
ለፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ
ዋይት ሐውስ
1600 ፔንሲልቫንያ አቬኑ ሰሜን ምዕራብ
ዋሽንግቶን ዲሲ 20500
የተከበሩ ፕሬዚደንት ኦባማ፤
ይህንን ደብዳቤ የምጽፍሎት በኢትዮጵያ ውስጥያለውን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ላሳውቆት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ተጎዳን፣በደል ተፈጸመብን በማለት የሚያሰማውን አቤቱታ፣ ህጋዊ ጥያቄዎችንና ሠላማዊ ሰልፎችን ሁሉ መንግሥት ከማዳመጥ ይልቅ ጉልበትንና ኃይሉን ሁሉ እንደሚጠቀም ያውቃሉ ብዬ አምናለሁ።
ይህ ሁኔታ ባግባቡ ካልተያዘ በሀገሪቷና በአካባቢው ሁሉ ያልተጠበቀና አስከፊ ሁኔታ ሊከሠት ይችላል።የኢትዮጵያና የዩናትድ እስቴት አሜሪካ ግንኙነት ከ1903 ጀምሮ እንደሆነ ይታወቃል። ስለዚህ የንግድና የወዳጅነት ውል ተፈራርመው ኢትዮጵያም ጥብቅ ወዳጅ ተብላ ትታወቅ ነበር። ኢትዮጵያ በአፍሪካ አብላጫውን የአሜሪካን ረድኤት እንድታገኝምሆኗል። በአጸፋው ኢትዮጵያም የአሜሪካ ወዳጅ በመሆን በዓለምና በአካባቢው ሁሉ ሠላምና መረጋጋት እንዲኖር ከኮሪያ ጦርነት ጀምሮ አስተዋጽኦ አድርጋለች። አሁን በቅርቡ በተከሰተው የአገር ውስጥ ችግሯ ኢትዮጵያውያንና ለኢትዮጵያ ቀና አመለካከት ያላቸው ሁሉ ዩናይትድ እስቴት አሜሪካ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን መቆም እንዳለባትና የኢትዮጵያንሕዝብ በመከፋፈልና ሰብዓዊ መብቶችን በመርገጥ ከታወቀ መንግሥት እራሷን ማራቅ አለባት ይላሉ።
በቅርቡም አንዳንድ ተቋማት እንደ አመንስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂዩማን ዋች ያሉትና የዩስ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሥሪያቤት እንደዘገቡት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ አስጊ ደረጃ መድረሱን ዘግበዋል። ምንም እንኳን የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና የከፋፍለህ ግዛ ተግባሩን ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ማካሔዱ የታወቀ ቢሆንም አሁን ግን የኢትዮጵያ ህዝብ በቃኝ ከማለቱም በላይ ግፍ የሚሸከምበት ጫንቃ ከእንግዲህ ወዲህ የለኝም በማለት ሥርዓቱን በሰላማዊ መንገድ እየታገለው ነው።
ከዚህ በታች የኢትዮጵያ መንግሥት በሕዝቡ ላይ የሚያደርሰውን ኢዲሞክራሲያዊና ግፍ ለዋቢነት ላቅርብ፦
፩) በተከታታይ የምርጫ ውጤቶች ተጭበርብረዋል፣ የተቃዋሚ ድርጅቶች መሪዎች፣ ጋዜጠኞችና የመንግሥትን ኢዲሞክራሲያዊ ፖሊሲዎችን የሚተቹ ለእስር ተዳርገዋል። በ2009 መንግሥት ሕዝባዊ ድርጅቶችን የሚገድብ ህግ ደንግጓል። ይህ ህግ ሕዝባዊ ድርጅቶችን፣ ሰብዓዊመብቶችን ለማስጠበቅ የቆሙትንና ተቆርቋሪ ድርጅቶችን አሽመድምዷቸዋል። የአገሪቷ ህገ መንግሥት በሚፈቅድላቸው መሠረት የመንግሥትን ብልሹ ተግባር በይፋ የሚቃወሙ ሁሉ ለኢላማ ተዳርገዋል፣ ተጉላልተዋል፣ ለእስር ተዳርገዋል። ስለዚህም እስር ቤቶች ውስጥ ታጉረው እስርቤቶች ጢም ብለው ሞልተዋል። የሚያሳዝነው በቅርቡ የቂሊንጦ ማጎሪያ በአብዛኛው የፖለቲካ እስረኞች በታሰሩበት ወህኒ ቤት የከፋ የእሳት ቃጠሎ አጠያያቂ በሆነ ሁኔታ ተነስቶ ነበር። ከነበልባሉ ሊያመልጡ የሞከሩ እስረኞች እስር ቤቱን ለመጠበቅ ማማ ላይ ባሉ ዘበኞች ተገድለዋል። ስለዚህ በመንግሥት ቁጥጥርና ከለላ ውስጥያሉት እንኳን ሳይቀሩ በአሳዛኝ ሁኔታ ተገድለዋል።
፪) አገሪቱ ላለፈው አንድ ዓመት በኦሮሞ ክልል በተነሳው ሁኔታ እየተናጠች ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ህጋዊ የሆነና ከቀዬቻቸው በቂ ምክንያት ተነግሯቸውና ተግባብተው የተፈናቀሉ ሳይሆኑ እንዲሁም ለንብረታቸው ተመጣጣኝ የሆነ ካሣም ተከፍሏቸው አይደለም። ተፈናቃዮች ትምህርት ቤት፣ ህክምና ቤትና መሠረታዊ የሆኑ ሁኔታዎች እንደሚሟላላቸው ቃልቢገባላቸውም ይህ ባዶ ተስፋ ሆኖባቸዋል። በአንጻሩ ተፈናቃዮች በቀን ከአንድ ዶላር ያነሰ እየተከፈላቸው ለቀን ሠራተኛነት ተዳረገዋል። ለከብቶቻቸውም የሣር ግጦሽና ውሃ እንኳን ተነፍጓቸዋል።
፫) በቅርቡ በአማራው አገር በጎንደር የተከሰተው ሁኔታ ሆን ተብሎ የወልቃይት ጠገዴን አካባቢ ወደ ትግራይ ግዛት፤የገዢው ክፍል ክልል ውስጥ የማጠቃለል ሁኔታ ነው። የአገሬውም ሰዎች ሆኑ በቀድሞው በአፄው ዘመን አስተዳዳሪ የነበሩት እንደሚሉት ወልቃይት ጠገዴ ትግራይን ከማዋሰን በስተቀር የትግራይ አካል ሆኖ አያውቅም ይላሉ። በታሪክ ግን ትግርኛ ተናጋሪዎች ለሥራ ፍለጋና የተሻለ የኑሮ እድል ፍለጋ በማለት ወደ ወልቃይት ጠገዴ ይመጡ ነበር። አንዳዶቹም እዚያው ኑሮ መስርተው ከአገሬው ሰው ጋር ተጋብተው ሁለት ቋንቋ እየተናገሩ በሰላምመኖር ጀመሩ። ይህ በኢትዮጵያ ሁሉ የተለመደ ነው።
፬) እራሱ የትግራይ ክልል አንድ ትልቅ ወህኒ ቤት ሆኗል። የሕዝብ ድምፅ ታፍኗል፤ ነፃነቱንም ተገፏል።
፭) የህወሃት መጥረቢያ እንዲሁ በሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ በሚገኙት ቀይባህርን የሚያዋስኑ በነበሩት በአፋር ህዝብ ላይ አርፏል። አፋሮችም ከመንግሥት ጋር እየተናነቁ ነው። ምክንያቱም ክልላቸውወደ ትግራይ እየተዋጠ ሲሆን በግዛታቸም ውስጥከጥቅም እየተገለሉ የበይ ተመልካች ሆነዋል። ይህ ሁኔታና የመንግሥት ጎጂ ፖሊሲ በኢትዮጵያ ሁሉ እየተከሰተ ሲሆን ህዝቡም እምቢተኝነቱን እያሳየ ነው።
፮) ምናልባት ታላቁ የመንግሥት ወንጀል በ1991 ዓ.ም. መጀመሪያ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ህዝብን ከህዝብና ያንዱን ሃይማኖት ተከታይ ከሌላው ሃይማኖት ተከታይ ጋር የማጋጨት ተግባሩ ሲሆን እየከፋፈለ እሱ ብቸኛ የበላይ ሃይል ሆኖ ለመቅረት ያደረገው ደባ ነው። ይህ መንግሥት እንደ መንግሥት በህዝብና በሃይማኖቶች መሃከል አቀራራቢ ድልድይ መዘርጋት ሳይሆን ተግባሩ የራሱን ጠባብ ጥቅም ለማስጠበቅ ብቻ የቆመ ነው።
፯) ብዙ የተለፈፈለት የኤኮኖሚዕድገት የሚባለውም የመንግሥት ባለሥልጣናትና ባለሟሎቻቸው ብቻ ጠቀመ እንጂ ለብዙኃኑ ህዝብ ይህን ያህል አልረባም። አንዳንዶቹም በአግባቡና በህጋዊ መንገድ የከበሩ አይደሉም። የህውሃት የንግድ ተቋማትም የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት በበላይነት ጨምድደው ያለተፎካካሪ ይዘውታል።
ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት ሌላ መንግሥት ወይም ገዢው አካል ከሥልጣን ከወረደ አገሪቱ እንደ ሩዋንዳ የህዝብ እልቂት ይደርስባታል እያሉ ያስፈራራሉ፤ ኢትዮጵያውያን ግን ለዘመናት በሠላምና በመግባባት ኖረዋል። ይህንን ታሪክ ግን ይህ መንግሥት ሆን ብሎ ያጥላላዋል። ኢትዮጵያውያን በትግላቸው ታሪክ ከጨቋኝ መንግሥታት ጋር ነው የተፋለሙት እንጂ የእርስበርስ ፍጅት ከጥቃቅን ግጭቶች ያለፈ አልነበረም። መንግሥት ሆን ብሎ ህዝብ ከህዝብ እንዲጋጭ የሞከረው ደባ እንዳልተሳካ እንሆ አሁን በምናየው የህዝብ የጋራ ትግል እያየነው ነው። የትግላቸው መርሆ ድምፅም “የአማራው ደም የኦሮሞውም ደም ነው” “የኦሮሞው ደም የአማራውም ደም ነው” ወ.ዘ.ተ.እየተባለ ሲያስተጋባ ነው የሰማነው። እነሆ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን እያስመሰከሩ ነው። ዋናው ነገር በታሪክ እደአየነው የህዝብ እልቂት (ጀኖሳይድ) በመንግሥት የሚፈጸም እኩይ ተግባር ነው እንጂ አንዱ ህዝብ በሌላው ህዝብ ላይ የሚያውጀው ዘመቻ አይደለም። ታሪክም ይህን ይመሰክራል። አሁን የህዝቡ ሥጋት ግን ይህ መንግሥት የራሱን ሰዎች ወይም ቅጥረኞችን በህዝብ ላይ ለእልቂት ያሠማራል የሚል ነው። ይህንንም በስውር ደባ በማካሄድ እነሆ ያልኩት ደረሰ ለማለት ነው ።
በመጨረሻም ይህ ጎሰኛ መንግሥት አካባቢውን የሚያረጋጋና የምዕራባውያንን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው ብሎ እራሱን ለማቅረብ ይሞክራል። ባንጻሩ ግን እራሷን ኢትዮጵያን መረጋጋት እያሳጣት ነው። እንዲያውምኢትዮጵያውያን የየራሳቸው የውስጥ ችግር ወደ አለባቸው አገሮች እየሸሹ ነው። ሆን ብለው አልመው ከሚገድሉት የመንግሥት ታጣቂዎች ለማምለጥ አንዳንዶቹ በተቻለ መጠን እየሞከሩ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት የአገሪቱን የመልክዓ ምድር ፖለቲካ ለእራሱ ጥቅም እያዋለውና የዓለምን ህብረተሰብ እያሳሳተ ነው። በቅርቡ እየተከሰቱያሉት የህዝብ ቁጣና ግንፈላ የመንግሥትን ተመጻዳቂነት የማክሸፍና ሐሰት ለመሆኑ ዋቢነት አለው። በየአገሩ የገነፈሉትን የህዝብ ቁጣዎችን የሚመሩ ይህንን መንግሥት ብቻ በሚያውቁት በወጣቶችና በሌሎችም ነው። የውሸት ተስፋ ሲመገቡ አድገው አሁን ለአቅመአዳም ሲደርሱ ያ ተስፋ እውን አልሆነም። ይህም የመንግሥትንየከሰረናእርባነ ቢስ ፖሊሲውን ያሳያል።
ስለዚህ ዩናይትድ እስቴት አሜሪካ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ያለውን ፖሊሲ መቀየር ይኖርበታል። የአሁኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው ሁኔታ ሊቀጥል አይችልም። ኢትዮጵያውያን ለሃያ አምስት ዓመታትሙሉ የተረገጠውን መብታቸውን ለማስጠበቅ ተነስተዋል። የመቻል ትዕግሥታቸው እስከ መጨረሻው ሄዷል። ስለዚህ ክቡር ፕሬዚዳንት አደራ የምልዎ አስተዳደሮ ለኢትዮጵያ ያለውን ፖሊሲ እንዲገመገም ቢያደርጉ የሁለቱንም አገሮች የአንድ መቶ አሥራ ሶስት ዓመት ወዳጅነትን ያጠነክራሉ።
እባክዎን ክቡር ፕሬዚዳንት የሥራዎን ዘመን ጨርሰው ከመልቀቅዎ በፊት ከእውነተኛው ታሪክና ከኢትዮጵያውያን ጎን እንጂ ህዝቡን ለአስከፊ ሁኔታ ከዳረገ መንግሥት ጎን እንዳልሆኑ አሁኑኑ ያረጋግጡ።በዚች እየታመሰች ባለችው አገርና በማያስተማምነው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ውስጥ ሠላም እንዲሰፍን እርዳታዎን ይለግሡ። ከታሪክ ተጠያቂነት ይዳኑ። ኢትዮጵያ አሁን የሚያስፈልጋት ወደ ባሰ የሰብዓዊ፣ የምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ተንሸራታ እንዳትገባ እጁንየሚዘረጋላትና ዓለምን ከፀፀት የሚያድን ብቻ ነው። በዓለም በሞላፈሰው ያሉት ኢትዮጵያውያንም ድምፅ አልባ ለሆነው ወገናቸው ሁሉ ቀንበቀን በመንግሥት ለችግር ለሚዳረጉ፣ ለሚገደሉ፣ ለሚሰቃዩና ስብዕናቸው ለቆሰለ ሁሉ ድምፅ የመሆንና አጋር የመሆን የሞራልና የታሪክ ግዴታ አለባቸው። የዚህች ታላቅ አገር ታላቅ ህዝብ ከአሁኑ የተሻለ ዕጣ ፈንታ ሊያገኝ ይገባዋል።
ከአክብሮት ጋር፣
ጌታቸው መታፈሪያ፣ ፒኤቺዲ
የፖለቲካል ሳይንስ ፕሮፌሰር
ሞርጋን እስቴት ዩኒቨርሲቲ
1700 ኢስት ኮልድ እስፕሪግ ሌን
ቦልቲሞር, ሜሪላንድ 21251
getachew.metaferia@morgan.edu
ኢትዮጵያና አሜሪካ ታሪክ፣ ዲፕሎማሲና ትንተና መጽሐፍ ደራሲ። ኒውዮርክ በአልጎራ የታተመ፣ 2009
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply