- እስካሁን ለምን በተደጋጋሚ ከሸፍን?
እንደምን አላችሁ፣ አሰላሙ አሌይኩም፣ አካም ጂርቱ፣ እንደምን አረፈዳችሁ (good afternoon everyone)። የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ጉባዔ በዚህ ስብሰባ ላይ እንድናገር ስለ ጋበዘኝ ልባዊ ምስጋናዬን ላቀርብ እወዳለሁ።
ከእናንተ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ጋር በመሆን ስለምትወዷት አገራችን የወደፊት ሁኔታ ለመወያየት መብቃት ታላቅ ዕድል ነው። በአሁኑ ወቅት አገራችን በከባድ ቀውስ ውስጥ እንደምትገኝ ሁላችንም የምናውቀው ሃቅ ነው፤ ይህም ቀውስ በአንድ ጊዜ የተከሰተ ሳይሆን ለዓመታት ሲጠራቀምና ሲከማች የቆየ ነው። የአገራችን የወደፊት ሁኔታ ሁላችንንም የሚያሳስበን በመሆኑ እናንተም ይህንኑ ሃሳብ እንዳቀርብ በጠየቃችሁኝ መሠረት እኛ ኢትዮጵያውያን በኅብረት በመሥራት ለአገራችን የተሻለ የወደፊት ተስፋ ማምጣት እንዴት እንደምንችል ሃሳቤን ከዚህ እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
በቅድሚያ ጥያቄዎችን እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ፤ ባለፉት ዓመታት ካገኘነው ውጤት በተሻለ ለወደፊቷ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የምናበረክተው አስተዋጽዖ ምንድነው? ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ ስናካሂደው የነበረው ትግል ነጻነትና እኩልነት የሰፈነባትን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንድንመሠርት ያላስቻለን ለምንድነው? ካለፉት የትግል ልምዶቻችን እንደገና እንድንቃኘው የሚያስፈልጉን የትኞቹን ነው? በለመድነውና በባህል በተቆራኘን ራሳችን ለሽንፈት በሚዳርግ መንገድ አሁንም መቀጠል ይገባናል? ወይስ የእኛ የረጅም ጊዜ ዕቅድ ውስጥ የተካተተ ባይሆንም ከሌሎች ቡድኖች በሚደርሱብን ምክንያት አጸፋ መመለሳችንን እንቀጥል? መፍትሄ ፍለጋ አውቀንም ይሁን ሳናውቅ ከመንገድ ወጥተናል? ከወጣንስ እንዴት መመለስ እንችላለን? ካልወጣን ያለምነውን ከግብ ማድረስ ለምን ተሳነን? ለችግራችን መፍትሄ እንዳናገኝ የሳትነው የት ላይ ነው?
በቅድሚያ ማወቅ የሚገባን ከዱሮ ዓመሎችንና ልምምዶችን መላቀቅ ቀላል እንደሆነ አቃልለን መመልከት የለብንም። ስለሆነም ኢትዮጵያ የእኛ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ዜጎች መብቶችና እሴቶች ክብርና እውቅና የምትሰጥ አገር እንድትሆን ካስፈለገ በመጀመሪያ ወደ ራሳችን መመልከት ይገባናል። አሁንም እየተከተልን ካለውና ካለፈው ታሪካችን ውስጥ መልካምና መጥፎ የምንላቸው የትኞቹ ናቸው? መልካም የምንላቸውን ለወደፊቱ እየጠበቅን በክፉ የተጠናወቱንን መጥፎ ባህሎችና አስተሳሰቦች እንዴት ነው የምናስወግደው? እነዚህ እያንዳንዳችን ራሳችንን ልንጠይቅ የሚገቡ ጥያቄዎች ናቸው።
ዛሬና በቀጣይ ባሉት ሳምንታት፣ ወራትና ዓመታት የምናደርጋቸው ውሳኔዎች የአገራችንን የወደፊት ዕጣ ይወስናሉ። ነገር ግን አንዳንዶቻችን የምንታገለው ከመደናገጥ፣ ተስፋ ከመቁረጥ ወይም በሁኔታዎች ግፊት በመነሳሳት ነው። የዚያኑ ያህል ደግሞ በዚህ ባለንበት አገር ያለው የኑሮ ሁኔታ ወጥሮ ሲይዘን ከትግል ሃሳባችን እንደናቀፋለን፤ ሆኖም እናንተ ስለ ወደፊቱ የአገራችንና የልጆቻን ሁኔታ ያሳሰባችሁ በመሆናችሁ እዚህ ተገኝታችኋል፤ ግድ ባይላችሁማ ኖሮ እዚህ ባልተገኛችሁ ነበር።
ስለዚህ የወቅቱ አንገብጋቢና ቀዳሚ ጉዳይ የሚያለያዩን ነገሮች እንዳሉ ሆነው ሁላችንንም ለሚመለከተው ችግራችን መፍትሄ ለማምጣትና ነጻ፣ እኩልነት የሰፈነባት፣ ዴሞክራሲዊት ኢትዮጵያን ለመመሥረት የምንችለው እንዴት ነው? የሚለው ነው። ይህንን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው ለሁላችንም የሚበጅ የወደፊት ማኅበራዊ መዋቅር መገንባት የምንችለው። ሆኖም አንዳንዶች ይህ አስተሳሰብ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የተከፋፈሉ አገራት የወደፊቱን በማለም ተግባራዊ ማድረግ ይቻል ይሆን እያሉ በአግራሞት ይጠይቃሉ?
በአንድ አነስተኛ ምሳሌ ልጀምር – ከራሳችን ማለትም ከእኔ እና እናንተ ልጀምር! በኢትዮጵያ ውስጥ ሁላችንም በበርካታ መንገዶች ልዩ መሆናችን ይጎላል። ነገር ግን ዛሬ እዚህ ስብሰባ ላይ ከእናንተ ኢትዮጵውያን ወገኖቼ ጋር ለመነጋገር ስመጣ በውስጤ ታላቅ ቅርበት፣ ወዳጅነትና አብሮነት እየተሰማኝ መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። ግን ቆም ብለን ካሰብነው ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? እንደኔ ዓይነት የቆዳው ቀለም የጠቆረ፣ በእምነቱ ክርስቲያን የሆነ፣ በሞቃታማዋ ጋምቤላ በወንዞች መካከል የተወለደ፣ ከትንሽ መንደር የመጣ፣ አኙዋክ ከተባለ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት 0.01 በመቶ የሆነ፣ የተረሳ፣ ከእናንተ የቆዳ ቀለማችሁ ፈገግ ካለ፣ ከደጋና በረሃማው የኢትዮጵያ ክልል – ከኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከአፋር፣ ከሶማሊ፣ ከትግራይና ከሌሎች ሥፍራዎች ከመጣችሁ ወገኖቼ ጋር እንዴት ለመገናኘት ቻልኩ?
የሁላችንም ባህል እና አኗኗር የተለያየ ቢሆንም ዛሬ ግን በዚህ ቦታ ለእያንዳንዳችን የሚጠቅምና ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚበጅ አንድ ዓላማ ተሰባስበናል። ማናችንም ብንሆን ግን ይህንን መሰሉ ትግል ስንጀምር በዚህ መልኩ አልነበረም፤ በጊዜ ብዛት ግን ሁላችንም እየተማርን አሁን ካለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፤ ልክ ነኝ አይደል?
የኔን ብነግራችሁ፤ የኔ ህይወት ፍጹም የተቀየረው ታህሳስ 3፤ 1996ዓም (December 13, 2003) በአኙዋክ ሕዝብ ላይ በደረሰው ጭፍጨፋ ምክንያት ነበር። ለሶስት ቀናት በተካሄደው ግድያ 424 የአኙዋክ መሪዎች በግፍ ተገደሉ። ግድያውን የፈጸሙት ህወሃት/ኢህአዴግ ያሰማራቸው ወታደሮች ከታጠቁ የደጋው ክፍል ሚሊሻዎች ጋር በመተባበር ነበር። የጭፍጨፋው ዋና ተልዕኮም የራሱን ዕድል በራሱ ለመወሰን ለፈለገው “የአኙዋክ ሕዝብ ትምህርት ለመስጠት” እንደሆነ በወቅቱ ተነግሯል።
ሕገመንግሥት በተባለው ሰነድ ላይ ይህ መብት በግልጽ የሰፈረ ቢሆንም አኙዋክና ሌሎች የላይኛው ናይል ሸለቆ ወገኖች መሬት ከነዋሪዎቹ ጋር ምክክር ሳይደረግ ለምን ሃብታቸውና መሬታቸው ይወሰዳል ብሎ መጠየቅ ዋጋ ያስከፍላል። በዚያን ወቅት ዋንኛው ምክንያት ነዳጅ ነበር፤ ሲቀጥል ደግሞ ለም ምድር፣ የውሃ ሃብትና ማዕድናትን መዝረፍ ሆነ። ይህ መሰሉ ድርጊት በመፈጸሙ ለልማት መንገድ ለመጥረግ በሚል 16ሺህ አኙዋኮች የመኖር ኅልውናቸው ስለተጠረገ በጎረቤት ኬኒያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ዑጋንዳ ተሰድደዋል።
ከ1996ዓም በፊትም በአገራችን ላይ ኢፍትሃዊነትና የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ ይካሄድ ነበር፤ ሆኖም እውነቱን ለመናገር በዚህ ዓይነቱ ትግል ሳይሆን ጋምቤላን ለማልማት በሚል ደፋ ቀና ስል ነበር። ነገር ግን የአኙዋክ ሕዝብ በአስከፊው የህይወት መስመር ውስጥ በገባበት ጊዜ በጣም ጥቂት የሆኑ ለመርዳት እጃቸውን የዘረጉ መሆናቸውን በወቅቱ መመልከት የሚያም ክስተት ነበር። ይህ የሆነው ከምክንያቶቹ እንደ ዓቢይ ምሳሌነት ሊጠቀስ የሚገባው እኛ ከሌሎቹ ኢትዮጵውያን የተለየን በመሆናችን ነበር። እውነቱን ለመናገር እኛ ከጋምቤላ የመጣን ወይም የደቡብ ኦሞ ሸለቆ ተወላጆች የሆኑ “እንደ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ” የምንታይ ባለመሆናችን ነው።
ትግሉ በብዙ መልኩ እየተካሄደ ከቆየ በኋላ አካሄዳችንን መመርመር አለብን በሚል አንድ ጥያቄ ለራሴ ማቅረብ ጀመርኩ፡- ይኸውም “የአኙዋክ ሕዝብ ለራሱ ብቻ ፍትህና ነጻነትን መጎናጸፍ ይችላል? የሚል ነበር። በሌላ አነጋገር እንደ ኦሮሞ ባሉ በሌሎች ላይ የሚደርሰውን በምንመለከትበት ጊዜ የሚሰማን ነው።
በ1997ዓም በተደረገው ምርጫ እና ከዚያ ጋር ተያይዞ በተካሄደው ማጭበርበር 197 ዜጎች በአዲስ አበባ ሲገደሉ ክስተቱ ሁላችንንም ሊያስተባብረን የሚችል ዕድል ነበር፤ ሆኖም ሳንጠቀምበት ቀረን። በዚያን ወቅት ግን እኔ ጭንቅላት ውስጥ ይደውል የነበረው በዘር ላይ፤ ያውም ደግሞ በአናሳ የዘር ድርጅት፤ የተመረኮዘ ድርጅት አቋቁሞ ፍትህን ማምጣት የሚቻለው እንዴት ነው? የሚለው ጥያቄ ነበር። በወቅቱ የቅንጅት ፓርቲ የተነሳበት ዓላማ በብዙዎች ዘንድ ታላቅ ተስፋ ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም ሁኔታው ከከሸፈ ከሁለት ዓመታት በኋላ የህወሃት/ኢህዴግ ሠራዊት ከጋምቤላ ወደ ሶማሌ ክልል ሲንቀሳቀስ ድምጻቸውን ያሰሙ አልነበሩም። የህወሃት ገፈት ቀማሽ የሆንነው እኛ አኙዋኮች ግን ሠራዊቱ ለምን ክልላችን ጥሎ እንደሄደ መገመት አላቃተንም ነበር። በዚህም በአንዳንድ ዓለምአቀፍ መያዶች ዘንድ “ያልተነገረው ዳርፉር” ተብሎ የሚጠቀሰውን የኦጋዴንን ዕልቂት አስከተለ።
በወቅቱ በአኙዋክ የፍትሕ ምክርቤት የነበርን ከኦጋዴን ወገኖቻችን ጋር ብዙም ግንኙነት ባይኖረንም ስለ ሶማሊ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ዕልቂት፣ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ፣ የመንደሮች መፍረስ፣ የመሰረታዊ ልማቶች መፍረስ እና ስደት ድምጻችንን ማሰማት እንዳለብን ግድ አለን። በዚህም ምክንያት ያኔ ነበር ከእነርሱ ጋር ግንኙነት የጀመርነው። አንድ እንድንሆን የሚያመጣን ነገር ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ለነጻነት፣ ለፍትሕና ለአገራችን ሕዝብ ብልጽግና ለመሥራት እንደሚችሉ ተስፋ የሚሰጠን ነው። ይህ ሆኖ ሳለ እኛ ኢትዮጵያውያን ትርጉም ሊሰጥና ገቢራዊ ለውጥ ሊመጣ በሚችል መልኩ መተባበር ያልቻልነው ለምን ይሆን? ለምን በተደጋጋሚ ባደረግናቸው ትግሎች ከሸፍን?
እኔ እንደማምነው ከሆነ የዚህ መልስ እኛ ኢትዮጵያውያን ተቀብለን በተግባር ላይ ያዋልናቸው ነገርግን ተዓማኒነት የሌላቸው፣ የማይጠቅሙ፣ የማይሰሩና እውነተኛ ያልሆኑ አመለካከቶቻችን ናቸው። እነዚህ አስተሳሰቦች በዚህ ዘመን የማይሰሩ ብቻ ሳይሆኑ ለጋራ ስኬታችን እንቅፋት በመሆን ክሽፈትን ያስከተሉብን ናቸው ብዬ አምናለሁ። እነዚህ እንደገና መመርመር፣ መታየትና መጠናት የሚያስፈልጋቸው ሲሆኑ ስህተት የሆኑትንና የማይጠቅሙትን ሁሉ ልናሸንፋቸው ወይም ልናስወግዳቸው የሚገቡ ናቸው።
ለጋራ ስኬታችን ዕንቅፋት የሆኑብን ምክንያቶች
ለጋራ ጥቅማችንና ስኬታችን ዕንቅፋት የሆኑብን ምክንያቶች የመጡት ከየት ነው? ብለን መጠየቅ መጀመሪያው ሲሆን እንዴት ከእነዚህ ዕንቅፋቶች አልፈን በከፍታዎች ላይ በመብረር የችግራችን ዋንኛ ምክንያቶች እንዳይሆኑ ማድረግ እንችላለን የሚለው በተጓዳኝ ሊጠየቅ ይገባዋል። በቅድሚያ ሊጠቀስ የሚገባው ዕንቅፋት ክሽፈት የተሞላበት አካሄዳችን ነው። በዘር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት ላይ የተመረኮዘ የተናጠል ወቅታዊ ትግል የመጀመሪያ ዕንቅፋት ነው ብዬ መጥቀስ እፈልጋለሁ።
- የተናጠል ወቅታዊ ትግሎች፡- ይህ ማለት በአንድ ወቅት የሚነሳና የሚከስም በዘር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካዊ አመለካከት ወይም ከአንድ ቡድን የተገነጠለ አንጃ ሃሳብ ላይ ትኩረት ያደረገ በነጠላ ሃሳብ ላይ የተመሠረተ ትግል ነው።
በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያውያን ትልቁ ችግር፤ ነጻነት፣ ፍትህና ለህዝባችን ሙሉ ዴሞክራሲ እንዳያገኝ ዕንቅፋት ሆኖ ከፊታችን የተጋረጠው ነገር ሁሉን አሳታፊ ዘላቂ ትግል ከማድረግ ይልቅ የተናጠል ወቅታዊ ትግል ማድረግ ነው። ይህ በነጠላ እየተነሳን የምናደርገው ትግል በጣም የምንወደውና የተዋሃደን የትግል ስትራቴጂ ቢሆንም በታሪካችን በተደጋጋሚ የተረዳነው ግን ይህ አቀራረብና አካሄድ ፈጽሞ እንደማይሰራ ነው።
የተናጠል ወቅታዊ ትግል በምናካሂድበት ጊዜ ዋንኛ ዓላማችን “የወቅቱን ፍላጎታችን” ማሳካት ነው። ይህንን እንድናደርግ የሚነሳሳን ደግሞ በወቅቱ የተከሰተ ግድያ፣ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ፣ ኢፍትሃዊነት፣ መሬት ነጠቃ፣ ወይም ተመሳሳይ በህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ወይም በፊት በነበሩት አገዛዞች ባደረሱት ጭቆና የሚጭረው ቅሬታ፣ ብስጭትና ንዴት ነው። ለእነዚህ ዓይነቶች ኢፍትሃዊ ተግባራት ምላሽ ስንሰጥ ሥራችንን የምናከናውነው ሌሎችን ሳንጋብዝ ወይም ሌሎች ከእኛ ጋር ሳይተባበሩ በተናጠል ነው። በመሆኑም የራሳችንን ሰልፎች፣ የራሳችንን የተቃውሞ ጥሪዎች፣ የራሳችንን ውይይቶች፣ የራሳችንን አቤቱታዎች (ፔቲሽን)፣ … በማቅረብ የራሳችንን ውሳኔዎች አሳልፈን ባላጋራችንን ለመታገል እንነሳና በራሳችን ችግር ላይ ራሳችን ጠላት ሆነን ክሽፈታችንን እንጋብዛለን።
ከዚህ በፊት የተካሄዱና በዚህ ምድብ ውስጥ የሚገቡ፤ ህወሃት/ኢህአዴግ ከአነሳሱ ጀምሮ እየነጠለ ጥቃት ሲያደረገባቸው በመቆየቱ የተነሳ የራሳቸውን የተናጠል ትግል ያደረጉ እጅግ በርካታዎችን መጥቀስ ይችላል። እነዚህ በተናጠል ከተካሄዱ ወቅታዊ ትግሎች መካከል የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ፣ የሲዳማ፣ የአኙዋክ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የአፋር፣ የሶማሊ፣ የሙስሊም፣ የክርስቲያን፣ አሁን ደግሞ የኦሮሞ ተቃውሞ፣ የአማራ ተጋድሎ፣ እያለ መዘርዝሩ ይቀጥላል። እኛ ስንጠቃ ሌሎች ከእኛ ጋር አለማበራቸውንና ድጋፍ አለማሳየታቸውን ስንመለከት እንናደዳለን፣ ተስፋ እንቆርጣለን። በመሆኑም እኛም ሆንን ሌሎች ለብቻችን ተጉዘን ስኬትን ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ወይም የማይቻል መሆኑ እንረዳለን። በሌላ በኩል ይህ ስሜት ሌሎች ከእኛ ጋር ለመተባበር አለመፈለጋቸው ንዴት፣ መራርነትና ጥርጣሬ ውስጥ ይከትተንና ሌሎች ስለ እኛ ግድ የላቸውም ወደሚል ድምዳሜ ላይ እንድንደርስ በማድረግ የበለጠ መራርነት፣ ቂም፣ ቅሬታ፣ ቅያሜ፣ ጥርጣሬ፣ ራስን ማግለል፣ ባይተዋርነት፣ ከዚያም አልፎ “አይፈልጉንም፤ አንፈልጋቸውም” ወደሚል ጥልቅና መራር ስሜት ውስጥ ያስገባናል።
እዚህ ላይ አንድ ማንሳት የምፈልገው ነጥብ አለ። ምናልባት ብዙዎቻችሁ እንደሰማችሁት ከጥቂት ሳምንታት በፊት የመኪና አደጋ ደርሶብኝ ነበር። አንድ የተማርኩት ትምህርት በቅጽበት የምትሰናበተውን ህይወታችንን በሚገባ ልንጠቀምበት እንደሚገባ ሲሆን እንኳን ነገ፣ በደቂቃዎች ምን እንደምንሆን ማስተማመኛ በሌለበት ሁኔታ ሰዎች ስለበቀልና ሌላውን ስለማጥፋት ስልት እየነደፉ ለመኖር መምረጣቸው ሳስብ በጣም አሳዘነኝ። በአደጋው ወቅት ሞትን ለቅጽበት አየሁት። እንዳልወሰደኝ ስረዳ ሰዎች በቅጽበት ታሪክ እንደሚሆኑ በመረዳት በህይወት ዘመናቸው ደግ ለመስራት ለራሳቸው አለመማላቸው አሰብኩ። መለስ ዜናዊ ሲነገረው ቢሰማና ለአንድ ቀን ቀና ሰው ስለመሆን ቢያስብ፣ ብለን ብንመኝ ቢያንስ በቅርቡ ያለቁትን በሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን ነፍስ ማትረፍ፣ እየሰፋ የመጣውን የጎሳ በሽታ መቀነስ በቻልን ነበር። ግን ያሳዝናል በተቃራኒው ነው የሆነው። ያለመውንና ያሰበውን ሳያይ ህይወቱ በጥላቻና በዘረኝነት እንደመረረች ሄደ። እኔ ዳግም የመኖር ዕድል እንደተሰጠኝ ነው የማምነው። እናም ትልቅ ትምህርት ወሰጄበታለሁ። ቅጽበት ለሆነች ህይወታችን ጥላቻና መራርነት፤ ቂምና በቀል የበላ ሆነው እንዲቆጣጠሩን በፍጹም መፍቀድ የለብንም፡፡
- ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ሊጠቅም የማይችል የትግል ስልት በተደጋጋሚ የምንከተለው ለምንድን ይሆን?
ሀ. ታሪካዊ ምክንያት፡- የተለያዩ እርስበርሳቸው የተቆራኙና ሥር የሰደዱ ሁሉን አቀፍ ከሆኑ መብቶች ጋር የሚጋጩ አመለካከቶች። እነዚህም፤
- ጎጠኝነት – አንድን ጎሣ ወይም ጎጥ ከፍ በማድረግ “አንዱ ጎሣ/ጎጥ ሁሉንም ነገር ለራሱ ማድረግ አለበት” ወይም “የመብላት ተራው የእኛ ነው” በሚል ከፋፋይነት ላይ የተመሠረተ ነው። ይህ ላለፉት አርባ ዓመታት ስናየው የኖርነው ሃቅ ሲሆን ለራሴ ጎጥ፣ መንደር፣ እና/ወይም ቤተሰብ እኔ ካልቆምኩለት ማን ይቆምለታል? የሚል አስተሳሰብና ራስንና “የራሴ” ብለን የምንጠራቸውን ለማዳን የተመሠረተ አሠራር በዚህ ውስጥ ይካተታል።
- አጸፋ/ብድር መመለስ፡- አንዱ ጎጥ ወይም ጎሣ በሌላው ላይ ብድሩን መመለስ፤ የራሴ ለሚባሉ ወገኖች፣ ለቅርብ ወዳጆች፣ ለታማኞች፣ በማድላት ጥቅማጥቅሞችን በወገንተኝነት በመነሳሳት መፈጸም የጎጠኝነት አመለካከት ነው።
- ዘውዳዊ – በዘውዳዊ አገዛዝ ሥር የነበረው የኢትዮጵያ ታሪክ በዘር፣ በቤተሰብ ትስስር፣ በደም፣ “በእገሌ ልጅነት”፣ ወይም ለመሣፍንትና ለመኳንንት ታማኝ በመሆን የተመሠረተ ነበር። ይህ ስሜት አሁን ከሞላ ጎደል መልኩን እየቀያየረ ሲንጸባረቅ ይስተዋላል።
- ፊውዳላዊነት – አንድን ቡድን ወይም ጎሣ ወይም ወገን ከሌላው የተለየ፣ የተሻለ፣ የተመረጠ፣ የበቃ፣ ወይም “ስዩመ” ስለሆነ የመግዛት/የመምራት መብት አለው፤ “ወርቃማ ዘር” ስለሆነ ትርፉንም ለራሱ የማድረግ ሥልጣን ተሰጥቶታል፤ ሌሎች ዕድለቢሶች በሥሩ የመሆን ግዴታ አለባቸው የሚል ነው። ይህ ዓይነት አስተሳሰብ የለም ብሎ የሚከራከር ሊኖር ቢችልም እውነታው ግን የፖለቲካ ሥልጣን ወይም ከሕዝብ የሚነጭ ሥልጣን ምንነትን ባልተለማመደችው አገራችን አሁንም እየታየ ያለ አስተሳሰብ ነው።
- ማርክሲስት-ሌኒንስት ኮሙኒዝም – የሚቃወሙትን ሁሉ የመርገጥ ባህርይ ያለው ሲሆን ከፊውዳላዊነት በተለየ መልኩ ማርክሲስታዊ አስተሳሰብ “ሰፊውን ሕዝብ” እየጠቀምኩ ነው ቢልም በተግባር ግን “በጭቁኑ ሕዝብ” ስም የራሱን ሥልጣን ማመቻቸት ነው። ይህ በተለምዶ “የግራው አመለካከት” እየተባለ የሚጠራው በ1960ዎቹ የአገራችንን ወጣቶች የተጣባ ርዕዮት ነው። በዚህ አመለካከት ውስጥ ለአንዱ መኖር የሌላው መጥፋት የግድ ነው የሚል ጽንፈኛ አመለካከት እንደ ሃይማኖት የሚወሰድ ነው። ደርግ “በጠላቶቻችን መቃብር ላይ …” ይል እንደነበረው አሁንም ይህ አባባል በግልጽ ሲነገር ባይሰማም በድርጊት “ለእኔ መኖር ያንተ መጥፋት የግድ ነው” የሚለው የከረረ የግራ አስተሳሰብ በሁሉም መስክ ሲንጸባረቅ ይታል።
- ሥልጣን የማግኛው መንገድ ይኼው ነው – ከሌሎች በመንጠቅ ሥልጣንን የራስ የማድረግ አካሄድ ነው። በታሪክ እንደታየው ሥልጣን ለማግኘት በተናጠል በሚደረግ ትግል አንዱን የዘር/የጎሣ ቡድን በሌሎች ላይ እንዲነግሥ በማድረግ ሌሎችን የበዪ ተመልካች ማድረግ ነው። የህወሃት/ኢህአዴግ የሥልጣን አወጣጥ ይህንን ስልት ከሌሎቹ ስልቶች ጋር ያጣመረ ሲሆን በወቅቱ የሚካሄዱት የተናጠል ትግሎችም ወደዚሁ የሚመሩ ናቸው።
- ከእናንተ ይልቅ እኛ ጭቆናን ታግለን ለድል የበቃን ስለሆነ ሥልጣን የመያዝና በሥልጣን የመቆየት እንዲሁም ምርኮን በመበዝበዝ ተጠቃሚ የመሆን ተራው የእኛ ነው፤ ይገባናል የሚል አመለካከትና አሠራር። ህወሃት የዚህ ሁነኛ ተጠቃሽ ነው። ደርግን ለመጣል ምንም እንኳን ሌሎችም አብረዋቸው የተዋጉ ቢሆንም በራሳቸው ብቃትና በብረት ሥልጣን ላይ እንደመጡ አሁንም በብረት ኃይል ሥልጣን ላይ የመቀጠል ጥማት በግልጽ ይታባቸዋል። ሥልጣን ከፈለግህ እንደ እኛ ተዋግተህ የራስህ ማድረግ ነው የሚል አስተሳሰብ በዚህ ውስጥ የሚካተት ነው።
ለ. አለመተማመን፡ የራስን ዓላማ በሚፈልጉት መንገድ እያስፋፉ ሌሎችን ግን በጥርጣሬ መመልከት፤
- በዘር ላይ በመመርኮዝ ሥልጣንን የመያዝ አባዜ፣ ክህደት፣ ክፍፍል፣ ጥቃት፣ ጉዳት፣ ቁስል፣ ክሽፈት፣ የቆዩ ቅሬታዎች ኢትዮጵያውያንን ሲከፋፍላቸው የኖረ ከመሆን አልፎ ተገቢው ቅጣት ካልተበየነ ወይም ሃብትና የዕድሉ ተጠቃሚነት ወደ እኛ ካልዞረ እነዚህ ቁርሾዎች ዕልባት ሊያገኙ አይችሉም የሚል አስተሳሰብ፤
- አንድን መሪ፣ ወይም አንድን ጎሣ፣ ዘር ወይም ቡድን ለመጥቀም የሚደረገው አሠራር አብሮ የመሥራትንና የመተባበርን ጥረቶች ሲያመክን መቆየቱ፤ ከህወሃት/ኢህአዴግ አሠራር ያልተለየ አዲስ መሪ የሚያመጣ ነገር ግን ለውጥ አልባ አካሄድ፤
- በኢትዮጵያውያን ዘንድ ያለው የድብቅነት፣ ምሥጢራዊነት፣ ተንኮለኝነት፣ መጠላለፍ፣ የሚናገሩትና የሚያደርጉት የመለያየት፣ የአስመሳይነት፣ የማታለልና የግብዝነት ባህርያት ግልጽነትን፣ መተማመንና ተጠያቂነት ያሳጣን በመሆኑ፤
- በአንዳንዶች ዘንድ በግል ወይም በቡድን በሚደረጉ ትግሎች ሥልጣን የመያዝ ድብቅ ምኞቶች መኖራቸው፤ ይህም ማለት “ምንም ችግር የለም አብረን እንሥራ” በሚል አብሮ ቆይቶ በኋላ ሥልጣን ላይ የመቆናጠጥ ድብቅ ዓላማ የማስፈጸም ሁኔታ፤
- ሌሎችን የማሳተፍ እና ወደ እነርሱ የመድረስ ፍላጎት አለመኖር፤ የመከፋፈል፣ የመለያየት፣ የማግለል፣ የመገለል እና ከሌሎች ጋር ለመነጋገር አለመፈለግ፤
- በተቀናጀ ዓላማ፣ መርህ፣ አመራርና አጀንዳ ለመመራት አለመፈለግ፤
- ከማንም ጋር ቢሆን አብሮ ለመሥራት ያለመፈለግና ይህንንም በጠነከረ ሁኔታ መቃወም፤ ምክንያቱም አብሮ በመሆን ሰበብ ሌላውን ለሥልጣን የማብቃት ፍርሃቻ ውስጥ መግባት፤ ወይም እኔ በታገልኩት አንተ ሥልጣን ልትይዝ የሚል አስተሳሰብ፤
- ተመቻችቶ ከተቀመጡበት የራስ ቡድን በመውጣት ከሌሎች ጋር መሥራት ከራስ ቡድን የመገለልና የመባረር አደጋ ውስጥ የሚያስገባ በመሆኑ፤
- ሌሎች የሚፈልጉን ለራሳቸው ዓላማ ማሳኪያ “ሊጠቀሙብን ነው” የሚል አስተሳሰብ በመያዝ በቀጣይ በእነርሱ መዳፍ ሥር በመውደቅ ለችግር እንዳረጋለን የሚል ፍርሃቻ ከዝርዝሮቹ ውስጥ በዋንኝነት የሚጠቀሱት ናቸው።
ሐ. በቅድሚያ ሰብዓዊ ፍጡር ተብሎ ከመጠራት ይልቅ “የዘር/የጎሣ” መለያን እንደማንነት መታወቂያ አድርጎ ላለመተው ማንገራገር፤ የዚህ ምክንያቶች፡-
- ከተለያዩ በርካታ ቡድኖች ድጋፍ ከማሰባሰብ ይልቅ የራሴ ከምንለው ጎሣ ወይም ቡድን የምንፈልገውን ድጋፍ ለማግኘት ቀላል በመሆኑና በተለይም ለዚህ ቡድን ልዩ መብትና ሥልጣን ለማስገኘት የምንታገል መሆናችንን በመግለጽ ተስፋ የሰጠን ከሆነ፤
- ከቡድኑ ወይም ከጎሣው ስብስብ ውጪ የሚሆኑትን ወይም የተለየ ሃሳብ የሚይዙትን እንደ ከሃዲ በመቁጠር ማግለልና ማዋረድ ስለሚቀል፤
- ከታሪክ አኳያ በዘር ላይ የተመሠረተ ነፍጥ የማንሳት (የአርነት ንቅናቄ) ትግልን ለመቀላቀል/ለማድረግ ቀላል በመሆኑ፤
- ከኅብረብሔራዊ ይልቅ በጎሣ ወይም በዘር ላይ በተመረኮዘ አጀንዳ ሥር ሰዎችን ማሰባሰብ የሚቀል በመሆኑ፤
- ኅብረብሔራዊ ከሆነው ይልቅ የራሴ በሚሉት ቡድን ተቀባይነት ለማግኘት የማይከብድ በመሆኑ፤ ቡድኑን በሚፈልጉት አቅጣጫ ለመንዳት ስለሚቀልና የመርህ ጥያቄ ስለማያስነሳ፤
- የቀድሞ ያልተፈወሱ ቁስሎች መገለልን በመፍጠራቸው የባይተዋርነት ወይም የብቸኝነትን ሠንሠለት ለመስበር አስቸጋሪ ማድረጋቸው ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ምክንያቶች ናቸው።
መ. በቅሬታ ወይም በክስተቶች የሚመራ ትግል ጥልቅ መሠረት ከሌለው አይዘልቅም፤
- በአንድ ወቅት የሚፈጸም ኢፍትሓዊነት፣ ግድያ ወይም አሠቃቂ ተግባር የአጸፋ ምላሽ እንድንሰጥ የሚያስተባብረን ቢሆንም ውሱን የተናጠል ወቅታዊ ትግል ከማካሄድ ሌላ ለዘላቂ ትግል ፋይዳ የሌለው መሆኑ፤ ይህ ዓይነቱ ቅሬታ ላይ ያተኮረ ትግል በአንድ ጎሣ፣ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ክልል፣ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው የተሰባሰቡበት በመሆኑ ለዚህ ቡድን ጥቅም ብቻ የሚሆን ምላሽ ከመስጠት ያለፈ ተግባር ለመፈጸም አለመቻሉ፤
- በስሜት የሚነዳ መሆኑ፤ ይህም ደግሞ በአንድ ወቅት የሚነሳሳውን ስሜት ለረጅም ጊዜ ብርታት ኖሮት ለማስቀጠል የሚቻል ባለመሆኑ፤
- እነዚህ በስሜት የሚነሳሱ ትግሎች ሌሎችን ወይም አብዛኛዎችን የሚያነሳሱ ባለመሆናቸው ወይም ሌሎችን በማዕቀፉ የሚይዝ ባለመሆኑ “የኔ ትግል አይደለም” ወይም “ለኔ ምን ይረባኛል?” ወይም “ለኔ ምን ፋይዳ አለው?” የሚሉ አስተሳሰቦችንና አመለካከቶችን በሌሎች ላይ የሚያመጣ በመሆኑ፤ ይህም ደግሞ እነዚህ ትግሉን ያልደገፉ ጥቃት በሚደርስባቸው ጊዜ በተራው “እኛ ስንሰቃይ ስላልረዳችሁን እኛ ስለእናንተ አያገባንም የሚል” አጸፋዊ ምላሽ የሚያስከትል በመሆኑ በዚህ ሥር ከሚጠቀሱት በርካታ ምክንያቶች የተወሰኑት ናቸው።
እነዚህን መሰናክሎች ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው?
ከላይ ከተጠቀሱት መሰናክሎች አኳያ እነዚህ እንቅፋት የሆኑብንን የታሪክ፣ ያለፉ ቅሬታዎችን፣ የግልና የጎሣ ግጭቶችና ምኞቶች አሸንፈን ይህንን የሽንፈት ዑደት ሰብረን የምንወጣው እንዴት ነው? የሚለው መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ነው። በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ከምንጊዜውም በላይ የከፋ አደጋ ተጋርጦብናል፤ ታዲያ ምን ማድረግ ነው የሚሻለን?
- የተለያዩ ሰዎችን የተካተቱበት ሁሉን አሳታፊ ዘላቂ ትግል መፍጠር፤
ሀ. ሁሉን አሳታፊ ዘላቂ ትግል እንደ ባህል በህዝብ ውስጥ እንዲሰርጽ ማደፋፈር፤
- ትግሉ የሰው ልጆችን ሕይወት፣ መብቶች እና የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ማንነት በሚያከብር መልኩ በመርህ ላይ መመሥረት፤
- ትግል ማለት መቃወም ብቻ አይደለም፤ ትክክለኛው ትግል ሁሉንም ኢትዮጵውያንንም የሚጠቅም መሆን መቻል አለበት – ይህ ደግሞ ተሳስተዋል የምንላቸውንም የሚጨምር ነው፤
- እንደ አገር ችግራችን የተጀመረው ህወሃት/ኢህአዴግ በ1983 ወደ ሥልጣን ሲመጣ አይደለም፤ ወደኋላ መለስ ብለን የቀደመውን ሥርዓታችንን፣ አንዳችን በሌላችን ላይ ያለንን አመለካከታችንን፣ ወዘተ ማጥናት ያስፈልገናል፤ ይህንን በማድረግ ሌሎችን በዘር፣ በጎሣ፣ በአመለካከት፣ በሃይማኖት፣ በቆዳ ቀለም፣ በፊት መልክ፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ ወዘተ ሳንከፋፍል ለሁሉም የሚበጅ የፍትሕ ሥርዓት፣ እኩል መብቶችና የኢኮኖሚ ጥቅማጥቅሞች፣ ነጻነትና አክብሮት ለመሥጠት የሚያስችል ሥርዓት ለመመሥረት ያስችለናል፤
- ለሥልጣን እና የራሳችንን ልዩ መብት ለማስከበር የምናደርገው የተናጠል ወቅታዊ ትግል ጊዜውን ጠብቆ የሚከሽፍ ነው። ከላይ ለማስረዳት እንደሞከርኩት እኔ ራሴ የነበርኩበት የአኙዋክ ትግል የተናጠል ወቅታዊ የነበረ በመሆኑ ከእኛ አካባቢ ያሉት ሌሎች ነጻነታቸውን ሳይጎናጸፉ በአኙዋክ ትግል መቼም ቢሆን ነጻነትን መጎናጸፍ እንደማይቻል ግልጽ ነበር። አሁንም ያለው ሁኔታ ይኸው ነው – በተናጠል የሚደረግ ወቅታዊ ትግል የታሰበበት ለመድረስ ራሱ ችግር ውስጥ የሚከት በመሆኑ።
- የምንፈልገውን ለውጥ ሆነን መገኘት ይገባናል። ይህ ከአሁኑ የሚጀምር እንጂ ሥልጣን ላይ ተኹኖ የሚታሰብ አይደለም። ስለሆነም ለምንሻው ለውጥ ከአሁኑ ኃላፊነት ልንወስድ ይገባናል።
- ከሌሎች አገራት መማር ያስፈልገናል፤ ከሶማሊያ፣ ከሊቢያ፣ ከሶሪያ፣ ወዘተ፤ የሚገባንን ትምህርት ልናገኝና ለአገራችን በተግባር ልናውለው ያስፈልጋል፤ የእነዚህ አገራት ዜጎች ተሰባስበው ለሕዝባቸው የሚጠቅምና ሁሉንም የሚሳትፍ የላቀ አጀንዳ ይዘው በመነሳት ተግባራዊ ማድረግ ተስኗቸው የራሳቸውን ከፋፋይ ሃሳቦችና ዓላማዎች ለመተግበር በመወጠን ለአገራቸው መፍረስ ከሆኑ ምክንያቶች አንዱ ሆነው ይጠቀሳሉ፤
- “ሌሎችም” ይገባቸዋል የሚል አስተሳሰብ በግልጽ ልናስቀምጥ ይገባናል፤ ባለፉት ጊዜያት ባብዛኛው ያለው አመለካከት የአንድን ቡድን ዓላማ ወደፊት በማድረግ አገሬን እወዳለሁ በሚል ማስመሰያ የሌሎችን መብቶች በመርገጥ የራስን ቡድን ብቻ ማበልጸግና ከፍ ማድረግ በተደጋጋሚ የከሰረና የማይሰራ መሆኑን መገንዘብ በውል ያስፈልጋል።
ለ. እነዚህን የላቁ መርኾዎች የሚያስተዋውቁ ፖለቲካዊ ያልሆኑ ተቋማት ሊፈጠሩ ይገባል፤
- ፈጣሪ ለእኛም ሆነ በቅርብና በሩቅ ለሚገኙት ወገኖቻችን የሰብዓዊነትን ክብር ሰጥቶናል፤ ይህንን ተጠቅመን በተሻለ አመለካከት ለሕዝባችን የሚረባውን ልናደርግለት ያስፈልጋል፤
- በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በዘር፣ በአርነት ንቅናቄዎች፣ በሃይማኖት ድርጅቶች፣ በክልል፣ እና በሌሎች ቡድኖች የተደራጁ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሠራ ዓላማ፣ ግብና መርኽ ሊኖራቸው ይገባል፤
- እነዚህን መርኾዎች በሲቪክ ድርጅቶች አማካኝነት እንዴት መጠናከር እንዳለባቸው፤ ወደፊት ሊመጣ ስላለው ችግር ካሁኑ እንዴት እነዚህን መርኾዎች ማቀናበር እንደሚገባ እንዲሁም ይህንን በማድረግ በኢትዮጵያ ላይ ሊመጣ ካለው መከራ እንዴት መጠበቅ እንደሚቻል ሊመክሩበት ይገባል፤
- እነዚህን ሁሉ በቅንብር በማካሄድ የአገራችንን የወደፊት ዕጣ እንዴት በሰላማዊ ሽግግር ለማምጣት እንደሚቻል እነዚህ ቡድኖች ሊመክሩበት የሚገባ ነው፤
- ሁሉንም የምታስተናግድና ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያ እንዴት መመሥረት እንደሚቻል በማጥናት በአገራችን ላይ ውድመትና ጥፋት እንዳይመጣ እንዴት መከላከል እንደሚቻል አስቀድሞ ሊሰራበት የሚገባ ተግባር ነው፤ ይህንንም ለመተግበር ሁሉን ዓቀፍ የሆነ ጠንካራ ተቋም – የኢትዮጵያ ጉዳዮች ተቋም (ኢጉተ) – የሚባል ካሁኑ ልንመሠርት እንችላለን (ወደፊት እንዳስፈላጊነቱ የሚቀየር ስም ነው፤ እኔ የራሴን ስም ነው የሰጠሁት፤ ወይም ይህንን ስብሰባ ወደዚያ የሚደርስ ልናደርገው እንችላለን)
- ተቋም ማቋቋም እና በዚያ መስክ የተቀናጀ ሥራ መሥራት ከሚለው አኳያ የጋራ ንቅናቄያችን በቅርቡ የኢትዮጵያ የዕርቅና ርትዓዊ ፍትሕ ምክርቤት የሚባል ተቋም መሥርቷል። ስለዚህ ተቋም በጥቂቱ የምለው ይኖረኛል።
ሐ. በሽግግር ወቅት ተቋማት ሊኖራቸው ስለሚገባ ባህርያት፤
- ለነጻነት፣ ለፍትሕ፣ ለደኅንነት፣ ለመብቶች መከበር እና ሁሉም ኢትዮጵያዊ – ትግሬዎችንም ጨምሮ – በሁሉም ክልል በሰላም በሚኖርበት ሁኔታ ላይ መሥራት፤
- የአገር ውስጥ ልዕልና እንዲከበርና ይህም በመርህ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በማድረግ መበታተንና መከፋፈል እንዳይኖር ማድረግ፤
- ለሁሉም ሰው ደኅንነት መሥጠት – የሁሉም ሰው ህይወት እንዲከበርና በማንም ሰው ላይ አንዳች አደጋ ወይም ጉዳት እንዲደርስ አለመፍቀድ፤ ይህ ደግሞ በተለይ በዘር ላይ የተመረኮዘ አደጋና ደም መፋሰስ እንዳይኖር ማድረግን ይጠቀልላል፤
- በሽግግሩ ወቅት ለኢፍትሃዊነት ማብቂያ ማድረግ፤ የሕግ የበላይነትን ማክበር፤ ይህንንም በማድረግ ትርጉም ያለው ተሃድሶ እንዲመጣ ማድረግና ይህም ደግሞ አድልዖ በሌለበት መልኩ ርትዓዊ ፍትህ በዕርቅ እንዲመጣ መሥራት፤
- ጠንካራ እና ገለልተኛ ድርጅቶች የሚኖሩ ከሆነ አገሪቱን ከመፈራረስ የሚታደጉ በመሆናቸው ብሶት ያለባቸው ወገኖች በግጭት፣ በዓመጽ ወይም በሌላ አገር ጠለላ በማግኘት መፍትሄ ከሚሹ ይልቅ በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ የሚገኝበትን መንገድ መፈለግ፤ ማመቻቸት፤
- በአገሪቷ ውስጥ በተንሰራፋው ሥር የሰደደ ጥላቻ ምክንያት ፍትሕ እንዳይጓደል ተቋማት መብቶች እንዲከበሩ እና የሕዝቡ ልዕልና እንዲከበር የማድረግ ሚና እንዲጫወቱ፤
በቅርባችን ያለችውን ሊቢያ ብንመለከት በተቃዋሚነት የተነሱት ኃይላት ለሕዝባቸው የሚጠቅም በመርህ ላይ የተመሠረተ ራዕይ ሊኖራቸው ባለመቻሉ፤ ለሁሉም የሚቆም ተቋም ባለመመሥረቱ አገራቸው ከሸፈች። በሶሪያም ዜጎች በትናንሽ ቡድኖች በመከፋፈላቸውና የጋራ ዓላማና ራዕይ ሳይኖራቸው በመቅረቱ በሚያሳዝን ሁኔታ አገራቸው ክፍቷን እየቀረች ነው።
የኢትዮጵያ የዕርቅና ርትዓዊ ፍትህ ምክርቤትን ማቋቋም ለምን አስፈለገ?
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲኖርና የወደፊቱ የአገራችን ሁኔታ ተስፋ ያለው እንዲሆን አንዱና ብቸኛ አማራጭ ዕርቅና ርትዓዊ ፍትሕ ማስፈን ስንችል ነው። ይህ ማለት ያለፉትን፣ አሁን ያሉትን እና ወደፊት ሊነሱ የሚችሉትን የበርካታ ዓመታት ጥርቅም ብሶቶች የምናመክንበትና ትርጉም ያለው ተሃድሶ ማድረግንም የሚጨምር ነው። ላለፉት መቶዎች ዓመታት እርስበርስ በተፈጠሩት ቁርቋሶዎች፣ ስህተቶች፣ በደሎች፣ … የተከሰተው የኅሊና ወቀሳ፣ ሃዘን፣ ቁስል፣ ህመም፣ መራርነት፣ … ይህንን ተከትሎ በማያቋርጥ አዙሪት ውስጥ እንድንገባ ያደረገንን ያለፈውን ህመማችን ሁሉ ወደ ዕርቅና ፈውስ መምጣት አለበት። እጅግ አሰቃቂ ነገሮች የደረሱብን ነን፤ በዚህም ምክንያት በአንድ ወቅት አሳዳጅ የነበረው ጊዜ ጠብቆ ተሳዳጅ ይሆናል፤ ይህ የማያቋርጥ የበዳይና የተበዳይ ዑደት አልለቅ ብሎን ዘመናትን አስቆጥረናል።
ከዚህ ግን መውጣት የምንችልበት አማራጭ መንገድ አለ። በአገራችን የሕግ የበላይነትን ተለማምደን የምናውቅበት ዘመን ባለመኖሩ ብሶቶቻችን መፍትሔ ሳያገኙ እዚህ ደርሰናል። ባለፉት ዘመናት የተከሰቱትን እያንዳንዱን ስህተቶች ወደኋላ ሄዶ ለማስተካከል አይቻልም፤ ነገር ግን ለወደፊቱ ህይወታችን አዲስ ራዕይ ከፈጠርን ይህን ያለፈውን ታሪካችንን በአንድ ምዕራፍ ዘግተን የወደፊቱን በአንድነት መጓዝ እንችላለን። ይህንን እናደርጋለን የምንል ከሆነ ያለፈው ታሪካችን አስተማሪያችን ሊሆነን ይገባል እንጂ የወደፊቱን የሚወስንልን አድርገን በመውሰድ በመንገዳችን ላይ ዕንቅፋት አድርገን ፍትሕ፣ የሕግ የበላይነትና የበለጸገች ኢትዮጵያን እንዳናይ ሊጋርደን አይገባም። እንግዲህ እነዚህ መሠረታዊ እሳቤዎች ከላይ በተጠቀሰው በምክርቤቱ ተልዕኮ ውስጥ የተካተቱ ናቸው።
የተናጠል ትግል የሚያደርጉ ግፍን በሚታገሉ ጊዜ የራሳቸውን የአርነት ንቅናቄ መፍጠር አማራጭ ያለው መፍትሄ አድርገው ይወስዳሉ። በ1960ዎቹ የተጀመረው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ጥያቄ መልስ ማስገኘት ቀዳሚ ዓላማው አድርጎ መቀጠል ነበረበት። ይህ ግን ሳይሆን ቀረ። ከዚያ ኪሣራ በኋላ ያየነው ነገር ቢኖር በየቦታው የራስን ወገን ነጻ ለማውጣትና ከኢትዮጵያ ለመገንጠል በየክልሉ የተነሱ የአርነት ንቅናቄዎችን ነው። ሁሉም ለነጻነት እታገላለሁ በማለት የራሱን የአርነት ንቅናቄ ዓላማ ማስተጋባት ጀመረ – የኦሮሞ ነጻነት ግምባር (ኦነግ)፤ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግምባር (ኦብነግ)፤ የቤንሻንጉል ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ቤሕነግ)፤ የጋምቤላ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ጋሕነግ)፤ የሲዳማ ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግምባር (ሲብነግ)፤ የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲዊ አንድነት ግምባር (አርዱፍ) ጥቂቶቹ ናቸው።
መብቶችን መጣስ የሚያስከትለውን ውጤት ለመረዳት ከዚህ በላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች ድርጅቶች ባህርይ ማጥናት ምላሽ የሚሰጥ ነው። ይህ ግን በራሱ ለችግሮች ዘላቂ ምላሽ የሚሰጥ ሳይሆን ይበልጡኑ ችግሮችን እያሰፋ የሚሄድና ስህተትን እየደገምን እንድንሄድ የሚያደርገን አካሄድ ነው። በሥልጣን ላይ የሚቀመጠው ማንም ይሁን ሥርዓቱን የሚገዳደር ጠንካራ ተቋም መመሥረት ነው እንጂ የሚያሻው ሌላ አካሄድ የሚፈይደው አንዳች ነገር የለም። አለመታደል ሆኖ ይህ አመለካከት አሁንም ህወሃትን እንታገላለን በሚሉ አንዳንዶች ዘንድ ያልተለወጠ አመለካከት ነው።
ከሁለት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ህወሃት/ኢህአዴግን በሃይማኖታቸው ውስጥ ጣልቃ መግባቱን ተቃውመው በሰላማዊ መንገድ መታገል ጀመሩ። አገር ቤት ያሉት የታገሉት ለአንድ ቀን፣ ለአንድ ሳምንት፣ ለአንድ ወር ወይም ለአንድ ዓመት ሳይሆን አገዛዙ አመራሮቻቸውን ሰንጥቆ በመግባት ዓላማውን ለማሳካት እስከቻለበት ጊዜ ድረስ ለሁለት ዓመታት ነበር። ብዙዎች እስርቤት ገቡ ከእነርሱም መካከል እስካሁን ያልተፈቱ አሉ። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ትግል ስኬት ሊያገኝ ያልቻለው ሌሎች በደል በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን – ኦሮሞዎች፣ አማራዎች፣ ሶማሊዎች፣ ወዘተ ትግሉን ሊቀላቀሉ ባለመቻላቸው ነው። ከእነዚህም ሌላ የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ችግሩን ችግራቸው አድርገው ባለመውሰዳቸውም ነው።
ባለፉት ጊዜያት እንደተከታተልነው የኦሮሞ ትግል፤ የአማራ ተጋድሎም እንዲሁ ተካሄደ፤ አሁንም በተወሰነ መልኩ ረገብ ቢልም በተለያየ መልኩ እየተካሄደ ነው። ኢትዮጵያውን ሙስሊሞችም ሆኑ ኦሮሞዎች፣ አማራዎች፣ … የሚጠይቁት አንድ ትልቅ ጥያቄ ለውድቀት ሳንዳረግ ተባብረን መቆም የምንችለው እንዴት ነው? የሚለው ነው። ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንዳየነው የዚህች አገር ችግር በተናጠል ትግል የሚፈታ አይደለም። ሁላችንም አብረን ነጻ ካልወጣን ማንም ብቻውን ነጻ መሆን አይችልም!
ትልቁ ጥያቄ – አሁን የምንታገለውን ሥርዓት ማፍረስ የምንፈልገው ይህንኑ በሚመስል ሌላ ሥርዓት ለመለወጥ ነው? በተናጠል ወቅታዊ ትግል የምናደርግ ከሆነ ውጤቱ ከዚህ የተለየ ሊሆን አይችልም። የአገራችንም ሁኔታ ባክኖ ይቀራል። መባከን ማለት አንድ ታላቅ ዋጋ ያለው ነገር እንደሚገባው ባለመጠቀማችን ምክንያት ዋጋው ከንቱ ሲሆንና ጥቅሙ ባክኖ ሲገኝ ነው። ይህ የእኛ ሁኔታ ሲሆን በተደጋጋሚ ታይቷል። ዓቅማችንና ዕድሎቻችንን በተደጋጋሚ ስናባክን ኖረናል።
በኢትዮጵያ ያለን የተፈጥሮ፣ የውሃ፣ የማዕድናት፣ ወዘተ ሃብት ብቻ ሳይሆን የሰውም ሃብት ነው ያለን። በጋምቤላ ስላለው የሺያ ዛፍ ሳስብ ብዙ ነገር ወደ አእምሮዬ ይመጣል። ይህ ዛፍ እጅግ በርካታ ለሆኑ ጥቅሞች በዓለም ዙሪያ መዋል ሲችል አለአግባብ እየተጨፈጨፈ ይገኛል። ይህንን ደግሞ ለመተካት በርካታ ዓስርተ ዓመታትን ይወሰዳል። በተመሳሳይ ሁኔታ እስቲ ስለ ወጣቶቻችን እናስብ። ስንቶቹ በድህነት፣ በዓመጽ፣ በመብት ገፈፋ፣ በህክምና ዕጦት፣ … ገና በጨቅላ ዕድሜቸው እየተቀጡ ይሆን?! ስንቶቹስ የህይወታቸውን መስመር ለማስተካከል ብለው እንደወጡ ቀርተዋል? ስንቶቹስ የአልጋ ቁራኛ ሆነዋል? እጅግ በጣም ብዙ! ስለዚህ ፈጣሪ የሰጠንን መርኾዎችን በመከተል ይህንን መከራ ማስቆም፤ አሁን ያለን ዕድል እንዳያመልጠን፤ እንዳይባክንብን አጥብቀን ልንሰራ ይገባናል።
አቅጣጫችንን ለመቀየር ከየትና እንዴት እንጀምር?
- በምንስማማባቸው ጉዳዮች ላይ የጋራ ራዕይ መቅረጽ፤ ስኬትን የምንሻ ከሆነ ለማግኘት የምንፈልገው ዋናው ነገር ምን እንደሆነ በቅድሚያ ልናውቅ ይገባናል። ይህንን ካስቀመጥን በኋላ አንድ የጋራ ራዕይ መቅረጽ ወደሚያስችለን ደረጃ ላይ እንደርሳለን። ይህ ራዕይ ሁላችንንም የራሴ ብለን በምንወስዳቸው እሴቶች ዙሪያ እና የሁሉንም ጥቅም ሊያስከብር በሚችል መሠረት ላይ ሊገነባ ይገባዋል። ወደ ሌሎች የተለያዩ አጀንዳዎች ከመገባቱ በፊት ይህ ራዕይ በቅድሚያ ተቀምጦ የሁሉንም አዎንታ ማግኘት አለበት።
- የጋራ ራዕይ፡ ማንኛውንም ችግር፣ ለዘመናት የተጠራቀመ ቅሬታ፣ አለመግባባት፣ … ለመፍታት ከመጀመራችን በፊት የጋራ ራዕይ በቅድሚያ ያስፈልገናል። የጋራ ራዕይ በስምምነት ከነደፍን በዚያ ላይ ተመርኩዘን ሁሉንም ችግሮች ወደ ስምምነት በሚያመጣ መልኩ መፍትሔ ልንሰጣቸው እንችላለን።
- ራዕያችን በስሜት ሳይሆን በመርህ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት፤ ለምሳሌ አንዱ መርህ “ከጎሣ በፊት ሰብዓዊነት ይቅደም” የሚለው ሊሆን ይችላል፤ ወይም “ሁላችንም ነጻ ካልወጣን ማንም ብቻውን ነጻ ሊሆን አይችልም” በሚል መርህ ለሌሎች ነጻነት ግድ ማለት።
- ይህንን የጋራ ራዕይ ለመንደፍ በሁሉም ባለጉዳዮች ዘንድ ውይይት እንዲኖር ማድረግ፤ ሁሉንም የሚያካትት ራዕይ ለመቅረጽ እንዲቻል፣ ሁሉንም የሚጠቅም የፍትሕ ሥርዓት ለመዘርጋትና ነጻነት ለማምጣት የአገራችን ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሁሉ ተገናኝተው መወያየት፣ መነጋገር ይገባቸዋል።
- በኢትዮጵያ ደም መፋሰስ እንዳከሰትና አገሪቷ እንዳትከፋፈል በኅብረት መሥራት፤
- በህወሃት/ኢህአዴግ ውስጥ ያሉትንም ጨምሮ የማንም ኢትዮጵያዊ ህይወት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ከለላ ማድረግ፤ ቃል መግባት።
- የጋራ ራዕይ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ጠቅሞ በሰው ህይወት፣ በንብረት ወይም በማንኛውም መዋዕለንዋይ ላይ ጥቃት እንዳይኖር በማድረግ ኢትዮጵያ ቀጣይ ሊቢያ ወይም ሶሪያ እንዳትሆን መታደግ።
ይህንን ዓይነት የጋራ ራዕይ መንደፍ ከቻልንና ሁሉንም ሊያስተባብር ወደሚችል ተቀባይነት ያለው መርህ ላይ እኛ ኢትዮጵያውያን መድረስ ከቻልን የሌሎችን ክብር፣ ማንነትና እሴት የምታከብር የሁላችንም የምትሆን አዲስ ኢትዮጵያን መመሥረት እንችላለን። የጋራ ንቅናቄያችን ከዚህ በፊት ሲያደርግ እንደኖረው አሁንም ለዚህ መሳካት የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ እና ከሁሉም ወገኖች ጋር ለመሥራት፤ ሁሉንም ወገኖች ወደ ውይይት ለማምጣት ያለውን ፍላጎትና ፈቃደኛነት በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ። ሁላችንም ለእያንዳንዳችን፤ እያንዳንዳችንም ለሁላችን መቆም አለብን።
ስለዚህ “የወንድሜ ጠባቂ ማነው?” የሚለውን ዘመናት ያስቆጠረው ጥያቄ ሲጠየቅ እያንዳንዳችን ኢትዮጵያውያን በዘር፣ በጎሣ፣ በቆዳ ቀለም፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በመልከዓምድር፣ በእውቀት፣ ወይም በማንኛውም መስፈርት ሳንከፋፈል “የወንድሜ ጠባቂ እኔ ነኝ፤ እኔን ያገባኛል” ማለት መቻል አለብን። ስለዚህ የምንታገለው ለመንቀል ብቻ ሳይን ለመትከልም መሆን አለበት። ይህንን የመትከል ሥራ የምናከናውንበት አንዱና ብቸና መንገድ ዕርቅና ርትዓዊ ፍትሕ ማስፈን ስንችል ነው።
ይህን ለማድረግና እያንዳንዳችን በትክክለኛው የአንድነት፣ የፍትህና የነጻነት መንገድ ለመጓዝ፤ ለመንቀል ብቻ ሳይሆን ለመትከልም እንድንችል ፈጣሪ ይርዳን!
አክባሪያችሁና ወንድማችሁ
ኦባንግ ሜቶ
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር
ኢሜይል፡- Obang@solidaritymovement.org
Leave a Reply