• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ውለታ የማታውቅ ሀገር

December 8, 2012 03:18 am by Editor 12 Comments

• ያ የኮሜዲ አውራ “እብድ” ተብሎ ጎዳና ላይ “ቆሼ” ይለቅማል!

• እርሱን ያፈራው ኅብረተሰብ የወደቀን ቀና ከማድረግ እንዳይቃና ይተጋል

• ስለዚህ ኅብረተሰቡ እንደ ድመት የራሱን ልጆች ይበላል!

ይኸውልህ ወዳጄ የተመለከትኩትን፣ የታዘብኩትን እና ያስተዋልኩትን እንደወረደ ላጫውትህ፡፡ ያ ጉምቱ የጥበብ ሰው፣ ያ የኮሜዲ-የጭውውት አውራ፣ ያ ጥበብን የተቀባው ባለትልቅ ተሰጥዖው ሰው፣ ያ ከሥነ-ሠብዕ ጥበብ ተሻግሮ የአዕዋፋትን ዝማሬ ምስጢር፣ የንፋስን ሿሿታ፣ የበር-መስኮት ሲጥሲጥታ ሳይቀር በጥበብ ሥራው ላይ አክሎ የሚከውንልህ ተዋናይ ልመንህ ታደሠ፣ ከፒያሳ ወረድ ብሎ ከሚገኘው ቢስ መብራት አደባባይ ላይ፣ እንደ ማንም ቆሼ ሲለቅም ተመለከትኩት፡፡

ልመንህን ያየ፣ እኔን-አንተን አየ፤ እኔን-አንተን ያየ ኅብረተሰቡን አየ፤ ኅብረተሰቡን ያየ-ተቋማቱን አየ ነው እያልኩህ ያለሁት ወዳጄ፡፡

ያ የጥበብ አውራ ልመንህ ታደሰ ሰውነቱ ገርጥቶ፣ የማይቀይራትን ጥቁር ሰማያዊ ወይም ጥቁር ሱፍ በውሃ ሰማያዊ ሸሚዝ አጥልቆ፣ የተጨራመተች ልሙጥ ጥቁር ቆዳ ጫማ ተጫምቶ፣ እንደ ባይንደር መሳይ ነገር ላይ የተጨረማመቱ ቡጭቅጫቂ ወረቀቶችን ይዞ የሥነ ሥዕል ንድፍ እንደሚሰራ ጀማሪ ሰዓሊ ከአደባባይ ሆኖ ድምም-ፍዝዝ ይላል፤ በጀርባው ባነገተው ጥቁር ቦርሳ /ኮሮጆ/ አንዳች ነገሮችን ሸክፏል፡፡ ልመንህ ታደሠ ተርቦም ሊሆን ይችላል-ማን ያውቃል?

ለጠቅ አድርጎ ደግሞ ከቢስ መብራት ሳይርቅ አቀርቅሮ ራመድ-ራመድ ይልና ወዲያው ቆሼ-ነገር ይለቅማል ከመሬት፤ ከዚያም ቀረብ ብሎ ከድማሜው ከሚያናጥበው ሰው ጋር ከራሱ ጋር ብቻ በሚያወራ ሰው ድምጸት አንዳች ውል የሌለው ነገር ያወራል፡፡

ብዙዎች የእድሜ አቻዎቹና የእድሜ ትንሾቹ እያፌዙበት ያልፋሉ፡፡ “ልመንህ በአደባባይ ‹ላይቭ› እየተወንክ ነው፣ ልመንህ አለባቸው ተካ ይጠራሃል- አትሄድም ቶሎ፣ ልመንህ ኑሮ ጠረረብህ፣ ልመንህ ከዋሺንግተን ተንደርድረህ ፒያሳ ጎዳና…” እና ሌላም ሌላ በጆሮዬ ያደመጥኩት ከኅብረተሰቡ የተበረከተለት አቀባበል ነው፡፡ የጎዳና ተዳዳሪዎች ብቻ በፍቅር ሲቀርቡት አስተውያለሁ፡፡ ሊንከባከቡት ይሞክራሉ ግን ደግሞ እርሱ አይመቻቸውም፡፡

“እብዱ” ልመንህ ፊቱን ወደ ፒያሳ አዙሮ ተንቀሳቀሰ፡፡

እንደ ብዙ ወጪ ወራጅ ኢትዮጵያዊያን እና ኢትዮጵያዊያት እኔም በለበጣ ከንፈሬን እየመጠጥኩ ተዘባበትኩበት፤ እንደ ብዙ አሽከርካሪዎች እኔም ገልመጥ አድርጌው የስላቅ ፈገግታ አሳይቼ የእርምጃዬን ማርሽ ጨምሬ ወደ መርካቶ እብስ ለማለት ፈልጌ ነበር፤ ግን አልቻልኩም፡፡ (በመጽሐፍ ቅዱስ ያለው የሣምራዊው ታሪክ ትውስ አለኝ) አንዳች የጥፋተኝነት ስሜት ጭምድድ አድርጎ ያዘኝ፡፡

አይምሰልህ ወዳጄ! ልመንህን እኔ በግል አልበደልኩትም፤ በአካልም አላውቀውም፡፡ በተናጥል ያስቀየመኩትም አንዳች ነገር የለም! በቅርቡ “አበደ” ብለው ከአሜሪካ አገር አውጥተው (ዲፖርት አደረጉት ነው የሚባለው) በተወለደበት ኅብረተሰብ ውስጥ አምጥተው ህዝቡ ውስጥ እስኪደፉት (እስኪጥሉት) ጊዜ ድረስ እንደዚህ ገፅ ለገፅ በአካል አይቼውም አግኝቼውም አላውቅ፡፡

በቲቪ ስክሪን እና በሲዲዎች ብቻ የምመለከተውና የማደንቀው ብርቅዬ አርቲስት ነበር፡፡ ነበር ልበል እንግዲህ-ጎዳና ላይ ጣልነው አይደል፡፡ እኔ እና እሱ በትውልድም፣ በደረጃም ዱባ እና ቅል የምንባል ነን፡፡ የትና የት ይልቀኛል መሰለህ ኢህአዴግ ከበረሃ ወደ አዲስ አበባ በትጥቅ ትግል አሸንፎ በገባ እና ሥልጣነ-መንበሩን በተቆናጠጠበት ጊዜ የነበረውን አስፈሪ የሽግግር ወቅት፣ የበቅሎ ቤቱን ፍንዳታ፣ በልጅ ዓይናችን ያየነውን የሸጎሌውን ፍንዳታና እልቂት፣ በየቤታችን ጣራ በስቶ የሚመጣውን ተባራሪ ጥይትና የመትረየስ እሩምታ የፈጠረብንን ዘግናኝ የፍርሃት አባዜ በጥበብ ሥራቸው ያረሳሱን ከነበሩ ኮሜዲያን አንዱ እና ዋናው ልመንህ ታደሠ ነበር፤ ከአለባቸው ተካ ጋር ተጣምሮ፡፡

እንደማስታውሰው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የመቶ ሃያ ፕሮግራምን አሁን (እሁድ መዝናኛ) ሲጀምር የዝግጅቱ አስኳል ተደርገው ከሚጠበቁት አርቲስቶች ልመንህ ታደሠ እና አለባቸው ተካ ዋናው ነበሩ፡፡ ዛሬ አለባቸው ተካ በድንገተኛ የመኪና አደጋ ካለፈ ሰነባበተ፤ ልመንህ ታደሠ ደግሞ አብዷል ተብሎ የወለደ (ያፈራ) ኅብረተሰብ ጥሎ አይጥልም ተብሎ ከአሜሪካን አገር ወደ አዲስ አበባ ፒያሳ-አራት ኪሎ ጎዳና ከደጅ ተደፍቷል፣ ተጥሏል ነው እያልኩህ ያለሁት፡፡

ግን እኮ የወለደ (ያፈራ) ኅብረተሰብ ጥሎ አይጥልም የሚለው አባባል ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰራ አይመስለኝም፡፡ ምናልባትም ወላጅ እናትህ ጥላ አትጥልህ ይሆናል፡፡ እንደ ኅብረተሰብ ግን ጥሎ እንዳይጥልህ ወይ በሥጋ የምትወለደው ቤተሰብ ከአጠገብህ ሊኖር ይገባል፤ አልያም በጎሳ፣ በሃይማኖት፣ በኑሮ መደብ ወይም በፖለቲካ ርዮት የምትቧደነው ቡድን ሊኖርህና ያም ቡድን በማህበረ-ፖለቲካው ጥሩ ሥፍራ ሊኖረው ግድ ነው፡፡

አለበለዚያ ከዚያ ውጭ ከሆንክ እንደ ልመንህ ታደሠ ልቀህ የጎላህበት፣ ሌት ተቀን የሰራህለት፣ ቋንቋውን የተቀኘህለት፣ ባህሉን ያዳበርክለት፣ ኪነቱን ያጎላህለት እና የኅብረተሰብ አገልግሎት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል የሰጠኸው ህዝብ (የግለሰብ እና የማህበራዊ ተቋማት ስብስብ) “ውይ!” ብሎ ከንፈሩን እንደ ጡጦ መጥጦ “ዋ እንደርሱ እንዳትሆን” እያለ ለራሱና ለቤተሰቡ መማሪያው ያደርግሃል እንጂ ለአንተ ምንም አይፈይድልህ፡፡ ምክንያቱም እንደ ኅብረተሰብ ገና ህፃን ልጅ ነው አሁን ያለው ኢትዮጵያዊ ስብስብ፡፡

ይህን የምልህ አንድ ልመንህ ታደሠን ዋቢ አድርጌ ብቻ እንዳይመስልህ፡፡ በርካታ ለኅብረተሰቡ አገልግሎት የሰጡ ሰዎችን ከሠፈሬ፣ ከአካባቢዬ ልጠራልህ እችላለሁ፣ ዳሩ ግን አንተ እነርሱን በጉልህ አታውቃቸውም፣ እኔ ጸሐፊውና የአካባቢዬ ሰዎች ብቻ ነን የምናውቃቸው፡፡ አንተ እና በዙሪያህ ያሉ ሰዎች የምታውቋቸው እኔ የማላውቃቸው ለኅብረተሰቡ ብዙ የሰሩ ሰዎች እንደሚኖሩም እገምታለሁ፡፡

ስለዚህ በጋራ በምናውቃቸው ሰዎች ብቻ ለመጨዋወት እንሞክር ካልከኝ ደግሞ አንሙትን ታውቀው የለ? ምነው አንሙት ያ አጭሩ

ባለዋሽንት የጊሽ አባይ ኪነት ቡድን ጥበበኛ፣ አዎን እንዴት እርሱን ታጣዋለህ- ውለታ መብላት ነው የሚሆንብህ፤ ከድምፃዊያን ይሁኔ በላይ እና ሰማኸኝ በለው ጋር “አንቱየዋ እነርሱ እኮ ልጆች ናቸው፣ ይጫወቱ በጊዜያቸው” ሲል በሙዚቃዊ ድራማው ላይ የሚያቀነቅነው ባለዋሽንቱ እረኛ! ይኸውልህ ከጥቂት ዓመታት በፊት እርሱም በኑሮ ደህይቶና ተደብቶ ሸራተን ፊት ለፊት ላስቲክና ማዳበሪያ ዘርግቶ ተቀምቶ ነበር፡፡ ለነፍሴ ያሉ አበውና እመው ዳቦ እና ጣሳ ውሃ ሲሰጡት በእርሱ የጥበብ በረከት ሲዝናና እና ሲጨፍር የነበረው ኅብረተሰብ እና የማህበረ ፖለቲካው ሊቃውንት በማርሴዲስ መኪና ፍስስ እያሉ ወደ ሸራተን ሆቴል ሲገቡ የለበጣ ፈገግታቸውን እያሳዩት በበላይነት መንፈስ እየተኮፈሱበት ያልፉ ነበር፡፡

አብረውት ከልጅነት እስከ እውቀት የተጠበቡት ጥበበኞች ዝና እና ገንዘብ እንደ አሸን ባፈሱበት በዚያ ወቅት እንኳ ለእርሱ ጠብ ያደረጉለት ነገር አልነበረም፡፡ በመጨረሻ እራሱን እየገዛ እየተነቃቃ ሲመጣ ግን እንዲህ አድርጌለት ነበር፣ እምቢ አለኝ እንጂ እንዲህ ላደርግለት አስቤ ነበር፣ ቅብርጥሶ እያሉ ሞራል በሚያንሳቸው አንዳንድ መጽሔቶች ሞራላቸውን ሊያነቃቁ ሞከሩ፡፡

እሺ ወዳጄ ደግሞ በሌላ ሰው ታሪክ ልሰልስህ፤ ደራሲና ተርጓሚ ህሩይ ምናሴን (አውግቸው ተረፈ) ታውቀዋለህን? እርሱም እንዲሁ አበደ ተብሎ ከአደባባይ ወድቆ የእርሱን ማበድ ሳይሆን የእኛን የማኅበረሰቡን ማበድ እና ሞራል ማጣት ገሃድ አውጥቶብን ነበር፡፡ አንድን ሰው በማህበረ-አገልግሎት ዘመኑ እንደ ሸንኮራ ምጥጥ አድርገን ተጠቅመን እንደማናችንም አንዳች የህይወት ውጣ ውረድ ሲገጥመው ግን ምጣጩን ገለባ ብለን አደባባይ እንጥለዋለን፡፡ ምንም ውለታ እና ባለዕዳነት እንኳ አይሰማንም-እኔ፣ አንተ እና ኅብረተሰቡ ወዳጄ፡፡

ጸሐፊ እና ጋዜጠኛ ሰለሞን ሙሉ ታፈሰንም እንዲሁ ከትውስታህ ትስተዋለህ ብዬ አልጠረጥርም-ወዳጄ፡፡ ይኸው ያን የመሰለ ጸሐፊ የኑሮ ውጣ ውረዱ ላይ የእኛን የወደቀ ላይ ምሣር ማብዛት ጨምረንበት አደባባይ ከወረወርነው ዓመታት አለፉ፡፡ እዚህ ጊዮርጊስ አደባባይ ላይ ተቀምጦ ዘወትር ይታዘበናል፡፡

ትላንት ቤቱ እየተመላለሱ ተልካሻ የጥበብ ሥራቸውን እንዲያቃናላቸው አድርገው ስማቸውን የገነቡ የጥበብ ነጋዴዎች ሁሉ ዛሬ በመኪና “ሰላም ነሽ ሰሌ” እያሉ ያልፉታል–እነርሱ ጥበብን ስለነገዱ አተረፉ፤ እርሱ ነጋዴ ባለመሆኑ አበደ ተባለ፣ አለቀ በቃ!

የሰለሞንን ብዕር ያልተጋራ እና ትሩፋቱን ያልተጠቀመበት የያን ጊዜው የኪነት ሰዎችና የማስታወቂያ ባለሙያዎች የሉም ለማለት እደፍራለሁ – ካለኝ መረጃ፡፡ ግን ዛሬ እነርሱም የእርሱ የገንዘብ ተጠቃሚዎቹም ሆኑ እኛ የጥበብ በረከቱን ያጣጣምን የኅብረተሰቡ አባላት በእርሱ የጎዳና ሕይወት የኛን የበላይነት እያሳየን ምንም ሳንፈይድ ባለዕዳነታችን ሳይሰማን እንደ ከብት በሃያ አንደኛው ክፍለዘመን የጦጣ ኑሮ እንኖራለን፡፡

ዘሪቱ ጌታሁን

ወዳጄ ከቀድሞዎቹ ሰለባዎች ዋቢ ከፈለክ ደግሞ ድምፃዊቷ ባለ-ክራር ሜሪ አርምዴን ታማ ቤቷን ዘግታ ስትቀመጥ የገጠማትን ወደ ኋላ ሄደህ አስታውስ፡፡ ሰሞኑን ደግሞ በመረዋ-ተርገብጋቢ ድምጽዋ “እንቁጣጣሽ … እንቁጣጣሽ …” እና “ትዝታን በፖስታ ልኬልሃለው፣ መልሱን በቶሎ እጠብቃለሁ” እያለች የምታዜመው ዘሪቱ ጌታሁን ታማ ሐኪም ወደ ውጭ አገር ሄደሽ ካልታከምሽ በሕይወት የምትቆዪው ለአንድ ዓመት ብቻ ነው ብሏት ቤቷን ዘግታ ተቀምጣለች፡፡

በቃ ዘጠኝ ሞት መጣ ቢሉት አንዱን ግባ በለው ዓይነት ማለት ነው የእርሷ ቆይታ፡፡ ወዳጄ አንተን ማስደበር እንዳይሆንብኝ እንጂ ሌሎች በርካታ የታዋቂ ሰዎችን ዋቢ ታሪክ እያነሳሁ ባወጋህ በወደድኩ፤ ግን ስንቱን አንስተን በማውራት ስንቱን የኅብረተሰብ አባላት አስቀይመን እንችለዋልን፡፡ ያ የጥበብ አውራ ልመንህ ታደሰ እመር-እመር እያለ በመራመድ የሚለክፉትን “ፍንዳታዎች” እና የሚያሽሟጥጡትን ሽማግሌ-“ግንባታዎች” የመልስ ምት እየሰጠ፤ በአንድ ብር ምጽዋት ሊያልፉት የሚፈልጉትን ቁንን ሰዎች ሁለት ብር የመልስ ምት እየሰጠ፣ ገንዘቡን እየበተነ ያልፋል፡፡

እኔም ጸሐፊው ከኋላው እከተላለሁ-ጅል ታዛቢ ሆኜ፡፡ ሲኒማ አምፔር ጋር አንድ ትልቅ ሰው አስቆሙትና እጁን ይዘው “ልመንህ ምነው እንዲህ ራስህን ጣልክ አሉት?” ሀዘኔታ በሚታይበት የፊት ገፅታ፡፡ እርሱ በባይንደር መሳይ ነገሩ የያዛቸውን ወረቀቶች እንዳይነጥቁት በመስጋት ይመስላል በአንድ እጁ ደረቱ ላይ ለጥፎ ለምን አትተወኝም እኔ ማናችሁንም አልፈልግም፣ ተጣልቻችኋለሁ አላቸው፡፡ ሰውየው ሳቃቸው መጣ፡፡ ሌሎች ብዙ ሰዎች ከበዋቸው ቆሙ፡፡ ልመንህ ተቆጣ፡፡ እጁን አስለቅቆ የአራት ኪሎን መንገድ ያዘ፡፡ አስፋልት ዳር ለነበሩ የጎዳና ተዳዳሪዎች የያዘውን አንድ-አንድ ብር ሣንቲም እንዳለ ለገሳቸው እናም እየሳቀ ከራሱ ጋር እያወራ ነጎደ፡፡

ይህ እየሆነ ያለው ተመሳሳይ ክንፎች ያላቸው ወፎች በጋራ ይበራሉ በሚል ብሂል ለመረዳዳት የተሰባሰቡ የሙያ ማህበራት ባሉበት ሀገር ነው፡፡ የደራሲያን ማህበር፣ የሴት ደራሲያን ማህበር፣ የኮሜዲያን ማህበር፣ የሙዚቃ ማህበር፣ የተውኔት ባለሙያዎች ማህበር፣ የፊልም ባለሙያዎች ማህበር፣ የፕሮዲሰሮች ማህበር፣ የ … ማህበር ባሉበት ሀገር ነው፡፡ አየህ ወዳጄ ሀበሻ አበሻ ነው፡፡ ግለሰብ ሆነ ኅብረተሰብ፣ ተቋም ሆነ ዳያስፖራ (በውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊ) በዚህ ረገድ የሚፈይደው በጎ ነገር የለም፡፡

በቅርቡ ከአሜሪካ አገር ለእረፍት የመጣ ጓደኛዬ ድምጻዊ ቴዎድሮስ ታደሠን በአንድ ቅዝቅዝ ባለ ሀበሻ ሬስቶራንት ውስጥ ሲዘፍን እንደተመለከተው በኩራት ነግሮኝ እዚህ እንደ ታምር የምናያቸውን ድምፃዊያን እዚያ በአንድ ቢራ በቅርብ እንመለከታቸዋለን አለኝ፤ ልመንህ ታደሠን ጨምሮ፡፡ አሜሪካ ሁላችንንም እኩል አድርጋናለች፤ ይህንንም ለእከሌ ድምፃዊ ድሮ እኮ ሀገር ቤት እንደ ብርቅ ነበር የማይህ፣ እዚህ ግን እንደዋዛ አገኘሁህ ብዬ ነግሬዋለሁ በማለት ሥለ-ብርቅዬዎቻችን ምንምነት ሲነግረኝ በእነርሱ ሥነ-ልቦና ላይ ስላሳረፈው አሉታዊ ጠባሳ (Trauma) ምንም አልተጨነቀም ነበር፡፡

በአንፃሩ ሌሎች አገራት ታዋቂ ሰዎቻቸውን የአርዓያነት ሚና በኅብረተሰብ ውስጥ ስለሚያጫውቷቸው ለታዋቂ ሰዎቻቸው እንክብካቤያቸው የላቀ ነው፡፡ ከእነዚህ ታዋቂ ሰዎች ጀርባ ባሕላቸው፣ ቋንቋቸው፣ እሴታቸው እና ባንዲራቸው መኖሩን ለደቂቃ አይዘነጉትም፡፡ እንግሊዛውያን ከሼክስፒርም፣ ከቻርልስ ዲከንስ-ም ሆነ ከእግር ኳስ ተጫዋቾቹ ቤካም እና ሩኒ ጀርባ ታላቋ እንግሊዝ መኖሯን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ በተለይ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን፡፡ እናም ለታዋቂ ሰዎቻቸው ይጠነቀቃሉ፡፡ የሰዎቻቸውን አያያዝ ያውቃሉ፡፡

በእንግሊዝ አገር ውስጥ ለጥበብ ሰዎቻቸው፣ ለጸሐፊዎቻቸው፣ ለጋዜጠኞቻቸው እና ለኅብረተሰቡ ምርምር ለሚያደርጉ ሰዎች በኑሮ ውጣ ውረድ ውስጥ ሰጥመው ለኅብረተሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎት እንዳይገቱ “አርት ሬዝደንስ” የተባለ ተቋማዊ አገልግሎት አላቸው፡፡ ቢታመሙ ያሳክሟቸዋል፣ ቢቸገሩ መፍትሄ ያመላክቷቸዋል፡፡

ይህ ዓይነቱ የአገልግሎት ተቋም በለጋሽ ግለሰብ፣ ድርጅቶችና በመንግሥታዊ ድጎማ የሚንቀሳቀስ ሲሆን የሥራውን እቅድ አቅርቦ ተቀባይነት የሚያገኝ ጥበበኛ እንደ ተፈቀደለት ጊዜያት ለሁለት ሣምንት፣ ለወራት፣ ለአንድ ዓመት እና ለሁለት ዓመት ለኑሮ የሚያስፈልጉ ነገሮች ሁሉ በተቋሙ ቀርቦለት የጥበብ ሱባዔ ይገባል ማለት ነው፡፡ እቅዱን ተግባራዊ እንዲያደርገው፡፡

አየህ ወዳጄ አርት ሬዝደንስ የተባሉት ተቋማት ጥበብን የማዋለድ ሥራ ይሰራሉ፡፡ የዚህ ጸሐፊ ጓደኛም የሦስት ወር አገልግሎት ተሰጥቶት ተግባራዊ ማድረግ ተስኖት የነበረውን ጥበባዊ ክህሎቱን ባህር ተሻግሮ ተወጥቷል፡፡ ወደ እንግሊዝ የመብረሪያውን የአየር ትኬት፣ የምግብና የመኝታ አገልግሎቱን እና የቀን ተቀን የኪስ ገንዘቡን ሁሉ ሰጥተው ነበር በውስጡ የታመቀውን ኪነት ያዋለዱት፡፡

አስተውለህ ከተመለከትክ በአፍሪካ ግብፅ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ቡርኪናፋሶ በመሳሰሉ አገራት ትልልቅ ፋውንዴሽን አሉ ለኅብረተሰባቸው አገልግሎት የሰጡ ሰዎች የህይወት ዕክል ሲገጥማቸው ሊያቃኗቸው የሚተጉበት፡፡ እዚህ የእኛ ሀገር ኢትዮጵያ ግን ምንም እንኳ የሦስት ሺህ ዓመት እንደ ሀገር የመቆም ታሪክ ቢኖረንም፣ ምንም እንኳ የቀደምት ሥልጣኔና ጥበብ ባለቤቶች ብንሆንም እንደ አንድ ኅብረተሰብ ገና በቅጡ አላደግንም፤ ገና ህፃን፡፡

በየዘርፉ ያገለገሉ አርዓያ ሰዎቻችንን የህይወት ውጣ ውረድ ሲገጥማቸው ቀና ልናደርጋቸው ከመጣር ይልቅ ቁልቁል ገደል ልንከታቸው እንረባረባለን፡፡ ታመው ከማሳከም ይልቅ ሞተው እናለቅስላቸዋለን፡፡ እንደ ልመንህ ታደሠ ያሉትን ወደ ሆስፒታል ወስደን ወደ ጤናቸው እና የመረጋጋት ህይወት ከመመለስ እና ብሄራዊ ክብራችንን ከመጠበቅ ይልቅ በጎዳና ከንፈር እንመጥላቸዋለን፡፡

አየህ ወዳጄ መፍትሄው እዚሁ ጉያችን ሥር አለ፤ የአእምሮ ህክምና አገልግሎት የሚሰጥባቸው ሆስፒታሎች አሉ፣ በዘርፉ ስፔሻሊስት ሐኪሞቹ አሉ፣ መድሃኒቶች አሉ ነገር ግን ይህን አቀናጅቶ ለእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ አገልግሎት የሚሰጥ የተደራጀ ተቋም የለንም፡፡ እናም ያላደገ ኅብረተሰብ ነን ያልኩት ለዚህ ነው፡፡ ያላደገ ኅብረተሰብ ያደጉ ግለሰቦቹን እንደ ድመት ካለማወቅ ወልዶ ይበላቸዋል፡፡

ስለዚህ ውጤቱ አንቺም- ዜሮ- ዜሮ፣ አንተም ዜሮ- ዜሮ፣ እርሱም ዜሮ ዜሮ፣ ሁላችንም ዜሮ ሆነ፡፡ ወዳጄ ታዋቂው ኢትዮጵያዊው ኮሜዲያን ልመንህ ታደሠ በአደባባይ ብቻውን ሲጋልብ በርቀት ይታየኛል፡፡ ለእርሱ የሰጠነውን ኅብረተሰባዊ ምላሽ የተመለከተ ዕጩ ጠቢብ በአገልግሎት መንፈስ ጥበብን ያጋራን ይመስልሃል? ይልቅ ጥበብን ይነግድብሃል!!

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Social Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Comments

  1. ሳተናው says

    December 8, 2012 03:20 am at 3:20 am

    እጅግ በጣም የሚያሳዝን ነው:: ያስለቅሳል::

    Reply
  2. በለው ! says

    December 8, 2012 06:52 pm at 6:52 pm

    “አንዱ በአንዱ ሲስቅ ጀምበር ትልቅ” አሉ….
    ለመሆኑ ያላበደው ማነው ? ማን በማን ይስቃል? ማንስ ማን ይረዳል? ሁሉም እረጂ ያሰፈልገዋል። የዚህን ጽሑፍ አቅራቢ ምስጋናዬ ይድረስዎ! “ውለታ የማታውቅ ሀገር!” አንዳንድ የመንገድ ጠቢባን የአሜሪካ ፕሬዜዳንት ያሉት ለእኛም ነው ብለው ካልተሞላፈጡ በቀር የሀገሩ ዜጋ ሙሉ መብት እና ድጋፍ ሊያገኝ ግድ ይላል።”ለሀገሬ ምን አደረኩላት እንጂ ሀገሬ ምን አደረገችልኝ አትበል!”ይህ አባባል የተነገረው እንደ እኛው ሀገር ዲአስፖራ (ፈላሽ) ሞልፋጦች ባንኮኒ ላይ እያደሩ ዘፋኙን በአንድ ቢራ አዘፍነዋለሁ ለሚሉት ነው።ሠርቶ ግብር መክፈል፤የጤናና የሕይወት ኢንሹራንስ፤ወለዶ ከብዶ ጥሩ ዜጋ እንዲሆን የሚያበረታታ መልዕክት እንጂ “የምትኖረው ለሀገርህ እንድትሠራ እንጂ ለአንተ እንድትኖር አደለም ማለታቸው እንዳልሆነ ብዙ ሰዎች በመልዕክቱ ግራ ይጋባሉ። በአሜሪካ እና በሌሎች በአደጉ ሀገሮች የሚደረግ የዜጋ እንክብካቤ በማልቀስ! በመናደድ! ብቻ የሚፈታ ሳይሆን መሳሪያ አንስቶ የሚያታኩስ ነው።አዎን አነኝህን ከያኒያን, ጠቢባን, ደረሲያን, ኮመዲያን, አዝማሪዎችን ሁሉ ሥቀንላቸዋል፣ ተዝናንተንባቸዋል፣ ጊዜያችንንም አሳልፈንባቸዋል፣ውበት እና ተድላቸውን አረፍታቸውን ነስተን እኛ አርፈንባቸዋል ዛሬ ሲደክሙ ሲታመሙ ሲበሳቆሉ ሲራቡ ሲጠሙ እንሳለቅባቸዋለን ? ? አንድ ሀገር ራዕይ ሳይኖረው… መብላት፣ መጠጣት፣ መዳራት ፣መተኛት፣ መነሳት፣ መስረቅ፣ ‘ባሕል እና ወግ’ ሲሆኑ ህዘብ አርዓያ የሚሆን መንግስት ሲያጣ ሐዝብ ባሕል፣ ቋንቋ ፣ሓይማኖት፣ ሲበርዝ (ሴት እና ሕፃናት) ዜጋ፣ መሬት፣ ሲሸጥ ‘በግሎባላይዜሽን’ ሲሞላፈጥ (ጉልቤ- አይዜሽን፡ የአንድን ሀገር ውስጠ ሚስጥር ማወቅ) (ግልብ-አይዜሽን፡ ያነድን ሀገር ቋንቋ፣ሃይማኖት፣ባሕል ትውልድ መበረዝ፣ስንደቅ እና ዳርድንበር ማጥፋት)
    ታዲያ ማን? ለማን? ነው የሚረዳው በየትኛው ባህል ነው አዲሱ ትውልድ የሚታነፀው? እነዴትስ ይቺ ሀገር የመተዛዘን፣ የመከባበር ፣ጥንታዊ ባሕልና ወግ ትመለሳለች እጅግ በጣም አስፈሪ አሳዛኝ ዘመን እና ትውልድ ከጋጠ-ወጥ አመራር ጋር ሁለንተናዊ ተሐድሶ ያስፈልገዋል ቀደም ብዬ ከታዘብኩት….እርስዎም ደግመው ይመልከቱ….
    http://www.diretube.com/diretube-exclusive/a-abreham-asmelash-needs-your-help-video_51f920c4f.html “መለስ አዝማሪ አደለም” በተስፋዬ ገብረአብ ፅሑፍ ላይ ከሰጠሁት አስተያየት የተወሰደ።

    Reply
  3. Jobii says

    December 8, 2012 10:41 pm at 10:41 pm

    Lib yemineka asazagn. Talak artist neber. Min indagegnew tinish mabrariya setehen bihon tiru neber. Anyhow, betam azignalehu

    Reply
  4. አ.በ. says

    December 9, 2012 05:04 am at 5:04 am

    የአእምሮ መታወክ የደረሰበት በምን የተነሳ ነው? ማለቴ ሊድን የሚችል የአእምሮ መታወክ ችግር አለ፣ በህክምና ሊድን የማይቸልም ደግሞ አለ። የሚታከምበት ወይም ቢያንስ ተገቢውን ክብካቤ ሊያገኝ ቢችል?

    Reply
  5. beaty kassa says

    December 9, 2012 10:43 am at 10:43 am

    wede zehafe, zehufehe kabade melekete alewe. wanawe kume negere , endate eneredada newe.

    Reply
  6. muya be lib neew says

    December 9, 2012 05:50 pm at 5:50 pm

    ወገን ከ ልመንህ ታደሰ ጋር ተምሬአለሁ ጎበዝ አስቂኝ ሰው ነው፡ያለ ቃላት በአመለካከት ብቻ ያስቃል፡፡
    ህመሙ ግን ለእኔ አዲስ ነገር ነው፣ ያሳዝናል ወንድሜ እንዳልከው ሆስፒታል ገብቶ ማሳከም የእኛ ግዴታ ነው ብየ አምናለሁ፡፡
    ተሰባስበን እንርዳው!!!

    Reply
  7. nebi says

    December 11, 2012 03:09 am at 3:09 am

    ያሳዝናል! ግለሰብ ግለስብን ሊገል ይችላል:: የተለመደ ነው:: ማህበረሰብ የሃገሪቱን ጉምቱ _ ጉምቱ የጥበብ ሰዎች: በማንኛውም የስራ ዘርፍ ዕድሜ ልካቸውን ሲያገለግሉ የነበሩ ዓውደ ሰብኦችን ዕርዳታ ሲፈልጉ መርዳት ባይሞከር: በውድቀታቸው ማላገጥ ከተያዘ ያቻ አገር መሞት ጀምራለች:: እንዴህ በምኑም_ በምኑም የወደቀ አገር የባህል እና የፖለቴካ ኣብዮት እንደሚያስፈልገው እሙን ነው:: ቁም ነገሩ ኣብዮቱን ማን ያምጣው ነው? ፍልስፍና የሌለን ህዝቦች: ፍልስፍና ያለው መሪ የተነሳን ህዝቦች:ፍቅር የተነፈግን ህዝቦች:: ለነገሩ ያልተዘራ ኣይበቅልም:: ይልቅ ጽሁፉን ሳነብ በጎዳና ተዳዳሪዎች ቀናሁ:: እኔያ የህብረተሰብ መተላለፊያ ኣዘቅት ላይ የበቀሉ ትሎች: ማህበረሰቡ የነፈጋቸውን ፍቅር እርስ በእርስ ሲለጋገሱ ማየት ያስደምማል ። ሌላማ ማን ለእነሱ ከእነሱ በላይ ኣላቸው!!

    Reply
  8. bibi says

    December 11, 2012 10:30 am at 10:30 am

    I don’t know the name of the writer of this piece but he has got a good writing skill. Yes, we’re lip service specialists !!!

    Reply
  9. koster says

    December 11, 2012 01:44 pm at 1:44 pm

    The list will be long, as long as woyane ethnic fascists are dismantelled there will be more or these kinds of these people, none of these are Tigrians but even Tigrians could be a victim of these home grown fascists if they do not conform to the looting and killing of these home grown fascists. The solution is to unite and say no to these home grown fascists.

    Reply
  10. MYS says

    December 13, 2012 01:44 am at 1:44 am

    What a writer! It is such a heart-touching story. Who is going to bring us together for such a cause? We lost trust among ourselves and as a result couldn’t get organized. Unless there is some sort of organized group, nobody can be helped be it a celebrity or a commoner.

    Reply
  11. አበጄ says

    December 13, 2012 03:36 am at 3:36 am

    -አስተያየቴን በሌላ ጊዜ ላርገዉ አሁን በጣም ኢሞሽናል ስለሆንሁ ኢሞሽናል ሁኘ የምሰጠዉ አስተያዬት የእኔን ኢሞሽን ከማስወጣት ዉጭ ጠቃሚ ላይሆን ይችላል።

    Reply
  12. tola says

    December 19, 2012 08:46 am at 8:46 am

    We are a society that consider mental disease as a taboo, it is a mistake taking Lemenh back to Ethiopia he could have gotten a special treatment in US as any other individual. We all have to contribute to help our people even those who laugh and make fun of Limeneh are crazy Mental health issue is assoicated with evil

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • “አስደንጋጭ”! 1 ሚሊዮን ከሚጠጋ ተፈታኝ ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገባው 30 ሺህ (3.3%) ብቻ ነው  January 27, 2023 09:11 am
  • የማይዘነጋዉ የኢትዮጵያዊያኖች የጀግንነት ተጋድሎ ታሪክ፡- ኮሎኔል ባጫ ሁንዴ (ታጠቅ) January 27, 2023 06:12 am
  • ጎርጎራ – የመጻዒው ዘመን ሙሽራ! የዉበት ፈርጥ! January 17, 2023 04:18 pm
  • ሁለተኛው መስቀል አደባባይ January 17, 2023 04:13 pm
  • በአቡዳቢ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን January 17, 2023 04:08 pm
  • በንፋስ ስልክ ላፍቶ ስምንት የመሬት ሌቦች ተያዙ January 16, 2023 11:36 am
  • ሺሻ ሲያስጨሱ በተገኙ ሆቴሎችና የምሽት ጭፈራ ቤቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ January 16, 2023 08:50 am
  • በሐሰተኛ መታወቂያ የደኅንነት አባል ነን ብለው ሲያጭበረብሩ የነበሩ ተያዙ January 13, 2023 02:03 pm
  • ተሽከርካሪ ወንበር ለትግራይ – “ናይ ኣካል ጉዱኣት ተሽከርካሪ ዘለዎ ወንበር” January 12, 2023 07:17 pm
  • የአማራው ኩራት፣ የኢትዮጵያ ዘብ፣ የትህነግን ቅስም ሰባሪ! January 12, 2023 04:00 pm
  • በኢትዮጵያ ላይ የተጣሉ ማዕቀብ እና ሌሎች አስገዳጅ ሕጎች ሙሉ ለሙሉ ተሰረዙ January 12, 2023 01:52 pm
  • የቻይና ዕዳ ስረዛ “Payday Loan Diplomacy” ወይስ ኢትዮጵያን ያዳነ ተግባር? January 12, 2023 11:00 am
  • የአዲስ አበባ አስተዳደር ከቋንቋ ጋር በተያያዘ ውሳኔ አስተላለፈ January 12, 2023 10:46 am
  • “አምባሳደሩ” የቀድሞ ጌቶቻቸውን እንዲያቋቁሙ ተሾሙ January 11, 2023 03:47 pm
  • መከላከያ ሸኔን የሚዋጉ ሚሊሻዎችን አሠልጥኖ አስመረቀ January 10, 2023 05:37 pm
  • በሰባት ተጠርጣሪዎች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ January 10, 2023 03:36 pm
  • የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አቅጣጫ January 6, 2023 03:26 pm
  • “ከዕብሪቱ አስተንፍሰነዋል” – ኢሳያስ January 2, 2023 07:29 pm
  • [ኢትዮጵያን] “አስታክኮ ኤርትራን መውጋት ለሚፈልግ ኃይል አንተባበርም” January 2, 2023 07:11 pm
  • የ፰ ወር ሕጻንና ጨቅላ ወንዶች የሚደፈሩባት ትግራይ December 14, 2022 02:49 pm
  • “ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው” የደጎች አውራ የመቄዶኒያው ቢንያም በለጠ December 14, 2022 09:59 am
  • “የሀብት ምዝገባ መረጃው ለሕዝብ ክፍት ይደረግ “ December 13, 2022 10:30 am
  • የኢትዮጵያ ዓለምአቀፋዊ የሌብነት ደረጃ December 13, 2022 09:42 am
  • ለብረት አቅላጮች ለመሸጥ በኤሌክትሪክ የብረት ማማዎች ስርቆት የ100 ሚሊዮን ብር ኪሳራ December 13, 2022 09:26 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2023 · Goolgule