
ያለሁት ካናዳ፤ ቶሮንቶ ነው፡፡ ከጥቂት ሳምንታት ቆይታ በኋላ ትላንት ማታ አንዱ የኢትዮጵያ ምግብና ዳንኪራ ቤት ለማምሸት ከዘመድ እና ሰሞኑን ከተዋውቅኳቸው ጥቂት ሰዎች ጋር ሄድኩ፡፡
ቤቱ በአንድ ሰሞን በአንድ ዜማ እጅግ ታዋቂ ሆኖ በነበረ ወጣት ድምፃዊ የሚተዳደር ነው፡፡ ስገባ ወጣቱን ድምፃዊ አየሁት፡፡ እንግዶቹን ዞር ዞር እያለ ሰላም ይላል፡፡ ከማውቀው ወፍሯል፡፡
ዘመናዊም ባህላዊም ዘፈን በዲጄ ሲለቀቀቅ ጠባቧ ቤት ንዝረቷ ይጨምራል፡፡
ከምሽቱ አምስት ሰአት ገደማ ቤቷ ሞላች፡፡ ከሀበሻ ውጪ ሌላ ዘር ያለው ሰው ግን አላየሁም፡፡
ስድስት ሆነን ከተቀመጥንበት ጠረጴዛ ጀርባ ባለጌ ወንበርና ጠረጴዛ ላይ አንዲት በህንድ ዘዬ የተሰራ “እዩኝ እዩኝ” ሆደ- ግልብ ብልጭልጭ ልብስ የለበሰች ረጅምና ቀጭን፣ ቆንጅዬ ልጅ ተቀምጣ ቢራ ትጠጣለች፡፡ አላግባብ ተከምሮ ሳር ከጫነ መኪና ካመሳሰላት ፀጉሯ ውጪ ልቅም ያለች ቆንጆ ናት፡፡
ቆየት ብዬ ዞር እያልኩ አተኩሬ ሳያት እንደማውቃት ገባኝ፡፡ እሷም ወጣትና ታዋቂ ዘፋኝ ናት፡፡
“እዩ….ሕይወት፤ ስደትና የጠጅ ቤት አግዳሚ ሰውን እኩል ያደርጋል!” አለኝ ሰሞኑን ከተዋወቅኳቸው ኢትዮጵያዊያን አንዱ፡፡ ሰላሳ ሊሞላው ትንሽ ለቀረው አመት እዚህ ሀገር ኖሯል፡፡
“እንዴት ማለት?” ሙዚቃውን ለማሸነፍ እንጥሌ እስኪርገበገብ መጮህ አለብኝና ጮክ ብዬ ጠየኩት፡፡
“እዚህ ምታይው ሰው እኩል አይደለም፡፡ ግማሹ በሱዳን የወገኑ ሬሳ ላይ እየተረማመደ የገባ ነው፡፡ ግማሹ ደግሞ በወግ በቦሌ በአውሮፕላን የመጣ ነው፡፡ አንዳንድ ሰው የገደለም አይጠፋም…እዚህ ከገባ በኋላ ግን ሁሉም እኩል ነው….ገባሽ?”
“ገባኝ…” አልኩና እሱን ለመስማት ቀና ካልኩበት ወደ ወንበሬ ተመለስኩ፡፡
ዲጄው የትግርኛ ዘፈን ከፈተ፡፡
“ኤ….ጭ!” አለ ሌላኛው፡፡ ነገሩ ቢገባኝም “ምነው… ምን ሆንክ?” አልኩት፡፡
“እዚህም አዲሳባም ትግርኛ ብቻ!…በዛ !አሁንስ በዛ…!” ብሎ ጠረጴዛውን ትቶ ወደ አላወቅኩት ቦታ ሄደ፡፡
እሱ በሄደበት አቅጣጫ የቆመ ሌላ ሰው ሙዚቃው መከፈቱን ተከትሎ የሁለቱንም እጆቹን ባለጌ ጣቶች ሲቀስር አየሁ፡፡
ዲጄው ሰምቶና አይቷቸው “ይለይላችሁ” ብሎ ነው መሰለኝ በመሃል ሌላ ዘፈን ተጫውቶ እንዳለቀ ሌላ ትግርኛ ዘፈን ሲለቅ ቅድም የተበሳጨው ልጅ ሳቅ አለና፤ “ይሄውልሽ ሕይወት…!ላለው ይጨመርለታል ማለት ይሄ ነው!” አለና ጮህ ብሎ ሳቀ፡፡
ከግማሽ ሰአት ቆይታ በኋላ የሁሉንም ብሄር ዘፈን ስሰማ የአንዱ መረሳቱ ስለከነከነኝ፤ “ የእንትን ዘፈን ለምን አይጫወትም?” ብዬ ቅድም በትግርኛ ዘፈን መደራረብ ሲበሳጭ የነበረውን ልጅ ጠየቅኩት፡፡
“አንቺ ደግሞ እንኳን አዘፍነናቸው ጩኸታቸውን እንዲሁም አልቻልነውም!” ብሎ መለሰለኝ፡፡
ትንሽ ቆይቶ ፤ የዲጄ ሰአት አበቃና ኋላችን ተቀምጣ የነበረቸው ዘፋኝ መድረክ ወጣች፡፡
እኛን እያስገሳች “አንበሳው አገሳ”ን ስትዘፍን ቤቱ በአንድ እግሩ ቆመ፡፡
“አድማስም ማዶ እዚህም ያለን
እንደትላንቱ ዛሬም አንድ ነን… !”
ሲባል ጩኸት በረከተ፡፡
ድምፅዋ የሚያምረው ዘፋኝ፤
“ይሄም ከኦሮሞ ይሄም ከአማራ ነው፣
ይሄም ከጉራጌ ይሄም ከትግራይ ነው፣
ይሄ ሰው ከደቡብ ይሄም ከምስራቅ ነው፣
ቢለያይም ቋንቋው ደማችን አንድ ነው፣
ቢለያይም ቋንቋው ደማችን አንድ ነው!”
ስትል፤ ቅድም በትግርኛ ዘፈን ድግግሞሽ ቆሽቱ ያረረውና የእንትን ብሄር ዘፈን ለምን አይከፈትም ስለው “አንቺ ደግሞ እነሱን እንኳን አዘፍነናቸው ጩኸታቸውን እንዲሁም አልቻልነው” ያለኝ ልጅና ደጋፊዎቹ እጃቸውን ወደ ላይ አድርገው በፍፁም “ኢትዮጵያዊ” ስሜት ዳንኪራውን ሲያስነኩት አይቼ ተቃርኖው አጅግ ከነከነኝም አሳቀኝም፡፡ ባለባለጌ ጣቱም ባለጌ ጣቶቹን ደብቆ እጁን ከፍ ከፍ እያደረገ ሲዘል ተመለከትኩት፡፡
ተምታታብኝ፡፡
በዚህ የተዘባረቀ ስሜት ውስጥ ሆኜና ተምታቶብኝ ሳለሁ የጉራጊኛ ሙዚቃ ሲከፈት ጥቂት ሰዎች ቦታውን ሰፋ ሰፋ አድርገው ጭፈራውን ያደሩት ጀመር፡፡
አንደኛው በተለይ ወደር የለውም፡፡
“አንቺ እንዴት ጎበዝ ነው?!” አልኩ ወደ እህቴ ዞሬ፡፡
“በጣም…በጣም!” አለች አሱ እሱን ማየቷን ሳታቆም፡፡
“ታውቂዋለሽ?”
“በስም…”
“ማን ይባላል?”
“ገመቹ”
“ማ?”
“ገመቹ!”
በድቅድቅ ጨለማ መሃል የብርሃን ፍንጣቂ ያየሁ መሰለኝና ፈገግ አልኩ፡፡
ፈገግ እንዳልኩ ልጅቱ ዘፈኗን ጨርሳ ወደ እኛ መጣች፡፡ በ አንበሳው አገሳ ሲጨፍሩ ላብ በላብ ከሆኑት ልጆች አንዱ ጋር ጠጋ ብላ ረጅም ቁመቷን በማጎንበስ ሰብራ ኮስተር ያለ የሚመስል ነገር ታወራዋለች፡፡
የሙዚቃው ጩኸት የሚሉትን ባያሰማኝም እሱ በእሺታ ጭንቅላቱን ላይና ታች ሲነቀንቅ ይታየኛል፡፡
ልጅቱ ስትሄድ “ሰላም ነው?” ብዬ ጠየቅኩት፡፡
“አዬ! ይቺን ምስኪን ልጅ የካናዳ መንግስት ከሀገር ሊያስወጣት ነው ባክሽ…” አለኝ፡፡
“ለምን?”
“ስድስት ወር ሞልቷታል፡፡ ማክሰኞ “ኢንተርቪው” አላት፡፡ ሊመልሷት ነው”
“ እና አንተን ለምን ፈለገችህ?”
“ፎቶግራፍ አነሳ የለም?”
“እና?”
“ከዶክተር ብርሃኑ ጋር ያነሳኋትን ፎቶ እንድሰጣት ነው ምትጠይቀኝ፡፡ እሱን ካሳየቻቸው ያለምንም ችግር እንድትቀር ይፈቅዱላታል” አለኝ፡፡
ወደ ዘፋኝቱ ዞርኩና ከደቂቃዎች በፊት መድረክ ላይ በስሜት ስታወርድ የነበረውን ግጥም አሰብኩ፡፡
“በእናቴም አንድ ነኝ ፤ በአባቴም አንድ ነኝ
ከኢትዮጵያ ሀገሬ የለም የሚለየኝ”
ከረጅሙ ምሽት ደስ ያሰኘኝን የገመቹን የጉራጊኛ ዳንኪራ ብቻ እያሰብኩ ወደ ቤታችን ሄድን፡፡
(ምንጭ: ነቆራ እና ሌሎችም ወጎች ከሕይወት እምሻው ጋር – Hiwot Emishaw፡፡ፎቶ ለማሳያነት የቀረበ)
Leave a Reply