
ባልና ሚስት ሆነን መስርተን ትዳር
ልጆችም አፍርተን አንዳችም ሳይቀር
ተመሥገን ፈጣሪ ምኞቴ ተሟላ
አልቀይርም ሕይወት ይሄንን በሌላ
ተሥፋ ለወደፊት ምሥጋና ሣሰማ
ነገሩ ሌላ ነው ለካሥ ያንቺ ዓላማ
የወለድናቸውን ልጆች በየተራ
መንፈሥ እየቀየርሽ በተንኮል በሤራ
እየመከርሻቸው የመለየት ሥራ
ቤታችን ነገሠ ኩርፊያ አተካራ
የገነባነውን ሐብትና ትዳር
መጠበቅ ሲገባን በጋራ በምክር
አንቺ ትብሽ እኔ በለን እንደአዋቂ
ቀጣይ ትዳር ሆኖ ወደፊት ዘላቂ
እንዲሠፍን ሰላም እንዲከተል ተድላ
ሁሌም እንደመትጋት በጋራ በመላ
አንቺ ግን ጥላቻ ልጆቹን አስተምረሽ
በጎሪጥ ተመልካች ከሁሉም አናክሰሽ
አጥሩ እንዲላላ ከውስጥ እንደመዥገር
እየቦረቦርሽው እንዳይኖረው ማገር
ይጠቅሰው የነበር ሁሉም በምሣሌ
ቤታችን አመራ ወደ አልባሌ
ለልጆቼ ባዳ ባይተዋር ላገሩ
የሌለ በዓለም በጎጥ በመንደሩ
እንድንሆን ከንቱ የሌላቸው ተስፋ
ለማድርግ አስበሽ ትዳሩን የከፋ
ለካሥ ነበር ያንቺ ዓላማ ውጥኑ
እኔ መቼ ገባኝ ተንኮል የዘመኑ
ሃያ ስድስት ዓመት እስቲ ይሁን ብሎ
ቤተስቡ ሁሉ ያንቺን ዕብደት ችሎ
በጊዜ ይገባታል ሁሉንም ተረድታ
ትመለስ ይሆናል ጥጋቧንም ገታ
ብሎ ቢታገስሽ ፈጥሪውን ፈርቶ
አንቺ ግን አይገባሽ ካልሆነ ተዋግቶ
ሥትኖሪ በትዳር በወግ በማዕረግ
ተጠልፌ ነበር ትዳሬን ሣላደርግ
የሚል ጉድ አመጥሽ እንደ ሠበር ዜና
ከማስቆጨት አልፎ ትንሽ የሚዝናና
እረ አደብ ግዢ ታሪክ አትፈብርኪ
ምን ቢደረግ ይሆን ባለሽ የምትርኪ
እግዜር ይሰጥንን በጋራ ተካፍሎ
እንደመብላት ዕና መጓዝ ተቻችሎ
አንቺ ግን አመጣሽ ሁሉም ይሁን ለኔ
ጥጋብ ልብ ደፍኖ ይበደል ወገኔ
ሠላምና ፍቅር አንድነት ባይገባሽ
የጊዜ ጉዳይ ነው ልምከርሽ ከሰማሽ
አይሳካልሽም በተንኮል በሴራ
ቤት ማፍረስ በቀላል የቆመ በጋራ
ልጆቼ መስሏቸው በትቢት ቢመሩ
በማሥተዋል ታሪክ ባንድላይ ሲማሩ
ያጠፋሁት ካለ እኔም በበኩሌ
ላንቺ የማይጥምሽ ሥሕተት ካመሌ
ሲሆን ተነጋግረን ሽማግሌ ጠርቶ
በይቅርታ መንፈሥ ችግሩን አብላልቶ
ፍታዊ የሆነ ዳኝነት ተሰርቶ
ይሥተካከልና ሁሉም እንደቀድሞ
ቤታችን እንግባ ትዳሩም ታክሞ
ይሕንን ቁምነገር አንቺስ መች አጣሺው
አልፈታ ቢልሽ በቂም የቋጠርሺው
ጊዜው ያንቺ ቢሆን በተንኮል መበተን
መለያየት ፍጡር ወገንነ ከወገን
እንዲሁም ይመጣል ጊዜ ለሰብሳቢ
በፈሪሃ እግዚአብሄር ሁሉንም ዓሳቢ
ይሄ እንደሚሆን ባልጠራጠርም
እስከዛ አደብ ግዢ በትቢት አይሆንም
መኖር አይቻልም ሁል ጊዜ በትቢት
ቀን እንዳጎልብሽ ወይዘሮ ደደቢት
ቦምቡ ፍቅርሽ 2017
(ጌትሽ ማሞ ባወጣው እንከባበር ዜማ ወትዋችነት የተገጠመ – ፎቶ አርአያ ጌታቸው)
Leave a Reply