ቢሄዱት… ቢሄዱት… ቢሄዱት… ቢሄዱት…
አያልቅ ሽቅቦሹ፥ አይቆም ቆልቁሎሹ
መንገድ እየሄዱ
መንገድ እየበሉ
መንገዱ እየጠጡ
አያልቅም ቢሄዱት፥ አያልቅም ቢጠግቡት፤
አወይ አማሪካን…
አወይ የሰው አገር
የበላን ያላየ፥ የዋጠን ያልሰማ
አወይ አማሪካን፥ ሰው በላብ ያደማ፤
ቢሄዱት ቢሄዱት፥ እረፍትን ማን አውቆት
እዚማ ከሆኑ…
እንቅልፍ ለምኔን፥ ለብሶ ነዪ መኛት፤
አወይ አማሪካን፥ አገረ ማራቶን አገረ እሩጫ
ለማምለጥ መፏደድ፥ ቢል ከሚሉ ጡጫ
መኖር አለመኖር፥ ካንድ ራስ ፍጥጫ፤
አወይ አማሪካን…
ቢሄዱት… ቢሄዱት… ቢሄዱት አያልቅ
መንገድ እንደ ጅማት የሚላግበት
አወይ አማሪካን ሕልም ያጠጠበት
እንቅልፍ ለምኔን የሚያነቡበት_
እንቅልፍ ለምኔን የሚገምጡበት_
እንቅልፍ ለምኔን የሚጎሹበት_
እንቅልፍ ለምኔን የሚዋቡበት_
አወይ አማሪካን…
“እንዴት አደራችሁ፥ እንደምን ዋላችሁ?»
ሙቶ አፈር በልቶት፥ ከተረሳሳችሁ
አይደንቅም አይገርምም፥ ዘመን መቁጠራችሁ
በእንዴት ከረማችሁ፥ ማዝገም ነው እጣችሁ፤
አወይ አማሪካን…
የሰው ትልቅ ትንሽ የተዘራበት
የሰው ትንሽ ትልቅ የበቀለበት
አያ ቢል ነግሦበት፣ ቢል የፈላበት
ሃገረ ኦባማ… ቴስት የበዛበት
ቢልን አሽሞንሙኖ፣ ቢል የሚሉበት
ችግርን በሩጫ የሚረግጡበት፤
አወይ አማሪካን…
ሕልም ያጠጠበት
እንቅልፍ ለምኔን የሚያነቡበት
ቢሄዱት… ቢሄዱት… ቢሄዱት አያልቅ
መንገድ እንደ ጅማት የሚላግበት፤
አወይ አማሪካን…
ታገርም አገሩ፣ እዚህ አለላቸሁ
አንደዜ ብቅ በሉ፣ ጉልበቱ ያላቸሁ፤
(Photo: Steve Brodner)
Leave a Reply