• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የግል አስተያየት

February 18, 2018 11:14 am by Editor Leave a Comment

የሃገራችን ፖለቲካ በፍጥነት በሚለዋወጡና አቅጣጫቸውን ለመተመን በሚከብዱ ሁኔታዎች ውስጥ ይዋኛል። ለእነዚህ በፍጥነት ለሚለዋወጡ ፖለቲካዊ ክስተቶች ገፊው ነገር  (driving force የምንለው) ምንድን ነው? ካለን በተለይም ላለፉት ሶስት ዓመታት በተከታታይ በመካሄድ ላይ ያለው ህዝባዊ ኣመጽ ነው። ይህ ኣመጽ በከፍተኛ ሁኔታ በፖለቲካው ላይ ተጽእኖ እየፈጠረ ነው። በብዙ ሃገራት ህዝቦች በአምባገነን ስርዓት ላይ ሲያምጹ 5  ዋና ዋና ክስተቶች ይፈጠራሉ። ህዝብ እምቢኝ ሲል አገዛዙ መረረኝ ብሎ ሲያምጽ አመጹ ተጽእኖ ፈጥሮበት የሚከሰቱት እነዚህ 5 ጉዳዮች፦

  1. በገዢው ፓርቲ ውስጥ መሰንጠቅ፣ መፈረካከስና አለመረጋጋትን ያመጣል።
  2. ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ያጠነክራል፣ ያበረታታል፣ ያደራጃል፣ ወኔ ይሰጣል።
  3. አዳዲስ መሪዎችን ከአመጹ መሃል ያወጣል::
  4. የለሂቁን ልዩነት ያጠባል። በህዝቡ ዘንድ ኣንድነትን ያጠነክራል።
  5. የዓለምን ድጋፍ ያገኛል ::

እነዚህ ክስተቶች በህዝብ ኣመጽ ጊዜ የሚከሰቱ ጉዳዮች ናቸው። እነዚህን መመዘኛዎች ይዘን የኢትዮጵያን የሶስት ዓመት ተከታታይ የመረረ ትግል ፍሬ ስንመዝን መጀመሪያ ላይ በጠቅስነው መስፈርት በኩል ከሞላ ጎዳል ተጽእኖው ጎልቶ ይታያል። ገዢውን ፓርቲ ህወሃት ኢሃዴግን በከፍተኛ ሁኔታ ሲመታው ታይቷል። ኢሃዴግ ከህዝቡ ተቃውሞ የተነሳ እንደ ባቢሎን ቋንቋው ሲዘበራረቅ፣ ኣፈ ጉባኤው ሲወድቅ ሲነሳ፣ ስራ ኣስፈጻሚው ለጥፋቱ ሁሉ “ሙሉ ሃላፊነት እወስዳለሁ” ማሩኝ ኣይነት ሲናዘዝ ብዙ ብዙ ሲያደርገው ይታያል። ይህ የህዝብ ማእበል ገዢውን ፓርቲ ክፉኛ ሰንጎ  ይዞታል። በርግጠኝነትም ወደፊት በዚህ መልኩ እንዳይቀጥል ኣድርጎታል። የህዝቡ ትግል በዚህ በኩል ጥሩ ውጤት ኣሳይቷል ማለት ይቻላል። ትግሉ ገና ሲቀጥል ደግሞ ገዢው ፓርቲ ኣልማረክም የተባልኩትን ኣላደርግም ብሎ ካመጸ ይህን ፓርቲ እስከ ሃቹ ሊበትነው ይችላል።

ተቃውሞውን ተከትሎ በገዢው ፓርቲ በኩል ለውጦች ኣሉ እንበል እንጂ ታዲያ ለውጡን በጥንቃቀ ማየት በጣም አስፈላጊ ነው። ከገዢው ፓርቲ ኣባል በሆኑት በኦህዴድና በብአዴን ኣካባቢ በተወሰነ ደረጃ ለስላሳ ቃላቶችን መጠቀም ታይቷል። ይህ በርግጥ የህዝብ ተቃውሞ ያመጣው ለውጥ ነው። ይሁን እንጂ  ህዝቡ ለሚፈልገው ለውጥ ተስፋ የሚያደርገው እነዚህን ድርጅቶች ኣይደለም። ኢሃዴግ ጥፋቱን ያምንና  በምድሪቱ ሰው እንደሌለ  በጥልቀት ታድሼ  የምቀጥለው እኔው ነኝ ኣይነት ነው ውሳኔው። ለውጡን ከመፍራቱ የተነሳ ከራሱ አባላት መሃል ህዝብ የሚፈልጋቸውን ቋንቋዎች እያናገረ የተበላሸበትን ቅቡልነት (legitimacy) በጥቂቱም ቢሆን ጠጋግኖ እድሜ መግዛት ይፈልጋል። ራሱ ህወሃት በረጅም ገመድ ያሰራቸውን የኦህዴድና የብአዴን ሰዎች ለዚህ ዓላማው ዋና መሳሪያ ኣድርጎ ያያቸዋል። በመሆኑም ህዝቡ ተቃዋሚን ተስፋ እንዳያደርግ ተቃዋሚውን እየመታ ለውጡ ከእጁ ሳይወጣ በቃላት እየደለለ ያለ ምንም መሰረታዊ ለውጥ መዋል ማደር ይሻል።

በቅርቡ በህዝብ ተቃውሞ ሲናጥ የቆየው መንግስት ብዙ እስረኞችን ፈቷል። ሌላው ቀርቶ በኦነግና በግንቦት ሰባት ኣባልነት ተጠርጥረው የተያዙትን ሳይቀር ፈቷል። የኢትዮጵያ ፓርላማ “ኣሸባሪ” ያላቸው ቡድኖች ናቸው እነዚህ ኣካላት። መንግስት ይህን ያህል ከተራመደ በሁዋላ በማግስቱ በመላ ሃገሪቱ ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ኣወጀ። ይሄ ኣዋጅ ዓለምን ኣስገርሟል ኣስከፍቷል። መንግስት ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ያወጀበት ምክንያት ኣንደኛ የህዝቡ ጥያቄ ስለገባው ነው። እስረኞችን መፍታት የህዝቡ ጥያቄ ግብ እንዳልሆነ ያውቃል። የሚቀጥለው ጥያቄ ስላስፈራው ነው በድንገት ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ እንዲያውጅ ያደረገው። የህዝቡ ጥያቄ ሃገራዊ መግባባት ይፈጠርና ወደ ምርጫ ገብተን የምንፈልገውን እንምረጥና በመረጥነው እንተዳደር ኢሃዴግ የተባለው ድርጅት በቃን እንደሆነ ገዢው ፓርቲ ተረድቷል። ሁለተኛ ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጁ የሚያሳየው ነገር ጠቅላይ ሚንስትሩ ስልጣን ከለቀቁ በሁዋላ ገዢው ፓርቲ  ህዝብ ወደሚፈልገው ለውጥ ለመጓዝ እስካሁን ኣለመወሰኑን ያሳያል።

አሁን በሚደረገው የጠቅላይ ሚንስትሩ ምርጫ ምን ኣልባት  ከራሱ ኣባላት ውስጥ ትንሽ ቅቡልነት ኣላቸው የሚላቸውን ሊጠቀም ይችል ይሆናል። ያም ቢሆን ግን የህዝቡ ጥያቄ የግለሰቦች ለውጥ ሳይሆን ኣጠቃላይ ሃገሪቱ ሽግግር ያስፈልጋታል ምርጫ እንግባ እስከሚል የሄደ በመሆኑ ማንንም ሾመ ማንን የህዝቡ ጥያቄ እንደማይቆም ስለተረዳ ነው ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ያወጀው። የሚገርመው ግን ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ የህዝቡን ኣመጽ ይቀለብሳል ወይ? ብለን መጠየቅ ኣለብን። መቼም እስካሁን ድረስ የተደረጉ አመጾች ሁሉ መንግስት ፈቅዶ ኣይደለም። የመከላከያ ሰራዊት በአራቱም ማእዘን እየዞረ ሰልፈኛውን ሲበትን ሲገድል የነበረው ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ስለታወጀ ኣይደለም። ይህ ኣዋጅ በተግባር የሚያመጣው ለውጥ የለም። ነገር ግን በመርህ ደረጃ ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ የሚታወጀው ህዝቡ የፖለቲካ ለውጥ ስለጠየቀ መሆን የለበትም። በመሰረቱ ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ በዓለም ሃገራት ኣልፎ ኣልፎ ይታወጃል። ለምሳሌ የተፈጥሮ አደጋ ሲገጥም፣ ከፍተኛ ጦርነት ሲመጣ፣ በሰው ሰራሽ ኣደጋ ጊዜ፣ በተላላፊ በሽታ ጊዜ ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ይኖራል።

የኢትዮጵያው የመከላከያ ሚንስትር ስለ ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጁ ሲናገሩ የአስቸኳይ ጊዜ ኣዋጁ መነሻ ህገ መንግስቱን ለመጠበቅ ነው ይላሉ። ይህ መነሻ በራሱ መሰረታዊ ችግር ኣለው።በመሰረቱ የኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ማለት የህግ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ህጋዊ የሆነ ህገወጥ ህግ ማለት ነው። ይህ ማለት ህብረተሰብን ከኣደጋ ለመጠበቅ ለጊዜው  ከህገ መንግስቱ የተወሰኑትን ኣንዳንድ ኣንቀጾች ለጊዜው መሻር ማለት ነው። ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ መጀመሪያ የሚሰብረው ህገ መንግስቱን ነው። በርግጥ የማይነኩ ኣንቀጾች ቢኖሩም ከዜጎች የእለት ከእለት ህይወት ጋር የተያያዙ ኣንዳንድ መብቶችን ሰብሮ ይታያል። ይሄ ነው ኣንዱ ዋና ጉዳይ። ህዝብ የመናገር ነጻነቴ ተነካ፣ እኩልነት ኣጣሁ፣ መልካም ኣስተዳደር ኣጣሁ ብሎ ሲጠይቅ ህገ መንግስቱ የሚፈቅደውን መብቴን አጣሁ ነው እያለ ያለው። ህገ መንግስታዊ መብቴ ይጠበቅልኝ የሚለውን ህዝብ ኣቶ ሲራጅ ህገ መንግስቱን ለመጠበቅ ኣስቸኳይ ጊዜ ኣውጀናል ቢሉት ራሳቸውን ሰውየውን ግምት ላይ ይጥላል። ህዝብ የታሰሩ ይፈቱ፣ ለውጥ እፈልጋለሁ ሲል አስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ኣይታወጅም።

የአሜሪካ ኤምባሲ የዛሬውን ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ በጽኑ እቃወመዋለሁ ያለው የኢትዮጵያውያን ጥያቄ የለውጥ ጥያቄ በመሆኑ ይህ ጥያቄ የሚፈታው በአፈና ሳይሆን በነጻ ውይይት የበለጠ ነጻነትን በማጎናጸፍ መሆኑን ስለሚያውቅ ነው። በርግጥም በመግለጫው ላይ ለኢትዮጵያ መንግስት የመከረው ይህንን ነው። በዚህ ኣጋጣሚ የአዲስ ኣበባው የአሜሪካ ኤምባሲ ያወጣውን መግለጫ ብዙ ኢትዮጵያውያን አድንቀዋል፣ እውነትም ኣሜሪካ ከኢትዮጵያውያን የለውጥ ጥያቄ ጎን በጽናት ቆማለች እንዲሉ ኣድርጓል። የመናገር መብቴ ይከበር ለሚል ህዝብ ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ሳይሆን ችግሩን የሚፈታው የበለጠ ነጻነት ነው የሚለው የአሜሪካ ኤምባሲ አሳብ ብሩህ ነው። በዚህ አጋጣሚ የተባበርችው አሜሪካን ክቡር አምባሳደር ማይክል ሬይነርን  ከልብ አመሰግናለሁ። ወደፊትም የኢትዮጵያውያን የለውጥ ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ ከጎናችን እንደሚሆኑ ጥርጥር የለኝም። የኤምባሲው ሙሉ መግለጫ እነሆ ።

ሁለተኛውን ጉዳይ እንመልከት።

በብዙ ሃገራት የህዝቦች ትግል ውስጥ ህዝብ ሲያምጽ ከፍተኛ ሞራል የሚያገኙት፣ የሚነቃቁት፣ በፍጥነት የሚደራጁት ተቃዋሚዎች ናቸው። በዚህ የኢትዮጵያውያን ትግል ወቅት እውነቱን ለመናገር የህዝቡ ትግል ሲያነቃቃው ሞራል እየሰጠው ሲደራጅ ብዙ ኣይታይም። ይሄ ጉዳይ ደግሞ ኣሳሳቢ ነው። ለምን ተቃዋሚው ኣይደራጅም? የህዝቡ ትግል ለምን በሃይል ኣላራመደውም? ካልን ህወሃት ኢሃዴግ በከፍተኛ ሁኔታ ሰርጎ በመግባት ፓርቲዎችን ስላሸመደመደ እስከ አመራር የራሱን ሰላዩች ኣስቀምጦ ስለሚኖር ነው። ኣንደኛው ዋና መንስኤ ይሄ ነው። መንግስት በመድብለ ፓርቲ ርዓት ከመነሻው ኣያምንም። መድበለ ፓርቲን የሚጠቀምበት ለምእራቡ ዓለም ማታለያ ነው። የኢትዮጵያ  ደህንነት ሰራተኛ ዋና ስራ ተቃዋሚን ማዳከም ነው። ህወሃት ኢሃዴግ የለውጥ ጥያቄ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሚመጣ ይልቅ ከራሱ ከአባለቱ ቢነሳ ይሻለዋል። ከዚህ ኣያያዙ የተነሳ የህዝቡ ተቃውሞ ያየለውን ያህል ተቃዋሚው ሃይል ሲያገኝ ኣልታየም።

ፖለቲካው በዘውግና በአንድነት ሃይል መከፋፈሉም ኣንዱ ሌላ ችግር ነው። የሆኖ ሆኖ ግን ተቃዋሚው ኣልወጣም ኣልታየም ማለት የለም ማለት ግን ኣይደለም። ኣንድ ቀን ነጻ ኣየር ቢፈጠር በጥቂት ወራት ውስጥ እንደ ቅንጅት ኣይነት ፓርቲ ተደራጅቶ ህዛብዊ ተቀባይነት ያገኛል። ሶስተኛው ጉዳይ ከተቃውሞ መሃል ኣዳዲስ ትንታግ ፖለቲከኞች መታየት ኣለመታየታቸው ነው። በ1997 ዓ.ም በነበረው ንቅናቄ ጊዜ ኣዳዲስ መሪዎች ብቅ ብለው የህዝቡን ልብ ማርከው ነበር። ህዝቡም እነዚህን ልጆቹን ሲያይ ጊዜ በፍቅር ወደቀ። ለውጥ ያለ ልክ ፈለገ። ይሁን እንጂ ያ መልካም ኣስተዳደር ዴሞክራሲ የተጠማ ህዝብ ያ የለውጥ ወራቱ ተበላሸበት። ዛሬ የሚታየውና ለሶስት ዓመታት የቆየው ህዝባዊ ኣመጽ ኣዳዲስ መሪዎችን  በማስተዋወቅና በማውጣት በኩል ጉልህ ውጤቱ ኣይታይም። በዓለም ታሪክ ውስጥ የተነሱ ታላላቅ መሪዎች ህዝባዊ አመጽ የወለዳቸው ናቸው። ማርቲን ሉተር ኪንግ ከሲቪል ራይት ንቅናቄ የተገኘ ምርጥ መሪ ነው። ማንዴላ ከንቅናቄ የወጡ ኣመጽ የወለዳቸው ናቸው። የህዝብ ትግል ሲነሳ ኣዳዲስ መሪዎችን ይፈጥራል ይጨምራል። በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ውጤት ጎልቶ ያልታየው እንደተለመደው የህወሃት ደህንነት በተለይ ተኩሮ በዚህ ኣካባቢ ስለሚንቀሳቀስ ነው። ብቅ የሚሉትን እያሰረ፣ ደብዛቸውን እያጠፋ፣ እያሸማቀቀ ስለሚኖር ነው። ይህም ሆኖ ግን ትግሉን እየመሩ ያሉ ቄሮዎች ሲገለጡ ኢትዮጵያውያን የሚኮሩባቸው ናቸው።

አራተኛው ነገር ደግሞ የለሂቁ ክፍፍል መቀነሱ፣ በህዝቡ መካከል ኣንድነት መጠናከሩ መታየቱ ነው። በርግጥ በህዝብ መካከል ከፍተኛ የአንድነት ስሜት ኣይሎ ይታያል። ኣንድ ጊዜ ጎንደር ላይ በነበረ ተቃውሞ ወቅት የኦሮሞው ደም የኔም ነው የሚል ድምጽ ከተሰማ በሁዋላ በኣማራና በኦሮሞ፣ በደቡቡና በሰሜኑ በሁሉም ብሄሮች መካከል ኣንድነቱ ጠንክሮ ይታያል። ይህ የህዝቡ ኣመጽ የሚያመጣው ውጤት ነው። ያለፈው ሶስት ኣመት ኣመጽ ይህን ፍሬ በማሳየቱ ብዙ ሰው ለሃገሪቱ መጻኢ እድል ያለውን ተስፋ ኣብርቶለታል። በሌላ በኩል በለሂቁ መካከል ያለው ክፍፍል መቀነስ ግን ጎልቶ ኣልታየም። በርግጥ የተጀማመሩ ህብረቶች ኣሉ። ይሁን እንጂ እንደ ቅንጅቱ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ የለሂቅ ክፍፍል መቀነስ እስካሁን ኣልተመዘገበም። ለዚህ ችግር መንስኤው ያው የመንግስት የደህንነትና የስለላ መዋቅር በዚህ ኣካባቢ ጠንካራ ቤሆኑ ነው። በርግጥ ታዲያ እያደር እየተሻሻለ መሄዱ ኣይቀርም፣ የስለላውን መረብ እየበጠሰ መጠናከሩ ኣይቀርም ብሎ ማመን ይቻላል።

አምስተኛው ጉዳይ የዓለም ዓቀፉን ማህበረሰብ መማረክ ነው። የኢትዮጵያውያን ትግል በዚህ በኩል ተሳክቶለታል። አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት በታሪካችን ባላየነው ልክ ይህን መንግስት እየተቃወሙ ከህዝቡ ጥያቄ ጎን ቆመው ሲታገሉ ይታያሉ። አሁን የወጣውን ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ በተመለከተ የአሜሪካን ኤምባሲ በከፍተኛ ሁኔታ ኣልስማማበትም በሚል ሃይለኛ ቋንቋ አውግዞታል። በዲፕሎማሲው መስክ ያፈራነው  ፍሬ በዚህ የሚገለጽ ብቻ ሳይሆን H.Res 128  ህግ ሆኖ ይጸድቅ ዘንድ በአሜሪካ ኮንግረስ በሂደት ላይ ነው። በዚህ ደረጃ የዓለም ኣቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያወያን የመረረ ተቃውሞ ተማርኳል። ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥን ለማምጣት ከፍተኛ ሃይል ነው።በአጠቃላይ የህዝቡን ተቃውሞ ስንገመግም አንድነትን እያጠናከረ፣ በአብዛኛው በብሄሮች መካከል ፍቅርን እያሳደገ ነው የመጣው። አልፎ ኣልፎ የሚነሱ የብሄር ግጭቶችም በገዢው ፓርቲ ሆን ተብሎ የተቀነባበሩ ተደርገው በህብረተሰቡ መታየታቸው የሚያሻየው ህዝቡ ኣንድነቱን እያሳደገ በዚህ ትግል ውስጥ ኣንድነቱን ጠብቆ ይዞ እንዳለ ነው።

ይህ በጎ ርምጃ ሲሆን በሚቀጥለውም የመጨረሻው የትግሉ ምእራፍ ይህ ኣንድነት መጠናከር ኣለበት። በሁለተኛ ደረጃ የፖለቲካው ለሂቅ ከማንኛውም ጊዜ በላይ ሰርጎ ገቦችን እየመነጠረ እያወጣ ክፍፍሉን መቀነስና ለህዝቡ ተስፋ መሆን ኣለበት። ህዝቡ ከኢሃዴግ መሃል ኣንዱ የተሻለ ቋንቋ ሲናገር ያንን ሰው የሚያሞካሸው ተቃዋሚው ተጠናክሮ ስለማያይ ነውና በዚህ ወቅት ተቃዋሚው መጠናከር ልዩነትን ማጥበብ ኣለበት። ሌላው ጉዳይ አዳዲስ መሪዎችን ማውጣት የህዝቡ ስራ ነው። ታለንት ያላቸውን መሪዎች በተለያዩ ማህበራዊ ኣጋጣሚዎች ማሳደግና መሰባሰቢያ ማድረግ ያስፈልጋል። ፓርቲዎችም ለነዚህ ኣዳዲስ መሪዎች ቦታ መስጠት በኣዳዲስ ኣስተሳሰቦች መራመድ ያስፈልገናል። የዓለም አቀፉ ኮሚኒቲም ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል የዲፕሎማሲ ትግላችንን መቀጠል ነው።

ገለታው ዘለቀ geletawzeleke@gmail.com)


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Opinions Tagged With: Right Column - Primary Sidebar, tplf

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • የተንጋደደው የገዱ መልስ February 6, 2026 03:05 pm
  • ሻዕቢያ “አክሱም ገብቶ ወጣቶች በጅምላ ሲረሽን ጸብ ተፋፍሟል …” February 4, 2026 01:15 pm
  • አደራ ጠባቂው የኢሉአባቦር ሕዝብ February 4, 2026 12:14 pm
  • የአውሬው ሪፖርተር ቀላቢዎች፡ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን January 28, 2026 09:56 am
  • በአሜሪካ ጥምር ዜግነት እንዲቀር ጥያቄ ቀረበ January 27, 2026 03:05 pm
  • “ከህወሓት፣ ከሻዕቢያ፣ ከግብፅ ሰዎች ጋር ሆኖ እንዴት የአማራን ጥያቄ ማስመለስ ይቻላል?” ኮሎኔል ፈንታው January 25, 2026 04:23 am
  • የኢትዮጵያ አየር ኃይል: ለአፍሪካ ሀገራት የመጀመሪያዎቹን የአየር ኃይል አብራሪዎች ያሰለጠነ ተቋም January 25, 2026 03:50 am
  • የአማረ ሪፖርተር እያደረሰ ያለው የብሔራዊ ደኅንነት አደጋ January 22, 2026 01:56 am
  • የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የማርያምን ማዕረግ ዝቅ አደረገች December 12, 2025 09:27 pm
  • ኢህአፓ: ከነጭ ሽብር ወደ “አዲስ አበባ ትናገር” የጎዳና ሽብር? December 12, 2025 09:11 pm
  • EOC Bans Haile Gebrselassie Over Are­qie Comments Linked to Doping November 21, 2025 07:47 pm
  • በሥራ ማቆም አድማ ጥሪ ዘርፍ ባለሙያው ጃዋር ሌላ ጥሪ አቀረበ November 17, 2025 09:25 am
  • የ-አብሮነት ማኅበር የመረጠው ሕቡዕ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይፋ ሆነ November 5, 2025 12:06 pm
  • “የኢሳያስ አፈወርቂ ውድቀት አይቀሬ ነው … “ፅምዶ” ራዕይ ዓልባ” ነው – ሼትል ትሮንቮል October 26, 2025 10:15 pm
  • አሜሪካ ስላልተቀበለችው ነው “የሽሽግር መንግሥት” ስብሰባው በአምስተርዳም ተካሄደው October 25, 2025 11:09 pm
  • በዓባይ ግድብ ምረቃ፡ የሕዝብ ደስታ፣ የቴድሮስ ካሳሁን ዝምታ September 14, 2025 04:27 am
  • ኢትዮጵያ የውኃ ኑክሊየር ማብላያዋን ልታስመርቅ ነው  August 29, 2025 11:46 pm
  • መከላከያ በፋኖ አመራሮች ላይ እርምጃ ወሰደ፤ ዘመነ በ“አንድ ማንኪያ ቅንነት” አንድ እንሁን አለ August 23, 2025 12:35 am
  • ፋኖን በፋይናንስና በሎጂስቲክስ የሚደግፉ የጎጃም ባለሃብቶች ከስደት ሊመለሱ ነው August 14, 2025 12:42 am
  • የበቀለ ገርባ የአሜሪካ ጥገኝነት ማመልከቻ ውድቅ ተደረገ August 13, 2025 12:16 pm
  • ሞዐ ተዋሕዶ “ነጻ አውጪ ግምባር” – ሞነግ August 13, 2025 12:58 am
  • የሃይማኖትና የመንግሥት ጥምረት በረከት ወይስ መርገም?  August 5, 2025 09:18 pm
  • የባከነ የስደት ሕይወት ከደባርቅ እስከ ኖርዌይ July 29, 2025 05:44 pm
  • “በዚህ ዓመት መጨረሻ ትግራይን እንቆጣጠራለን”፤ ቲፒኤፍ July 22, 2025 01:28 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2026 · Goolgule