እርሳስ በጓደኛው፤ በብዕር እስክሪፕቶ
ባለው ገደብ የለሽ፤ ነጻነቱ ቀንቶ
እንዳሻው ቢናገር፤ የልቡን አውጥቶ
እንዲህ አልክ ብሎ፤ ያለውን አጥፍቶ
የሚያስወግድበት፤ በላጲስ አንሥቶ
ስለማይከላ፤ ሲናገር አፍ ከፍቶ ፡፡
እሱ ግን ዘለዓለም፤ በላጲሱ ጠፍቶ
መኖሩ አስመርሮት፤ በእጅጉ ተከፍቶ
እኔስ ለምን እንዴት? ማለት ጀመረና
ጠየቀ አፋጠጠ፤ ተሰማው ፍነና
ነጻነቱን ሊያውጅ፤ ተነሣ ይሄ ጀግና
ከእንግዲህ በኋላ፤ አለ ቆፍጠን ብሎ
የነበረውን ፍርሐት፤ ከልቡላይ ነቅሎ
ከእንግዲህ ወዲህ፤ አለ አንሥቶ ክንዱን
ባናቴ ያለው ላጲስ፤ ገደብ የለሽ ሥልጣን
አብቅቷል ብያለሁ፤ ይሰማ አዋጀ
የሚጸና ይሆናል፤ በትውልድ ልጅ ልጀ
ከዚህች ቀን በኋላ፤ ማንም ያላወቀ
በእውቀት ያለበቃ፤ ከንቱ ያልጠነቀቀ
ዐሥሬ እየጻፈ፤ እየለቀለቀ
ዐሥሬ የሚያጠፋ፤ መሀይም የወደቀ
ውሸት የሚደጋግም፤ በላጲስ እየፋቀ
በእጁ አይይዘኝም፤ አለቀ ደቀቀ
ከቶም አይገዛኝም፤ ብሎ አስታወቀ ፡፡
ከእንግዲህ ወዲህ፤ መብቴን ተገፍፌ
አልኖርም ብያለሁ፤ እያለ መዳፌ
እኔም እንደ ብዕር፤ ያሻኝን ብል ጽፌ
ወይም ተናግሬ፤ በዓለም ሕግ ታቅፌ
ያ የተናገርኩት፤ የጻፍኩት ቃል ርኡስ
ይቀመጣል እንጅ፤ እዛው ሳይደመሰስ
ማንም አይፍቀውም፤ እያነሣ ላጲስ
ይሄው አውጃለሁ፤ ይሁን እንደ ቃል ቅዱስ፡፡
ከእንግዲህ በኋላ፤ በዚህ አዋጅ ሥሩ
ስሕተት እንኳን ቢሆን፤ የጻፍኩት ቃል ዘሩ
ይቀመጣል እንጂ፤ ልክ እንደ ብዕሩ
ሠረዝ ተደርጎበት፤ ሳይጠፋ ነገሩ
ለታሪክ ለትምህርት፤ ጠቀምጦ በክብሩ
ከእንግዲህ ወዲህ፤ የማንም ምን ውላጅ
ከቶም አይፍቀኝም፤ እኔን በላጲስ ፈንጅ፡፡
መስከረም 2007ዓ.ም.
(ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)
በለው ! says
**************************
አርሳስ…
እርሳስ በእስክሪብቶ ሁልግዜ ተዛብቶ
እኔ እየጠፋሁኝ አንተ አትጠፋ ከቶ?
እስክሪብቶ…
አንተማ ሞኝ ነህ አጥፊህን በራስህ ተሸክመህ
ለእግር ሸንካይ በመቅረጫ ተሸራርፈህ
እኔማ ቀለሜ ላይፈስ ታፍኜ ከላይም ከታችም
የሚፃፍ ሞልቶ አንድም ዘጋቢና ፀሐፊ አልተገኘም።
ላጲስ…
እኔ የሰማሁት የዓሳ ሽታ ከራስ ነው
የእርሳስ ላይ ጭንቅላትን አጥፊ ማነው ያለው
እርሳስማ አጠፋኝ ሲል ስሜን አጠፋው
እስኪሪብቶ ተሳለቀብኝ እንደማላጠፋው
የተፃፈን ቀበኛ የሚፅፍን የሚያጠፋው ማነው!?
በለው!
Amsalu Gebrekidan says
ይሄንን ግጥም ብዙ ሰው እንዳልገባው ሳይ አዘንኩ፡፡ ለነገሩ እንኳን ቅኔያዊው ይቅርና የትውልዱ በቋንቋው ራሱን ሐሳቡን የመግለጽ ችሎታ እጅግ ከመድከሙ የተነሣ የቋንቋው ጥራት አሽቆልቁሎ ተራ ንግግር እንኳን በአግባቡ መግለጽ የምንቸገር ትውልድ እየሆንን ከመሆኑ የተነሣ ቅኔ ለምን አልገባህም ብሎ ማለት ምጸት ነው የሚሆነው፡፡
ይሄውላቹህ እርሳሱ የሚወክለው ሐሳቡን በነጻነት የመግለጽ መብቶቹን አጥቶ ተረግጦ የሚኖረውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይወክላል፡፡ ላጲሱ ደግኖ ገደብ የለሽ ሥልጣን ይዘው የሚረግጡትን ግፈኛ ገዥዎቹን ይወክላል፡፡ እስክሪፕቶና ብዕሩ ደግሞ በነጻነት ሐሳቡን የመግለጽ መብት ያለውን የምዕራቡን ዓለም ሕዝብ ይወክላል፡፡ አሁንስ?
ሳባ says
አመሰግናለሁ አምሳለው ግን አኔ ገና ሳነበው ቅኔ መሆኑ ገብቶኝ ነበር. ልንገርህ አኔ ethiopia ውስጥ አደለም ያደኩት ግን የላፕሱና የርሳሱ ቅኔ ስለገባኝና አንተ ደግሞ sure ስላደርክልኝ አመሰግናለሁ.