ፋኖና ኦነግ ሸኔ በማጣቀስ በውጭ አገራት የሚቀርቡ የጥገኝነት መጠየቂያ ማመልከቻዎች ተቀባይነት እንደማያገኙ ይህንኑ ጉዳይ በማስፈጸም የሚሠሩ አንድ ባለሙያ ለጎልጉል ጥቆማ ሰጡ። ድርጅቶቹ “ነውጥ ቡድኖች” ወይም “violent group s” በሚል የተፈረጁበት አግባብ መኖሩንም አክለው ገልጸዋል።
ከአገራቸው በተለያዩ ምክንያቶች ተሰድደው ጥገኝነት የሚጠይቁ ወገኖች ከለላ ለማግኘት በሚያስገቡት የስደተኝነት ማመልከቻ በአሁኑ ሰዓት እንደየብሔራቸው ወይም ብሔራቸውን በመቀየር በብዛት በማስረጃነት የሚጠቀሙት የፋኖና የኦነግ ሸኔን ትግል እንደሆነ ይታወቃል።
“ለምሳሌ በካናዳ ድርጅቶቹ “violent groups” ተብለዋል” የሚሉት የሕግ ባለሙያ ይህን የተረዱት በሥራቸው አማካይነት የደንበኞቻቸውን ጉዳይ ሲከታተሉ ነው። ባለሙያው ከተሞቹን ለይተው በስም ባይጠሩም መረጃውን የሰሙት ከሚመለከታቸው አካላት እንደሆነ አልሸሸጉም።
ሁሉም አገራት በኢትዮጵያ ባሏቸው ኤምባሲዎችና ዲፕሎማቶች፣ ከዓለም ዓቀፍ ድርጅት ሪፖርቶችና በምሥጢር በሚቀርቡላቸው የስለላ ሪፖርት ስለፈለጉት ዜጎች ከሚያውቁት በላይ መረጃ እንዳላቸው ያስታወቁት ባለሙያው “ይህ ጸሐይ የሞቀው የዓለም ዕውነት ነው” በማለት ነው።
በዚሁ መነሻ ጥገኝነት የሚሰጡት የምዕራቡ ዓለም አገራት ስለ ፋኖና ኦነግ ሸኔ አየር ላይ በቡድኖቹ ደጋፊዎችና የራሳቸው ሚዲያዎች የሚባለውን ሳይሆን አገራቱ እንደ መረጃ የሚወስዱት በራሳቸው አገባብ የራሳቸው መረጃ በመሰብሰብ ነው። በዋናነት ስለ አገራቱ ባላቸው መረጃ ተንተርሰው የስደተኞችን ማመልከቻ እንደሚያስተናገዱ የጠቆሙት የመረጃው ባለቤት “ስደተኛ ተቀባይ አገራት ስለሁሉም እንቅስቃሴ ባዕድ አይደሉምና ራስን በመረጃ ማብቃት ግድ ነው” ብለዋል።
“እኔ” አሉ የሕግ ባለሙያው “እኔ ይህን የምለው ስደት ጠያቂዎች ተስፋቸው እንዳይጨልም ነው። የስደት ማመልከቻ ምላሽ እንደሚቀያየር ቢታመንም አሁን ላይ ያለው እውነት ግን ይህ ነው” በማለት መረጃውን አጋርተዋል።
ከለላ ሰጪ አገራት እንደ ፖለቲካ ፍላጎታቸው፣ ዓላማቸውና በወቅቱ ካለው መንግሥት ጋር ካላቸው ግንኙነት አንጻር እያወቁ እንዳላወቁ በመሆን ዓላማቸው እንዲሳካ ሲሉ የስደት ማመልከቻ ላይ ያላቸው ቁጥጥር እንደሚጠብቅና እንደሚላላ ይታወቃል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የጥገኝነት ማመልከቻ ጭራሽ ቁጥጥር አልባ የሚሆንበትና ለይስሙላ ማመልከቻ የሚቀርበበት አግባብ እንዳለ አስታውሰው “አሁን ላይ ድርጅቶቹ “violent groups” ስለተባሉ ተጠንቀቁ” ሲሉ ጥገኝነት ጠያቂዎችን መክረዋል። የሚለወጥ ነገር ካለ ሲለወጥ መረጃውን እንደሚያካፍሉም ጠቁመዋል።
የሕግ ባለሙያው ባሉበት አካባቢ ያለውን ጠቅሰው የሰጡትን መረጃ ተከትሎ ያነጋገርናቸው “ስለተባለው ጉዳይ ለጊዜው መረጃ” እንደሌላቸው ጠቁመው “አሁን የሰላም ድርድር ጥያቄ ቀርቧል፤ የተወሰነ ርቀትም እየሄደ እንደሆነ ይሰማል፤ ይህንን እያካሄዱ ያሉት አገራት ደግሞ ጥገኝነት የሚፈቅዱት ዋናዎቹ አገራት ናቸው። የሰላም ስምምነቱን የማይቀበሉ ከሆነ “violent groups” ከሚለው ከፍ ብሎ ሊሄድ የሚችል ፍረጃ እንደሚኖር አመላካች ነው” ብለዋል።
በሌላ አነጋገር አሁን ላይ በስፋት እየተነገረ ያለው ድርድር ወደ ፍሬ እንዳይመጣ ቡድኖቹ የሚያደናቅፉ ከሆነ እንደነ አልቃይዳ በዓለምአቀፍ ደረጃ የአሸባሪ ቡድኖች ቋት ውስጥ የሚመደቡ ይሆናል። ይህም ከሁለቱ ቡድኖች የሚሰጥ የድጋፍ ማስረጃ በየትኛውም ዓለም በጸረ-አሸባሪነት ትግል ውስጥ ያሉ አገራት ለጥገኝነትን የማይቀበሉት ይሆናል። እንዲህ ያለውን መረጃ ይዘው የሚመጡም የአሸባሪ ድርጅት አባል ተብለው ጥገኝነት በሚጠይቁበት አገር ክስ ሊመሠረትባቸው እንደሚችል ቀደምት አሠራሮች ይጠቁማሉ።
በዘመነ ትህነግ የሥርዓቱ ሰዎች ባገኙት መድረክ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 11 በመቶ አድጓል እያሉ ሲደሰኩሩ በመቆየታቸው በየአገራቱ የሚገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳያቸው ውድቅ ሲደረግባቸው መቆየቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ከጥገኝነት ሰጪ አገራቱ ሲነገር የነበረው ምክንያት “አገራችሁ በልማት እያደገች ነው፤ 11 በመቶ ዕድገት በተከታታይ እያስመዘገበች ነው፤ ስለዚህ መሰደድ የለባችሁም” የሚሉ ተስፋ አጨላሚና ቅስም ሰባሪ ምክንያቶች ይሰጡ እንደነበር ይታወሳል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
በዘር በጎሳ በቋንቋ እያላከኩ ተጨቆንኩ አስራቡኝ ገደሉን ገለመሌ እያሉ ጥገኝነት ማግኘት ቀርቷል። ዛሬ የውሸት ፊኛ ነፍተው ማመልከቻ ያስገቡ ሁሉ እየተደረሰባቸው ወደ መጡበት እየተሸኙ ነው። ትላንት ኤርትራዊው ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት አርጋን እያለ በአረብና በአውሮፓ ምድር በዚህም በዚያም ጥገኝነት ሲያገኝ፤ ወዲያው ትግሬውና አማራውም በኤርትራ ስም ሲነግድ ፤ቆይቶ አሁን ደግሞ ሌሎች ብሂርተኞች ጥገኝነት ፈላጊ ሆኑ። እውነትን ለማወቅ የዘገዪ ወይም ሆን ብለው ኢትዮጵያን ማፈራረስ የሚፈልጉ እንደ ግብጽ ያሉ በዚህም በዚያም እሳት እያቀበሉና አይዞአችሁ በማለት ባህር ቢያሻግሯቸውም ጊዜው አሁን የስደተኛ አይደለም። ተሰዳጅ ከመብዛቱ የተነሳ ሃገራት ለረጅም ጊዜ የነበራቸውን የስደተኞች አቀባበል ፓሊሲ እየቀየሩ ይገኛሉ። በቅርቡ በፓናማ በኩል ብዙ ሺህ ዶላር ከፍለው ወደ አሜሪካ ሊገቡ ሲሉ የተይዙት ቻይናዊያን ወደ ሃገራቸው እንደተመለሱ ማንበብ ያስፈልጋል። ገና ብዙ ገመና ይመጣል!
አሁን በሜክሲኮ በኩል በሺህ የሚቆጠር ህዝብ መጉረፉም ለመከራ እንጂ ለጤና አይሆንም። በተለይ ዶናልድ ትራምፕ ከተመረጠ እየተለቀሙ ወደ መጡበት እንደሚመለሱ የታወቀ ነው። ዛሬ በአሜሪካ፤ በጀርመን፤ በምስራቅ አውሮፓ የነጭ አክራሪዎችና የናዚ ተከታዪች ቁጥር መብዛት ከስደተኛ ጥላቻ ጋር የተያያዘ ነው። በእርግዝና ለጉብኝት መጥተው ልጆቻቸን በአውሮፓና በአውስትራሊያ እንዲሁም በሰሜን አሜሪካ በመውለድ ዜግነት የሚገኝበት መንገድ ሁሉ በቅርቡ ይዘጋጋል። እልፍ ሃብትና ንብረት በሃገራቸው ላይ እያላቸው ከሃገር በመውጣት ባልሰሩበት የመንግስት ተጠዋሪ የሆኑ ወስላቶች ሁሉ የሚጋለጡበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ባጭሩ ዓለም ሰልችቶታል። አዋጊና ተዋጊው፤ ተጋዳዩና አጋዳዪ ሌላውን እሳት ውስጥ እየወሸቀ የራሳቸውን ዘመድና አዝማድ ወደ ውጭ በተዘረፈ ሃብትና ንብረት ማመቻቸቱም በሩ እየጠበበ ነው። ፋኖ በለው ኦነግ ሸኔ፤ ወያኔ በለው ሻቢያ ከአሁን በህዋላ ምንም ምክንያት ቢደረደር ጥገኝነት የማግኘት መንገድ እየጠበበና ለመዘጋት ጥቂት እንደቀረው በጉልህ ማየት ይቻላል።
ዝም ብሎ ውሃ በቀጠነ ጦርነትን እንደ መፍትሄ ከመውሰድ ይልቅ አማራጭ መንገዶችን በሰከነ እይታ መፈተሽ አስፈላጊ ነው። መንግስትም ቢሆን እዚህ ጋ የእኔን ስም ጠርቶ ሲያነጥስ ሰምቼዋለሁ በማለት ሰውን እያፈሱ እስር ቤት ከመክተት ይልቅ ነገሮችን ለማስከን ሆደ ሰፊ መሆን መቻል አለበት። በምንም ሂሳብ አንድ የመንግስት ሃይል በራሱ ህዝብ ላይ ድሮና አውሮፕላን መጠቀም የለበትም። በመገዳደል የሚመጣው ረሃብና መከራ ብቻ ነው። የኦነጉም ሆነ የፋኖው ትግል ሁለ አቅፍ እስካልሆነ ድረስ ትርፍ አያመጣም። ሰው በሰውነቱ የሚከበርባት ኢትዮጵያ እንድትኖር ካስፈለገ ህገ መንግስቱ መቀየር አለበት። ሻቢያና ወያኔ ከዚያም ኦሮሞው የተጋቱት የፈጠራ የፓለቲካ አተላ ለቆሻሻ መዳረግ አለበት። የዛሬ መቶ ዓመት አማራ ይህን ሰራኝ፤ ሚኒሊክ እንዲህ አረገ እያለ በማያውቀው ታሪክ የራስን ሰንካላ ሃሳብ እየሰኩ ህዝብን ማወናበድ መቆም አለበት። ቂምና በቀል የተላበሰ የፓለቲካ ድርጅት ዘላቂነት የለውምና ሌላውን ስንኮንን ዛሬ ላይ በብሄር ነጻነት ስም የሚፈጸመውን በደልና ገመና መመዘን አስፈላጊ ነው። ያለፈ በደልን የሚያሰላ ህዝብ ፈውስ የለውም። ሁሌ እንደተገዳደለና እንደተሰደደ ነው የሚኖረው። ችግሩ ያኔና ዛሬ ዓለም አንድ አለመሆኗ ነው። መጠጊያ የለም። ቀን እያለ ሃገራችን የሁላችን መኖሪያ እንድትሆን አጥብቀን እንስራ።