• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ግልፅ ደብዳቤ ለአቶ ጀዋር መሐመድ

October 30, 2016 03:16 am by Editor Leave a Comment

በኢትዮሚዲያ ላይ በለንደን ላይ ያደረጉትን ንግግር ከዚህ በታች የተቀነጨበውን አየውና ይህንን ልፅፍ ተነሳሳሁ።

“የኦሮሞ ወጣቶችን ወክዬ ለውጭው ማህረሰብ የማስተላልፈው መልዕክት አለኝ። ካሁን በዋላ በኢትዮጵያ ቢሆን ቢሆን ታግለን መብታችንን አስመልሰን ከሌሎች ጋር አብረን እንኖራለን። ካልሆነ ግን ያችን ሀገር በታትነን ጥለናት እንሄዳለን እንጂ እንደ ትላንቱ የማይረቡት እላያችን ላይ ተጭነው እንዲያስተዳድሩን አንፈቅድም።” ጀዋር መሐመድ፥ ከለንደን ንግግር ከኢትዮሚዲያ የተወሰደ።

በመጀመሪያ አሳቤን ይረዱልኝ። በክርክር ለማሸነፍ አሳቡም ምኞቱም የለኝም። እርስዎንም እንደ ጠላት ለመቁጠርና ለመፈረጅ በልቤ ውስጥ ያለው ፍቅር አይፈቅድልኝም። ነገሬ ከአስተሳሰብዎ ጋር ነው። ለማሳመን ብዙ ትንታኔ አልገባም። ቃሌን አጭር በማድረግ ከቃሌ ጀርባ ያለውን ቅን መንፈስ እንዲረዱ ተስፋ ማድረግን እመርጣለሁ። እርስዎ እስላም እኔ ክርስቲያን፥ እርስዎ ኦሮሞ እኔ አማራ መሆናችን ለመግባባት እንቅፋት ይሆናል ብዬ አላስብም። ለእኔ እርስዎ የሀገር ልጅ ነዎት። ሃይማኖት የግል ሀገር የጋራ ነው የሚለውን አባባል ልቀያይረውና፥ በጥንድ እውነት መግለፅ ይፈቀድልኝ፤ ሃይማኖት የግል ፈጣሪ የጋራ ነው። ዘራችን የግል ኢትዮጵያ የጋራ ናት። ስለዚህም የጋራ በሆነ ነገር ላይ ሁለታችንም አንድ ነን። በዚህ መንፈስ እንዲያደምጡኝ አደራ እላለው።

በመጀመሪያ ራሴን ላስተዋውቅና፥ እኔ ያለፈውን የታሪክ ቁርሾ በይቅርታ ዘግተን፥ የወደፊቱን ታሪካችንን በፍትህ መስርተን፥ ነፃ የሚያወጣንን እውነት ተነጋግረን፥ አዲሲቷን ኢትዮጵያ እንገንባ ብዬ የምሞግት ነኝ። ይህንን ካልኩ አሁን ወደ ዝርዝር ሀሳቤ ልግባ።

የጎንደር ሕዝብ ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ወንድምነት በአደባባይ አጋርነቱንና ፍቅሩን ሲያስተጋባ፥ የፍቅር ቋንቋ መናገሩን ያሳይ ነበር። ያንንም የፍቅር ጥሪ ወንድሙ የኦሮሞ ሕዝብ ተረድቶ፥ ምላሹን ፍቅሩንና አጋርነቱን በአደባባይ ሲያሳይ ፍቅርን መናገሩ እንደሆነ ይገልጥ ነበር። ይህንን የሕዝብ ፍቅር ቋንቋ ለምድራችን ፈውስ ተስፋ ጭላንጭል ያመጣል ተብሎ ሲጠበቅ፥ በዚህ ወሳኝ ወቅት በለንደን ያቀረቡት ንግግርዎ ተስፋውን በዜሮ እንዳባዙት ይቆጠራል። ይህንን ግልፅ ደብዳቤ ለመፃፍ የፈለኩት እንኪያ ሰላምታ ከእርስዎ ጋር ለመግጠም ሳይሆን፥ ለሚያየንና ለሚሰማን ሁሉ መግባባትን ፍንጥቅ ማድረግ ይቻል ይሆናል የሚል ተስፋ ፍቅር በልቤ ውስጥ ስለጫረብኝ ነው። ለዚህም የምተማመነው በሀገር ልጅነታችን ላይ ያለኝ አመኔታ ነው።

ኢትዮጵያ የአንድነቷ መሰረት የሕዝቧ ማንነት ነው። የኢትዮጵያ አንድነት በመንግስት ስራ ወይንም መንግስት በሚያወጣው አዋጅ ቁጥጥር ስርም አይደለም። ነገሩን ካስተዋልነው በሊሂቃን አስተሳሰብና ፍልስፍና ስርም አይደለም። በእኔና በእርስዎ እጅም አይደለም። የታሪክ ጉዳይ ሆኖ የኢትዮጵያ አንድነት ጅማሬው ላይ የመንግስታት እጅ ቢኖርበትም፥ ሕዝቡን የሚያስተሳስረው ፍቅር ግን ሰው ሰራሽ አርተፊሻል ሳይሆን “ተፈጥሯዊነት”(organic) ነው። ይህን ሕዝቡ በታሪክ አጋጣሚና በፈጣሪ አሳብ አብሮ ለዘመናት በመኖር ያመጣው እውነታ ነው።

ኦሮሞ ፍታዊ ሆኖ የሚኖርበት ለመድረስ በመንገዱ ላይ የቆመው ኢትዮጵያ ሳትሆን እንደ እርስዎ ያለው አስተሳሰብ ነው ብዬ እገምታለሁ። ለኔ ኢትዮጵያ ከኦሮሞ ተነጥሎ በኦሮሞ የድል መንገድ ላይ የቆመ ደንቃራ አድርጌ አልወስድም። ለምን ቢባል መላውን ኢትዮጵያ በጂኦግራፊ፥ በቤተሰብነት፥ በአብሮ ነዋሪነት፥ በደግነቱ አያይዞ፥ ተጋብቶ ተደባልቆና ተዋልዶ እዚህ ያደረሰው በተቀዳሚነት የኦሮሞ ሕዝብ ነው። ፍትህና ዲሞክራሲ ያለባት መድረሻ እንድትሆን የሚፈልጉት ኢትዮጵያ ከሆነ መነሻዎን ኢትዮጵያ ማድረግ ያለብዎት ይመስለኛል። ያልተነሱበትን ነገር መድረሻ ላይ አገኘዋለው ማለት ዘበት ነው።

ለእኔ ኦሮሞ የኢትዮጵያን የወደፊት ብሩሕ ተስፋ ለመቅረፅ የመሪነቱን ሚና ይጫወታል። ለዚያም በሀገር ቤት ያለው የኦሮሞ ሕዝብ የመሪነቱን ሃላፊነት በብቃት እየተወጣው ነው። እርስዎስ አጥር ሆኖ ከሌላው ሕዝብ የሚከልልዎትን የውልጃ ማንነት ሳይለቁ (ወደው አይደለም ኦሮሞ ሆነው የተወለዱት)፥ በምርጫዎ ከሁሉ ሕዝብ ጋር በእኩልነት የሚያያይዝዎትን ኢትዮጵያዊነትን መርጠው በጋርዮሽ ቢሞግቱ ምን ይመስልዎታል? አንደኛ ኦሮሞ መሆንዎን መምረጥዎ ባልከፋ፥ መልካም ነውና። ለነገሩ ሁሉም በግሉ በመጀመሪያ የተለያየ ዘር ግኝት ነው። ታዲያ የሚያስተሳስረን ጉራጌው ጉራጌ ኢትዮጵያዊትን አንግቦ፥ ጋምቤላው ጋምቤላ ኢትዮጵያዊነትን ወዶ፥ ትግሬው ትግሬ ኢትዮጵያዊነትን መርጦ፥ አማራው አማራ ኢትዮጵያዊነትን ተቀብሎ ወዘተረፈ በጋሪዮሽ መያያዛችን ነው። ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ መሆንና ለኦሮሞ እኩልነት ማቀንቀን የሚቃረኑ አይደሉም፥ እንደውም የሚደጋገፉ እንጂ። ዋነኛው ጉዳይ ከኖርንም አብረን፥ ተበታትነን ከጠፋንም አብረን እንደሆነ በማወቅ የመቆራኘታችንን ሚስጢር ጥልቀቱን ማስተዋሉ ላይ ነው።

ኢትዮጵያን በታትኖ ኦሮሞን መገንባት የሚለው አሳብ የማይሆን ነገር ነው። በኢትዮጵያ መቃብር ላይ የሚገነባ የኦሮሞ በረከት በዚያች ምድር ይኖራል ብሎ ማሰብ ከንቱ አስተሳሰብ ነው ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም የኢትዮጵያ መቃብር ካለ፥ ከኢትዮጵያ መቃብር ስር የኦሮሞ መቃብር አለ። ለምን ቢባል ከማንም ይልቅ ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ የሚያሰኛትና እንደ ደም ስር ሁሉንም የሚያያይዘው ኦሮሞ ከሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመዋለድና በመደባለቅ ስርና መሰረት ስለሆነ ነው።

ነገር በምሳሌ እንዲሉ ሁላችንም ያለነው ውቂያኖስ ላይ የሚንሳፈፍ ኢትዮጵያ በሚባል ትልቅ መርከብ ላይ ነው። እርስዎ የሚሉት ቢሆን ቢሆን ተባብረን መርከቡን በእኩልነት እየኖርንበት እንሂድ፥ ካልሆነ መርከቡን በታትነን በኦሮሞ ጀልባ እንኖራለን ነው። ያስተውሉ፥

1ኛ/ ሌላው ይበታተን የሚሉት ትልቁን 80 በላይ ብሔረሰብ የሚይዘውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ነው።

2ኛ/ ኦሮሞ እንደ ጀልባ በኢትዮጵያ መርከብ ላይ የተቀመጠ ማንነት ያለው አይደለም። ኦሮሞ የመርከቡ አካልና መካከለኛ ክፍል ነው። ይህ መሬት ላይ ያለ በሕዝቡ አብሮነት ለዘመናት የተገለጠ ሐቅ ነው።

3ኛ/ መርከቡ ከተበታተነ፥ የመርከቡ መካከለኛም አብሮ ሰምጦ ይቀራል። ከዚህ ውጭ ያለ አስተሳሰብ ሕልውና በሕልም ደረጃ ያለ ነው።

4ኛ/ የመርከቡን መሪ ማን ይያዝ የሚለው ጉዳይ የእኛ ምርጫ አይደለም። የእኛ ትግል መሪዉን ለመያዝ ሳይሆን፥ መሪዉን የሚይዘውን አካል ሕዝብ እንዲመርጥ እውነተኛ ዲሞክራሲ እንዲኖር ነው። እውነተኛ ዲሞክራሲ ባለበት ብዙ የሕዝብ ቁጥር ያለው ኦሮሞ ከሁሉ ይበልጥ ይመቸዋል።

ታዲያ የነገሬ ፍፃሜ ይህ ነው፥ ከ 50 ዓመታት በላይ ከቆየው የኦሮሞ ትግል ልምድ ከቀሰሙ በዋላ የደረሱበት ይህ አስተሳሰብዎ፥ ሁሉም የሚፈልገውን ይህንን ዲሞክራሲ እውን ለማድረግ የሚያስችል መላ በውኑ ነውን?

ለማንኛውም ለሁላችንም ልቦና ይስጠን።

አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ!


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡

Filed Under: Opinions Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

Recent Posts

  • ለሱዳንና ኤርትራ ሲከራከሩ የነበሩት አበባው ባለመመረጣቸው “በጣም ተድጃለሁ” አሉ June 26, 2026 12:29 am
  • “ትህነግ ወደ ዓለምአቀፍ ወንጀለኛነትና አሸባሪነት እየተምዘገዘገ ነው” June 25, 2026 01:00 am
  • አሜሪካ በሕገወጡ ትህነግ አመራሮች ላይ ጠንካራ የቪዛ እገዳ ጣለ June 18, 2026 10:29 am
  • እንደ ሌሊት ወፏ የሚንቀሳቀሰው ኢህአፓ/ትብብር   June 18, 2026 09:36 am
  • የታርጋ ጫጫታ June 15, 2026 05:16 pm
  • ፋንታኹን ዋቄ ከአሜሪካ የሃይማኖት እልቂት አወጁ June 15, 2026 02:12 am
  • ሕገወጡ ትህነግ ወጣቶችን ለዳግም ዕልቂት እያሰናዳ ለፈረንጆች “ኢትዮጵያን አውግዙልኝ” እያለ ነው June 11, 2026 12:57 am
  • በሐዘንና ግልፅ ደብዳቤ ስም የተሸፈነ የድህረ ምርጫ ሀገር የማተራመስ ስትራቴጂ June 10, 2026 12:19 am
  • የጽምዶ ልክፍት June 9, 2026 12:49 am
  • ገዳዩ ማነው? አስገዳዩስ ማነው? June 5, 2026 02:37 pm
  • ጽንፈኝነት ግን በኢትዮጵያ ምድር ፈጽሞ ቦታ የለውም! June 5, 2026 01:47 pm
  • የትብብሩ “ብናሸንፍም ፓርላማ አንገባም” መግለጫ “ወንበር ስታጡ ነው” የሚል ከፍተኛ ተቃውሞ አስነሳ June 4, 2026 12:04 am
  • አዲሱ የትራምፕ የምርጫ መመሪያ፡ የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን አፍ ያስዘጋ፤ ተቃዋሚዎች ተስፋ ያስቆረጠ June 3, 2026 08:50 pm
  • “ኢህአፓ ከምርጫው በኋላ ይሰነጠቃል” May 29, 2026 07:07 pm
  • ሪፖርተር፡ “ስውር ተልዕኮ” – በከባድ ወንጀል ሊከሰስ May 6, 2026 11:55 pm
  • የፋኖ ኃይል በደረሰበት ጉዳት ሃምሳ ሺህ የሚጠጋ ትጥቅ ጥሎ ጠፋ April 29, 2026 02:27 pm
  • አዲሱ የቴድሮስ ካሳሁን 888 ኮድ፤ እንደ 666?! April 15, 2026 05:53 am
  • ምኑ ነው ያሳቃችሁ፤ ያስደሰታችሁ? April 2, 2026 10:52 am
  • የጀዋር መሃመድ የፖለቲካ ማንነት እና የባዕዳን ተልዕኮ April 2, 2026 10:16 am
  • ከግብፅ በዳያስፖራ ትርምስ ጠማቂዎች በኩል ፋኖ ወደ አዲስ አበባ የላከው “ስጦታ” March 27, 2026 09:14 am
  • “ሰላማዊ ታጋዮቹ” እነ ልደቱ ከአራጁ ሸኔ ጋር ተጣምረዋል March 25, 2026 01:04 pm
  • ጸረ-ኢትዮጵያዊ የሆነው የሪፖርተር አዘጋገብ March 19, 2026 11:54 am
  • የአውሬው ሪፖርተር ቀላቢዎች፡ የኦሮሚያ የልማት ድርጅቶች March 18, 2026 10:48 am
  • የጃኖ ስጦታና የዶሮ ፖለቲካ በጎንደር March 10, 2026 09:24 am
Copyright © 2026 · Goolgule