• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

የተመሠቃቀለውን የፖለቲካ ውጥንቅጣችንና ነፃነታችን።

December 30, 2012 04:26 am by Editor Leave a Comment

በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የወያኔን ቡድን ከሥልጣን ለማውረድ የሚደረገው ትግል አሁንም ቀጥሏል። ይህ ትግል አንድነት የለውም። ይህ ትግል አንድ ማዕከል የለውም። ይህ ትግል አንድ መሪ የለውም። ያለንበትን መርምረን ወደፊት እንዴት እንደምንሄድ መወያየት አለብን። ለዚህ ይረዳ ዘንድ፤ በኔ በኩል መደረግ አለባቸው የምላቸውን እጠቁማለሁ። ይቺ ሀገር ያንቺም፣ ያንተም፣ የነሱም፣ የኛም የሁላችን የኢትዮጵያዊያን ሀገር ናት። ስለሆነም ሁላችንም ለወደፊቷ እኩል ባለጉዳዮች ነን። ማንም የነገዋን ሀገራችን እድል ሲወስን፤ እኛ የበይ ተመልካች መሆን አይገባንም። “ከወያኔ የተሻለ እስከመጣ ድረስ እኔ ምን ቸገረኝ!” ብለን ለሌሎች ጉዳዩን የምንተወው ሊሆንም አይገባም። አዎ የሚሻል ይኖራል። ያባሰም አለ። የሚሻለውም ሆነ የባሰው ሲመጣ የራሱን አጀንዳ ይዞ ስለሆነ የሚመጣው፤ እኛም ሆነ የሀገራችን ጉዳይ በሌሎች አጀንዳ ይያዛል ብለን ማለም የዋህነት ነው። ማንኛውም ድርጅት የራሱን አጀንዳ አራማጅ መሆኑ፤ የፖለቲካ ድርጅት የሕልውና መሠረታዊ ሀ ሁ ነው። ታጋዮች ሆነው ጦራቸውን የማይቀስሩትም ቢሆኑ፤ ሀገራቸውን ነፃ ሊያወጣ የተነሣ ድርጅትን መመርመርና ማወቅ ግዴታ አለባቸው።

ወያኔን የሚቃወሙ በየመልኩና በየቦታው መኖራቸው ግልፅ ነው። እነኚህ ድርጅቶች በሙሉ፤ እያንዳንዳቸው የተነሱበትና አንዱ ከሌላው የሚለይበት፤ የየራሳቸው አጀንዳ አሉዋቸው። አንድ ሀገራዊ አጀንዳ ቢኖራቸውና ሁሉም እኩል ለሀገራቸው የተነሱ ቢሆኑ ኖሮ፤ በተለያየ ወቅትና በተለያይ ቦታ ቢፈጠሩም፤ በመሰባሰብ አንድ ድርጅት ብቻ በመሠረቱ ነበር። ስለዚህ የተለያየ አጀንዳ እንዳላቸው መቀበሉ ግዴታ ነው። የተለያየ አጀንዳ ስላላቸው ደግሞ፤ የተለያየ ውጤትን ፈላጊ መሆናቸው የተጠበቀ ነው። ልዩነታቸው በጥቃቅን ጉዳዮች ከሆነ፤ በተወሰነ ደረጃ እነኚህን ልዩነቶች አጣጥመው፤ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመስማማት፤ አንድ ግንባር ፈጥረው፤ ትግሉን በኅብረት ያካሂዱ ነበር። ይህ እስካሁን አልተደረገም። ለወደፊቱ አይደረግም የሚል ተስፋ አስቆራጭ እምነት የለኝም። ለወደፊቱ ያለኝ ምኞት ከፍ ያለ ነው። በአሁኑ ጊዜ የጠራ ብርሃን አይታየኝም። ሆኖም እኔ ይኼን አቋም ብይዝም፤ ሌሎች ይኼን ይቀበላሉ ማለት አልችልም።

ባሁኑ ሰዓት ትግሉ ወደፊት እንዳይገፋ የሚፈታተኑት ጥቂት ጉዳዮች አሉ። እኒህ መሠረታዊ የእምነትና የአመለካካት ጉዳዮች ናቸው። እኒህ የእምነትና የአመለካከት ጉዳዮች ደግሞ፤ ለመቀራረብና ጉልበት ያለው ኃይል ለማሰባሰብ አስቸጋሪ እንቅፋት ሆነውብናል። ታዲያ ብዙዎች ያልተሰባሰቡበትና የጠራ የአመለካከት አንድነት ያልተፈጠረበት ትግል፤ አድሮ መበታተንን ያስከትላል። ይኼን ደግሞ ላለፉት አርባና ሃምሳ ዓመታት ታሪካችን አስታቅፈን፤ ባዲስ ምዕራፍ ወደፊት መሄድ አለብን።

ባሁን ሰዓት የወያኔ ቡድን በሚያካሂደው ወያኔያዊ ግዛታዊ አስተዳደር፤ ሀገራችን ብዙ ችግሮች ገጥመዋታል። በወያኔ እስር ቤቶች የታጎሩት ኢትዮጵያዊያን፣ የተዛባዉ አስተዳደራዊ ልማት፣ የሠራዊቱ አወቃቀርና የሥልጣን አመዳደብ፣ የብሔር ብሔሮች ጥያቄ፣ የነፃ አውጭዎች ጋጋታ፣ የውጭ መሬት ተቀራማጮች እውነታ፣ የደንበሩ መሠጠት፣ የኤርትራ ጉዳይ፣ የወያኔ ሥልጣናትና ከሕዝብ የዘረፉት ንብረት፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ የተባረሩት አማራዎችና የተገደሉባቸው ዘመዶቻቸው፣ በዓለም የተበተነው ስደተኛ ኢትዮጵያዊና ሀገራዊ ጥማቱ፣ ወያኔ በመሸጥ ላይ ያለው የሕፃናት ዓለም አቀፋዊ ብተና፣ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚሰቃዩት እህቶቻችን፣ ወዘተ. . . ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሠጣቸው መልሶች፤ ያስተባብሩናል ወይንም ያለያዩናል። ከዚህ ተነስተን ደግሞ፤ ጠንካራ ድርጅት ሊመሠረት የሚቻልበትን መንገድ በኅብረት እናበጃለን።

አንድ ነገር ግልፅ ነው። የወያኔው ቡድን በምንም መንገድ ሥልጣን ለቆና በሕዝብ ድምፅ ተገዝቶ ሀገራችንን በሰላም ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ይመራታል ብሎ የሚያልም፤ ከንቅልፉ ያልነቃ ነውና መቀስቀስ አለበት። ይህን በአሁን ሰዓት ያልተገነዘበ ኢትዮጵያዊ አለ ብሎ መቀበል ያስቸግረኛል። ከወያኔ የራቁ መስለው የሚንቀሳቀሱ የግል ጥቅማቸው ከሀገራቸው ሕልውና የበለጠባቸው አስመሳዮች በርግጥ ሊቀላምዱ ይችላሉ። ከዚህ በተረፈ ግን፤ ሁላችንም ወያኔ ካልተገፋ አይወድቅም በሚለው ብንስማማም፤ እንዴት በሚለው ላይ ውይይት አላደረግንበትም። ታዲያ አንድ ወገን ኃላፊነቱን ጨብጦ፤ እርምጃ ለመውሰድ ቢነሣ፤ ይህ ጉዳይ የሁላችንንም ነገ ወሳኝ ስለሆነ ያገባኛል ማለት አለብን። አንድ ሠራዊት ተመሠረተ ሲባል፤ ማን መሠረተው? አጀንዳው ምንድን ነው? እቅዱ ምንድን ነው? ብለን መጠየቅ ግዴታችን ነው። እንዲያው ቀድሟልና እንከተለው ወይንም እንደግፈው ማለቱ የዋህነት ነው። ወያኔን እናውድም የሚለው ባዶ ቃል ብቻ የትም አያስኬድም። የሃምሳ ዓመታት የትግል ትምህርታችንን ገደል አንክተተው። ሕዝብን ነፃ አውጥቶ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የሚመሠርት ሠራዊት፤ ከሀገራዊ ውይይቱ የመነጨ ይሆናል። ሕዝብን ነፃ አውጥቶ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የሚመሠርት ሠራዊት፤ በሕዝባዊና ሀገራዊ ሁሉን አቀፍ ድርጅት ይመራል። በግትርነትና በምኞት ሀገር አቀፍ ትግል አይካሄድም።

ይኼን ትግል አንዳንዶች የትግሬዎችና የቀሪዎቹ ኢትዮጵያዊያን ጠብ አድርገው ያዩታል። ሌሎች ደግሞ የነፃ አውጪዎችና የሀገር ወዳዶች አድርገው ያዩታል። ቀሪዎች ደግሞ ከውጭ ሀገር ባነበቡትና ባገኙት ተመክሮዎች አጣብቀው ትርጉም ሊሠጡት ይፈልጋሉ። የተወሰነው ክፍል ደግሞ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና የኢትዮጵያዊያን የጨቋኝና ተጨቋኝ አድርገው ያቀርቡታል። ከሀገራችን የምጣኔ ሀብት ሥምሪትም አንፃር የሚመለከቱትና፤ የሀገራችን ሀብት በአንድ ቡድን ተጠፍርቆ መያዙና ለመመዝበሪያ መንገዱ የሆነውንም ሥልጣን ጨምድደው መያዛቸው ያስቆጣቸው አሉ። ወያኔ የሠጣቸውን ተቀብለው ሌላም ይገባናል፤ አንሦናል ባዮችም አሉ። ጥያቄው፤ የጠመንጃ አንሽዎቹ መሠረት የት ላይ ነው የወደቀው? ነው።

እጃችንን አጣጥፈን እንቀመጥ የሚሉ ካሉ የተሣሣቱ ናቸው። ለመፍትሔው፤ ሕዝብ፣ ሕዝብ ስልም፤ ሕዝቡ እንደሚነሳ፤ እምነት ስላለኝ ነው። አንዳንዶቻችን ታዲያ ሕዝቡ ለምን አይነሳም? የምንል አለን። እስኪ ረጋ ብለን ራሳችንን እንጠይቅ! ማነው ከመካከላችን በሕዝቡ መካከል ገብቶ፣ ችግራቸውን አብሮ ተካፍሎ፣ ከሕዝቡ ጋር ሆኖ መፍትሔ ምንድን ነው? የሚለውን ከሕዝቡ ተምሮ፤ ቅመሙን ይዞልን የመጣ? ይኼ አዎ! ድካምን ይጠይቃል። ታዲያ የሕዝብ ትግል ማለት፤ አድካሚ፣ ትዕግሥትን አስጨራሽና ሕዝቡ ማዕከል የሆነበት ማለት አይደለም እንዴ? ወይንስ ነፃ አጭዎቹ ከውጭ እስክንመጣለት ሕዝቡ እየጠበቀን ነው የሚለውን፤ እኛ አቡክተን እኛው ጋግረን ያስቀመጥነውን እንጀራ እየበላን ነው?

“የጦር ቡድን ተመስርቶ አንድ ከተማ ቢይዝ፤ ወታደሩ ተገልብጦ ወደኛ ይመጣል” የሚል ዜማ ይሰማል። ከተኛንበት እንንቃ። ትግሉን እንደጋቢ ከላይ ላይ ደርበን እንሂድ ቢባል፤ ሲሞቅና ሲበርድ የሚለበስና የሚጣል የውጭ አካል ይሆናል። ትግሉ የሚሳካው፤ ትግሉን ሕይወት ብለው ሲይዙትና ከሰውነት አዋኅደው፤ ትግሉን ሲሆኑት ነው። በአንድ ነፃ አውጪ ድርጅት ጠመንጃ ነፃነት የሚመጣበትን መንገድ ሳስበው፤ ሰውነቴ ይጨማደዳል። በዚህ የነፃ አውጪ ድርጅት መሪዎች አዳራሽ ነው የምንንፈላሠሠው ወይንስ ይህ የነፃ አውጪ ድርጅት ነፃ እንዲወጣ “በሚታገልለት” ሕዝብ እውነታ? የሚለው ከፊቴ ይደቀናል።

በዚህ ጽሑፍ ጥቂት የውይይት ነጥቦችን አንስቻለሁ።

ሀ)   መነሻዬ፤ መታገያ መርኀችን ምንድን ነው? እንወያይበት።

ለዚህ ጥያቄ የምንሠጠውን መልስ ወሳኝ ነው። ይህ ትግል የእኔ፣ ያንተ ወይንም ያንቺ የግል ትግል አይደለም። ይህ ትግል የኢትዮጵያዊያን በአንድነት ትግል ነው። ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ከወያኔ ጋር በሀገራቸው በትንንቅንቅ ላይ ነው ያሉት። እኛም ሀገራዊ ውይይቶች አድርገን፤ ከሞላ ጎደል ሁላችንን የሚያስማማ መታገያ አንድ መርኅ ላይ እንድረስ እላለሁ። ይህ አሁን የለንም። ድቅድቁን የሀገራችን የፖለቲካ ጨለማ እኔ ብቻ ነኝ ትክክለኛ፣ ለሀገሪቱ እኔ አውቃለሁ ወይንም የምላችሁን ስሙ የማዛችሁን ሥሩ የሚለው ቅኝት፤ ቢያንስ በኛ ደረጃ አልፎበታል። ተማክረን እናደርገው። ሀገራዊ ውይይት ይቅደም። ሀገርን ሰብስቦ ውይይት ይደረግ የሚል ብዥታ የለኝም። ከሞላ ጎደል ግን፤ በዬተገኘው መድረክ፤ ግልፅ መውጣት ያለባቸውን ሀገራዊ ጉዳዮች ማኘክና ማላመጥ አለብን። መልሱ በሁላችንም ዘንድ አንድ ይሁንና እንነሳ።

ለ)   ቀጥሎ፤ የኢትዮጵያዊያንን ትግል ማን ይምራው? እንወቅ።

በመሪነትና በታጋይነት ማዕከለኛውን ቦታ መያዝ ያለበት፤ ሕዝቡ ነው። የማያዳግም ሀገራዊ ነፃነት የሚያመጣና ሕዝቡን የሚያስነሣ ድርጅት ሕዝባዊ ነው። አንድ ወገንተኛ ሳይሆን አብዛኛውን ያቀፈ ነው። አብዛኛውን ያቀፍ ድርጅት ደግሞ፤ ማዕከላዊ ለሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች፤ አብዛኞችን ያካተተ መልስ በግልፅ ያስቀምጣል። ሀገር ቤት ያለውን እውነታ ያላካተተ፣ ሀገር ቤት ያለውን ታጋይ ያላስቀደመና በዚያ ያልተመራ ድርጅት፤ ጉልቻን ከመቀያየር የተለዬ የሚያመጣው ፋይዳ የለም። እኔ፤ ሀገር ቤት ውስጥ፤ ከወያኔ ጋር እየተጋፈጠ ያለው ወጣት፤ በሀገሪቱ ውስጥ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ተመሥርቶ፤ የአሁን ትግሉን የሚመራ ድርጅት ውስጥ ውስጡን ይፈጥራል የሚል እምነት አለኝ። አሁን አለ የሚል እምነት የለኝም።

ሐ) ሌላው፤ የትጥቅ ትግሉን የተመለከተ ጉዳይ ነው። እንመርምረው።

ከገጠር ወደ ከተማ ወይንስ በከተማ ውስጥ የሚለው ጥያቄ መልስ አልተሠጠውም። ዓለም አቀፉ የፖለቲካ ሀቅና የሀገራችን የፖለቲካ እውነታ፤ የተወሰኑ የታጠቁ ታጋዮች ከገጠር ተነስተው እንደወያኔ እየበረሩ አዲስ አበባ የሚገቡበት ክፍት ክስተት የትናንት ሆኗል። በኔ ግምት፤ ትግሉ ሕዝቡ ባለበትና በከተማ ውስጥ ነው። ትክክለኛ ድርጅት ከተመሠረተ፤ ባጭር ጊዜ ውስጥ የወያኔ ቡድን ይቀበራል። ሕዝቡን በያለበት የሚያስነሣ ድርጅት አጭር ትግል ነው የሚኖረው። ይህ የታጠቀ ቡድን አስፈላጊነትን ያጎላዋል እንጂ አላስፈላጊ አያደርገውም። የዚህን የታጠቀ ቡድን መልክ፣ ይዘት፣ አወቃቀር፤ አካሂያድና ሚና መሪ ድርጅቱ በቦታው፣ በሰዓቱና በሂደቱ ይወስነዋል።

ከዝግጅት ክፍሉ፡- አቶ አንዱ ዓለም ተፈራ እንደዜጋ ያላቸውን ሃሳብ በጽሁፍ እንደገለጹ ሁሉ ያገባኛል የምንል ወገኖች ደግሞ በተመሳሳይ መልኩ ሃሳባችንን (የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ) በግለሰብ ላይ ሳይሆን በጉዳዩ ላይ ብቻ በማድረግ ውይይቱን ማዳበር ይቻላል፡፡ እኛ እንደሚዲያ ሁሉንም እንደምናስተናግድ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

Print Friendly, PDF & Email

60

SHARES
Share on Facebook
Tweet
Follow us
Share
Share
Share
Share
Share

Filed Under: Opinions

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • ቤተሰቦች አስከሬን መውሰድ እንደሚችሉ ተነገረ January 14, 2021 06:48 pm
  • ስብሃት፤ “ከሞትን ቆይተናል፤ … አሁን የቀብር ሥነ-ስርዓታችን” እየተፈጸመ ነው January 14, 2021 01:37 pm
  • “ተመልሰን እንነሳለን” ያሉት ህወሓቶች ተመልሰው ወደማይነሱበት ተሸኙ January 13, 2021 01:12 pm
  • አፋር ነፃ አውጪ (ኡጉጉሙን) ለመጠቀም የታቀደው የህወሃት ሤራ ከሽፏል January 13, 2021 01:10 pm
  • ህወሃትን ወደ ጅቡቲ ለማሻገር ሲሰሩ የነበሩ የአፋር ታጣቂዎች በሰላም ወደ ክልሉ ገቡ January 13, 2021 06:47 am
  • በታህሳስ ወር ብቻ ከ344 ሚሊየን ብር በላይ የኮንትሮባንድ ዕቃ ተያዘ January 13, 2021 06:10 am
  • የብልፅግና ፓርቲ ቀጣይ ፈተና ምን ሊሆን ይችላል? January 13, 2021 04:10 am
  • ለትምህርት እንዲሆነን January 11, 2021 01:20 pm
  • “ከተቀበሩበት የጃርት ጉድጓድ ነው ያወጣናቸው” መቶ አለቃ ስዩም ቱርቦ January 11, 2021 12:11 pm
  • የተደመሰሱና በቁጥጥር ሥር የዋሉ የወንበዴው አባላት ይፋ ሆነ January 7, 2021 01:16 pm
  • ዐቢይና መኮንኖቹ በመቀሌ፤ “ድሉ የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው” December 13, 2020 02:36 pm
  • ወንበዴው ህወሓት ከ1.4 ትሪሊዮን ብር በላይ ዘርፎ በውጭ አገራት ባንኮች አስቀምጧል December 8, 2020 01:05 am
  • ማይካድራ – የትህነግ የዘር ማጥፋት ጥግ ቋሚ ምስክር December 8, 2020 12:57 am
  • የወልቃይት ጠገዴ እናቶች ሰቆቃ ሲታወስ December 8, 2020 12:50 am
  • የደብረጽዮን ዋሻ December 7, 2020 11:30 pm
  • ባለ ከዘራው ኮሎኔል December 7, 2020 05:15 pm
  • ሰላማዊ ሕይወት በማይጨው December 7, 2020 04:12 pm
  • ተጠርጣሪ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊሶች የመያዣ ትዕዛዝ ወጣባቸው December 7, 2020 11:46 am
  • ከ3 ሺህ በላይ ተተኳሽ ጥይቶች በወልዲያ ጉምሩክ ሊያሳልፉ የሞከሩ 4 ግለሰቦች ተያዙ! December 7, 2020 11:18 am
  • ወንበዴዎቹ ይጠቀሙባቸው የነበሩ ተሽከርካሪዎችና የግል ሰነዶቻቸው ተያዙ December 7, 2020 10:50 am
  • ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በሶማሌ ክልል ተመሠረተ December 7, 2020 10:31 am
  • የኦነግ ሸኔ አባላትን ዕድሜ ለማሳጠር የጂፒኤስ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው December 7, 2020 12:38 am
  • የቆሰሉ ወታደሮች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጎበኙ December 6, 2020 11:41 pm
  • “ከዚህ በኋላ ይዘን እንታገላለን እንጂ ሠጥተን አንጠይቅም” ኮሎኔል ደመቀ December 2, 2020 12:24 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2021 · Goolgule