ። የሃሳብ መቀጨጭ እንዲስፋፋ አመቻቸ። እንደሚታወቀው ካፒታሊዝም ሊያድግ የሚችለው በሰፊ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ወይም ደግሞ ብሄራዊ ባህርይ ባለው ብሄርተኛ ኃይል ብቻ ነው። የካፒታሊዝም ዕድገት ከዕውነተኛ ሳይንስና ከቴክኖሎጂ ፈጠራ ጋር የተያያዘ መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ ሰፋ ያለ የህብረተሰብ ኃይልን ያካተተ መሆን አለበት። ከዚህም በላይ ካፒታሊዝም ሊያድግና ሊስፋፋ የሚችለው በአንድ ክልል ብቻ ሲገደብ ሳይሆን ሰፋ ያለ መድረክ ሲነጠፍለት ብቻ ነው። የወያኔው የትግሬን ክልል ብቻ የማልማት ስትራቴጂ በአንድ በብረት በታጠረ ትንሽ ቤት ነክ ነገር እንዳይወጣ እዚያ በዚያው ብቻ እየተሽከረከረ እንደሚኖር እንስሳ ዐይነት አካሄድ ነው። የማያፈናፍንና ለዕድገት የማያመች አጉል የብልጣ ብልጦች አስተሳሰብ ነው።
ያም ሆነ ይህ ወያኔ በአቶ መለስ ግንባር ቀደምትነትና ከውጭ ኃይሎች ጋር በመመሳጠር ፖሊሲ እያወጡ ተግባራዊ ማድረግ ለጊዜው የጠቀመው ቢመስለውም አገሪቱን ትርምስ ውስጥ የሚከታትን ሁኔታ ነው ያዘጋጀው። የአገሪቱ ገበያ ከውጭ በሚመጣ ተመሳሳይ ምርት ክፍት በመሆኑ በተለይም የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ እንዲሁም የጫማ ፋብሪካዎች እንዲዳከሙ ሆነዋል። በአገሪቱ ገበያ ላይ በጠቀሜታ(Second Hand Goods) ላይ የዋሉ ዕቃዎችና ልብሶች በመራገፋቸው የገበያው ኢኮኖሚ ስርዓት እንዲያጣ ተደረገ ። የህዝቡ የመግዛት ኃይልም በጣም የተዳከመ በመሆኑ እነዚህን በሽታን ሊያመጡ የሚችሉ የሰከንድ ሃንድ ዕቃዎችን እየገዛ እንዲጠቀም ተገደደ። በኢኮኖሚው ፖሊሲው ምክንያት ህብረተስብአዊ ሀብት ለመፍጠር ባለመቻሉ ሰፊው ህዝብ ወደ ድህነት እንዲገፈተር አደረገ። ሌሎችን በመጋፋቱ የስራ መስክ እንዳይከፈትና ለስራ ፈላጊው የስራ ዕድል እንዳያገኝ በማድረግ ገበያው እንዲጠብ አደረገ። ገበያውን በአንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲያመራ በማድረግና ውድድር እንዳይኖር መንገዱን በመዝጋቱ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት እንዲፈጠር ለማድረግ በቃ። በደንብ የተጠና አጠቃላይና ሁለ-ገብ ፖሊሲ ስለሌለው በአገሪቱ ውስጥ ያልተስተካከለ ዕድገት እንዲታይ ማድረግ ቻለ። በዚህም ምክንያት በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍለ-ሀገሮች ውስጥ ድህነት ተስፋፋ። ሰፊው ህዝብ በኑሮ ውድነት የተነሳ በድብቅ ረሃብ እንዲኖር ተገደደ። ባጭሩ በአወቅሁኝ ባይነትና በከፍተኛ እልክ በሚያካሂደው የተዘበራረቀ ፖሊሲ ህዝቡ ወዴት እንደሚያመራ ግራ ገብቶታል። የኑሮ ትርጉም ጠፍቶታል። ከዚህ ጋር ተደምሮ ለውጭ ከበርቴዎች በመዋዕለ-ነዋይ ስም የሚሰጠው ሰፋፊ መሬት መፈናቀልንና ህብረተሰብአዊ እሴትን እየገፈፈ ነው። ወያኔ የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ ባለመረዳቱና ለመረዳትም ስለማይፈልግ ለራሱም ሆነ ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ የማያመች አገር ጥሎ የሚሄድ አገዛዝ ሆኗል። ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ፣ ማህበረሰብአዊ፣ ርዕዮተ-ዓለማዊ፣ የሃይማኖትና የአካባቢ ቀውስ በመፍጠር ኢትዮጵያ እንደ ህብረ-ብሄር እንዳትኖር እያደረገ ነው። በዚህም ተግባሩም ያራመደውና የሚያራምደው ፖሊሲ የውጭ ኃይሎችን የሚጥቅምና አገራችንን የሚያዳክም፣ የህዝባችንን ሞራል የሚሰብር መሆኑን በፍጹም የተገነዘበ አይመስልም። በዚህ ዐይነቱ ወንጀለኛ የስትራቴጂ ስህተት አገሪቱን መቀመቅ ውስጥ በመክተቱ በታሪክ እየተወቀሰ ይኖራል። ይህ ድርጊቱ ቆሜለታለሁ ለሚለው የትግሬ ብሄረ-ሰብም በፍጹም የሚበጅ አይደለም።
4.1 አዲስ ህብረተሰብአዊ ክስትተ- በአዲሱ የገበያ ወይም የተቅዋም ማስተካከያ(Structrural Adjeustment Program) ፖሊሲ አማካይነት በአገሪቱ ውስጥ ከወያኔ በሻገርና ሌሎች የአገራችንን ህልውና የሚቀናቀኑ፣ ለዕድገትም የማያመቹ ኃይሎች በአለፉት 20 ዐመታት ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎችን በመያዝ የአገራችንን የህብረተሰብ ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ እያዛነፉ ነው። የሪል ስቴት ግንባታ መጧጧፍ፣ የኮሞዲቲ ገበያ መከፈት፣ አዳዲስ ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መቋቋም፣ የሆቴል ቤቶች እዚህና እዚያ መሰራት፣ እንዲሁም መንግስት ነኝ የሚለው አካል የዓለም አቀፍ ንግድ ድርጅት ለመሆን ያስገባው ማመልከቻ፣ ወዘተ…፣ ግሎባላይዜሽን አገሮችን ከማሰስና ጥቂቱን የህብረተሰብ ክፍል ከመጥቀምና አበዛኛውን ደግሞ ከማድኸየት ጋር የተያያዘ ነው። በዚህ ረገድ አዲስ ራሱን ከህበረተሰቡ አግሎ የሚኖር፣ አዲስ የፍጆታ አጠቃቀም የለመደና የአገር ሀብት የሚያወድም የህብረተሰብ ከፍል አስቸጋሪ ሁኔታ እየፈጠረ ነው። ይህ ከገዢው መደብ ጋር የተቆላለፈ አዲሱ አቀባባይ ከበርቴ ይበልጥ የተሳሰረው ከውጭ የአማካሪ ድርጅቶች(Consulting firms) ጋር በመሆኑ አገሪቱን ለአደጋ አጋልጧታል። ምክንያቱም የኮንሰልቲንግ ኩባንያዎች ዋና ዓላማ በእየአንዳንዱ አገር ውስጥ የተስተካከለ ዕድገት ማምጣት ሳይሆን ለእንደዚህ ላለው ራሱን አግልሎ ለሚኖር የህብረተሰብ ክፍል የማይሆን ምክር በመሰጠት ትርፍ ሊገኝ የሚችልበት መስክ እንዲያድግና በተለያየ መልክ ወደ ውጭ ሊወጣ የሚችልበትን ዘዴ ማዘጋጀት ነው። በዚህም የተነሳ ይህ ዐይነቱ በአገራችን ውስጥ ብቅ ያለው አዲሱ መጤ የህብረተሰብ ክፍል ከውጭ የኮንሰልቲንግ ኩባንያዎችና አማካሪዎች ጋር መተሳሰሩ በአገራችን ውስጥ ዘላቂና ተከታታይነት ያለው፣ እንዲሁም ሰፊውን ህዝብ የሚጠቅም ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዳይመጣ አግዷል። በተለይም ባለፉት አስራ- አምስት ዐመታት ይህና አየር በአየር የሚባለው የማጭበርበሪያ ዘዴ መስፋፋትና የመሬት ቅሚያ የአገሪቱን የኢኮኖሚ በከፈተኛ ደረጃ እንዲናጋ አድርጓል። የኢኮኖሚን ዕድገት ህግ የሚጥስ ተግባር በመስፋፋቱ በሀብታምና በደሃ መሃከል ያለው ልዩነት ከምን ጊዜውም በላይ ሰፍቷል። ከዚህም ባሻገር ይህ አዲስ የህበረተሰብ ክፍል በተለይም ከውጭ መንግስታት ጋርና አጎአ( African Growth & Opportunity Act)(AGO) ከሚባለው አዲሱ አሜሪካኖች የአፍሪካን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያዛንፉበት ስትራቴጂ ጋር መቆላለፉና የፕላንቴሽን ኢኮኖሚ እንዲስፋፋ በሩን በመክፈቱ ወደፊት ለሚከሰት አዲስ ሁኔታ ከአሁኑ መሰናክል ፈጥሯል።
4.2 የባህል መከስከስ ሁኔታ- ከዚህ ስንነሳ ይህ አዲሱ የህብረተሰብ ክፍልና በጠቅላላው በነፃ ገበያ ስም በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ህብረተሰብአዊ መዘበራረቅን ነው ያስከተለው። የህብረተሰቡ እሴት እንዲወድቅ ነው ያደረገው። የወጣት ሴቶች ወደ ሴተኛ አዳሪነት መሰማራት፣ የኤድስ በሽታ መስፋፋት፣ መንግስት ራሱ ኤጀንሲ ከፍቶ ወጣትና ያልተማሩ ሴቶችን ለአረብ አገሮች መሸጥ፣ በየከተማዎች ውስጥ፣ በተለይም በአዲስ አበባ ልክ እንደ ሻይ ቤትና እንደ ሆቴል ቤቶች የጨአት መቃሚያ ቤቶች መክፈትና ይህንን እንደሙያ አድርጎ መውሰድ፣ ሰፋ ያለ የሙያና የስራ መስክ ባለመከፈቱ ወጣቱ ባልባሌ ቦታ እንዲውል መገደዱ፣ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የወሲብ ግኑኝነት መፈጠሩና ወጣቱን እንዲበላሽ መደረጉ፣ በተለይም ደግሞ የተራድዖ ድርጅቶች የሚባሉት እዚህና እዚያ ቢሮ ከፍተው የአገራችንን ወጣት ማበላሸትና ለህዝባችን እሴት ተቀናቃኝ መሆን፣ ይህ ሁሉ የሚያሳየው አገሪቱ የቱን ያህል የባህል ውድቀት ላይ እንደምትገኝ ነው። እንደሚታወቀው ለጥሩና ለተስተካከለ የኢኮኖሚ ዕድገት ያልተረበሸና አገር ወዳድነትን የተላበሰ እሴት እንዲኖር ያስፈልጋል። የአንድ አገር ባህል መኮትኮትና ማደግ የአንድ ህዝብ አለኝታ ብቻ ሳይሆን፣ ጠንካራ ባህል ያለው አገርና ህዝብ ከውጭ በሚመጣ ርካሽ ባህል በቀላሉ አይጠቃም። ከዚህ ስንነሳ ከ 22 ዐመት ጀምሮ በወያኔ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የተካሄደው አገርን የማበላሸት ዘዬ ጠቅላላውን የህብረተሰብ ክፍል፣ በተለይም ደግሞ የእናቶቻችንና የአባቶቻችንን መንፈስ እያናወጠው ነው።
5.0 የንቦት 1997 ዓ.ም ምርጫ- ሌላው የስትራቴጂ ስህተት የምለው የግንቦት ሰባቱን የ1997 ዓ.ም የምርጫ ድል ለመጠቀም ያለመቻል ነው። እንደሚታወቀው የግንቦት ሰባቱ ምርጫ የተካሄደው ወያኔ፣ በተለይም መለስ ዜናዊ በአንድ በኩል ህዝባዊ ሌጂቲሜሲ አገኛለሁ ብሎ በማሰቡ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ለዓለም ኮሙኒቲው ለሚባለው ለመመጻደቅ ያህል ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ችለናል ለማለት የተደረገ ምርጫ ነው። የግንቦቱ ሰባት ምርጫ እንዲካሄድ የተደረገው መለስ ዜናዊና ወያኔ ፈልገውትና ዲሞክራቶች ስለነበሩ፣ ወይም የአገራችንን የተወሰሳሰበ ችግር በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ ስለነበሩ አይደለም። ያም ሆነ ይህ ከምርጫው አንድ ሳምንትና በምርጫው ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ ከማን ጋር እንደቆመ በገሃድ ያሳየበት ነበር። በብዙ ሚሊዮን በመቆጠር በሰላማዊው ሰልፍም ላይ ሆነ በምርጫው ላይ በዲሲፕሊን በመካፈል በአንድ በኩል ብሶቱን፣ በሌላ ወገን ደግሞ በቃህ፣ ከእንግዲህ ወዲያ ሀገር ማመስ የለብህም በማለት ለቅንጅትና ለህብረት ድምጹን የሰጠበትና ወያኔም ሀፍረቱን እንዲከናነብ ያደረገበት ወቅት ነበር። የምርጫው ውጤትና የህዝቡ ስሜት ለወያኔም ሆነ ለቅንጅትና ለህብረት ከመቅጽበት የመጣባቸው ነገር ነበር። ወያኔ ማሸነፍ እችላለሁ ብሎ ተዝናንቶ ይጠባበቅ ነበር፤ ቅንጅት ደግሞ ቢያንስ ብዙ መቀመጫ ሊያገኝ እንደሚችል መገመት የሚቻልበት የምርጫ ወቅት ነበር። ይሁንና ቅንጅት ባልጠበቀው ሁኔታ ወያኔን በብዙ ሚሊዮን ድምጽ አሸነፈው። ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ ከሱ ጋር መሆኑን አረጋገጠለት። የኢትዮጵያ ህዝብ ወያኔን እንደማይፈልገው አረጋገጠ።
እንግዲህ እዚህ ላይ ነበር ግራ መጋባት የተፈጠረው። እንደሚታወቀው የራሱ የቅንጅት አፈጣጣር እንደሚያረጋግጠው ከረዢም ጊዜ በቲዎሪና በመሰረታዊ የአገሪቱ ጥያቄዎች ላይ፣ ማለትም የብሄራዊ ነፃነት ጉዳይና የውጭ ኃይሎች በአገራችን ላይ ያላቸውን ጣልቃ ገብነት፣ የመንግስትን የመጨቆኛ መኪና ጉዳይ፣ አገዛዙ እስከዚያ ጊዜ ድረስ የተከተለውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲና፣ በዚህም አማካይነት በህዝቡ ላይ የደረሰውን ድህነት፣ ከዚህም በመነሳት አገዛዙ አገራችንና ህዝባችንን ሊጠቅም የሚችል ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ግንባታ ለማካሄድ ያለመቻል፣ በግሎባላይዜሽን ስም የመጣውን የባህል እሴት መከስከስና የአገራችን አቅጣጫ ደብዛው መጥፋት፣ ወዘተ…፣ እነዚህን የመሳሰሉትን የአገር ጥያቄዎች በማንሳትና በመከራከር የተመሰረተ ሳይሆን፣ የጊዜው ሁኔታ አስገድዶት በአስቸኳይ የተቋቋመ „የፓርቲዎች“ ትብብር ነበር ማለት ይቻላል። አመሰራረቱና የምርጫው ተሳትፎ የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ የሚያንፀባርቅ ነው። ቅንጅት የፖለቲካው ክፍተትና የአገራችን የተዳከመ የኢኮኖሚና የባህል መከስከስና የምሁር ክፍተት ውጤት እንጂ ከረዢም ጊዜ አንፃር ብሄራዊ ነፃነትን፣ እኩልነትን፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶችን፣ የአገር ዕድገትን፣ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትን በመቃወም፣ ወዘተ… አጀንዳው አድርጎ ሲታገል የነበረ የፓርቲዎች ስብስብ አልነበረም። አብዛኛው በሊበራል ዲሞክራሲ፣ በነጻ ገበያና በውጭ ኃይሎች የሚተማመን እንጂ በኢትዮጵያ ህዝብ የሚተማመንና ለአገራችን ዕውነተኛ ነፃነት የቆመ የሚያስመስለው ብዙም ነገር አልነበረም። በተለይም ደግሞ ከዚህና ከዚያኛው ብሄረ-ሰቦች የተውጣጡ ግለሰቦች አጀንዳቸው እንዴት አድርገን ስልጣን ይዘን የራሳችንን አጀንዳ ተግባራዊ እናደርጋለን ብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ስለነበር አካሄዳቸው የሚያመረቃና፣ ለአንድነትና ለሰፊ የኢኮኖሚ ግንባታ የሚያመች አልነበረም። የአገራችንን የተወሳሰቡ ችግሮች ስትራቴጂያዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት የማያመቹ እንቅስቃሴዎች ነበር፤ ናቸውም። ስለሆነም ከሰኔው ጭፍጨፋ በኋላ አንዳንድ የቅንጅት መሪዎች ህዝቡ ያገኘውን ድል እንዴት አድርገን ልናጎናጽፈው እንችላለን ብሎ መሯሯጥ ሳይሆን በውጭ ኃይሎች በመተማመንና፣ በተለይም እንደነ ቲም ክላርክ ከመሰለው የኢንግሊዛዊውና ሌላ ተግባር ከነበረው ጋር በማበርና በሱ ላይ በመተማመን በህዳር ወር ሊጠራ የታቀደውን ሰላማዊ ሰልፍና የቤት ውስጥ አድማ እንዲከሽፍ ተደረገ። በመለሰ ዜናዊና በውጭ ኃይሎች ሸዋጅነት፣ በተለይም አንዳንድ የቅንጅት መሪዎች በውጭ ኃይሎች ላይ ሙሉ ዕምነት ስለነበራቸው፣ የዚህ ዐይነቱ የተቀነባበረ ሽወዳ ሰለባ በመሆን ሰፊው ህዝባችን ድሉን እንዲነጠቅ ተደረገ።
ከዚህ ዐይነቱ ግልጽ ያልሆነና አወዛጋቤ አካሄድ በአሸናፊነት የወጣው ወያኔና መለሰ ዜናዊ ብቻ ናቸው። ከእንግዲህ ወዲያ ትምህርት መቅሰም አለብን በማለት ሁሉን ነገር እያጠበቡና፣ በተለይም በወጣቱ ላይ በመዝመት የህዝባችን ሞራል እንዲሰበር ሆነ። ብዙ ወጣት አመልጣለሁ ሲል ተቀነጠሰ። የፖለቲካውና የኢኮኖሚው ሁኔታ እየተበላሸ መጣ። ወያኔ ከእንግዲህ ወዲያ ኃይሌን መነጠቅ የለብኝም፤ የሚጋፈጠኝም ኃይል መኖር የለበትም በማለት በኢኮኖሚው ላይም ዘመቻ ማድረግ ጀመረ። ይቀናቀኑኛል የሚላቸውን ታታሪ መለስተኛ ከበርቴዎች በጊዜው ቀረጥ አልከፈላችሁም በማለትና፣ ክፍያ(Share) ሽጡልኝ በማለት ከኢኮኖሚ ውስጥ እንዲወጡ አደረጋቸው። ራሱ ብቸኛው ተዋናይ ወደ መሆን አመራ። በኤፈርት ስር ብዙ የኢኮኖሚ ሴከተሮችን ማጠቃለልና ማስፋፋት ተያያዘው።
በቅንጅት መሪዎች ዘንድ ይህ ሁሉ ስህተት ለምን ተሰራ? ከላይ እንዳልኩት ቅንጅትም ሆነ የተለያዩ ድርጅቶች የረዢም ጊዜ የአደረጃጀት ልምድ የሚጎዳለቸው ብቻ ሳይሆን፣ የአገሪቱንና የዓለምን ሁኔታ ሊመረምሩበት የሚያስችላቸው የጠራ ቲዎሪና የአሰራር ስልት ዘዴ የነበራቸው አልነበሩም። በዚህም ምክንያት የተነደፈው ፕሮግራም ኢትዮጵያን እንደ ህብረተሰብና እንደ ህብረ-ብሄር (Nation-State) እንደትገነባ የሚያስችላት አልነበረም። ይህም ማለት እያንዳንዱ ድርጅት ከፍተኛ የሆነ ምሁራዊ ክፍተት ነበረው። አቋሙ በገበያ ኢኮኖሚና በሊበራል ዲሞክራሲ ዙሪያ የሚሽከረከር እንጂ ሰፋ ያለና ከረዢም ጊዜ አንፃር የተተለመ ብሄራዊ አጀንዳ አልነበረም። ከዚህም በላይ ደግሞ እያንዳንዱ ፓርቲ የዓለምን ኢኮኖሚና ፖለቲካ በየዋህነት መነፅር ነበር የሚመለከተው። ጊዜው የግሎባላይዜሽን ዘመን ነው እየተባለ የሚሰበክበት ጊዜ ስለነበር ሁሉም ሀገር ወደ ገበያ ኢኮኖሚና ወደ ሊበራል ዲሞክራሲ የሚያመራ ነው ተብሎ ነበር ግንዛቤ ውስጥ የተገባው። የነፉኩያማ ወይም የኒዎ ኮንሰርቫቲቦች ዕቅድ ተግባራዊ የሚሆንበትና፣ ዘመኑ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ነው ተብሎ የተደመደመበት ወቅት ነበር። ስለዚህም የቅንጅት መሪዎች አመለካከት ከዚህ ዐይነቱ የአሜሪካን የግሎባል ስትራቴጂ አመለካከት ውጭ አልነበረም ማለት ይቻላል። አጀንዳቸው ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ነፃነት የሚያስከብርና አገራችንን በጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረት ላይ እንድትቆም የሚያደርግ አልነበረም። የቅንጅት መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ወጣቱም፣ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያን ህዝብ አጀንዳና ህልም ተግባራዊ ለማድረግ ሳይሆን የአሜሪካንን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ እዚህና እዚያ አለሁ፣ አለሁ የሚለው ጊዜ ያመጣለት ኃይል የሚጠባበቀውና የሚመኘው ይህንንም ያህል ዕውነተኛና ዲሞክራሲያዊት፣ እንዲሁም ራሷን የቻለች ኢትዮጵያን ማየት ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ዕድል ከአሜሪካን የጂኦ ፖለቲካል ጥቅም ጋር በማገናኘት ነበር። ይህ ተራ ውንጀላ ሳይሆን፣ የሚሰጠው ሀታት፣ ተጨባጩ ሁኔታና የትግሉ ስትራቴጅ የሚያረጋግጠው ጉዳይ ነው። ስለሆነም ትክክለኛ ስትራቴጂ የሌለውና ምክር ለመቀበል የማይፈልገው አዲስ ኃይል የግንቦት ሰባት የምርጫን ውጤት እንዲከሽፍ አደረገ። ህዝባችን ልዩ ዐይነት ሰቆቃ ውስጥ እንዲገባ የበኩሉን አስተዋጽዖ አበረከተ። ይህ ዐይነቱ የቅንጅት መሪዎች የሰሩት ስትራቴጂያዊ ስህተት ባለፉታ ስምንት ዐመታት እየተደጋገመ ይሰራል። በአገር ቤት ውስጥ እንቀሳቀሳለን የሚሉ ተቃዋሚ ድርጅቶችና፣ በውጭ እንቀሳቀሳለሁ የሚለው የተወሰነው ኃይል የአገዛዙን ባህርይና ከውጭ ኃይሎች ጋር በመቆላለፍ በአገሪቱ ላይ የሚያደርሱትን አገር አፍራሽና ህዝብ በታኝ ፖሊሲ ለመረዳት በፍጹም ዝግጁ አይደሉም። እንዲያው ብቻ በነፃነትና በዲሞክራሲ ስም እዚህና እዚያ በመንቀሳቀስና የማይሆን ገለጻ በመስጠት በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ኢትዮጵያዊ ዕውነቱን እንዳይረዳ መንገዱን ሁሉ ዘግተዋል። ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር የኢትዮጵያን ህዝብ የሚውክል መንግስት የለም። በአሜሪካንና በእንግሊዝ የሚደገፍ ማፊያዊ መንግስት ነት ያለው። ዕውነተኛ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚፃረር፣ ለብሄራዊ ነፃነታችን ጠንቅ የሆነ፣ የህዝባችንን በሰላምና ተቻችሎ መኖር የማይፈልግ፣ በአጭሩ የውጭ ኃይሎች ተጠሪ መንግስት ነው ያለው። ዛሬ ግንዛቤ ውስጥ መገባት ያለበት ጉዳይ ይህ ሀቅና፣ በዐይናችን የምናየው የአገራችን የተወሳሰበና የመበታተን ሁኔታ ነው። ከዚህ ስንነሳ ምን መደረግ አለበት በሚለው ላይ እንወያይ።
6.0 ምን መደረግ አለበት ! ዛሬ በአገራችንንም ሆነ በአካባቢው ያለውን፣ ከግብጽ እስከ ቱኔዚያና ሊቢያ እንዲሁም ሶሪያና ሊባኖን፣ በተጨማሪም በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ያለውን አስቸጋሪ የአገዛዝ ሁኔታና የፖለቲካ ቀውስ ስንመለከት፣ እኛ ብቻ ሳንሆን ብዙ ህዝቦች ግራ እንደተጋቡ እንመለከታለን። በተለያዩ አገሮች በአንድ በኩል ኤሊት በሚባለው፣ በሌላ ወገን ደግሞ ሰፊው ህዝብ በሚባለው መሀከል የዓላማና የፍላጎት ስምምነት ስለሌለ ትግሉ እጅግ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። በየአገሮች በኤሊቱ ዘንድ ያለው አለመግባባትና በአንድ የጋራ ግምባርና አጀንዳ ስር ተሰልፎ ለህዝብ አመራር ለመስጠት ያለመቻል አገሮችን እያተራመሰ ነው። በዚህ ዐይነቱ ትርምስ ውስጥ፣ አሜሪካ በተጠሪዎቹ አማካይነት፣ ማለትም በዓለም የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ አማካይነት፣ አሁን ደግሞ አፍሪኮም የሚባለውን እጅግ አደገኛና ወራሪ ጦር በማቋቋም፣ የአውሮፓው አንድነትም እንደዚሁ ተዋናይ በመሆን በኤሊቱ ላይ ግፊት እያደረጉና፣ ይህንን ካልተቀበልክና ተግባራዊ ካላደረግህ በማለት ትልቅ ውዥንብር እየፈጠሩ ነው። በዚህም ምክንያት በየአገሮች ውስጥ ያለው ኤሊት በውዥንበር ዓለም ውስጥ የሚገኝ ሆኗል። አንዳንድ ኤክስፐርቶች እንደሚሉት ከሆነ የግልባል ካፒታሊስት ኢኮኖሚ በፈጠረው አንድ ዐይነት አመለካከት ብዙ አገሮች ውዥንብር ውስጥ ወድቀዋል። በራሳቸው ጥረት መስራት የሚችሉትን እንዳይሰሩ ታግደዋል። በዚህም ምክንያት የፖለቲካው መድረክ ችግር ፈቺ መሆኑ ቀርቶ ሁኔታዎችን እያበላሸና፣ በተለይም ደግሞ ለአክራሪዎች አመቺ ሁኔታን እንደፈጠረ ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት ብዙ አገሮች፣ ኢትዮጵያችንንም ጨምሮ እንደ አገር ነፃ ሆነው የመኖር ዕድላቸው እያከተመ የመጣ ነው የሚሉ አሉ። ኢትዮጵያና ከላይ የተዘረዘሩት ሌሎች አገሮች የፈራረሱ መንግስታት(failed states) ነው የሚያሰኛቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ ያረጋግጣሉ። በተለይም ከስምንት ወር በፊት የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ያወጣቸው አስራሁለት ምሶሶዎች(pillars) የሚባሉ ለአንድ አገር እንደ አገር ለመኖርና ሙሉ በሙሉ ለመንቀሳቀስ የሚያስችላቸው መሳሪያዎች በእነዚህ አገሮች አንዳቸውም የተሟሉ ስላልሆነ አገርነት የሚያሰኛቸው ምንም ነገር የለም በማለት ያለውን ህብረተሰብአዊ ትርምስና የህዝቦች ሞራላ መከስከስ ያሳያሉ።
ወደ አገራችን ስንመጣ፣ በእኔ ዕምነት፣ አብዮቱ ከከሸፈም በኋላና፣ ወያኔ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ በቲዎሪ፣ በሳይንስና በተለይም ደግሞ የአገርን የወደፊት ዕድል በሚመለከት ምንም የተሰራ ስራ የለም ብል ተራ የስም ማጥፋት ሆኖ እንደማይወሰድብኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ከዚህ ስነሳ እያንዳንዱ ድርጅትም ሆነ ስለ ኢትዮጵያ ያገባኛል የሚል ሁሉ አንዳንድ አነስተኛ መግለጫዎች ከመስጠቱ በስተቀር ለአገር ነፃነትና ክብር ከሚደረግ ስትራቴጂያዊ ትግል አንፃር ሲታይ ሁሉንም ሊያሰባስብ የሚችል ሰፋ ያለ ፕሮግራም አዘል ሀተታ ሲያቀርብ አይታይም። በተለይም በድርጅት መልክ ተደራጅተናል የሚሉና በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ገንዘብ ከዚህም ከዚያም የሚሰበስቡና የሚያሰባሰቡ የሰፊውን ህዝብ አስተሳሰብ ሊሰበስብና ስትራቴጂያዊ አመለካከት እንዲኖረው የሚሰጡት ትምህርት አዘል ትንተና እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ቢኖር እንኳ አመርቂ አይደለም። አብዛኛው ገለጻ ወያኔን ከመውንጀል የሚያልፍ አይደለም። በየቦታው የሚደረጉ የአዳራሽ ስብሰባዎች በጥቃቅን ነገር ላይ ከመወያየትና እኛም ተደራጅተናል ከማለት በስተቀርና ድምጽን ከማሰማት ባሻገር፣ የአገራችን ሁኔታ በአንዳች ነገር ቢለወጥ እንኳ እንዴት አድርገው መቆጣጠር እንደሚችሉና፣ አፍጠው አግጠው ያሉት ችግሮች ደረጃ በደረጃ እንዴት መቀረፍ እንዳለባቸው መንገዱን ሲያሳዩ አይታይም።
ይህ ብቻ አይደለም የፓርቲዎችና የድርጅቶች ጋጋታ ሁላችንንም ግራ እያጋበ የመጣ ነው። አንደኛው ከሌላው የሚለይበት ምክንያትና ነጥብ ወይም አጀንዳ በፍጹም አይታወቅም። ሁሉም ለመድበለ-ፓርቲ፣ ለሊበራል ዲሞክራሲና ለነፃ ገበያ የሚታገል መሆኑን ነው የሚያበስርልን። በሌላ ወገን ደግሞ እነዚህ ነጥቦች በሁሉም አቅጣጫ በደቀቀ አገር፣ ኢኮኖሚው እጁና እግሩ በማይታወቅበት አገር፣ አገሪቱ አሁንም በግሎባላይዜሽን በምትደቅበት ወቅት፣ አገዛዙ በውጭ ኃይል ተደግፎ ህዝባችንን መላወሻና መተንፈሻ ባሳጣበት ወቅት፣ ባህላዊ ውድቀት አፍጦ አግጦ በሚታይበት አገር፣ ባጭሩ ብዙ ነገሮች በተመሰቃቀሉበት አገር እንዴት ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ሲያስረዱን አይታይም፤ አይሰማም። ይህ አንደኛው ሲሆን፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት ህዝባችን በከፍተኛ ደረጃ መንፈሱ በተዳከመበትና ነፃነቱን በተነጠቀበት ወቅት የብዙ ድርጅቶች ጋጋታና ሽኩቻ ወዴት እንደሚያደርሰን ግልጽ አይደለም። በእኔ ዕምነት የብዙ ድርጅቶች እዚህና እዚያ መቋቋም ዕውነተኛ ነፃነትን ከመሻትና ከራስ ጋር ከማዋሃድ፣ እንዲሁም ለአገር ብሄራዊ ነፃነት ከመቆርቆርና የተከበረች አገር ከመገንባት ጋር የተያያዘ አይደለም። በዚህም ምክንያት የፓርቲዎች ጋጋታና በየቦታው ሰዎችን መመልመል፣ አንደኛው ሌላውን ከመጥላት ወይም ከመናቅ፣ አብሮ ለመስራት ካለመፈለግ ጋር የተያያዘ ነው ብል የምሳሳት አይመስለኝም። ዕውነተኛ ነፃነትን ከመሻት የተነሳ በብሄረተኝነት ስሜት ከልብ የተቋቋሙ ድርጅቶች አይደሉም የምናየው።
ከዚህ ስነሳ ተቃዋሚ ነኝ ወይም ፓርቲና እንቅስቃሴ አለኝ በሚለው ኢትዮጵያዊ ኃይል ዘንድ ከፍተኛ የሆነ የቲዎሪ ክፍተት፣ ግልጽ ያልሆነ ያሰራር ዘዴና የዓላማ ግልጽነት አለመኖር በደንብ ይታያል። አብዛኛዎቹ ድርጅቶች ወይም የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ስልጣንን ተረክቦ አገርን ለማስተዳደር ከፍተኛ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን የተወሳሰበ ዕውቀት እንደሚያስፈልግ የተረዱ አይመስልም። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያለ በብዙ ችግሮች የተተበተበ አገርና፣ በክንውን ላይ የነበረ የህብረ-ብሄር ግንባታ ተቀልብሶ ክልላዊ ስሜት እንዲዳብር በተደረገበት አገር፣ እንዲሁም የብሄረተኝነት ስሜት እንዲሟጠጥ በተደረገበት ሁኔታ ውስጥ፣ በምን ዐይነት ሳይንስና ቲዎሪ ብንመራ ነው አገራችንን በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት የምንችለው? የሚለው ከባድ ጥያቄ ለውይይት ቀርቦ ክርክር ሲደረግበት አይታይም። አብዛኛው ድርጅት የተያያዘው አሁንም እንዴት አድርጌ ፕሪንሲፕልና ዕምነት የሌላቸውን ሰዎች አሰባስቤ ነው ስልጣን መያዝ እችላለሁ የሚለው ነው የሚያሳስበው። የብዙ ፓርቲዎች መፈጠርና ወዲህና ወዲያ መሯሯጥ በብዙዎቻችን ዘንድ፣ በተለይም ከፊዩዳል የጥርጣሬ አመለካከት ባልተላቀቅን ሰዎች ዘንድ አለመተማመን እንዲፈጠር አድርጓል። ነገሮችን በጥቁርና በነጭ መሀከል እየከፋፈሉ፣ ወይም ይህንን ድርጅት ደግፍ ካለበለዚያም ወደጠላት ወገን ነው የምትሰለፈው ዐይነት አባባል ተስፋፍቷል። ካለኝ የፀና ዕምነት ስነሳና ከፖለቲካ ተመልካችና ተንታኝ አመለካከቴ ይህ ዐይነት አካሄድ ለማንም የሚበጅ አይደለም። ኃይል የሚጨርስና የተቆጠበ ሪሶርስን የሚያባክን ነው። የኛ መሻኮት፣ በጥርጣሬ ዐይን መተያየትና በአንድ የጠራ አጀንዳ አካባቢ ለመሰለፍ ያለመቻል የመጨረሻ መጨረሻ የኢትዮጵያን ህዝብ ሀሞት ከማፍሰስ ባሻገር፣ የኢትዮጵያን ዕድገት የሚጠሉትን ያስደስታል፣ የዛሬውን አመፀኛ አገዛዝ ለጊዜውም ቢሆን ይጠቅማል፤ ዕድሜውንም ያረዝማል።
ከአንዳንድ አገሮች ታሪክ የምንማረው ቁም ነገር አለ። በ17ኛውና በ18ኛው ክፍለ-ዘመን እንግሊዝና ፈረንሳይ በዕድገት ቀድመው በሄዱበት ዘመን ጀርመን እንደ ህብረ-ብሄር የተቋቋመች አለነበረችም። በክፍፍሉና ባለመግባባት የተነሳ ጀርመን በተለያዩ ኃይሎች፣ በስዊድን፣ በዴንማርክ፣ በፈረንሳይ፣ በአውስትሪያና በሌሎችም አገሮች ጦርነት እየተከፈተባት ትጠቃ ነበር። ይህንን የተመለከቱ ምሁራን ነገሩ በዚህ መቀጠል እንደሌለበት ይመለከታሉ። ለዚህ ሁሉ ችግር ስር የሰደደው ኋላ ቀር የሆነው ፊዩዳላዊ አመለካከት እንደሆነ ይገነዘባሉ። የመሬት ከበርቴውና አሪስቶክራሲው ለውጥን ባለመፈለግ ለጀርመን ወደ ኋላ መቅረት ተጠያቄዎች እንደሆኑ ይረዳሉ። በዚህ ላይ ደግሞ ህዝቡ የተማረ ስላልነበር ዝም ብሎ የሚገዛ ነበር። ይህ ሁኔታና የትናንሽ መንግስታት አስተሳሰብ ለጀርመን መጠቃት ዋናው ምክንያት እንደሆነ ይደርሱበታል። ስለሆነም ይህ ሁኔታ የግዴታ መለወጥ እንዳለበት፣ ለዚህ ደግሞ ለስልጣኔ የሚጠቅምና ጀርመንን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከኋላ-ቀርነት ሊያወጣት የሚችል ዘዴ ይፈልጋሉ። የተለያዩ አገሮችን ስልጣኔም እየተዘዋወሩ በማየትና በማጥናት ለጀርመን የሚያዋጣውን መንገድ ይቀይሳሉ። የስልጣኔው መንገድ በዕውቀት መታጠቅ እንደሆነና፣ ጀርመንን የአሳቢዎችና የገጣሚዎች እንዲሁም የፈጣሪዎች አገር ማድረግ ብቻ ፍቱኑ መንገድ እንደሆነ ይደርሱበታል። በዚህ ላይ ርብርቦሽ ያደርጋሉ። ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ዝግጅት ያደርጋሉ። የገዢው መደብና የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል እንዲነቁና ብሄራዊ ስሜት እንዲኖራቸው ቲያትር፣ ግጥም፣ ሊትሬቸርና ልዩ ልዩ ውብ ስራዎችን ያስፋፋሉ። በተስፋፋና በዘመናዊ ዕድገት አማካይነት ብቻ ጀርመንን ካለችበት ሁኔታ አውጥቶ ታላቅ አገር ማድረግ እንደሚቻል ያመለክታሉ። ለዚህ ደግሞ የግዴታ በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ በሰፊው የሚዘረጋ የኢንዱስትሪ አብዮት መካሄድ እንዳለበት ያስረዳሉ። ይህ ዐይነቱ የኢንዱስትሪ ተከላ መሰበጣጠርና በሁሉም አካባቢ መዘርጋት እንዳለበት ቅስቀሳ ያደርጋሉ። እንግሊዝና ፈረንሳይ ሄደው የእነሱን ዕድገት የተመለከቱት አንዳንድ ምሁራን በተለይም እንግሊዝ የተጓዘችበትን መንገድ መከተል እንደሌለባቸው ግልጽ ይሆንላቸዋል። ምክንያቱም በኢንዱስትሪ አብዮት የተነሳ ከገጠሩ ከፍተኛ የህዝብ መፈናቀልና ወደ ከተማዎች፣ በተለይም ወደ ለንደን የተሰደደው እጅግ አስቀያሚ በሆነ መልክ መኖሩን ሲመለከቱ ይህ ዐይነቱን ንጹህ በነፃ ንግድና በሊበራሊዝም ለይ የተመረኮዘ የዕድገት መንገድ ጀርመን መከተል እንደሌለባት በግልጽ ያመለክታሉ። ስለዚህም የተሰበጣጠረ (decentralization)፣ ጥበባዊ የሆነና ሰብአዊነትን የተላበሰ የኢንዱስትሪ አብዮት ማካሄድ እንደሚያስፈልግ በግልጽ ያብራራሉ። ለዚህ ቁልፉ ደግሞ በየበታው የኢንጂነሪንግ ትምህርት ቤቶች መክፈትና፣ ይህም ከሰው ፍላጎትና ከአገር ግንባታ ጋር መያያዝ እንዳለበት ያሳያሉ። የባህል ለውጥ እንዲመጣ ደግሞ የግዴታ ውብ ውብ ከተማዎችና መንደሮች መገንባትና፣ እነዚህም በባቡር ሃዲድ መያያዝ እንዳለባቸው ግልጽ ይሆንላቸዋል። ምክንያቱም ቀላል ነው። ውብ ውብ ከተማዎች ሲሰሩ፣ ቲያትር ቤቶችና መጻህፍት ቤቶች ሲቋቋሙ፣ በተጨማሪም ለሰፊው ህዝብ ዕውቀት እንዲዳረስና የማታ የህዝብ ትምህርት ቤቶች ሲቋቋሙ ህዝቡ ማሰብ ይጀምራል፤ የመፍጠር ኃይሉም ያድጋል። ርስ በርስ መናቆሩን ትቶ እንደ አንድ ህዝብ ይነሳል። በዕውቀት አማካይነት ራሱን በማግኘት ከሌላውም ጋር ተስማምቶ መኖር ይችላል። ባጭሩ የጀርመኑ መንገድ ዕውነተኛው የህዳሴ (Renaissance) መንገድ ነው። ሁለንታዊ ነው። ስር ነቀልና በአንድ አካባቢ ብቻ ያተኮረ የዕድገት ፈለግ አልነበረም። ይህንን ዐይነቱንም ሆነ ጃፓን የተከተለችውን የዕድገት ፈለግ ለመከተል የሚቀጥሉት ዝርዝር ነጥቦች እንደመመሪያ መወሰድ አለባቸው።
6.1 የብሄረተኝነት ወይም የብሄራዊ ስሜት ጉዳይ- ለጀርመንም ሆነ ለጃፓን እንዲሁም ለተቀሩት የኢንዱስትሪ አገሮች በአፍላው ወቅት የግዴታ የብሄራዊ ስሜት ማደግ ለዕድገት አስፈላጊውና መሰረተ-ሃሳብ እንደሆነ የተደረሰበት ጉዳይ ነው። በተለይም ወደ ኋላ የቀሩት ጀርመንና ጃፓን ሲጀምሩ፣ ካሉበት ሁኔታ ለመነሳትና ራሳችውን ለማስከበር የግዴታ በብሄራዊ ስሜት ማዳበር አለብን ብለው በማመን ነው የአገራቸውን ግንባታ የጀመሩት። ብሄራዊ ስሜት የሌለው እንደሚናቅና፣ ለስራም የማይዘጋጅና ዲሲፕሊንም ስለማይኖረው ብሄራዊ ስሜትን ማሳደግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑ የተደረሰበትና ወደ ተግባርም ሲመነዘር ጥሩ ውጤት ያመጣ ነው። የእያንዳንዱ አገር ምሁርና ህዝብ በመጀመሪያ ደረጃ በራሱ በመተማመን መታገልና ቆንጆ አገር መገንባት አለበት። የአንድ አገር ኤሊት የሌላ አገር ጠበቃ መሆን የለበትም፤ ወይም ደግሞ ነፃ አውጣኝ እያለ መለማመጥ የለበትም። በተለይም የሬናሳንስ መሰረታዊ ሃሳብ ይህንን ራስን ዝቅ አድርጎ መመልከትን ይቃወማል። በራስ ላይ የሚተማመንና ያወቀ ግለሰብኝነት የሬናሳንስ ቁልፍ ሃሳቦች ናቸው። ኤሊቱና ህዝብ እጅ ለእጅ ተያይዘው የሚታገሉበት መድረክ ሲፈጠርና መተማመን ሲጎለምስ አንድን ነፃና ዲሞክራሲያዊ አገር ለመገንባት መንገዱ ሁሉ ይቀላል።
ከዚህ ስንነሳ በተለይም ዛሬ በአገርቤት ውስጥም ሆነ በውጭ ዓለም በሚኖረው ኢትዮጵያዊ ኤሊት ዘንድ ያለው የብሄረተኝነት አመለካከት በሳይንስና በጥበብ ላይ የተመረኮዘ አይደለም። በራስ ዕምነትና በጠቅላላው ኢትዮጵያዊ የመንፈስ ኃይልና ተባብሮ በመነሳት አንድ የጠነከረ አገር መገንባት ያስፈልጋል በሚለው የፀና አስተሳሰብ ላይ የተገነባ የትግል አካሄድ አይደለም ያለው። አብዛኛው ኢትዮጵያን ነፃ አወጣለሁ ብሎ እዚህና እዚያ የሚንቀሳቀሰው ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል በራሱና በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚተመማን አይደለም። አሁንም እንደትላንትናው በውጭው ኃይሎች የሚተማመንና የዓለምን የፖለቲካና የኢኮኖሚ አወቃቀር በሚገባ የተገነዘበ አይመስልም። አንዳንዱ ባለው ተደማጭነትና ያለውን ደካማና ዕውቀተ-አልባ ሁኔታ በመገንዘብ የወደፊቱን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ የኢትዮጵያ ህዝብ በሚመኘውና ሰላምንና ብልጽግናን በሚያመጣ መልክ ማዘጋጀት ሳይሆን፣ ለውጭ ኃይሎች የሚያመችና አገራችንም የውጭ ኃይሎች ተቀጥያ በመሆን ዘለዓለማዊ ውዝግብ የሚፈጠርባት የሚያደርግ አደገኛ አካሄድ ነው። ይህም ማለት ብሄራዊ ባህርይ የጎደለውና በራስና በሰፊው ህዝብ ላይ ዕምነት ያልተጣለበትና የማይጣልበት ፖለቲካ የመጨረሻ መጨረሻ የኢትዮያን ህዝብ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በፍጹም ሊያደርገው አይችልም። ከድህነትም የሚያላቅቀው ሊሆን አይችልም። ስለሆነም በብሄራዊ ነፃነት ላይ ትክክለኛ አመለካከት እስከሌለ ድረስ ለነፃና ለብሄራዊ ኢኮኖሚ ግንባታ የሚደረገው ትግል ከፍተኛ ፈተና ውስጥ ይወድቃል። ዕውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባትና ህዝባችንም ተቻችሎ እንዲኖር ለማድረግ በፍጹም አይቻልም ማለት ነው።
6.2 የስምምነት(Harmony) ጉዳይ- ለአንድ አገር ፈጣን ዕድገት በተለይም ኤሊት ነኝ በሚለው ዘንድ ብሄራዊ ስምምነትና የብሄራዊ አጀንዳ መኖር አለባቸው። እያንዳንዱ ኤሊት ባይ ነኝ የራሱን ስሜትና ፍላጎት የማያስቀድም መሆን አለበት። ስምምነትን ለመፍጠርና በጋራ ለመስራት የሚችል መሆን አለበት። በዚህና በዚያ እያለ ቡድናዊ ስሜት በመፍጠር ህዝብን የሚበጠብጥ መሆን የለበትም። የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ የሚከተል መሆን የለበትም። ለእንደዚህ ዐይነቱ ስምምነትን የሚያደፈርስ አካሄድ ዋናው ምክንያት በበቂው ዕውቀት አለመቅሰም ወይም አለመኖር ነው። ለምሳሌ በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ- ዘመን የተነሱትን የጀርመን ምሁራንና የጃፓኑን የሜጂ ዲናስቲ አካሄድ ላጠና በመሀከላቸው በሁሉም ዘንድ ተመጣጣኝ ዕውቀት ስለነበረና የሚፈልጉትን ያውቁ ስለነበር ምንም የሚያሻክራቸው ነገር አልነበረም። አንደኛው ሌላውን በማክበርና በመከባበር በስምምነትና ለአንድ ዓላማ ይሰሩ ነበር። ይኸውም የተከበረና ጠንካራ አገር መገንባት። ስለዚህም በተለይም አሁን በአለንበት በተወሳሰበና ዕውነቱን ከውሸት መለየት በማይቻልበት ዓለም ውስጥ የነገሮችን ሂደት በቅጡ ለመረዳት የሚያስችል ሳይንሳዊ ዕውቀት መሻት እጅግ አስፈላጊ ነው። ኒዎ-ሊበራሊዝምና ኒዎ-ክላሲካል አመለካከቶች፣ ወይም የሊበራል ዲሞክራሲ አመለካከት የተወሳሰበውን የዓለምንና የአገራችንን ሁኔታ በበቂው እንድንገነዘብ የሚያስችሉን የቲዎሪ መሳሪያዎች እንዳይደሉ መረዳት እጅግ ያስፈልጋል።
ከዚህ ስንነሳ በእኛ በኢትዮጵያኖች ዘንድ ያለው የተለያየ አመለካከትና የዕውቀት መሰረት ለወደፊቱ ለምንገነባት አዲሲቱ ኢትዮጵያ ትልቅ እንቅፋት እንደሚሆን ከአሁኑ መተንበይ ይቻላል። በተለይም የየካቲቱ አብዮት ከከሸፈ በኋላና የነፃ ገበያና የሊበራል ዲሞክራሲ አመለካከት ቦታውን ከተኩት ወዲህ ተቃዋሚ ነኝ በሚለውና በምሁሩ ዘንድ የአገራችንን የወደፊቱን ዕድል በሚመለከት ረገድ ምንም ዐይነት የሚያመረቃ ክርክር ሲካሄድ አይታይም። በሁሉም ዘንድ አንድ ዐይነት ድምፅን ያለማሰማት ስምምነት ያለ ይመስላል። ይኸውም የአገራችን የተወሳሰበ ችግር መፍትሄው በሊበራል ዲሞክራሲና በነፃ ገበያ ተራ የፎርሙላ ሊፈቱ ይችላሉ የሚለው ተራ ግንዛቤና ዕምነት ነው። ይህ ዐይነቱ ቀላል መፍትሄ በራሱ ለማያቋርጥ ህብረተሰብአዊ ቀውስ ዋና ምክንያት በመሆን በአንድ በኩል ስልጣን በጨበጠው ኤሊት ዘንድ መወዛገብን ሲያስከትል፣ በሌላ ወገን ደግሞ በህዝቡና በፖለቲካ ኤሊቱ ዘንድ ከፍተኛ ቅራኔ እንደሚፈጠር ከአሁኑ መተንበይ ይቻላል። ምክንያቱም ለዕውነተኛ ነፃነትና ዲሞክራሲ የታገለው ህዝብ ፍላጎቱና ምኞቱ በነፃ ገበያና በሊበራል ዲሞክራሲ ተጨናግፎበት ሲቀር የግዴታ በፖለቲካ ኤሊቱ ላይ ጫና ስለሚያደርግበት ነው። ስለሆነም ህዝባችንና ኤሊቱ ሌላ ህብረተሰብአዊ ትርምስ ውስጥ እንዳይገቡ ከተፈለገ የነቁ ኃይሎች ከዚህ ዐይነቱ የአጭር ጉዞ አመለካከት በመላቀቅ ለዕውነተኛ ዕድገትና ህዝቡን ለሚያሳትፍ ዲሞክራሲያዊ መብቶች በመታገል የትግሉን ፈር መልክ ማሲያዝ አለባቸው።
6.3 የፓለቲካ ኢንጂነሪንግ ጉዳይ- እንደሚታወቀው በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር የተለያየ አመለካከት ያለውና፣ የብሄረ-ሰብ አመለካከትን የሙጥኝ ብሎ ወደ ፊት በሚጓዝበት አገር እንዴት አድርጎ ጥበባዊና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ መንደፍና መከተል አለብኝ የሚለው ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። በተለይም እንደኛ በአለው አገር ውስጥ በፍልስፍና ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ በማይታወቅበትና፣ የፖለቲካ ጥያቄ ከስልጣን መያዝ ጋር በሚጣመርበት ሁኔታ ውስጥ ተግባራዊ መሆን ያለበት ፖለቲካ አስቸጋሪ ነው። በዚህ መሰረታዊ ጥያቄ ላይ በግልጽ መነጋገር የሚያስፈልግ ይመስለኛል። የጠራ በሳይንስና በምሁራዊ አመለካከት ላይ የተገነባ የፖለቲካ ቲዎሪ እስከሌለ ድረስ አንድን አገርና ህዝብን ማደራጀት እጅግ አስቸጋሪ ነው። እንደሚታወቀው ፖለቲካ በመሸንገልና በማታለል ላይ የሚሆን ነገር ሳይሆን ብስለትንና አርቆ አስተዋይነትን የሚጠይቅ ነው። በሎጂክና በዲያሌክቲክ መሳሪያ እየተነተነ የሚቀርብ መሆን አለበት። ማንኛውም ታጋይ ነኝ ባይ ፖለቲካ ቁልፍና ወሳኝ መሆኑን በመረዳት በመጀመሪያ ደረጃ ከፍልስፍና ጋር ማገናኘት አለበት። ፖለቲካ ይህንንም ያንንም እያግበሰበሱ ለማበጥ ሳይሆን ዕውነተኛ ነፃነት የሚገኝበት መንገድ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ በእያንዳንዱ ነጥብ ላይ በግልጽ መነጋገር ያስፈልጋል። ፖለቲካ የአገር መገንቢያ ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን በመረዳት፣ የፖለቲካ ሰላም ሲሰፍን ብቻ የዕድገቱም መንገድ ቀና እንደሚሆን መገንዘብ ያስፈልጋል። ውስጣዊ ሰላም በሌለበትና የተስተካከለ ዕድገት በማይታይበት አገር ሁኔታው ለበጥባጮች ያመቻሉ።
ከዚህ ስንነሳ እያንዳንዱ በአገር ፖለቲካ ውስጥ እሳተፈላሁ የሚል የዓለም አቀፍን ፖለቲካ የተረዳ መሆን አለበት። በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ውስጥ በሁለት አገሮች መሀከል ወንድማማችነት የለም። እያንዳንዱ አገር ለራሱ ጥቅም ብሎ ነው የሚታገለው። በተለይም በአሁኑ ወቅት ደካማ አገሮችን በተለያዩ የንግድና የሚሊተሪ ስምምነቶች እያሰሩ ወደ ኋላ እንዲቀሩ በሚደረግበትና ውዥንብር በሚነዛበት ዓለም፣ የዓለምን ሁኔታና፣ ፖለቲካንና የተዋናዮችን ምንነት መረዳት ያስፈልጋል። ሳይኮሎጂካቸውን ማንበብ ያስፈልጋል። የብዙ አገር መሪዎች በተለይም የየአገራቸውን ጥቅም ሳይሆን የትላልቅ ኢንዱስትሪዎችንና የፊናንስ ተቋሞችን ጥቅም አስጠባቂ በመሆናቸው በሁለት አገሮች መሀከል፣ ወይም ደግሞ በጋራ ገበያ አገሮችና በደካማ አገሮች መሀከል የሚደረገው ውይይትና ስምምነት ደካማ አገሮችን የሚጎዳ ሆኗል። ትግሉ ደካማ አገሮችን ዘለዓለማዊ ሎሌ ንዲሆኑና ዝም ብለው ካለምንም ክርክር እንዲቀበሉ የሚያደርግ አካሄድ ነው። በተወሳሰቡ ስምምነቶች በማሰር ዕውነተኛ ነፃነትን ማሳጣት ነው። በዚህም አማካይነት አንድ ወጥ የሆነ የዓለም መንግስት በመፍጠር የደካማ አገሮችን ብሄራዊ ነፃነት ለዘለዓለም መንጠቅና ዕድላቸውንም ራሳቸው እንዳይወስኑ ማድረግ ነው።
6.4 ህብረ-ብሄርንና ብሄራዊ ኢኮኖሚን የመገንባት ጉዳይ- እያንዳንዱ አገር እንደ ህብረ-ብሄር መታየት አለበት። ይህ ማለት ግን እያንዳንዱ ብሄረ-ሰብ ተጨፍልቆ ይታይ ማለት አይደለም። በሌላው ወገን ግን የእያንዳንዱ ብሄረሰብ አካል ገለሰብ መሆኑንና በመጀመሪያ ደረጃ ግለሰባዊ ነፃነትን መቀዳጀት እንዳለበት መገንዘብ አለበት። እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱ የሆነ ውስጣዊ ነጻነት ሲሰማው ብቻ ነው ራሱን ማወቅ የሚችለውና ከሌላው ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ አገር መገንባት የሚችለው። በአንፃሩ በብሄረ-ሰብ ስሜት የሚለከፍ በጠባብ ስሜት በመወጠር ዕውነተኛ ነፃነትን መቀዳጀት አይችልም። በጠባብ ዓለም ውስጥ እንደሚኖርና ዕውነተኛ የስልጣኔ ብርሃንን እንደማያይ ሰው ነው። ስለዚህም እያንዳንዱ ግለሰብ ሰፋ ባለ አገር ውስጥ ነው ማንነቱን ሊገልጽና የስልጣኔ ባለቤት ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ አለበት።
ከዚህ ስንነሳ የግዴታ ማንኛውም ድርጅት ለብሄራዊ ኢኮኖሚ መታገል አለበት። ይህም ማለት ደግሞ በዓለም አቀፍ የሚደገፈውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ መቃወምም መሆኑን መገንዘብ ያሻል። ማንኛውም አገር በዓለም አቀፍ ኢንስቲቱሽኖች በመደገፍ ዕውነተኛ ብሄራዊና ጠንካራ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ሊገነባ አይችልም። ስለዚህም እያንዳንዱ ለኢትዮጵያ እታገላለሁ የሚል ድርጅት በብሄራዊ ኢኮኖሚ ላይ ግልጽ አመለካከትና ዓላማ እንዲኖረው ያስፈልጋል። ዕውነተኛ በማኑፋክቱር ላየ የተመሰረተና ሰፊ የአገር ውስጥ ገበያ ብቻ ነው ምርታማነትን ሊያሳድግና ግለሰባዊ ነፃነትን ሊያቀዳጅ የሚችለው። በሌላ ወገን ግን ደግሞ ግለሰባዊ ጥቅምና ህብረተሰባዊ ፍላጎቶች መደጋገፍ አለባቸው። የተወሰኑ ሰዎች መበልጸግ ብቻ የአንድን አገር ዕድገት ሊያፋጥንና ዕውነተኛ ነፃነት ሊያመጣ አይችልም። ስለሆነም ለዕውነተኛ ብሄራዊ ኢኮኖሚ ግንባታ የግዴታ ሁለ-ገብ አመለካከትና እንቅስቃሴ ያስፈልጋል።ተከታታይነት እንዲኖረው ያስፈልጋል። ለዕውነተኛና ብሂራዊ ኢኮኖሚ ግንባታ ቁልፉ ዕውቀት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂዎች መሆናቸውን መረዳት ያስፈልጋል። ፈጠራና(Innovation) አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እየተከሉ ምርታማነትን ማሳደግ በማይቻልበት አገር ስለ ኢኮኖሚ ዕድገትና ስለብሄራዊ ኢኮኖሚ ማውራት በፍጹም አይቻልም።
6.5 የምንነሳበት ወይም የመለኪያችን (Benchmark) መሰረት- የምርጫ 1997 ዓ.ም ከመጀመሩ ቀደሞ ብሎ አዲስ አበባና ውጭ አገር የሚናፈስ አንድ ነገር ነበር። ይኸውም ኢትዮጵያን ከኬንያ ጋር ማወዳደርና፣ ኬንያ የደረሰችበት የዕድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ ኢትዮጵያ በዚያን ጊዜ በነበራት የኢኮኖሚ ሁኔታ 40 ዐመት እንደሚያስፈልጋት ነበር የሚወራው። አሁን ደግሞ የሚናፈሰው ጋናን ለመሆን ነው። የጋና ዲሞክራሲ፣ የጋና የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ወዘተ…፣ እየተባለ ነው የሚናፈሰው። ይህንን ዐይነቱን መለኪያ የሚያነሱ ሰዎች ለምን ሌላ አገርን ወስደው ከዚያ በመነሳት፣ ኢትዮጵያም ከተወሰኑ ዐመታት በኋላ እዚያ መድረስ አለባት፣ እዚያ ለመድረስ ደግሞ ከመጀመሪያውኑ መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች እነዚህ እነዚህ ነገሮች ናቸው በማለት ለማስረዳት እንደማይሞክሩ ነው። የጋናንም ሆነ የኬንያን ዲሞክራሲና የኢኮኖሚ ዕድገት ስንመለከት ሁለቱም አገሮች ነፃ ኢኮኖሚ የላቸውም። ጥሬ-ሀብታቸውም በውጭ ኩባንያዎች ቁጥጥር ስር ያሉ ናቸው። የኬንያ ገበሬ መርዝ እየተነሰነሰበት አበባና ሻይ ለዓለም ገበያ የሚያመርትና የሚያቀርብ ነው። የጋና ህዝብ የወርቁ ተጠቃሚ አይደለም። አሁን ደግሞ ተገኝቷል የተባለው ዘይትና እየተቆፈረ የሚወጣው በእርግጥ ለትክክለኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ይውል አይውል እንደሆን፣ ሰፊው የጋና ህዝብም አዲስ ተስፋ ይጎናጸፍ አይጎናጸፍ ከአሁኑ በትክክል መናገር አይቻልም። አንድ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ሁለቱም አገሮች ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና ከዓለም ባንክ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እስካለተላቀቁ ድረስና ሁለገብ የሆነ ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እስካልተከተሉና ተግባራዊ እስካላደረጉ ድረስ በምንም ዐይነት የተስተካከለ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊያመጡ አይችሉም።
ከዚህ ስንነሳ ኢትዮጵያ ኬንያንና ጋናን እንደ ቤንች ማርክ የምትወስድበት ምንም ምክንያት የላትም። ኢትዮጵያ እንደሞዴል አድርጋ ልትወስዳቸው የምትችላቸው የተለያዩ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች አሉ። ስዊዘር ላንድን፣ አውስትሪያን፣ ስዊድንና ሌሎች ምዕራብ አውሮፓ አገሮችን እንደሞዴል መውሰድ ትችላለች። ጥያቄው ይህንን ወይም ያኛውን አገር እንደ ሞዴል ወይም እንደ ቤንች ማርክ የመውሰዱ ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህ አገሮች ምን ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲና የህብረተሰብ ግንባታ መንገድ ቢቀይሱ ነው እዚህ ደረጃ ሊደርሱ የቻሉት? ብሎ መጠየቅና ማጥናት ያስፈልጋል። ላይ የጠቅስኳቸውን የምራብ አውሮፓ አገሮች ሁኔታ ስመለከትና የተከተሉትን የኢኮኖሚ ሞዴል ካለብዙም መጨነቅ ስመለከት ተግባራዊ ያደረጉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የኒዎ-ሊበራል ፖሊሲ ጋር በፍጹም የሚጣጣም አይደለም። የእነሱ የዕድገት ደረጃ ብቻ ሳይሆን ጠቅላላው የካፒታሊስት አገሮችና፣ እንዲሁም ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ የተከተሉት ሁለ-ገብና በከፍተኛ ንቃተ-ህሊና ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንጂ ተራ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዳልሆነ በሺህ የሚቆጠሩ የኢኮኖሚ ታሪክ መጽሀፎች ያረጋግጣሉ። ስለሆነም መምረጥ የሚኖርብንና እንደመነሻ መውሰድ ያለብን፣ ለመድረስ የምንፈለገው ቦታ ዓላማችንን ከፍ ስናደርግ ብቻ ነው። እዚህ ላይ ጥያቄ የቤንች ማርክ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ ፍላጎትም እንዲኖር ያስፈልጋል። በሌላ ወገን ግን ቤንች ማርኩን ዝቅ አድርጎ የሚንቀሳቀስ ህበረተሰብና ኤሊት ቁም ነገርና ታሪካዊ ስራዎች በፍጹም ሊሰሩ አይችሉም።
6.6 ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ የመፍጠር ጉዳይ- በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች በተለይም በአፍሪካ ውስጥ ያለው ችግር ሰፋ ያለና የተገለጸለት፣ እንዲሁም በሁሉም አቅጣጫ የሚንቀሳቀስ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ያለመኖር ችግር ነው። በዚህም ምክንያት በተለያዩ አገሮች በዕድገት ስም የሚካሄደውን ዘረፋና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚባሉት በየአገሩ እየገቡ የሚያካሂዱትን ድህነትን ፈልፋይና የህዝብን ኑሮ የሚያመሰቃቅል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚቃወም ባለመኖሩ የአፍሪካ ህዝብና የአገራችንም ጭምር በከፍተኛ ሰቆቃ ውስጥ እንዲወድቁና መሰረታዊ መብታቸው እንዲነፈግ ሆኗል። የየአገሩ መንግስታት የዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ፖሊሲና የዓለም ኮሙኒቲ የሚባለውን ግፊት ከመቀበል በስተቀር የህዝቦቻቸውን መብት ሲያስጠብቁ አይታይም።
እንደሚታውቀው በታሪክ ውስጥ ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ለስልጣኔ ዋናው በር ቀዳጅ ነው። በተለይም ከአውሮፓው የሬናስን እንቅስቃሴ የምንማረው በጊዜው እንደዚያ ዐይነት ሰፋ ያለ በሁሉም መልክ የሚገለጽ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ባይኖር ኖሮ የአውሮፓ ህዝብ ኑሮ ለብዙ ዘመናት ጨልሞ ይቆይ፣ ወይም ደግሞ እንደብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የተዝረከረከ ኑሮ ይኖር ነበር። ስለሆነም አገራችን ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የምንፈልግ ከሆነ በተለይም የነቃና ኃላፊነት የሚሰማው ከማንም ድርጅት ጋር ያልተሳሰረ ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ማካሄድ ያስፈልጋል። በተለይም በዛሬው የኢትዮጵያችን ሁኔታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በደንብ ባልተደራጁበትና በሚንገዳገዱበት ወቅት የነቃ ኩሙኒቲ መመስረቱ እጅግ አስፈላጊ ነው።
የዛሬው የኢትዮጵያችንና የሌሎችም አፍሪካ አገሮች ህልውናና እንደ አገር የመኖር ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ወድቋል። ኢትዮጵያችንና የተቀሩት የአፍሪካ አገሮች በግሎባላይዜሽን ከመታሸታቸው የተነሳ ባህላቸው፣ ኢኮኖሚያቸው፣ የማህበራዊ ኑሮ ሁኔታቸው፣ የህብረተሰብአዊ አወቃቀርና የፖለቲካው ሁኔታ፣ እንዲሁም አጠቃላዩ ህብረተሰብአዊ እሴት ተበላሽቷል፤ ተዘበራርቋል። አብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮች ነፃና የራሳቸው ህልውና እንዳላቸው የማይቆጠሩበት ደረጃ ወድቀዋል። ግሎባላይዜሽን ባስፋፋው አንድ ዐይነት የኒዎ-ሊበራል አመለካከት አብዛኛው ህዝብ ወደ ነጋዴነትና ወደ ሽፍጠኝነት ተሰማርቷል። የኒዎ-ሊበራል አመለካከትንና የነፃ ንግድን የማይቀበል ልክ እንደ አውሮፓው የጨለማ የካቶሊክ ሃይማኖት የአንድ አስተሳሰብ ዘመን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስፋፋትና በመስበክ፣ ይህንን አደገኛና ጨለማን የሚያመጣ ርዕዮተ-ዓለም የሚቃወሙ ምሁራን ክትትል ይደረግባቸዋል። ስልካቸውና ኢሜይላቸውም ይጠለፍባቸዋል። የመንግስት ጠላት እየተባሉ በጥርጣሬ ይታያሉ። እንዲሰቃዩም ይደረጋል፤ ወይም ተደማጭነት እንዳይኖራቸው ተንኮል ይሸረባል። ሁሉም ነገሮች ስታንደርዳይዝድ መሆን አለባቸው በሚል አጉል አካሄድ፣ ምናልባትም አንድ ቀን እኛም ራሳችን ነጭ እንድንሆን የምንገደድበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል። ሰውነታችን ነጭ፣ ጸጉራችን ብሎንድ፣ ዐይናችን ደግሞ ሰማያዊ እንዲሆኑ የምንገደድበት ቀን መምጣቱ የማይቀር ነው። ማጋነን አይሁንብኝና ሁሉም ነገር ወደዚያ የሚያመራ ነው የሚመስለው። በሌላ አነጋገር እያንዳንዱ አገር የራሱን ታሪክ፣ ባህልና የአኗኗር ስልትና የኢኮኖሚ አወቃቀር እንደፈለገውና ለህዝቡ በሚያመች መንገድ መቀየስና ማዘጋጅት የለበትም። በዚህ ዐይነቱ አንድ ዐይነት አመለካከትና የግሎባል ኢኮኖሚ ግፊት የተነሳ ልክ አውሮፓ ውስጥ በነዳንቴ ዘመን የነበረው ዐይነት የአመለካከት መዘበራረቅ፣ በተለያየ ቋንቋ መናገርና አለመግባባት፣ ህብረተሰብአዊ እሴትንና የተፈጥሮን ህግ የሚጥስና የሚቀናቀን የፆታ ግኑኝነት ማስፋፋት፣ የወንበዴዎች መጠናከርና ወደ ማፍያነት ማምራት፣ እንዲሁም መንግስታት የአገሮቻቸው አለኝታ ከመሆን ይልቅ ወደ ማፍያ ተግባርነት መለወጥና አገርን እየሸጡ እንዲዘረፍ ማድረግ፣ ለአቅመ-አዳም ያልደረሱ ሴቶች ጥቂት ገንዘብ እናገኛለን እያሉ ራሳቸውን መሸጥ፣ ወዘተ…፣ እነዚህ ሁሉ ከግሎባላይዜሽንና ከኒዎ-ሊበራል ርዕዮተ-ዓለም ጋር የተያያዙ ናቸው። ስለሆነም ከእንደዚህ ዐይነቱ ቅጥ ያጣ ሁኔታ ለመውጣትና ለመላቀቅ፣ እንዲሁም ደግሞ ዕውነተኛ ነፃነትን ለመቀዳጀት የገበያ ኢኮኖሚና የሊበራል ዲሞክራሲ አስተሳሰብ እንደ ፍቱን መሳሪያ ሊያገለግሉ በፉጹም አይችሉም። እነ ዳንቴ፣ እነ ፔትራርካና እነ ዳንቪንቺና ሌሎችም የሬናሳንስ ምሁሮች እንዳደረጉት ኢትዮጵያችንም ሁለ-ገብ የባህል እንቅስቃሴና ዕውነተኛ የመንፈስ ተሃድሶ ያስፈልጋታል። በዚህ አማካይነት ብቻ እንደ አገርና እንደ ህብረተሰብ መኖርና መገንባት ትችላለች። ከዚህ ውጭ የሚታሰብ የአገራችንን ችግር የባሰውኑ የሚያራዝምና ስር እንዲሰድ የሚያደርግ ብቻ ነው። ስለሆነም በተለይም ወጣቱ ትውልድ በአዲስ አስተሳሰብ በመነሳትና በመታጠቅ ለአዲሲቱና ለነገይቱ ኢትዮጵያ መታገል አለበት።
6.7 የባህልን መሰረተ-ሃሳብ የመረዳት አስፈላጊነት- አብዛኛውን ጊዜ ስለ ባህል በሚወራበት ጊዜ ኢትዮጵያ ጥንታዊ ባህል ያላት አገር ነች እየተባለ ነው። ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ጥንታዊ የመንግስት አደረጃጀት ያላቸው አገሮች በሙሉ የተለያዩ ባህሎች ነበራቸው። ባህል የአንድ ህዝብ የዕድገቱ መግለጫ ነው። እንደ ማህበረሰብ ከተደራጀ ጀምሮ አውቆም ሆነ ሳያውቅ የፈጠረው ነው። ባህል በፊደልና በቋንቋ የሚገለጽ ሲሆን፣ በጠቅላላው በአኗኗር ስልትም ይገለጻል። አንድ ህዝብ ወይም ማሀበረሰብ ራሱን ለማሸነፍ ሲል ከተፈጥሮ ጋር የሚያደርገው ግኑኝነትና የተፈጥሮን ሀብት መጠቀም ራሱ ባህላዊ ክንውን ነው። ባህል በመሰረቱ አንድ ቦታ ላይ ቆሞ የሚቀር አይደለም። እንደ ህብረተሰብ ዕድገት ውስጣዊ ኃይሉም ያድጋል። አንድ ማህበረሰብ በምርት ኃይሎች ዕድገት የአመራረት ስልቱንና አኗኗሩን ሲለውጥ ባህሉም ይቀየራል። የማሰብ ኃይሉ ይዳብራል። በጥልቀትና በሰፊው እያሰበ ሲሄድ ተፈጥሮ የምትለግሰውን ከመጠቀም አልፎ አዳዲስ ነገሮችን በመፍጠር የበለጠ ውብ ውብ ስራዎችን መስራት ይጀምራል። ተፈጥሮን ዝም ብሎ የሚያዛባ መሆኑ ቀርቶ የተፈጥሮን ህግ በመረዳት ለተፈጥሮ የበለጠ ውብት በመስጠት በሱና በተፈጥሮ መሀከል ሚዛናዊ ግኑኝነት እንዲፈጠር ያደርጋል። ይህ በራሱ ጥረት የሚያደርገው ለውጥ ሲሆን በንግድ አማካይነት ከውጭ ዓለም ጋር ግኑኝነት ሲፈጥር ባህሉ እየተለወጠ ወይም እየተበላሸ ሊመጣ ይችላል።
በመሰረቱ ባህል በሚታዩና በማይታዩ ነገሮች የሚገለጽ ነው። እነዚህ መንፈሳዊና ማቴሪያላዊ ናቸው።ዕውነተኛ ባህላዊ ምጥቀት ሊኖር የሚችለው እያንዳንዱ ግለሰብ መንፈሳዊ ጥራትና ጥንካሬም ሲኖረው ነው። በዚህ አማካይነት እየረቀቀ ማሰብ ሲጀምር መንፈሳዊና ማቴሪያላዊ ነገሮችን በማጣመር ህብረተሰብአዊ ሚዛን እንዲኖር ያደርጋል። በማቴሪያል የሚገለጸው ባህላዊ ዕድገት ደግሞ በቆንጆ ከተማዎች ግንባታ፣ በአዳዲስ መሳሪያዎች ፈጠራና ወደ ሌላ የዕድገት ደረጃ መድረስ የሚገለጽ ነው። ራሱ የባቡር ሃዲድና ባቡር ስራ ከፍተኛ የባህል እንቅስቃሴ ውጤቶች ናቸው። በአውሮፓ የህብረተሰብ ዕድገት ታሪክ ውስጥ የምንረዳው ከማቴሪያል ዕድገት በፊት የመንፈሳዊ እንቅስቃሴ ነበር። ሳይንስ፣ ሊትሬቸር፣ አርኪተክቸር፣ ክላሲካል ሙዚቃና ሌሎች የማይዳሰሱ ነገሮች የዳበሩት በመጀመሪያ የመንፈሳዊ ብስለትና እንቅስቃሴ በመቅደሙ ብቻ ነው።
በታሪክ ውስጥ በብዙ አገሮች እንደተረጋገጠው ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወርድ ሲዋረዱ የመጡ ባህሎች ለአንድ ህበረተሰብ ዕድገት ጠንቅ ሊሆኑ እንደሚችሉም ነው። የአንድን ህዝብ የማሰብ ኃይል በማፈን አዳዲስ መሳሪያዎች እንዳይፈጥርና ኑሮውን እንዳያሻሽል ያግዱታል። አንድ ህዝብ ተፈጥሮን ከመቆጣጠር ይልቅ የተፈጥሮ አደጋ ሰለባ በመሆን ዘለዓለሙን እየተሰቃየ እንዲኖር ይገደዳል። ይህ አንደኛው ሲሆን፣ ባህል በስነ-ምግባርነትና በሞራል፣ በዲሲፕሊን፣ በአሰራር ዘዴ፣ በአነጋገር ስልትና ሌላውን በማክበር፣ በአለመዋሸትና ለሀቅ መቆም፣ ኃላፊነትን መቀበልና አርቆ በማሰብ፣ ሎጂካዊ አስተሳሰብና በትንተናዊ በተወሳሰቡ የአተናትንና የአገላለጽ ዘዴዎች፣ወዘተ…፣ የሚገለጽ ነው። እነዚህ ነገሮች የሚጎድሉት ትውልድ ወይም ህዝብ በምንም ዐይነት ዕውነተኛ ነፃነትን ሊቀዳጅ አይችልም፤ የተከበረች አገርም በፍጹም መገንባት አይችልም። ከዚህ ስንነሳ የአንድ አገር ዕድገትና ብሄራዊ ክብር መጠበቅ በተለይም በማይታየው ባህል የሚወሰን ነው። በታሪክ እንደተረጋገጠው ለአንድ አገር ውድቀት ዋናው ምክንያት የባህል ውድቀት በሚከሰትበት ጊዜ ነው። እንደዚህ ዐይነቱ የባህል መከስከስ በግሪክ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ4ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ሶፊስቲያዊ አስተሳሰብ በተስፋፋበት ወቅት ስልጣኔው መውደቅ የቻለበት ዘመን ነበር። የሮማውያንም አገዛዝ ሊወድቅ የቻለው በሞራል መበላሸትና በማበጥ ነው። በእንደዚህ ዐይነቱ የሞራል መበላሸት ወቅት ውስጥ የአገዛዞችም ፖለቲካ ወደ ጦርነትና ወደ ዘረፋ፣ እንዲሁም አገሮችን ወደ ማፈራረስ ያመራል።
ወደ አገራችን ስንመጣ በአንድ በኩል የፊዩዳሉን ወደ ኋላ የሚጎትት አስተሳሰብና የተፈጥሮን ሚዛን የሚያናጋ የአሰራርና የአኗኗር ስልት የሚጋፋ አዲስ ባህል መዳበር ባለመቻሉ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ደግሞ እጀግ የተዘበራረቀ የካፒታሊዝም አጉል ባህል በመስፋፋቱ፣ አሁን ደግሞ በግሎባላይዜሽን ስም ሁሉ ነገር አቅድ ባጣበት ወቅት የሰፊውን ህዝብ መንፈስ ሊያድስ የሚችል ባህል ማዳበር የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል ማለት ይቻላል። በዚህም ምክንያት ሁለት የተበላሹ ነገሮች ሲጣመሩ በተራው ህዝብና በተፈጥሮ ላይ ዘመቻ እንዲካሄድባቸው እየተደረገ ነው። ስለሆነም የባህል ተሃድሶና እየመላለሱ ጥያቄዎችን የማቅረቡና የመጠየቁ ጉዳይ ለችግራችን ዐይነተኛ መፍትሄ እንደሚሆኑ መረዳት ያስፈልጋል።
6.8 የድርጅትና የኢንስቲቶሽኖችን አስፈላጊነት የመረዳት ጉዳይ- የአንድ አገር ዕድገት ሊፋጠንና መልክ ሊይዝ የሚችለው
ሁሉም በየፊናው ሲደራጅና፣ ይሁንና ደግሞ አገርን በጋራ የመገንባት ኃላፊነትን እንደመሰረታዊ ሃሳብ ወይም መነሻ አድርጎ ሲወስድ ብቻ ነው። ድርጅት ስራዎችን ማቀላጠፊያ ዘዴ ነው። ኃይልን መሰብሰቢያና በተወሰነ የአሰራር ዘዴ ለተወሰነ ግብ መንቀሳቀሺያ መሰላል ነው። ማንኛውም ድርጅት በተለይም ደግሞ አገርን የሚመለከት ነገር ሊሰራ የሚችለው በዲሲፕሊን የታነጸና ኃላፊነት የሚሰማው ድርጀት በየቦታው ሲኖር ብቻ ነው። ድርጅትና ኢንስቲቱሽኖች የሰውንና በተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ሀብቶችን ማንቀሳቀሻ መሳሪያዎች ናቸው። አንድ አገር የተለያዩ ድርጅቶችና ኢንስቲቱሽኖች ከሌሏት ዕውነተኛውን ዕድገት ልትጎናጸፍ አትችልም። ከዚህ ስንነሳ በአገራችንም ሆነ በብዙ የአፍሪካ አገሮች ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ዘመናዊና ኃላፊነት የሚሰማቸው ኢንስቲቱሽኖችና ድርጅቶች በየቦታው ስላልተተከሉ ሀብትንና በየቦታው ስራ-አጥቶ ወይም ፈቶ የተቀመጠውን ሰፊ ህዝብ ማንቀሳቀስ አልተቻለም። በደንብ ያልተደራጁ ድርጅቶችና ኢንስቲቱሽኖች አለመኖር እንደሚታውቀው ለድህነት አንደኛው ምክንት ነው።
በአገራችንም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ያለው ችግር ድርጅትንና ኢንስቲቱሽኖችን የመመስረት ባህል አለመኖርና፤ ወይም አስፈላጊነታቸውn ያለመረዳት ነው። ከዚህ ስንነሳ ለአገር እንታገላለን የሚሉትን የተለያዩ ተቃዋሚ ኃይሎችን ሁኔታ ስንመለከት በቂና ብቃት ያለው ድርጅት ለመመስረትና ሪሶርስ ለማንቀሳቀስ ችግር እንደ አለባቸው መገንዘብ እንችላለን። ሌላው ቢቀር እንኳ እዚህ ውጭ አገር ስንትና ስንት ዕውቀት በተትረፈረበት አገር መደራጀትና ትክክለኛ ዕውቀት መገብየት የማንችልበት ደረጃ ደርሰናል። መንቀሳቀስና ኃላፊነታችንንም ልንወጣ የምንችለው ባለንበት አገር የራሳችን ኢንስቲቱሽኖች ሲኖሩንና በሚገባ ስንደራጅ ብቻ ነው። በኢንስቲቱሽን አማካይነት ብዙ ዕውቀትና ኢንፎርሜሽን መሰብሰብ እንችላለን። ሌላውንም ማስተማር እንችላለን። በዚህ ረገድ ብቻ ነው ታሪካዊ ኃላፊነታችንን መወጣት የምንችለው። ስላዳመጣችሁኝ በጣም አመሰግናለሁ።
ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)
fekadubekele@gmx.de
Leave a Reply