ከባርነት ሞትን የመረጥከው ወንዱ፣
አፉን ክፍት አርጎ የዋጠህ መቃብሩ፣
የማዋይህ አለኝ ስማኝ ሰማእቱ፡፡
የፈሰሰው ደምህ በህልሜ እየታየኝ፣
አጥንትህ ከመቃብር እየጎራበጠኝ፣
እሾህ ቀጋ ሆኖ አላስተኛህ አለኝ፡፡
ለፍትህ ስትጮህ የቀረኸው ባጭር፣
ጎንደር ደብረታቦር ወልድያ ባህርዳር፣
ቡሬና ዳንግላ ማጀቴና አቸፈር፣
ዛሬም ወንድሞችህ ታስረዋል ግዮን ዳር፡፡
በስናይፐር የፈጁህ ህሊና ቢሶቹ፣
ለውጥ አመጣን ብለው ያንኑ ደገሙ፣
አንድ አስገዳይ ነቅለው ሌላውን ተከሉ፡፡
አጥንትህን ከአምቦ ከእሬቻ ለቃቅሞ፣
መሰላል አረገው ከለማ ጋር ሰርቶ፡፡
በስንት በጎች ደም እንደተነከረ፣
እጁን ሳይታጠብ አቢይ ቀደሰ፡፡
ኢያሱና ሙሴን ተከተሉ እያሉ፣
ስንቱን ዘልዛላ እንከፍ ከጀርባ አሰለፉ፡፡
ተመራጩ አስገዳይ መራጩም ገዳይ ነው፣
የሌላው ማሽቃበጥ ምን እሚሉት ጉድ ነው?
ትናንትናም ያአድጊ ዛሬም ይህአድጊ ነው፣
አሸርጋጅ የበዛው የምን ለውጥ አይቶ ነው?
አጋዚ ሰው ፈጅ እያለ እሚጮኸው፣
ጆሮ ጠቢ አቢይን ቅዱስ አርጎ አረፈው፡፡
እንኳን ፈሪሳውያን እነ ሆድ አምላኩ፣
እነ ኦባንግ ሜቶም ለይሁዳ ሰገዱ፡፡
ስንቱ ወለወልዳ ስትሞት ያለቀሰው፣
አዛኝ አንጓች መስሎ የአዞ እምባ ያነባው፣
አስገዳይህ ሲነግስ ደስ ይበልህ አለው፡፡
ስንቱን ላስፈጀ ጉድ ድጋፍ እየሰጡ፣
የፍትህ ታጋይ ነን ብለውን አረፉ፡፡
እንዳንተ በጽናት መታገል ሲለግሙ፣
በአጥንቶችህ ባላ አቢይን ሰቀሉ፡፡
ታሪክ በደም ጥፈህ በክብር ያለፍከው፣
ስማኝ ሰማእቱ የኔ መልእክት ይህ ነው፡፡
አንተ ሙተህ አዝነን ሳይወጣ ሳልስትህ፣
የምዕራብ ዲፕሎማት እንዲሁም ገዳይህ፣
ፖለቲካ ቁማር ዘረጉ እመቃብርህ፡፡
የሞትክለት ህልምህ እንዳይደርስ ከዳሩ፣
የነደደው እሳት እንዲጠፋ ፍሙ፣
ትልቅ ማዳፈኛ ከምድጃ ጎለቱ፡፡
አስገዳይ ለማንገስ ፓርላማ ከተሙ፣
የሕዝብ ተወካዮች ብለው አፍጣጮቹ፣
እንደ ኦሪት ሁሉ ህማማትን ጣሱ፣
መነኩሳትን አስረው እነሱ እያሽካኩ፣
ድግስ እየዋጡ ዳንኪራ እየመቱ፣
ጉልቻን አንስተው ጉልቻ ጎለቱ፡፡
እየታገልን ነው ሲሉ የነበሩ፣
በራሳቸው እምነት ብቃትን ስላጡ፣
ወደ ላይ አንጋጠው አቢይ አቢይ አሉ፣
እንኳን የሞቱትን ፈጣሪን ረሱ፡፡
የራሱን ልብ አሞት የተጠራጠረ፣
በካድሬው አቢይ ቃል አመነና ማለ፡፡
ዳሩ ይህም ቢሆን እንዳይልህ ክፍት፣
አርማህን አንስቷል ፍም ጎራሹ ወጣት፡፡
ብቁ ሰማእታት እንደ አንተ የፀኑ፣
ነፃነት ወይም ሞት ብለው የቆረጡ፣
ሞረሽ ይጣራሉ በዱር በገደሉ፡፡
ያሳደደህ ቢነግስ በህማማቱ እለት፣
አዳኝህ ይነሳል ቅዳምሽ እሁድ ማግስት፡፡
ሐዋርያት ዝቅዝቅ ታስረው ቢታረዱ፣
ክርስትና ሰፍቷል ቁመትና ወርዱ፡፡
ክርስቶስ ተሰቅሎ ተቀብሮ እንዳልቀረው፣
ያንተም ህልም እሚያርግ ዘላለም ህያው ነው፡፡
ገዳይ አስገዳዮች አንተን የሰውቱ፣
አስገዳይ ለማንገስ አንተን የረሱቱ፣
እንደ ፈሪሳውያን ይሁዳ ዘ አስቆርቱ፣
ታሪክ ሲመትራቸው ሲያርዳቸው ይኑሩ፡፡
ምድር ታሪክህን እንዳሳማረችው፣
ሰማዩም ነፍስህን በምቾት ያኑረው፣
እኛም አደራህን አኝከን አንብላው፣
ስማኝ ሰማእቱ መልእክቴ ይኸው ነው፡፡
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
መጋቢት ሁለት ሺ አሥር ዓ.ም.
Leave a Reply