• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ዝምታሽ አልበዛም ኢትዮጵያዬ?

April 4, 2014 07:16 pm by Editor Leave a Comment

(ይህ ጽሁፍ “የተገነቡትና በመገንባት ላይ ያሉት የመታሰቢያ ሐውልቶች የሠማዕታት ወይስ የቅሱፋን?” በሚል ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው ለጻፉት የተሰጠ ምላሽ ነው)


መቼም ታሪክሽ መያዣ መጨበጫ ያጣ ይመስላል፡፡ ሁሉም ተነስቶ የሚጽፈው አይነት ሆኖልሻል፡፡ አንዳች እውነት ውስጡ ለማግኘት በደንብ መበርበር የሚፈልግ፤ አንደኛው የሚጽፈውን ሌላኛው በእርግጥም ድብን አድርጎ አሳማኝ በሆነ ሁኔታ የሚሽርበት አይነት ነው፡፡ ሀገሬ ግን በመሀከል ቤት ቁጭ ብለሽ ታሪክ አልባ እየሆንሽ ያለሽ መሰለኝ፡፡ በ‹‹አዋቂነት እርሾ›› ሰበብ ሁሉም እየተነሳ የሚጽፍብሽ አይነት ሆነሽ፤ ቀራጺውም፤ ሰዓሊውም፤ የታሪክ ምሩቁም፤ ፖለቲከኛውም፤ ለቀስተኛውም፤ አላቃሹም፤ ታሪክ ጸሐፊ ሆኖብሽ የተቸገርሽ መሰለኝ ሀገሬ፡፡ ሀገሬ ምናባቴ ላርግሽ? ምን ይሻልሽ ይሆን? እኔም ታዲያ ልጠይቅሻ፡፡ እንደእናት አንድ በይኝ፡፡ መልስ ስጪኝ እናት አለም፡፡

አንድነትን ሰበብ አድርገው ማንነትን የሚሞግቱ ‹‹አዋቂዎችሽ›› ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡ አሁንም የሚሉት ያላቸው መሰለኝ፡፡ እያሉም ነው፡፡ በመከባበርና በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ አንድነትሽን የሚናፍቁና ቢሆን የሚወዱ እንዳሉ የተረዱት ‹‹አዋቂዎችሽ›› እናትነትሽ ለእነርሱ እንጂ ለሌላው እንዳልሆነ እየመሰከሩልሽ ነው፡፡ ሌሎችስ ማን አላቸው ያላንቺ? ሀገሬ ይገርምሻል አዋቂ የሚባሉት ሰዎችሽ ለሽምግልናና ለማሳያ የምንጠቀምባቸው የነበሩ ግለሰቦች ነበሩ፡፡ ዘቀጡ፡፡ ለልጆችሽ እልህ እንጂ ታሪክና መሰንበቻውን የሚያቆይሽ ነገር አላስቀምጥልሽ ብለው ይኸው አሰቃዩን፡፡ ‹‹አዋቂዎችሽ›› ግን ምን ነካቸው?

ሀገሬ ግን እውነት ታውቂናለሽ? እኛ በእርግጥም በውስጥሽ አለን? ነው ወይስ ተሳስተሸ ይሆን ያኖርሽን? አሁን መቼም አንቺ ስለሆንሽ እንጂ ሌላ ሀገር ቢሆን እንዲህ ይዘቀጣል? ይግረምሽ ብሎ አንደኛው ሠዓሊሽ ‹‹የታሪክ ምሁር›› ነኝ ብሎ ነው መሰለኝ ለህትመት ያበቃውን አየሁልሽና ከፋኝ፡፡ ስለዚህም እነግርሻለሁ፡፡ ቢያቅርሽም ቅሉ ስሚኝ፡፡ ወደድሽም ጠላሽም ጊዜ ስጪኝ ሀገሬ፡፡

ሠዓሊው ሰውዬሽ የመታሰቢያ ሐውልቶችሽ ለማን እና ለምን እንደሚሰሩ (ጠበቅ ተደርጎ ይነበብ) በሚሞግትበት (ምናልባት በተለይ ለኦሮሞ ህዝብ ያለውን የወረደ የክብር ልክና ስሜት ያሳየበት ይመስላል) ጽሁፉ ሕወሓት/ኢህአዴግን ሀገር አጥፊ ነው እያለ፤ በትጥቅ ትግሉም ግዜ ያለፉትን ታጋዮች በህይወት ካሉት እንደማይለዩ፤ ኢህአዴግ ለወደፊቱም እያኖረ ያለው ነገር መልካም አይደለም ሲል ያክላል፡፡ በዚህ ጽሑፉ ግን የአንቺ አንድነት ያሳሰበው መስሎ ልጆችሽን (በተለይ የኦሮሞ ተወላጆችና ብሔሩን በአጠቃላይ) ሙልጭ አድርጎ ያንቺ እንዳልሆኑ አስረድቶልሻል፡፡ ልጅሽ ከሆነ ገስጪው ሀገሬ፡፡

ሰዓሊው ‹‹ታሪከኛ›› ልጅሽ መሳይ ገንጣይሽ ትምክህቱን አራግፎታል አልኩሽ፡፡ መቼም አይተሽዋል፡፡ ሰምተሽውማል ብዬ አስባለሁ፡፡ እውነቴን ነው ዝም አትበይው፡፡ ጥሩ ልጅሽ አልመሰለኝም፡፡ እውነት ሀገሬ፤ ይህ ነገር ጥሩ አይደለም፡፡ ምን እንዳለ ታውቂያለሽ ኢትዮጵያዬ? አጼ ምኒልክ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ በሚል ለጨፈጨፉት ዜጎችሽ መታሰቢያነት የሚቆም ሀውልት ተገቢነቱን ሞገተ፡፡ በተለይ በአርሲ ለተከወነው የቆመውን የአኖሌን ሀውልት ጉዳይ ሲያነሳ፤ ኦሮሞዎችን በጅምላ ታሪካቸውን የማያውቁ ብሎ ተሳለቀባቸው፡፡ ምን ያለው ነው ታዲያ ይሄ ሀገሬ? ንገሪኝ ግድ የለሽም፡፡ እኔ እንደሁ ልጅሽ ነኝ፡፡ ግዴለም ንገሪኝ፡፡ ስለአንቺ አንድነት የሚዘምሩ መስለው መርዛቸውን የሚረጩብሽ በዙ እኮ፡፡ ሀገሬ ዝም አትበይ እንጂ፡፡ ምን ነክቶሻል፡፡ ግዴለም ያልለመደብሽን ዝምታ ከየት አመጣሽው? ቁጣሽ የት ሄደ እናትአለም? ሀገሬ ግድ የለሽም በርትተሽ ተቆጪ፡፡ ወኔሽን ሰለቡት እንዴ? አለን ብለው፤ መስለው አስኮረፉሽ እንዴ?

ሠዐሊው ልጅሽ ነኝ ባይ ‹‹ይታያችሁ ኢትዮጵያ አንድ እንዳትሆን ሲታገሉ ተገቢ እርምጃ የተወሰደባቸው የሀገር ጠላቶች፤ የአንድነት እንቅፋቶች ሆነው እያለ መስዋዕትንት የከፈሉ ይሉዋቸዋል›› ብሎ በግፍ የተጨፈጨፉ ዜጎችሽ ላይ ተሳለቀ፡፡ አንድነትሽ ሲናድ በወቅቱ ለመመለስ የተደረገ ነው ብሎ የሚያምነውን ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ ተገቢ ነው ይልሻል፡፡ ቤታችን፣ መኩሪያችን ብለው በእናት መስለው የሚኖሩትን ብሔር ብሔረሰቦችሽን ‹‹ጎጦች›› አላቸው፡፡ ዜጎች ዛሬ ላይ ላሉበት ነገር ዋጋ የከፈሉላቸውን ወንድም እህቶቻቸውን ለማሰብ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ፤ ብሎም የመታሰቢያ ሐውልቶችን መስራታቸውን ሁሉ ‹‹አጥፊ›› ነው ብሎ ፈረጀልሽ፡፡ የእርሱን ስድብና ፉከራ ግን ‹‹ምርቃት›› ነው ሊልሽ ይሆን? እንደሁ ጠይቂልኝ፡፡ እባክሽ ሀገሬ ግድ የለሽም ጠይቂው፡፡

ሀገሬ መቼም አንቺ እንደ ልጅሽ ነይ ባዩ ሠዐሊ ልጆችሽ ታሪካቸውን የሚስቱ/የማያውቁ አይመስልሽም አይደል? እርሱን እርግጠኛ ነኝ፡፡ እንደው ይህ ሠዐሊ ሲስልሽ ባየሁት፡፡ እውነት ግን ሠዐሊ ነው ኢትዮጵያዬ? ግዴለሽም በደንብ አጣሪ፡፡ በአንቺ የዋህነት አይሆንም፡፡ ሠውየው ሌላ አጀንዳ ያለው ይመስላል፡፡ ታሪክን የ‹‹ፈጠራ ወሬ›› ነው ብሎ ይሞግታል፡፡ ፈጠራ ማለት ምንድነው እናት አለም? ሥዕል ሊፈጠር ይችላል፡፡ ታሪክ ግን እንዴት እንዲህ ሊሆን ይችላል? ሰውየውን አስረጂልኝማ፡፡ ግዴለም ሠውየው አንዳች ነገር ሆኖ ይሆናል፡፡

ጭራሽ ብሎ ብሎ ኢትዮጵያዬ፤ ኦሮሞ ልጆችሽን ኢትዮጵያዊያን አይደላችሁ ብሎዋቸው አረፈ፡፡ እንግድነታቸውን ነገራቸው፡፡ አይገርምሽም ስላንቺ አንድነት የሚያስብ የሚመስለው ሠዐሊ አንቺን አንድ እንደሆንሽ ሲደሰኩር አርፍዶ ልጆችሽን ግን ያንቺ እንዳልሆኑ ነገራቸው፡፡ ‹‹ታዲያ ሀገራቸው የት ነው?›› ብለሽ ጠይቂው በሞቴ፡፡ እናት አለም እባክሽ ጠይቂው፡፡ በእኔ ሞት ይሁንብሽ ጠይቂው፡፡ ምን እንዳለ ልንገርሽማ ‹‹የኦሮሞ ህዝብ እነዚህን የልብ ወለድ ገጸባህሪያትንና ዓላማቸውን ምሳሌ አርአያ አንዲያደርጉ የሚወተውቱ የኦሮሞን ህዝብ ሊያሳስቱ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ያለውን አንድነትና ዝምድና ሊያራርቁ ሊሸረሽሩ፣ ሊያሻክሩ የሚችሉ መርዘኛ የፈጠራ ወሬዎች የሚሰበክበት የጥፋት ማዕከል እንደሚያደርገው በቀላሉ መገመት ይቻላል›› ይላል ስለ አኖሌ ሀውልትና ሙዚየሙ ሲያወሳ፡፡ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ያለው አንድነት ነው ልዩነት? ሀገሬ ግዴለም ጠይቂው፡፡ አትፍሪ እናት አለም ብቻ ጠይቀሽው ይውጣልሽ፡፡ ምን ይልሽ ይሆን እንስማው፡፡ ቀጠለና ምን ደግሞ አለ አትይኝም? እርሱ መች ትቶት ኢትዮጵያዬ ‹‹የኦሮሞ ሕዝብ ብዙ ባለአእምሮ ዜጎች ያሉት አስተዋይ የሕዝባችን አካል ነው›› አይል መሰለሽ? ገራሚ ነው፡፡

የኦሮሞን ህዝብ እንግድነት በግልጽ አስፍሮልሻል፡፡ ኢትዮጵያዬ መቼም እንዲህ ታሪክ አልባ የሚያረጉሽን ሠዐሊውንና መሰሎቻቸውን ምን ትያቸው ይሆን? ‹‹ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ባለው የሀገራችን ታሪክ ግን የሌሎቹ ብሔረሰቦች በሀገሪቱ መኖር በአንድም በሌላም አጋጣሚዎች ተጠቅሶ ሲገኝ የኦሮሞዎቹ ግን ጨርሶ የለም›› ይልሻል፡፡ እውነት እነርሱ ብቻ ነበር ያልነበሩት? ጨርሶ ደግሞ ሲያስረግጥልሽ ምን ቢልሽ ጥሩ ነው? ‹‹ይህም የሆነበት ምክንያት በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው በሀገሪቱ ስላልነበሩ ነው፡፡ የግራኝ ወረራ በፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ ከገቡ በ‰ላ ግን በሀገሪቱ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳይ ላይ ሚና ለመጫወት ሲበቁ እንደእንግድነታቸው አልነበረም›› ብሎሽ እርፍ፡፡ አክሎም ተሳትፎ ለማድረግ ፈጣን እንደነበሩ አትቶልሻል፡፡

ተመልሶ ደግሞ አንዳንዶች (በእርሱ አገላለጽ የጥፋት ኃይሎች) ኦሮሚያን እንገነጥላለን፤ ነጻ መንግስት እንመሰርታለን ገለመሌ ሲሉ የቅርብ ግዜ እንግዶች እንደሆኑ ማስታወስ ይኖርበት እንደሁ ይጠይቅማል፡፡ የማንን ሀገር እንደሚገነጥሉም ግራ የገባው መስሎ ይጠይቃል፡፡ ሀገር አልባ ናቸው እንዴ ልጆችሽ? እሰኪ ንገሪያቸው ባክሽ፡፡ ሀገራችሁ አይለሁም ካልሽም፤ የት እንደሁ መሆን የሚገባቸው አሳይያቸው ባክሽ፡፡ ምክንያቱም ልጅሽ ነኝ ባዩ ሠዐሊ ‹‹ኢትዮጵያዊ አይደለንም ካሉ ሀገሪቱን ለቀው ወደመጡበት የመመለስ መብታቸው የተጠበቀ ነው›› ብሎ አዋጅ ነግሮልሻል፡፡ በነገርሽ ላይ ኢትዮጵያዬ እርሱ ግን አዋጅ ነጋሪና ነጋሪት ጎሳሚ ያደረገው ማነው? ሹመት ሰጥተሽው ነው ወይስ? ግዴለም ግን ልጆችሽ ይከፉብሻል፡፡ መከፋታቸው ደግሞ ጥልቅ ይሆን ይመስለኛል፡፡ ይህንን ብሎ ያበቃ መሰለሽ? ‹‹አጼ ምኒልክ አደረጉ የተባለውን ሁሉ እውነት አድርገውት ቢሆን እን£ ልክ ነበሩ›› ብሎ እርፍ፡፡ ሀገሬ የልጆችሽ ጡት ሲቆረጥ አያምሽም እንዴ? እናት አለም ለምን ዝም ትያለሽ? ተናገሪ እንጂ እንዴት በልጆችሽ ቁስል ሲቀለድ ዝም ትያለሽ?

ሰውየው ሀሳቡ ምን እንደሁ እንጃ፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር ልጠቁምሽ እወዳለሁ፡፡ ካንቺ ባላቅ ሀገሬ፤ አንድነትሽን እየሰበኩ ልዩነትሽን የሚያሰፉ ልጆች ነን ባዮች እየበዙልሽም እየበዙብሽም ነው፡፡ አንድ ብትያቸው መልካም ይመስለኛል፡፡ ኦሮሞ ልጆችሽ ‹‹በሌለና ባልነበረ ቅዠትና የተረት ተረት ታሪክ እየፈጠሩ›› እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ግድየለም ሀገሬ ዝምታሽ እውነት ለመናገር ደስ አላለኝም፡፡

ታዲያ ሠዐሊው ሰውዬ ‹‹ከዘመን በፊት ኢትዮጵያዊ ያላቸው ሆኖ ለመገኘት ያላቸውን ቅን ፍላጎት ብናደንቅም ማንነት ባልነበረና በሌለ ታሪክ ላይ አይመሰረትምና እናዝናለን›› ብሎ አረፈው፡፡ አሁን አማረ አለ የሀገሬ ሰው፡፡ ምን ማለት ነው ታዲያ ኢትዮጵያዬ? ግዴለሽም ሠውየው ሌሎችን ይላል እንጂ እርሱ እራሱ ከእውቅ የሥነ-ልቦና ሐኪሞችሽ በአንዱ መታየት ያለበት ይመስለኛል፡፡ እኔ አልድገመው እንጂ ሰውየው ብዙ ስድብም ተሳድቦ ነበር፡፡ ለነገሩ እዛው ታይዋለሽ፡፡ ‹‹የጨለማ እድሜ ጸሐይ እስክትወጣ ድረስ ነው›› ብሎ ዛቻ ቢጤም አስፍሮዋል፡፡ ማን እንደሁ እንጃ፡፡ እንደፍቅር ሠባኪም ያደርገዋል፡፡ እንዴት ነው ግን እናት አለም በስምሽ የሚነገደው? አስበሽዋል አንድነትሽን በማሳበብ እንዴት እንደሚዘባበቱብሽ? አይተሽ ዝም አትበያቸው ባክሽ፡፡ የደም እንባ የሚያነቡ መኖራቸውንም ተናግሮዋል፡፡ ነገ የእርሱና የመሰለቹ መሆኑን ይናገራል፡፡

ሲደመድም ደግሞ መድኃኔአለም ልቡና ይስጣችሁ ብሎ ነበር፡፡ ልቡና ተሰጥቶት የጻፈ ነው የሚመስለው፡፡ ግን ይመስልሻል ሀገሬ? እውነት ልቡና ያለው ሠው እንዲህ ይጽፋል? ዘላለማዊ ክብር እንደሻማ ቀልጠው ይህቺን ሀገር (አንቺን ማለቱ እኮ ነው፡፡ ድንቄም) ከነጻነትሽ ጋር ላቆዩ ለአርበኞቹ እናት አባቶቻችን ይሁን ይላል፡፡ ይህኛው አገላለጽ ከልብ ቢሆን ደግ ሀሳብ ነበር፡፡ ነገር ግን አይመስልም፡፡ ሰውየው ምን እንደነካው እንጃ፤ ብዙ ዘላበደ፡፡

ሀገሬ ልጅሽ መሆኑን፤ ካንቺ አብራክ መውጣቱን ተጠራጠርኩ፡፡ አንድነትሽን የሚፈትነው እራሱ እያለ፤ ሌሎችን አስታኮ የልቡን ነገረሽ እኮ፡፡ እርሱ እንደሻማ ቀለጡ የሚላቸው እነማንን እንደሆነ አልነገረንም፡፡ እውነት እውነት ግን ሀገሬ፤ እኔ ደስ አላለኝም፡፡ ለምን እንደሆነ መቼም ይገባሻል፡፡ እርግጠኛ ነኝ ይህንን በማለቱ አልተደሰትሽም፡፡

እኔ የሚገርመኝ ባንቺ አንድነት ላይ የሚከራከሩት ሰዎች ሌሎችን ማሰብ አይፈልጉም፡፡ አንድነትሽን የሚመኙና የሚያስቡት እነርሱ ብቻ እንደሆኑ ያስቡና ሌላውን ከጨዋታው ውጪ ያደርጉታል፡፡ ፓርቲዎችሽም ቢሆኑ እንዲሁ ይመስሉኛል፡፡ በስመ ተቃዋሚ ከያሉበት ይጠራሩና ስለአንድነትሽ የሚዘምሩ መስለው ልዩነትሽን የሚያፈካ መነጽር ያጠልቁልናል፡፡ ለምን እንዲህ እንድናስብ እንደሚወዱ አላውቅም፡፡ ግን በቃ እንዲህ ናቸው፡፡

አሁን አሁን ደግሞ አዋቂ ነን ባዮችሽ፤ ህዝብሽን የሚከፍል፤ የሚሰነጥቅና የጎሪጥ የሚያተያይ ሀሳብ ያራምዱ ይዘዋል፡፡ እኔ ግን ዝምታሽን እሞግታለሁ፡፡ ለምን ዝም ትያቸዋለሽ? ግድየለም ንገሪያቸው ስለልጆችሽ፡፡ እንግድነት የመጣህ ነህ፤ ቤተኛው እኔ ነኝ እየተባባሉ የሚዛለቁ ይመስልሻል? ግዴለም ሀገሬ አንድ ነገር አድርጊ እንጂ? ዝምታሽን ልሞግተው እማ፡፡

ክፉሽ መቼም ቢሆን አይመረጥም፡፡ ልጆችሽም መልካም ቢሆኑልሽ እመርጣለሁ፡፡ አሁን ግን መከፋቴ ባሰ መሰለኝ፡፡ ስላንቺ ያወሩ የመሰሉኝ ሰዎች ሁሉ ያሳምሙኛል፡፡ ከ80 በላይ ብሔሮችና ብሔረሰቦች እንዳሉ ንገሪያቸውማ፡፡ እኒህ ህዝቦች ተዋልደው እየኖሩ እንደሆነ ንገሪልኝማ፡፡ አይሆንም ካሉሽ ግን ሌላ ነገር እንዳይሆንብሽ እሰጋለሁ፡፡ መከፋትሽን እገምታለሁ፡፡ ለመኖር ግን እራስን መፈለግ ግድ የሚልበት ሁኔታ እንዳለ አለማውቅ፤ ልጆችሽ በእርሱ ተጠምደው እራሳቸውን ሲፈልጉ፤ አንድነትሽን የሰበኩ እየመሰላቸው ልጆቼ ብለሽ የምትናገሪላቸውን የሚያስቀይሙብሽን አንድ ካላልሽ ራስን በመፈለግ ውስጥ አንቺን እንዳያጡሽ እፈራለሁ፡፡ ታሪክ አዋቂ ነን ተብሎ የሚደሰኮረው፤ እሳት ሆኖ እንዳይበላሽ እፈራለሁ፡፡ ግን እኔ እልሻለሁ፤ ፖለቲካዊ ምልከታው የቱንም ያህል ይሁን ስፋቱ፤ አንቺነትሽን ለጥርጥር የሚዳርጉ የበረከቱ አዋቂዎችሽ ግን ብቅ ብለዋል፡፡ ትልልቅ ተብዬዎቹም ሆኑ ትንንሾቹ አዋቂዎችሽ ልብ ያሉት ያልመሰለኝ ነገር አለ፡፡ ሀገሬ በይ እንግዲህ ዝም አትበይ….ግድ የለም ዝም አትበይ…..እንደውም በዚህ ሙቀት ውስጥ ሀገርን ፍለጋ መሄድ ምኑ ላይ ይሆን ክፋቱ? ምክንያቱም ኢትዮጵያዬ አንደኛው ገጣሚ ልጅሽ እንዳለው፤

‹‹ሀገር ረቂቅ ነው ቃሉ

ሀገር ውስብስብ ነው ውሉ››

እኔ ግን እልሻለሁ ዝምታሽ የበዛ መሠለኝ፡፡ ቸር ያቆይሽ፡፡ እኔም ቸር መሆን ምኞቴ ነው፡፡ ስለሆነም ደህና ይግጠምሽ፡፡

አብርሃም ተስፋዬ

atbrms@gmail.com

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Opinions Tagged With: Left Column

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የማርያምን ማዕረግ ዝቅ አደረገች December 12, 2025 09:27 pm
  • ኢህአፓ: ከነጭ ሽብር ወደ “አዲስ አበባ ትናገር” የጎዳና ሽብር? December 12, 2025 09:11 pm
  • EOC Bans Haile Gebrselassie Over Are­qie Comments Linked to Doping November 21, 2025 07:47 pm
  • በሥራ ማቆም አድማ ጥሪ ዘርፍ ባለሙያው ጃዋር ሌላ ጥሪ አቀረበ November 17, 2025 09:25 am
  • የ-አብሮነት ማኅበር የመረጠው ሕቡዕ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይፋ ሆነ November 5, 2025 12:06 pm
  • “የኢሳያስ አፈወርቂ ውድቀት አይቀሬ ነው … “ፅምዶ” ራዕይ ዓልባ” ነው – ሼትል ትሮንቮል October 26, 2025 10:15 pm
  • አሜሪካ ስላልተቀበለችው ነው “የሽሽግር መንግሥት” ስብሰባው በአምስተርዳም ተካሄደው October 25, 2025 11:09 pm
  • በዓባይ ግድብ ምረቃ፡ የሕዝብ ደስታ፣ የቴድሮስ ካሳሁን ዝምታ September 14, 2025 04:27 am
  • ኢትዮጵያ የውኃ ኑክሊየር ማብላያዋን ልታስመርቅ ነው  August 29, 2025 11:46 pm
  • መከላከያ በፋኖ አመራሮች ላይ እርምጃ ወሰደ፤ ዘመነ በ“አንድ ማንኪያ ቅንነት” አንድ እንሁን አለ August 23, 2025 12:35 am
  • ፋኖን በፋይናንስና በሎጂስቲክስ የሚደግፉ የጎጃም ባለሃብቶች ከስደት ሊመለሱ ነው August 14, 2025 12:42 am
  • የበቀለ ገርባ የአሜሪካ ጥገኝነት ማመልከቻ ውድቅ ተደረገ August 13, 2025 12:16 pm
  • ሞዐ ተዋሕዶ “ነጻ አውጪ ግምባር” – ሞነግ August 13, 2025 12:58 am
  • የሃይማኖትና የመንግሥት ጥምረት በረከት ወይስ መርገም?  August 5, 2025 09:18 pm
  • የባከነ የስደት ሕይወት ከደባርቅ እስከ ኖርዌይ July 29, 2025 05:44 pm
  • “በዚህ ዓመት መጨረሻ ትግራይን እንቆጣጠራለን”፤ ቲፒኤፍ July 22, 2025 01:28 am
  • Rusted screws, metal spikes and plastic rubbish: the horrific sexual violence used against Tigray’s women July 4, 2025 01:48 am
  • በሞርሞን ቤ/ክ ዕርዳታ የኪዳነምህረት ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ማምለኪያ ሥፍራ አገኘች July 2, 2025 01:28 pm
  • የበረከት ስምዖን “አየር ላይ ትዕይንት” አየር ላይ ተበተነ July 2, 2025 01:24 am
  • “ዐቢይ ይውረድ፣ እኛ እንውጣ፣ በተራችን እንግዛ” ስልቴዎች (ስብሃት፣ ልደቱ፤ ቴዎድሮስ) June 11, 2025 01:56 am
  • ኤሊያስ መሠረት የሚሠራው ለማነው? ለብጽልግና? ወይስ …? June 3, 2025 01:27 am
  • በግንቦት 20 – የሁለት መሪዎች ወግ May 28, 2025 02:01 am
  • በፈቃዳቸው የተመለመሉ ወጣቶች ሁርሶ ሥልጠና ጀመሩ May 22, 2025 09:11 am
  • ድብቁ ሤራ ሲጋለጥ – “ሦስትን ወደ አራት” May 21, 2025 01:01 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2026 · Goolgule