ጋዜጣዊ መግለጫ
በ1929 ዓ/ም ፋሺሽት ኢጣልያ 30000 ኢትዮጵያውያንን በአዲስ አበባ ከተማ በሶስት ቀኖች ውስጥ የጨፈጨፈችበት 80ኛ የየካቲት 12 ቀን ዝክረ-በዓል በዓለም-አቀፍ ደረጃ ተከብሯል። እስካሁን ለድርጅታችን በደረሰው ዜና መሠረት፤ በዓሉ በአዲስ አበባ፤ በዳላስ፤ በአትላንታ፤ በማያሚ፤ በኒውዮርክ፤ በዋሺንግተን ዲ.ሲ.፤ በሮም፤ በኮሎኝ፤ በአውሮራ፤ በቫንኩቨር፤ በቶሮንቶ፤ በሲያትል፤ በፕሪቶሪያና በስቶክሆልም ተከብሯል። የአከባበሩም ዘዴ በአብዛኛው በጸሎት ሲሆን፤ እንደ ዳላስ፤ ኒውዮርክ፤ ፕሪቶሪያና ሮም ባሉ ከተሞች በጉባኤ፤ እንዲሁም በዋሺንግተን ዲ.ሲ. በሰላማዊ ሰልፍ ተከናውኗል።
ካጋጠሙት እጅግ የሚያበረታቱ ክስተቶች ውስጥ፤ ከፍ ያለ ምሥጋና የሚገባቸው የመገናኛ ብዙኃን ስለ ሰማእታቱ ቀን ሰፊ ግንዛቤ እንዲገኝ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ነው። እነዚህም ቪ.ኦ.ኤ. ሬዲዮ፤ የጀርመን ሬዲዮ፤ ኢሳት፤ ሕበር ሬዲዮ፤ ኢ.ቢ.ኤስ (ርእዮት)፤ የዳላስ ኢትዮጵያ መረዳጃ ማሕበር ሬዲዮ፤ ማሕደረ ሬዲዮ፤ ጣና ሪዲዮ፤ እና ኤስ.ቢ.ኤስ (አውስትሬሊያ) ሬዲዮ ናቸው።
ከተገኙው መልካም ውጤቶች ውስጥ፤
(ሀ) ቫቲካን፤ ፋሺሽት ኢጣልያን ደግፋ ስለ ነበር፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ ከታች በተመለከተው ድረ-ገጻችን የሚገኘው አቤቱታ በ700 ተጨማሪ ሰዎች በላይ ተፈርሟል። ባሁኑ ጊዜ የፈራሚዎች ቁጥር 5600 ቢደርስም የሚፈለገው 100000 ስለሆነ ተጨማሪ ጥረት እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው።
(ለ) በኢጣልያ፤ ሮም ከተማ በተከናወነው፤ በአብዛኛው ኢጣልያኖችና ጥቂት ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ጉባኤ፤ ውይይቱ ያተኮረው በኢትዮጵያ ላይ ተፈጽሞ ለነበረው የጦር ወንጀል ተጠያቂ የነበሩ ፋሺሽቶች የጀርመን ተጠያቂዎች ነረምበርግ (Nuremburg) በተሰኘው የፍትሕ ሥርዓት እንደ ተከሰሱ ወንጀል ፈጻሚ የነበሩ ኢጣልያኖችም ለፍትሕ መቅረብ እንደነበረባቸው ሐሳቦች በመለዋወጥ ነበር።
(ሐ) ሮም በተከናወነው ጉባኤ የተነሳው ሌላው አርእስት “የኢትዮጵያ ጨፍጫፊ” በመባል ለሚታወቀው ለሮዶልፎ ግራዚያኒ፤ የቫቲካን ተወካይ በተገኙበት፤ እ.አ.አ. በነሐሴ 2012 ስለ ተመረቀለት መታሰቢያና መናፈሻ ነበር። አፊሌ በምትባል የኢጣልያ ከተማ የሚገኘው መታሰቢያ እንዲወገድና ለጉዳዩም ተጠያቂ የሆኑት የከተማው ከንቲባ እና ምክትል ከንቲባ የእስር ፍርድ ተበይኖባቸው ጉዳዩ በይግባኝ በመታየት ላይ ቢሆንም ሮም የሚገኙ የኢትዮጵያ ወዳጆች በቅርብ እየተከታተሉት ነው።
ፋሺሽት ኢጣልያ በኢትዮጵያ ላይ ለፈጸመችው እጅግ ከባድ የጦር ወንጀል፤ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በመጨፍጨፋቸው፤ 2000 ቤተ ክርስቲያኖች፤ 525000 ቤቶችና 14 ሚሊዮን እንስሶች በመውደማቸውና ብዙ ንብረት በመዘረፉ እንዲሁም ቫቲካን ለፋሺሽቶቹ ስለ ፈጸመችው ድጋፍ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታ እንዲጠየቅና ተገቢው ካሣ እንዲከፈለው፤ ድርጅታችን ጥረቱን እየቀጠለ ነው፡፡
ቸሩ የኢትዮጵያ አምላክ ለውድ ሐገራችን የሚገባውን ፍትሕ እንድናስገኝ ይርዳን።
ዓለምአቀፍሕብረትለፍትሕ – የኢትዮጵያጉዳይ
4002 Blacksmith Drive, Garland, TX 75044; Tel: (214)703 9022
www.globalallianceforethiopia.org; E-mail: info@globalallianceforethiopia.com
Leave a Reply