ክፍል አንድ
ፍርሃት የግለሰቦች ባህሪ መገለጫ ስለሆነ በማኅበረሰብ ደረጃ የሚኖረውን ገጽታ እና ትርጓሜ ማስቀመጥ ያስቸግራል። አንዱ ሰው የሚፈራውን ነገር ሌላው ላይፈራው ስለሚችል ፍርሃት እንደ የግለሰቡ ባህሪ እና ጥንካሬ ወይም ስነ-ልቦናዊ ሁኔታ የተለያየ መልክ ይኖረዋል። ይሁንና በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የሚጋሩት ባህልና ስነ-ልቦናዊ ሁኔታ እንደመኖሩ ሁሉ የሚጋሩትም ፍርሃት ወይም ደስታ ወይም ሃዘን ወይም ድፍረት ወይም ሌሎች ባህሪያት ይኖራል። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ሰዋዊ ባህሪያት ለአንድ ማህበረሰብ ወይም ለበርካታ ሰዎች የወል መገለጫ ተደርጎ ሲገለጽ ይስተዋላል። ‘የዚህ አካባቢ ሰዎች ጀግኖች ወይም ጸብ ፈሪዎች ወይም እሩህ ሩህዎች ወይም ጨካኞች ወይም ቂመኞች ወይም ገራገሮች ወይም ተንኮለኖች ወይም ጎጠኞች ወይም ሌላ ባህሪ ያላቸው ናቸው’ የሚል አገላለጽ የተለመደ ነው። ይህ አይነቱ አነጋገር ሳይንሳዊ መሰረት ያለው ባይሆንም በአካባቢው ላይ ጎላ ብለው በሚታዩ ሰዎች ላይ ተደጋግሞና ተዘውትረው የሚታዩ ተመሳሳይ ባህሪያት የአካባቢው ሰው ሁሉ መገለጫ ተደርገው ስለሚወሰዱ ድምዳሜው ለስህተት የተጋለጠ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ለመግለጽ እወዳለሁ። ከዚህ መንደርደሪያ በመነሳት በዚህ ጥልቅ ጥናት ባላካሄድኩበት ነገር ግን ደጋግሜ ሳብሰለስለው በቆየሁት የፍርሃት ባህል እና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ድባብ ዙሪያ ያለኝን ምልከታ ለአንባቢያን ለማካፈልና በጉዳዩም ላይ ለመወያየት ወሰንኩ።
በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የፍርሃት ድባብ እንዲሰፍን እና ከዚያም አልፎ ባህል እንዲሆን ምክንያት ከሆኑት በርካታ ነገሮች መካከል የተወሰኑትን ልጥቀስና በእኛ ማኅበረሰብ ውስጥ ያላቸውን ገጽታ በመጠኑ ለመዳሰስ እሞክራለሁ። በስነ-ልቦና ጠበብቶች ከሚጠቀሱት ዋና ዋና የፍርሃት ምንጮች መካከል፤ ነፃነትን ማጣት፣ ነገ የሚሆነውን ማወቅ አለመቻል፣ የህሊና እና የአካል ቁስልን ባስከተሉ ትላንቶች ውስጥ ማለፍ፣ የማያቋርጥ ብስጭት ወይም ንዴት፣ ድህነት በሚያስከትለው ስቃይ ውስጥ መማቀቅ፣ አጋር እና አለኝታ ማጣት፣ በሌሎች ክፉኛ መነቀፍ፣ መንጓጠጥ፣ መጠላት እና መገለል፣ በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነትን ማጣት፣ የሞት አደጋን ማሰብ፣ ሽንፈት ወይም ስኬት አልባ ሆኖ መቆየት፣ እና ሌሎችም ይገኙበታል። ከእነኝህ መክንያቶች ውስጥ የአንዱ መከሰት አንድን ሰው ወደ ፍርሃት ውስጥ ሊከት እንደሚችል ጥናቶች ይጠቁማሉ። እነኝህ ምክንያቶች ተደራርበውና በአንድ ጊዜ በአንድ ሰው ወይም በአንድ ማኅበረሰብ አባላት ላይ ሲከሰቱና ዕልባት ሳያገኙ እረዘም ላለ ጊዜ ሲቆዩ ደግሞ አደጋቸው የከፋ ነው የሚሆነው። ከዚህም በመነሳት ወደ እኛ ማህበረሰ ስንመለስ በግላችንም ሆነ በጋራ ህይወታችን ከላይ ከተጠቀሱት የፍርሃት መንሰዔዎች መካከል ስንቶቹ በህይወታችን ውስጥ ተከስተዋል፣ ስንቶቹን በአሸናፊነት አለፍናቸዋል፣ ስንቶቹስ ዛሬም ድረስ አብረውን ይኖራሉ፤ የሚሊቱን ጥያቄዎች እያንዳንዱ ሰው እራሱን እንዲጠይቅ እየተውኩ በወል በምንጋራቸው ጥቂት የፍርሃት መንሰዔዎች ላይ ላተኩር።
የነፃነት ማጣት
ሰብአዊ መብቶች በገፍ በሚጣሱበት እና ዜጎች የሰውነት ክብራቸው ተገፎ፣ ተዋርደውና ነፃነታቸውን ተነጥቀው በሚኖሩበት አገር ሁሉ ፍርሃት ትልቁ ገዢ ኃይል ነው። በእንዲህ ያለው ማህበረሰብ ውስጥ የፍርሃት ሰለባ የሆኑት እና ነፃነት አልባ ሕይወትን የሚገፉት ተጨቋኞቹ ብቻ ሳይሆኑ ጨቋኞቹም ጭምር ናቸው። ተጨቋኖቹ በግፍ ልንገደል፣ ልንታሰር፣ የስቃይ ሰለባ ልንሆን፣ ታፍነን ልንሰወር፣ ከሃገር ልንሰደድ፣ ከሥራ ልንባረር፣ ንብረታችን ሊወረስ፣ በግዞት ከቦታ ቦታ ልንዛወር፣ ከቅያችን ልንፈናቀል፣ በሃሰት ክስ ልንወነጀል፣ ደሞዛችንን ልንነጠቅ፣ ከሥራ ደረጃችን ልንቀነስ፣ ወዘት … እያሉ አደጋዎችን እያሰቡ በሽብርና በፍርሃት ቆፈን ተይዘው ‘ጎመን በጤና’ በሚል የማፈግፈጊያ ስልት መብቶቻቸውን አሳልፈው በመስጠት የግፍ እንቆቋቸውን እየተጎነጩ መራራ ሕይወታቸውን ይመራሉ። ጨቋኞቹም ይህን በነፍጥ እና በሕግ አንበርክከው ነፃነቱን የነጠቁትና ለስቃይ የዳረጉት ሕዝብ በአንድ አይነት ተአምር በቁጣ ገንፍሎ ከተነሳ አንድም ቀን እንደማያሳድራቸው ጠንቅቀው ስለሚያውቁ እያንዳንዱን ደቂቃና ሰዓታት ልክ እንደ ተጨቋኙ በፍርሃት እና በሽብር ነው የሚያሳልፉት። ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱም፣ የእለት ሥራቸውንም ሲያከናውኑ፣ ሲተኙም ሆነ ሲዝናኑ በሠራዊትና በመሣሪያዎች ጋጋታ ታጅበው ነው። ምናልባትም ከተጨቋኞቹም በባሰ ፍርሃት ውስጥ ነው የሚኖሩት።
ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ በቅጡ ያጤንን እንደሆነ ገዢና ተገዢ እርስ በእርስ የሚፈራሩበት፤ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ ተቃዋሚዎች መንግሥትን የሚፈሩበትና አንዱ ሌላውን የማያምንበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። የመንግሥት ፍርሃት ከተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎች አልፎ የሲቪክ ማኅበረሰቡን፣ የሙያ ማኅበራትን፣ ነጋዴውን፣ ምሁራኑን፣ ገበሬውን፣ ወጣቱን እና ሌላውንም የኅብረተሰብ ክፍል ክፉኛ የሚፈራበትና በቁራኛ የሚከታተልበት፤ እነሱም መንግስትን እንደ ተናካሽ አውሬ የሚፈሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በመንግሥትና በሕዝቡ፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በመንግሥት፣ በሕዝቡና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ካለመተማመን የመነጨው ይህ ጥልቅ ፍርሃት በአገሪቱ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ጥቁር ደመናን ጋርዷል። በገዢው ኃይል በኩል ያለውን የፍርሃት ድባብ ለመመልከት በየጊዜው መንግሥት የሚወስዳቸውን የኃይል እርምጃዎች፣ የሚያወጣቸውን የማፈኛ ሕጎች፣ እያጠናከረ የሄደውን የሥለላና የአፈና መዋቅር፣ በመገናኛ ብዙሃን የሚያሰራጫቸውን ሕግን ያልተከተሉ እና በሽብር መንፈስ የተዋጡ መግለጫና ዘገባዎችን መመልከት በቂ ነው። በተለይም የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ የተቀሰቀሰው የሕዝብ ቁጣ ያስደነበረው የወያኔ መንግሥት ከላይ የጠቀስኳቸውን እና አጥብቆ የሚፈራቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ቀፍድዶ ለመያዝና እንቅስቃሴዎቻቸውን ለመገደብ ባወጣቸው የጸረ-ሽብር፣ የሲቪክ እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መተዳደሪያ፣ የፕሬስ እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ምዝገባ፣ የፀረ-ሙስና እና ሌሎች አዋጆች ሥርዓቱ የአፈና እና የመብት እረገጣ ተግባሩን ሕጋዊ ወደማድረግ ሂደት የተሸጋገረ መሆኑን ያሳያሉ። ፍጹም ሰላማዊ እና ሕጋዊ በሆነ መልኩ የመብት ጥያቄዎችን ባነሱ ዜጎች ላይ፤ አቅመ ደካሞችን እንኳን ሳይለይ ‘የፈሪ በትሩን’ ሲያሳርፍ በተደጋጋሚ ተስተውሏል።
ባለፉት ሃያ አመታት የአገዛዝ ሥርዓቱ የፈሪ በትሩን በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ አሳርፏል። ብዕርና ወረቀት በያዙ ከከፍተኛ ደረጃ ተማሪዎች እስከ አንደኛ ደረጃ ትመህርት ቤት ሕፃናት ጋር ሳይቀር በተደጋጋሚ ጊዜያት ተላትሟል። በርካቶችን ገድሏል፣ አስሮ አሰቃይቷል፣ ደብድቧል፣ ከትምህርት ገበታቸው ላይ አፈናቅሏል፣ ከአገር አሰድዷል፣ በሃሰት ወንጅሎ አስፈርዷል። በእምነት ቤቶች ውስጥ ገብቶ ከአማኞች፣ ከመንፈሳዊ አባቶች እና ይህን አለም ሸሽተው በገዳም ከከተሙ መነኮሳት ጋር ሳይቀር ተላትሟል። የኃይማኖት ተቋማት እንዲከፋፈሉና በገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ተሿሚዎች ቁጥጥር ስር እንዲወድቁ ተደርገዋል። ምእመናን በመስጊዶችና በቤተክርስቲያን ውስጥ እያሉ በታጠቁ ኃይሎች ተገድለዋል፣ ተደብድበዋል፣ ተዋርደዋል። ቀሳውስት ጥምጥማቸውን እንዲያወልቁ እና መስቀላቸውን እንዲጥሉ ተደርጎ በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ የማሰቃየት ተግባር ተፈጽሞቻቸውል። ኢማሞች ጺማቸው እየተጎተተ ተወስደው ተደብድበዋል፣ ታስረዋል። ይህ ሕዝብን የማዋረድ እና የማሸበር ተግባር የመነጨው እንደ እኔ እምነት የገዢው ኃይል እየተባባሰበት ከመጣው የፍርሃት እና የመሸበር ስሜት የተነሳ በራስ የመተማመን ስሜቱ እየተቦረቦረ በመሄዱ ነው። ዛሬ ሥርዓቱ የገዛ ጥላውንም የሚፈራበት፣ አባላቱ ላይ እንኳን እምነት ያጣበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ለእዚህም አንዱ ማሳያው በነጋ በጠባ ቁጥር ማቆሚያ በሌለው የግምገማ ስብሰባ አባላቱን ሲያስጨንቅ መታየቱ እና ለዚሁ የሚያባክነው ጌዜ እና የሕዝብ ገንዘብ፣ የባለሥልጣናት ተደጋጋሚ ሹም ሽር እና ከአገር ከድተው የሚወጡ ባለሥልጣናት እና የወያኔ አባላት ቁጥር መጨመሩ ነው።
ይህ የገዢው ኃይል የሕግን ልጓም በመበጣጠስ የፈረጠመ ክንዱን ይቀናቀኑኛል ባላቸው ግለሰቦች፣ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ኃይሎችና የሙያ ማኅበራትና አባላቶቻቸው ላይ ሁሉ ማሳረፉ ቀሪውን የኅብረተሰብ ክፍል ክፉኛ እንዲደነብርና በፍርሃት ቆፈን እንዲሸማቀቅ አድርጎታል። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብቶች መከበር፣ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች እና የሕግ የበላይነት መረጋገጥ የሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የዕለት ተዕለት ሕይወት የሚነካ ቢሆንም የጥቂቶች ጉዳይ ተደርጎ ተወስዷል። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ጥቂት የሲቪክ ማኅበራት፣ ጥቂት ጋዜጠኞች፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና በጠአት የሚቆጠሩ ግለሰቦ ብቻ ናቸው ባላቸው ውሱን ጉልበት እና አቅም ሲወያዩ፣ የምንግሥትን መጥፎ ተግባራት ሲቃወሙ፣ ለዜጎች መብት ሲሟገቱ እና ባደባባይ ሲጮሁ የሚስተዋለው።
በድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ መቆየት
ሌላው እና ትልቁ የፍርሃት ምንጭ በከፋ ድህነት ውስጥ ለረዥም ጊዜ እየማቀቁ መቆየት እና ድህነቱ ባስከተለው የስቃይ ህይወት አካላዊና መንፈሳው አቅም ተሸርሽሮ ክፉኛ መጎዳት እና መዳከም ነው። ሕዝብን በድህነት ውስጥ አምቆ በማቆየት ለሰው ልጅ ከሚገባው ክብር ወርዶና ከእንስሳ ያልተሻለ ሕይወት እንዲኖር በማድረግ ቅስሙን መስበር የአምባገነኖች አንዱ የሥልጣን እድሜአቸውን ማራዘሚያ ሥልት ነው። የድህነት ክፋቱ ኪስን ብቻ ሳይሆን የሚያራቁተው ክብርንም ጭምር ነው። አንድ ሰው በመንገድ ላይ ቆሞና እራሱን ከመጽዋቾቹ ሥር ዝቅ አድርጎ ቁራሽ ምግብ ወይም ቤሳ ሲለምንና ሲማጸን በኩራትና በደስታ ስሜት ውስጥ ሆኖ አይደለም። እያፈረ እና እየተሸማቀቀ በተሸናፊነትና በዝቅተኝነት ስሜት ውስጥ ሆኖ ነው። ይህ ክስተት በሙሉ ጤንነት እና በወጣትነት ወይም በጉልምስና እድሜ ላይ ባሉ ሰዎች ውስጥ ሲሆን ደግሞ ያለው የውስጥ ሕመም እና የሕሊና ቁስል እጅግ የከፋ ነው። የድህነት ክፋቱ ያፈሩትን ቅሪት ብቻ ሳይሆን የሚያሳጣው ወይም ኑሮን ለማሸነፍ የሚያስችል አቅምን ብቻ ሳይሆን የሚሸረሽረው መንፋሳዊ ወኔንም ጭምር ነው ከላያችን ገፎ የሚወስደው። ከሰውነት ደረጃ ላይ የሚያቆመንን መንፈሳዊ ልዕልና ካጣን በኋላ ቁሳዊ ድህነቱን ብናሸንፈው እንኳን መንፈሳዊ ድህነቱ ይከተለናል። እዚህ ላይ ለማሳሰብ የምወደው ነገር ድሃ ሁሉ ፈሪ ነው ወይም በፍርሃት ቆፈን የተተበተበ ነው የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይወሰድ ነው። በከፋ የኢኮኖሚ ድህነት ውስጥ እየኖሩ ክብራቸውን አስጠብቀውና እና በላቀ የመንፈሳዊ ወኔያቸው እራሳቸውንና አገራቸውን አስከብረው ያለፉ ድሃ አያት ቅድመ አያቶቻችንን ማሰብ የግድ ይላል። ዛሬም የገንዘብ እጦትና ድህነት ያላላሸዋቸውና መንፈሳዊ ልዕልናቸውን አስጠብቀው በክብር የሚሞቱ ወገኖች አሉን፤ ትቂቶች ቢሆኑም።
የዚህ ጽሁፍ ትኩረት ግን በቁሳዊውም ሆነ በመንፈሳዊ ማንነታቸው ውስጥ ድህነትና ፍርሃት ተረባርበው ወይም ከሁለቱ በአንዱ ተጠልፈው ስብእናቸው ፈተና ውስጥ የወደቀባቸውን ሰዎች የሚመለከት ነው። በተለይም በዚህ ግለኝነት በነገሠበት እና ገንዘብ በሚመለክበት የአለም ወቅታዊ ሁኔታ ውስጥ መናጢ ድሃ ሆኖ ለዘመናት መቆየት መዘዙ ብዙ ነው። ብዙዎች ከዚህ መቋጫው ከጠፋው የድህነት አረንቋ ለማምለጥ ስደትን አማራጭ አድርገው በተለያዩ አቅጣጫዎች አገሪቷን ለቀው ለአረብ አገራት ባርነት ተሰደዋል። ቀሪዎች ደግሞ የአገዛዝ ሥርዓቱ ሎሌ በመሆን ነፃነታቸው በቤሳ መሸቀጥን ቀጥለዋል። ለሁለቱም እድሉን ያጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ድሆች ደግሞ በየጎዳናው ላይ ተበትነው ዝናብ፣ ውርጭና ፀሃይ እየተፈራረቁባቸው የመጽዋቾቻቸው ደጅ ጠኞች ሆነዋል።
ከተወሰኑ አሥርት አመታት በፊት አንድ ሰው በድህነቱ ምክንያት እራሱንና ልጆቹ የትምህርት፣ የጤና አገልግሎት፣ መሰረታዊ የሆን አልባሳትና መጠለያ ጎጆ ባለቤት ለማድረግ የሚገጥመው ፈተና ቢኖርም ይህን ያህል የመረረ አልነበረም። ዜጎች በወር ከሁለት ብር አንስቶ እንደ የአቅማቸው የቀበሌ እና የኪራይ ቤቶችን ቤቶች ተከራይተው የመጠለያ ችግራቸውን ይቀርፉ ነበር። በአገሪቷ ውስጥ የነበሩ በርካታ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ከመመዝገቢያ ያልዘለለ አነስተኛ ገንዘብ እየተቀበሉ ተማሪዎችን በነጻ ያስተናግዱ ነበር። ብዙ ምሁራንንም አፍርተዋል። በየቀበሌው ከተደራጁ ጤና ጣቢያዎች አንስቶ በተለያዩ የመንግሥት ሆስፒታሎች ዜጎች በነፃና እጅግ ተመጣታኝ በሆነ ክፍያ ጥሩ ሕክምና የማግኘት እድል ነበራቸው። በአንድ ብር በሚገዛው አስር ትንንሽ ዳቦ ወላጆች ልጆቻቸውን አብልተው ያሳድሩ ነበር። ዛሬ አገሪቱ በልማት እየገስገሰች እንደሆነ በሚነገርበት በዚህ ወቅት ዜጎች በኑሮ ውድነትና ዋስትና ማጣት በጨለማ ህይወት ውስጥ እየተደናበሩ ይገኛሉ።
መንግሥት በኢኮኖሚውም፣ በፖለቲካውም ሆነ በሌሎች ኃይማኖታዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ያሻውን ቢያደርግ በሕዝብ በኩል መላሹ ዝምታ ሆኗል። አብዛኛው ሕዝብ ከተዘፈቀበት የድህነት አረንቋ ሳይወጣ በርካታ ነገሮች ተቀይረዋል። በመቶና በሁለት መቶ ይገዛ የነበር ጤፍ በሺዎች ሲያወጣ ምላሹ ዝምታ ሆኗል። ቲማቲም እንኳን ባቅሟ በኪሎ ከሁለት ብር ወደ ሃያ ብር ስትጠጋ አንዳንዴም ስትዘል ዝምታ፣ የቤት ኪራይ ከመቶዎች ወደ ሺዎች ሲንር ዝምታ፣ የነዳጅ ዋጋ በየጊዜው ሲያሻቅብ ዝምታ፣ የመብራት፣ የውሃ፣ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች በሰአታት፣ ከዚያም ለቀናት አንዳንዴም በተወሰኑ ቦታዎች ለሳምንታት ሲጠፉ ዝምታ፣ መነኮሳት እና አድባራት ሲዘረፉና ሲዋረዱ ዝምታ፣ መስጊዶች እና ኢማሞች ሲዋክቡና ሲታሰሩ ዝምታ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሲደበደቡ፣ ሲታሰሩና ሲሳደዱ ዝምታ፣ የንግዱ ማኅበረሰቡ ሲዋክብና ሲጉላላ ዝምታ፣ ገበሬዎች በማዳበሪያ እዳ ንብረታቸውን ሲነጠቁና ከዛም አልፎ ከትውልድ ትውልድ ያቆዩትን ይዞታቸውን እየተነጠቀ ለውጪ ቱጃሮች ሲቸበቸብ ዝምታ፣ ወንዶች ሚስቶቻቸውና ሴት ልጆቻቸው እፊታቸው ሲደፈሩና ሲጠቁ እያዩ ዝምታ፣ እናቶች ልጆቻቸውና ባሎቻቸው በየወጡበት ሲቀሩ እያዩ ዝምታ፣ በየከተማው የሚገኙ ነዋሪዎች ቤታቸ በላያቸው ላይ እንዲፈርስ እየተደረገ ከነልጆቻቸ በየሜዳው ተበትነው ይዞታቸው ለስግብግብ ባለሃብቶች ሲሰጥ ዝምታ፣ የሙያ ማኅበራት ሲጠቁ ዝምታ፣ መምህራኖች ሲዋከቡ ዝምታ፣ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው ‘በድህነት ቅነሳ እስትራቴጂ’ ስም ሲፈናቀሉና ለርሃብ ሲዳረጉ ዝምታ፣ ባለሥልጣናት የከፋ ሙስና ውስጥ ተዘፍቀው ሲንቦጫረቁ ዝምታ፣ ሕፃናት ሳይቀሩ በየአደባባዩ ግንባራቸው በጥይት እየተቦደሰ ሲረሸኑ ዝምታ፣ የአገሪቷ የትምህርት ሥርዓት ክፉኛ አቆልቁሎ ትውልድን ወደማክሰም ደረጃ ላይ ሲደርስ እየተመለከትን ዝምታ፣ መንግሥት ድህነትን ሸሽተው ከሃገር የሚሰደዱ ወጣቶችን መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችው እያለና ገንዘብ እየቃረመ ለዘመናዊው ባርነት እያዘጋጀ ፓስፖርት ሰጥቶ ሲያሰድድ ዝምታ፣ በየጎዳናው የወደቁ ሕፃናቶችን በጉዲፈቻ ስም መንግስት ለውጪ ዜጎች በብዙ ሺ ዶላር ሲቸበችብ እያየን ዝም፣ መንግስት የራሱን ሕገ-መንግስት እየናደ የፈቀደውን ሁሉ በዜጎች ላይ ሲፈጽም የህዝብ ምላሽ ዝምታ፣ ዝምታ፣ ዝምታ…..። ስንቱ ተጠቅሶ ይቻላል?
አንድ ሕዝብ ይህ ሁሉ ውርጅብኝ ያለፋታ ሲዥጎደጎድበት እና መገለጫ የሌልውን ግፍ እና ጭቆና በጫንቃው ላይ ሲጫንበት ውስጥ ውስጡን እያጉረመረመ፣ እያለቀሰና ልቡ እየደማ እንዴት ነህ ሲሉት ደህንነቱን ለመግለጽ ‘እግዚያብሄር/ አላህ ይመስገን’ እያለ የውሸት ሳቅ እየሳቀ እንዲኖር ያስገደደው ምንድን ነው? መንፈሱና አካሉ በቁሙ ተሸርሽረው እያለቁ ባልሞትኩም ባይነት የአያቶቹን ገድል በህሊናው እያመነዥከ በዘመኑ ለተጋረጡበት ፈተናዎች፤ በተለይም ድህነት፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጭቆዎችና በገዛ አገሩ ተዋርዶ መኖርን ለመሸሽ ስደትን ወይም ልመናን ወይም ሕሊናን ቀብሮ ለሥርዓቱ አገልጋይ መሆንን ከማን ተማረ? ይህ ጥልቅ የሆነው ዝምታችን የፍርሃት? ወይስ የትእግስት? ወይስ በፍርሃትና በትእግስተኛነት መካከል ሌላ ደሴት ወይም መንጠልጠያ ስፍራ አለ? እራሳችንን እንጠይቅ!
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት በኢትዮጵያዊያን ላይ እያሰፈነ ስላለው የፍርሃት ባህል ቀደም ሲል ባሰራጨሁት የዚህ ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል ውስጥ ባለሙያዎች በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ለፍርሃት ባህል መስፈን መንሰዔዎች ያሏቸውን ነጥቦች ዘርዝሬ ነበር። በክፍል አንድ ጽሑፌ መግቢያ ላይ እንደገለጽኩት ምንም እንኳን ፍርሃት የግለሰቦች ባህሪ መገለጫዎች መካከል አንዱ ቢሆንም የዚህ ጽሑፍ ትኩረት በወል የምንጋራቸውና በማኅበረሰብ ደረጃም በሚንጸባረቁት የፍርሃት ምልክቶች ላይ ብቻ ያተኮረ ነው። በመሆኑም በዚህ ክፍል ውስጥ የህሊና እና የአካል ቁስልን ባስከተሉ ትላንቶች ውስጥ ማለፍ የሚፈጥረውን የፍርሃት ቆፈንና የሚያስከትለውን መዘዝ በመቃኘት ፅሑፌን ልደምድም።
በአለማችን ታሪክ ከሰው ልጅ አዕምሮ ተፍቀው የማይወጡና እጅግ አሰቃቂ በመሆናቸው ሲታወሱ የሚኖሩ በርካታ ጦርነቶችና የእርስ በርስ እልቂቶች ተከስተዋል። የመጀመሪያውና የሁለተኛው የአለም ጦርነቶች፣ የኦሽዊትዝ ጭፍጨፋ፣ የአፓርታይድ የግፍ አገዛዝ፣ የሩዋንዳው የዘር ማጥፋት እልቂት፣ እንዲሁም በተለያዩ የአፍሪቃ እና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ውስጥ የተከሰቱትና የሚሊዪኖችን ሕይወት የቀጠፉት እልቂቶች በዋነኝነት ተጠቃሾች ናቸው። እነኚህ በክፉ ክስተትነታቸው በታሪክ የሚወሱት አጋጣሚዎች ካስከተሉት እልቆ መሳፍርት የሌለው ሰብአዊ ቀውስ እና የንብረት ውድመት ባሻገር ከትውልድ ትውልድ የሚወራረስ ትምህርትንም አስተምረው አልፈዋል። በተለይም የምዕራቡ አለም በራሱም ሆነ በርቀት በሌሎች ላይም የተፈጸሙትን እነዚህን መሰል መጥፎ ክስተቶች በአግባቡ በመመርመር፣ መረጃዎችን ሰብስቦና አደራጅቶ በማስቀመጥ፣ በመጽሐፍ ከትቦና እና በፊልም ቀርጾ በማኖር ቀጣዩ ትውልድ እነኚህን መሰል አደጋዎችን ከሚያስከትሉ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ፣ ኃይማኖታዊና ኢኮኖሚያው ቀውሶችና ቅራኔዎች እራሱን በማራቅ ችግሮችን እጅግ በሰለጠነና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲፈታ ማድረግ ችለዋል። ዛሬ ላይ ያለው ትውልዳቸውም እነ ናዚ እና ሌሎች አንባገነኖች በታሪካቸው ውስጥ ያደረሱትን ሰቆቃና ግፍ እያሰብ የሚሸማቀቅ ወይም በፍርሃት የሚርድ ሳይሆን ታሪክን በታሪክነቱ ትቶ ሙሉ አቅሙንና ጊዜውን ከሳይንስና ተክኖሎጂ ጋር አዋህዶ በዚህ ምድር ላይ ያሻውን ሁሉ ለማድረግ የሚያስችል አቅም በመገንባት ላይ ይገኛል።
ወደ አገራችን ስንመለስ ኢትዮጵያም ዛሬ ያለችበትን ጂዮግራፊያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ሌሎች ገጽታዎች ለመላበስ ያበቋት እጅግ በርካታ ክፉ እና በጎ ተበለው የሚጠቀሱ የታሪክ ክስተቶችን አስተናግዳለች። ምንም እንኳን ከላይ ከተጠቀሱት የአለማችን አሰቃቂ ታሪኮች ጋር ባይወዳደርም አገራችንም ከውጭ ወራሪዎች በተሰነዘረባት ጥቃትም ሆነ በልጆቿ መካከል በተከሰቱ የእርስ በእርስ ግጭቶች በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ውድ ልጆቿን አጥታለች። ድህነትን ጠራርጎ ሊያስወግድ ይችል ከነበረው አቅም በላይ በብዙ እጥፍ የሚገመት አንጡራ ሃብቷን በጦርነቶች፣ በግጭቶችና በዘራፊዎች ተነጥቃለች። ይህ እና ሌሎች በርካታ ምክንያቶችም ተደራርበው አገሪቱን ከድሃም ድሃ ተብለው ከሚጠቀሱት አገሮች ተርታ አሰልፈዋታል። እንግዲህ ትልቁ ጥያቄ እኛስ እንደ ሌላው ዓለም ሕዝብ አገራችን ካለፈችበት የረዥም ዘመን ታሪክ እና በየወቅቱ ከተከሰቱ መጥፎና በጎ የታሪክ ክስተቶች ምን ተማርን? ተምረንስ ለዛሬ እኛነታችን ምን አተረፍን? በአያቶቻችን እና በእኛ መካከል በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካ ተክለ አቋማችንም ሆነ አመለካከታችን ዙሪያ ለውጦች አሉ ወይ? ለውጣችን ቁልቁል ወይስ ካለፉት ወገኖቻችን የህይወት ተመክሮ ትምህርት ወስደን የደረስንበት የላቀ የአስተሳሰብና የኑሮ ደረጃ አለ? የታሪክ መዛግብቶቻችንስ ያለፉ ነገስታቶችን እና የጦር አበጋዞቻቸውን ከማወደስና ገድላቸውን ከመተረክ ባለፈ በቀጣዩ ትውልድ ሕይወት የጎላ ሚና ሊኖራቸ በሚችል መልኩ ተዘጋጅተዋል ወይ? ወይስ ‘እኔ የገሌ ዘር’ እያለ እንዲያዜምና በአያቶቹ ገድል እንዲያቅራራ ብቻ ተደርገው ነው የተዘከሩት? እንደ እኔ እምነት ከምዕራቡ አለም እኛንና ብዙዎች የአፍሪቃ አገራትን ከሚለዩን ነገሮች መካከል ጥቂቶቹ ከነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ የሚመነጩ ይመስለኛል።
የዛሬ መቶ እና ሁለት መቶ አመት በፊት የተፈጠሩ የታሪክ ክስተቶችን ፍጹም በተዛባ መልኩ እያጣቀስን ልክ የእኛ የልፋት ውጤት አስመስለን እስኪያልበን የምንፎክርና የምንጨፍር እኛ ነን። ታሪክን እና ጀግኖችን ማወደስ ተገቢ ቢሆንም የኛን ድርሻ እነሱን በማወደስ ብቻ ስንገታው አደጋ ላይ ይጥለናል። እንደ አያቶቻችን ታሪክን መስራት ሲያቅተን ታሪክ ሰሪዎችን በማውሳትና በዜማና በግጥም ማወደስ ብቻ ብንኮፈስ የዛሬውን ማንነታችንን አይሸፍነውም። ይህ በአያቶቻችን ታሪክ ውስጥ ተደብቀን ‘በኢትዮጵያዊነቴ እኮራለሁ’ እያሉ ማዜም፣ መፎከር፣ ማቅራራትና ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ዛሬ ከተጣቡን የድህነት፣ የፖለቲካ ጭቆና እና ማኅበራዊ ቀውስ የማያስጥለን እና ነፃ የማያወጣን እሰከ ሆነ ድረስ ኩራታችን ከድንፋታ አያልፍም። አገሬን እወዳልሁ፣ በኢትዮጵያዊነቴ እኮራለሁ እያሉ ባንዲራ ለብሶ ማቅራራት በተግባር ካልታገዘ የውሸት ወይም ባዶ ኩራት (false pride) ነው የሚሆነው። እውነተኛ ኩራት የሚመነጨው ከራስ ነው፤ የራስን ማንነትን በማወቅና በመቀበል ላይ የሚመሰረት ነው። ማንነትን አምኖ መቀበል አቅማችንንም አብረን እንድፈትሽ ይረዳል። የዛሬ ባዶነታችንን በአያቶቻችን የታሪክ ገድል እንድንሞላ ወደሚያስገድድ የሞራል ክስረት ውስጥም እንዳንገባ ይረዳናል። የዛሬ ውርደታችንን በአድዋ ድል እና በሌሎች የአያቶቻችን ተጋድሎዎች በተገኙ ስኬቶችን ልንሸፍነው ከመጣር ይልቅ ታሪክ እንድንሰራ ብርታት ይሆነናል።
በሌላ በኩል የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ያሳቀፉንን የዘረኝነት መርዝ እያራባን በታሪክ ተፈጽመዋል የተባሉ አንዳንድ ክስተቶችን እየመነዘርን ‘ያንተ ቅም ቅም አያትህ የእኔን ቅም ቅም አይታቶች በድሎ ነበር፤ ስለዚህ በቅም ቅም አያቶቼ ላይ ያንተ ዘሮች ላደረሱት በደል ኃላፊነቱን አንተ ትወስዳለህ እያልን ድርጊቱን ዛሬ ላይ እንደተፈጠረ በመቁጠር የምንጋጭና ለመነጣጠል እንቅልፍ አጥተን የምናድርም አለን። እራስን እንደተበዳይ ሌላውን የኅብረተሰብ ክፍል እንደ በዳይ በመቁጥርና የተዛባን ታሪክ በመተንተን ለዛሬው በዘረኝነት መርዝ ለተለወሰው የፖለቲካ አጀንዳቸው ማሳኪያነት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ካፈር የሚለውሱ ኢትዮጵያዊያኖችም (እነሱ ኢትዮጵያዊ አይደለንም ቢሉም) ልብ ሊገዙ ይገባል። በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ጎሣዎች በገዛ አገራቸው እኩል መብትና ጥቅም እንዲረጋገጥላቸውና የሁሉም አገር እንድትሆን ከመጣር ይልቅ በዘረኝነት ስሜት ውስጥ ተወጥሮ ኢትዮጵያዊነትን መካድና ከራስ ጎሣ ውጭ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል እንደ ጠላት መቁጠር መዘዙ ብዙ ነው። ይህን ለመረዳት ብዙ ምርምር አያስፈልገውም። በቅርባችን ካለችው ከሩዋንዳ ትምህርት መውሰድ ይቻላል። ይህን የዘረኝነት እሳት እየተቀባበሉ የፖለቲካ መታገያቸው ያደረጉ ኃይሎችም ከዚህ እኩይ ተግባራቸው እንዲታቀቡ በስሙ የሚነግዱበት ሕዝብ ሊያወግዛቸው ይገባል።
እርቀን ሳንሄድ የቅርብ ጊዜ ታሪካችንን እንኳን ብንፈትሽ ዛሬ ለምንገኝባቸው እጅግ ውስብስብ እና ፈታኝ ችግሮች መንስዔ የሆኑትን ነገሮች በቀላሉ ልንገነዘብ እንችላለን። የችግሮቻችንን ምንጮች እና ያስከተሉብንን መዘዝ በቅጡ መረዳት ከቻልን ከተዘፈቅንበት አረንቋ ውስጥ ለመውጣት ጊዜ ላይወስድብ ይችላል። መወጣጫውም ላይርቀን ይችላል። ትልቁ ጥያቄ ችግሮቻችንን ከመዘርዘር ባለፈ ምንስዔዎቻቸውንም በቅጡ ተረድተነዋል ወይ? እንደ አንድ አገር ሕዝብ በችግሮቻችን እና በችግሮቹ ምንጭ ዙሪያ የጠራ የጋራ ግንዛቤ አለን ወይ? በፖለቲካ እና በሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ስንደራጅስ ከነዚህ ግንዛቤዎች ተነስተን ነው ወይ? የጋራ የሆኑ ችግሮች ሰዎችን ያስባስባሉ፣ ለድርጅቶች መፈጠርም መንስዔ ይሆናሉ፣ ችግሮቹንም ለመቋቋም እና ለማስወገድ “ከአንድ ብርቱ …” እንደሚባለው ኃይልን ይፈጥራሉ። ይሁንና ስብስቡ ወይም የተደራጀው ኃይል ፊት ለፊት ከተጋረጡት ችግሮች ጋር ከመፋለም ባለፈ በድጋሚ እንዳይከሰቱ ምንጮቻቸውን ለማድረቅ የሚያስችል እይታ ከሌለው እና አቅሙንም በዚያ ደረጃ ካላሳደገ ይህ አይነቱ ማኅበረሰብ ሁሌም ለተመሳሳይ አደጋዎች የተጋለጥ ነው። የችግሩን መንሰዔ አጥንቶ ምንጩን ለማንጠፍ ከሚያወጣው ጉልበት፣ ገንዘብና ጊዜ የበለጠ አዳዲስ ችግሮች በተከሰቱ ቁጥር ከተኛበት እየባነነ ተነስቶ ችግሮቹን ለመቋቋም የሚያስችሉ ድርጅቶችን ለመፍጠርና ለማፍረስ የሚያወጣው ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት እጅግ የላቀ ነው። በእንዲህ አይነት ማኅበረሰብ ውስጥ ጠንካራ የሆኑና ልምድ ያካበቱ ድርጅቶችን መፍጠር አይቻልም። ብዙዎቹ ድርጅቶች ሳይጎረምሱ፣ ሳይጎለምሱ እና ሳያረጁ በጨቅላነታቸው ይሞታሉ ወይም ደንዝዘው ስማቸውን ብቻ ይዘው ይቀራሉ። ይህ አይነቱ ማህበረሰብ አውራ የሚሆኑና በምሳሌነት ሊጠቀሱ የሚችሉም የፖለቲካ፣ የኃይማኖት እና የማኅበራዊ ህይወት መሪዎችን የመፍጠር አቅም የለውም፤ አይፈጥርምም፤ በራሳቸው ጥረት ቢፈጠሩም ጎልተው እንዲታዩ እድሉን አይሰጥም። ትላንት ያነገሳቸውን በማግስቱ አፈር ከድሜ ሲደባልቃቸው ምንም አመክንዮ አይፈልግም። ሲያከብርም፣ ሲሾምም፣ ሲያዋርድም ሆነ ሲኮንን በስሜት ነው። በተለይም እንደኛ በብዙ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ተተብትቦ ግራ ለተጋባ ማኅበረሰብ ልምድና በእውቀት የጎለበቱና የሕዝብ አመኔታን ያገኙ ባለ ዕራይ ድርጅቶችና ግለሰቦች መኖር እጅግ ወሳኝ ነው።
የፖለቲካም ሆነ ሌሎች ልዩነቶቻችንን የምንይዝበት መንገድ ሊፈተሽ ይገባዋል። የቀዝቃዛው የአለም ጦርነት ማብቂያን ተከትሎ የፈረሰውና ጀርመንን ለሁለት ከፍሏት የነበረው ግንብ ሲናድ ምስራቅና ምዕራቡን ወደ አንድ አገር ከመለወጥ ባለፈ መላው አውሮፓን አንድ ያደረገ ክስተትን ፈጥሯል። የሰብአዊ መብቶች እና የዲሞክራሲ ጽንሰ ሃሳቦች የልዩነት ማጦዣ ምክንያቶች ከመሆን ወጥተው ጀርመንን ብቻ ሳይሆን አውሮፓን ያዋሃዱ ተጨባጭ እውነታዎችን ፈጥረዋል። ይህን ተከትሎም ከታሪክ ለመማር ዝግጁ በሆኑ በበርካታ የአለማችን አገራት በመሬት የተገነቡም ሆነ በሰዎች አዕምሮ ውስጥ የተካቡ የልዩነት ግንቦች ሁሉ ፈርሰው ዜጎች ለጋራ ራዕይ በጋራ የመቆም ጽናትን አሳይተዋል። ሕዝባቸውንም ነጻ አውጥተዋል። ሌሎች እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የተለያዩ አገሮች (አብላጫዎቹ የአፍሪቃ አገራት) የልዩነቶቻቸውን ግንቦች አጠንክረውና አዳዲስ ግንቦችን በአይምሯቸው ውስጥም ገንብተው የተሰበጣጠረና የሚፈራራ የኅብረተሰብ ክፍልን በመፍጠር ጉዞዋቸውን ቀጥለዋል። የጎሣ ግንቦች፣ የሥልጣን ግንቦች፣ የኃይማኖት ልዩነት ግንቦች፣ የድሃና የሃብታም ግንቦች፣ የጨቋንና የተጭቋኝ ግንቦች፣ ሌሎች ማኅበረሰቡን በአንድ ላይ እንዳይቆም እና ድህነትና አንባገነንነትን አሽቀንጥሮ እንዳይጥል አቅም የሚያሳጡ በርካታ የልዩነት ግንቦች ተገንብተዋል።
ድርጅቶችን እና መሪ የሚሆኑ ግለሰቦችን እየፈጠርንና መልሰን እየደፈጠጥን የመጣንበትን የ50 ዓመታት የፖለቲካ ጉዞ ወደ ኋላ መለስ ብለን ብንቃኝ ይህንን እውነታ ያረጋግጥልናል። ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ለቁጥር የሚታክቱ የፖለቲካ፣ የሙያና በማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮሩ ድርጅቶች ተፈጥረው ብዙዎች ካለሙበት ሳይደርሱ ከስመዋል። ጥቂቶችም ባልሞት ባይ ተጋዳይነት በመኖርና ባለመኖር መካከል ሆነው ቀጥለዋል። በከሰሙትም እግር ሌሎች በርካቶች ተተክተው በተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ ወድቀው የኅብረተሰቡን ቀልብ ለመሳብ ደፋ ቀና ሲሉ ይስተዋላል። እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው በዚህ ዘመን ውስጥ ብቅ ብለው በከሰሙትም፣ ተውተርትረው ቆይተው በተዳከሙትም፣ አዳዲስ ስም እየያዙ በተፈጠሩትም ድርጅቶች ውስጥ ዋነኛ ተዋናዮቹና የድርጅቶቹ ፈጣሪዎችም ሆኑ አጥፊዎቹ አንድ አይነት ሰዎች መሆናቸው ነው። ትላንት በአንድ ድርጅት ጥላ ስር ሆነው ሌሎችን እንደ ጠላት ይፈርጁ የነበሩ ሰዎች ዛሬ የብዙ ድርጅቶች ፈጣሪዎች ሆነዋል። ትላንት በጠላትነት የሚፈራረጁ ድርጅቶች አባል የነበሩ ሰዎች ቂማቸውን እንዳረገዙ ዛሬ በአንድ ድርጅት ጥላ ሥር የተሰባሰቡበትንም ሁኔታ እናያለን። በድርጅቶቹ መካከል እጅግ ጠባብ የሆኑ የርዕዮታለም ልዩነቶች ከመኖራቸው ውጭ አብዛኛዎቹ የመጨረሻ ግባቸው አንድ እና አንድ ነው። ዲሞክራሲ የሰፈነባት፣ የሕግ ልዕልና የተረጋገጠባት፣ ሰብአዊ መብቶች የተከበሩባት እና ድህነትን ያሸነፈች ኢትዮጵያን ማየት፣ መፍጠር ነው። በነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የሚለያዩ ድርጅቶች ያሉ አይመስለኝም፤ ሊኖርም አይችልም። ልዩነቱ እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ ድርጅቶቹ በሚከተሉት አቅጣጫና መንገድ ቅየሳ ላይ ነው።
በዚህ የ50 ዓመት ጉዞ ውስጥ በሽብር መንፈስና በነውጥ ተግባራት የተሞላው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በድርጅቶች መካከል እርስ በርስ አለመተማመንንና መካካድን ፈጥሯል። ይህም አለመግባባቶቹ ከጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት አልፈው እልቂትን አስከትለዋል። በዚያም የተነሳ አገሪቷ በፍርሃት እንድትዋጥና ሕዝቧም በስጋት እንዲኖር፤ የፍርሃት ባህልም እንዲጎለብት ከፍ ያለ ሚና ተጫውቷል። ዛሬ በእያንዳንዳችን አዕምሮ ውስጥ በርካታ የልዩነት ግንቦች ተፈጥረዋል። በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በሲቪክ ማኅበራት፣ በኃይማኖት ተቋማት፣ በማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከልም የበርሊን ግንብ አይነት ግዙፍ የልዩነት ግንቦች ተፈጥረዋል። የዛሬዎቹ ኃይሎች ከገዢው ፓርቲ በስተቀር በትጥቅ የተደራጁ ስላልሆኑ ነው እንጂ ለመጠፋፋት ቅርብ ናቸው። ትልቁና እያንዳንዳችን እራሳችንን ልንጠይቅ የሚገባን፤ እነዚህን ግንቦች ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዴት ንደን እና በላያቸው ላይ ተረማምደን ልብ ለልብ እንዋሃዳልን? እንዴት እንደ አንድ ሕዝብ የጋራ ዕራይ፣ የጋራ መዝሙር፣ የጋራ ህልም፣ የጋራ መፈክር፣ የጋራ መድረክና የጋራ አገር እንፈጥራለን? እንዴት ከቂም፣ ከበቀልና ከቁርሾ ሽረን ከታይታና ከቧልት ፖለቲካ ወደ እውነተኛ የፖለቲካ ሕይወት እንመለሳለን?
ለማጠቃለል ያህል በእኔ እምነት ከተተበተብንበት ውስብስብ ችግሮችና ከተጫነን የፍርሃት ድባብ ለመላቀቅ፤ አልፎም ጤናማ የሆነ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሥርዓት ባለቤት የሆነ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚከተሉት ተግዳሮቶች ቢቀድሙ ይበጃል እላለሁ::
- ዛሬ ለፖለቲካ ንትርክና እርስ በርስ መፈራራት እንደ ምክንያት የሚነሱት የታሪካችን ክፍሎች ከፖለቲካ፣ ከኃይማኖት እና ከሌሎች ወገንተኝነት ነጻ በሆኑ ምሁራን በአግባቡ የሚጠኑበት ማዕከል ቢኖረን። የመወዛገቢያ ነጥብ የሆኑትም ታሪካዊ ኩነቶችን በአግባቡ ቢጠኑ እና በተለያዩ መንገዶችም ተደግፈው ለማስተማሪያነት ቢውሉ በድንቁርና ላይ ከተመሰረቱት ታሪክ ጠቀስ የሆኑና በጥላቻ መንፈስ የተሞሉ ክርክሮች ወጥተን እውቀትን በዋጁ ውይይቶች ላይ እናተኩራልን።
- የሩቁን ለታሪክ ምሁራን እንተወና ባለፉት አምሣ ዓመታት ከ1960 ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ በፖለቲካ ትግል ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑ ኃይሎች ዛሬም በአገሪቷ የለት ተዕለት የፖለቲካ ህይወት ውስጥ በግራና በቀኝ ሆነው እና በመቶ ድርጅቶች ጉያ ውስጥ መሽገው በአገሪቷና በድሃው ሕዝብ እጣፈንታ ላይ ወሳኞች ሆነው ቀጥለዋል። በተለይም ‘ያ ትውልድ’ በሚል የሚታወቀው የኅብረተሰብ ክፍል ከልጅነት እስከ አዋቂነት ክቡር ሕይወቱን፣ ጊዜውን፣ ገንዘቡን እና እውቀቱን ያለምንም ስስት የዛችን አገር እጣ ፈንታ ለማቅናት መስዋዕትነት ሲከፍል ቆይቷል፤ ዛሬም ዋነኛ ተዋናይና አድራጊ ፈጣሪ ሆኖ ቀጥሏል። ይህ ትውልድ ትላንትናም ሆነ ዛሬ በገዢና በነጻ አውጪዎቻች ቡድኖች ተፈራርጆ እርስ በርሱ ተጨራርሷል፣ ቂምና ቁርሾም ተጋብቷል፣ ተሰዷል አሰድዷል። ዛሬም በልቡ ቂም ይዞና በቀልን አርግዞ በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ መሽጎ የጎሪጥ ይተያያል። ባገኘው አጋጣሚም ሆሉ ይናቆራል። ‘ቂም ተይዞ ጉዞ’ እንዲሉ ትላንት በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ሆነው በጠላትነት ይፈራረጁና ሊገዳደሉ ይፍላለጉ የነበሩ ሰዎች ይህን ሸክማቸውን በንስሃ እና በይቅር ባይነት ከላያቸው ላይ ሳያራግፉ ውስጥ ውስጡን እየተብሰከሰኩና እየተፈራሩ ገሚሶቹ በልጅነታቸው በቆረቡባቸው ድርጅቶች እየማሉ ቀሪዎቹም ዘመኑ በወለዳቸው አዳዲስ ድርጅቶች ውስጥ ሆነው የለበጣ ውህደት እየመሰረቱ በዋዜማው ይፈረካከሳሉ። እንደ እኔ እምነት ከዚህ የእርስ በርስ መፈራረጅ፣ መፈራራትና የቆየ ቂምና ጥላቻ ሳንሽር የምንክበው ካብ ሁሉ የእምቧ ካብ ነው የሚሆነው። እየሆነ ያለውም ይሄው ነው። ከዚህ አዙሪት ወጥተንና ከቂም ተላቀን የጋራ ራዕይ እንዲኖረን እያንዳንዱ ግለሰብ እራሱን ለይቅርታ ማዘጋጀት አለበት። ከልብ የበደላቸውን ይቅርታ ለመጠየቅና ይቅርታ ለመቀበል። ከድርጅታዊ ወገንተኝነትም እራሱን ነጻ አውጥቶ በሱና በድርጅቱ ላይ የተፈጸመውን በደል ብቻ ሳይሆን እሱም ጠላት ብሎ በፈረጃቸው ሰዎችና ድርጅቶች ላይ ያደረሰውን ግፍና በደል ለመናዘዝና ለደረሰውም ሁሉ አቀፍ ጥፋት ድርሻቸውን በድፍረት በማንሳት የተጠታቂነት ባህልን ‘ሀ’ ብለው ሊጀምር ይገባዋል።
- ይህ ሁኔታም የደረሰውን የጉዳት መጠን በቅጡ እንድናውቅ ከማድረጉም ባሻገር እርስ በርስ የመወነጃጀሉን ታሪክ እንድንገታውና ልባችንንም በፖለቲካ ንስሃ አንጽተን የሚነገርለትን ያህል የተሳካ ባይሆንም እንኳ ልክ እንደ ደቡብ አፍሪቃው ‘በእውነት’ ላይ ወደ ተመሰረተ የእርቅ እና የሰላም መድረክ እንድቀርብ እድል ይፈጥርልናል።
- የልጆቹን እርስ በርስ መጨራረስ እየተመለከት ፓለቲካ እንዲህ ከሆነ አርፎ መቀመጥ ይበጃል፤ እርም የፖለቲካ ነገር በሚል አይምሮውን ጥርቅም አድርጎ ዘግቶ የለት ጉርሱን ብቻ እየቃረመ የአገሩን የፖለቲካ እጣፈንታ ለእዝጌሩ ትቶ ደግ ቀንና መልካም አስተዳደርን እንደመና ከሰማይ እንዲወርድለት የሚጠባበቀውም የኅብረተሰብ ክፍል አይኑን ይገልጣል፤ ከመጠፋፋት ወደ ሰለጠነ የውይይት ባህል በሚሻገረው የፓለቲካ ኃይልም ላይ እምነት ያሳድራል፤ እራሱንም ከፍርሃት ነጻ አውጥቶ በሙሉ ልብ በአገሩ ጉዳይ ባለቤት ይሆናል።
- ስለዚህም የገዢው ኃይል ወያኔ ካለበት ጥልቅ ፍርሃት እና የሥልጣን ጥም የተነሳ ለእንዲህ ያለው ለውጥም ሆነ የሰላምና የእርቅ ጎዳና ገና ዝግጁ ባይሆንም የተቀሩት የፖለቲካ ሃይሎች መንገዱን በመጀመር ለዘመናት በመካከላቸው የቆየውን ቁርሾና ቂም ከአዕምሯቸው በማውጣት ከልብ የመነጨ እርቅ በማድረግ የልዩነት ግንቦችን ማፈራረስ ይጠበቅባቸውል። የሰላም፣ የእርቅ እና የእውነት አፈላላፉ ጉባዔ ያስፈልገናል።
በእውነት ላይ ተመስርተው ተቃዋሚዎች በቅል ልቦና ከታረቁ አብረው ከሠሩ በኢትዮጵያዊና በኢትዮጵያዊያን ላይ ለዘመናት እንደ መዥገር ተጣብቀው ደማችንን የሚመጡትን፣ ክብራችንን ገፈው እርቃን ያስቀሩንን፤ ድኅነት፣ እርዛት፣ አንባገነናዊ ሥርዓትና ጭቆና፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ ጦርነትና የእርስ በርስ ግጭቶች፣ ድንቁርና፣ ጨለምተኝነት፣ ፍርሃት፣ ሙስና እና ጥላቻን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ነቅለን መጣል እንችላለን። ቅን ልቦና ይኑረን! ለዘመናት የተጫነንን ሸክማችንንም እናራግፍ። ያኔ ለፍቅር በፍቅር፣ ለሰላም በሰላም፣ ለነጻነት በነጻነት፣ ለአንድነታችን በአንድነት የምንሰራበትና ታሪክ ዘካሪ ብቻ ሳንሆን ታሪክ ሰሪ የምንሆንበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም።
ቸር እንሰንብት!
ያሬድ ኃይለማርያም ከብራስልስ
Leave a Reply