እ.ኤ.አ. ቅዳሜ ኖቬምበር 23, 2013 ዓ.ም. በጀርመን ኑረንበርግ ከተማ የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲ ኢሕአፓ ያዘጋጀው ሰልፍ ተካሄደ።በቅርቡ የሳዑድ አረቢያ መንግስትና ዜጎች በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸሙትን እና አሁንም እየፈፀሙ የሚገኘውን ዘግናኝና ኢሰብዓዊ ድርጊት ለማውገዝ ቁጥራቸው ከ400 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ከተለያዩ የጀርመን ከተሞች የተገኙ ሲሆን በዕለቱ በኢትዮጵያውያን ላይ ይፈፀም የነበረውን ዘግናኝ ድርጊቶች ፎቶ የያዙ በራሪ ወረቀቶችን በመበተን ኢትዮጵያውያን የሚገኙበትን አሰቃቂ ሁኔታ ለአለማቀፍ ማህበረሰብ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራም ተሰርቷል።
ከዚህ ጎን ለጎን የወያኔ አስተዳደር በቅርቡ ሰማያዊ ፓርቲ ይህንን የሳዑዲ መንግስትን ድርጊት ለማውገዝ በአዲስ አበባ የጠራውን ሰልፍ በኃይል መበተኑን የሰልፉ ታዳሚዎች በተለያዩ መፈክሮች የተቃወሙት ሲሆን በሰልፉ መዝጊያ ንግግር ላይም በጀርመን የኢሕአፓ የፕሮፓጋንዳና ቅስቀሳ ክፍል ተጠሪ ወጣት በየነ መስፍን ‘‘የወያኔ ድርጊት በቁስላችን ላይ ጥዝጣዜን የጨመረ ፋሽስታዊ ድርጊት ነው‘‘ ሲል ገልጾታል።
ይህ ከሶስት ሰዓት በላይ የፈጀ ሰልፍ ከመጠናቀቁ በፊት የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበራት ተጠሪዎች ‚‘‘ዛሬ በአደባባይ ድማፃችንን ከማሰማት ባሻገር በወገኖቻችን ላይ እየተፈፀመ ላለው ግፍ ዋናዎቹን ወንጀል ፈፃሚዎችና ተባባሪዎችን በአለማቀፍ ፍርድ ቤቶች እንዲዳኙ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመራችንን እንገልፃለን‘‘ ሲሉ ሃሳባቸውን ከመግለጻቸው ባሻገር የወጣት ዜጎቻችን በዚህ መጠን መሰደድ የሀገሪቱ የፖለቲካ ስርአት መዝቀጥ ውጤት ነው በማለት መልእክቶቻቸውን አስተላልፈዋል።
በየነ መስፍን ከጀርመን
Leave a Reply