የኢትዮጵያን ሕዝብ በነጻ አውጪ ስም እስካሁን በግፍ እየገዛ ያለው የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግምባር ሥልጣን በኃይል ከመያዙ በፊት ሲፈጽም የነበረውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ፤ ሥልጣን ከያዘም በኋላ ላለፉት 25 ዓመታት ቀጥሎበታል፡፡ ህወሃት ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ግፍ ያልተፈጸመበት አካባቢ የለም የሚለው አባባል የተጋነነ አይደለም፡፡
“ኦጋዴን፤ የኢትዮጵያ [የህወሃት] ድብቅ ኃፍረት” በሚል ርዕስ ጋዜጠኛ ግራሃም ፔብልስ በኦጋዴን የሚካሄደውን የሚዘገንን ግፍ ሰኔ 15፤ 2008ዓም (June 22, 2016) ዩትዩብ ላይ ለቋል፡፡ (ዘጋቢ ፊልሙ እዚህ ላይ ይገኛል)
“በዛፍ ላይ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ሰቅለውኝ ነበር፤ በርካታ ደቂቃዎች ካለፉ በኋላ አወረዱኝ፤ … ከዚያም ካሁን በኋላ የምንልሽን ታደርጊያለሽ አለበለዚያ እንገድልሻለን አሉኝ” የግፍ ዶፍ የወረደባት አናብ ከተናገረችው፡፡
የሚዲና የዕርዳታ ሥራዎችን የሚያካሂዱ ሁሉ ወደ ኦጋዴን እንዳይገቡ በህወሃት ትዕዛዝ ተደርጎባቸው ባለበት ባሁኑ ወቅት በኦጋዴን የሚካሄደው ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፤ እስር፣ እንግልት፣ ወከባ፣ … በድብቅ ቀጥሏል ይላል ጋዜጠኛ ግራሃም፡፡
ዘጋቢ ፊልሙን ለመሥራት መረጃው የተሰበሰበው ከሚሊታሪው የኮበለሉና ሌሎች ለህይወታቸው ያልሳሱ ደፋሮች በሰጡት ምስክርነት ነው፡፡ በተለይም ከኢትዮጵያ ኮብለለው በቅርቡ ኬኒያ ልትዘጋው ወደ ወሰነችው የዳዳብ የስደተኞች ካምፕ የሚገኙ ሦስት ሴቶች የህወሃት ሠራዊት ስላደረሰባቸው መከራ፣ ሥቃይና አስገድዶ መድፈር ተግባራት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ወደ ዳዳብ በግንቦት 2006ዓም የመጣችው ሚሪያም ለሁለት ዓመት ተኩል እንዴት እንደተሰቃየች፣ አስገድዶ መድፈርና ድብደባ እንዴት እንደተፈጸመባት ትናግራለች፤
“እንደ ማሰቃያ ይሆን ዘንድ እስኪደክመኝ ድረስ ሬሣ አቅፌ እንድቆም ተደርጌአለሁ፤ ከዚያም ሚጥሚጣ የሞላበት ላስቲክ በራሴ ላይ አስረውብኛል፤ ገመዱን ሲያስሩት አጥብቀው ከአንገቴ ጋር በማሰራቸው ራሴን ስቼ ወድቄ ነበር፡፡ ከዚያ ለብዙ ሆነ እየተፈራረቁ አስገድደው ደፈሩኝ …”
“ኦጋዴን በሚገኘው እስርቤት 1097 የምንሆን ነበርን፤ ቁጥሩን በትክክል አውቀዋለሁ ምክንያቱም በየቀኑ ማለዳ ላይ እያሰለፉ ከቆጠሩን በኋላ በቡድን በቡድን እያደረጉ ይከፋፍሉን ነበር፤ …
“(የተያዝን ጊዜ) እህቴን ጉሮሮዋን አንቀው መረጃ አምጪ አሏት፤ ምንም እንደማታውቅ ብትነግራቸውም አልሰሟትም፤ ከሌሎቻችን ጋር ተቀላቅላ እንድትቀመጥ አደረጓት ከዚያም ሁላችን እያየን አራት ቤቶቻችን አቃጠሏቸው፤ ቤቱን እያቃጠሉ እህቴን ከመካከል ነጥለው ግምባሯ ላይ በጥይት መቷት፤ እህቴን እስከሞት ስትደማ አየኋት፤ ከእርሷ አጠገብ ሌላ ሴት ልጅ በድብደባ ብዛት ሞታ ነበር፤ ከዚያም እኔን ሬሣ ባለበት ጉድጓድ ውስጥ ጣሉኝ፤ በዚያ ጉድጓድ ውስጥ አራት ቀንና አራት ምሽት አሳለፍኩ፤ ጥፋተኛ መሆኔን እንድናዘዝ ምርመራ ይካሄድብኝ ነበር፤ አለበለዚያ መጨረሻዬ እንደ ሬሣው እንደሚሆን ይነግሩኝ ነበር፤ እኔም ምንም የምናዘዘው የለኝም የምታርዱኝ ከሆነ እረዱኝ አልኳቸው፤ (ጉድጓድ ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ) ከሬሣው መካከል አንዱ ጉሮሮው ታርዶ፤ አንገቱም በዱልዱም ነገር ተቆርጦ ጭንቅላቱ እዚያው የቀረው አካሉ ጎን ነበር፤…”
በመስከረም 2007ዓም ወደ ዳዳብ ካምፕ የመጣቸው አናብ ደግሞ “የኢትዮጵያ ሠራዊት በጅምላ ከገደሉ በኋላ በጅምላ የሚቀብሩበትን ቦታ በመደበቅ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ያደርጋሉ፤ አንዳንዶቹ መቼም አይገኙም፤ አንዳንዶቹ ግን በቁሻሻ ጉድጓዶች ውስጥ ተገኝተዋል” ትላለች፡፡
በእርሷ ላይ የደረሰውን በተመለከተ ስትናገር አናብ እንዲህ ትላለች፤ “ወደ እስር ቤት ተወስጄ በሽቦ ታነቅሁኝ፤ ይህ ዓይነቱን ተግባር በተደጋጋሚ ሲፈጽሙ ቆይተው በኋላ እስርቤት ተዉኝ፤ በተያዝኩ ጊዜ ከፊት፥ ከኋላና ጭኔ ላይ በጎማ ጠፍር ገርፈውናል፤ ከእኔ ጋር የተያዙ አምስት ልጃገረዶች ነበሩ፤ ከተያዙት ውስጥ ትልቋ 19ዓመቷ አካባቢ ነበር፤ ትንሽዋ ደግሞ ወደ 15ዓመት አካባቢ ነበረች፤ በተያዝንበት ወቅት ልጆቹን ክፉኛ ሲደበድቧቸውና በሰደፍ ሲመቷቸው አይቻለሁ፤ ልብሳቸውንም ቀዳድደውባቸው ብጣቂ እራፊ አድርገው ተመልሰዋል፤ ይህንን በየጊዜው የሚያደርጉት ተግባር ነው፤ …
“መረጃ እንድንሰጣቸው በየጊዜው ይመረምሩን ነበር፤ ሴቶችን ‘አስገድደን እንደፍራችኋለን’ እያሉ ያስፈራራሉ፤ ‘አንደፈርም’ ብለው አሻፈረን የሚሉትን ደግሞ ያንቋቸዋል፤ ሴቶቹ ራሳቸውን ስተው ባሉበት ወቅት እንኳን ይደፍሯቸዋል … እኔ የታሰርኩበት ትንሽ ክፍል ውስጥ ሰባት ሴቶች ነበሩ፤ ከዚያ ክፍል ነጻ የተለቀቀ የለም ማለት ይቻላል፤ ከእኛ በፊት እዚያ ክፍል የነበሩት ታርደዋል፤ ሌሎቹም በረሃብ እንዲሞቱ ተደርገዋል፤ ሬሣቸውንም በየጉድጓዱ ወርውረውታል፤ እኛ የነበርንበት ክፍል ሬሣ ነበር፤ የክፍሉን ሁኔታ ማንም ሊገምት የሚችል አይደልም (መግለጽ አይቻልም)፤ በክፍሉ የነበረው ሬሣ ባብዛኛው የወጣት ወንዶች ነው፤ እስከ አራት ቀናት ሬሣው በክፍሉ እንዲቆይ ይደረጋል፤ ከዚያ አውጥተው በየቦታው፤ በየመንገዱ ይወረውሩታል፤ …”
እንደ ሚሪያም በግንቦት 2006 ዓም ወደ ዳዳብ የመጣችው ፋጡማ “ወታደሮቹ እናንተ የኦጋዴንን ሰዎች እናጠፋችኋለን፤ ምንም ዓይነት ነዋሪ እዚህ አካባቢ አንፈልግም፤ እንጨርሳችኋለን” ይሉናል፡፡ “እስርቤት ሳለሁ አንቀውኝ ነበር፤ በሳንጃም ወግተውኛል፤ በየጊዜው መላ አካላቴን ደብድበውኛል፤ ጭንቅላቴን በኤሌትሪክ ጠብሰውታል፤ የማያደርጉት ዓይነት ስቃይ የለም …” በማለት ምሬት እና ሰቆቃ በተሞላበት ድምጽ ምስክርነቷን ስትሰጥ ትደመጣለች፡፡ ኦብነግ በአካባቢው እንዳለ እና ሠራዊቱ አንድ መቀመጫ ቦታ እንደሌለው፤ በተገኘው አጋጣሚ ወደ ሰፈር እንደሚመጡ እና የሚፈልጉትን እንደሚያገኙ ፋጡማ ትናገራለች፡፡
ህወሃት በበረሃ በነበረበት ጊዜ ተጋዳላዮቹ በየምሽቱና በየሌሊቱ ወደ መንደራቸውና ሰፈራቸው በሚመጡበት ጊዜ የትግራይ እናቶች ልጆቻቸውን ምግብና መጠጥ እያሲያዙ፤ ስንቅ እንየቋጠሩ ይልኩ ነበር አቶ ስዬ አብርሃ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ እንዲያውም የራሳቸውን እናት ጠቅሰው ብዙዎችን ይመግቡ እንደነበርና ለበርካታ ተጋዳላዮች “እናት” እንደነበሩ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በህወሃት አዛዥነት ወደ ሥፍራው የተላከው ሠራዊት አስገድዶ መድፈር አንዱ የጥቃት መሣሪያው ነው፡፡ በወታደራዊ ሠፈሮች ውስጥ ሴቶች ለወሲብ መገልገያ ሆነዋል፤ ከሚደርስባቸው ሰቆቃ በተጨማሪ በተደጋጋሚ በበርካታዎች ይደፈራሉ በሚለው የግራሃም የቪዲዮ ዘገባ ላይ የስቃይ እንባ የምታፈሰውን ሚሪያም “በተደጋጋሚ ተደፍሬአለሁ፤ ድርጊቱ መደበኛ እየሆነ ከመምጣቱ የተነሳ ተቀበልነው” ስትል ያሳያል፡፡ “ብዙዎች በጣም አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፤ አንዳንዶችም የሚጥል በሽታ ይዟቸዋል ሌሎችም እውር ሆነዋል፤ እኔም ራሴ ከደረሰብኝ ስቃይና ድብደባ የተነሳ አሁን እየተሻለኝ ቢሆንም የጡንቻ መኮማተርና የሚጥል በሽታ ይዞኛል፡፡”
የኦጋዴን ጭፍጨፋ መሃንዲሱና ጀማሪው ሞት እንደ ቡሽ ክዳን ያስፈነጠረው መለስ ነው፡፡ የሙት ውርስ እንጠብቃለን የሚሉት አወዳሾቹም በሙት መንፈስ እየተመሩ ግፉን ቀጥለውበታል፡፡
የኢትዮጵያን ስም ይዞ በኦጋዴን ወገኖቻችን ላይ የዘመተው የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግምባር ሠራዊት ኦጋዴን በደረሰበት ጊዜ የፈጸመውን እማኞቹ በግልጽ ያስረዳሉ፡፡ “የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ይሁኑ ወይም ልዩ ፖሊስ እኔ አላውቅም” የምትለው ፋጡማ ሰፈሮቻቸው በወራሪው ሠራዊት ከተከበበ በኋላ ከብቶቻቸው፤ ግመሎቻቸው፤ … በአጠቃላይ ንብረታቸው እንደተዘረፈ ትናገራለች፡፡ ከሁለቱ ሴቶች ጋር በመስማማትም ወንዶች እየተነጠሉ እንደተገደሉ ታስረዳለች፡፡ በተለይ የተማሩ የሚባሉ የኦጋዴን ወጣቶችን እየለዩ እንደገደሉ የሟች ቤተሰብ የሆኑት እነዚህ እህቶች በቃለምልልሱ ላይ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ሁልጊዜ የሚባሉትም “አንዳችሁንም አናስተርፍም፤ እንጨርሳችኋልን” መሆኑን ግፍ፤ እልህና ሲቃ በሞላው ድምጽ ይናገራሉ፡፡ ዘጋቢ ፊልሙ ላይ በተሰጠው መረጃ መሠረት ይህንን ግፍ የሚፈጽሙት ግዢው ህወሃት በልዩ ሁኔታ ያሰለጠናቸው በትምህርት ያልታነጹ፤ ወታደራዊ ዲሲፒሊን የሌላቸውና ከወሮበላ የማይተናነስ ባህርይ ያላቸው ጨካኝ ፓራሚሊታሪዎች እንደሆኑ ያስረዳል፡፡
ህወሃትንና ሹሞቹን በዚህ የኦጋዴን ዘር ማጥፋትና በሰብዓዊ ዘር ላይ በሚፈጸም ወንጀል ማስከሰስ፤ ለፍርድ ማቅረብ የኦጋዴን ወገኖችንና የመላ ኢትዮጵያ ልጆችን ትብብር ይጠይቃል፡፡ ስቃይ፣ መከራ፣ ሰቆቃ፣ … ካላስተባበረን ሌላ ምን ሊያስተባብረን ይችላል? ሰዎች ደስታን እንደመሰላቸው ሊተረጉሙት ይችላሉ፤ ግፍ ግን ቋንቋውና ስሜቱ አንድ ዓይነት ነው – እስከ አጥንት ይዘልቃል፤ መቅኔን ይቆጠቁጣል፡፡
ከአዘጋጆቹ፤ ምንም እንኳን በጋዜጠኛነት ተግባር ላይ የምንገኝ ቢሆንም የእነዚህ እህቶቻችን እና ወንድሞቻችን መከራና ስቃይ ያመናል፤ ያስለቅሰናል፡፡ ከአንዲት እናት የተወለድን ሰብዓዊ ፍጡር እንደመሆናችን የሴቶች ስቃይ ከምንም በላይ ልባችንን ያሳምማል፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊ ይህንን ስቃይ ማቅረብ ሌላውን ዜና የመዘገብ ያህል ቀላል አይደለም፡፡ ድርጊቱ አሁን የተፈጸመ ያህል እየተሰማቸው አሁንም ትኩስ እንባ እያፈሰሱ ስቃያቸውን የገለጹት እህቶቻችን ህመም የማያመውና የማያስለቅሰው ህወሃትና በድንቁርና ጭለማ ውስጥ የገቡት ጀሌዎቹ ናቸው፡፡ ህወሃት ይህንን ዓይነቱን ግፍ ሲደርግ ኖሯል፤ አሁንም እያደረገ ነው፤ ኢትዮጵያ ግን አሁንም ከእናንተ የኦጋዴን ግፉአን ጋር ታለቅሳለች፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
gud says
Shabia — your days are numbered !
Shabia clowns and it’s loyal Servants shall be ….
gud says
ONLF is destroyed for good . Milas bicha Kerew !
Oh EPRDF Sintun be Milas bitcha askerehew ?
ዘላለም says
ጎልጉል አዘጋጅ፣ “የህወሓት ነፍጠኞች” የሚለውን ገላጭ ሐረግ በጽሑፍ ያየሁት ገና ዛሬ ነው። ሌላ ሥፍራ ተብሎ እንደሆነ አላውቅም። ግን በጣም ትክክለኛ አባባል ነው። አማራን ነፍጠኛ ማለት የተለመደ ነው። ህወሓት የሚደጋግማት ቃል ነች። በተለይ ወደ አፋር፣ ወደ ጋምቤላ፣ ወደ ጉሙዝ ቤኒሻንጉል፣ ወደ ጎፋ ወዘተ ብትሄድ ዛሬ የኢኮኖሚውን እንቅስቃሴ የያዙት ህወሓቶች ናቸው። ይኸ የጥላቻ ወሬ አይደለም። አማራውን እያጥላሉ ራሳቸው ገብተውበታል። ያልተስማማቸው ሁሉ ይሻርና በሚስማማቸው ይተካል። ወይም እስር ቤት ይላካል። የዚህን ዓይነት ግፍ ዝርዝር በጽሑፍና በዜና ማሠራጫ ለሁሉም ማዳረስ አለባችሁ። የጋምቤላ ኗሪ አፋርና ጋሞጎፋም “ነጻ አውጭ” ነን ባዮቹ ሌቦች እንደሆኑ ማወቃቸው ተገቢ ነው። በርቱ
Samson says
Am so Sorry…..