”ዛሬም ታለቅሳለች!”
ትላ’ትናም – ዛሬም
ቁማም – ተቀምጣም
በውኗም – በህልሟም፤
እምባ እያዘነበች
ደም እያፈሰሰች፤
ሁሉንም እያየች
ዛሬም ታለቅሳለች።…….
‘’ረስታ – ተረስታ
በራሷ ላይ ዘግታ፤
ከጥዋት እስከማታ
እንቅልፏን ተኝታ’’።
ተብሎ ተወርቶባት
ለብዙ ዘመናት
ታሪክ ተጽፎባት፤…….
እሷ ግን፣ እሷ ናት
ዓለም የሚያያት፤
እምባ እያዘነበች
እህህ…… ትላለች
ትንሰቀሰቃለች፤
ሁሉንም እያየች
ዛሬም ታለቅሳለች።………
ተማፅኖ ተማሎ
ተገዝቶ ምሎ
ገ’ሎና አስገድሎ ፤
‘’ለ’ርሀብ – ‘ርዛትሽ
ለልመና – ፅናትሽ
ለፍትህ – እጦትሽ
ለሰላም – ለፍቅርሽ፤
መድሀኒት አውቃለሁ
እኔ እሻልሻለሁ’’፤
ብሎ የሚገባው
እምባዋን ሊጠርገው
መፍሰሱን ሊያቆመው፤……
ጭራሽ አብሶባት
ሀዘን ደራርቦባት፤
ማቁን አስለብሶ
አመድ አስነስንሶ፤
ሰይፉንም አስታጥቆ
ደረት አስደልቆ፤
ዙሪያ እያስረገደ
ሙሾ እያስወረደ፤
ሰድቦና አሰድቦ
ክብሯንም አዋርዶ፤
እዬዬ….. አሰኝቶ
የዛሩን ተወ’ቶ፤
ደም – ከደም አቃብቶ
ምሱንም አግኝቶ፤
ይሄዳል ማን ቀርቶ
አስለቃሽ ተከቶ።……..
እሷ ግን፣ እሷ ናት
ዓለም የሚያያት።…..
አለቀልሽ ሲሏት
ነፍስ እየዘራባት፤
የነቁጥ ጭላንጭሊት
ደ’ሞ ሲታይባት፤
‘’የልጆቿ’’ ልክፍት
አዙሮ ሲጥላት
ጨለማ ሲያስገባት፤
ስትደነባበር……
ስትውተረተር…..
ጣር ሲያጣጥራት……..
ሺ’ ዘመን አለፋት።
ትውልድ ሁሉ ዘንግቶ
ሰው ምሆኑን ‘ረስቶ፤
ማንነቱን አ’ቶ
አደራውን ከድቶ፤
መፍትሄ የጠፋው
ምን ይሆን መጨረሻው፤
ደም አስለቃሽ፣ ያለመታከቱ
ያለመማሩ፣ ከታሪክ – ከትላንቱ
የ’ሷም አይን ያለመጥፋቱ።
——//—-
e-mail: philiposmw@gmail.com
Leave a Reply